Posted on May 2, 2017


 በኢትዮጵያ ሰሜን ክፍል ጎንደረና ጎጃም የቦንብ አደጋዎች እየበረከቱ ነው። ከቦንብ አደጋዎች በተጨማሪ የሽምቅ ውጊያ ስለመኖሩ መደመጥ ከተጀመረ ሰነባብቷል። መንግስት በይፋ ማስተባበያና መቃወሚያ ባያቀርብም አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ አገራት ለዜጎቻቸው ምክር በመስጠት ስም ” ችግር አለ” ሲሉ ማረጋገጫ እየሰጡ ነው።

ዛጎል ዜና- በጎንደር የተለያዩ ስፍራዎች በጎበዝ አለቃ ራሳቸውን ማደራጀታቸውን የሚገልጹ፣ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሃይል ናቸው የሚባሉና ” ከፋኝ” ተብለው የሚጠሩ ተደጋጋሚ የሽምቅ ውጊያ ከፍተው ጉዳት ማድረሳቸውን መስማት የተለመደ ሆኗል። አንዳንድ ጊዜ የሚቀርቡት መርጃዎች ከበድ ያሉም ናቸው። ይሁንና እንደ ቦንብ አደጋዎቹ በሌሎች ገለልተኛ ክፍሎች ስምና ቦታ ተጠቅሶ ማረጋገጫ አልቀረበም።

ethiopian-federal-police-on-action

ፎቶ በ1997 ምርጫ ወቅት ሮይተርስ አዲስ አበባ ካነሳቸው ምስሎች

Audio Player

ዛጎል ያነጋገረው የድብረታቦር ነዋሪ ግጭቶች እንዳሉና ህዝቡ ከመንድስት ጋር ሆድና ጀርባ መሆኑንን ይናገራል። አያይዞም ችግሩ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር የሚባባስና የሚሰፋ እንደሆነ ግምቱን አስፍሯል። ሌላ የመሃል ፒያሳ ነዋሪ ” ችግሩ አለ። የሽምቅ ጥቃቶች ይፋጸማሉ። ግን ከቁጥጥር ውጪ የሚወጣ አይመስለኝም” ባይ ናት።
በውጪ አገር የሚኖር የጎንደር በለሳ ተወላጅ በበኩሉ ” ህወሃት ጫካ እያለ ቀን ገበሬ፣ ማታ ታጋይ በመሆን ነበር ሽፍትነቱን የጀመሩት” ሲል አስትያየቱን ይሰጣል። እንደ እሱ አባባል በአማራ ክልል በተለይም በጎንደርና በጎጃም አንዳንድ ቀበሌዎች አሁን ያለው እንቅስቃሴ ከዚሁ ከቀድሞው የህወሃት ልምድ ጋር ይመሳሰላል። ህዝብ ጉያው ያደረጋቸው ታጋዮች ሃይላቸው እየጎለበተ እንጂ እየመነመነ ሊሄድ እንደማይችልም ይናገራል። አያይዞም መንግስት ህዝብ ጉያ ውስጥ ገብቶ ርምጃ በወሰደ ቁጥር ጠላት እያፈራና ችግሩን እያሰፋው ስለሚሄድ ችግሩን በነጻ ውይይት መፍታቱ የተሻለ እንደሆነ ይመክራል።
አስተያየት ሰጪዎቹ የሚስማሙበት ዋና ጉዳይ ቢኖር የፖለቲካ ችግር መኖሩ ላይ ነው። አዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑ ለዛጎል እንዳልሉት ” በሁሉም ወገን የሚወራውና እውነቱ ይለያያሉ። አገሪቱ ግን ወደ ከፋ የፖለቲካ ቀውስ እያመራች ነው” ሲሉ ስጋቱ ሊገፈፍ የሚችልበት መንገድ ላይ ቢተኮር የተሻለ እንደሆነ ያሳስባሉ። ” የጥላቻ ፖለቲካ መጨረሻው ክፉ በመሆኑ እዛ ከመድረሳቸን በፊት ጠባብ፣ ትምክህት… እየተባለ ጆሮ አልፋ ዲስኩር ከማቅረብ የዘለለ ቆራጥ የስብዕና ውስኔ መወሰን ግድ ነው” በማለት መንግስት ከፕሮፓጋንዳ የዘለለ ስራ ሊሰራና የሳት ማጥፋት ሩጫውን ሊያቆም እንደሚገባ ይገልጻሉ።
ባለፈው ቅዳሜ በባህር ዳር ” ባለ አገሩ” ኮንሰርት እየተካሄደ ባለበት ወቅት በተወረወረ ቦንብ ሁለት የፌደራል ፖሊሶች መሞታቸውንና እስከ አምስት የሚጠጉ መቁሰላቸውን ለቪኦኤ የገለጸው ወጣት እንዳለው ” ችግሩ ፖለቲካዊ” ነው ሲል የድርጊቱን ፈጻሚዎች ዓላማ ማወቅ እንደማያስቸግር አመልክቷል።
የቦንብ ጥቃት አደጋ መደጋገሙና የመንግስት ታጣቂዎች መገደላቸው የፖለቲካ ትግል ውጤት መሆኑ የጠቆመው ወጣት ከሰላማዊ ሰዎች ወገን የደረሰ ጉዳት እንደሌለ ባህር ዳር ሆኖ ለቪኦኤ ሲያስረዳ ከተናገረው ለመረዳት ተችሏል።

ማምሻውን በባህር ዳር መስቀል አደባባይ በሚገኘው ሚሊኒዬም የወጣቶች ስፖርት ማዕከል ውስጥ ፍንዳታው የደረሰው ታጣቂዎች የጸጥታ ማስከበር ስራቸውን አጠናቀው ስብሰብ በለው እያወሩ በነበረበት ወቅት ነው። ሁሉም ሙዚቃው ላይ ትኩረቱን ባደረገበት ሰዓት የተወረወረው ቦንብ ስላተፋው ህይወትና አደጋ የሚወጡት መረጃዎች መጠነኛ መዛባት ታይቶባቸዋል።
በማህበራዊ ገጽ በተለምዶ የክልሉን ዜና የሚያበስሩት የሰጡት ዳታና ኢሳት የአካባቢውን ምንጮች ጠቅሶ እንዳለው 31 የሚጠጉ ሰዎች ቆስለዋል። ለቪኦኤ የተናገረው ወጣት ግን ከሰላማዊ ሰዎች የተጎዱ አለመኖራቸውንና ጥቃቱ ጨላማን ተገን በማድረግ የተሰባሰቡ የመንግስት ታጣቂዎችን ብቻ ለይቶ ያጠቃ መሆኑን አስረድቷል። የተጎዱ አርቲስቶችም እንደሌሉ ተናግሯል። ህዝብ የዳሽን ቢራ ስሙን ቀይሮ ” ባለ ሃገሩ ቢራ” መባሉን ከህዝብ የተሰወረ እንዳልሆነም ጠቁሟል።
ሲያብራራም ከዛሬ አራት ወር በፊትም ማዲንጎ አፉወርቅ ኮንሰርት ላይ ተመሳሳይ የቦንብ ፍንዳታ መድረሱን አመልክቷል። ኮንሰርት ካለ የቦንብ ጥቃት የሚጠበቅ እንደሆነም አውስቷል። ወደ አዲስ ዘመንና ደብረታቦር የተባባሰ ችግር መኖሩንም አመልክቷል። ቪኦኤ ወደ አማራ ክልል የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽንስ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ንግሡ ጥላሁን ያደረገው ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ እንዳልተሳካ አመልክቷል።
አሜሪካ በጎንደር የተለያዩ ፍንዳታዎች እንደነበሩ ጠቀሳ ዜጎቿ ጥንቃቄ እንዲወስዱ ማስጠንቀቂያ መስጠቷ አይዘነጋም።
በተያያዘ ዜና አብርሃም ወልዴ በድርጃታቸው ባለ አገሩ አይዶል ስም ይህ ኮንሰርት ስለመዘጋጀቱም ሆነ ስለ ስሙ ጉዳይ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ መናገሩ ታውቋል። ኮንሰርቱን አቋርጦ የተመለሰውና የነበረው መረጃ የተሳሳተ እንደሆነ ያመለከተው አርጋኸኝ ወራሽ አውቆም ይሁን ሳያውቅ ለኢሳት ሬዲዮ የሰጠው መረጃም አነጋጋሪ ሆኗል።
አርጋኸኝ ወራሽ ለኢሳት ገሃድ መረጃ ለመስጠት ተስማምቶና አውቆ ከሆነ ምን አልባትም “የኮማንድ ፖስቱን አዋጅ ጥሷል” በሚል ሊጠየቅ እንደሚችል በማህበራዊ ሚዲያዎች በስፋት እየተነገረ ነው።
የኢህአዴግ ንብረት የሆነው ፋና ብሮድ ካስቲንግ የባለ ሃገሩ ኮንሰርት በተሳካ ሁኔታ ተካሂዷል ማለቱ አይዘነጋም። በዘገባው የቦንብ ፍንዳታ መደረሱንና ኮንሰርቱ መቋረጡን ግን በዝምታ አልፎታል።

በመጨረሻም ዚናው ከተላለፈ አንድ ቀን በሁዋላ የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊ ለቪኦኤ እንዳሉት ሁለት የፌደራል ፖሊስ አባላት በቦንብ ጥቃቱ ጉዳት ደርሶባቸዋል።  የሞተ  አባለ  አለመኖሩን አመልከተዋል። የተወረወረው ቦንብ በምን ምክንያት እንደሆነ ተጠይቀው ” የወረወሩት ናቸው የሚያውቁት” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።