April 17, 2017 18:39

 

ለመላ የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳ ለኢየሱስ ክርስቶስ ብርሀነ ትንሳኤ አደረሳችሁ፡፡

በአጋጣሚ የኦሪት መጽሐፈቅዱስ መጻህፍት በአብዛኛው በተለይም ከታላቁ አባት አብርሃም በኋላ ከጥቂቶቹ በቀር የእስራኤልን ታሪክ የሚዘክሩ በመሆናቸው እስራኤልም ከሕዝብ ሁሉ ተለይቶ ብቸኛው እግዚአብሔርን የሚያመልክ ሕዝብ ተደርጎ እንዲታይ አድርጎታል፡፡ እውነታው ግን ከእስራኤልም በላይ ለእግዚአብሔር ቅርብ የሆኑ ሌሎች ሕዝቦች እንደነበሩ ይሄው መጽሐፍ መዝግቦ እናነበዋለን፡፡ ለሁላችሁም ይገባችሁ ዘንድ ቀላል ምሳሌ እግዚአብሔር ራሱ የመሰከረለት ኢዮብ እስራኤላዊ አልነበረም፡፡ የክርስቶስ ምሳሌ የሆነው ታላቁ ካህን መልከጼዴቅም እስራኤላዊ አልነበረም፡፡ የሙሴ አማት የነበረውን ኢትዮጵያዊው ካህንንም አስታውሱ፡፡ እነዚህ ሁሉ እግዚአብሄርን የሚያመልኩና ቀድመውም ሥርዓት ሰርተው ከእስራኤል ውጭ የሆኑ ሌሎች ሕዝቦች አካል ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ግን እግዚአብሔርን የማያምኑም ሌሎች ሕዝቦች የአህያን ሥጋ ጥንቱንም አይበሉም፡፡ የኦሪት እምነት ተከታዮቹ ደግሞ ከዚህ የዘለቀ ሕግ አላቸው፡፡

እግዚአብሔርን የካደ ለሰይጣን ያደረ የማይረባ አእምሮ

የታላቁን ፈላስፋ የቅዱስ ጳውሎስን አንድ ንግግር እዚህ ጋር ልጠቅስ ወደድሁ፡፡ እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልፈለጉት መጠን የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው ይላል፡፡ የሚገርምና የሚያስፈራ አባባል ነው፡፡ ሰው ለማይረባ አእምሮ ከተሰጠ በኋላ ምንም እድል የለውም፡፡ ቅዱሱን የሚያረክስ ርኩሱን የሚቀድስ፣ እውነትን የሚተላ ውሸትን የሚወድ፣ በሥጋው እንኳን የሚያስፈልገውን ሳይሆን የሚፈልገውን እያደረግ ራሱን ወደማጥፋት ይሄዳል፡፡ ኢትዮጵያን ዛሬ የሙጥኝ ብሎ ሕዝቡን እገደለ እየፈነጨ ያለው ቡድን ማንነቱ ሲታይ የዚህ የማይረባ አእምሮ ሰለባ ውጤት ነው፡፡ ወያኔ በሉት በሥሩ ያካተታቸው ቡድኖች፣ ሌሎችም በ60ዎቹ ተነስተው የነበሩ በርካታ የመጀመሪያ መሠረታዊ መነሻቸው እግዚአብሔርን መካድና በርካሽ ማርክሲስታዊና ሌኒናው ፍልስፍና መገዛት ነው፡፡ እነዚህ አእምሮዎች ራሳቸውን ልክ እንደ ልዩና ምጡቅ አድርገው ያስባሉ፡፡ የረከሱበት አእምሮአቸው ግን ከራሳቸው አልፎ ብዙ ሕዝብንና አገርንም አርክሷል፡፡ አለም አለማትን (ዩኒቨርስ ብዙዎች የሚያውቁት ነው እውነታው ግን መልቲቨርስ ነው) ፈጥሮ የሚገዛ ኃያል እግዚአብሔር በእነሱ ከአሉ እንኳን በማይቆጠር አእምሮ ሥሌት የለም ብለው የካዱ ከእንሰሳ በወረደ አስተሳሰብ ያሉ ናቸው፡፡ አሳዛኙ ነገር ደግሞ የ60ዎቹ ትውልድ እርስ በእርስ በመጫረስ በቀር አንድም ስኬታዊ በሳይንስና በፍልስፍና የገፋ ሰው አናይባቸውም፡፡ ከሀዲዎቹን ማለቴ ነው፡፡ ከአሉም ምሳሌ ንገሩን፡፡ በእንሰሶች ብዙ ሕጎች አሉ፡፡ የ60ዎቹ ትውልድ ሕግ አለው ከተባለ አንድና አንድ ነው ስኬታማ ለመሆን ተቃዋሚ የምትለውን ሁሉ ግደል አጥፋ የሚል፡፡ አረመኔያዊነታቸው እርስ በእርስ መጫረሳቸውን አልፎ ይሄው ዛሬም ድረስ የምናየውን አረመኔያዊ ድርጊት ይፈጽማሉ፡፡ ዛሬ ወያኔን እድል ቀንቶት ያለበትን ቦታ ሌሎችም ቢያገኙት የተሻለ ነበር የሚል እምነት የለኝም፡፡ ወያኔ ከእነዛ አረመኔዎች አንዱ ነው፡፡ የዛን ዘምን ትውልድ ሌላው መገለጫው ከመጠን ያለፈ ሥግብግብነትና፣ ፍርሐት ነው፡፡ ለነገሩ የአረመኔነታቸውም ምክነያት ይሄው ስግብግብነትና ፍርሐት ነው፡፡ ጭንቅላታቸው ለማይረባ አእምሮ ስለተሰጠ አንደም መልካ ነገር ማሰብ አይችሉም፡፡ ሁኔታዎች ስላላመያመቿቸው እንጂ ሕዝቡን ሁሉ ጨርሰው እነሱ ቢኖሩም ይወዳሉ፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ የወደቀቸው በእንዲህ ያለ ፍጹም አረመኔያዊ በሆኑ አእምሮዎች ነው፡፡ ልብ በሉ ወያኔ ውስጥ ያለው ሁሉ ላይሆን ይችላል፡፡ በዋናነት የመሪነቱን ቦታ የያዙት ግን እንደዚያ ናቸው፡፡ እነዚህ አረመኔዎች ግን እግዚአብሔርን ካዱ እንጂ አያምኑም ማለት አደለም፡፡ አሳምረው የሚያምኑት ጌታ አላቸው፡፡ እሱም የሰዎች ሁሉ ልጆች ጠላት የሆነው ሰይጣን ነው፡፡ በሳይንስና በፍልስፍና እያመንኩ ነኝ የሚለው የ60ዎቹን ትውልድ ማንነት ስታጣሩ በአብዛኛው በጥንቆላ ሥራ የተሰማሩ ሰዎችን በማማከር የሚኖርና ሕይወቱን ሁሉ ለሰይጣን ግብር ያቀረበ ነው፡፡ ወያኔ ስልጣን ከወጣ እንደ ሰደድ እሳት የተስፋፋው የጥንቆላ ሥራ አንዱ መገለጫው ነው፡፡ ብዛት የላውን ቄስ  በደብተራነት ሥራ ሌላውን በቃልቻነትና ጥንቆላ አሰማርቶ የሚንቀሳቀስ ሥርዓት ነው አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው፡፡   በአንድ ወቅት አዲስ አበቤን ጉድ ያሰኘ (ነገሩ ጉድ ያሰኘው ሚዲያ ላይ መቅረቡ እንጂ ሁሉም በየስርቻው ያውቀዋል) ጠንቋይ የነበረውን ታምራት ገለታን ያልተሳለመ የመንግስት ባለስልጣን እንዳልነበረ በሰፊው ሲነገር ነበር፡፡ በአጠቃላይ ከጥንቆላ ጋር የተያያዘውን የዛሬዋን ኢትዮጵያን ጉዳይ ስናስተውል እንደነግጣለን፡፡ ዛሬ ሀብት ንብረት ለማግኘት በቃ በሥፋት አይነተኛ ዘዴ ተብሎ የተያዘው ጥንቆላ ነው፡፡ ልብ በሉ ጥንቆላ ከጥንትም ጀምሮ ነበር፡፡ ጥንቆላን እንደኋላ ቀር አስተሳሰብ ይቆጥራል ተብሎ የሚታሰበው 60ዎቹ ትውልድና አሁን ያለው ግን ዋነኛ መኖሪያ እንዳደረገው ስናስተውል ሊገርም ይችላል፡፡ ይህ ሁሉ የክፋት ውጤት ነው፡፡ ለማይረባ አእምሮ መሰጠት፡፡

በቅርቡ አንዳንድ ተማሪዎች የድህረምረቃቸውን በዚሁ በማሕበረሰቡ ተንሰራፍቶ በሚገኘው ጥንቆላ ላይ ለማድረግ እየሞከሩ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ምን ደረጃ እንደደረሱ አላውቅም፡፡ የወጣም ጽሁፍ አላነበብኩም፡፡ ሆኖም ጉዳዩ በሽፍንፍኑ ስለሚፈጸም እንጂ ሁኔታውን ላስተዋለ ምን እየሆንን ነው; እውን ኢትዮጵያ እግዚአብሔርን የሚያምኑ ሕዝቦች መኖሪያ ናት ወይ የሚለውን እንድንታዘብ ያስገደደናል፡፡ ብዙዎች ይህን ሲያነቡ ሊንቆራጠጡ ይችላሉ ግን በይፋ ብናውራው ፍሬውን ከገለባ ለመለየት ይረዳል፡፡

የዛሬው አሕያ ማረድ ሂደት

ከላይ የጠቀስኩት እግዝአብሔርን በመካድ የገባ የአእምሮ መንቀዝና ወደ ሰይጣናዊ መርሆ ማዘንበል ሂደት ቀስ በቀስ ሕዝብ የነበረውን እምነቶችና እሴቶች ሁሉ አጥፍቶ ወደራሱ ጎራ መቀላቀል ሂደት እንደሆነ ላስተዋለው ግልጽ ነው፡፡ ከተወሰነ ዓመት በፊት ለጆሮ እንኳን ፈጽሞ የማይሰሙ ነውሮች አሁን አሁን ጭራሽ የክብር እሴቶቻችንን እያጥላሉ ነውሮች የክብርን ማማውን እየወጡበት እናያለን፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም የዚሁ ሰለባ አንዱ አካል ነው፡፡ አህያ በኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን በአብዛኛው አፍሪካና በመላው ክርስቲያን፣ ሙስሊምም ሆነ አይሁዳውያን ዘንድ ከማይበሉ እንሰሶች ነው፡፡ ሌላውን አፍሪካ ባላውቅም ኢትዮጵያ ጥንቱንም ኦሪታዊ መሆኗ (ኦሪታዊ ያልሆኑ ነበሩ ለሚለው አብራራለሁ) ኬንያ ደግሞ በባሕልም ይሁን ዛሬ አብዛኛው ከሚከተለው እምነት አንጻር አሕያ ከማይበላባቸው አገራት ዋነኞቹ ለመሆናቸው ጥርጣሬ የለንም፡፡ አስገራሚው ነገር ግን የአሕያን ቄራ ለመክፈት እነዚህ አገሮች ቀዳሚዎች መሆናቸው ነው፡፡ በእርግጥም ኬንያ የዛን ያህል የጠነከረ ድርጊቱን የሚቃወም ሕዝብ መኖሩን አላውቅም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ለማይረባ አእምሮ ከተሰጡት በቀር ሁሉም የሚያወግዘው እጅግ አዋራጅ የሆነ የረከሰ ድርጊት ነው፡፡ ማንም ሕዝብ እሴቱ ከሆነው ነገር ውጭ ሲያመጡበት መቃወም የተለመደ ነገር ነው፡፡ ለኢትዮጵያውያን ግን (ለሙስሊሙም ለክርስቲያኑም) ጉዳዩ የእሴት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ፍጹም ሐይማኖታዊ የሆነ እምነትን ተገዶ እንዲተው ከመደረግ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የሀይማኖት ጉዳይን የእሴት ጉዳይ አድርጎ ማሰብ ሌላው ክህደት ነው፡፡ ሀይማኖት በእርግጥም ሰማያዊ አምላክን የመታዘዝ ጉዳይ እንጂ የምድራዊ እሴት ጉዳይ አደለም፡፡ ዛሬ የወያኔው ቡድን ይህን ድርጊት በኢትዮጵያ አፈር ላይ ሊፈጽመው ድፍረቱን ያገኘው ከላይ የጠቀስኩት ከ60ዎቹ ጀምሮ ያደረገው ልምምዱ ነው፡፡ ለዚህ ቡድን ገንዘብ እንጂ የሕዝብ እሴት፣ እምነት፣ ማንነት ጉዳይ ምኑም አደለም፡፡ ሁኔታዎች ስላልተመቹለትና እስካሁንም ያልተፈታውን የሕዝብ ተቃውሞ እየፈራ እንጂ ሁሉንም ማንነቱን አስጥሎ ሕዝቡን ማንነት አልባ ማድረግ አላማው የሆነ ቡድን ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ዋነኛ በተባሉት የኦርቶዶክስና እስልምና እምነቶች ላይ ያነጣጠረው ዘመቻ ዋነኛ ኢላማው የሕዝብን ማንነት የሚያጎሉ እሴቶች በእነዚህ እምነቶች በኩል ተጠብቆ መያዙ ነው፡፡  ለዚህ ተባባሪ ሆነው የተሰማሩ በየእምነቱ ያሉ የወያኔ ቡድን ወኪሎች አሉ፡፡ ሰማያዊ መንግስትን እንዲነገሩበት በተሰጣቸው መድረክ ሁሉ ዋነኛ የወያኔ ካድሬ ሆነው የምንሰማቸው የተሰጣቸውን ተልዕኮ መወጣት ነው፡፡ ዛሬ በይፋ የአህያ ሥጋ በዚህች አገር እያረድን ለውጭ ገበያ ልናቀርብ ነው ሲባል የአንዳቸውንም ድምጽ አለመስማታችን በዘመናት እነዚህ እምነቶች በምን አይነት አስተሳሰብ በአላቸው ሰዎች መዳፍ እንደገቡ እንታዘባለን፡፡  ይህን ጉዳይ ለሌሎች መተው እመርጣለሁ፡፡ ግን ዝም ከተባለ ሁሉንም እያወረድን እናየዋለን፡፡ ሆኖም ተራው ሕዝብ እምነቴ ባሕሌ የማይፈቅዱትን ነገር በቀዬዬና በምድሬ አታደርጉም በሚል እስከሞት መስዋዕትነት ሲከፍል  አሕያ ርኩስ ነው የሚሉት እምነቶች ቢያንስ ለሽፋን ያህል መናገር አልፈለጉም፡፡ ማንም አእምሮ ያለው በሕሉና እምነቱ የማይፈቅደውን ድርጊት የሚፈፅም ባዕድ ድርጅት በቄየው ሲመጣ ንብረቱን ማቃጠል አደለም ይህን ባዕድ የእምነቱና የባሕሉ ጸር የሆነን የረከሰ ነገር ወደቄየው የሚያመጡትን ቢያቃጥል በወንጀለኝነት የሚጠየቅበት ሕግ አይኖርም፡፡ ምን አልባትም የአገሪቱን እሴትና ሀይማኖታዊ ሥርዓቶችን በማስጠበቅ ሊያሸልመው በተገባ ነበር እንጂ፡፡ ሕግ አልባውና አረመኔው የወያኔ ቡድን በሂደት የመጣባቸውን ሕዝብንንና አገርን የማውደም አቅሙን እንዳዳበረ ስላአመነና ጉልበቱም ስላለው በሕገ ወጥ መልክ የአገሪቱ ሕግ የማይፈቅደውን ድርጊት በኢጥዮጵያውያን ላይ ሊፈፅም ቻለ፡፡ በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት አህያን ማረድ ሕገ-ወጥ እንደሆነ ነው የሚገባኝ፡፡ ሁሉም አገር የየራሱን እሴት የሚጠብቅ ሕግ አለው፡፡ የመንግስትነት ተግባሩም የሕዝብንና አገርን ማንነት የሚጠብቁ ሕግጋትን መጠበቅ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሁሌም እንደሚሆነው የወያኔ ቡድን ያደረገው የለመደውን ሲፈጽም የኖረውን ሕገወጥ ድርጊቱን ነው፡፡ ዛሬ አገሪቱን እዚህ ያደረሳት አረንቋ ውስጥ ያስገባት የወያኔው ሕግ አልባ ዋልጌ ቡድን ራሱ አወጣሁት የሚለውን ሕገ መንግስት ሁሉ ሽሮ በምትኩ አያሌ ዜጎችን ወንጀለኛ ለማድረግ አያሌ ሕገ-ወጥ ሕጎችን በማውጣት የፈጸማቸውና እየፈጸማቸው ያሉት ድርጊቶቹ ናቸው፡፡ ዛሬ የአህያ ቄራ መክፈትን ማሰብ የዚህ ሁሉ ባህሪው ውጤት ነው፡፡

በአህያው ቄራ ምክነያት የሕዝብ አስተያየቶች

እንታዘብኩት አብዛኛዎቹ አስተያየቶች እኔ ጥሩና በእርግጥም ከማንነታችን ጋር የተያያዙ ናቸው ሆኖም የአንዳንዶች አስተያየት አልተመቸኝም፡፡ እንደኔ እንደትክክለኛ ኢትዮጵያዊነት እንዲሁም እንኛውም የክርስትናም ሆነ እስልምና ሌላ ኢትዮጵያዊ የሆነ ባህላዊ እምነት አሕያን አርዳለሁ የሚል ቄራ መወገዝ ያለበት ነው፡፡ ይሄ ምን አለበት የሚያስብል የተራ ፍልስፍና ጉዳይ አደለም፡፡ ይልቁንም ጥልቅ የሆነ የሰብዕናን ምንነት የሚረዳ ፍትሀዊ ፍልስፍና እንጂ፡፡ እኔ የፈላስፋውን የቅዱስ ጳውሎስን አስተምሮት ከሚያደንቁት አንዱ ነኝ፡፡ ጳውሎስ በእንድ ስፍራ ስለሚበሉና ስለማይበሉ የተናገረውን በመጥቀስ በስጋ ገበያ የታረደውን ሁሉ መብላት ይቻላል ብሎ መናገር ከፍልስፍና የወረደ ነው፡፡ ራሱ ጳውሎስ በዛው መልዕክቱ ከምንም በላይ ለአእምሮ ጥንቃቄ እንዲደረግ ያስጠነቅቃል፡፡ ለቻይናዊ የውሻ ሥጋ ስለበላ ክርስቲያን አደለህም ማለት አይቻልም፡፡ ለኮሪያም እንዲሁ፡፡  ለኢትዮጵያዊው ግን የውሻ ሥጋ

ሆነ ሌላ መብላት ምን ችግር የለውም ብሎ በድፍረት የውሻ ሥጋ መብላት በእርግጥም መርከስ ነው፡፡ ጉዳዩ ከሥጋው ጋር አደለም ከሕሊናው ጋር እንጂ፡፡ ለሕንዳዊው የበሬ ሥጋ መርከስ ሊሆን ይችላል፡፡ በአጠቃላ አብዛኞቹ አስተያየቶች የአገሪቱንና የሕዝቧን እሴትና እምነትን በመደገፍ ድርጊቱን የሚያወግዙ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ዘመናዊ በመምሰል ነገሩን ስህተት አደለም ብለው የተከራከሩት በእኔ እምነት የስብዕና ምንነት ያልገባቸው ናቸው፡፡ በብዙ ማሕበራዊ ደረ-ገጾች አስተያየት በመስጠት የሚታወቁት አቶ ሥዩም ተሾመ የባሉ ግለሰብ የበሬ ሥጋ እየበላህ የአህያ ሥጋ አትብሉ ማለት አትችልም በሚል ያቀረቡት ግን ግለሰቡን በሌሎች አስተያየታቸው የማከብራቸውን ያህል በዚህ አስተያየታቸው ግን ትልቅ ስህተተታዊ ትንታኔ መስጠታቸውን መጠቆም እፈልጋለሁ፡፡ የሕዝብን ማንነት ከተራ ባሕል ጉዳይ ጋር ማንጻጸርም ይከብዳል፡፡ የኢትዮጵያውያን የአህያን ሥጋ ማርከስ ግን ከማንነት እሴት ብቻ የሚመነጭ አደለም ከላይ እንደጠቆምኩት ከጥንት ጀምሮ ከፈጣሪ የተሠጠን ትዕዛዝ መፈጸም እንጂ፡፡ የጅብ ቆዳን ለመዳህኒትነት መጠቀምን እንደ ምሳሌ ያቀረቡበት የአስተያየት ሰጭው አመክንዮ የሕዝብን ማንነት አለመረዳት ነው፡፡ የጅብን ቆዳ ለመዳሕኒትነት አንገት ላይ ማንጠልጠልን በምን መሥፈርት ከዚህ ጉዳይ ጋር እንዳነሱት ሊገባኝ አልቻለም፡፡ አስተያየት ሰጨው የላስተዋሉት ነገር ግን ቆዳውን የምንጠቀምበት ነገር ሁሉ ለመብል የምንጠቀምባቸው ብቻ እንዳልሆኑ መዘንጋታቸው ነው፡፡ ለማስተዋል ይረዳ ዘንድ ብዙ አዳኞች የአራዊትን ቆዳ ይለብሳሉ፣ የዝንጀሮ ጎፈር ዛሬም ድረስ በተለይ በኦሮምኛ ሸዋ ሕዝብ ዘንድ በዘፈን መድረኮች ሁሉ የምናየው ነው፡፡ የነበር፣ የአንበሳ፣ ሌሎችም ቆዳዎች እንደጌጥ እንደሚጠቀሙባቸው አንዘንጋ፡፡ አህያንና ፈረስንም እኮ ቆዳቸውን ሳንነካ አልኖርንም፡፡ ባይሆን በእኛ ባሕል ውሻን መንካት የተለመደ አደለም፡፡ አሕያና ፈረስን ለመጓጓዣነት የምንጠቀመው ቆዳቸውን ሳንነካ አደለም፡፡ ጉዳዩ እኮ የተነሳው ከመሠረታዊ አሕያን ከማረድ ጋር በተያያዘ እጅግ የጠለቀ ማሕበራዊ እሴትና እምነት ከአለው ሕዝብ ጋር የተያያዘውን ፍልስፍና ከመጠበቅ ጋር እንጂ በእምነቱና በእሴቶቹ ተቀብሏቸው ከሚገኙ መገልገያዎቹ ጋር አደለም፡፡ ምን አለበት ከተባለ ደግሞ የአህያን ስጋ መብላት ለኢትዮጵያዊ የሞት ያህል ችግር አለበት ነው መልሱ፡፡

ዓለም አቀፋዊ ነው ምናምን የሚለውም አስተያየት አመክንዮዋዊ አደለም፡፡ ሲጀምር የአህያ ሥጋና ቆዳ ጉዳይ ዓለም ዓቀፋዊ ሳይሆን ቻይናዊ ከዛ ቬትናማዊና አፍሪካዊ ኢፍትሀዊነት ነው፡፡ የሕዝብን እሴትና እምነትን ተጋፍቶ በማንአለብኝነት እየተፈጸመ ያለ አምባገነናዊ ሥርዓት አልበኛ ቡድኖች የሚያደርጉት ድርጊት፡፡ ገዘብ ከአመጣ ምን አለበት ከተባለም ገንዘብ የሌላው ከገንዘብ ይልቅ እምነቱንና ማንነቱን የሚፈልገው የደሀው ሕዝብ አስተሳሰብ አደለም፡፡ ገንዘብ ከተገኘ የሰውንም ልጅ ለእርድ ለማቅረብ ወደኋላ የማይሉ አረመኔዎች አስተሳሰብ እንጂ፡፡ በዘመናችን የባሪያ ንግድ አለም አቀፋዊ ማዕቀብ ባይኖርበት ኖሮ የወያኔ ቡድን ሕዝብ ለመነገድ የሚመኝ ቡድን ነው፡፡ ዛሬ በየአረብ አገራቱ ከባርነት ባልተናነሰ ተሰማርተው ያሉ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን ለወያኔ ምኑም አደለም ያቺ ደም ተፍተው የሚያመጧት የውጭ ምንዛሬ እንጂ፡፡

የአህያ ቄራው እውን ሥጋውን ለቬትናም ለማቅረብ ነው;

በቬትናም የአህያ ሥጋ ምን ያህል ተወዳጅ እንደሆነ አላውቅም፡፡ የአሕያው ቆዳ ለተባለው መድሐኒትነት ስለሚፈለግ ብዙ ዋጋ ሊያወጣ እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ የአህያ ሥጋ ግን ምን ዋጋ ቢያወጣ ነው ከኢትዮጵያ ወይም ከኬንያ ቬትናም ድረስ ተጉዞ የሚሸጠው የሚለው ሌላው ጥያቄ ነው፡፡ የጅብ ሥጋ ለሆቴል በማቅረብ ወንጀል የሚሰሩ ሰዎች በአሉባት አገር ከቻይናው ቄራ ጋር ተባብረው ለኢትዮጵያውያን ከማቅረብ ምን ያግዳቸዋል፡፡ በሕግ ይጠየቃሉ የሚል መልስ መቼም አይኖርም፡፡ ሲጀምር የአህያ ቄራ በኢትዮጵያ የተቋቋመው ከአገሪቱ ህግ ውጭ በወያኔ ወሳኔ መሆኑ መታሰብ አለበት፡፡ ሲቀጥል ግን የሕግ ከለላ እንኳን አለ ብንል ወያኔዎቹን ጨምሮ ከበዙት ወንጀለኞች አንጻር ተፈጻሚ መሆን አይችልም፡፡ ሁኔታዎች የሚያሳዩት የአህያን ሥጋ ቬትናም መሸጥ በሚል ሽፋን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማቅረብ እንደሆነ ማሰብ ስህተት አደለም፡፡ የአገሪቱንም ህግ ጥሶ የሕዝቡን እምነትና እሴት ገፍቶ የአህያን ቄራ በኢትዮጵያ ምድር ያቋቋመ የወያኔው ቡድን ሥጋውን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለማቅረብ ከቻይናዎች ጋር የማይመሳጠርበት ምንም አይነት ሕሊና እንደለለው ማስተዋል ብልህነት ነው፡፡ እንኳን ቤትናም ድረስ ለመካከለኛው ምስራቅ በቅርበት የከብት ሥጋ የሚያቀርቡ ቄራዎች ብዛት ሥጋቸውን ለኢትዮጵያውያን በማቅረብ ገበያቸውን እንደሚያካክሱ እናውቃለን፡፡

ሌላው አነሰም በዛም በጉልበት ሠራተኝነት የሚቀጠረው ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ለዚህ ኢትዮጵያዊ የሚደርስበት ተጽኖ ምን ይሆናል; ማንነት በየትኛውም ዋጋ አይገኝም፡፡ ማንነቱን ያጣ ሕዝብ መጨረሻው ባርነት ነው፡፡ ማንነት እንኳን በሰው በእንስሳም አለ፡፡ አንበሳ ምን ቢርበው ጅብ አይበላም፡፡ አብዛኞቹ ስጋ በሎች ምን ቢርባቸው ሌላውን ሥጋ በል አይበሉም፡፡ በኦሪት እንዲበሉና እንዳይበሉ የተዘረዘሩት እንሰሶችም ያለምክነያት አይደለም፡፡ አብዛኛ ነገሩም ከተፈጥሮዋዊ ስነሕይወታዊ ሰንሰለት ጋር ይያያዛል፡፡ መበላት ያልነበረባቸው  በችግር ምክነያት ተበልተው ይሆናል፡፡ ያ ማለት ግን ለሰው ልጅ ተስማሚ ሆነው አደለም፡፡ የአመጋገብ ሥርዓትን ከአየን ከእንስሳት ይልቅ የሰው ልጅ የፈነገጠ ነው፡፡ ተክልም ሥጋም በይ የሆነ ሰው ነው፡፡ ተክሉ መርዝ ካልሆነ አልቀረውም፡፡ እንስሳው ላይ ነው ገደቡ፡፡ በእርግጥም የማይበሉት እንስሳት ከስነሕይወት አንጻርም ለሰው ልጅ ተስማሚ እንዳልሆኑ ይገመታል፡፡

ኢኮኖሚያዊ አደጋው

የውጭ ምንዛሬ በሚል የሕዝብን እሴትና እምነት ተጋፍቶ የአሕያን ቄራ በኢትዮጵያ ምድር የከፈተው ወያኔ እንደሚለው ሳይሆን የተባለው ሁሉ እንኳን ትክክል ነው ብለን ብናምን አህያ አሁን ለማህበረሰቡ እየሰጠቸው ካለው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አንጻር  የዚህ ቄራ መገንባት ከፍተኛ የኢኮኖም ቀውስ እንደሚፈጠር መገመት ምሁራዊነት አይጠይቅም፡፡ አንድ አህያ በተለይም በከተሞች በአመት ቢያንስ 5ሺ ብር ማግባት ትችላለች ብንል፡፡ እድሜ ልኳን ምን ሊኆን እንደሚችል ግምቱ፡፡ አሁን ያለው የአህያ ቁጥር ቢበዛ 4ሚሊየን ነው የተባለው ቄራ በቀን 200 ከገደለ በአመት ከ70ሺ አህዮችን የጨርሳል፡፡ ልብ በሉ ይሄ ፍጹም አዲስ የሆን አይያን የሚገድል ነው፡፡ እስከዛሬ አሕያ በተለያዩ ምክነያቶች ከሚሞትበት ምክነያቶች ሌላ፡፡ አሁንም ባለው ሁኔታ የአህያ ቁጥር እየጨመረ አይመስልም፡፡ ይሄ ሲታከልበት ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት 60 ዓመት ምንም አህያ የሌለባት አገር ትሆናለች፡፡ በቻይና የህያን ቆዳ ለመዳኒት ከተባለበት ጀምሮ የአህያ ቁጥር በግማሽ እንደቀነሰ ይገመታል፡፡ እንግዲህ ማንነታችንንም አርክሰን፣ የገንዘብ ምንጫችንንም አጥተን ከዛም በላይ የሥነሕየውት አካል የሆነችውን አህያን ራሷን አጥፍተን የምንቀርበትን ሕገወጥ ድርጊት ነው በሕገወጡ ወያኔ እየተሰራ ያለው፡፡

 

መፍትሄው ምንድነው;

በእኔ እምነት መፍትሄው አንድና አንድ ነው፡፡ እኔ ፍጹም ንብረትን በማውደም የማምን ሰው አደለሁም ለእኔ የአህያው ቄራ ንብረት ሳይሆን የኢትዮጵያውያንን ማንነት ማጥፊያ ነው ብዬ ስለማምን መፍትሄው ከኢትዮጵያ ምድር ማስወገድ ብቻ ነው፡፡ ወያኔ ራሱ ሕገ ወጥ ሥራ እየሠራ ሕጋዊ ሥራ የሚሠሩትን ሕገወጥ ይላል፡፡ ይህን ቄራ ማቃጠል በምንም መስፈርት ሕገ-ወጥ አደለም፡፡ ንብረት ነው ልንል አንችልም፡፡ በሕገወጥ መንገድ የተገነባ ማንኛውም ሕገወጥ ንብረት ሌላ ጠቀሜታ ኖሮት ለሌላ አገልግሎት እስካልዋለ ድረስ ማጥፋት ትክክለኛው እርምጃ ነው፡፡ ከምንም በላይ በዋጋ የማይተመነውን የሕዝብን እሴትና እምነት የሚያጠፋን ግንባታ ማቃጠል ስህተት አደለም፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ የሕገወጥ አደንን ለመከላከል የአራዊቶች ቆዳና ጥርስ ሌሎችም አካላት ዋጋ ስለሚያወጡ ተብሎ እንደንብረትነት ለሌላ ገብያ እንኳን አይቀርቡም፡፡ በየትኛውም ገበየ የእነዚህን አራዊት አካላት መሸጥን ለማውገዝ ያለው አማራጭ የእነዚህ አራዊት አካላት በተያዙበት ሁሉ ሙሉ በሙሉ ተቃጥለው ወንጀለኞቹን እድል ማሳጣት ነው፡፡ ወያኔ ከቻይና ድርጅቱ ጋር የፈጸመው ተመሳሳይ የውንብድና ሥራ ሰለሆነ የዚህን ድርጅት ንብረቱን ማውደም ትክክል ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ እንመንግስት ማንነቱንና እምነቱን የሚከላከልለት አካል ከሌለ ሕዝቡ ራሱን በራሱ የመጠበቅ መብት አለው፡፡

 

አቤቱ ቅዱስ አባት እግዚአብሔር ሆይ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ጠብቅ

 

D.Sertse Desta

Source        –       By ሳተናው