Wednesday, 12 April 2017 12:14

በይርጋ አበበ

ውዝግብና መወነጃጀል፤ አለፍ ሲልም መወቃቀስና መጠላለፍ “መለያው” የሆነው ያለፉት 26 ዓመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ በተለይ ካለፉት 12 ዓመታት ወዲህ ተዳክሞ ታይቷል። በተቃዋሚ ፓርቲዎችና በገዥው ፓርቲ መካከል ከሚፈጠረው አለመግባባትና አተካሮ በዘለለ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በመካከላቸው ባለባቸው የመጠላላትና ያለመተማመን ችግር የተነሳ አንዱ ሌላውን ሲወነጅለው አንደኛው ሌላኛውን “ተለጣፊና የጥቅም ተካፋይ” እያለ በአደባባይ ሲዘልፈው መስማት የተለመደ ሆኗል።
ከዚህም ባለፈ አንድ ፓርቲ በውስጠ ዴሞክራሲ እጦት ሲታመስና ህልውናውን እስከማጣት ድረስ አደጋ ላይ ወድቆ ማየትም አዲስ አይደለም። በተለይ ከኃላፊነቱ የተነሳው አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ በተተኪው ላይ አሉታዊና አፍራሽ ወሬዎችን ከመንዛት ጀምሮ ለድብድበ እስከመገባበዝ ሲደርስም ተመልክተናል። ለአብነትም በቅርቡ ከፓርቲ ኃላፊነቱ የተነሳው በአቶ ይልቃል ጌትነት የሚመራው የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ቡድን እና በአቶ የሽዋስ አሰፋ የሚመራው አዲሱ ስራ አሰፈጻሚ ላይ እርስበርስ የሚያደርጉት ሹኩቻ ማንሳት በቂ ነው።
ይህን ሁሉ ውስብስብ ፈተና የተጋፈጠው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሰሞኑን አንድ ክስተት አስተናግዷል። ከተመሰረተ ወደ 25 ዓመታትን ያስቆጠረው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና አምስት ዓመታትን እንኳን ያላስቆጠረው ሰማያዊ ፓርቲ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል። እነዚህ ሁለት የዕድሜ ልዩነት ያላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጋራ ለመስራት ከመስማማታቸውም በዘለለ ተዋህደው ለመቀጠል ስለሚችሉበት ሂደት እየተዘጋጁ መሆናቸውን 68 ገጽ ባለው የጋራ ስምምነት ሰነድ አስታውቀዋል።
ይህ የሁለቱ ፓርቲዎች ስምምነት ካለፉት ጊዜያት ተመሳሳይ ክስተቶች በምን ይለያል? የፓርቲዎቹ ቅድመ ድርድር ሂደት ምን ይመስላል? በሁለቱ ፓርቲዎች መከካከል ያለው ተፈጥሯዊ ልዩነት በምን አይነት ሰው ሰራሽ መፍትሔ ሊጠብ ይችላል? የሚሉትንና ተያያዥ ነጥቦችን ከዚሀ በታች አቅርበነዋል።
                                                                                                    የአበራሽን ጠባሳ ያዬ በእሳት አይጫወትም
በኢህአዴግ የስልጣን ዘመን በተቃውሞ ጎራ ህጋዊ ፈቃድ አግኝቶ በመንቀሳቀስ የመጀመሪያው ፓርቲ የቀድሞው “የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት (መአህድ) ወይም የአሁኑ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)” ነው። የቀድሞው የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የቀዶ ጥገና ህክምና ስፔሻሊስትና በተለይም በደርግ የስልጣን ዘመን የመጀመሪያዎቹ ወራት የቀዳማዊ ኃይለስላሴ የግል ሃኪም የነበሩት ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ አማካኝነት የተቋቋመው መአህድ አንጋፋና በኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ ትግል እንቅስቃሴ ውስጥ ያለው ሚና ቀላል አይደለም። በመኢአድ እና ሰማያዊ የስምምነት ፊርማ ስነስርዓት ላይ ስለ መኢአድ የፖለቲካ ትግል ታሪክ የተናገሩት የመኢአዱ ሊቀመንበር ዶክተር በዛብህ ደምሴ “በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የመኢአድን በር ሳይረግጥ ያለፈ ፖለቲከኛ እና የፖለቲካ ፓርቲ የለም” ሲሉ ተደምጠዋል። የሰማያዊ ፓርቲ አቻቸው አቶ የሽዋስ አሰፋ በበኩላቸው ከዶክተር በዛብሀ ጋር የሚስማማ አስተያየት ሰጥተዋል።
እንደ ሁለቱ ፓርቲዎች ጎምቱ ሰዎች አሰተያየት “መኢአድ” በአገሪቱ ውስጥ ለሚንቀሳቀሱ የተቃዋሚ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች መፈጠር ምክንያት ቢሆንም ከአቻ ፓርቲዎች ጋር በጣምራነት ለመስራት ያደረገው ጥረት ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱን ዶክተር በዛብህ ደምሴ ሲናገሩ “በ1997 ዓም ኢህአዴግን መገዳደር የቻለውን ቅንጅትን መፍጠር የቻለው መኢአድ ቢሆንም በቅንጅት አባል ፓርቲዎች አመራሮች መካከል በተነሳ ያልተገባ ውዝግብ ፓርቲው የታሰበውን ያህል ሊንቀሳቀስ አልቻለም” ሲሉ ተናግረዋል። ከቅንጅት መፍረስ በኋላም መኢአድ ከቀድሞው አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት) ጋር ለመቀናጀት ወይም ለመዋሃድ ጥረት ቢያደርግም በውጫዊና ውስጣዊ ችግሮች የፓርቲዎቹ አብሮ የመስራት ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል። ከ1997 ዓም በፊትም ቢሆን መኢአድ ከጉያው ከበቀለው ኢዴፓ ጋር በጋራ ለመስራት ጥረት አድርጎ የነበረ ቢሆንም ሳይሳካ መቅረቱ የቅርብ ሩቅ ታሪክ ሰነድ ነው።     
ከላይ የተጠቀሱት ክስተቶች በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል አለመተማመንን ፈጥረዋል። በዚህም ምክንያት ተነጋግሮና ተግባብቶ በጋራ ከመስራት ይልቅ ተሳሳይ ዓላማ፣ ርዕዮተ ዓለም፣ የትግል ስልት እና ፖሊሲ ያላቸው ፓርቲዎችም ቢሆኑ በራሳቸው መንገድ መሄድን መርጠው በተናጠል ሲንቀሳቀሱ ይታያሉ። ፓርቲዎችን ከሚደግፈው ህዝብም “ወይ ተባበሩ ወይ ተሰባበሩ” የሚል ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲቀርብ ከፓርቲዎቹ የሚሰጠው ምላሽ “ከማን ጋር ልተባበር ማንን ልመን?” አይነት መልስ ነው። ይህም አገሬው “እባብ ያየ በልጥ በረየ ወይም የአበራሽን ጠባሳ ያዬ በእሳት አይጫወትም” እንደሚለው ለቀጣይ ድል ከመንቀሳቀስ ይልቅ ሁልጊዜ ያለፈውን ውድቀት ብቻ እያነሱ በራሳቸው ትራክ ይሄዳሉ። የሮጡ እየመሰላቸውም በቆሙበት ይረግጣሉ ወይም በወታደራዊ ቋንቋ “ባለህበት ሂድ” እንዲሉ የቆሙበትን መሬት ደጋግመው ይረግጣሉ።
የቅንጅት ተሞክሮ ለመኢአድ ሰማያዊ አብሮ የመስራት ስምምነት
1997 ዓም በተካሄደው ምርጫ “ክስተት” የነበረው ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ አንደኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በቅጡ ሳያከብር መሪዎቹ ወደ ቃሊቲ የወረዱ ሲሆን የቅንጅቱ አባል ፓርቲዎችም ወደየጎሬያቸው ሲገቡ ጊዜ አልፈጀባቸውም ነበር። ወይም በአጭር ቋንቋ ቅንጅት ፈረሰ። የመኢአዱ ሊቀመንበር ዶክተር በዛብህ ደምሴ ለቅንጅት መፍረስ ምክንያቱ የእነ ቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ መሆኑ እንደሆነ ገልጸዋል። ዶክተር በዛብህ ሀሳባቸውን ሲያጠናክሩም የቅንጅት አባል ፓርቲዎች ጥልቀት ያለው ውይይት አለማድረጋቸውን ተናግረዋል። ውይይታቸው ሾላ በድፍኑ መሆኑ ደግሞ በአመራሮቹ መካከል አለመግባባትን ከመፍጠሩም በላይ “እኔ ያልኩት ካልሆነ” አይነት “ፊውዳላዊ” አካሄድ ለቅንጅት ውድቀት አንዱ እና ዋናው ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል።
መኢአድና ሰማያዊስ እስከ ውህደት የሚዘልቅ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ሲፈራረሙ ከቅንጅት ውድቀት ምን ትምህርት ወስዳችኋል? ተብለው ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ተጠይቀው ነበር። አመራሮቹ መልሰ ሲሰጡም “ላለፉት አራት ወራት ከሁለቱም ፓርቲዎች የተውጣጣ ስድስት አባላት ያሉት ኮሚቴ ተዋቅሮ ስራውን ሲያከናውን ቆይቷል። ከግል ጥቅምና ዝና ይልቅ ለህዝብና ለአገር ጥያቄ ቅድሚያ መስጠት ስለሚቻልበት ጉዳይ ሰፊ ጥናት ተደርጓል። ሁለቱ ፓርቲዎች በመመሪያቸው፣ በደንቦቻቸው እና በፕሮግራሞቻቸው ተመሳሳይ ናቸው። በመሆኑም የሁለቱ ፓርቲዎች ውህደት የሚደረገው በአካላዊ ሳይሆን የአእምሯዊ ውህደት በመሆኑ በቀላሉ የሚፈርስ አይሆንም” በማለት እዚህ ወሳኔ ላይ ከመድረሳቸው በፊት ሰፊ የጥሞና ጊዜ መውሰዳቸውን አስታውቀዋል። በዚህም መሰረት መኢአድና ሰማያዊ በጋራ ከመስራት ጀምሮ እስከ ውህደት የሚያደርሰው ግንኙነት “የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ” ብሎ በቀላሉ ተወለካክፎ እንደማይወድቅ ነው የገለጹት። 
የእድሜ ልዩነት የሚፈጥረው የአስተሳሰብ ክፍተት
መኢአድ እንደ ፓርቲም ሆነ የፓርቲው አመራሮች እንደ ግለሰብ እና ሰማያዊም ሆነ የፓርቲው አመራሮች እድሜ ልዩነት መኖሩ ግልጽ ነው። ከመኢአድ አመራሮች መካከል አብዛኞቹ ከ50ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ እስከ 70ዎቹ መገባደጃ ላይ የሚገኙ በእድሜ የገፉ ሲሆን የሰማያዊ አቻዎቻቸው ደግሞ ከ40ዎቹ መጀመሪያ ቢበዛ አጋማሽ የሚያልፍ አይደለም። እንዲያውም አንዳንዶቹ የ40ኛ ዓመት ልደታቸውን ያላከበሩም አሉበት።
25 ዓመት የትግል ዘመን ያስቆጠረውን መኢአድን የሚመሩት አንጋፋዎቹ የፓርቲው መሪዎች አምስት ዓመታትን እንኳን ያልደፈነውን ሰማያዊ ፓርቲን ከሚመሩት ወጣቶች ጋር ትልቅ የሚባል የእድሜ ልዩነት ስላለ የአስተሳሰብና የውሳኔ ሰጭነት ክፈተት አይፈጠርም ወይ? ተብለው ተጠይቀው ነበር። የሁለቱ ፓርቲዎች አመራሮች ግን ይህ የእድሜ ልዩነት የሃሳብ ልዩነትን አቻችሎ ለመሄድ እንቅፋት እንደማይሆን ገልጸው “ልጅ ከአባቱ እየተማረ አባቱን እንደሚተካ ሁሉ ሰማያዊ ፓርቲም ከአያቱ እየተማረ አያቱን (መኢአድን) ይተካል” ሲሉ መልስ ሰጥተዋል። 
ፓርቲዎች ባለፉት ጊዜያት አብሮ ለመስራት (ለውህደት፣ ለቅንጅት እና ለግንባር) ያደረጓቸው ጥረቶች ያልተሳኩት በእድሜ ልዩነት ሳይሆን በሌሎች ችግሮች መሆኑን የመኢአዱ ሊቀመንበር ዶክተር በዛብህ ደምሴ ገልጸዋል። ዶክተር በዛብህ በመግለጫቸው “ጥልቅና ዝርዝር በሆነ መልክ ባለመጠናት ወደ ወህደት መሄድ፣ የሃሳብ ልዩነት ሲያጋጥም በመቻቻል ፖለቲካዊ መፍትሔ ከማስቀመጥ ይልቅ ወደ መጠላለፍ መግባት፣ እኔ ያልኩት ይሁን የሚል መንፈስ ማሳደር እና ከህዝብ አጀንዳ ይልቅ ለግል ስብዕና መጨነቅ” ለፓርቲዎቹ አብሮ የመስራት ጥረት መኮላሸት ዋና ዋና ምክንያት መሆናቸውን ገልጸዋል።
ቀደም ባሉት ጊዜያት የተለያዩ ፓርቲዎች አብሮ ለመስራት ያደረጓቸውን ጥረቶች አለመሳካት ምክንያቶች በደንብ ለይተን አውቀናቸዋል ካላችሁ እናንተስ በዚህ አዙሪት ችግር ውስጥ ላለመግባታችሁ የምትሰጡት ዋሰትና ምንድን ነው? የሚል ጥያቄ ለሁለቱ ፓርቲ አመራሮቸ ቀርቦላቸው ነበር።  
የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሽዋስ አሰፋ እስካሁን የተደረጉ የውህደትም ሆነ የቅንጅትና የግንባር ሂደቶች የታሰበውን ያህል ውጤት ማምጣት ባይችሉም ሙከራዎቹን በዜሮ ማባዛት እንደማይገባ ተናግረዋል። ሆኖም የአሁኑ የሁለቱ ፓርቲዎች ጥረት እስከቀራኒዮ የሚጓዝ እንደሆነ እምነታቸውን ገልጸው ለዚህም እሳቸውም ሆኑ ፓርቲያቸው እንዲሁም የመኢአድ አመራሮችና አባላት ከፍተኛ መስዋእትነት እንደሚከፍሉ ተናግረዋል። “እስካሁን የተካሄዱ ደርድሮች ሁሉ የስርዓት ለውጥ አምጥተዋል ባይባልም ለሰላማዊ ትግል መጎልበት ያደረጉት አስተዋጽኦ ግን አሊ የማይባል ነው” ያሉት አቶ የሽዋስ “ገዥው ፓርቲ እየኖረ ያለው በራሱ ጥንካሬ ሳይሆን በተፎካካሪዎች ድክመት ነው። ይህ ድክመትም ትብብሮችን አድርጎ እስከመጨረሻው የማስቀጠል ቁርጠኝነት የማይታይባቸው መሆኑ ነው” በማለት ተናግረዋል። የመኢአድና የሰማያዊ ወደ ውህደት የሚያመራ አብሮ የመስራት ስምምነት ግን በቀያፋ ግቢ የሚገታ ሳይሆን እስከ ቀራኒዮ የሚጓዝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።  
የመኢአዱ ሊቀመንበር ዶክተር በዛብሀ በበኩላቸው “ሁለቱ ፓርቲዎች (መኢአድና ሰማያዊ) በረጋ ጥናት ላይ ተመርኩዘው ወደፊት ለሚያደረጉት ውህደት በር ከፋች መሆኑን ላረጋግጥ እወዳለሁ” ሲሉ የስምምነቱን ደረጃ ገልጸዋል። ይህ ስምምነትም በሁኔታዎች የሚለዋወጥ ሳይሆን ለዓላማው የታመነ መሆኑን ገልጸዋል። ዓላማውን ሲያስቀምጡም “ኢህአዴግን መገዳደር የሚችልና በምርጫ ኢህአዴግን አስወግዶ ሊተካ የሚችል ግዙፍ የፖለቲካ ፓርቲ መመስረት” እንደሆነ ተናግረዋል።
መደምደሚያ
የመኢአድ እና ሰማያዊ ፓርቲዎች በጋራ የመስራት ስምምነት በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የህግ ድጋፍ ሳያስፈልገው መካሄድ እንደሚችል የተገለጸ ሲሆን የፓርቲዎቹን ተደራሽነትና አደረጃጀት ይዘትም አቶ አዳነ ጥላሁን ገልፀዋል። በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል በሚያስብል መልኩ ሁለቱ ፓርቲዎች አባላትና ጽ/ቤት እንዳላቸው የገለጹት የመኢአዱ ዋና ጸሀፊ አቶ አዳነ ጥላሁን ሁለቱ ፓርቲዎች ለምን በጋራ መስራት እንደሚገባቸው የኮሚቴውን ሪፖርትም አቅርበዋል። በተናጠል የሚወጣውን የሁለቱን ፓርቲዎች ገንዘብና ጊዜ ከመቆጠብም በላይ በአባላት መካከል መግባባትን የሚፈጥር መሆኑንም ገልጸዋል።
ሁለቱ ፓርቲዎች በደረሱበት ስምምነት ዙሪያ አስያየታቸውን ለሰንደቅ ጋዜጣ የሰጡ ግለሰቦች እንደገለጹትም “ልዩነትን በመቻቻል መፍታት የሚችል የሰለጠነ ፖለቲካ በአገራችን አለመዳበሩ የታሪካችን አንዱ አሳዛኝ ክፍል ነው።  እነዚህ ፓርቲዎች እስከ ውህደት የሚዘልቁ ከሆነ በዋናነት የሚጠቀመው የአገሪቱ ህዝብና ስልጣን ላይ ያለው ፓርቲም ጭምር ነው። ምክንያቱም ህዝቡ የተደራጀ አማራጭ እንዲኖረው ሲያደርግ ኢህአዴግም ራሱን እንዲፈትሽ አስገዳጅ መፍትሔ ይፈጠርለታል” ሲሉ የተናገሩ ሲሆን “ሆኖም እንዳለፉት ጊዜያት ሁሉ የአሁኑ ሙከራም በአጭር እንዳይደናቀፍ በተለይ በፓርቲዎቹ አባላት ደጋፊዎችና አመራሮች መካከል ሰፊ ስራ ሊሰራ ይገባል እንጂ ሁል ጊዜ ድክመትንና ውድቀትን በገዥው ፓርቲ እያሳበቡ መሄድ ለማንም አይበጅም” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።  
ፖለቲካ ብዙ ፈተናዎች የሚያጋጥሙት ዘርፍ ሲሆን በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ዴሞክራሲ ባልሰፈነበትና ድህነት በተንሰራፋበት አገር ፈተናው ድርብ ይሆናል” ያሉት ሌላው አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው “እየሱስ ክርስቶስ በጌቴሴማኔ የአትክልት ቦታ ሆኖ ሲጸልይ ቢቻልህስ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ አለ። ሆኖም ጽዋውን መጠጣቱ እንደማይቀር ሲያውቅ እስከ ቀራኒዮ ድረስ ታምኖ ዓላማውን አሳክቷል። እነዚህ ፓርቲዎችም ሲመቻቸው ተዋህደው ሲከፋቸው የሚለያዩ ሳይሆን ውስጣቸውን እየፈተሹና ውጫዊ ፈተናዎችን ደግሞ እየተቋቋሙ እስከ መጨረሻው ሊጓዙ ይገባል እንጂ መሃል ላይ ተደናቅፈው ሊወድቁ አይገባም” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ስንደቅ