April 21, 2017

✔ ደግሞ ዘፋኝና ዘፈንን ደገፈ ብላችሁ ተንጫጩ አሏችሁ ። ዳሩ እኔ ምን አገባኝ ስትንጫጫ ውለህ ስትንጫጫ ብታድር.!

✔ ጦማሬን ሳያነቡና ፤ አንብበውም መልእክቴ ሳይገባዎትና ሳይረዱት አስተያየት እንዳይሰጡ ይመከራሉ ። ተናግሬያለሁ።

✔የቴዎድሮስ ካሳሁን ” ኢትዮጵያ ” የተሰኘው አዲሱ ሥራው አሁን በሥራ ላይ ያለውን የህዝብ መዝሙር ተክቶ “የኢትዮጵያ የህዝብ መዝሙር ” ቢሆን ደስታዬ ወደር የለውም ።

.ገዢያችን ኢህአዴግ በኢትዮጵያችን ውስጥ ለማድረግ የሚፈልገውን እና የሚያቅዳቸውን እቅዶች ለአባላቱ የሚገልጽበት እንዲሁም ሊወቅጥ የሚፈልጋቸው አካላትም ካሉ በነገር ወጋ ወጋ በማድረግ መልእክቶቹን የሚተነፍስባት “አዲስ ራዕይ ” የምትባል አቅጣጫ ጠቋሚ መጽሔት አለችው ። ይኽች መጽሔት የድርጅቱ ልሳን ናት ። ሟቹ ጠቅላይ ሚንስትር እና አቶ በረከት ስምኦን በር ዘግተው ያዘጋጇት የነበረችና በብርቱም የደከሙባት መጽሔት እንደሆነችም ይነገርላታል ።

ታዲያ ይህች መጽሔት ዘንድሮ በ2009 ዓም በወርሐ መስከረምና ጥቅምት እትሟ ላይ ” ኢትዮጵያዊነትን ” በሚመለከት አንድ ለየት የሚል እና በኢህአዴግ ተፈጥሮ ውስጥ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ኢትዮጵያዊነትን በተመለከተ የሚገርም እንግዳ ሃሳብ ይዛ ወጥታ ነበር ። በወቅቱ በዚህ ጉዳይ ላይ መጽሔቷን ካነበብኩ በኋላ የራሴን ምልከታ ለመጻፍ ፈልጌ ምክንያቱን በውል በማላውቀው ሁኔታ እጄን እያየዘኝ ለብዙ ጊዜ ሳልጽፍ እስከ አሁን ድረስ ቆየሁ ።

አሁን ግን ጊዜው ደርሰ መሰለኝ አንዳች ስሜት ጻፍ ጻፍ አለኝና ይህችን አጠር ያለች ጦማር ለመጻፍ ተነሳሳሁ ። ምክንያተ ጽሕፈቴም አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን ወይም “ቴዲ አፍሮ” በቅርቡ ” ኢትዮጵያ ” በሚል ርዕስ ያወጣውን ዘፈን ተከትሎ በፀረ ኢትዮጵያዊነት ጎራ የተሰለፉ ወገኖች እስኪነስራቸው ድረስ በልጁ ላይ እሪሪ ሲሉና ሲያላዝኑ ባይ ግዜ አረ በህግ ለማለት ያህል ብዕሬን ማንሳቴ ይታወቅልኝ ።

ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግን ጠፍጥፎ የሠራው ህውሓት ፀረ ኢትዮጵያ አቋም የሚያራምድ ፓርቲ ነው እየተባለ በብዙዎች ዘንድ ሲወቀስ የኖረ ፓርቲ መሆኑ ይታወቃል ። ከራሱ ከህውሓት ፈጣሪዎች መካከል የሆኑና ከድርጅቱ ጋር እህል ውኃቸው ሲያልቅ የተወገዱና ሰማኒያቸውን በይፋ የቀደዱ የድርጅቷ አንጋፋ አባላት በጋዜጣዊ መግለጫም ሆነ በቃለ መጠይቅ እንዲሁም በመጽሐፍ መልክ የህውሓትን ፀረ ኢትዮጵያዊነት ደጋግመው እስኪያቅረን ድረስ ሲነግሩን መክረማቸውም የአደባባይ ሀቅ ነው ።

ትውልዱ በሰፈሩ እንጂ በሀገሩ እንዳይመካ እና ጠባብ ሆኖ በጎጥ እያሰበ ጎሰኛ ሆኖ በመንደርተኝነት ደረጃ ወርዶ እንዲኖር አድርገው በመቅረጽ ያለፉትን 25 ዓመታት የኢትዮጵያዊነትን መንፈስ ከኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ጠራርገው ለማውጣት ያልፈነቀሉት ድንጋይ ያልቧጠጡት ጋራ እንዳልነበረም ይታወቃል ። ዓላማቸው የተሳካ በመሰለ ጊዜ ሁሉ በድንገት በሚፈጠሩ ክስተቶች ኢትዮጵያዊነት ሳይታሰብ ግንፍል ብሎ እየወጣ ድካማቸውን ሁሉ አፈር ከድሜ እያስጋጠባቸው ሲያደናብራቸውም ብዙ ጊዜ ተመልክተናል ።

በተለይ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት ሳይወዱ በግዳቸው መስማት የማይፈልጉትን ቀረርቶና ሽለላ ሁሉ በቴሌቭዥንና በራዲዮ እያሰሙ ኢትዮጵያ ተወረረች ተነስ ብለው 80 ሺህ ኢትዮጵያዊ ወጣት ጭዳ አድርገው በከንቱ ደሙ እንዲፈስ ማድረጋቸውም አይዘነጋም ።

ኢትዮጵያ ለአርጀንቲናው የዓለም ወጣቶች ዋንጫና ለደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ዋንጫ ባለፈች ጊዜ ከሞያሌ እስከ ዛላንበሳ ከቶጎጫሌ እስከ አሶሳ ድረስ ህዝብ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራውን ይዞ ወጥቶ ኢትዮጵያዊነት ሊጠፋ የማይችል መንፈስ መሆኑን በግልፅ አሳይቷል ። ምርጫ ዘጠና ሰባት ላይም አሸናፊ የነበሩት የአንድነት ኃይሎች መሆናቸው እሙን እንደነበር አይዘነጋም ።

በቅርቡ በኦሮሚያ ፣ በአማራና በደቡብ በኮንሶ ህዝባዊ አመጽ መነሳቱን ተከትሎ አገዛዙ እስከአሁን ድረስ ሀገሪቱን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና በወታደራዊ አስተዳደር ሥር እንድትወድቅ ያደረጋት ህዝባዊ አመጽ መከሰቱ ይታወቃል ። አመጹ የብዙ የዜጎችን ክቡር ህይወት የቀጠፈና በመቶ ሚልየን የሚገመት የሀገሪቱ ንብረትም የወደመበት እንደነበርም ይታወሳል ። በተለይ የአማራውና የኦሮሞው ማኅበረሰብ በሰልፎቹ ላይ አንድነቱን መግለጹ ፤የመንግሥቱን ከፍተኛ ሹም አቶ ጌታቸው ረዳን ጭምር ወደ አደባባይ አውጥቶ ” ምን ሲደረግ ነው ሁለቱ ብሔሮች አንድ የሚሆኑት.? እሳትና ቤንዚን ፣ እሳትና ጭድ አድርገናቸዋል ብለን ስናበቃ በምን አግባብ ነው እንዲህ ሊስማሙ የቻሉት? 25 ዓመት ሙሉ የደከምነው ድካም ከንቱና ዋጋ ቢስ እኮ ነው የሆነብን ። እያሉ ያለሀፍረት እስኪ ጮሁ ድረስ የታዘብንበት ጊዜም የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው ።

አመጹን ተከትሎ ነው እንግዲህ ገዢው ኢህአዴግ ወጣቶቹ ያመጹበትን እና የሀገር ንብረት ያወደሙበትን ምክንያት መርምሬና ገምግሜ የደረስኩበት ድምዳሜ ነው ብሎ የድርጅቱ ልሳን በሆነችው ” አዲስ ራዕይ ” መጽሔት 11ኛ ዓመት ቅፅ 5 ቁጥር 6 ገፅ 68 ላይ የግምገማውን ውጤት የነገረን ።

የግምገማውን ውጤት እንደሚከተለው አቀርበዋለሁ ።

ይሁንና የሚጠበቀውን ያህል ጠንካራ የሀገር ፍቅርና ብሔራዊ የሀገር ስሜት ተገንብቷል ለማለት የሚያስደፍር ሁኔታ ላይ አንገኝም ። በዚህ ረገድ ኢህአዴግና የሚመራው መንግሥት የሠሩት ሥራ ደካማ እንደሆነ ይቀበላሉ ። በትምህርት ቤቶች የሚሰጠው የስነ ዜጋ ትምህርትም የታሰበውን ያህል ውጤታማ አልሆነም ። የመንግሥትም ሆነ የግል ሚዲያዎችም ዜጎች ብሔራዊ ስሜትና የሀገር ፍቅር እንዲያጎለብቱ የረባ አስተዋፅኦ አላደረጉም ። ይልቁንም አሉታዊ አስተዋፅኦቸው የሚያይልበት ሁኔታ ይታያል ።

በአሁኑ ወቅት በወጣትነት ዕድሜ ያለው በኢህአዴግ በምትመራዋ ኢትዮጵያ ያደገ በመሆኑ በታላላቅ ወንድሞቹና እህቶቹ የነበረውን ብሔራዊ ስሜትና ሀገራዊ ፍቅር ሊወርስ ላለመቻሉ ዋነኛው ተጠያቂ ኢህአዴግ እንደሆነም አያከራክርም ” ። በማለት እርግጡን በመናዘዝ በሁላችን ፊት ንስሐ መግባቱን ግልጥ ባለ አማርኛ ይነገርናል ። ኢህአዴግ በዚህ ኑዛዜው ላይ በደርግ ዘመን የተወለዱና ያደጉ ልጆች ቢያንስ በሀገር ፍቅር ያበዱ መሆናቸውን ያምንና ይህን ሀገርን የመውደድና የማፍቀር ብሔራዊ ስሜት ድራሹን ያጠፋው ራሱ መሆኑን ይነግረናል ።

ነገር ግን ይላል ኢህአዴግ ሆዬ.! “ነገር ግን ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ወጣቱም በአይኑ ከሚያየውና ከነ ጉድለቱም ቢሆን ተጠቃሚ ከሆነበት ሀገራዊ ለውጥና እድገት እንዲሁም በቀጣይ ከፈነጠቀው ተስፋ በመነሳት በሀገሩ ላይ ፍቅርና እምነት ማሳደር ይገባዋል ። በማለት ኑዛዜውን ይደመድማል ። ሌላ 25 ዓመት ጠብቁ ነው አማርኛው ።

zemedkun Bekele

በነገራችን ላይ ይህን የኢህአዴግን የግምገማ ውጤት ተከትሎ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶሳችንም በ2009 ዓም በወርሐ ጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ማጠቃለያ ላይ ባወጣው የአቋም መግለጫ ላይ የቤተክርስቲያኒቱ ሰባኪያነ ወንጌል የሆኑ አገልጋዮች ለስብከት በቆሙበት ዓውደምህረት ላይ ሁሉ ” ኢትዮጵያዊነትን ” በአዲስ መልክ ለምእመናን እንዲያስተምሩ ብሎ መመሪያ ማውጣቱም አይዘነጋም ።

የሆነው ሆኖ የኢህአዴግን የጎሳ ፖለቲካን ጡጦ ጠብተው ያደጉ እንደ ጀዋር መሃመድ አይነት ጠባቦችን ህውሓት ማፍራቷ ግን አልቀረም ። ጀዋር አቶ አባ ዱላ ገመዳ በሪሞት የሚቆጣጠሩት የአገዛዙ የገደል ማሚቶ መሆኑም ይታወቃል ። እንዲያውም አሁን አጠገቡ ሆነው በደንብ የዘረኝነት መርዙን በደንብ እንዲጋተው እና እንዲተፋው አቶ ጁነዲን ሳዶን በኬንያ በኩል አድርገው በመሸኘት አሜሪካ አስገብተው እየተቆጣጠሩ እንዲያስለፈልፉት መደረጉም ግልጽ ነው ።

ታዲያ አሁን ይህን እንደ ዳይነሶር ከኢትዮጵያ ምድር እንዲጠፋ የተደረገን ኢትዮጵያዊነት ለመመለስ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን /ቴዲ አፍሮ / እንደ ዜጋ ኢህአዴግ እንደ ፓርቲ ያመነውንና የተናዘዘውን ኑዛዜ ሰምቶ ፣ እንደ ክርስቲያንነቱም በፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ በወርሐ ጥቅምት ባሳለፈው ውሳኔና በሰጠው መመሪያ መሰረት ኢትዮጵያዊነት በአዲስ መልክ ይሰበክ የሚለውን መልእክት አድምጦ ፤ እሱም በሙያው ኢትዮጵያዊነትን ለመስበክ ተነሳ ። እናም ምኑ ላይ ነው የዚህ ልጅ ጥፋት ። ግንበኛ አይደል ፣ አናጢ አይደል ፣ ስፖርተኛ አይደል ፣ ኢንጅነር አይደል ፣ ዶክተር አይደል ፣ በቃ ሙያው መዝፈን ነው ። ጽድቅና ኩነኔውን ትተን እንደዜጋ በሙያው ሀገሩን በማወደሱ ምክንያት ይህ ሁሉ ውርጅብኝ እና መግፋት ሊፈጸምበት አይገባም ። ስለ እውነት ከሆነ የአሁኑ የቲዴ ” ኢትዮጵያ ” የሚለው ዘፈኑ ለትችት እንኳ አይመችም ። ሽንጥና ዳሌ የሌለበት ንፁህ የህዝብ መዝሙር ነው ።

በዚህ ዘፈኑ እንደከዚህ በፊቱ እምዬ ምኒሊክን ቢያነሳ ኑሮ ሻአቢያ ፣ ህውሓትና ኦነግ እሪሪሪሪሪ ይሉ ነበር ። አፄ ኃይለሥላሴንም ቢያነሳ አሁንም ሸአቢያ ፣ ህውሓትና ኦነግ ይጮሁ ነበር ። ደርግን አላነሳም እንጂ ቢያነሳ ኑሮ ሸአቢያና ህውሓት ማለቃቀሳቸው አይቀርም ነበር ። መለስ ዜናዊን ቢያወድስ ኑሮ ደግሞ ምን ሊገጥመው እንደሚችል እናንተው ገምቱ ። ከተቃዋሚው ወገን ብቻ ሳይሆን ከፓርቲው አባላት ጭምር ማለቴ ነው ። የሆነው ሆኖ ቴዲ በዚህኛው ” ኢትዮጵያ ” በተሰኘው ዘፈኑ ኢትዮጵያን ከማንም እና ከምንም ጋር ሳያነካከ ” ኢትዮጵያን በራሷ ረቂቅ አድርጎ በሙያው ገልጿታል ። በፍፁም ሸአቢያንም ፣ ህውሓትንም ፣ ኦነግንም የሚያላዝኑበት አንዳችም አይነት አጀንዳ አላስቀረላቸውም ። እንዲያም ሆኖ ግን በተለይ የህውሓትና የኦነግ ሰዎች ማለቃቀሳቸውን አልቀረም ። ክፉ አመል ።

በተለይ የአድዋ ተወላጅ ነው የሚባለው አይነስውሩ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ፀጋይ በዚህ በኩል ዋነኛ ተጠቃሽ ነው ። ዝም ብሎ ይበጠረቀዋል ። በጥራቃ ያለው ማን ነበር.? በነገራችን ላይ ” ርዕዮት ” የሚባለው ራድዮ አዘጋጆችና ባለቤቶች ይሄው ወዲ አድዋ አይነስውሩ ቴዎድሮስ ፀጋይና አቶ ታምራት ነገራ ናቸው ። አቶ ታምራት የቅንጅት ተመራጭና የአዲስ ነገር ጋዜጣም ዋና አዘጋጅ የነበረ ሰው ነው ። አቶ ታምራት ይሠሩበት ከነበረው ተወዳጅዋ ጋዜጣ አዲስ ነገር ጋዜጣ ላይም ቴዲን እየወቀጡ ዋጋ ሲከፍሉ እንደነበር አስታውሳለሁ ። ይኽ ሰው ከኢትዮጵያ ከወጣ በኋላ አንዳንዴ ” ኦሮሞ ኦሮሞ ” መጫወትም ሲዳዳው አያለሁ ። ጠርጥር አለ ሰውየው ። ያልጠረጠረ ተመነጠረ አለ ሌኒን.!

አንዳንድ የህውሓት ሰዎች ልጁን የሚተቹበትን ነገር ቢያጡ ቴዲን ድሃ አይረዳም ወደሚል ክስ ወርደውት አረፈዋል ። ነገር ግን መርዳት አለመርዳት የልጁ መብት ቢሆንም ቴዲ በተለያዩ ጊዜያት ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች እጁን መዘርጋቱ ይታወቃል ። ከሁሉ ከሁሉ በሶማሌ ላንድ የሚኖር አንድ ኢትዮጵያዊ የትግራዋይ ተወላጅ ልጅ በሀገሪቱ ፍርድቤት 700 ሺብር የደም ካሳ ካላመጣ በሠይፍ አንገቱን ተቆርጦ እንደሚሞት በሚድያ በወጣ ጊዜ ህውሓት ጆሮ ዳባ ልበስ ነበር ያለችው ። ኤፈርትም ፣ የኤድናሞልና የጎላጉል ህንጻ ባለቤቶችም የሰንሻይን ሪል ስቴት ባለቤት አቶ ሳሙኤል ብትሉ ሁሉም የትግራዋይ ባለሃብቶች “የራሱ ጉዳይ ነው” ብለው ዝም ሲሉ ቴዲ እኮ ነው የደም ካሳ የተባለውን ብር ከፍሎ ይህን ልጅ ነፃ የወጣው ። ሙሉ የህውሓት አባላት ቴዲን ቢጠሉት እንኳ የትግራይ ልጆችና የዚህ ከሞት የተረፈ ልጅ ቤተሰቦችና ዘመድ አዝማድ ጓደኞች ቴዲን ሊጠሉት አይችሉም ።

እኔ ዘፈኑን ልገመግም አይደለም የተነሳሁት ። በደንብ ግን እንደሁላችሁም አድምጬዋለሁ ። ያውም ደጋግሜ ነው ያደመጥኩት ። ደግሞስ አዳሜ የአደባባይና የፌስ ቡክ ላይ ጧሚ ፣ ጸሎተኛና ክርስቲያን ሆነህ ነው እንጂ እንኳን የቴዲን “አሸው ” እና ” ይሞታል ወይ ታዲያ ” የሚል ዘፈን መሳይ ጩኸት ስትኮሞክም አይደል እንዴ ውለህ የምታድረው ። አስመሳይ ሁላ ። በቃ ልጁ ኢትዮጵያን ገልጿታል ብቻ ማለት አይገልፀውም ። እንደ አንድ ዜጋ ሀገሩን ከአእምሮ በላይ በሆነ ጥበብ ገልጿታል ። ያውም አፍ ለመክፈት ቀዳዳ በማያሰጥ መልኩ በደንብ ተዘጋጅቶበት ነው ስለኢትዮጵያ ያዜመው ።

ህውሓት ኢትዮጵያዊነት እንዲጠፋ ያደረግሁት እኔ ነኝ ። እናም አጥፍቻለሁ ብሎ በግልጽ ተናዝዟል ። ቴሌቭዥን ጋዜጣና ራዲዮውም በዚህ ጉዳይ ላይ ተጠያቂ እንደሆኑ አምኗል ። አበበ ጊደይ የተባለ ጮሌ 24 ሰዓት ሙሉ ስለ እንግሊዝ ኳስ እንዲያደነቁረን የፈረደብንም ኢህአዴግ መሆኑ ይታወቃል ። እናም ቴዲ የኢህአዴግን ኑዛዜ አይቶ የማርያም መንገድ በማግኘቱ ሀገሩን በዚህ ረቂቅ መንገድ በማወደሱ ሊሸለም ፣ በሚዲያም ሥራው ሊለቀቅለት ሲገባ መልሶ ኑዛዜውን መቅደድ ነውር ነው ። በቃ ባትደግፉት እንኳ ዝም በሉት ። ኢትዮጵያ ፣ ኢትዮጵያ ፣ ኢትዮጵያ ይበልበት ።

ኦነጎች የቴዲን ፖስተሮች በእግራቸው በመረጋገጥ ልጁን የጎዱት ቢመስላቸውም ለጁ ግን ላይወርድ የተሰቀለ ከጨረቃ የተጎራበተ ሰው ሆኖ አርፎታል ። እንኳን ሌሎች ሰዎች ይቅርና ቴዲ ራሱ ከወጣበት ከፍታ ልውረድ ቢል እንኳን በቀላሉ መውረድ የሚችል አይመስለኝም ።

አሁን ይህችን ጦማሬን በማዘጋጀት ላይ ሳለሁ አንድ Yonas Tekelea የተባለ ሰው የቴዲ አፍሮን “ኢትዮጵያ “የተሰኘውን ቢልቦርድ የአገዛዙ ሰዎች ቀጭን ትእዛዝ ለደህንነቶች በመስጠት ፖስተሩ ከተሰቀሉበት ሥፍራ እያወረዱት ነው የሚል መልእክት ጽፎ አየሁ ። እናም ዜናው እውነት ከሆነ በእውነት አሳፋሪ ድርጊት ነው የሚሆነው ። አንዲት የትግርኛ ዘፋኝ ባለፈው ጊዜ መቀሌ ላይ በሰረገላ ተቀምጣ ፣ በማርሽ ባንድ ታጅባ ፣ አንዱ ሲዲዋ 50 ሺህ ብር በጨረታ መሸጡን መስማታችን ይታወሳል ። ኤደንም ቴዲም በዜግነታቸው እኩል ሊታዩ ይገባል ። ባለፈው ጊዜ ኦነጎች የልጁን ፖስተሮች በእግራቸው ረግጠው እልሃቸውን መወጣታቸውን አሳይተውን ነበር ። አሁን ደግሞ የኦነግ መንትያ ወንድሞች በአዲስ አበባ የተሰቀለውን የቴዲን ቢል ቦርድ በማውረድ ፀረ ኢትዮጵያዊ አቋማቸውን እያሳዩ መሆኑኑ እያሳዩን ነው ።

ይህን ፖስቴን ተከትሎ የሚመጡ ጥያቄዎችና ዘፈን ኃጢአት አይደለም ወይ.? እናም አንተ እንዴት ዘፋኝን ትደግፋለህ.? የሚሉ ሰዎች ማጉረምረሞች እንደጉድ እንደሚመጡ ይጠበቃል ። እኔም እላቸዋለሁ ዘፋኝነትም ሆነ ዘፈን የእግዚአብሔርን መንግሥት አያስወርሱም ። ይሄንን አምናለሁ ። እንደ ሰው ዘፈኑን አልሰማም ማለት ግን አይቻለኝም ። እንዲያ ብል በጥራቃ ነው የምሰኘው ። ቀነኒሳ ፣ ኃይሌና ፣ ስለሺ ስህን ተከታትለው የገቡበትን የሩጫ ወድድር አስመልክቶ ቴዲ አፍሮ በዘፈነው ” መርቆ ሸኝቶ ለዓለም ፣ አስይዞ ሰንደቅ ዓላማ ” የሚለውን ዘፈን ስሰማ በወቅቱ እንባዬ ለምን ያለ ከልካይ ገደቡን ጥሶ ይወርድና ይፈስ እንደነበር ያን ጊዜም ሆነ አሁን ምንም አይነት ምላሽ የለኝም ።

ጎበዝ.! የዜግነት ክብር በኢትዮጵያችን ምንትስ ሆኖ የሚለውን ብሔራዊ መዝሙር በየትምህርት ቤቱ ስንዘምር መንግሥተ ሰማያት ያስገባናል ብለን እኮ አይደለም ። ነገር ግን የኢትዮጵያ በሔራዊ መዝሙር ነው ስለተባልን ነው ሙስሊም ክርስቲያን ሳንል ቆመንና ቀጥ ብለን የምንዘምረው ።

በእኔ በኩል ፤ በእኔ ዕይታ.! እንደ እኔ እንደ እኔ ፤ እንዲያውም ይኽ አሁን ቴዎድሮስ ካሳሁን ያቀረበው ” ኢትዮጵያ ” የተባለው ሥራው አሁን በሥራ ላይ ያለውን የህዝብ መዝሙር ተክቶ “የኢትዮጵያ የህዝብ መዝሙር ” ቢሆን ደስታዬ ወደር የለውም ። አከተመ ። አራት ነጥብ ።

ይህንንም ራሴው በእጄ ጻፍኩት ። +4915217428134 ደግሞ የቫይበር ፣ የኢሞና የኋትስአፕ መልእክቶችን የምቀበልበት የእጅ ስልኬ ነው ።

ሻሎም.! ሰላም.!

ዘመድኩን በቀለ ነኝ።


ሚያዝያ 11 /2009 ዓም


ከራየን ወንዝ ማዶ።