አቶ አሰፋ ጫቦ

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

(ዘ-ሐበሻ) እውቁ ፖለቲከኛ አቶ አሰፋ ጫቦ አረፉ:: አንጋፋ ጸሓፊ፤ ማራኪ ተናጋሪ እና አንደበተ ርቱእ የፖለቲከኛና የሕግ ምሁር የነበሩት አቶ አሰፋ ዳላስ ቴክሳስ ሆስፒታል ውስጥ ሲታከሙ ቆይተው በዛሬው እለት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
_________________

አሰፋ በሕይወት ዘመናቸው ስለኢሳያስ አፈወርቂና ኦነግ ያቀረቡትን ዘገባ ለማድመጥ እዚህ ይጫኑ

_________________

አቶ አሰፋ በሕይወት በነበሩበት ወቅት ባሳሰቡት መሰረት አስከሬናቸው ወደ ሃገር ቤት ተልኮ የሃገራቸውን አፈር እንደሚቀምስ ተገልጿል:: አቶ አሰፋ ማን ናቸው? በሕይወት በነበሩበት ወቅት እውቁ ጸሐፊ አፈንዲ ሙተቂ እንዲህ ገልጿቸዋል:::

በ1995 ነው፡፡ በዚያ ዓመት የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው የጭሮ (አሰበ ተፈሪ) ከተማ ስራ ጀምሬ ነበር (ከጥቂት ወራት ቆይታ በኋላ ተውኩት እንጂ)፡፡ በዘመኑ ከዞኑ አስተዳዳሪዎች ይበልጥ የሚፈራ አብደላ ኢድሪስ የተባለ የኦህዴድ (OPDO) ካድሬ ነበር፡፡ በተለይ አብደላ በኦነግነት በሚጠረጠሩ ሰዎች ላይ ምህረት የለሽ እርምጃ ይወስዳል ተብሎ ስለሚነገር ወጣቶች እርሱን ሲያዩት በጣም ይሸበራሉ፡፡
ታዲያ አንድ ቀን “ነጃት ካፌ” (የአህመድ ጋሼ ቤት) ከሚባለው ካፍቴሪያ ሆኜ ከጓደኞቼ ጋር ሻይ ቡና በማለት ላይ ሳለሁ አብደላ ኢድሪስ ከጓዶቹ ጋር መጣ፡፡ ከበረንዳው ላይ ቁጭ ብለው ትኩስ ነገር እንዲመጣላቸው ካዘዙ በኋላ ጨዋታ ቢጤ ጀመሩ፡፡ በመሀሉ እብደት የጀማመረው አንድ ወጣት ወደ አካባቢው መጣና “ለከፋ” ጀመረ፡፡ አብደላንም “ሰላም ጋሼ” አለው፡፡
“እንተዋወቃለን እንዴ?” (አብደላ ነው እንዲህ የሚለው)
“ረሳኸኝ እንዴ? በደምብ ነው የምንተዋወቀው”
“ማን ትባላለህ?”
“ኦነግ”
“አቤት ምን አልክ?” ብሎ ከወንበሩ ተነሳ አብደላ፡፡
ልጁ ሳቅ እያለ “ኦነግ ስልሽ ደስ አለሽ እንዴ? እኔ የናንተን ኦነግ አይደለም ያልኩት፡፡ ይልቅ ቁጭ በል”
አብደላም ግራ በመጋባት “ምን እያልክ ነው ታዲያ?” በማለት ጠየቀው፡፡
“እኔ የኛን ኦነግ ነው ያልኩት፡፡ ኦነግ ስል Omotic Liberation Front (የኦሞቲክ ነጻነት ግንባር) ማለቴ እንጂ ስለናንተ ኦነግ አልተናገርኩም፡፡ ለመናገርም መብት የለኝም” አለው፡፡ ይኼኔ በበረንዳው የነበረው ታዳሚ በሙሉ በሳቅ አውካካ፡፡ ለቁጣ የተነሳው አብደላም ሳቅ በሳቅ ሆነና አረፈው፡፡
በኋላ ላይ እንደሰማሁት ያ ልጅ የወላይታ ተወላጅ ነበረ፡፡ ለዚያም ነው “የኦሞቲክ ነጻነት ግንባር ነኝ” ያለው፡፡ ያ አብደላ የሚሉት ካድሬ በበኩሉ ሀገር ሲያተራማምስ ከርሞ የህዝብ ቁጣ ሲገነፍል ከድርጅቱ ተባረረ፡፡ ይባስ ብሎም ድርጅቱ ራሱ አብደላ በድብቅ የገደላቸውና የዘረፋቸው ሰዎች እንዳሉ አመነና ወደ ፍርድ ቤት ወሰደው፡፡ እዚያም የ25 ዓመት እስራት ተፈረደበት፡፡
*****
ከዚህ በፊት ይህንን ጨዋታ ጽፈነው ነበር፡፡ ጨዋታውን የደገምንላችሁ በልጁ አንደበት የተገለጸውን “የኦሞቲክ ነጻነት ግንባር” የተባለ ድርጅት የመሰረተው ዛሬ በመስመር ላይ ያገኘነው ሰውዬ መሆኑን በእግረ-መንገድ ልንገልጽላችሁ ስለፈልግን ነው፡፡ ይሁንና ምክንያታችን ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ዛሬ ያገኘነው ሰው እንዲህ ዓይነት ጨዋታዎችን ስንነግረው ከኛ የሰማውን ነገር በስላቃዊና በኮሚክ አጻጻፉ ደጉሶ አጃዒበኛ ድርሰት የሚቀምምበት ችሎታ ስላለው ጭምር ነው፡፡ ሰውዬው ወደፊት ይህንን ጨዋታ እየወዘወዘው ለየት ያለ መጣጥፍ ባያወጣለት አፈንዲ ምን አለ በሉኝ!!… (ርዕሱን ከወዲሁ ስንገምት “የሁለት ኦነጎች ወግ” የሚል ሊሆን ይችላል)፡፡
አዎን! ሰውዬው በርዕሱ ላይ በስም የገለጽነው አሰፋ ጫቦ ነው፡፡ ደቡብ ኢትዮጵያ ካፈራቸው ሶስት ስመ-ጥር ፖለቲከኞች አንዱ ነው (ሌሎቹ የሲዳማው ወልደአማኑኤል ዱባለ እና የሐዲያው ዶ/ር በየነ ጴጥሮስ ናቸው)፡፡ አሰፋ ጫቦ ግን ፖለቲከኛ ብቻ አይደለም፡፡ አንጋፋ የህግ ባለሙያ፣ ዳኛ፣ ጠበቃ፣ የሀገር አስተዳዳሪ፣ አንደበተ ርቱዕ ተናጋሪ፣ የስነ-ቃልና የባህል አዋቂ፣ የታሪክ ምሁር፣ ደራሲ፣ ጸሐፊ፣ ይህንን ሁሉ ነው፡፡
አሰፋ ጫቦ በአጼ ኃይለ ሥላሤ ዘመን የፓርላማ አባልም ነበረ፡፡ በፓርላማው ውስጥ ሆነው ታሪካዊውን የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ይደግፉ ከነበሩት ጥቂት ተራማጅ ግለሰቦች መካከል አንዱ እርሱ ነው፡፡ የሃይለ ሥላሤ መንግሥት ከስልጣን ሲባረር ደግሞ ከባሮ ቱምሳ፣ ዘገዬ አስፋው፣ ኢብሳ ጉተማ፣ አብዩ ገለታ እና ከሌሎችም ጋር ኢጭአት (የኢትዮጵያ ጭቁኖች አብዮታዊ ትግል) የተባለ ድርጅት በመመስረት ከደርግ መንግሥት ጋር ለመስራት ሞከሩ (አሰፋ ጫቦ፣ ባሮ ቱምሳና ዘገየ አስፋው ኢጭአትን በመወከል “የህዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት” የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ሆነው ነበር)፡፡
ከዓመት በኋላ ግን የደርግ አብዮት ልጆቹን መብላት ጀመረና እነ ኃይሌ ፊዳንና መስፍን ካሡን እንክት አድርጎ ዋጣቸው፡፡ የአሰፋን ነፍስ ግን አላህ በተአምሩ አተረፋት፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን የአብዮቱ የቅጣት ጠበል ለርሱም አልቀረለትም፡፡ ለአስር ዓመታት በስመ-መጥፎው የማዕከላዊ እስር ቤት የግፍን ጽዋ ሲጠጣት ከረመና በ1981 ተለቀቀ (አሰፋ ጫቦ የማዕከላዊ ቆይታው ምን ይመስል እንደነበረ “እንዲህ መለስ ብለው ሲያዩት” የሚል ርዕስ በሰጠው ውብ መጣጥፍ አስነብቦን ነበረ)፡፡
አሰፋ ጫቦ በብዙዎች ቀልብ ውስጥ የገባው በ1983 መጨረሻ ላይ “የኦሞቲክ ነጻነት ግንባርን መስርቶ እንደገና ወደ ፖለቲካው ውስጥ በገባበት ጊዜ ነው፡፡ በዚያ ዘመን 87 ወንበሮች በነበሩት የተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ልበ ሙሉእ ሆነው የተሰማቸውን ከሚናገሩት ጥቂት ሰዎች መካከል አንዱ እርሱ ነበረ፡፡
አሰፋ ጫቦ በ1985 አጋማሽ ላይ ከቪኦኤው ጌታሁን ታምራት ጋር ያደረገው ቃለ-ምልልስ በሀገር አቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ አድርጎት ነበረ፡፡ አልፎ ተርፎም ቃለ-ምልልሱ አሰፋንና የያኔውን የሽግግር መንግሥት ያፋታ ሰበብ ሆኗል፡፡ አሰፋም ከዚያች ቃለ ምልልስ በኋላ ወደ ምክር ቤቱ አልተመለሰም፡፡ እርሱ ምክር ቤቱን ጥሎ ሲኮበልልም የምክር ቤቱ ግርማ ሞገስ መገፈፍ ጀመረ፡፡ ቀስ በቀስም ምክር ቤቱ አንደበት አልባ ሆነና ቁጭ አለ፡፡ በ1987 መጨረሻ ላይ ደግሞ ያኛው ምክር ቤት ተበትኖ አሁን የምናየው ፓርላማ መጣ፡፡
*****
ታዲያ አሰፋ ወደ ውጪ ኮብልሎም አላረፈም፡፡ ገና ሀገረ አሜሪካ ከመግባቱ ብዕሩን ጨበጠና “አጃዒብ” የሚያስብሉ መጣጥፎችን ያዥጎደጉድ ጀመር፡፡ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ በጦቢያ መጽሔት፣ በኢትኦጵ መጽሔት እና በሌሎችም የፕሬስ ውጤቶች ላይ ሲጽፋቸው በነበሩት መጣጥፎች ብዙ አድናቂዎችን አፈራ፡፡ ከዚህም አልፎ የርሱን አጻጻፍ የሚከተሉ ብዕረኞችም ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ፡፡
በምርጫ 97 ማግስት ግን እነዚያ መጽሔቶች በጅምላ ተዘጉ፡፡ አሰፋ ጫቦም አለሁ ሳይለን ተሰወረብን፡፡ አድራሻው ቢፈለግ ምንም ሊገኝ አልቻለም፡፡ በተለይም ኢንተርኔቱ ጽሑፎችን ለአንባቢያን የማዳረሱን ስራ ቀላል ባደረገበት ዘመን የርሱ መጥፋት በጣም አሳስቦን ነበረ፡፡ በዛሬዋ ዕለት ግን በለስ ቀንቶን አሰፋ ጫቦ በህይወት እንዳለ ለማረጋገጥ ቻልን፡፡
*****
በመግቢያዬ እንደጠቀስኩት ይህንን “ቂራአ” የመጻፍ “ነሻጣ” የመጣልኝ ባለፈው ሌሊት ሊነጋጋ ሲል ነው፡፡ የቀድሞው “ኢትኦጵ” መፅሔት ዋና አዘጋጅ የሆነው ወሰን ሰገድ ገብረኪዳን በፌስቡክ ግድ ግዳው ስለአሰፋ ጫቦ ጽፎ አየሁት፡፡ በጽሑፉ ውስጥ አሰፋ ጫቦን “ታግ” ያደረገ መሆኑ ደግሞ የሰውዬውን ማንነት እንዳጣራ ቀሰቀሰኝ፡፡ ወደ ፌስቡክ ፕሮፋይሉ ሄጄም ከላይ እስከ ታች ጎረጎርኩትና ከነ ፎቶግራፉ እውነተኛውን አሰፋ ጫቦ ሆኖ አገኘሁት፡፡ ነገር ግን በዚህ ብቻ አላበቃሁም፡፡ ወደ ኢንቦክሱም ጎራ አልኩኝና “ኦሪጂናሌው አሰፋ ጫቦ ነህ ወይስ እኛ የማናውቀው አሰፋ ነህ?” ብዬ ጠየቅኩት፡፡ እርሱም በጥያቄዬ ተገርሞ “አረ.. አንተ ሰውዬ!!… ደሞ አሰፋ ጫቦ ራሱን እያባዛ ነው በለኛ” በማለት ከልቤ አሳቀኝ፡፡ እኔም ስቄ ሳበቃ በአሰፋ ጫቦ ናፍቆት ለሚብሰለሰሉ ወዳጆቻችን “አንድ የምንፈልገው ሰው ተገኘ” በማለት እንደምለፍፍ ነገርኩት፡፡ እነሆ ውሳኔዬን ተግባራዊ አደረግኩት፡፡