April 27, 2017

በብዙ ነገሮች ከመሠረታዊ መረጃ ሕዝቡ እንዲያፈነግጥ በማድረግ ትኩረትን ማዛባት እጅግ እየበዛ ነው፡፡ እኔ እንደመሠለኝ አብዛኞቹ ሚዲያዎች መጻፍ በሚችሉ ግን መረጃን አንሻፈው ለሕዝብ በሚያደርሱ ጸሐፍት ተወርሰዋል፡፡ የግል አስተያየት መስጠት ማንም ሰው መብቱ ቢሆንም ለሚሰጠው መረጃ ሀላፊነት የማይሰማው ከሆነ ወይም ልዩ ሴራን ለማሳካት በመሠሪነት የተዛባ መረጃን የሚያስተላልፉ ከሆን አደጋው የከፋ ነው፡፡ በቀጥታ ለዚህ ጽሑፌ ያበቃኝን ጉዳይ ልጠቁምና እኔ ከሥር መሠረቱ ስለማውቀው ነገር ልናግር፡፡ ሰሞኑን አንድ ቆንጂት የተባለች ጸሀፊ ኃይሌ ገብረሥላሴ ጤፍን ለደቾች(ኒዘላንድ) አሳልፎ እንደሰጠ አደርጋ ለሕዝብ አስነብባለች፡፡ ይህ ጽሑፍ ፍጹም ውሸት ከመሆኑም በላይ ዓላማው ሕዝብን በተሳሳተ መረጃ ማባዘን ይመስላል፡፡ ጸሀፊዋ ስለዚህ ጉዳይ የወሬወሬ ሰምታ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ቀላሉን ነገር እንኳን አጣርታ የምታውቅ አልመሰለኝም፡፡ የሕዝብን ትኩረት ለመሳብ ይመስላል በግዙፍ ቃላቶች ግን አንድም እውነት የለሌበት ታሪክ ነው ለሕዝብ ያስነበበቸው፡፡ ከትንሹ ወደ ትልቁ ልሂድ፡፡ በመጀመሪያ ጤፍ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝ የሚለው መቼም ቢያንስ ኤርትራ ጤፍ እንደምታመርት እናውቃለን፡፡ ከዛ በተረፈ ግን ጤፍ በሌሎች አገሮችም እንደኛ ለምግብነት ባይሆንም ይመረታል፡፡ የጤፍ ለደቾች ተላልፎ የተሰጠበት ሂደት ግን ኃይሌ የሚያውቀው ጉዳይ አደለም፡፡ ሂደቱን ቀለል አድርጌ ልግለጸው. ጤፍን ለደቾች የሰጣቸው በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ተቋም የደብረዘይት ምርምር ማዕከል ነው፡፡ መጀመሪያ የወጣው በምርምር ሥም ነበር፡፡ ሆኖም ግን ለደቾችት ተሰጠ የተባለው የጤፍ መጠን ለምርምር ሥራ ከሚውለው በጣም የበዛ ስለነበር ተመራማሪዎቹ ወይ ተሸውደዋል ወይ ደግሞ ሸጠውታል፡፡ 12 ዝርያዎች ነበሩ መጠኑን መናገር አልፈለኩም ምክነያቱም በትክክል የተባለው ላይሆን ይችላል፡፡ ይህ የሆነው በፈረንጆች 2004 በፊት ነው፡፡ በኋላ ላይ የደቹ ምርምር ተቋም ይመስለኛል ኡትሬክት ዩኒቨርሲቲ ለሶይል ኤንድ ክሮፕ ለተባለ ድርጅት ዝርያዎቹን አሳልፎ ይሰጣል፡፡ ከዛይ ይህ ድርጅት ጤፍን ለዳቦ እንዲሆን አደርኩት በሚል የባለቤትነት መብት ለአውሮፓ ሥነምርምር ባለቤትነት አስከባሪ ተቋም ያመለክታል፡፡ በዚህ ሂደት አንድ ካናዳ የሚገኝ አንቲ ባዮ ፓይሬት(የሥነሕይወት ባለቤት ገፋፊዎችን የሚከስ) ድርጅት የደቹን ድርጅት ሥራ ለዓለም ያጋልጣል፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ ነበር ይሄ ድርጅት በቀጥታ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመፈራረም መብቱን ኢትዮጵያ ሰጥታኛለች ለማለት ኢትዮጵያ መጥቶ ውል የፈጸመው፡፡ ይህ ውል ሲፈጸም የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ተቋም ዋና ሰጭ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ተቋም የዝርያዎቹ ባለቤት፣ የደቹ ሶይል ኤንድ ክሮፕ የነበረው ሲፈራረም ኸልዝ ፎድ ኤንድ ፐርፎረማንስ ተብሎ ተቀባይ በኢትዮጵያ የደች ኤምባሲ፣ ዶ/ር ተወልድ ብርሀን ገብረእግዚአብሄር (የፍስሀ ገብረእግዚአብሔር ወንድም)ና ኃይሌ ገብረስላሴ ምስክር ሆነው በፈረንጆች 2005 ውሉ ተፈረመ፡፡ ያችን ፊርማ እንዳገኙ ድርጅቱ ትቶት የነበረውን የፓተንት ማመልከቻ እንደገና ቀጠለ፡፡ ብዙ ሰዎች ፓተንቱ እንዳይሰጠው ሞክረው ነበር ግን ከኢትዮጵያ ወገን ባለቤተ ሆኖ የቀረበ በመጥፋቱ ከብዙ ጊዜ በኋላ በፈረንጆች 2008 ሕዳር መሠለኝ የተሰጠው፡፡

እንግዲህ ጸሐፊዋ ይችን ኃይሌ ምስክር ሆኖ የተሳተፈባትን ፊንጭ ሰምታ ሊሆን ይችላል፡፡ ኃይሌን ለምስክርነት ያበቃው በወቅቱ ከኒዘርላነድ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ሥለነበረው ይመስላል፡፡ በኋላ ላይ ድርጅቱ ጤፍን ሲያዋድድ የነበረውም የኢትዮጵያ አትሌቶች እንዲህ አለምን የሚያስደምሙት ጤፍ እየበሉ ነው ሲል ነበር፡፡ ያም ሆን ይህ ግን ኃይሌ ስለጤፍ መውጣት ጉዳይ የማያውቀው ነገር መጣበት እንጂ እሱ እጁ የለበትም፡፡ ይልቁንም ብዙ በሙያው የነበሩ ባለሙያዎች ሊጠየቁ በተገባ ነበር፡፡ የደቹ ካመፓኒ ለኢትዮጵያ ሊሰጣቸው ቃል የገባቸው ብዙ ጥቅሞች ነበሩ፡፡ ሆኖም ኋላ ላይ ከሥሬያለሁ በማለት ሥሙን ቀይሮ መሥራት ጀመረ፡፡ የባለቤትነት መብቱን በተመለከተም ኃይሌ የሚሰጠውና የሚነሳው ጉዳይ አደለም፡፡ ይህ የሚሆነው በስነምርምር ባለቤት አስከባሪ ተቋማት ነው፡፡ ሰውዬውም ይህን ያገኘው ከአውሮጳው ተቋም ነው፡፡ ለአሜርካውም አመልክቶ ነበር ያግኝ አያግኝ አላውቅም፡፡ ፈራሚዎቹ የነበሩት እኮ የተማርን ነን የሚሉ ነበሩ፡፡ ከዚህም ያለፈ ሥህተት ተሰርቷል፡፡ ጉዳዩ እስከዛሬም እንደተወዛገበ ነው፡፡   እውነታው ይህ ነው፡፡ ለመረጃ ያህል እንጂ ይህን አስመልክቶ ብዙ ጥፋት ያጠፉ ሌሎች ግለሰቦች አሉ፡፡

ስለ ኃይሌና ጤፍ ይህን ካልኩ ሕዝብ በተሳሳተ መረጃ ከትክክለኛ መንገድ እየወጣ ነው፡፡ በተለይ ዲያስፖራው እንደፈለጋቸው ለሚዘውሩት ተመችቷል፡፡ የሀገር ቤቱን ጉዳይ በትክክል እየተከታተለ ሕዝቦን ወደ ሥኬት የሚያመጣ ሥራ የሚሠራ አንደም አይታይም፡፡በውጭ የሚኖሩ ተቃዋሚ በሉት፣ ሚዲያ ሌላ ድርጅት ከገንዘብ ጋር እንጂ ከኢትዮጵያ ጋር ባለው ትኩረት ተስፋ አስቆራጭ ነው፡፡ በአሁን ጊዜ ትልቅ የሚያሰኘው ጥሩ ተቃዋሚ መስሎ ማውራት ብቻ ነው፡፡ በብዛት ደግሞ የወያኔ ሰላዮች ናቸው ወሬውን የሚያናፍሱት፡፡ የሚጠይቅ የለም፡፡ ዝም ብሎ አብሮ ማናፍስ እንጂ፡፡ ብዙ ሚዲያዎች አሁን እየሰሩ ያሉት ሰውን በወሬ ማጦዝ ላይ ነው፡፡ ትክክል የሚሰሩ ሰዎች ከኋላ ሥም ይለጠፍላቸዋል፡፡ ሰሞኑን ፕ/ር ኤፍሬም ይሳቅና ኃይሌ ጀመሩት የተባለው ወያኔን የማዳን ሽምግልና ትክክለኛ መረጃ አይመስለኝም፡፡ ሰው ከሜዳ ተንስቶ ያወራል፡፡ አንድ ነገር አውቃለሁ ኤፍሬምም ኃይሌም ከብዙዎቻችን ዜጋ በተሸለ አስተዋጾ አድርገዋል፡፡ በ97ቱ መርጫ ጊዜ ያደረጉት የሽምግልና ስኬት የሚያስመሰግናቸው እንጂ የሚያስወቅሳቸው አደለም፡፡ ቀጥሎም ብዙ አስበው ነበር፡፡ ነገሮች በሌሎች ሰዎች ጣልቃ ገብነት ቀሩ እንጂ፡፡ ያን ሁሉ ሲደረግ እነዚህን ሰዎች የረዳችው አልነበረም፡፡ ኃይሌ ብዙ ወጪዎች እንደሸፈነ አውቃለሁ፡፡ ኤፍሬም ብዙ አስበው ነበር፡፡ ተቃዋሚ ተብዬዎች የራሳቸውን ድክመት በኤፍሬም ለጠፈው የኤፍሬም ጥረት እንዳይሆን ሆነ፡፡ ከኤፍሬም በላይ ለኢትዮጵያ አስባለሁ የሚል ካለ በሥራ ይመዘን፡፡ ኤፍሬም በዘመናቸው ሁሉ ኢትዮጵያን ወክለው የሚኖረ ሰው ናቸው፡፡ የሚለብሱት ሳይቀር ምስክር ነው፡፡ አሁን እየሞከሩት ናቸው የተባለው ሽምግልና በህወሐቶች መካከል ነው ወይስ በኢትዮጵያ የተሻለ ነገር እንዲመጣ; ይሄን ማንም ሊመልስልኝ አይችልም፡፡ ምክነያቱም ሁሉም የሚፈልገው ተቃርኖን ነው እንጂ የኢትዮጵያን ሰላም አይመስለም፡፡ ይህን መረጃ ለማግኘት ራሴው አሞክራለሁ፡፡ ኤፍሬምና ኃይሌ እንደሰው ሊሳሳቱ ይችላሉ ግን እነሱ ላይ የራስን ድክመት ከመለጠፍ ራስን ማይት ነው፡፡ በተቃራኒው    አንዳንድ ለዘመናት የልባቸውን ሰርተው አሁንደ ደግሞ ዲያስፖራውን ተቀላቅለው ሌላ ምዕራፍ ሥራቸውን የሚሰሩት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቷቸው እናያለን፡፡

ይልቅ ሰሞኑን የደህንነት ኃላፊ ነበርኩ ባዩ የተናገሩት ነገር ለእኔ የሚዋጥ አደለም፡፡ ግለሰቡ በአገለገሉበት 20 አመት ስንቱን አስገድለው  ስንቱን አሳስረው ሌላም ሌላም አድርገው ነው ዛሬ ጻድቅ የሆኑብን፡፡ ያ ባይሆን 20 ዓመት የሰሩለት ቡድን ራሱ አያኖራቸውም ነበር፡፡ የተናገሩትም የተለየ ነገር ሳይሆን ማንም ሰው ሥራዬ ብሎ ቢከታተል የሚደርስባቸውን ወሬዎች ነው፡፡ ይልቁንም ወያኔ እንዴት እንደተወሳሰበ ሊያገዝፉት ነው የሞከሩት፡፡ ሰው ጠፍቶ እንጂ የወያኔ ኢነተለጀንስ ቀፎ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ወያኔ ከጫካ ጀምራ በወሬ ነው የምትፈታው፡፡ 20 ዓመት ሰራሁ የሚሉት ግለሰብን ንግግር ራሱ ላስተዋለው የወያኔ ቡድን ምን በምን አይነት ብቃት ላይ ያሉ ግለሰቦችን እንዳሰማራ እናያለን፡፡ የወያኔ ሴኩሪቲ በቃ በሆድ አደሮች የተሞላ እንጂ የሴኩሪቲ ችሎታ ያላቸው አደሉመ፡፡ ለመሆኑ እኚህ ግለሰብ አሁን እየሰሩ ያሉት 20 ዓመት ላገለገሉት ቡድን ላለመሆኑ ምን ማስተማመኛ አለ፡፡ አያሌው ስለተባሉ; አማራ ስለሆኑ; አማራውን እኮ ሲያስፈጁት ነበር እኮ፡፡ ሰውዬው በየተቃዋሚዎቹ ተሰግስገው ያሉት የወያኔ ሰላዮች ናቸው እያሉን እክ ነው፡፡ በእርግጥም ሊሆን ይችላል፡፡ ምክነያቱም ተቃዋሚዎቹ መጀመሪያም ድርጅት ሲመሰርቱ ለእንጀራ ብለው እንጂ ለነጻነት ለመታገል አደለም፡፡ ሰውዬው ግን እያሉ ያሉት ማንንም አትመኑ ተስፋ ቆርጣችሁ ተቀመጡ አይነት ነው፡፡ ከአልሆነ እንዲህ ያለውን በመረጃነት ያን ያህል የማይረባ ነገር ለምን ያወራሉ፡፡ እሽ ወያኔ በየድርጅቱ የራሷን ሰው አስገብታለች፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ ዛሬ ጸረ ወያኔ ሆኖ ወያኔን መህሏ ገብቶ ለታሪክ እንዳትታሰብ ማድረግ እንዴት አልተቻለም; ዛሬም ኤርትራ ነን የሚሉት ግንቦት 7 ና አያሌ ሌሎችስ አሁንም እየታገልን ነው ብለው ሊነግሩን የሞራል ብቃቱ አላቸው; እነዚህን እየጠቀሱ ነው ወያኔዎች እንግዲህ የሚኖሩብን፡፡ እጁ ላይ ሰባራ ስንጥር የሌለውን መረራን ለምን አሰሩት; እነ እስክንድር ነጋ ለምን ኢላማ ተደረጉ; የወያኔ ሴኩሪቲ የምትሉት ሊቋቋማቸው እንደማይችል ስለሚታወቅ እኮ ነው፡፡ ትንሽ መሻሪያ ይዞ የተጠጋ ቢኖር ወያኔ እድሜዋ ቢበዛ ጥቂት ወራት በሆነ፡፡ ይልቅ ነውር የማያውቁ ግግም ያሉ ደጋፊዎች ሞለተዋታል፡፡ ወያኔ በጭካኔና በወሬ ሕዝቡን ማሸበር ነው እኮ አንደ ተለየ ጥብቅ ሴኩሪቲ ያለው ያስመሰላት፡፡ ይልቅ አሁን መሠራት ከአለበት መሐላቸው ገብቶ መበታተን ነው፡፡ ለዚህ በመንግስት መዋቅር ሥር ያሉ የክልልም የፌደራልም ሰራተኞች ሆነው ኢትዮጵያ ነገር የሚቆጫቸው ወሳኝ ሚና ይቻወታሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ወያኔ ከሠራዊቱ ሀላፊነት ማሰወጣት ነው፡፡ በውድ ሳይሆን በግድ፡፡ ወሳኝ ከተባሉ ተቋማትም እንዲሁ፡፡ ወሬ ማብዛት አያስፈልግም፡፡ መረጃ አለኝ ያሉት ግለሰብ መረጃውን ይህን ሊሰሩ ለሚችሉ ይስጡት፡፡ ሚዲያ ላይ ማውራት አደለም፡፡ ሲጀምር የሚሰጢር ነገር ከሆነ ለሚዲያ አደለም መቅረብ ያበት፡፡ እርምጃው ከውሥጥ ሊሆን ይገባል፡፡ ይህ ነው መሆን ያበት፡፡ 10 ዓመት ሙሉ ኤርትራ ተቃዋሚ ነኝ እያሉ አይንን በጨው ታጥቦ የሕዝብን ነጻነት እታገላለሁ ከሚሉ በላይ ከእንግዲህ ጠላት የለንም፡፡ ሁሉም በየፊናው የበኩሉን ያድርግ፡፡ ኢትዮጵያውያን ነን የምትሉ ራሳችሁን አውጡ፡፡ ዲያሰፖራ ፖለቲከኞችና ሚዲያዎች ቢዚነስ የሚሰሩበት ሕዝብ መሆን ይብቃ፡፡ ወያኔ እንዲህ አደረገኝ እያሉ ማላዘኑ ይብቃ እኔም እነድህ አደርኩት ማለትን እንቻል፡፡ ወያኔወችን እኛ እንሰልላቸው፡፡ እነሱ አደሉም፡፡

አመሰግናለሁ!

እግዚአብሔር ኃይሉን ይስጠን!

ልዑል እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይጠብቅ!

አሜን!

ሰርጸ ደስታ