Wednesday, 12 April 2017 12:00

 የኤርትራ መንግስት በተባበሩት መንግስታት የተጣለበትን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ በመተላለፍ ከሰሜን ኮሪያ የተለያዩ የጦር መሳሪያና ወታደራዊ መገናኛ መሳሪያዎች ሲያጓጉዝ በመያዙ የአሜሪካ መንግስት በኤርትራ ባህር ኃይል ላይ አዲስ ማዕቀብ መጣሉን የቪኦኤ የእንግሊዘኛው ድረገፅ አመልክቷል።

 በዚህም መሰረት የኤርትራ ባህር ሀይል የሚፈፅማቸው ማናቸውም የጦር መሳሪያ ቁሶች እንደ ኢራን፣ሶሪያና ሰሜን ኮሪያ ሁሉ በአሜሪካ ማዕቀብ ስር እንዲወድቅ የተደረገ መሆኑን ይሄው ዘገባ ያመለክታል። ሰሜን ኮሪያ በጦር መሳሪያ ማዕቀብ ሥር ስትሆን ኤርትራ ይህንን ጥሰት የፈፀመችው በአንድ መልኩ በራሷ ላይ የተጣለውን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ በመተላለፍ ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ በሰሜን ኮሪያ ላይ የተጣለውን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ወደ ጎን በማለት ነው። እንደ ዘገባው ከሆነ ኤርትራ ከሰሜን ኮሪያ ጦር መሳሪያ ለመሸመት የተገደደችው ከተጣለባት ማዕቀብ ጋር በተያያዘ ከሌሎች ጦር መሳሪያ አቅራቢ ሀገራት ግዥ መፈፀም የማትችል በመሆኗ ነው።

የኤርትራ መንግስት በተባበሩት መንግስታት ፀጥታው ምክር ቤት የተጣለበትን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ በመተላለፍ የጦር መሳሪያና ወታደራዊ መገናኛ መሳሪያዎችን ለማስገባት ሙከራ ሲያደርግ የሰሞኑ የመጀመሪያው አይደለም። እንደ ቪኦኤ ዘገባ ከሆነ እ.ኤ.አ በ2016 ዓ.ም 45 የታሸጉ ሳጥኖችን የያዘ መርከብ ወደ ኤርትራ ሲጓጓዝ በነበረበት ወቅት በቁጥጥር ስር ውሎ ፍተሻ ሲደረግበት በርካታ ጂፒኤስ አንቴናዎች፣ ወታደራዊ ሬዲዮ መገናኛዎች፣የጦር መሳሪያ መለዋወጫዎችና መሰል ወታደራዊ ቁሳቁሶች ተገኝተውበታል።

ጉዳዩን ያጣራው የተባበሩት መንግስታት በመጨረሻ በደረሰበት ድምዳሜ ሽያጩን ያከናወነው ግሎኮም የተባለ የማሌዥያ ኩባንያ ሲሆን መሳሪያው እንዲላክ የተደረገው በሰሜን ኮሪያ በኩል ነው። ኤርትራ ከሰሜን ኮሪያ ጋር እየፈጠረችው ያለው ሚስጥራዊ ወዳጅነት አሜሪካ በኤርትራ ላይ የምትከተለውን ፖሊሲ የበለጠ እያጠበቀች እንድትሄድ ያደርጋታል የሚሉ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው።

በዚሁ ዙሪያ ለአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ የእንግሊዘኛው ድረገፅ ማብራሪያ የሰጡጥ  በስቶኮልም ኢንተርናሽናል ፒስ ሪሰርች ኢኒስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ፒተር ዊዝማን፤ ሰሜን ኮሪያ ለኤርትራና መሰል ሀገራት የምትሸጣቸው ጦር መሳሪያዎች በቀድሞዋ ሶቬት ህብረት ተፈብርከው መጠነኛ ማሻሻያ የተደረገላቸው ኋላ ቀር መሳሪያዎች ናቸው። እንደ ሚስተር ዊዝማን ገለፃ ከሰሜን ኮሪያ ጦር መሳሪያ የሚገዙ ሀገራት ኢኮኖሚያቸው የደቀቀ ሀገራት ናቸው። ኤርትራ የሰሞኑን የአሜሪካ መንግስት አዲስ ማዕቀብ በማስታወቂያ ሚኒስትሯ በኩል ያወገዘች መሆኑን ይሄው ዘገባ ጨምሮ አመልክቷል።

ስንደቅ