የሕወሐት ዝቃጭ እና ዘረኛ ስርአት ማብቂያው ጠርዝ
=============================
በነገራችን ላይ ሕወሐት መራሹ አንባገነናዊ መንግስት አልቆለታል። ጨርሶ እንዳይወገድ የጀርባ አጥንት የሆነው በተቃዋሚነት ስም የተቀመጡ ኃይሎች መሆናቸው የምናዝንበት ሀቅ ነው። ተቃዋሚ ስንል በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ በህገወጥነት በወያኔ ተፈርዶባቸው የተደራጁ ሀይሎች ሲሆኑ ችግራችን ቀጣይ እንዲሆን ከፍተኛውን አስተዋጽኦ አበርካች ሆነዋል። መቸም ትልቅ ድፍረት እንደሚሆን ይሰማኛል። ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ በመላ ከአጥናፍ አጥናፍ ተንቀሳቅሶ ይህ ስርአት ይወገድ ሲል የተደራጁት ሀይሎች የት ገቡ በሚያሰኝ መንፈስ ከሕዝብ ጎን ቆመው ብቁ አመራር መስጠት ቀርቶ የትነታቸው የጠፋበት ሁኔታ ነበር የተገነዘብነው።
 የአገር ውስጥ ሰላማዊ ታጋይ ነን ብለው የተደራጁ ያውም እኛ ትልቅ ነን የሚሉት እንደመድረክ አይነቶች የጋለ ሕዝባዊ ንቅናቄ ሲነሳ ተቃዋሚ ከመሆን ወደ ተረብ እና እንካስለካንትያ የገቡ መሪወችንም ታዝበናል። የወልቃይት፣ የጸገዴ፣ የአርማጭሆ፣ የጸለምት፣ የማህል ጎንደር፣ የባህርዳር፣ የዳንግላ፣ የደብረማርቆስ፣ የቆላደጋዳሞት ሕዝብ ተነስቶ የደም ዋጋ ሲከፍል የሕዝብ ትግልን ወደፖለቲካ ክርክር ለመለወጥ የሞከሩት እና ከሕወሐት ያልተለየ የፖለቲካ ቀመር ያንጸባረቁት የአረና ወይንም የመድረክ ሰወች እና መሪወች ቁልፍ የሆነውን ሕዝባዊ ተጋድሎ መንፈስ እና አላማ ሳይረዱ ትግሉን ከማገዝ የሕዝብ ትግልን ማደናቀፍ እንዳሳዩ ብንተች ተገቢም አስፈላጊም ነው። ትግል እና ይሉንታ። ትግል እና ተክለሰውነት። ትግል እና የእኔነት ፋዳቢስ ውዳሴን ካልታገልን ከአንባ ገነኗ ሕወሐት እና ሕወሐት መራሽ ከሆነው ስርአት የተለየን ልንሆን አንችልም።
ኢትዮጵያ ውስጥ የመሪነት ክፍት ቦታን በገሀድ የታዘብነው በዚህ የሞት የሽረት ትግሉ መሆኑን ማንም የሚገነዘበው ነው። እንዲህ ያሉ ትችቶች መመዝገብ ይገባቸዋል።
 የስርአት ለውጥ አመጣለሁ ብሎ የተደራጀ ኃይል ትግሉ ፍሞ እና ግሎ፣ ታጋይ ዜጎች ያለአመራር በየቀየው ሲወድቁ የትነበራችሁ? ምን ተፈጠረ? የጎደለው ምን ነበር? ብለን ብንጠይቅ ተገቢ ነው። መልስም ያስፈልጋል። በባሕርዳር እና የጎንደር ከተሞች ሕዝብ በመስከረም እና የጥቅምት ወራት ተከታታይ የስራ ማቆም አድማ አድርጓል። ሰላማዊ የሆነ ሕዝባዊ እንቢተኝነት አሳይቶ ሞቷል። ወጣት ልጆች በትግሉ ወድቀዋል። ይህ ለተደራጀው ክፍል እና በተቃዋሚነት ለተሰለፈው ትልቅ ግብአት ነበር። መስዋ’እት መሆን ለነጻነት ተገቢም አስፈላጊም ነው። በይበልጥም እንደ ሕወሀት አይነት ካንሰር ከአለበት ሊነቀል እና ሕዝብ አገር እና ሕዝብ ፈውስ ሊያገኝ የሚችለው በተቃራኒ በቆሙ የህዝብ አጋሮች ትግል እና የመሪነት ብቃት ነው። ይህን በአለፈው አላየንም። ትግሉ አሁንም እንደቀጠለ ነው። መስዋእትነቱም እንዲሁ።
ሕወሐት አሁንም በሕዝባዊው ትግል አጣብቂኝ ውስጥ እንዳለች ከአገር የሚወጡ፣ እና በድብቅ ስብሰባወች የሚንጸባረቁት ሀሳቦች አመላካች ናቸው። ሕወሐት መግዛት ተስኗታል። ለመግዛት አቅምም ሆነ ጉልበት አልባ ናት። ይህ ማለት ጠበንጃ አልቆባታል ሳይሆን። እንዳለፉት 26 አመታት ሕዝብ ለጥ እና ሰጥ ብሎ የሚገዛ አለመሆኑን በደሙ ፍሳሽ፣ በአጥንቱ ክስካሽ አሳይቷል። ሕወሐት ከፖለቲካው ተወርውራለች። ገና ከጥንት ጠዋቱ ስትነሳ እና የአረብ ፔትሮ ዶላር ስትሰበስብ« የኢትዮጵያን ደመኛ ጠላቶች ከጎን ስታሰልፍ። የሲያድባሬን መንግስት አማራን ላጠፋ ተነስቻለሁ ተደራጅቻለሁ ብላ መሳሪያና ማንኛውንም የዲፕሎማሲ ድጋፍ ስትለገስ የነበራትን ሁሉ ድጋፍም ሆነ ፖለቲካው ስውር ጎዳና በአደባባይ ተሰጥቶላት ዋና ጠላቴ ብላ የተሰለፈችበት ሕዝብ ስደት፣ እንግልት፣ ሞት፣ እስራት፣ መገፋት በቃ ብሎ ተነስቶ የቁም ስቅሏን አሳይቷታል። ጠላቴም ነሽ በቃኝ ብሎ አንገሽግሾት ጭቆናን፣ ሞትን፣ ስደትን በቃን ብሎ ከተነሳ ወራትን አስቆጥሯል። ትግሉ Oneway road ሆኗል። ሕወሐትን እና ሕወሐት መራሹን ስርአት ሳያስወግድ አይመለስም።
26 አመታት የተጠቀመችበት ዘርን ከዘር የማጋጨቱ እና ገላጋይ እና ህግ አስከባሪ ሆኖ የመቅረቡ ዘረኛ ዘዴዋም በጎንደር ወጣቶች ተሰብሯል። “የኦሮሞ ደም ደሜ ነው። በቀለ ገርባም ይፈታ” የሚለውን ማስታወስ ይገባል። ያነን መልሶ ለማምጣት እና ሁለቱን ዘሮች እያጋጩ መቀጠሉ ከመከነ ወዲህ ሕወሐት ባዶነቷን ብሎም ሚጢጢነቷን ብትረዳም ሕዝብን እናታግላለን ብለው የተደራጁ ከገቡበት ድብርት አልተላቀቁም። እንደ በላይ ዘለቀ፣ እንደአሞራው ውብነህ። እንደ ጸጋየ ደብተራው ወይንም የስልሳወቹ ታጋይ ሞት አይፈሬወች የግንባር ቀደምነት ሚናቸውን እየተወጡ አይደለም። እንዴውም በሌሉበት የትግል አውድማ ሲወዳደሩ ማየት ምን ያህል ያሳዝናል። መሪ እንደጧፍ በርቶ ሕዝብ ካላስከተለ ምኑን መሪ ሊሆን ይችላል? መሪ ትግሉ ሲጎመራ እንደግስላ ተነስቶ ሞትን ሞቶ ካላሳየ ምኑን መሪ ሆነው? ድርጅትስ ከህዝብ በፊት መስዋ’እትነት ካላሳየ ምኑን ተደራጀው።
 ሕወሐት መራሹ ስርአት አልቆለታል። ሕወሐት እንደድርጅት የነቀዘች እና የበሰበሰች ጸረሕዝብ መሆኗ ታውቆ በየአደባባዩ የሚነገር ታሪኳ ሆኗል። ለመኖር እና ይህን ዝቃጭ፣ ዘረኛ ስርአት ለማስቀጠል እነ አባይ ፀሐየም እንዳልቻሉ በድብቅ የወጣው ቃላቸው መስካሪ ነው። የባህርዳሩ የባንዶች ስብሰባም በጀግና ልጆች አፈር ከድሜ ግጦ እርቃኑን የቀረ ሆኗል። የኦሕዴዱ ጉደኛ የባንዳ ቡድንም እንዲሁ ቀፎው እንጅ ስብእና ያለው ኃይ አለመሆኑን በኦሮሚያ ወጣቶች እልህ አስጨራሽ ትግል ተጋልጧል። እናም ይህን ዝቃጭ ዘረኛ ስርአት እና መንግስት ለማስቀጠል ያልቻለችው ሕወሐት እና ተቀጣሪ ሚኒስቴሯ በሕዝብ ጥያቄ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን አራዝመናል ብሎ አቧልቶብናል። በቃ የሕወሐት እድሜ።
የዚህ ዝቃጭ ስርአት ማብቃቱን ብዙ ማመሳከር ሳይፈልግ የአባይ ፀሀየውን ኑዛዜ ማዳመጥ በቂ ነው። ግን ግን ታጋይ አታጋይ ድርጅቶች ከገቡበት ሰመመን ወጥተው ትግሉን መመራት፣ መቀላቀል ይገባቸዋል። መተባበር በእራሳቸው ውስጥ እርቅን እና አንድነትን መፍጠር ይኖርባቸዋል። ለመሆኑ ሌጋሲየ ይህ ነው ብለው ቢያልፉም በዚህች ባለቀች ሰአት እስኪ ክንዳቸውን ልምዳቸውን ያሳዩ። ተቃዋሚ መተባበር እና ይህን ትግል ዳር ማድረስ ይገባል። ስርአቱ አልቆልኛል ብሎ በሚያጣጥርበት በዚህ ሰአት ሀይልን አስተባብሮ የሕዝብን መስዋእትነት ዳር ያላደረሰ የተቃዋሚ ጎራ “ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ” እንዲሉ ነው።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
ኢትዮጵያ ለዘለአለም ትኑር!!!
ትግሉ እስከ ድል ይቀጥላል!!!