እንደምታውቁት በዚህ ዘመን የሥነኪን (በዘልማድ የሥነጥበብና የኪነጥበብ) ሥራዎች ገበያ ሆን ተብሎ የሕገወጦች ሲሳይ እንዲሆን በማድረግ ጉልበት እውቀት ገንዘባቸውን አፍስሰው የደከሙት ከያኔያንና አሳታሚዎች ከገበያ ውጭ እንዲሆኑ ከስረው እንዲጠፉ ሲደረግ የመኖሩ ነገር የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ሥነኪን በሀገራችን በሁሉም ጎን እየኮሰመነች፣ እየጎሰቆለች፣ እየጫጨች፣ እየተዳከመች መሆኗ በግልጽ የሚታይ ጉዳይ ነው፡፡

ዘርፉ ያቀፋቸው የሥነኪን ማኅበረሰብ በተለያየ ጊዜ መብታችን ይከበር! ፣ ሠርተን መብላት አልቻልንም፣ በአደባባይ እየተዘረፍን ባዷችንን ስንቀር መንግሥት በዝምታ ሊመለከተን አይገባም! ፣ መንግሥት የሥራ ደኅንነት ዋስትናችንን የማስከበር ግዴታውን በመወጣት ከችግራችን ይታደገን!….” እያሉ የሚያሰሙት የመረረ የብሶት ጩኸታቸው አይሎ በሚመጣበት ወቅት ይሄንን ብሶት ለማስተንፈስ ያህል ለዚያው ሰሞን የይስሙላ የዘመቻ እርምጃዎች ይወሰዱና ወዲያውኑ ነገሮች ወደነበሩበት ቦታ እንዲመለሱ በማድረግ አገዛዙ በሀገራችን ሥነኪንና በባለሞያዎቿ ጢባጢቦ ሲጫወት መቆየቱ ይታወቃል፡፡

ይሄን የተገነዘቡ የዘርፉ ባለሙያዎች እኛ የምንፈልገው ከስንት ጊዜ አንድ ጊዜ የሚወሰድ የዘመቻ እርምጃ ሳይሆን በጸጥታ ኃይሉ እይታ ሕገወጥ ድርጊቱ እንደሌሎች የወንጀል ተግባሮች ሁሉ ትኩረት ተሰጥቶት ዘወትር በሕገ ወጥ ድርጊትነቱ እየታየ የሚተላለፉ ዜጎች ሲገኙ በሕግ ተጠያቂ የሚሆኑበት ሁኔታ እንዲኖር ነው፡፡ ሕጉ ተፈጻሚነት ያግኝ! የጸጥታ አስከባሪ (የፖሊስ) አባላት ይህ ድርጊት በአደባባይ በዓይናቸው ስር ሲፈጸም በዝምታ አይመልከቱ!
ሕገወጥ ቅጅ ሲሸጡ ሲያጋጥሟቸው ስርቆት የሚፈጽሙ ግለሰቦች ሲያጋጥሟቸው በሕግ ተጠያቂ እንደሚያደርጓቸው ሁሉ እነኝህንም ተጠያቂ ያድርጉ!” እያሉ ቢጮሁም አገዛዙ ሆን ብሎ የሚያደረገው ውንብድና በመሆኑ ሰሚ አላገኙም፡፡
የዘርፉ ባለሙያዎች ጉዳያችን ብለው በቀጥታና በቅርበት ሲከታተሉት የነበረው ጎንደር በፋሲል ሙዚቃ ቤት እጅ ከፍንጅ ተይዞ የነበረውን በርካታ ሚሊዮን (አእላፋት) ገንዘብ ይንቀሳቀስበት የነበረ የሕገ ወጥ ቅጂ ተግባር አገዛዙ ፈጽሞ ባልተጠበቀና እጅግ በሚገርም ሁኔታ ያለአንዳች የተጠያቂነትና የኃላፊነት ስሜት ዓይን ባወጣ ነውረኛ ተግባር ፍትሕ በአደባባይ ተደፍልቃ ፍትሕ ሳይሰጥ ጉዳዩ እንዲዘጋ በማድረጉ ይህ ሕገወጥ ተግባር እንዲቀጥል ያለውን ፍላጎት በሚገባ ያረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡

አዲስ አበባ ውስጥ ካሉት ሕገወጥ ቅጅ ከሚሠሩት ግለሰቦች ውስጥ አገዛዙ ያደራጃቸው እንዳሉም ይነገራል፡፡ ይህ የወንበዴ ቡድን ከዚህም የከፉ በርካታ የውንብድናና የክህደት ተግባሮችን በዚህች ሀገርና ሕዝብ ላይ ሲፈጽም ኖሯልና፣ በግልጽ እየተየ ያለውም ግልጽ ጉዳይ የሚያሳየው ይሄንኑ በመሆኑ ይሄንን አያደርግም!” ለማለት ይከብዳል፡፡
ለመሆኑ ወያኔ ሥነኪን እንድትጠፋ እንድትከስም ይሄንን የውንብድና ተግባር የሚፈጽመው ለምንድነው? መባሉ አይቀርምና ወያኔ ይሄንን የውንብድና ተግባር በሥነኪን ላይ የሚፈጽምበት ምክንያት ሥነኪን ማለትም ሙዚቃ (ዘፈን)፣ ተውኔት (ቲያትር)፣ ሥዕልና ቅርፃቅርፅ፣ ሥነ ግጥምና ሌሎች የድርሰት ሥራዎች በተፈጥሯቸው የሕዝብ ጠበቆች ናቸው፡፡ ወገኝተኝነታቸው ለሕዝብ ለተበዳይ ለተገፋ ነው፡፡ ብሶት የመተንፈሻ፣ ቅሬታ የማሰሚያ፣ የማስተማሪያ፣ የማንቂያ፣ የመቀስቀሻ መንገዶች ናቸው፡፡ ይሄ ሲባል ግን አንባገነኖን ሥነኪንን እንድታገለግላቸው አድርገዋት አያውቁም ወይም አያደጓትም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ተገዳ ያለፈቃዷ እጇን ጠምዝዘው በመሆኑ እንድታገለግላቸው የሚያደርጓት ወዳና ፈቅዳ እንዳደረገችው ሁሉ የእነሱም አገልጋይ እንደሆነች ልንቆጥራት አንችልም፡፡ ሥነ ኪን የተፈጠረችበት ዓላማና ግቧ ግን ለሕዝብ፣ ለእውነት ጥብቅና ቆሞ በመታገል የሕዝብን ሁለንተናዊ ሕይዎት፣ የሀገርን ሁኔታ ምቹና ሰላማዊ ማድረግ!” የሚለው ነው፡፡ የሥነኪን ተፈጥሮ ይሄ መሆኑና በከያኔያን የሥነኪን ሥራዎችም ይሄ መንጸባረቁ ነው ወያኔን ያልተመቸውና የሀገራችንን ሥነኪን ደብዛዋን ለማጥፋት ከገባ ጊዜ ጀምሮ በሸፍጠኛ ተንኮሉ እያዳከመ ወደ መቃብሯ ሲገፋት የቆየበት ምክንያት፡፡

በታሪክ እንደምታስታውሱት ፋሺስት ጣሊያን ሊመሠርተው ለፈለገው ቅኝ አገዛዝ ትልቅ እንቅፋት ሆነውብኛል!” በማለት አዝማሪዎችን ልቅም አድርጎ ነበር የፈጃቸው፡፡ በሥራዎቻቸው ሕዝቡ አሻፈረኝ እንዲል፣ አርበኞችን እንዲቀላቀልና እንዲደግፍ፣ ባንዶች እንዲያፍሩ እንዲሸማቀቁ፣ ሕዝብ ባንድነትን እንዲጸየፈው ወዘተረፈ. በየሠርጉ፣ በየማኅበሩ፣ በየገበያው፣ በየበዓላት መከወኛ ሥፍራዎች፣ በየመጠጥ ቤቱ ወዘተረፈ. እየዞሩ ሞያዊ ግዴታቸውን በመወጣታቸው ነበር ጣሊያን እንቅፋቴ ብሎ የፈጃቸው፡፡ ጊዜ ይገድበናል እንጅ በብዙ መልኩ አገላብጠን ብናየው ዛሬም ወያኔ እያደረገ ያለው ፋሽስት ከወሰደው እርምጃ የከፋ እንጅ ያነሰ አይደለም፡፡

ሕዝቡ ቢነቃና ቢተባበር ግን ኦሪጅናል (ንጥር) የሥነኪን ሥራ ኅትመቶችን ገዝቶ በመጠቀም ብቻ ወያኔ በሀገር ጥበብ ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት በጣም አነስተኛ እንዲሆን በማድረግ የሀገርን ጥበብ ከመጥፋት ታድገን እድገት እንድታሳይ ማድረግ ይቻላል፡፡ ጥበብ ተጠባቢዋን ማሳደር ማስተዳደር የማትችልበት ደረጃ ላይ በመድረሷ ተረካቢ ባለሞያ ከያኔያንን እያጣች እውቀቷም እየተረሳ እየጠፋና እየደከመ ነውና፡፡ በመሆኑም ለሽዎች ዓመታት ሲበስል፣ ሲዘመን፣ ሲጠበብ፣ ሲዳብር የመጣው የዚህች ሀገር ጥበብ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል!” በሚለው ጠባብና ደንቆሮ አገዛዝ እንዳልነበረ ሆኖ ከመጥፋቱና ሀገሪቱ ሥልጣኔዋን፣ ጥንታዊነቷን፣ ማንነቷን፣ ታሪኳን፣ እሴቶቿን የሚያሳይላትን፣ የሚያረጋግጥላትን ጥበብ አጥታ የራሷ ጥበብ ያልነበራትና የሌላት አዲስ ተመሥራች መሐይም ሀገር መስላ ከመታየቷ በፊት ሕዝብ ይሄንን የበሰለና ኃላፊነት የተሞላበት ግንዛቤ ሊይዝ በሚችልበት ጉዳይ ላይ መረባረብ ይጠበቅብናል፡፡
ነገ የቴዎድሮስ ካሳሁን የዘፈን ሥራ ገበያ ላይ ይውላል፡፡ ከላይ ከገለጽኩላቹህ ምክንያት በተጨማሪ የዚህን ከያኔ ኦሪጅናል (ንጥር) ቅጂ ለመግዛት የምንገደድበት ሌላኛው ምክንያት ደግሞ ልጁ ሥነኪን ለሀገሩና ለሕዝቡ የጫነችበትን ሞያዊ ግዴታ ለመወጣት ጥረት በማድረጉ ከጨለማው አበጋዞች ወይም ከጥፋት ኃይሎች ምን ያህል ፈተና እንዲደርስበት እንደተደረገና እየተደረገም እንዳለ በሚገባ የምታውቁት እውነት ነው፡፡ እንዲያው ሌላ ሌላውን ትተን ቀላሉንና እንዲያጣ የተደረገውን ጥቅም ብቻ እንኳን ብናይ በተለያየ ጊዜ ከሁለት የንግድ ድርጅቶች ብቻ ከሃያ ሚሊዮን (አእላፋት) ብር በላይ የሥራ ውል እንዲሰረዝበት ተደርጎ ከፍተኛ ጥቅም አጥቷል፣ ተመሳሳይ ሥራዎችንም የማግኘት ዕድል እንዳያገኝ ተደርጓል፡፡ ለእኛ ለሕዝብ ሲል፣ ለሀገር ሲል፣ ለማንነት ሲል፣ ለታሪክ ሲል ነው ቴዲ ይሄንን ዋጋ ለመክፈል የተገደደው፡፡ ይህ የእሱ ዕዳ በከባዱ ስላለብን ኦሪጅናል (ንጥር) ቅጂውን መገብየታችን በጥቂቱም ቢሆን ያጣውን ጥቅም ሊያካክስለት ይችላልና ይሄንን በማድረግ ዕዳችንን እንድንወጣ አደራየ ጥብቅ ነው፡፡
በተረፈ ሌላው ላሳስባቹህ የምፈልገው ጥብቅ ጉዳይ ቢኖር ኢትዮጵያበለሚለው የቴዲ አዲስ ዜማው ላይ ከአንዳንድ አካላት ሲሰነዘር የሰማሁትን ትችት ምናልባት በሌሎችም ሥራዎች ዓየን!” የሚል ትችት ልትሰሙ ብትችሉ ለእነኝህ ትችቶች ፈጽሞ ጆሮ እንዳትሰጡ ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ በግልጽ መናገር የምፈልገው ጉዳይ ቢኖር የዘፈን አቀናባሪዎች በተለይ ዋና ዋናዎቹ የቴዲን ዘፈኖች እንዳያቀናብሩለት በአገዛዙ ከባድ ጫና ሲደረግባቸው ነው የቆየው፡፡
ቴዲ አማራጭ ቢያጣ የውጪ ባለሙያዎችን ለመጠቀም የሞከረበት አጋጣሚም ነበር፡፡ በዋጋቸው አይቀመሴነትና ለእኛ ዘፈኖች ቃናና ቅኝት ባዳ የመሆናቸው ችግሮች አሰናከሉት እንጅ፡፡ በዚህ ምክንያት ቴዲ አዳዲስ አቀናባሪዎችን ለመጠቀም የተገደደበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በመሆኑ ያለው ሁኔታ እንዲህ አስቸጋሪና የተወሳሰበ በሆነበት ሁኔታ ቅንብሩ እንዲህ ሆነ፣ ዜማው ምንትስ አለ…” እያሉ መተቸት ልጁ የገጠመውን ፈተና አለማገናዘብ በመሆኑ ከዚህም የተነሣ ትችቱ በፍጹም አግባብነት የሌለው በመሆኑ ማየት መስማትና ማገናዘብ ለተሳናቸው ተችዎች ትችን ጆሮ ሳትሰጡ የቴዲን ዘፈኖች መኮምኮም ብቻ ነው ያለባቹህ እላለሁ፡፡ደናቁርቱ ተችዎች ትናንትን ናፋቂዎች ናቹህ!” ቢሏቹህ አዎ! ትናንትን ናፋቂ የሆነው ታሪክ ያለን ወይም ባለታሪክ ሕዝብ ስለሆንን ነው፡፡ ትናንትን የማይናፍቅ ወይም ለትናንት ክብርና አክብሮት የማይሰጥ ባንዳና ታሪክ የሌለው ማንዘራሽ ብቻ ነው!” በሏቸው አመሰግናለሁ!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com