ምስጢረ ህወሃት በሰላዩ አንደበት
ህወሃትን የከዳዉ የቀድሞው ሰላይ ከሳዲቅ አህመድ ጋር ቆይታ አድርጓል!!
ሰላዩ ማእከላዊ ድረስ እስረኛ ሆኖ በመግባት ዳኛ ብርቱኳን ሚደቅሳንና ኢንጂኒየር ሐይሉ ሻዉልን ለመሰለል ከተሰማሩት ግብረሃሎች አንዱ መሆኑን ይናገራል። የምርጫ 97 ግርግርን ተከትሎ ጦር ካምፕ ታፍሰዉ የተወሰዱ ወጣቶች በኢንጂኒየር ሐይሉ ሻዉል ላይ እንዲመሰክሩ በማግባባት ተልእኮ የተሰጠዉ መሆኑን፣ ዳኛ ብርቱኳን ሚደቅሳ ለልጇ ስትል በህወሃት የሚመራዉን መንግስት ይቅርታ እንድትጠይቅ የማእከላዊ ወጥ ቤት ሰራተኛ መስሎ በምግባት የማግባባት ተልእኮ እንደተሰጠዉ ያስረዳል።
ሙስሊሙ ማህበረሰብን በመሰል ረገድም መስጊድ ድረስ በመግባት፣ ሰላት ሰግዶ፣ሰላምታ ተለዋዉጦ ምእምናንን በመሰለል ተግባር ላይ ሲሰማራ ሌላ ሙስሊም ሰላይ ሙስሊምን መስጊድ ዉስጥ መሰለል አትችልም ብሎ እንዳስቆመዉ ይገልጻል።
በመስጊድ ዉስጥ ስለላዉን የምትቀጥል ከሆነ ለምእምኑ ማንነትህን ከነገርኩ እስከግድያ የሚያበቃ ድብደባ ይደርስብሃል ብሎ እንዳስጠነቀቀዉ ያስረዳል።
ህወሃት መራሹ መንግስት ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎችን ቁርዓን አስቀርቶ (አስተምሮ) ወደ መስጊድ እንዳስገባም ያጋልጻል። የዘጠኙም ክልሎች መታወቂያ ያለዉ የቀድሞ ሰላይ እስር ቤት ዉስጥ ለመሰለል ተልእኮ ተሰጥቶት ሲታሰር ገላዉ ላይ የሚለጠፍ የሬድዮ መገናኛን ይለብስ እንደነበር ያስረዳል። እስር ቤት ዉስጥ ያሉ እስረኞች የማያዉቋቸዉ እስረኞች ወደነሱ ሲቀርቡና ሲያወሯቸዉ ገላቸዉ ላይ የለበሱት የሬድዮ መገናኛ ሊኖር ስለሚችልና በዚያ የሬድዮ መገናኛ የህወሃት ባለስልጣኖች በቀጥታ ስለሚሰሙና ድምጹ ሊቀረጽ ስለሚችል ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል ሲል ያስጠነቅቃል።
ደቡብ አፍሪካ ድረስ በመሔድ የስለላ ተግባርን የተማረዉ የቀድሞ ሰላይ ይህም ሆኖ ግን ሰራዊቱም ሆነ ሰላዩ አጋጣሚዉን ካገኘ በህወሃት ላይ ከመነሳት የሚያግደዉ ነገር እንደሌለ ያስረዳል። የደሴዉ የሸህ ኑሩ ግድያ በህወሃት ደህንነቶች እንደተቀነባበረ የሚያስረዳዉ የቀድሞ ሰላይ ደሴ እስርቤት ዉስጥ በሐሰት የተወነጀሉ ሙስሊሞችን ለመሰለልና በቅጣት ማቅለያ ለማግባባት ለስለላ ተግባር እስር ቤት የገቡ የአካባቢዉ ተወላጅ የሆኑ ሙስሊም ሰላይ ጓደኞች እንዳሉትና ጉዳዩ በሐይማኖት የመጣ በመሆኑ እነዚህ ሰላዮች ከፍተኛ ጭንቀት ዉስጥ የገቡ መሆኑን ያስረዳል። በወታደራዊ መዋቅር ዉስጥም አማራና ኦሮሞ የሆኑ የጦር መኮንኖች እንደሚሰለሉ፤ እነዚህ የጦር መኮንኖች ሆን ተብሎ በሙስና እንዲዘፈቁ ተደርጎ የስልጣን እርከናቸዉ እንዳያግ የሚደረግበትን ተጨባጭ ያስረዳል። በመጨረሻም ይህንን አምባገነናዊ ስርዓት ማገልገል የታከተዉ ሰላይ ስርዓቱን ከድቶ መሰወሩን ይገልጻል።