ግርማ ሠይፉ ማሩ

ግርማ ሠይፉ ማሩ

ግርማ ሠይፉ ማሩ

በሀገራችን ኢትዮጵያ የሕግ አወጣጥ ሥርዓት ችግር እንዳለበት ለማወቅ ብዙ የሚጠቀሱ ሕጎች ቢኖሩም አሁን ረቂቅ ተብሎ በእጃቸን የገባው “የኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ላይ ያለውን ሕገ-መንግስታዊ ልዩ ጥቅም ለመወሰን የወጣ አዋጅ” በሚል ርዕስ የገባው የቅርቡ እና ወሣኙ ይመስለኛል፡፡

ይህ ረቂቅ አዋጅ “የኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም ዝርዝር በሕግ እንደሚወሰን በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ (5) ስለሚደነግግና ይህንን ሕግ ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣” ይላል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ፈንፊኔ የሚል ቃል የለውም ሕገ መንግሥቱ ሲጠቀስ ቃል መቀየር አይቻልም፡፡ ይህን ማድረግ ካስፈለገ ሕገ መንግሥቱ መሻሻል ነው ያለበት፡፡ ይህ ብቻም አይደለም ፊንፊኔ በአዲስ አበባ የአንድ አካባቢ መጠሪያ ነው እንጂ አጠቃላይ አሁን አዲስ አበባ ለሚባለው አይደለም፡፡ ስለዚህ ይህ አካሄድ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ይህ ሕገ መንግሥት በቃላት ጭመራና ቅነሣ መሸርሸር ከጀመረ ቆይቷል፡፡ ሕገ መንግሰቱ ለምሣሌ ዘላን እንጂ አርብቶ አደር የሚል ቃል አይጠቀምም፡፡ የኢትዮጵያ ሱማሌ የሚባል ክልል በሕገ-መንግሰት ውስጥ የለም፡፡ ድሬዳዋ የሚባል የከተማ መስተዳድርም በሕገ መንግሥት የለም፡፡

በጣም የሚያስገርመው ደግሞ አንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ 5 ተግራዊ የሚያደርግ አዋጅ ለማውጣት ከ49/2 -49/4 ያሉትን የሕገ መንግሰት ድንጋጌዎች ከጫወታ ያስወጣቸዋል፡፡
• 49/2 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር እራስን በራሱ የማስተዳደር ሙለ ስልጣን ይኖረዋል፡፡ ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል፡፡ በዚህ ረቂቅ አዋጅ መሰረት ከተማ መስተዳደሩ በዚህ አዋጅ በሚቋቋም ጉባዔ እንዲሁም ደግሞ በቀጥታ በኦሮሚያ ጨፌ ጣልቃ ይገባበታል፡፡\

• 49/3 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተጠሪነቱ ለፌዴራል መንግሰቱ ይሆናል፡፡ ቢልም አሁን ሌላ ተጠሪ የሆነ አካል ጉባዔ እና የኦሮሚያ ጨፌ ተደንግጎለታል፡፡

• 49/4 የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በዚህ ሕገ-መንግሰት በተደነገገው መሰረት በፌዴራል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይወከላል፡፡ ቢልም በዚህ ረቂት አዋጅ መሰረት ግን ቀድሞ ለኦሮሞ ተወላጆች 25 ከመቶ ወንበር መልቀቅ ይኖርበታል፡፡ በዚህ አይበቃም የሕገ መንግሥቱን አንቀፅ 25 “የእኩልነት መብትን” ይፃረራል፡፡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የየትኛው ብሔር አባል መሆናቸው ለልዩነቱ መሰረት መሆኑ ደግሞ ግልፅ የሕገ መንግሰት ድንጋጌ ጥሰት ነው፡፡

በዚህ ረቂቅ አዋጅ የትርጉም ክፍል “የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች” ማለት የአዲስ አበባ ከተማ ከመመስረቱ በፊት ጀምሮ ነባር ነዋሪ የነበሩ ወይም አሁንም በከተማው ነዋሪ የሆኑ ኦሮሞዎች ማለት ነው፡፡” ይላል፡፡ አዲስ አበባ ከተመሰረተች 125 ዓመት ሲሆን፤ ኦሮሞ የሚባል ክልል የተመሰረተው ደግሞ 25 ዓመት ቢሆን ነው፡፡ ይህ ብቻም አይደለም መሬቱ ቀድሞ የኦሮሞዎች ነበር ከተባለ ከዚያ በፊት የማን ነበር? ኦሮሞዎች እንዴት በቁጥጥራቸው ውስጥ አደረጉት? ብሉ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ በ `systeme thinking` የአንድን ችግር መሰረታዊ የሆነውን መንሥዔ ለመረዳት አምስት ጊዜ “ግን ለምን? but why five times” ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይጠቅማል ይላል፡፡ ለዚህም ነው ከኦሮሞ በፈት አሁን አዲስ አበባ በምትባለው መሬት ላይ እነማን ይኖሩ እንደነበር? ብሎ መጠየቅ አስፈላጊ የሚያደርገው፡፡ የዚህ መልስ ሲገኝ ነው በአዲስ አበባ ለሚኖሩ ኦሮሞዎች የተለየ ጥቅም የምንሰጠው፡፡ ምድር ስትፈጠር ጀምሮ ኦሮሞዎች አዲስ አበባ ነዋሪ ነበሩ የሚለን የምናገኝ አይመሰለኝም፡፡
ይህ ረቂቅ አዋጅ በአንቀፅ 8 “የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች መብት” በሚል ርዕስ አንድም እርባና የሌለው የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች እንደማነኛውም ሰው ሊከበርላቸው የሚገባን መብት ይጠቅሳል፤ የሚያሳዝነው በአንቀፅ 10 መርዕ አልባ “የልዩ ጥቅሙ መርሆዎች” በሚል ያስቀምጣል፡፡ እነዚህም፤

1. የከተማ አስተዳደሩ የሚያወጣቸው ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ ሕጎችና ዕቅዶች የከተማው ነዋሪ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ሕገ መንግስታዊ መብቶች የሚያስከብር መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ ይህ ከላይ የገለፅኩትን የእኩልነት መብት አንቀፅ 25 የሚፃረር ነው፡፡

2. የከተማ አስተዳደሩ የሚያወጣቸው ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ ሕጎችና ዕቅዶች የነዋሪ የኦሮሞ ተወላጆችን ጥቅሞችና ፍላጎቶች ግምት ውስጥ ያስገባና መብቶቻቸውን የሚያስከብር መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡

3. የመስተዳድሩ ምክር ቤት ከክልሉ መብቶችና ጥቅሞች ጋር በሚያያዙ ጉዳዮች ላይ በሚሰጠው ውሣኔ የክልሉን ጥቅሞች ከግምት ውስጥ በማስገባት ይወስናል፡፡
ይህን የሚያነብ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ያልሆነ አዲስ አበቤ ነዋሪ ለምን ግብር እንደሚከፍ ደጋግሞ ያስባል፡፡ በዓለም ላይ የዚህ ዓይት መርዕ አልባነት ያለባቸው ተሞክሮዎች ካሉ ለመማር ዝግጁ ነኝ፡፡ እነደ ሰው መብት ከመጠየቅ ወርዶ በብሔር ተወላጅነት የሚገኝ መብት አሳዛኝ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ጥያቄ በዕዳጣን/አነስተኛ ቁጥር ባላቸው ሕዝቦች ቢጠየቅ በድምፅ ብልጫ ከጫወታ ውጭ እንዳይሆኑ ሊረዳ ይችላል የሚል ቅን ሃሳብ ማንሳት ይችላል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን የዚህ መርዕ ደራሲያን ማፈር አለባቸው፡፡ መርዕ አልባ ዘረኞች ናቸው፡፡
አንቀፅ 11 “.ስለ አስተዳደራዊ ጥቅሞች” በሚል ርዕስ

• በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ውስጥ ነዋሪ የሆነው የኦሮሞ ተወላጆች የራሳቸውን እድል በራሳቸው የመወሰን መብት ይኖራቸዋል፡፡ ምን ማለት ነው? የገባው ካለ ቢያስረዳኝ፡፡ መገንጠል ይችላሉ ለማለት ነው? እኔ እሰከሚገባኝ ማንኛውም ዜጋ የራሱን እድል ወሣኝ እርሱ ብቻ ነው፡፡ የኦሮሞ ተወላጆች የራሳቸው እድል የሚባለው ነገር ምንድነው? አሁን ባለው መረጃ የአዲስ አበባ ነዋሪ 49 ከመቶ አማራ፤ 20 ከመቶ ኦሮሞ፤ 17 ከመቶ ጉራጌ እና 6 ከመቶ ትግራይ ነው፡፡

• በከተማው መስተዳደር ም/ቤት ውስጥ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች እንደ ከተማው ነዋሪ ያላቸው ውክልና እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከምክር ቤት ወንበር 25% የማያንስ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች ብቻ የሚወከሉበት መቀመጫ ይኖራቸዋል፡፡ ማለት ሕገ-መንግሥቱን አንቀፅ 25 የእኩልነት ድንጋጌ ጋር ይጋጫል አይገፀውም፡፡

• ሌላው አስገራሚ ድንጋጌ ደግሞ “በኦሮሚያ የመንግስታዊና ህዝባዊ ድርጅቶች መስሪያ ቤቶች ውስጥ ወይም ጉዳዮች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ወንጀል ሰርተው ወደ ፊንፊኔ/አዲስ አበባ በመምጣት የሚደበቁትን ተጠሪጣሪ ወንጀለኞች የክልሉ ፖሊስ፣ አቃቤ ህግና ፍርድ ቤቶች የመመርመር፣ የመያዝና የመቅጣት ሙሉ መብት ይኖራቸዋል፡፡” የሚል ክልሉ ማነኛውንም የተለየ አመለካከት ያለውን ዜጋ አድኖ ለማያዝ ያለውን ፍላጉት የሚያሳይ ነው፡፡ ይህን አንቀፅ ሳነብ በኤርትረና ኢትዮጵያ ጫጉል ዘመን ሻቢያ ሲሰራ የነበረው አፈና ትውስ አለኝ፡፡ ይህ አዋጅ ቶሎ ፀድቆ ይህን ተቃውሞ ያሰመን ዜጎች በኦሮሚያ ጉዳዮች ላይ ወንጀል ፈፅማችሁ ተብለን እንደማንታሰር ማረጋገጫ የለንም፡፡

አንቀፅ 13 ባህላዊና ታሪካዊ መብቶች በሚል ርዕስ ታሪክ በጉልበት ሊጭኑብን ይፈልጋሉ፡፡ “በፊንፊኔ/አዲስ አበባ የሚኖረው የዛሬውና መጪው ትውልድ የፊንፊኔን ታሪክ በተዛበ መልኩ ሳይሆን ኦሮሞዎች ይኖሩበት የነበረች ጥንታዊ መሬታቸው እንደነበረችና በኃይል ተገፍተው ወደ ዳር በመገፋታቸው ቁጥራቸው እየተመናመነ መሄዱንና ወደ አናሳነት መቀየራቸውን ህዝቡ እንዲያውቅና እውቅና እንዲሰጥ የከተማ አስተዳደሩ በትምህርት ስርዓት፣ በሚዲያ፣በህዝባዊ መድረኮችና በመሳሰሉት የመስራት ግዴታ ይኖራዋል፡፡” ይልና ቀጥሎም በመስተዳድሩ ውስጥ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የታሪክ ማስተማሪያ መፃሕፍት ውስጥ የኦሮሞ ህዝብ የፊንፊኔ/አዲስ አበባ የጥንት ነባር ሕዝብ መሆኑን አዲሱ ትውልድ እንዲገነዘብ ይደረጋል፡፡” ይላል፡፡ ከላይ ከኦሮሞ በፊት ማን ነበረ ብሎ የማይጠይቅ ትውልድ፣ የፈለግነውን የምንጭነው አዲስ ትውልድ አለ ብለው መገመታቸው ያስገርማል፡፡ የኦሮሞ ተወላጆች በሀይል ተገፍቶ ነው ብለን ለማስተማር ሀይል የተጠቀመው ብሔር ደግሞ የቱ ነው? ብሎ ጥያቄ ይኖራል:: መቼም ዛሬ አማራ እንደማይባል ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

አንቀፅ 14 ሰለ ኤኮኖሚያዊ ጥቅሞች እንዲህ የሚል ድንጋጌ አላት “በከተማው የሚኖረው የኦሮሞ ተወላጅ ከመሬቱ ያለመፈናቀል ሙሉ ዋስትና አለው፡፡” ይህን አንቀፅ የፃፈ እጅ ያመነጨ ጭንቅላት እንዴት እንደሚባል ማሰብ ነው፡፡ ከዛንችስ ነዋሪ የሆነ የኦሮሞ ተወላጅ ለብቻው ከመሬቱ ያለመፈናቀል መብት አንዴት እንደሚተገበር አስቡት፡፡ ሌሎቹም እንዲሁ ዝባዝንኬ ናቸው፡፡ ምን እንደሚሻለን አይገባኝም በፌስ ቡክ ጫጫታ የሚመራ መንግሰት፤ መንግሰት ብለን መኖራችን እራሱን እኛንም ትዝብት ላይ የሚጥል ነው፡፡
ሌላው ሀብታሙ አያሌው ነቅሎ መትከል የሚለውን ነገር ያስታወሰኝ ድንጋጌ ደግሞ፤

“የከተማ ነዋሪ የሆነው የኦሮሞ ተወላጆች በንግድና በሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የስራ መስኮች ውስጥ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እንዲያድግ የድጋፍ ርምጃዎችን በመውሰድ ነባሩን የኦሮሞ ህዝብ በከተማው ከሚኖረው አብዛኛው ማህበረሰብ ጋር ፍትሃዊ የሐብት ክፍፍል እንዲኖር የከተማ አስተዳደሩ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ግዴታ አለበት፡፡” ይህ ግዴታ ለመፈፀም መቼም ከዚህ በፊትም ያለ ልምድ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የቀድሞውን ኮሚኒኬሸን ሚኒስትር ጌታቸው ረዳን ስጠቅስ የሚናደዱ ይኖራሉ፡፡ ቢሆንም ግን በሥልጣን ማብቂያው ላይ ከሸገር ሬዲዮ ጋር ባደረገው ቆይታ “ችግሩ ስርዓት ፍትሓዊ ይሁን ሳይሆን እናንተ በቃችሁ ተረኛ እኛ ነን” የሚል ሃሳብ ሰንዝሮ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ተሰልፈን በበቂ ሁኔታ የኦሮሞ ተወላጆች ካገኙ በኋላ ጥቅም ለማግኘት እንሰለፋለን፡፡ የኤኮኖሚ ተጠቃሚነት በድካምና ጥረት፣ መሆኑ ቀርቶ ለተወሰኑ ብሐር ተወላጆች ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ግዴታ በማስቀመጥ ሲሆን ያሳዝናል፡፡

አስገራሚው ነገር ደግሞ በአዲስ አበባ ላይ ልዩ ጥቅም የሚያገኘው የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ የዛሬ ሁለት ዓመት ምን አልባትም ሁለት ወር አዲስ አበባ ከጭሮ ወይም ከወለጋ የመጣ ይሆናል፡፡ መብት የሚነፈገው እና ሁለተኛ ዜጋ የሚሆነው ደግሞ ምን አልባትም የዛሬ መቶ ዓመት ወይም ከዚያ በለይ ወደ አዲስ አበባ የመጣ ጉራጌ፣ አማራ ትግሬ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ብቻ አይበቃም፤ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ከአዲስ አበባ በሀይል እንዲወጡ በማድረግ በፈፀሙት ወንጀል እስር ቢቀርላቸው ካሣ መክፈላቸው፣ ብሎም መሸማቀቅ ይጠብቃቸዋል፡፡

በሕገ መንግሰት ድንጋጊ መኖሩን አዲስ አበባን ልዩ ቢያደርጋትም ኦሮሞ በዙሪያቸው የሚገኝ ሌሎችም አሉ፡፡ ለምሣሌ ሐረር፡፡ ሲዳማም በአዋሳ ከተማ ልዩ መብት ይኑረኝ ብሎ መጠየቅ አለበት፡፡ በተጨማሪ መሬቶች ወደቀድሞ ባለይዞታቸው ይመለስ ልዩ ጥቅም ይገባቸዋል ከተባለ አሁን በሁሉም አካባቢ ያሉት በሰዎች ዝውውር የተፈጠሩ ከተሞች ለቀድሞ ነዋሪዎች ልዩ ጥቅም መስጠት አለባቸው፡፡ ለምሣሌ መቀሌ ለእንደርታ ልዩ ጥቅም መስጠት ይኖርባታል ማለት ነው፡፡

ለማነኛውም ወዳጄ ሰዩም ተሸመ ይህን ጉዳይ ከሕገ መንግሰት ጥሰት ጋር በደንብ አድርጎ አስቀምጦታል፡፡ ይሕ ረቂቅ አዋጅ ከሆነ በእኔ እምነት መሰረት አደረኩት ያለውን ሕገ-መንግሰት ቀዶ የጣለ ይሆናል፡፡ ሕገ መንግሰቱም አይረቤና ባለቤት የሌለው እንደሆነ የሚረጋገጥበት ይመስለኛል፡፡ ይህ ረቂቅ አዋጅ ሊፀድቅ የሚቀርበው በኦሮሚያ ጨፌ ቢሆን ሊያስገርም አይችልም፣ የሌሎች ብሔር ተወካይ ነን የሚሉም በሚገኙበት የፌዴራል ምክር ቤት ነው፡፡

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለነገሩ ከከተማው መስተዳድርም ሆነ አሁን ጥቅም ተብለው የተዘረዘሩትን ነገሮች በተግባራ ከተዋቸው ቆይቷል፡፡ እንደዛ ባይሆን ኖሮ ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በሚወጣጡ የከተማ ኑሮ ዘይቤ በማያውቁ ሰዎች አይመራም ነበር፡፡ እስኪ ኢህአዴግ ከገባ ጀምሮ የአዲስ አበባ ልጅ በዚህ ደረጃ ሃላፊ ነበር ሊባል አይችልም፡፡ ይህን ዝምታ ግን ጠብ ያለሽ በዳቦ እንደማለት ነው፡፡
እንደ ኤርሚያስ ለገሠ የአባይ ፀኃዬ እና የአስመላሽን ድምፅ መስማት ጠቃሚ ቢሆንም …… እኔ ግን አልቻልኩም ……..

Source     –     Ethiopian Review