Wednesday, 26 April 2017 12:12

 በይርጋ አበበ

በ2008 ዓ.ም በተቃውሞ ሲናጥ የነበረው የኦሮሚያ መሬት በ2009 ዓ.ም መባቻ አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት እየታየበት ይመስላል። በመንግስት ጥልቅ ተሃድሶ እና የፓርቲዎች መደበኛ ግምገማ ማድረጉን ተከትሎ የክልሉ ገዥ ፓርቲ ሁለቱን ሊቃነመናብርት (አቶ ሙክታር ከድር እና ወይዘሮ አስቴር ማሞን) በአቶ ለማ መገርሳ እና በዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በመተካት ዓመቱን መጀመሩ ይታወሳል።

በሌላ በኩል ደግሞ ቀደም ሲል በክልሉ ከስምንት ሚሊዮን በላይ ወጣት እንዳለ የቀድሞው የክልሉ ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ፍቃዱ ተሰማ (ከሰንደቅ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ) መግለጻቸው ይታወቃል። ይህ የህብረተሰብ ክፍል የእለት ጉርሱን ለማግኘት የግድ የስራ እድል ሊፈጠርለት እንደሚገባ ግልጽ ነው። ምን ያህል ርቀት እንደሚያስጉዘው ባይታወቅም የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ግን “የኦሮሚያ የኢኮኖሚ አብዮት” ብሎ በጀመረው መሰረት ከአገር አቋራጭ አውቶብስ እስከ ወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ እና ፋብሪካ ግንባታ እንቅስቃሴ ጀምሯል።

ከዚህ በተጨማሪም ከአጎራባች የሶማሌ ክልል ጋር በተፈጠረ ግጭት በርካቶች ህይወታቸው ማለፉን ገለጸው የክልሉ መንግስት ከሶማሌ ክልል ጋር ለተፈጠረው ችግር መፍትሔ እየፈለገ ሲሆን፣ በቀጣይ በአካባቢው የጥይት ድምጽ እንዳይሰማም የድንበር ማካለል ስራ ለማከናወን እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ተናግሯል። የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ለማ መገርሳ ሚያዝያ 13 ቀን 2009 ዓም በኦሮሞ ባህል ማዕከል ባለሃብቶችን ሰብስበው ባካሄዱት ውይይትም ክልሉ “በለውጥ ጎዳና ላይ” መሆኑን ገልጸዋል። አቶ ለማ በውይይታቸው ወቅትም “ኦሮሚያ ካልተለወጠች ኢትዮጵያ አትለወጥም” ሲሉ የተናገሩ ሲሆን በሌላ በኩል ከተሰብሳቢ ባለሃብቶች መካከልም “ክልላችሁ የሌላ ብሔር ተወላጆችን ያሰወጣል” የሚል ቅሬታም አቅርበው ነበር። እነዚህንና ሌሎች ሰሞነኛ የኦሮሚያን ወቅታዊ ሁኔታ “ሰሞነኛው የኦሮሞ ፖለቲካ” በሚል ርዕስ ከዚህ በታች አቅርበነዋል።

የኦሮሚያ – ሶማሌ ድንበር ግጭትና መፍትሔ
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስትን ካዋቀሩት ዘጠኝ ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች መካከል የኦሮሚያ ክልልን ያህል በቆዳ ስፋት የተንበሸበሸ ክልል የለም። ከትግራይ ክልል በስተቀር ከሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ጋር በድንበር የሚዋሰነው ኦሮሚያ ክልል ከሶማሌ አቻው ጋር በተደጋጋሚ ጊዜ እሰጣ ገባ ውስጥ ገብቶ ነበር። ከአውሮፓ ባለግዙፍ ኢኮኖሚዋ ጀርመን ጋር ተስተካካይ የቆዳ ስፋት ያለው ኦሮሚያ ክልል እና በቆዳ ስፋት የአገሪቱ ሶስተኛው ትልቁ የሶማሌ ክልል በየጊዜው የሚያገረሸው የግጭታቸው መንስዔ የአርብቶ አደሮች የግጦሽ መሬትና የውሃ ፍላጎት ሲሆን ከዚህ ባለፈም የይገባኛል ጥያቄ እንዳለበትም ይነገራል።

የሁለቱን ክልሎች የድንበር አካባቢ ግጭት በተመለከተ አስተያየታቸውን ለሰንደቅ ጋዜጣ የሰጡት የኦሮሚያ ክልል ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አዲሱ አረጋ “ድርጊቱ ተራ ውንብድና ተብሎ የሚታይ ሳይሆን በግልጽ ሰዎችን በማፈናቀል፣ በመግደል እና ድንበር በማስፋፋት ውስጥ የነበሩ መሆኑ የወንጀላቸውን ጥልቀት ፍርድ ቤት አጣርቶ ይወስነዋል” ሲሉ ተናግረዋል። አቶ አዲሱ አያይዘውም በዚህ ድርጊት ውስጥ ተሳታፊ ከነበሩት መካከል የተወሰኑት በቁጥጥር ስር ውለው ወንጀላቸው እየተጣራ መሆኑንና ቀሪዎቹንም ለማያዝ መንግስት ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በተያያዘም የኦሮሞ ኦቦ ነጻነት ግንባር፣ የኦሮሞ ነጻነት አንድነት ግንባር፣ የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ እና የኦሮሚያ ነጻነት ብሔራዊ ፓርቲ የተባሉ አራት ኦሮሚያ ተኮር የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ለዝግጅት ክፍላችን በላኩት መግለጫ የሰላም ስምምነቱን መደገፋቸውን ገልጸዋል።

ሆኖም ፓርቲዎቹ “ከዚህ በፊት ከጅምሩ ጀምሮ የፌዴራል መንግስትም ጣልቃ ገብቶ ሰላማዊ መፍትሔ ይሰጥ ብለን በምንጮህበት ወቅት በሁለቱ መንግስታት በኩል የተፈጠረ ሳይሆን የተራ ሽፍታ እንቅስቃሴ ነው ተብሎ ነበር የተነገረው” ሲሉ ገልጸዋል። የፓርቲዎቹ መግለጫ አክሎም “የሰላም ስምምነቱን የሁለቱ ክልሎች መሪዎች ሲፈራረሙ የዚህን አይነት ስምምነት ከአስር ዓመት በፊት ብንፈራረም ኖሮ የህዝብ እልቂት አይከሰትም ነበር ብለው በቁጭት ሲናገሩ ሰምተናል። ይህም ጉዳዩ ግራ የሚያጋባ መሆኑን ብንመለከትም አሁንም ችግሩ በድጋሚ እንዳይከሰት ቀደም ሲል በ1997 ዓ.ም የተካሄደውን ህዝበ ውሳኔ የህዝብ ድምጽ ተከብሮ ከቦታቸው የተፈናቀሉትን መንግስት እንዲያቋቁማቸው፤ ህዝበ ውሳኔ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች ደግሞ ህዝቡ በፍላጎቱ ሲተዳደርበት በነበረው የህዝብ ፍላጎትና መብት ተከብሮ የተፈናቀሉት ተመልሰው እንዲቋቋሙና የችግሩ ፈጣሪዎች በህግ እንዲጠየቁ” በማለት አስታውቀዋል።

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ በበኩላቸው “ችግሩ በታጠቁ ሀይሎች የተካሄደ መሆኑን በኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ በኩል የተገለጸ ነው። ይህ ችግር በኦሮሚያ እና በሌሎች አጎራባች ክልሎች ላይም እየተስተዋለ ነው” ሲሉ ለሰንደቅ ጋዜጣ ተናግረዋል። አቶ ሙላቱ አያይዘውም “ሲጀመር በአንድ አገር እየኖርን የአንድ አገር ዜጎች ሆነን አለመግባባትን ለመፍታት ጠብመንጃ የምናነሳበት ምክንያት አይገባኝም። ሁለቱም የአንድ አገር ዜጋ ከመሆናቸውም በላይ የትኛው መሬት የየትኛው እንደሆነ ለማወቅ ህዝብን ማነጋገር በቂ መልስ መስጠት ይችላል። ምክንያቱም በመሬቱ የሚኖሩት ሰዎች የሚሰጡት ምስክርነት ትልቅ ዋጋ አለው” ሲሉ የተናገሩ ሲሆን ግጭቱን አስመልክቶ ሲናገሩም “ይህ ቴዚያን ቲዎሪ ነው” ብለዋል። (ቴዚያን ቲዎሪ ማለት በመንግስት ላይ ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች ሲነሱ ሌላ የመወያያ አጀንዳ በመፍጠር የህዝብን ጥያቄ ለማስቀየስ የሚደረግ ቲዎሪ ነው)

የኦሮሚያ – ሶማሌ ግጭት ለጊዜው የተረጋጋ ሲሆን በቀጣይም እንዳይነሳ የሁለቱ ክልሎች ባለስልጣናት ባካሄዱት ውሳኔ መሰረት በቀጣዮቹ ሶስት ወራት የድንበር ማካለሉ ስራ ይከናወናል። አቶ አዲሱ አረጋ “የድንበር ማካለሉ የሚከናወነው በ1997 ዓ.ም በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ መሰረት ይሆናል” ሲሉ ለሰንደቅ ጋዜጣ የተናገሩ ሲሆን አያይዘውም ለተጎጂዎች መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።

የኢኮኖሚ አብዮቱ እና የአቶ ለማ መገርሳ ንግግር

የቀድሞው የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር የነበሩትና አሁን ክልሉን ከአቶ ሙክታር ተቀብለው በፕሬዝዳንትነት እያስተዳደሩ ያሉት አቶ ለማ መገርሳ ናቸው። አቶ ለማ በሚያስተዳደሩት ክልል “ስር የሰደደ ችግር” መኖሩን ገልጸው ይህን ችግር ለማስተካከልም ቁርጠኛ ውሳኔ ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል። ነገር ግን ለዚህ የአቶ ለማ መገርሳ ካቢኔ ውሳኔ ተፈጻሚነት ህዝቡ ራሱን ከነብስ አባት (God father) እንዲያርቅና የራሱን መብት ለማስከበር የእጅ መንሻና መደለያ ከመስጠት እንዲቆጠብ ተማጽነዋል። “ተቆራጭ የሚፈልግ ብዙ ሰው አለ እናንተ እስከሰጣችሁት ድረስ በቃኝ የሚል የለም። ነገር ግን ተቆራጭ ባበዛችሁ መጠን መጨረሻ ላይ ደም ግፊት ብቻ ሳይሆን እሱም ይገድላችኋል” ሲሉ በክልሉ የተሰገሰጉትን የነብስ አባቶች (ያለ እጅ መንሻ ጉዳይ የማይፈጽሙ ካድሬዎችን) ባለሃብቱ እንዲዋጋላቸው ተናግረዋል።

“የአገሪቱ ጅዲፒ ከ40 እስከ 60 በመቶ የሚሆነው ከኦሮሚያ ክልል የሚገኝ ነው” ያሉት አቶ ለማ “ኦሮሚያ ካልተለወጠች ኢትዮጵያ አትለወጥም” ሲሉም ተናግረዋል። “ቢያንስ ሁላችንም እኩል ተጠቃሚ ባንሆን እኩል እድል ግን ማግኘት አለብን። የምንጠቀመው ሊለያይ ይችላል ምክንያቱም የለፋነውን ያህል ነው ልንጠቀም የምንችለው። እኩል እድል ግን ማግኘት ይኖርብናል። ለዚህች አገር መፍረስም ሆነ ማደግ ወይም ለመለወጥ ኦሮሚያ ትልቅ ድርሻ አለው። ጂዲፒያችን በዚህን ያህል አደገ የምንለው ከ40 እስከ 60 ከመቶው የሚሆነው ግብርና የኦሮሚያ አስተዋጸኦ ነው። ይህ ማጋነን አይሆንም። ኢንዱስትሪውም ከፊንፊኔ (አዲስ አበባ) ቀጥሎ የኦሮሚያ ክልል ነው” ብለዋል።

“ክልላችሁ የሌሎች ብሔር ተወላጆችን ያስወጣል” የሚል ጥያቄ ከባለሀብቶቹ የቀረበላቸው አቶ ለማ “የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ማንንም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ለማባረር ስልጣኑም ፈቃዱም የለውም። እውነት ነው ሁላችንም የተለያየ ስም አለን ግን ሁላችንም ኢትዮጵያዊያን ነን። እንኳን ኢትዮጵያዊውን ከራሱ ቤት ማባረር ይቅርና የውጭ ዜጋውንም እኮ እየጋበዝን እያስተናገድን አይደል እንዴ? ይህ ሊታሰብ የሚችል አይደለም። አንዳንዶቻችሁ በየማኪያቶ ቤትና በየአረቄ ቤቱ የሚወራውን ሰምታችሁ እንዳትረበሹ ስለምፈልግ ነው” በማለት በክልሉ ሁሉም የአገሪቱ ዜጎች በእኩልነት እንደሚስተናገዱ የመንግስታቸውን አቋም ተናግረዋል።

ኦሮሚያና የኦሮሞ ፖለቲከኞች ሰሞንኛ ጉዳይ

በኦሮሞ ህዝብ ስም የተመሰረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በርከት ያሉ ቢሆንም በህጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱት ግን ገዥውን ኦህዴድን ጨምሮ ሰባት (ቀደም ሲል የተጠቀሱት አራቱ እና ኦህዴድ እንዳሉ ሆነው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ እና የገዳ ስርዓት አራማጅ ፓርቲ) ናቸው።

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ 11 የፓርቲው አመራሮች ከታሰሩ ከአንድ ዓመት በላይ አስቆጥረዋል። የፓርቲው ዋና ጸሀፊ አቶ በቀለ ነጋ ደግሞ በቁም እስር ሲሆኑ የፓርቲው ሊቀመንበር ረዳት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በሀይል ለመናድ በማሴር ክስ ተመስርቶባቸው በእስር ላይ ከሆኑ አምስት ወር ሆኗቸዋል።

እነ አቶ በቀለ ገርባ ለግንቦት 6 ቀን 2009 ዓ.ም ለብይን ሲቀጠሩ፤ ከትናንት በስትያ ሰኞ ሚያዝያ 16 ቀን 2009 ዓ.ም ለአምስተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረቡት ደክተር መረራ ጉዲና ለሚያዝያ 26 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል። በአገሪቱም ሆነ በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ያለውን ሁኔታ በንቃት እየተከታተለ መሆኑን የሚገልጸው ኦፌኮ “ሁኔታው አለባብሰው ቢያሱ በአረም የመለሱ ነው” ሲል በምክትል ሊቀመንበሩ አቶ ሙላቱ ገመቹ በኩል ገልጿል። የሰብአዊ መብት ኮሚሽነር አዲሱ ገብረእግዚአብሔር ሰሞኑን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት “በኦሮሚያ ክልል ለደረሰው ግጭት ኦፌኮ እጁ አለበት” ሲሉ ገልጸዋል። ፓርቲውም በህግ ሊጠየቅ እንደሚገባው ተናግረዋል።

ከኦፌኮ በተጨማሪ ደግሞ አራቱ ፓርቲዎች ለዝግጅት ክፍላችን በጋራ በላኩት መግለጫ መንግስት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በሚያደርገው ድርድር መሳተፍ አልቻልንም ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል። ፓርቲዎቹ በመግለጫቸውም “ድርድሩ እንኳንስ የኦሮሞን ህዝብ ችግር የተቀረውን የኢትዮጵያ ህዝብ ችግር ፈቶ የህዝቡን መብት ያስከብራል የሚል እምነት ስለሌለን ከድርድሩ የሚገኝ ውጤት ምንም ይሁን ምን እኛ አራቱ በኦሮሞ ህዝብ ስም የተደራጀን ፓርቲዎች የማንቀበልና እንደ ህግም ሆኖ የሚወጣ ነገር ካለ በግድ ሊጫንብን የማይገባ መሆኑን ከወዲሁ እንገልጻለን” በማለት አስታውቀዋል። (ድርድሩ የተጠራው ለአገር አቀፍ ፓርቲዎች እንጂ ለክልል ፓርቲዎች አለመሆኑን ልብ ይሏል)

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ፤ “ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ማግኘት ያለበትን የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልዩ ጥቅሞች የሚመለከት ዝግጅት ተጠናቆ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ እንደሚጸድቅ ተናግረው ነበር” ያሉት አራቱ ፓርቲዎች ይህን የአቶ ኃይለማሪያምን መገለጫ የተመለከቱት በጥርጣሬ መሆኑን ተናግረዋል። ምክንያታቸውን ሲያቀርቡም “ኦሮሚያ ከፊንፊኔ ማግኘት ያለበት ልዩ ጥቅም ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ብቻ አይደለም” ሲሉ የገለጹ ሲሆን ፓርቲዎቹ ተጨማሪ ጥቅም ሲሉ የገለጹት “በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንግስት ኦሮሚያን የጨመረ የጋራ አስተዳደር እንዲኖርና ከአማርኛ ቋንቋ እኩል ኦሮምኛ ቋንቋ የስራ ቋንቋ የሚሆንበት ከተማ እንዲሆን አጥብቀን ለማሳሰብ እንወዳለን” ብለዋል።

በቅርቡ የሰብአዊ መብት ኮሚሽነር ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ያቀረቡትን ሪፖርት በተመለከተም ሪፖርቱን እንደማይቀበሉት ገልጸዋል። ምክንያታቸውን ሲያስቀምጡም “ኮሚሽነሩ ገለልተኛ አይደሉም፣ በኦሮሚያ የደረሰው ጉዳት ተመጣጣኝ አይደለም እና ሪፖርቱም ከሃቅ የራቀ ነው” የሚል ነው። ሪፖርቱም እንደገና በዓለም አቀፍ ገለልተኛ ወገኖች እንዲጣራ” ሲሉ አሳስበዋል።

ስንደቅ