12 Apr, 2017

ከመድረክ በተጨማሪ ሰማያዊና መአሕድ ራሳቸውን አግልለዋል

ከጥር 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና 21 አገር አቀፍ ፓርቲዎች ስምንት ዙር ውይይት ካደረጉ በኋላ፣ ስምንተኛውን ዙር ውይይት ሚያዚያ 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ሲያካሂዱ በዝርዝር የድርድር ደንቡ ላይ ተስማሙ፡፡ በስምምነቱ መድረክ ሰማያዊና መአሕድ የሉበትም፡፡

ከሚፈለገው ጊዜ በላይ ዘግይቷል እየተባለ በሚተቸው ውይይት ፓርቲዎቹ አስቀድመው በተወሰኑ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ መስማማት ችለው ነበር፡፡ ፓርቲዎቹ ውይይቶቹና ድርድሮቹ የሚካሄዱባቸውን ዝርዝር ሥነ ሥርዓቶች ለመወሰን ባደረጉት ጥረትም በስምምነት ለመወሰን 12 ጉዳዮችን ለይተዋል፡፡ እነዚህም ጉዳዮች የድርድሩ ዓላማዎች፣ የድርድርና የክርክር ተሳታፊ ፓርቲዎች፣ የድርድርና የክርክር አባል ፓርቲዎችና የፓርቲ ተወካዮች ብዛት፣ ምልዓተ ጉባዔና ውሳኔ አሰጣጥ፣ የድርድር አጀንዳ ስለማቅረብና የማቅረቢያ ጊዜ ገደብ፣ እንዲሁም የድርድር አጀንዳ አወሳሰንና አጀማመር፣ የሚዲያ አጠቃቀም፣ የንግግርና የተናጋሪዎች አሰያየም፣ የድርድርና የክርክር አመራር፣ ታዛቢዎችና የሚኖራቸው ሚና፣ ሥነ ምግባርና ዲሲፕሊን፣ ውስጣዊ አደረጃጀት፣ አስተዳደርና የሎጂስቲክስ ድጋፍና የስብሰባ ቦታ ናቸው፡፡

ከእነዚህ ጉዳዮች መካከል በአብዛኛዎቹ ላይ ስምምነት የተደረገ ቢሆንም፣ ሁለት ጉዳዮች ግን ውይይቱን ባለበት እንዲረግጥ አድርገውት ነበር፡፡ እነዚህም በአብዛኛው በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና በመድረክ የተነሱ ነበሩ፡፡ ሁለቱ አጀንዳዎች ውይይቱ ወይም ድርድር በተናጠል ወይም በተወካይ አልያም አንድ ለአንድ ይደረግና ማን ያደራድር የሚሉ ነበሩ፡፡

ኢሕአዴግ ከ21 አገር አቀፍ ፓርቲዎች ጋር እያደረገ ባለው ውይይት ላይ በስድስት ዙሮች ከተሳተፈ በኋላ፣ በሰባተኛው ራሱን ያገለለው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) መጋቢት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ በጽሕፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጸው፣ በዋና አደራዳሪነት አልያም ለብቻው በጎንዮሽ ከኢሕአዴግ ጋር ለመደራደር ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ከውይይቱ ራሱን አግልሏል፡፡

በተመሳሳይ ነፃና ገለልተኛ አደራዳሪ አስፈላጊ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ጉዳይም ይበልጥ አጨቃጫቂ ሆኖ ቆይቷል፡፡ አደራዳሪ ማን ይሁን በሚለው ጉዳይ ላይ አንዳንድ ፓርቲዎች ነፃና ገለልተኛ አደራዳሪ ያስፈልጋል ሲሉ፣ ኢሕአዴግና ሌሎች ፓርቲዎች ግን ድርድሩን ተሳታፊ ፓርቲዎች በፈረቃ ሊያደርጉት እንደሚገባ አቋም ይዘው ነበር፡፡

ይህን ልዩነት ለማቻቻል ጥረት እየተደረገ እያለ ሰማያዊ ፓርቲና የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ) ነፃና ገለልተኛ አደራዳሪ የማይኖር ከሆነ በድርድሩ መሳተፍ እንደማይፈልጉ በመግለጽ፣ እንደ መድረክ ሁሉ ራሳቸውን አግለዋል፡፡

ነገር ግን ሚያዚያ 2 ቀን 2009 ዓ.ም. በተካሄደው ስምንተኛው ዙር ውይይት የተቀሩት ፓርቲዎች ሰፊ ጊዜ ወስደው ከመከሩ በኋላ ልዩነቶቻቸውን ለማቻቻል ሞክረዋል፡፡ በዚህም ፓርቲዎቹ ድርድሩን ያለነፃና ገለልተኛ አደራዳሪ ለማካሄድ ወስነዋል፡፡

በመርህ ደረጃ ድርድሩን ፓርቲዎቹ በፈረቃ እንዲመሩት ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ይሁንና ፓርቲዎቹ እንዴት አድርገው በፈረቃ ድርድሩን ይምሩት የሚለው ጉዳይ ተጨማሪ ውይይት ጠይቆ ነበር፡፡ በመጨረሻም ድርድሩን የሚመራ ኮሚቴ ከፓርቲዎቹ ተውጣጥቶ እንዲቋቋም ተስማምተዋል፡፡ የኮሚቴውን አባላት ቁጥር ለመወሰንና አባላቱን ለመምረጥ ለሚያዚያ 11 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ይዘዋል፡፡ በዕለቱ ፓርቲዎቹ እስካሁን ያካሄዷቸውን ውይይቶች ቃለ ጉባዔ መርምረው ለማፅደቅም ተስማምተዋል።

በተጨማሪም ፓርቲዎቹ የተደራዳሪ ፓርቲዎች ሥነ ምግባር፣ የሚዲያ ሚና፣ ውስጣዊ አደረጃጀት፣ የግብዓት አቅርቦትና የድርድሩ ስያሜ ላይ ተስማምተዋል፡፡ ድርድሩ ያለሚድያ በዝግ እንዲካሄድ ስምምነት ላይ የተደረሰ ሲሆን፣ ድርድሩን የሚመራው ኮሚቴ ግን ድርድሩ ሲጠናቀቅ በጋዜጣዊ መግለጫ ውጤቱን እንደሚያሳውቅ ተገልጿል፡፡

ድርድሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲካሄድም ፓርቲዎቹ መግባባት ላይ ደርሰዋል። ፓርቲዎቹ የመደራደሪያ ሰነዱን ‹‹የአገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች የድርድር አሠራር ደንብ›› በሚል ስያሜ አፅድቀውታል። በድርድሩ ወቅት የውስጥና የውጭ ታዛቢዎች ተገኝተው ሒደቱን መታዘብ እንደሚችሉም ተስማምተዋል፡፡

ተሳታፊ ፓርቲዎች ከዚህ ቀደም የድርድሩ ዓላማዎች ላይ መስማማታቸው ይታወሳል፡፡ በዚህም በአገሪቱ ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ ሥልጣን በምርጫ ሥርዓት ብቻ ለአሸናፊ የፖለቲካ ፓርቲ የሚተላለፍበትን ሥርዓት ይበልጥ ለማስፋት፣ በድርድር ወቅት የሚነሱ የተለያዩ ሐሳቦችን እንደ ግብዓት በመጠቀም መሠረታዊ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው ሕጎችን ለማሻሻልና የአፈጻጸም ጉድለቶችን ለማስተካከል፣ የፓርቲዎችን የዴሞክራሲያዊ የእርስ በርስ ግንኙነት ለማጠናከርና ለአገሪቱ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ዕድገት የሚኖራቸውን አስተዋጽኦ ለማጎልበት፣ ሕዝቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀርቡትን አማራጭ ሐሳብና ያላቸውን ሐሳብ ተገንዝቦ በዕውቀትና በመረጃ ላይ ተመሥርቶ እንዲንቀሳቀስ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር፣ ለብሔራዊ መግባባት አስተዋጽኦ ለማድረግ፣ እንዲሁም የአገሪቱን የፖለቲካ ምኅዳር ችግሮች ነቅሶ በማውጣት ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ድርድሩን እንደ መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም ተስማምተዋል፡፡

Source         –