“እጄና እግሬን የፊጥኝ ታስሬ ድብደባ ተፈጽሞብኛል፣ ተዘቅዝቄ ተግርፌያለው፣ የእግር ጉልበቴ በምስማር እየተወጋው መቅኒዬ እንዲፈስ ተደርጓል ”

ሰብአዊ መብቶች ሰዎች ሁሉ፣ ሰው ሆነው በመፈጠራቸው ብቻ ያገኟቸው መብቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ተፈጥሮአዊ ባህሪ ያላቸው መብቶች የትኛውም አካል የሚሰጠው ወይም የሚከለክለው አይደለም ። ሰዎች ሰብአዊ ፍጡር በመሆናቸው ብቻ የሚያገኟቸው መብቶች ነው።ይህ መብት በዘር፣ በቀለም፣ በጾታ፣ በቋንቋ፣ በፖለቲካ አቋም፣ በአመካከት፣ በዜግነት፣ በሀብት ደረጃ፣ ወዘተ ልዩነት ሳይደረግባቸው፤ እውቅና እና ጥበቃ ሊደረግለት የሚገባ ዋና እና መሰረታዊ መብት ነው።ሰብአዊ መብት በዓለም አቀፍ ደረጃ በእኩል ተቀባይነት ያገኘው ፅንሰ ሃሳብ፣አንድ ሰው በተናጠል ወይም በቡድን ያሉትን መብቶች እና ነፃነቶች እንዲከበረልት መብት ያለው ሲሆን፣በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ሰው በግሉ ወይም ከሌሎች ጋር በጋራ ያለበትን የሌሎችን መብት የማክበር ግዴታን ጭምር ያካተተ ነው ፡፡ የሰዎች ሰብዓዊ መብት እንዲከበርና የመብት ጥሰት ከተፈጸመ ተገቢውን የሆነ እርማት እንዲደረግ የሚከታተል ገለልተኛ ተቋም ያስፈልጋል።

ይሁን እንጂ በአገራችን የሰብዓዊ መብት አያያዝ በተመለከት ጉዳዮን የሚከታተል ገለልተኛ ተቋም በሚፈለገው ደረጃ ለማግኘት አልታደልንም። ሆኖም ግን የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ሰመጉ)፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ)።በኢትዮጵያ የሽግግር ወቅት የተቋቋመ ትልቅ ተቋም ነው። የተቋም መስራቾች በአገራችን ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የጎላ ድርሻ ያበረከቱና አሁንም እያበረከቱ የሚገኙ ናቸው። ከእነዚህም መካከል የኔታ/ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም በዋነኝነት የሚጠቀሱ ናቸው።ይህ ተቋም የመጀመሪያው መንግሥታዊ ያልሆነ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም ነው። (ሰመጉ) ወይም (ኢሰመጉ) በአገራችን ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ የበኩሉን አስተዋጽዖ በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡ሆኖም ግን ከመስረታው ጀምሮ እስካሁን ባለው የሥራ ሂደቱ፣በሥልጣን ላይ የሚገኘው መንግሥት በተቋሙ ላይ ቀጥተኛ በሆነ እንዲሁም በተዘዋዋሪ መንገድ ከፍተኛ ተጽዕኖ እየተደረገበት ያለ ተቋም ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣በሥልጣን ላይ የሚገኘው መንግሥት፤ለአገዛዙ ሥርዓት በሚያመች መልኩ አድርጎ ያዋቀረው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ በዜጎች ላይ ለሚፈጸመው መንግሥታዊ የሰብዓዊ ጥሰት ከፍተኛ ሽፋን በመስጠት ፣ ለደረሰው ኢሰብዓዊ ድርጊት፤ ተቋማዊ በሆነ መንገድ ሌላዉን ተጠያቂ ለማድረግ ተግቶ በመስራት ላይ የሚገኝ ተቋም ነው ፣ለማለት በሚያስደፍር ደራጃ ከኮሚሽኑ የሚወጡ ሪፖርቶች ይህን ጥርጣሬ የሚያጠናክሩ ናቸው ። ለዚህም እንደ-ማሳያ የሚከተሉን ማንሳት ተገቢነቱ አሻሚ ይሆንም፡፡ በእነ መቶ ኣለቃ ጌታቸው መኮንን የክስ መዝገብ ስር የሚገኙ 16 ተከሳሾች፣መካከል የአብዛኞቹ እስረኞቹ ጠበቃ የሆኑት፣ አቶ ወንድሙ ኢብሳ “እኔ እና ደንበኛሄ (15ኛ ተከሳሽ አቶ አግባው ሰጠኝ) ፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በሚቋቋምበት ወቅት በፓርላማ በነበረን ቆይታ ፣በአገራችን የዜጎች ሰብዓዊ መብት ተከብሮ የማየት ከፍተኛ ጉጉት ስለነበረን በበጎ ጎን የኮሚሽኑ መቋቋም እንመለከተው ነበር ።ይህ ተቋም አሁን ላይ ፣እንዲህ ያለ ከእውነት የራቀ ሪፖርት ሲያቅርብ በደንበኛሄ ላይ ከደረሰው ኢሰባዓዊ ድርጊት በተጨማሪ ያኔ በበጎ ጎን መቋቋሙን መመልከቴ አሁን ላይ ጥያቄ የሚያጭርብኝ ሆኖ አግኝቼዋለው። ይህም በመሆኑ በኮሚሽኑ ሪፖርት ሙሉ ለሙሉ ቅሬታ አለኝ። በማለት አቤቱታቸውን ገልጸዋል ።

በእነ መቶ ኣለቃ ጌታቸው መኮንን የክስ መዝገብ ስር የሚገኙ 16 ተከሳሾች፣ ከቂሊንጦ እስር ቤት ቃጠሎ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ ጥሰት እንደ ተፈፀመባቸው በተደጋጋሚ ሲገልጽ ከርመዋል። አቶ አግባው ሰጠኝ “እጄና እግሬን የፊጥኝ ታስሬ ድብደባ ተፈጽሞብኛል ፣ ተዘቅዝቄ ተግርፌያለው፣ የእግር ጉልበቴ በምስማር እየተወጋው መቅኒዬ እንዲፈስ ተደርጓል “በማለት በአካሉ ላይ የደረሰውን ጉዳት በማሰየት ፣ ድብደባ ሲፈጸምበት አብረውት የነበሩ የሰው ምስክሮችን እማኝ አድርጉ ፤ለፍርድ ቤት አቤቱታ አቅርቦ ነበር። ሌላኛው ተከሳሽ ፣አቶ አንጋው ተገኝ ከሁለት አመት በላይ በማዕከላዊ እና በቂሊንጦ በእስር ቆይታው በደረሰበት ከፍተኛ ድብደባ ፣ የጆሮ ታንቡር መሰንጠቅ የአይን ግርዶሽ እና የግራ አግር መሸምቀቅ የአካል ጉዳት ተጋላጭ ሆኗል።ለእረጅም ጊዜ በህመም ሲሰቃይ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ይህን ተከትሎ ሥር የሰደደበት በሽታ በጆሮ ላይ የፈጠረው የውስጥ ቁስለት እየሰፋ ሄዶ መስማት እስኪሣነው ድረስ ለበሽታ ተዳርጎል። ይህን ችግሩ በተደጋጋሚ ለፍርድ ቤት አቤቱታውን ሲያቅርብ ነበር። ለምሳሌነት እነዚህን እንደ-ማሳያ የተወሰዱ ቢሆንም ፣ በእስረኞች ላይ የደረሰው እና እየደረሰ ያለው ሰብዓዊ ጥሰት ቁጥር ስፍር እንደሌለው ጉዳዮን በቅርበት የሚከታተሉ ትዝብታቸውን በተለያየ መንገድ እየገለፁ ይገኛል።


እስረኞች ደርሶብናል ለሚሉት የሰብዓዊ ጥሰት አቤቱታቸውን የሰማው ከፍተኛው ፍርድ ቤት፣ ጉዳዩን አጣርቶ ሪፖርት እንዲያቀርቡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ኮሚሽኑ ደረስኩበት ያለው ድምዳሜ ለፍርድ ቤቱ በሪፖርት መልክ ሲያቀርብ ፣እስረኞች ደረሰብን ላሉት የሰብዓዊ ጥሰት አንዳችም እውቅና ያልሰጠ ሲሆን፣ እስረኞች ያቀረብቱ አቤቱታ በማስረጃ የተደገፈ አይደለም በማለትእንዲሁም ኮሚሽኑ ሪፓርት አቅርቧል። በወቅት በፍርድ ቤቱ ከፍተኛ ውጥረት ተከስቶ ነበር፣በተለይ አቶ አግባው ሰጠኝ፣አቶ አንጋው ተገኝ ፣አቶ ተስፋዬ ታሪኩ እንዲሁም ጠበቃ አቶ ወንድሙ ኢብሳ፤ የኮሚሽኑ ሪፖርት አስመልክተው የሰጡት አሰተያየት በከፍተኛ ቅሬታ እጅግ በጣም ልብ በሚነካ ሐዘን እና ዕንባ በተቀላቀለበት መልኩ ነበር፡፡ የእለቱን ችሎት በመምራት ላይ የነበሩ ሦስቱም ዳኞች ይቅርብ በነበረው የእስረኞች እና የጠበቃ ቅሬታና አቤቱታ እንዲሁም በችሎት ታዳሚ የነበሩ ቤተሰብ ፣ የእስረኞች የሥራ ባልደረባ እና ጓደኞች ያሳዩት የነበረው ከፍተኛ ሐዘኔታ እና ቁጭት፤ዳኞቹ ሊቋቋሙት ያልቻሉት በፊታቸው ላይ በግልጽ በሚታይ መልኩ መረበሻቸው እንዲሁም ሐዘኔታ እንደተሰማቸው እኔም በቦታው ላይ ስለ ነበሩክ የታዘብከት እውነት ነው። በኮሚሽኑ የቀረበው ሪፖርት በድጋሚ እንዲጣራ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል ። አንባቢያን ይህ ከላይ የተገለጸው የኮሚሽኑ ሪፖርት የቂሊንጦ እስር ቤት መቃጠል ተከትሎ፣ እስረኞች በሸዋ ሮቢት ለሦስት ወር በነበራቸው የእስር ቆይታ የተፈጸመባቸው የሰብዓዊ በተመለከተ ነው። እንዲህ አይነቱ አሰቃቂ የሰብዓዊ ድርጊት በእስረኞቹ ላይ የተፈጸመው ፣ የቅሊንጦ እስር ቤት “እኛ ነን ያቃጠልነው” በማለት ቃላቸውን በግዴታ እንዲሰጡ ነው። ይህን በተመለከተ “ቃላችን የሰጠነው በግዳጅ ስቃይ ደርሶብን “ነው በማለት እስረኞቹ ለፍርድ ቤት ቃላቸውን ሰጥቷል።

ይህን ሃቅ ወደ ጎን በመተው ኮሚሽነር ዶ/ር አዲሱ ገ/እግዚአብሄር የሚመሩት “የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን” በተለያየ ወቅቅ በብዙሃን መገናኛ በመቅር ፣ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ እንደሆን በሚመስል መልኩ፣በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ የሚያቀሩብት ሪፓርት ከወዴት የመጣ ነው ?! ይህ በእንዲህ እንዳለ ፣በዚሁ ሳምንት ኮሚሽነር ዶ/ር አዲሱ ገ/እግዚአብሄር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመቅረብ ሌላ ፍፁም ከእውነት የራቀ ወይም ወደ-መፍትሔ ሊያቀርብ የማይችል የተቋማቸውን ሪፖርት ይዘው መቅረባቸው፤ የተቋሙ ገለልተኝነትን በይበልጥ ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ እንደሆነ ለመገመት ብዙም የሚቸግር አይደለም፡፡ ……… (ክፍል ሁለት) ይቀጥላል….የኮሚሽኑን የ11 ወር ሪፖርት በተመለከት…..

(ይድነቃቸው ከበደ)