ትንሳኤ ራድዮ እንደዘገበው በአማራ ክልል ከሚገኙ 68 ሆስፒታሎች አርባዎቹ በህክምና መሳሪያዎች አለመሟላት የተነሳ ለህሙማን ተገቢውን ህክምና ለመስጠት ፈተና እየሆነባቸው መሆኑ ተገለጸ::

የገዥው መንግስት ለምርጫ ቅስቀሳ ብቻ “ተጠናቀዋል” በሚል ያስመረቃቸው አዳዲስ ሆስፒታሎችና ነባር ሆስፒታሎች ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት መቸገራቸውን የተለያዩ የህብረተሰቡ አካላት ተናግረዋል፡፡በሰሜን ጐንደር ዞን ጣቁሳ ወረዳ የሚገኘው የደልጊ ሆስፒታል በሚሰጠው አገልግሎት ዙሪያ ሰሞኑን ከተገልጋዮች ጋር ሲወያይ ከተገልጋዮች ለተነሱት ቅሬታዎች መልስ የሰጡት የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ታደለ ሙሌ ለታካሚዎች ሆስፒታሉ የላቦራቶር፣ የራጅ፣ የላውንደሪ፣ የአልትራሳውንድ መሳሪያዎች ባለመሟላታቸው ተገቢውን አገልግሎት እየሰጡ አለመሆኑን ገልጸዋል::

ችግሩ ከአቅማቸው በላይ መሆኑን ለክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ቢያሳውቁም እስካሁን የረባ ምላሽ ማግኘት ባለመቻላቸው ሆስፒታሉ የተሟላ አገልግሎት ለመስጠትን አለመቻሉን ለተወያዮቹ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ በአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ የጤና ግብዓት አቅርቦት ዋና የሥራ ሂደት መሪ አቶ እድሜዓለም አድማሱ ለመንግሰት ብዙሃን መገናኛ ጋዜጠኞች እንደገለጹት በደልጊ ሆስፒታል የተነሳው ችግር ደልጊን ጨምሮ በክልሉ ከሚገኙ 68 ሆስፒታሎች ውስጥ አርባዎቹ ላይ ችግሩ እንዳለ ገልጸዋል::

የመርዓዊና የቡሬ ሆስፒታሎች አውቶክሌቭ፣ የመርጡለ ማርያም ሆስፒታል የአውቶክሌቭና የላውንደሪ፣ የደልጊ ሆስፒታል የኤክስራይ መሳሪያ … የሚስተዋሉ ዋና ዋና ችግሮች መሆናቸው አቶ እድሜዓለም በማሳያነት አንስተዋል:: አቶ እድሜዓለም እንደሚሉት አዉቶክሌቭ፣ የእጥበት መሳሪያ (ላውንደሪ)፣ ኤክስሬይ፣ የኬምስትሪ መሳሪያ፣ የኤክስሬይ ሞኒተር፣አንስቴዥያ (የሰመመን መስጫ)፣ አልትራሳውንድ መሳሪያዎች ከነባር ሆስፒታሎች ውጭ በአብዛኛዎቹ ሆስፒታሎች የሉም:: ይህ መሆኑ ለህሙማን ተገቢውን ህክምና ለመስጠት ፈተና እየሆነ መምጣቱንም አቶ እድሜዓለም አስረድተዋል::

የገዥው መንግስት ለምርጫ ቅስቀሳ ካስመረቃቸው ሆስፒታሎች ውስጥ የህንጻ ግንባታቸው ያልተጠናቀቁ የመኖራቸውን ያህል የአንድ ጤና ጣቢያ ያክል አገልግሎት እየሰጡ አለመሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡