Sunday, 23 April 2017 00:00

የገርማሞ ልጅ ተገርሞ ሊያስገርመን?

Written by  ደመቀ ከበደ – ማንኩሳ – ጎጃም

 የገርማሞ ልጅ ተገርሞ ሊያስገርመን?

 የፀበል ዳር እንኮይ ወንዝ ያወዛት ቅጠል
ተሸፍና ዋርካ ከልሏት የዛፍ ጠል….
የት ነበር ያረኩት ቀፎየን ስል ኖሬ
ንብ ተከትዬ ባይ ጎጃም ኖራ ማሬ
ፍካሬና እማሬ ለግጥም ሁነኛ ተቀብኦዎች ናቸው ይላል፤ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲው የቋንቋ መምህር ፕሮፌሰር ተሾመ ይመር፡፡ ሀሳብህን ስትፈክረው እማሬውን (ኑባሬውን) አታሳጣው መሆኑ ነው፡፡ ቴዲ ፈክሯልም፤ አዕምሯልም፡፡ እንኳን መሃል ሸገር ላደገው እሱ ቀርቶ፣ ከእኔ ጋር ጥጃ ለጠበቀ የጎጃም (በጥቅሉ የክፍለ ሀገር) ሳተናም፣ እንኮይ የሚበላ የዱር ፍሬ መሆኑን ከዘነጋነውና የአማርኛ ቃል ስለመሆኑ መጠራጠር ከጀመርን ቆየትየት ብለናል፡፡
‹‹እንኮይ እንኮይ እንኮይ
የኔ ፉርኖ ዳቦ ልግመጥሽ ወይ››
የሚል ቆየት ያለ ተወዳጅ ዜማ በኢትዮጵያ ሬዲዮ አዳምጥ ነበር፡፡ በልጅነቴ ምንም የገጠር ከተማ (ሞጣ ቀራኒዮ ባድግም) የትምህርት መዘጋትን ተከትሎ ሰኔ ግም ሲል፣ ሀምሌ ከነደናው አገሩን ሲወረው ከወንዝ ሙላት ታግለን እንጨት (ጭራሮ ለቀማ) ገጠር ወዳ ጫካ ስንሰማራ ትዝ ይለኛል፡፡ በተለይ ሶታነት ሲሰማን በነበረ ጊዜ (በከተምቾው በፈነዳን ጊዜ) የብብታችንን ፀጉር፣ የጉልበታችንን ስር ጭገርና የፂማችንንና ሸንጎበታችንን (የከንፈር የላይኛው ፀጉር) የበለጠ ለማጥቆርና ‹ደርሰናል› ለማለት፣ በምላጭ ለመፈግፈግ እንዲመቸን እንጨት ለቀማ መሄድ የምንናፍቀው ጉዳይ ነበር፡፡
በሁለት ምክንያት የበለጠ እወደው ነበር፤ አንድ-ማንም ሳያይ የጉርምስና ውጤቶቼን ለማየት (የአካላቴን ለውጥ)፣
ሁለት – የዱር ፍሬዎችን ለመብላት፡፡ ሾላ፣ ዶቅማ፣ ዋንዛ፣ እሼ፣ …. እና እንኮይ!! እንኮይ ቢጫ ቀለም ያለው፣ የቄብ ዶሮ እንቁላል የምታክል፣ ኮምጠጥ የምትል ግን ኮምጣጤነቷ ጣፋጭነቷን የማያግድባት እንደ ሎሚ ያልጠነከረ ገላ ያላት፣ ልስላሴዋ እንቁላል የሚመስል ግን ፍፁም ክብ የሆነች ፍሬ ነች፡፡
እንኮይ በገጠሩ ዘመዶቼና ለእንደኔ አይነቱ ገጠሬነት ናፋቂ ለጎረምሳው የፍቅር ስጦታ፣ ለጎልማሳው የሶታነቱ ትዝታ ናት፡፡
በእንጨት (ጭራሮ) ለቀማ ጊዜ ጎረምሳና ኮረዳ አንድ ላይ ቢሄዱ ነውር የለበትም፤ አንድ ላይ ቢለቅሙም እንደዚያው፡፡ የተፈቀደ የፍቅር መጀማመሪያ ሁነት ነው የሚመስለን፡፡ ከየዛፉ ቆርጠን፣ በአኮፋዳችንና በየኪሳችን ጠርቀን ካጠራቀምን በኋላ ለየከጀልናት ደበቅ እያደረግን እንሰጣለን፡፡ በጄ ካለችና ልቧ ከከጀለ ትቀበላለች፤ ካልሆነም አትቀበልም፡፡ እንኮይ ግን እንደ ዶቅማ ቶሎ አይገኝም፡፡ በእርግጥ ከአካባቢ አካባቢ ካልተለያየ በቀር እኛ ዘንድ ውድ ነበር፡፡ ውድነቱን እንወደው ነበር፤ ለፍተን ደክመን ስናገኘው ለወደድናት የምንሰጠው ውድ ነገር ነበርና፡፡
አሁን የገርማሞ ልጅ፡-
‹‹የፀበል ዳር እንኮይ ወንዝ ያወዛት ቅጠል
ተሸፍና ዋርካ ከልሏት የዛፍ ጠል›› በሚለው ስንኙ፤
‹‹የፀበል ዳር እንኮይ…›› ሲል በ”ፍቅር እስከ መቃብር” ውስጥ በዛብህ ለሰብለወንጌል ፍቅር ውዴታውን ከእንኮይ ጋር ማዛመዱ በፍካሬም በእማሬም ሰምሮለታል፤
‹‹ወንዝ ያወዛት ቅጠል›› ሲላት ደግሞ ያች የፊታውራሪን ወተትና ቅቤ እየጠጣች ያደገች ኮረዳ፤ ትምቡኬ ገላዋና ጉንጯ በዓይነ ህሊናችን እንድትመጣ ‹‹ምስለ ክሰታውን›› ሰማይ አድርሶታል፤ በዚያም ላይ ዓባይ ጎጃምን እንደ መቀነት ዞሯታልና ወዲያውም በገጠር ቀዬዎች ዓባይ ዓባይነቱን (ላልቶ) ብቻ ሳይሆን ፀበልነቱን የሚቀበሉትም ባላገሮች አሉና ባህላዊ እሴቱን (ፎክሎሩን) አጢኖታል ያስብለዋል፤
‹‹ተሸፍና ዋርካ…›› ብሎም ያሳምረዋል፡፡ በፊውዳሉ የእነ ፊታውራሪ ዘመን ‹‹ክብር›› እንደ መርግ ለሚጫናቸው መሸሻ፤ ሰብለ ከእልፍኝ የማትወጣ ብትሆን ቁብ አይባልም፡፡ በዛብህ መሸሻንና መሸሻነታቸውን ከዋርካ ቢገዝፈው፣ ዘመኑን ከመርግ ቢከብደው፣ ፍቅር ባፈዳው ኮስማና ገላውና ጢቢኛ ልቡ የሚቻለው አይደለም፤ እንደ ዋርካ ትልቅ ዛፍ የለም፡፡ እንደ ዋርካ ረጅም ዕድሜ የሚቆይም እንዲያው፡፡ በዚያ ላይ የጊዜው ባለጊዜ ነበሩ ፊታውራሪ፡፡
‹‹ተሸፍና ዋርካ…›› ይለንና ‹‹ከልሏት የዛፍ ጠል›› ን ሲደግመው ይህ ደግሞ ልቀቱን ያረቀዋል፡፡ ትልቁ ዋርካ በስሩ ያሉትን ዛፎች ሁሉ ደቃቃ ያደርጋቸዋል። ዋርካ ግንዱ ብቻ ሳይሆን ቅርጫፉም ሰፊ ነው፡፡ ስለዚህ እንኳን በዝናብ ጊዜ በፀሀይ ወቅትም ጥላው ይቀዘቅዛል፤ ሲዘንብ ከየቅጠሎቹ የሚረግፈው ጠፈጠፍ (ጠል) እንደ ጤዛ ቶሎ አይረግፍም፤ ጥላውም ጠሉም ቀስ ያለ ነው የዋርካ፡፡ ስለሆነም የዋርካ ስር ተክሎች ሁሉ ቢያድጉም አይጎመሩም፡፡
ሰብለም ለበዛብህ እንዲያ ማለት ናት፡፡ የዋርካው ጠል የስሩን ተክሎች እንደማያስጎነቁላቸው፣ ቢያጎነቁሉም እንደማያስጎመራቸው ሁሉ ሰብለም የ‹‹ዋርካው ቤተሰቧ›› ጠል ተጭኗት ያልጎመራች ነበረች፡፡ የዋርካው ስር ተክሎች ወዲያ በቅርጫፉ፣ ወዲህ በግንዱና በስሩ እንደተቀፈደዱት ሁሉ ሰብለም በፊታውራሪ የታሰረች ‹‹የለመለመች ግን ያልጎመራች ቅጠል›› ነበረች፡፡
የገርማሞ ልጅ ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› ሞዝቆታል፤ ተቀኝቶታል፣ ፈክሮታል፣ አዕምሮታልም።
‹‹የት ነበር ያረኩት ቀፎየን ስል ኖሬ
ንብ ተከትዬ ባይ ጎጃም ኖራ ማሬ››
ይህ ስንኝ ደግሞ አንድምታው ሸጋ ነው፡፡
ቀፎ እንደ ዛሬው ዘምኖ ደጅ ሳይሰጣ፣ በጭራሮና በቀርከሃ ሳጠራ እየሰራ ዛፍ ላይ ነበር የሚሰቀል፡፡ ጎጃም የቀይ ማር አዘማሪ፣ አምራችና ጠጃም ነው፡፡ ጠላ እንኳን ተጠምቆ ውብ ሲሆን ‹‹ጠጅ ያስንቃል›› ነው እሚል፡፡
ለጎጃሜ ጤፍ እንጀራው እህሉ ሲሆን ማር ወጡ ነው፤ የዛሬን አያድርገውና፡፡
ባላገር በሞላ በጋውን ያሽሞነሞነውን ቀፎ፣ የበልጉን መብለግለግ፣ የክረምቱን መስገምገም ያይና ከዛፎቹ መሀል ይሰቅለዋል፤ አንዱን ሳይሆን እልፉን፡፡ የቀፎው ብዛት የዛፉን ቅርንጫፍ ያህል ቢሆን ነው፤ ዋርካ፣ ግራር፣ ዝግባና ብሳና የመሳሰሉ  ቅርንጫፈ ብዙ ዛፎች ከሆኑ ባላገር ታድሏል፤ ብዙ ቀፎ ይሰቅላል፡፡
አደይ አበባይቱን ዘፍኖላት፣ መስከረሚቱን አዚሞላት፣ ጥቅምቲቱ ደረስኩ ስትለው ያገሬ ባላገር ‹‹የጥቅምት ማር›› ቆረጣ ይጀምራል፡፡ እየፎከረ እንደሚያጭደው ማኛ ጤፉ፣ እየዘፈነ ጭስ እያጠነ ማሩን ይቆርጣል፡፡
ብዛቱ ‹‹ቀፎዬ የት ነው›› ሊያስብለው ይችላልና፣ በሰበቡ ከጎረቤቱ ጋር ሊጣላና በክትክታና ወይራ ሽመል ሊናከት ይችላል፡፡
ማር ለጎጃሜ ጥፍጥናው፣ ውዴታውን መግለጫው ነው፡፡ የወደደውን ‹‹ማር፣ ማርዬ፣ ማርዋ›› ይላል፡፡ ጥር ላይ ልጁን እንኳን ሲድር ‹‹ማሬ›› ብሎ ካልዘፈነ ይነሆልላል፡፡ የእምቦቃቅላ ልጁን የከንፈር ጠብታ (ለሀጭ) እንኳን ‹ማር› ጠብ ይለዋል ነው እሚል፡፡
ወዲህ በምስራቁ ጎጃም በደጀን፣ እነማይ፣ ደብረወርቅ፣ ደብረማርቆስ፣ ጎዛምን፣ ሁለት እጁ እነሴ (ሞጣ ቀራኒዮ) እና መርጡ ለማሪያም እስከ ባሶሊበን ባለው ቀዬ ‹‹ማሬ›› ብሎ ዘፍኖ ባሶ ምት መምታት (እስክስታ) የባህሉ አንዱ አካል ነው፡፡
ወዲያም በምዕራቡ አዴት፣ ባህርዳር፣ ቡሬ፣ ፍኖተሰላም፣ ጅጋም አልባሶ መደንከር ወግ ነው፤ ሁሉም ግን ማሬ ቢል ማር ከቀፎው ቆርጦ ነው፡፡
ማሪቱ ሰብለወንጌልም ከቀፎዋ ወጥታ የት ሄደች ብሎ በዛብህ ዓባይን ተሻግሮ ሲፈልጋት ልቡን ይዛ እዚያ ነበረች – ጎጃም፡፡
በጎጃሜ ንግግር ‹‹የት ኑረህ ነው?›› ካለህ ስፈልግህ ቆየህ፣ የት ነበርክ እያለህ ነው ማለት ነው፡፡
ጎጃም ሲናገር ‹‹እዚህ ኑራ!!›› ካለ ‹‹ለካ እዚህ ነበረችና›› እያለ ነው ማለት ነው፤
እናም የገርማሞ ልጅ
….የት ነበር ያረኩት ቀፎየን ስል ኖሬ
ንብ ተከትዬ ባይ ጎጃም ኖራ ማሬ….
ሰብለ የት ነች ስል በከበቧት ጀሌዎች ‹‹ንቦች›› የት እንዳለች አወቅሁ እያለህ ነው፡፡
‹‹ለካ ሰብለ ውዴ፣ ጎጃም ነበረች ለካ›› ማለቱ ነው፤ እንጂማ ‹‹ማሬ ማሬ››ን ትዝ ሊያሰኝህም አይደል፤ እረ እሱ እቴ ጎጃሜ ኖሯል – ሸገር መስሎ!!
ለማንቻውም ወረታው ውበትም፣ ቻላቸው አሸናፊም ‹‹ማሬ፣ ማርዘነቤ፣ ማርዋ›› ሲሉ እሷን (ፍቅረኛቸውን) እየፈከሩ ማሩን እያዕመሩ ነው፡፡
ቀፎው የገርማሞ ልጅ ልብ በማሪቱ ሰብለ ሲነሆልል፣ ንቦቹ ከበዋት እነ ፊታውራሪ ስር ነበረች፡፡
ኧሯ!!! ጎጃም ኖራ ማሩ!!!
ይህንን ጉድማ አሁን አናበቃውም።
እያረፍን እያንዳንዱን ስንኝ እንዘልቃለን፣ በገባን ልክ እንሰልቀዋለን!
ወይ መታደልህ እያልን!!