ለግንቦት ፮፳፻፱ (6, 2009) .በዳግማዊ መአሕድ አዘጋጅነት በዋሽንግተን ዲሲ ታላቅ ዓለም አቀፍ የአማራ ጉባኤ ለማድረግልዩ ቀጠሮ ተይዟል፡፡ ሲመስለኝ የዚህ ጉባኤ ዋነኛ ዓላማ አማራን በአንድነት እንዲሰባሰብና በአንድ ድርጅት ተጠቃሎ በብርታት እንዲታገል ለማስቻል ይመስለኛል ወይም አለበት፡፡ ይሄ ካልሆነና ማስታወቂያ ላይ እንደተገለጸው የመአሕድን የብር ኢዮቤልዩ (Jubilee) ክብረ በዓል አክብሮ ለመለያየት ከሆነ አሁንም አለመንቃታችን ትንሽ የሚያስደነግጥ ይመስለኛል፡፡ ይሄንን አጋጣሚ በመጠቀም መናገር ማጋራት የምፈልገው ቁም ነገር አለ፡፡ በቅድሚያ ግን ለሁሉም የአማራ ወገኖች ክፍት የሆነ ይሄንን ጉባኤ ለማዘጋጀት ስላበቃን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይድረሰው፡፡ አዘጋጆቹንም እንዲሁ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡ በእርግጥ በጣም ዘግይተናል፡፡

ይሁንና ከቀረ የዘገየ ይሻላልና ከዚህ በኋላ በምናደርገው እንቅስቃሴ በመዘግየታችን ያጣነውን ጥቅምና የደረሰብንን ጉዳት ሊያካክስ በሚችል ትጋት ከሠራን መዘግየታችን ብዙም የሚያስቆጭ አይሆንም፡፡


በዚህ ጽሑፌ ላይ ይህ ጉባኤ በአንክሮ እንዲመለከታቸው የምፈልጋቸውን ጉዳዮች ናነሣ ፈልጌያለሁ፡፡ ትንሽ ጊዜ ታገሱና ከኔ ጋራ ቆዩበጥሞና ተከታተሉኝበእኔ እምነት ይህ ጉባኤ በቅድሚያ ሊያከናውናቸው የሚገቡና ጊዜ የማይሰጣቸውን ሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ መምከር ይኖርበታል ብየ አምናለሁ፡፡

1አማራ የተደራጀበት ዓላማና ምክንያት ገና ያልገባቸው የገዛ ወገኖቹ አሉና የተደራጀበትን ምክንያትና አስፈላጊነት ጉዳይ ላይ የጠራ ግንዛቤ አስጨብጦ የቀሩትን፣ ራሳቸውን ያገለሉትን ወገኖች አስረድቶና አሳምኖ በማምጣቱ ጉዳይ ላይ፡፡


2
አንድ ሆኖ የሚጠቃለለው የአማራ ድርጅት ከሕዝብ ጋር የሚገናኝበት፣ ዓላማ፣ ግብ፣ ተግባሩን፣ ክንውኑን፣ ርዕዮተዓለሙን፣ ትምህርቶቹን፣ ዜናዎችን፣ መረጃዎችን ወዘተረፈ ለሕዝብ የሚያቀርብበት የመገኛ ብዙኃን በተቻለ ፍጥነት ማቋቋም በሚችልበት ጉዳይ ላይ፡፡


3
ከፋኝእያሉ በየስፍራው እየታገሉ ያሉ ወገኖቻችንን በመደገፍ ያለውን የትጥቅ ትግል ማጠናከር ማሳደግ ማስፋፋት በሚቻልበት ጉዳይ ላይ፡፡


ጉባኤው እነኝህን ጉዳዮች መክሮባቸው ውጤት ሊገኝ የሚያልበትን አቅጣጫ ይዞ ይወጣ ዘንድ የግድ ያስፈልገናል እላለሁ፡፡ ሌሎቹ ጉዳዮች ጊዜ የሚሰጡና እነኝህን ሦስት ዐበይት ጉዳዮች ስንፈታ አብረው የሚፈቱ ናቸው፡፡ እንዴትየሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የጠቀስኳቸውን ነጥቦች እያንዳንዳቸውን በዝርዝር መመልከት ያስፈልጋልና እንያቸው፦
1
ኛ ላይ ስለመደራጀት ላነሣሁት ነጥብ፦ አንድ በጣም የሚገርመኝ ነገር አለ፡፡ አማራ በማንነቱ የመደራጀቱን ጉዳይ አስፈላጊነት ስናወራ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ (የእምነተ አሥተዳደርድርጅት ነን ከሚሉና ደጋፊዎቻቸው ነን ከሚሉ ማኅበራትና ግለሰቦች የሚነሣ ከፍተኛ ቅሬታ አለ፡፡ በእኔ እምነት ይሄ ቅሬታ በሁለት ምክንያቶች ይፈጠራል፡፡
አንደኛው አማራ የሚደራጅበትን ምክንያትና ዓላማ ለመረዳት ካለመቻል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የያዙትን ሀገራዊ ወይም ፖለቲካዊ (እምነተ አሥተዳደራዊጉዳይ አብስለውና ጠንቅቀው ካለማወቅ ይመነጫል፡፡
ይሄም ማለት ምን ማለት ነው፦ አማራ የሚደራጀው እንደሌሎቹ ማለትም እንደ ወያኔና ወያኔ እንደፈለፈላቸው ጎሳ ተኮር የፖለቲካ ድርጅቶች ጠባብ የሆነ አመለካከት ይዞ የብሔረሰቡን ተወላጆች ከሌሎች ብሔረሰቦችና ጎሳዎች በተለየ መልኩ ተጠቃሚ በማድረግ፣ ኢፍትሐዊ ተግባር ለመፈጸምና የሀገርን ህልውና ለድርድር ለማቅረብ ወይም አደጋ ላይ ለመጣል ሳይሆን ከሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ እንደ ወያኔ፣ ኦነግ፣ ሸአቢያና ከመሳሰሉት የሀገር ውስጥ የጥፋት ኃይሎች እና ከጥቅማቸው፣ ከዕኩይ ዓላማቸው የተነሣ አማራን ጠላት አድርገው ከፈረጁ ባዕዳን ታሪካዊ የጠላት ኃይሎች ከረጅም ጊዜ በፊት ጀምሮ በማንነቱ የተቃጣበትን የታወጀበትን የዘር ማጥፋት ጥቃትና ዘመቻ ለመመከትና ህልውናውን ለማስቀጠል እንደሆነ የሚደራጀውና የሚታገለው ተደጋግሞ ቢነገራቸውም በሚያሳዝንና ግራ በሚያጋባ መልኩ
ሊገባቸው አልቻለም፡፡


ምናልባትም በአማራ ሕዝብ ላይ የተፈጸመውና እየተፈጸመ ያለው እጅግ አሰቃቂ ግፍና የዘር ማጥፋት ወንጀል የሚሰማቸው፣ የሚገዳቸው፣ የሚከነክናቸው ስላልሆኑ ይሆናል፡፡ ለዛም ነው በወገኖቻችን ላይ ኢሰብአዊ ግፍና የዘር ማጥፋት ወንጀል ከፈጸሙና ወደፊትም እንደሚፈጽሙ ከሚዝቱ የጥፋት ኃይሎች ጋር የጥፋት ኃይሎቹ ለዚህ በአማራ ላይ ለፈጸሙት ወንጀላቸው ይቅርታ ሳይጠይቁና ሳይጸጸቱ እጃቸው በንጹሐን ወገኖቻችን ደም እንደተጨማለቀና ዕኩይ ሰይጣናዊ ዓላማቸውን መተዋቸውን ሳይገልጹና ሳይጸጸቱ ከእነሱ ጋር ጥምረት እየፈጠሩና ለመፍጠርም ጥረት እያደረጉ የሚገኙት፡፡
ለማንኛውም በአማራ መደራጀት ላይ ብዥታ ያለበት አካል ቢኖር አማራ ለመቸውም ቢሆን በሌሎቹ የጎሳ ተኮር ጠባብ ድርጅቶች ቅርጽ መልክና ዓላማ አልተደራጀም አይደራጅምም!!! ይሄንን ለማድረግ ማንነቱ፣ ታሪኩ፣ ባሕሉ፣ ሥልጣኔው፣ አስተሳሰቡ ሁለንተናው ፈጽሞ አይፈቅድለትምና፡፡ ይሄንንማ እኔም እራሴ የወያኔ ቅጥረኞች አማራን ከማንነቱ፣ ከከፍታው ለማውረድና ለማርከስ በአማራ ስም ለጠባብ ፖለቲካዊ ዓላማ ለመጀራጀት በቃጣቸው ጊዜ ከማንም በፊት በማጋለጥ፣ በመቃወም፣ በማውገዝ ሕዝቡን ሳስጠነቅቅበት የቆየሁት ጉዳይ ነውና አማራ የተደራጀው ለዚህ አይደለም፡፡
እንደ እነዚህ የአንድነት ኃይል ነን ባዮች አካላት አባባል በአማራ ላይ ያነጣጠረ የዘር ማጥፋት ጥቃት ቢኖርም ዲሞክራሲን (መስፍነ ሕዝብንበማስፈን ሊቀረፍ ሊፈታ የሚችል ችግር ነውና ሙሉ ትኩረታችንን ዲሞክራሲያዊ (መስፍነ ሕዝባዊሥርዓት ልንመሠርት በምንችልበት ጉዳይ ላይ እናተኩር!” ሲሉ ይሰማሉ፡፡ ነገር ግን ዲሞክራሲ ሊፈታና ሊመልሰው የሚችለው ፖለቲካዊ (እምነተ አሥተዳደራዊችግሮችንና አለመግባባቶችን እንጅ እንደ አንድን ዘር ጨርሶ ለጥፋት ቆርጦ የተሸመቀ ዕኩይና ሰይጣናዊ ዓላማን ዓይነት አረመኔያዊ ፍላጎትንና ጥያቄን ሊፈተና ሊመልስ የማይችል መሆኑን እነኝህ አካላት የሚያውቁ አልመሰለኝም፡፡


አንድ ጉዳይ ፖለቲካዊ ጉዳይ ነው የሚባለው ጉዳዩ በፍትሕ ሊዳኝና ሊፈታ የሚችል ጉዳይ ሲሆን ነው፡፡ በፍትሕ ሊፈታና ሊዳኝ ሊስተናገድ የማይችል ጽንፈኛና አግባብነት የሌለው ጉዳይ ፖለቲካዊ ጉዳይ ነው አይባልም፡፡ የአማራን ዘር ለማጥፋት የሚፈልጉ የጥፋት ኃይሎች ኢፍትሐዊ ጥቅማቸው ሊከበር የሚችለው አማራ ሲጠፋ ብቻ ነው!” ብለው የሚያምኑ በመሆናቸው ይህ ጽንፈኛ ጥያቄያቸው ፍላጎታቸው በመነጋገር፣ በፍትሕ ሊፈታ ሊመለስ የሚችል አይደለም፡፡ በመሆኑም ፍላጎታቸው አጋንንታዊ እንጅ ፖለቲካዊ (እምነተ አስተዳደራዊአይደለም፡፡ ስለሆነም ዲሞክራሲ (መስፍነ ሕዝብየሚፈታው ወይም የሚመልሰው ጥያቄ ፍላጎት አይደለም፡፡

ወደ የአንድነት ኃይል ነን ባዮች ሁለተኛው የአማራን መደራጀት በተመለከተ የተሳሳተ አስተሳሰባቸውን የያዙበት ምክንያት ማለትም የያዙትን ሀገራዊ ወይም ፖለቲካዊ ጉዳይ አብስለውና ጠንቅቀው ካለማወቅ ይመነጫል!” ወዳልኩት ጉዳይ ሳልፍ፦ እነኝህ አካላት ለምሳሌ ግንቦት እና ልሳኑ ኢሳት እራሳቸውን ፖለቲካ እንደገባቸው አድርገው ይቆጥራሉ፡፡ ነገር ግን ምንም የገባቸው ነገር እንደሌለና ደመነፍሳቸውን የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን እዚሁ ላይ ላረጋግጥላቹህ እችላለሁ፡፡ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ያነሣሁት ነው አዲስ ነገር አይደለም፡፡ የሚያስብ ጭንቅላት ካላቸው እንዴት ሊገባቸው እንዳልቻለ ስለገርመኝ ነው አሁንም የማነሣው፡፡ እሱ ምንድን ነው፦ ብሔረሰብ ወይም ጎሳ ተኮር ፖለቲካዊ አደረጃጀት ፀረ ዲሞክራሲ (መስፍነ ሕዝብ፣ ፀረ ሰብአዊ መብት፣ ፀረ ፍትሕ፣ ኋላ ቀር አስተሳሰብ … መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህም ምክንያት ይህ ጎሳ ተኮር ፖለቲካ በምዕራቡ ወይም በሠለጠነው የዓለማችን ክፍል እንዳይሠራ መደረጉን ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ገልጫለሁ፡፡ እነኝህ የአንድነት ኃይሎች ነን ባዮችና መሰሎቻቸው የአማራን በማንነቱ መደራጀት የሚቃወሙት የብሔረሰብ ወይም የጎሳ ተኮርን ፖለቲካዊ አደረጃጀት ፀረ ዲሞክራሲነት፣ ፀረ ሰብአዊ መብትነት፣ ፀረ ፍትሕነት፣ ኋላ ቀርነት … ስለሚያውቁና አደረጃጀቱን ስለሚያወግዙ ስለሚቃወሙ፤ አማራም የሚደራጀውም ሌሎቹ ጎሳ ተኮር ድርጅቶች ለተደራጁበት ዓይነት ጠባብ የጥፋት ዓላማ መስሏቸው ነው የአማራን በማንነቱ መደራጀቱን የሚቃወሙት እንዳንል ለሌሎቹ የጎሳ ተኮር ጅርጅቶች እውቅና ሰጥተው ከነሱ ጋር አብረው ይሠራሉና፣ ይደግፏቸዋልና፣ ያበረታቷቸዋልና፣ የአየር ሰዓት ሰጥተው ያስተናግዷቸዋልና ምክንያታቸው ይሄ አይደለም ማለት ነው፡፡ ሌላ ታዲያ ምን ሊሆን ይችላልብለን ስንጠይቅ ምላሹ ከላይ ያልኳቹህ ማለትም የያዙትን ሀገራዊ ወይም ፖለቲካዊ ጉዳይ አብስለውና ጠንቅቀው አለማወቃቸው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በማሳያዎች ባረጋግጥላቹህ መልካም ይመስለኛል፡፡


እነኝህ አካላት አማራ የሚደራጀው እንደሌሎቹ ጎሳ ተኮር ድርጅቶች ለመጥበብ መስሏቸው ነው የአማራን በማንነቱ መደራጀት የማይደግፉ እንበልና በዚህ ምክንያት የአማራን መደራጀት የማይደግፉ ከሆነም የሌሎቹንም እንዲሁ አለመደገፍ ወይም መቃወም ይኖርባቸው ነበር፡፡ ይሄንን ሲያደርጉ ግን አይታዩም፡፡ ይሄንን ሳያደርጉ የአማራን መደራጀት ብቻ ከሆነ የሚቃወሙት በእርግጠኝነት እነኝህ አካላት የሚሠሩትን ነገር አያውቁምወይም ደግሞ ዓላማቸው አማራን ከጨዋታ ውጪ ማድረግ ነው ዓላማና ግባቸው፡፡ ምክኒያቱም እንደምታውቁት ከደርግ ውድቀት በኋላ ያለው የሀገራችን ፖለቲካ እየተወሰነ ያለው በብሔረሰብ ወይም በጎሳ አደረጃጀቶች ውክልና ነውና፡፡ እንደምታስታውሱት በሽግግሩ መንግሥት ምክር ቤት ወቅት በማንነቱ ያልተወከለው ብቸኛው ብሔረሰብ አማራ ነበረ፡፡ አማራ በማንነቱ ተደራጅቶ ባለመወከሉ ምን ያህል እንደተጎዳ፣ መብትና ጥቅሙን እንዳጣ፣ ለጥቃት እንደተጋለጠ፣ የሚደርስበትን ግፍ ማስታወቅ ማጋለጥ መከላከል እንዳይችል እንዳደረገው በግልጽ የሚታወቅ ጉዳይ ነው፡፡

ፕሮፌሰር (ሊቀ ጠበብት) ዐሥራት ወ/ኢየሱስ ይሄንን ክፍተት ለመሙላት ነበር ለመሠዋት የዳረጋቸውን አማራን አደራጅቶ የማታገል ትግል ሲታገሉ የነበሩት፡፡


ወያኔ ዘግይቶ አማራ በሽግግር መንግሥቱ አለመወከሉ የሚፈጥረውን ፖለቲካዊ የማስመሰል ክፍተት በመረዳቱ የአጋር ድርጅቱን የኢሕዴንን (የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄንስም ወደ ብአዴን (ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄወደሚል ቀይሮ አማራ በብአዴን እንደተወከለ አስመስሎ አቀረበና የነበረውን ክፍተት ከዚያ በኋላ ላለው የደፈነ በማስመሰል ይሄው እስከዛሬም እንዳወናበደ አለ፡፡


ነገር ግን የቀድሞው ኢሕዴን የኋላው ብአዴን ትግል ላይ በነበረበት ወቅትም ሕወሀት የትግሬን ሕዝብ የትግል ዓላማው ማዕከሉ እንዳደረገው ሁሉ ኢሕዴንም የአማራን ሕዝብ የትግል ዓላማው ምክንያቱ ወይም ማዕከሉ ሊያደርግ አይደለም ከናካቴውም አስቦት አያውቅም ነበረ፡፡ እንኳንና ያኔ አሁንም በአማራ ስም ከተቋቋመ በኋላም እንኳ አማራን በአማራነቱ ከሚያጠቁ የጥፋት ኃይሎች ጎን ቆሞና ቀኝ እጅ ሆኖ አማራን ሲያጠቃ፣ ሲፈጅና ሲያስፈጅ ኖረ እንጅ ለአማራ ሕዝብ መብት፣ ህልውናና ጥቅም ለቅጽበት እንኳ ቆሞ አያውቅም፡፡ በአማራ ሕዝብ ላይ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ግፍ በዘነበበት በዚህ ሃያ ስድስት የመከራ የፍዳ ዓመታት ውስጥም ይህ ድርጅት ለአንዲት ጊዜም ቢሆን ስለ አማራ ሕዝብ ድምፁን ሲያሰማ ታይቶና ተሰምቶም አያውቅም፡፡


ማለት የፈለኩት የሀገሪቱ ፖለቲካ በብሔረሰብ ወይም በጎሳ አደረጃጀቶች ውክልና እየተወሰነ ባለበት ሁኔታና የወያኔን ዘመን ብቻ አይደለም የምላቹህ አሁን በቅርቡ ዋሽንግተን ዲሲ የተመሠረተውን ሀገራዊ ንቅናቄንም ብትመለከቱ ቀጣዩ የሀገራችን ፖለቲካዊ ሁኔታም እንዲወሰን የሚፈለገውና የሚታሰበው በጎሳ ፖለቲካ አጀረጃጀቶች ውክልና እንደሆነ በግልጽ እየታየ ባለበት ሁኔታ አማራን እንዳይደራጅ መከላከል መቃወም ማለት አማራን ከጨዋታ ውጭ ለማድረግ ማሴር ካልሆነ በስተቀር እንዴት ሆኖ ነው ለአማራ ማሰብ ሊሆን የሚችለው??? ወይ ደግሞ የሀገሪቱ ፖለቲካ በጎሳ ወይም በብሔረሰብ አጀረጃጀቶች እጅ እንዳይወድቅ፣ በእነሱ ውክልና እንዳይወሰን ጥረት እያደረጉ፣ እየሠሩ፣ እየታገሉ አማራን እንዳይደራጅ ተከላክለው ቢሆን ልንገነዘባቸው ልንረዳቸው በቻልን ነበር፡፡ የሀገርን ፖለቲካ በጎሳ አደረጃጀቶች ውክልና እንዲወሰን መፍቀድ አደገኛና የሀገርን ፖለቲካ እስከወዲያኛው እንደተበላሸ እንዲቀር የሚያደርግ በመሆኑ መወገድ ያለበት አሠራር በመሆኑ፡፡ እነሱ ግን እያደረጉት ያለው የዚህን ተቃራኒ ነው፡፡ ይሄ በሆነበት ሁኔታ እንዴት ብለን ነው እነኝህ አካላት የሚሠሩትን ነገር ጠንቅቀው ያውቃሉ፣ ፖለቲካው ገብቷቸዋል ልንል የምንችለውበፍጹም!


በመሆኑም ይሄንን የጠራ ግንዛቤ በማጣት አማራን በማንነቱ ከማደራጀትና ከመደራጀት እራሳቸውን ያገለሉና የሚቃወሙ እንደ የጎንደር ኅብረት (ጎኅያሉ ማኅበራዊ ድርጅቶችና ግለሰቦች አማራ የተደራጀበት ምክንያት ህልውናውን ከታወጀበት ጥፋት የመታደግ ዓላማና ከወደፊት ሀገራዊ ፖለቲካዊ ጠቋሚ ምኅዳር አቅጣጫ አኳያ ተረድተው ወደ መደራጀቱ በመምጣት መጫወት ያለባቸውን ሚና መጫወት እንዲችሉ አጥብቄ ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ አማራ በአማራነቱ ከውጭና ከውስጥ የተጋፈጠውና የታወጀበት ጥፋት የሚመስላቹህንና ብዙዎቻችን የምናውቀውን ያህል ብቻ አይደለም፡፡ ሊገለጽ ከሚችለው በላይ እጅግ የተወሳሰበና ከባድም ነው፡፡ ይሄንን የጥፋት ዘመቻን ለመከላከል በአጭር ታጥቆ ያለመነሣት ሌላ ምንም አማራጭ የለም፡፡ አማራ የተጋፈጠው ትግል ማንነትን የማስከበርን ዓይነት ያህል ቀላል ትግል አይደለም፡፡ ማንነትን የመታደግና ከፈጽሞ ጥፋት የመዳን ህልውናን የማረጋገጥ የማስቀጠል የሞት ሽረት ትግል ነው የተጋፈጠው፡፡ አማራ ሊያጠፉት የሚፈልጉት የሀገር ውስጥ ጠላቶቹ የጥፋት ዓላማቸውን ቢተዉ ወይም ቢጠፉም እንኳ በማንነቱ የታወጀበትን ጥፋት ውጫዊም ነውና ወይም ሊያጠፉት የሚፈልጉ ባዕዳን ጠላቶቹ አሉና ወይም ይኖራሉና የአማራ ፖለቲካዊ ትግል ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እስኪመሠረት ድረስ ቢሆንም ህልውናውን የመታደግ የማስቀጠል ትግሉ ግን ሊያጠፉት የሚፈልጉ ባዕዳን እስካሉ ጊዜ ድረስ ዘለዓለማዊ ነው፡፡ በዚህ የአማራ ህልውናውን የማስጠበቅ ትግል እንደወገንነታቸው የሌሎች ብሔረሰቦችና ጎሳዎች ተወላጆችም እንደ አንድ የአማራ ተወላጅ በሙሉ የተቆርቋሪነት ስሜት ከወንድማቸው ከአማራ ሕዝብ ጎን ቆመው አብረውን እንደሚታገሉ እንጠብቃለን፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ለሌሎች ህልውና ከኮሪያ እስከ
ሊቢያ ከኮንጎ እስከ ዚምባቡዌ ወዘተርፈ ዘመተን ዋጋ የከፈልን ነንና እኛ ለእኛ መሆን ይገደናል ብየ አላስብም፡፡


ከዓመታት በፊት የዘር ማጥፋት ወንጀል በአማራ ሕዝብ ላይ በታሪክ ሒደት ውስጥ ከትናንት እስከዛሬ!” በሚለው ጽሑፌ ላይ በጥልቀት እንደገለጽኩት ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ብሔረሰቦች ወይም ጎሳዎች ከአማራ በስተቀር የዘር ማጥፋት ጥቃት የተፈጸመበትና የታወጀበት ብሔረሰብ ወይም ጎሳ የለም፡፡ እርግጥ ነው ከ16ኛው መቶ ክ/ዘ ከኦሮሞ ብሔረሰብ መግባትና መስፋፋት ጋር በተያያዘ ኦሮሞ ሲስፋፋ ያጠፋቸውና ውጦ ኦሮሞ አድርጎ ያስቀራቸው ነባር ጎሳዎች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በዘመነ ወያኔም በአኙዋክ ጎሳ ላይ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት ጥቃት አለ፡፡ ይሁንና እነኝህ ጥቃቶች በባዕዳን ኃይሎች ሙሉ ድጋፍ በከፍተኛ ደረጃ ከ9ኛው መቶ ክ/ዘ ጀምሮ በአማራ ላይ ሲፈጸም ከቆየው ጥቃት ጋር በዓይነትም ሆነ በይዘት የሚመጣጠኑ አይደሉም፡፡


በመሆኑም ለአማራ ህልውናውን የመታደግ ማንነትን የማስከበር ሳይሆን ህልውናን የመታደግ ትግል የምርጫ ጉዳይ አይደለምና ይሄንን በመገንዘብ ወደኋላ የቀራቹህ ግለሰቦችም ሆናቹህ ማኅበራት ይሄንን በመረዳት ፈጥናቹህ ትቀላቀሉ ዘንድ በግሌ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡ ጉባኤው ሊመክርበት ይገባል ወዳልኩት 2ኛው ነጥብ ልለፍ፦ አብሶ በዚህ ባለንበት ዘመን የብዙኃን መገናኛ ፋይዳ ምን ያህል ጠቃሚና አንገብጋቢ እንደሆነ ለሁሉም ግልጽ ይመስለኛል፡፡ ኢሳት አቅጣጫ ባይስት ኖሮ ኢሳትን የመጠቀሙ ዕድል ይኖር ስለነበረ ለዚህ የሚወጣን ወጪ ጉልበትና ጊዜ ለሌላ አንገብጋቢ ጉዳይ መጠቀም በቻልን ነበር፡፡ እንደምታዩት ግን ኢሳት በጣም በርቀት አቅጣጫ ስቶ ነጉዷል፡፡ በዚህም ምክንያት ኢሳትና የአንድነት ኃይል ነን ባዮች አማራን እንደ ጦስ ዶሮ ወይም እንደ መሥዋዕት በግ የመጠቀም ዘይቤን ተያይዘውታል፡፡ የአማራን ጥቅሞች መሥዋዕት በማድረግ ከአማራ ጥቅም በተጻራሪ የቆሙ አካላትን ለማስደረሰት፣ ለማባበል፣ ለማግባባት የመጣር ርካሽ ነውረኛና የደንቆሮ አባዜ ውስጥ ወድቀዋል፡፡ ኢሳትም ሆነ የአንድነት ኃይል ነን ባዮች ይሄንን ሲያደርጉ እንደ ኦነግ ያሉ ተገንጣይ የጥፋት ኃይሎችን ያባበሉ ያግባቡ መስሎ ይሰማቸዋል፡፡ ደንቆሮ በመሆናቸው ይሄንን ሲያደርጉ ልብ ያላሉትና አደገኛ ስሕተታቸው ምንድን ነው መሰላቹህ የጥፋት ኃይሎቹን በአማራ መጠቃት መደሰታቹህ፣ ከአማራ ጥቅም በተጻራሪ መቆማቹህ፣ ጥቅማቹህን በአማራ መጎዳት ላይ መመሥረታቹህ ትክክል ነው፣ ግፉበት!” እያሏቸውና ይሄንን አደገኛ የሆነ ትምህርት እያስተማሯቸው፣ ከጥፋት አስተሳሰባቸው እንዳይመለሱ እያደረጓቸው እንደሆነ ልብ ሊሉት፣ ሊያስተውሉት አልቻሉም፡፡ ከዚህ የበለጠ ድንቁርና አለ ብትሉኝ ላምን አልችልም፡፡ እንዲህ እያደረጉ መጥፎ ትምህርት እያስተማሩ እንዴት ከጥፋት ዓላማቸው እንመልሳቸዋለን ብለው እንደሚያስቡ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ የያዙትን ሀገራዊ ጉዳይ ወይም ፖለቲካ አብስለውና ጠንቅቀው አያውቁትም፣ በእውርድምብስ ነው የሚራመዱት የምላቹህ ለዚህ ነው፡፡


እኛ አማሮች ለሌሎች ኢፍትሐዊና አግባብነት ለሌለው ጥቅም ሲባል እውነት፣ ታሪክና የአማራ ጥቅም የተጨፈለቀባት የተሠዋባት ኢትዮጵያ እንድትፈጠር መቸም ቢሆን ፈጽሞ ፈጽሞ አንፈቅድም!!!!!!… ከኦነግ ከወያኔ ከሸአቢያና ከሌሎችም የሚነሣ እንዲህ ዓይነት አሳፋሪና ነውረኛ ጥያቄንም መቸም ቢሆን አንቀበልም አናስተናግድምም!!! ታሪክና እውነት በታሪክነቱ እንደነበረ ሆኖ ሳይበረዝ ሳይከለስ መቀመጥና መተላለፍ ይኖርበታል እንጅ የዚህን ወይም የዚያን ስም ይጎዳልና የነበረውና የተፈጸመው ታሪክና እውነት ተደምስሶ ያልነበረና ያልተፈጸመ የውሸት ታሪክና የውሸት እውነት በቦታው እንዲተካ ፈጽሞ አንፈቅድም!!! ጉባኤው በዚህ ጉዳይ ላይ የጸና አቋም ይዞ መውጣት ይኖርበታል፡፡ ከእነኝህ አካላት ጋር መግባባት ከቻልን ለእውነት በመገዛትና ለእውነት በመታመን ነው ልንግባባ የሚገባው፡፡ እንደሚታየው ግን በሌላኛው ጎራ ያሉ አካላት ለዚህ ፈጽሞ ዝግጁ አይደሉምከእውነት በመራቅ የሥነልቡና ቀውሳቸውንና የማንነት ኪሳራቸውን ለማከም ሲሉ የፈጠሩትን የገዛ ፈጠራቸውን በማመንና ሌላውንም አካል ይሄንን ፈጠራ እንዲቀበል ለማድረግ በመጣር በከፍተኛ የሞራል (የቅስምዝቅጠትና የሥነልቡና ቀውስ ውስጥ ሰጥመው ነው ያሉት፡፡ ከዚህ ፈቀቅ ማለት ስለማይፈልጉ ጥቅማቸውን በአማራ መጥፋት ወይም በኢትዮጵያ መፍረስ ላይ መሥርተዋል፡፡ ወያኔ በሚቀጥለው ዓመት የነበረውን እንዳልነበረ ያልነበረውን እንደነበረ የሚያደርግ፣ በሐሰተኛና በፈጠራ ታሪክ የተሞላ የታሪክ ትምህርትን በትምህርት ተቋማት እንዲሰጥ ለማድረግ ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡ በምንም ተአምር ይሄንን ውንብድናና አሳፋሪ አስነዋሪ ተግባር በዝምታ ልንመለከት አይገባም!

ኢሳት እነ ኦነግን ላለማስቀየም ወይም ለማባበል ለማግባባት!” በሚለው የደንቆሮ ፈሊጡ ገና ወደፊት ብዙ የሚያጠፋው፣ የሚያፈራርሰው፣ የሚያሳክረው የአማራና የሀገር ታሪክ፣ እሴቶች መኖራቸው አይቀርምና የብዙኃን መገናኛ ማቋቋማችን የግድ አስፈላጊ የሚሆንበት ምክንያት እንዲህ ዓይነት ድርጊት በተፈጸመ ጊዜ ትክክለኛውን ታሪክ በመናገር ማረሚያ ለመስጠት፣ ሕዝብን ከሚረጭበት የተወናበደና የፈጠራ ታሪክ ሰለባነት ለመታደግ፣ ትክክለኛ ታሪክ የሚናገሩ፣ የጥፋት ኃይሎችን የኋላ ታሪክና የጥፋት ተግባሮች በመረጃ የሚያጋልጡ፣ በሐሳብ የሚሞግቱ ምሁራንንኢሳት እነ ኦነግ ያኮርፉብኛል በሚል ሒሳብ ከእንግዲህ የሚያስተናግድ አይደለምና እንደ እነኝህ ያሉ ምሁራንን ለማስተናገድ፣ ኢሳት በዚህ የደነቆረ ዘይቤው ምክንያት አዳፍኖ የሚያስቀራቸውን በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለሕዝብ እንዲደርስ ለማድረግ፣ በእነዚህ ምክንያቶች ብቻ ሳይሆን ጅርጅቱ ከሕዝብ ጋር የሚገናኝበት፣ ዓላማ ግብ ተግባር ክንውኑን፣ ርዕዮተዓለሙን፣ ትምህርቶቹን፣ መረጃዎችን፣ ዜናዎችን ወዘተረፈለሕዝብ የሚያደርስበት የመገኛ ብዙኃን እጅግ በጣም አንገብጋቢ በሆነ ደረጃ አስፈላጊ ነውና ጉባኤው ራዲዮና ቴሌቪዥን (ነጋሪተወግና ምርዓየ ኩነትበተቻለ ፍጥነት ሊያቋቁም በሚችልበት ሁኔታ ላይ መምከርና ውሳኔ ማሳለፍ ይኖርበታል፡፡


ወደ 3ኛው ነጥብ ሳልፍ፦ የአማራ የፖለቲካ ድርጅት የመቋቋም ዓላማና ግብ ህልውናውን ከፈጽሞ ጥፋት ለመታደግ፣ በሀገርና ሕዝብ ላይ በኃይል ተጭኖ ያለን አንባገነን የጥፋት ኃይል ገርስሶ ለማስወገድና በምትኩም ፍትሐዊና ዲሞክራሲያዊ (መስፍነ ሕዝባዊመንግሥት እንዲቋቋም ለማድረግ ነው፡፡ ይሄንን ለማድረግ ደግሞ ሁሉን አቀፍ ትግል ማድረግ የግድ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ ይሄንን ግብ ለማሳካት የሚፈልገው የገንዘብ ወጪ በጣም ከፍተኛ እንደሆነ መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ በተለይም እኛ እንደ ወያኔና ሸአቢያ ሌሎችም የጥፋት ኃይሎች ሁሉ አሳልፈን የምንሰጠው የምንሸጠው የምንለውጠው የሀገር ጥቅም ስለማይኖርና ማንነታችንም ይሄንን እንድናደርግ ስለማይፈቅድልን ከዚህ የተነሣ እንደ ወያኔና ሸአቢያ ከባዕዳን ልናገኘው የምንችለው ድጋፍና እርዳታ ይኖራል ተብሎ አይገመትም፣ የኢትዮጵያን ባላንጦች ከጎን ማሰለፍ አንችልም፡፡
በዚህ ምክንያት ትግሉን ለማንቀሳቀስ ከፍተኛ የሆነ የአቅም ማነስ ችግር ይፈታተነን ይሆናል፡፡ ሕዝባችንን ጥሬ ቆርጥሞም ቢሆን ለእኔ ይቅርብኝ!” እያለ ትግሉን እንዲደግፍ የማስቻል ጠንካራ ሕዝብን የማንቃትና የማዘጋጀት ሥራ በርትተን መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ ምንም ይሁን ምን ግን በቻልነው መጠን በተንቀሳቀስን ቁጥር፣ ጥረት ባደረግን ቁጥር ወደ ድል የምናደርገውን ጉዞ እየተራመድንና እየተጠጋን በመሆኑ በምንም ያህል መጠን እንንቀሳቀስ እንቅስቃሴያችን የራሱ የሆነ ዋጋ አለውና ልንንቀውና ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም፡፡ ሕዝቡ ትግሉን የራሱ አድርጎ እንዲያስብና እንዲይዘው ካደረግን ይህ የአቅም ውስንነት ፈተና ሊሆን የሚችልበትን ጉልበት ይቀንሳልና የአቅም ውስንነት ፈተናው ተስፋ የሚያስቆርጥ አይሆንም፡፡ ታሪካችንን (የአማራን ታሪክልብ ብለን ካጤነውም ሕዝባችን በሚጨበጥና በሚዳሰስ ኃይል ታምኖና ተመክቶ አይደለም ከዮዲት ጉዲት ጀምሮ ፈጽሞ ሊያጠፋው ከመጣበትና ፈጽሞ ሊያጠፉት ከሚችሉ ከባባድ ፈተናዎቹ የዳነው የተረፈው፡፡ ተአምራዊ በሆነ በአምላኩ በእግዚአብሔር ረድኤት እንጅ፡፡


በመሆኑም ምንም ያህል ተስፋ አስቆራጭ ፈተና ቢገጥመን ትናንት ካሳለፍነው የሚብስ የለምና ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም፡፡ ትናንት ፍጹም ተስፋ አስቆራጭ ከሆነ ፈተናና ጥፋት በታደገን በአምላካችን በእግዚአብሔር ታምነን እንሠማራያለጥርጥርም እናሸንፋለን!!!


እንግዲህ ሐሳቦቸ እነኝህ ናቸው ጉባኤተኛው ከጉባኤው በፊት ይሄንን ጽሑፍ አንብቦ ቢገባ በአንድ ቀን ፈጭቶ ሰልቆ አቡክቶ ለመጋገር በመሞከር ከመቸገር ይልቅ የተቦካውን የመጋገር ያህል ነገሩን ቀላል እንዲያደርገው በማሰብ ነው ይሄንን ጽሑፍ ያዘጋጀሁት፡፡ ጽሑፉን ከማጠናቀቄ በፊት አንድ አጥብቄ ማሳሰብ የምፈልገው ጉዳይ ቢኖር አማራ በአንድ ድርጅት የመጠቃለሉን ነገር የሚቃወሙ ወይም የማይፈልጉ አማራ ነኝ የሚሉ ወገኖች ቢኖሩ አንድም ተራ የሥልጣን ጥመኞች ናቸው ካልሆነ ደግሞ የወያኔ ቅጥረኞች ናቸውና እነኝህን እንቅፋቶች ተረባርቦ በቶሎ ነጥሎ በመለየት ለሕዝብ ማጋለጥ ያስፈልጋል፡፡ ግፍ እየዘነበበት ካለው ወገናቸው ይልቅ የግል ጥቅማቸውን የሚያስቀድሙ ካሉ እነኝህ ለምንም አይጠቅሙምና ተለይተው ወተው በሕዝብ ሊታወቁና ሊወገዙ ይገባል፡፡


የሥልጣን ጥመኝነት ወይም ቅጥረኝነት ካልሆነ በስተቀር ኃይል ሊከፋፍልና ሊያዳክም እንደሚችል እየታወቀ እዚህም እዚያም ተለያይቶ ምንትስ ነኝ!” እያለ ማንም ሁለትና ሦስት ሰው እየሆነ በአማራ ሕዝብ ስም ድርጅትን በየቦታው አቋቋምኩ ሊል አይችልም፡፡ ከጉባኤው በፊት ሁሉም የአማራ ተቆርቋሪ ነኝ የሚል በአማራ ስም የተደራጀ ድርጅትና ማኅበር ሁሉ በዚህ ጉባኤ ተሳታፊ እንዲሆንና ተገልሎ እንዳይቀር ለማድረግ በታዋቂ ሰዎችና በሀገር ሽማግሌዎች ጥረት መደረግ ይኖርበታል፡፡ በምንም ዓይነት መልኩ በዚህ ጉባኤ ላይ ላለመሳተፍ ምክንያት ሆኖ ሊጠቀስ የሚችል ነገር እንዳይኖር መደረግ ይኖርበታል፡፡ የጉባኤው አዘጋጅ ወይም ጋባዡ ዳግማዊ መአሕድና እያንዳንዱ አማራ በተለይም የልኂቃኑ ክፍል ይሄንን የማድረግ ኃላፊነትና ግዴታ አለበት፡፡ የእኛም የዳግማዊ መአሕድም ስም ፈርሶ ሁላችንንም የሚያጠቃልል አዲስ የጋራ ስምና አዲስ ኃላፊዎች (አመራሮችይመረጡ!” የሚሉ አካለት ቢኖሩ እንኳ ጉዳያችን አንገብጋቢውና ጊዜ የማይሰጠው የሕዝባችን ህልውና ጉዳይ ነው እንጅ የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ስምና ኃላፊዎች የመለወጥ ጉዳይ አይደለምና በምርጫው የወያኔ ቅጥረኛ ሰርጎ እንዳይገባ ጥንቃቄ በተሞላበት አኪያሔድ ይሄን እስከ ማድረግ ድረስ የዳግማዊ መአሕድ አመራሮችና ጉባኤው ፈቃደኛና ዝግጁ ሊሆን ይገባል እላለሁ፡፡


አደራአደራአደራበምንም ዓይነት መልኩ ይህ ጉባኤ ሁሉንም አሳትፎ የተሳካ ውጤት ማስመዝገብ አለበት እንጅ መክሸፍ የለበትምና ሁሉም ሽኩቻንና ሌሎች ነገሮችን ትቶ በግልጽና በስውር በሚወሰዱ ጥቃቶች እየተፈጀ እያለቀ ያለውን የወገኑን ጉዳይ በማስቀደም አሁን አንድ የሆነ ደረጃ ላይ መድረስ ይጠበቅብናልና የማታስተውሉ ግለሰቦች ካላቹህ እባካቹህእባካቹህበፈጣሪ ስም ልለምናቹህኃላፊነት ይሰማቹህበተረፈ አደራ አደራ አደራ!!!


ወገኔ ሆይ ትግልህ አማራጭ በሌለው ሁኔታ መራራ ነውና ባጭር ታጠቅ!!!


ልዑል እግዚአብሔር ጉባኤውን የተሳካ ያድርግልንአሜን!!!


ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!


ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው


amsalugkidan@gmail.com

                                                                              http://www.ethiopanorama.com