Monday, 24 April 2017 00:00

Written by  አለማየሁ አንበሴ

  • በኦሮሚያ 108 ሰዎች የተገደሉት ባልተመጣጠነ እርምጃ በመሆኑ ፍትህ ያሻቸዋል ተብሏል
• ያልተመጣጠነ እርምጃ የወሰዱ የፀጥታ አካላት ለህግ እንዲቀርቡ ተጠይቋል
• ኦነግ፣ ኦፌኮ፣ ኦኤምኤን፣ ኢሳት፣ ሰማያዊና ቤተ-አማራ አባባሾች ናቸው – ኮሚሽኑ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በኦሮሚያ፣ በአማራና በደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞን የነበሩ ተቃውሞና ግጭቶችን አስመልክቶ ያደረገውን የምርመራ ሪፖርት ሰሞኑን ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አቅርቧል፡፡
በኦሮሚያ ተቃውሞና ግጭቱ በተከሰተባቸው ፊኒፊኔ ዙሪያ፣ ምስራቅ ሸዋ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ምዕራብ ሸዋ፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ ምስራቅ ሀረርጌ፣ ምዕራብ ሀረርጌ፣ ምስራቅ ወለጋ፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ፣ ጉጂ፣ ምዕራብ ጉጂ፣ ባሌ፣ ምዕራብ አርሲና ምስራቅ አርሲ በጠቅላላው በ15 ዞኖችና 91 ወረዳዎች እንዲሁም ከተማዎች ኮሚሽኑ ምርመራ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር፣ በደቡብ ጎንደር፣ በባህር ዳር፣ በምዕራብ ጎጃም፣ ምስራቅ ጎጃምና አዊ ዞን በጠቅላላው በ6 ዞኖችና 55 ወረዳዎች እንዲሁም ከተማዎች ኮሚሽኑ ማጣራት አድርጓል፡፡ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ክልል፣ ጌዴኦ ዞን በ6 ወረዳዎችና ከተማዎች የነበረው ግጭት ከሰብአዊ መብት አያያዝና አጠባበቅ አንፃር ምርመራ ተደርጓል ብሏል – ኮሚሽኑ፡፡
በ175 ገጾች ተሰናድቶ ከቀረበው የኮሚሽኑ ሪፖርት ተጨምቆ የተዘጋጀው አጠቃላይ የሪፖርቱ ፍሬ ሀሳብና ግኝት እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡
ምርመራው እንዴት ተከናወነ?
በተጠቀሱት አካባቢዎች ከሰኔ 2008 ዓ.ም እስከ መስከረም መጨረሻ 2009 ዓ.ም ተፈጥረው የነበሩ ግጭትና ተቃውሞዎችን ተከትሎ፣ የሰብአዊ መብት መጣሱን ለማረጋገጥ ምርመራው ተደርጓል። የምርመራና የመረጃ አሰባሰብ ዘዴዎቹም 1ኛ፡- ምርመራው በተካሄደባቸው አካባቢዎች ካሉ የመንግስት ተወካዮች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት ተወካዮች፣ የተጎጂ ቤተሰቦች፣ በአካባቢው ካሉ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ጋር ስለተፈጠረው ግጭት፣ ስለ ግጭቱ መንስኤ፣ ስለደረሰው ጉዳትና ሌሎች ጉዳዮች ላይ የተደረገ ቃለ ምልልስና የቡድን ውይይት በመጀመሪያ ደረጃ መረጃነት ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡ 2ኛ፡- ችግሩ በተከሰተባቸው ቦታዎች የምርመራ ቡድኑ በአካል በመገኘት የሰበሰባቸው  የቪዲዮና የፎቶ ምስሎች፣ በምልከታ የተገኙ መረጃዎች፣ የህክምና ማስረጃዎችና ሰነዶች በሁለተኛ ደረጃ መረጃነት ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡
ኦሮሚያን በተመለከተ
ኮሚሽኑ  ኦሮሚያን በተመለከተ እንደየአካባቢዎቹ ሁኔታ በሁለት ከፍሎ ሪፖርቱን አቅርቧል፡፡ በመጀመሪያ ያቀረበው ሐምሌ 30 የተላለፈን የአመፅ ጥሪ ተከትሎ፣ በምስራቅ ሸዋ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ምስራቅ አርሲ፣ ባሌ፣ ምዕራብ ጉጂና ፊኒፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የተመለከተውን ሪፖርት ነው፡፡ በነዚህ ዞኖች ለተፈጠረው ግጭት የመልካም አስተዳደር ችግርና የስራ አጥነት በዋና መንስኤነት ተጠቅሰዋል፡፡
በምስራቅ ሸዋ ዞን ቦሰት ወረዳ፣ የወለንጪቲ ገጠር ቀበሌዎች እንዲሁም በፊኒፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ቡራዩ ከተማ ከህዳር 2008 ዓ.ም እስከ ታህሣሥ 2008 ዓ.ም ድረስ ግርግር አልተለያቸውም ነበር ተብሏል፡፡ ሁከቱን ወደ አዲስ አበባ ከተማ ማስፋፋት በሚል ሀሳብ፣ በቡራዩ ከተማ ተደጋጋሚ ተቃውሞ መደረጉ ተጠቅሷል፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አባላትና ደጋፊ ወጣቶች ተሳትፎአቸው የጎላ ነው ተብሏል፡፡ ወጣቶቹ፤ “ኦሮሞ መሬት አይሸጥም፣ መረራ መሬት አይሸጥም” የሚሉ መፈክሮችን ማሰማታቸውን ሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡
በቡራዩ ከተማ ህዳር 8 ቀን 2008 ዓ.ም የኦፌኮ አባላትና ደጋፊዎች፣ የዶ/ር መረራን ፎቶግራፍ የያዘ ኮፊያ በማድረግ፣ “ኦሮሚያ የኔ ናት” የሚል መፈክር አንግበው የመረበሽ ሙከራ አድርገዋል ይላል – ሪፖርቱ፡፡ ከህዳር 16-23 ቀን 2008 ዓ.ም በቡራዩ መሰናዶ ት/ቤት “የባርነት እምቢታ ትግል!” የሚል ፅሁፍ መበተኑን፤ ይህን ተከትሎም የት/ ቤቶች መስኮቶች መሰባበራቸውን፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ መቀዳደዱን ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡ የአንበሳ አውቶቡስም ተቃጥሏል ተብሏል፡፡
ሁኔታዎች በዚህ መልኩ ከቀጠሉ በኋላ በመላ ኦሮሚያ ሐምሌ 30 አመፅ እንዲካሄድ በተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገፆች እና በኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (OMN) መተላለፉን፣ በጥሪው መሰረትም ከቦሶት ወረዳ 33 ቀበሌዎች የተሰባሰቡ ወጣቶች፣ ከጅቡቲ ወደ አዲስ አበባ በሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ላይ መንገድ በመዝጋት፣ ድንጋይ በመወርወር፣ የኦነግን አርማ በማውለብለብ፣ የፖሊስ ፅ/ቤቶችን በመሰባበር ለአመፁ ጥሪ ምላሽ መስጠታቸውን የኮሚሽኑ ሪፖርት ይጠቁማል፡፡ ነገር ግን ሁኔታው ሳይባባስ፣ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት ሳይደርስ ችግሩ እንዲቆም ተደርጓል፤ ብሏል፡፡
በተመሳሳይ በቡራዩ ከተማ ለአመፁ ጥሪ ምላሽ በመስጠት፣ ወጣቶች ወደ አዲስ አበባ ከተማ ለመግባት ሙከራ ማድረጋቸውንና የፀጥታ ኃይሉ፣ የሰው ህይወትና አካል ላይ ጉዳት ሳይደርስ መቆጣጠር መቻሉ ተጠቅሷል፡፡ በአጠቃላይ ሐምሌ 30 በነበረው የአመፅ ጥሪ በሰሜን ሸዋ፣ ምስራቅ ሸዋ፣ ምስራቅ አርሲ፣ ባሌ፣ ምዕራብ ጉጂና ፊኒፊኔ ዙሪያ ለሰው ህይወት ማለፍ ምክንያት የሆነ ችግር አለመፈጠሩን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡ በአንፃሩ ምዕራብ ሸዋ፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ ምዕራብ አርሲ፣ ምስራቅ ሀረርጌ፣ ምዕራብ ሀረርጌ፣ ምስራቅ ወለጋ፣ ምዕራብ ወለጋና ቄለም ወለጋ ሐምሌ 30 ቀን 2008 ዓ.ም በተጠራው ሰልፍ፣ ግጭት ተፈጥሮ በሰው ህይወትና አካል ላይ ጉዳት ደርሷል። በወቅቱ ለተቃውሞ ጥሪ ምላሽ ሳይሰጡ በተረጋጋ ሁኔታ የቀጠሉ የኦሮሚያ አካባቢዎች፡- ሰሜን ሸዋ ኢሉአባቦራ፣ ጅማና አሰላ ከተማ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በኢሬቻ በአል የተከሰተው ሁኔታ
ኮሚሽኑ በበአሉ ላይ ለ56 ዜጎች ህልፈት ምክንያት ሆኗል ባለውና ከዚያ ቀጥሎ በተፈጠሩ ተቃውሞዎች ዙሪያ አተኩሮ ማጣራት ማድረጉን አስታውቋል፡፡
የኢሬቻን በአል በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ነበር የታቀደው፡፡ ለዚህም የፀጥታ ኃይሉ፣ የኦሮሚያ ክልልና የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ሰፊ ዝግጅት አድርገው ነበር፡፡ ለዚህ ሲባል የኢህአዴግ አርማ ያለባቸው ቢልቦርዶች፣ ፖስተሮች፣ ኮፊያዎች፣ ቲ-ሸርቶችና ሌሎች የመልዕክት ማስተላለፊያ ቁሳቁሶችን ላለመጠቀም ተወስኗል – በወቅቱ። በተመሳሳይ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች መድረኩን ለፖለቲካ አላማ እንዳይጠቀሙበት ማሳሰቢያ ቢሰጥም፣ OMN የቅስቀሳ መልዕክት ማስተላለፉን፣ ኦነግ በበኩሉ በአሉን ለአመፅ ማቀጣጠያነት ለመጠቀም እየሰራ እንደነበር የምርመራ ግኝቴ አመላክቷል ብሏል – ኮሚሽኑ፡፡
በድምሩ ከመላዋ ኦሮሚያ 2.5 ሚሊዮን ሰዎች በበአሉ ላይ ታድመው ነበር፡፡ በበአሉ ዋዜማ አብዛኛው የበአሉ ታዳሚ ወደ ከተማዋ ገብቷል። በዋዜማው ወጣቶች ተቃውሞ ማሰማት ጀመሩ ይላል – ኮሚሽኑ፡፡ በመቀጠልም ከሌሊቱ 8 ሰዓት እስከ 10 ሰዓት ከተለያዩ ዞኖች በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች በአይሱዙ ተሽከርካሪዎች ተጭነው፣ መንግስትን የሚያወግዝ መፈክር እያሠሙ ወደ ቢሸፍቱ ከተማ ገብተው፣ በአሉ ወደሚከበርበት ሆራ ሃይቅ ማምራታቸውን ይጠቁማል፡፡ ታዳሚዎች ወደ በአሉ ቦታ መግባት የጀመሩት ከሌሊቱ 8 ሰዓት ነበር፡፡ ከንጋቱ 2 ሰዓት ሲሆን 2.5 ሚሊዮን ሰዎች ተጨናንቀው በበአሉ ቦታ ተገኝተዋል፡፡ ከ2፡30 እስከ 3 ሰዓት የኢፌዲሪ አየር ሃይል፣ እንኳን ደህና መጣችሁ የሚል የመልካም ምኞት መግለጫ ወረቀት በተነ፡፡ ፕሮግራሙን አባ ገዳዎች ሊያስጀምሩ ሲሉ፣ ከ200 እስከ 300 የሚሆኑ ወጣቶች በአሉን ማወክ ጀመሩ ይላል – ኮሚሽኑ፡፡ የአባ ገዳዎች ህብረት ሰብሳቢ አባገዳ በየነ ሰንበቶ፣ በሰአቱ ባለመድረሳቸው፣ የቀድሞ አባገዳ ነገሠ ገነኦ ከሌሎች አባገዳዎች ጋር በመሆን ‹‹ሁከቱን›› ለማስቆም በድምፅ ማጉያ መናገር ሲጀምሩ፣ አንድ ወጣት የድምጽ ማጉያውን ከአባ ገዳው ቀምቶ፣ መንግስትን የሚያወግዝና አመፅን የሚገልፅ መልዕክት ማሠማት ጀመረ – እንደ ኮሚሽኑ ሪፖርት፡፡
አባገዳዎች ከወጣቱ የድምፅ ማጉያው ቀምተው ማረጋጋታቸውን ቀጠሉ፡፡ ወጣቶቹ የኦነግን አርማ በማውለብለብና እጅ በማጣመር ተቃውሞ ማሳየት ጀመሩ፡፡ መንግስት የሚቃወሙ የእምቢታ ድምፆችና ጩኸቶች ጎልተው ተሠሙ፤ የፀጥታ ሃይሎች ሁኔታውን ለማረጋጋት ጥረት ማድረግ ጀመሩ። ወጣቶቹ ከፀጥታ ሃይሎቹ ጋር ግብግብ ፈጠሩ፡፡ በዚህ መሃል ከጠዋቱ 4፡30 ላይ ከፀጥታ ሃይሎች 3 አስለቃሽ ጪስ ተተኮሰ፡፡ ተሣታፊዎች ህይወታቸውን ለማትረፍ መሯሯጥና መገፋፋት ጀመሩ፡፡ በዚህ ክስተት በአካባቢው በነበረው ገደል በመግባትና በመረጋገጥ 56 ሰዎች ህይወታቸው ጠፍቷል ይላል – ሪፖርቱ፡፡ ይሄን ተከትሎም ተቃውሞና ግጭቱ እንደገና አገረሸ ብሏል፡፡
የኮሚሽኑ የኦሮሚያ ግኝቶች
በክልሉ ለተፈጠረው ችግር መሠረታዊ መነሻ የሐምሌ 30 ቀን 2008 ዓ.ም የአመፅ ጥሪና የመስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም የኢሬቻ በአል እንደሆነ ኮሚሽኑ ይገልፃል፡፡ በኦሮሚያ ክልል በድጋሚ ላገረሸው ችግር መንስኤው የመልካም አስተዳደር ችግርና የመብት ጥሠት ነው ብሏል- ኮሚሽኑ፡፡ ለዚህ ችግር መፍትሄ በጊዜ አለመበጀቱ ችግሩ መቋጫ እንዳይኖረው አድርጓል ብሏል፡፡ ወጣቱ የስራ እድል ማጣቱ፣ የስራ ቅጥሮች በዘመድ አዝማድ መሆናቸውና ቃል የተገቡ ፕሮጀክቶች በጊዜው አለመጠናቀቅ የመሣሠሉት ለቅሬታ መንስኤ እንደሆኑ እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ የሚያገኘው ልዩ ጥቅም ተግባራዊ አለመደረጉ ስር የሰደደ ቅራኔ ፈጥሯል ያለው ሪፖርቱ፤ የብሔረሰብ፣ ሃይማኖታዊና የጎሣ አድሎአዊነት የነበራቸው አስተዳደሮችም ለችግሩ መንስኤ ናቸው ብሏል፡፡
ሁኔታውን ያባባሱት ደግሞ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ኦነግ፣ በሠላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሰው የዶ/ር መረራ ኦፌኮ እና የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ (OMN) እንዲሁም ማህበራዊ ድረ-ገፆች ናቸው ብሏል – ኮሚሽኑ፡፡
በኢሬቻ በአል ወቅት ችግሩ እንደተፈጠረ መንግስት በሄሊኮፕተር ጥቃት እንደፈፀመና ከ600 በላይ ሰዎች የመገደላቸው መረጃ በፍጥነት መሰራጨቱ፣ ከዚያ በኋላ ለተፈጠሩት ችግሮች አባባሽ ሁኔታ ነበር ተብሏል፡፡ ኮሚሽኑ ከአቢሲ በተቀረጸ ምስል፣ ከተተኮሰው አስለቃሽ ጭስ ውጪ ሌላ የተተኮሰ የጦር መሣሪያ እንደሌለ ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡ ኦነግና ሌሎች ድርጅቶች አመፁን እንደሚመሩትና ኢትዮጵያን ለመበተን እንደሚሠሩ የምርመራ ግኝቶቼ አመላክተውኛል ሲልም ጠቁሟል – ሪፖርቱ፡፡
የተወሰደውን የሃይል እርምጃ በተመለከተ
የሐምሌ እና ነሐሴ 30 የተቃውሞ ጥሪንና የኢሬቻ በአልን ተከትሎ በፊኒፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን፣ በምዕራብ አርሲ፣ በባሌ፣ በምዕራብ ጉጂ፣ በምዕራብ ሸዋና ምስራቅ ሸዋ፣ ጉጂ የተካሄዱ ብጥብጦች በገጀራ፣ በስለት፣ በጦር መሳሪያ፣ በቤንዚንና ማቀጣጠያዎች ታጅቦ በኢንቨስትመንቶች ላይ ያነጣጠረ ነበር ብሏል – የኮሚሽኑ ሪፖርት፡፡
ይኼን ተከትሎም የፀጥታ ሃይሎች በወሰዱት እርምጃ በመቂ፣ በአለም ጤና፣ በሠበታ፣  በቡራዩ፣ በወልመራ፣ በአቃቂ በሲቪሎች ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ፣ ነገር ግን ፖሊሶች መሞታቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡ በተለይ በቦሶት፣ በሊበን ጩቋላ ሁለት ቀናት የፈጀ ውጊያ መደረጉን ሪፖርቱ አመልክቷል። በሌሎች አካባቢዎችም የታጠቁ ሃይሎች ጉዳት አድርሰዋል ብሏል፡፡ ሁከትና ብጥብጡ በጦር መሳሪያ የታገዘ ስለሆነ በነዚህ አካባቢዎች የተወሰደው እርምጃ ተመጣጣኝ ነበር፤ የፀጥታ ሃይሎች ከሃይል እርምጃ ውጪ ምንም አማራጭ አልነበራቸውም ብሏል – ሪፖርቱ፡፡ በሊበን ጩቋላ ወረዳ፣ 5 የአንድ ቤተሠብ አባላት ላይ የተፈፀመው ግድያ ማወዛገቡን የጠቀሰው ሪፖርቱ፤ በቀጣይ ሊጣራ የሚገባው ጉዳይ መሆኑን አመልክቷል፡፡ በአብዛኞቹ አካባቢዎች የሙሉ ቀን ውጊያ የተደረገባቸው በመሆኑም የፀጥታ ሃይሉ የወሰደው እርምጃ ተመጣጣኝ ነው ብሏል – ኮሚሽኑ።
በአዳሚ ቱሉና ሎሜ ወረዳ ድልድይ በመዝጋት ላይ ባሉ ሁለት ወጣቶች ላይ የተወሰደው እርምጃ ተመጣጣኝ አለመሆኑንና በአዳሚ ቱሉ (ዝዋይ) ማረሚያ ቤት ለማምለጥ የሞከሩ 14 ታራሚዎች መገደላቸውም ህግን የተከተለ፣ተመጣጣኝና አስፈላጊ አልነበረም ብሏል – ሪፖርቱ፡፡
በባሌ ዞን የተደረጉ ሰልፎች በጦር መሳሪያ ያልታገዙ መሆናቸውን በመጠቆምም፣ የተወሠዱት እርምጃዎች ተመጣጣኝ አልነበሩም ብሏል፡፡ ተመጣጣኝ ባልሆኑት እርምጃዎች በሮቤ ከተማ የ2 ሰዎች ህይወት ጠፍቷል፤ 2 ተጎድተዋል፣ በራይቱ ወረዳ 8 ሰዎች ላይ ባልተመጣጠነ ጥቃት የአካል ጉዳት ሲደርስ፣ 6ቱ ሴት ህፃናት ናቸው ብሏል፡፡ በምስራቅና በምዕራብ ሃረርጌ በተወሠዱ እርምጃዎች፣ በሃሮማይ ወረዳ የ28 ሰዎች ህይወት የጠፋበት እርምጃ ህግን የተከተለና ተመጣጣኝ አልነበረም፡፡ ሰልፎቹም በትጥቅ ያልተደገፉ፣ አደጋ ያልደቀኑ ነበሩ ብሏል – ኮሚሽኑ፡፡ በጭሮ ወረዳ በ73 ሠዎች ላይ የተፈፀመ ድብደባ የመብት ጥሠት ነው ብሏል፡፡ በምእራብ አርሲ ደዶላ 3 ወጣቶች፣ በነቀምቴ 12 ሰዎች፣ በጊምቢ 1 ሰው መገደላቸው ህግን ያልተከተሉ፣ተመጣጣኝ ያልሆኑ ናቸው፤ የህግ ተጠያቂነትም ማስከተል አለባቸው ብሏል – ኮሚሽኑ በሪፖርቱ፡፡
በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት
ንብረቶች ከጥቃት ለመከላከል በቂ ጥረት አለመደረጉን ይጠቁማል – ሪፖርቱ፡፡ በሠበታ 12 ፋብሪካዎችና የእርሻ ልማት ላይ ጉዳት ሲደርስና የብሄር ጥቃት ሲፈጸም በከተማዋ 256 ፖሊሶች የነበሩ ቢሆንም ጥቃቱን ለመከላከል ጥረት አላደረጉም ብሏል – ኮሚሽኑ፡፡ በአማራ፣ በትግራይ፣ በወላይታና ሌሎች ብሄር ተወላጆች ላይ በግጭቱ ጥቃት ደርሷል ያለው ሪፖርቱ፤ የኦሮሞ ህዝብ ግን ጥቃቱን ለመከላከል ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፣ ለዚህም ሊመሰገን ይገባዋል ብሏል፡፡ የሃይማኖት ጥቃትም መፈፀሙን ሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡ በክልሉ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ መስፋፋት ለችግሩ መባባስና ለሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት ሆኗል ተብሏል። በግጭቶቹም ሴቶችና ህፃናት ይበልጥ ተጎጂ ነበሩ ተብሏል፡፡ የሉና እርሻ ልማት ሲቃጠል፣ 10 ሴቶች መደፈራቸውንና ደፋሪዎቹ ድርጊቱን መፈፀማቸውን ቢያምኑም ተደፈርኩ ያለች ሴት አለመገኘቷን ያመለከተው ሪፖርቱ፤ በዚህም የተነሳ ፖሊሶች ጉዳዩን ወደ ፍ/ቤት ለመውሰድ መቸገራቸውን ጠቁሟል፡፡
ችግሩን አስቀድሞ ለመከላከል
የተደረገ ጥረት
በተጠቀሱት ዞኖች ተቃውሞና ግጭቱ ሊያጋጥም እንደሚችል የመንግሥት አካላትና የፀጥታ ኃይሎች እያወቁ፣ ጉዳቱን አስቀድሞ ለመቀነስ ጥረት አላደረጉም ብሏል – ኮሚሽኑ፡፡
በኢሬቻ በአል ግልፅ አደጋ መደቀኑ እየታወቀ፣ በአሉ እንዲካሄድ መደረጉ ህዝባዊ ኃላፊነት የጎደለው መሆኑን የጠቆመው የኮሚሽኑ ሪፖርት፤ በጉዳዩ ባለስልጣናት በህግ ሊጠየቁ ይገባል ብሏል። በበአሉ ማክበሪያ ቦታ የነበረው ገደል ሊደፈን ይገባ ነበር ያለው ኮሚሽኑ፤ ለዚህም የበአሉ አዘጋጅ ኮሚቴ አባላት በህግ ሊጠየቁ ይገባል ብሏል፡፡ በሌላ በኩል የፀጥታ ኃይሎች በበአሉ እለት ትዕግስት ማሳየታቸውን ኮሚሽኑ አድንቋል፡፡
በአጠቃላይ ከሐምሌ 2008 እስከ መስከረም 2009 ዓ.ም ድረስ የ462 ሲቪልና የ33 የፀጥታ ኃይሎች በምድሩ የ495 ሰዎች ህይወት አልፏል። 338 ሲቪልና 126 የፀጥታ ኃይሎች በድምሩ በ464 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሷል ያለው ኮሚሽኑ፤በመቶ ሚሊዮን ብር  የሚገመት ንብረት መውደሙንም ጠቁሟል፡፡
የኦነግ እና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አባላት “ሁከቱን” በማስተባበራቸው በህግ ሊጠየቁ ይገባል ያለው ኮሚሽኑ፤ 14 ታራሚዎችን የገደሉትና ትዕዛዝ ያስተላለፉትም ለፍርድ እንዲቀርቡ  ጠይቋል። ያልተመጣጠነ እርምጃ የወሰዱና ያዘዙ በህግ ይጠየቁም ብሏል፡፡ በጠቅላላው 108 ሰዎች የተገደሉት ባልተመጣጠነ እርምጃ በመሆኑ ፍትህ ያሻቸዋል ብሏል – ኮሚሽኑ፡፡
ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች በመንግስት ሊቋቋሙ እንደሚገባና ሪፖርቱ እስከቀረበበት ቀን ድረስ ተጎጂዎችን በድጋሚ የማቋቋም ስራ አለመጀመሩን  ኮሚሽኑ ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡
የጌዴኦ ዞን ግጭትን በተመለከተ
ግጭቱ በዲላ፣ ይርጋ ጨፌ፣ ወናጎ፣ ኮቸሬ ወረዳ ነበር ለ2 ቀናት የተከሰተው፡፡ በግጭቱ ነጋዴዎችና ወጣቶች ተሳታፊ ነበሩ፡፡ መንስኤው የመልካም አስተዳደር ችግሮች ናቸው ተብሏል፡፡ በዞኑ የተደረጉ ሰልፎች ህገ ወጥና በኃይል የታጀቡ ነበሩ፡፡ የግጭቱ መንስኤ በአንድ የገበያ ቦታ ባለቤትነት ላይ የተሰጠ የፍ/ቤት ውሳኔ ነው፡፡ ውሳኔውን የመንግስት አካላት ጭምር አልቀበልም ማለታቸው ተጠቅሷል። የፖሊስ አባላትን ጨምሮ አንዳንድ የመንግስት አካላት የጌዴኦ ብሔር ተወላጅ ባልሆኑት ላይ ባካሄዱት የዘር ላይ ቅስቀሳ ምክንያት ብጥብጡ መነሳቱን እንዲሁም የጌዴኦ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት የተባለም “ሌሎች ብሄረሰቦች ከጌዴኦ ይውጡልን” የሚል ዘመቻ ማካሄዱ በኮሚሽኑ የምርመራ ግኝት ላይ ተጠቁሟል።
በብጥብጡ ከሁሉም ብሄረሰቦች በድምሩ የ34 ሰዎች ህይወት ጠፍቷል፡፡ 32ቱ ሴቶች ናቸው። 178 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሷል፡፡ ከጌዴኦ ብሄር ውጪ የሆኑ 8 ሺህ 450 ዜጎች ተፈናቅለዋል። ይህም የመብት ጥሰት ነው ብሏል – ኮሚሽኑ፡፡ 497 የአማራ፣ 187 የስልጤ፣ 179 የኦሮሞ፣ 168 የጉራጌ እንዲሁም 62 ጥቃቱን የተቃወሙ የጌዴኦ ብሄር አባላት ተፈናቅለዋል፡፡ 21 የጋሞ፣ 9 የወላይታ፣ 7 የትግራይ፣ 5 የቡርጂ፣ 2 የሲዳማና 1 የአርጎባ ብሄር ተወላጆች ንብረት እንዲወድም ተደርጓል – በሪፖርቱ መሰረት፡፡ በመስጊድና በቤተ ክርስቲያን ላይ ቃጠሎ ተፈፅሟል። 15 ሟቾች ደግሞ ህፃናት ናቸው ተብሏል፡፡
የጌድኦ ዞን አስተዳደርና የጌዴኦ ዞን የፀጥታ አካል፣ የዜጎችን መብት ማስከበር አለመቻላቸውን የጠቀሰው ሪፖርቱ፤ እነዚህ አካላት በህግ ተጠያቂ ሊደረጉ ይገባል ብሏል፡፡ በ34 ሰዎች ህይወት መጥፋትም ተጠያቂዎች እንደሆኑ ጠቁሟል፡፡
አማራ ክልልን በተመለከተ
በአማራ ክልል በጎንደር ከተማ፣ ሰሜን ጎንደር፣ ደቡብ ጎንደር፤ በባህር ዳር ከተማ፣ ምዕራብ ጎጃም፣ ምስራቅ ጎጃምና አዊ ዞን የተፈጠረውን ግጭት ማጣራቱን ኮሚሽኑ አመልክቷል፡፡
በክልሉ በተለይ በሰሜን ጎንደር ዞን፣ በ2008 ዓ.ም ተደጋጋሚ ተቃውሞዎች መታየታቸውን፣ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች “የወልቃይት ማንነት ጥያቄ አልተመለሰም፣ የአማራ ክልል ካርታ ተቆርጦ ወደ ትግራይ ክልል ተወስዷል፣ የትግራይ ብሄር የበላይነት አለ፣ የራስ ዳሽን ተራራ የሚገኘው በትግራይ ክልል ውስጥ ነው ተብሎ በመማሪያ መፅሃፍ መታተሙ አግባብ አይደለም፣ በትግራይና በአማራ ክልል መካከል የሚገኘው የጠገዴ ድንበር ምላሽ ሊሰጠው ይገባል” በሚሉ ምክንያቶች ተቃውሞዎች እንደነበሩ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሐምሌ 4 ቀን 2008 ዓ.ም ከሌሊቱ 10፡30 በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው የነበሩ ግለሰቦችን የፌደራል ፀረ ሽብር ግብረ ሃይል በጎንደር ከተማ በቁጥጥር ስር ለማዋል  ያደረገውን እንቅስቃሴ ተከትሎ፣ ሁከትና ብጥብጥ ተፈጥሯል ብሏል – ሪፖርቱ፡፡ ፌስቡክና ኢሣት ሁከቱን አባብሰዋል ተብሏል፡፡
የተቃውሞው ምክንያት የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ስራ አጥነት፣ የመሬት አስተዳደር ችግር፣ የመሰረተ ልማት አለመሟላት፣ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ አለመስፋፋት ናቸው ብሏል – ሪፖርቱ፡፡
ከወልቃይት ጉዳይ ጋር በተያያዘ የድንበር ምላሽ አልተሠጠም የሚሉና የጎንደር መሬት ለሱዳን ተሰጠ የሚሉ አባባሽ ምክንያቶች ነበሩ ብሏል – ኮሚሽኑ፡፡ በክልሉ የተካሄዱት ሰልፎች በሙሉ ህገ ወጥ ነበሩ ያለው ሪፖርቱ፤ የባህር ዳሩን ሰልፍ ግን ሠማያዊ ፓርቲ እንዳስተገበረውና ባለቀ ሰአት ፓርቲው ሃላፊነት አልወስድም ማለቱን ጠቁሟል፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ሰልፍ ምክንያት ለመጣው ችግር ኃላፊነቱን ሰማያዊ ይወስዳል ተብሏል፡፡
ተቃውሞው የሀገሪቱን ሰንደቅ አላማ በማቃጠል፣ ባንኮችና ሆቴሎች ላይ ጉዳት በማድረስ፣ በውሃ መሰረተ ልማት ላይ ውድመት በመፈጸም እንዲሁም በትግራይ ተወላጆች ላይ ጉዳት በማድረስ የታጀበ ነበር፤ በትጥቅ የታገዘም ነው ብሏል – ኮሚሽኑ። በተቃውሞው የትግራይ ብሄር ተወላጆችን ለይቶ የማጥቃት እንቅስቃሴ መደረጉንና 11 ሺህ 678 ተወላጆች መፈናቀላቸውን ሪፖርቱ ጠቁሟል። የክልሉ መንግስትና የወረዳ አስተዳደሮችም ተገቢውን የደህንነት ጥበቃ አላደረጉም ተብሏል፡፡ ህብረተሰቡ ግን ለትግራይ ተወላጆች ከለላ በመሆኑ ይደርስ የነበረው ጉዳት አለመድረሱን አስታውቋል – ኮሚሽኑ፡፡  የክልሉ መንግስት አመራሮች አደጋዎቹን ለመከላከል ተነሳሽነት ካለማሳየታቸውም በላይ እንደ ጨኧት፣ አምባጊዮርጊስ፣ ጪስ አባይ ቦታዎች አመራሩ አስተዳደሩን ጥሎ በመኮብለሉ፣ መንግስት ወድቋል በሚል የጎበዝ አለቃዎች እስከ መምረጥ ተደርሶ ነበር ብሏል – ሪፖርቱ፡፡
የኃይል እርምጃ አወሳሰድ
በሽብር የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በጎንደር ከተማ ለመያዝ በተደረገው እንቅስቃሴ ከፀጥታ ኃይሎች 12፣ ከነዋሪዎች 4፣ በድምሩ የ16 ሰዎች ህይወት ጠፍቷል ያለው ሪፖርቱ፤ የፀጥታ ኃይሉ የወሰደው እርምጃ ህጋዊ ነበር ብሏል፡፡
በባህር ዳር ከተማ ማረሚያ ቤት የተወሰደውን እርምጃ በተመለከተ በአድማ ታግዞ የተደረገ የማምለጥ ሙከራ ስለነበር እርምጃው ተመጣጣኝና ህግን የተከተለ ነው ተብሏል፡፡ እንጅባራ ከተማ ላይ የተወሰደው እርምጃና 2 ወጣቶች የተገደሉበት እንዲሁ ህግን የተከተለ ነበር ይላል – ሪፖርቱ፡፡
በጎንደር ከተማ አዘዞ አካባቢ 2 ወጣት ሴቶች መገደላቸው፣ በደምቢያ ወረዳ 2 ወጣቶች፣ ደባርቅ 1 ወጣት፣ ቡሬ ከተማ 1 ወጣት፣ አዴት ከተማ 1 ሰው፣ ወንበራ ወረዳ 2 ሰዎች፣ ደብረ ታቦር 2 ሰዎች፣ ስማዳ 4 ሰዎች፣ ወረታ  2 ሰዎች፣ እንጅባራ ከተማ 2 ሰዎች፣ ዳንግላ 3 ሰዎች መገደላቸው ከህግ አግባብ ውጪ የሆኑና ተመጣጣኝ ያልነበሩ በመሆናቸው እርምጃ ወሳጆች በህግ ይጠየቁ ብሏል – ኮሚሽኑ፡፡
በአማራ ክልል በጠቅላላው 110 ሲቪሎችና 30 የፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን፣ 276 ሲቪሎችና 100 የፀጥታ አካላት መቁሰላቸውን ሪፖርቱ አመላክቷል። የክልሉ መንግስት ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ተመልሰው እንዲቋቋሙና አጥፊዎች ተለይተው ለህግ እንዲቀርቡ ማድረግ አለበት ሲል ኮሚሽኑ ምክረ ሀሳቡን አቅርቧል፡፡ የአድማ መበተኛ መሳሪያዎች ተሟልተው፣ ለፖሊስ አካላትም ስልጠና መስጠት እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡
ያልተመጣጠነ እርምጃ የወሰዱ የፀጥታ አካላት ተጣርተው ለህግ እንዲቀርቡ የጠየቀው  ኮሚሽኑ፤ ኃላፊነታቸውን ባልተወጡ አስተዳደሮች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ አሳስቧል፡፡ ህገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውርም የሚገታበት ሁኔታ መፈጠር አለበት ተብሏል፡፡
በአጠቃላይ በሶስቱም ክልሎች በነበረው ችግር በኦሮሚያ ኦነግ እና ኦፌኮ ተጠያቂ የተደረጉ የፖለቲካ ድርጅቶች ሲሆኑ OMN እና ማህበራዊ ድረ ገፆች አባባሽ ናቸው ተብሏል፡፡ በጌዴኦ ለነበረውም የጌዴኦ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ከተጠያቂዎቹ አንዱ ሲሆን በአማራ ክልል በተለይ በባህር ዳር ሰማያዊ ፓርቲ እንዲሁም ኢሳት እና ቤተ አማራ የመሳሰሉ ድረ ገፆች አባባሽ ነበሩ ተብሏል፡፡

Source          –                   Addis Admass