Sunday, 07 May 2017 00:00

መንግስት ከግለሰብ ጋዜጠኞች ጋር እልህ መጋባቱን እንዲያቆም ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ

መንግስት ከግለሰብ ጋዜጠኞች ጋር እልህ መጋባቱን እንዲያቆም ተጠየቀ

– የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ከፖለቲካ ወገንተኝነትና ከአወዳሽነት አልተቀላቀሉም
– የአገሪቱ ፕሬሶች በጥቃቅንና አነስተኛ ደረጃ የሚገኙ ናቸው

የአገሪቱን ገፅታ በአለማቀፍ መድረኮች ላይ እያበላሸ ያለው የጋዜጠኞች እስር ጉዳይ እንዲታሰብበትና መንግስት ከግለሰብ ጋዜጠኞች ጋር እልህ መጋባቱን  እንዲያቆም ተጠየቀ፡፡ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን እስከ አሁን ድረስ የኤዲቶሪያል ነፃነታቸውን አለመቀዳጀታቸውንና የአገሪቱ ፕሬሶች በጥቃቅንና አነስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙም ተገልጿል፡፡
ሰሞኑን በተከበረው አለማቀፍ የፕሬስ ነፃነት ቀን ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን መምህር አቶ ተሻገር ሽፈራውና የሪፖርተር ጋዜጣ ባለቤት አቶ አማረ አረጋዊ፤ በአገራችን ፕሬስ ዙሪያ ባቀረቧቸው ፅሁፎች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡ የቀረቡትን የመነሻ ፅሁፎች ተከትሎም ከተሳታፊዎች የተለያዩ ሃሳቦች ተንፀባርቀዋል፡፡
እስካሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ነፃ ሆኖ መቆም የቻለ ፕሬስ መገንባት አለመቻሉን በጥናታዊ ፅሁፋቸው ላይ ያቀረቡት አቶ አማረ አረጋዊ፤አሁን ያሉትም ቢሆኑ እየተንገዳገዱ ለመቆም የሚታገሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ እስካሁን ጋዜጣ ማተም የሚችል የግል ማተሚያ ቤት አለመኖርና ማተሚያ ቤት በመንግስት የተያዘ መሆኑ ለነፃ ፕሬሶች ራስ ምታት ሆኖ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡
የመንግሥት ሚዲያዎች ደግሞ እስካሁን ድረስ የኤዲቶሪያል ነፃነታቸውን አልተቀዳጁም ያሉት አቶ አማረ፤ በዚህም የተነሳ በሀገሪቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን አልቻሉም ብለዋል፡፡ በሀገሪቱ የፀረ ሙስና እና የመልካም አስተዳደር ማስፈን ትግል ውስጥ የመንግስት ሚዲያዎች ሚና የሚፈለገውን ያህል አለመሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ የጋዜጠኝነት መምህሩ አቶ ተሻገር ሽፈራው በበኩላቸው፤ አሁን ባለው የኢፌዲሪ ህገ መንግሥት ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ ጉዳይ በግልፅ የሰፈረ ቢሆንም እስከ ዛሬ ይህ ነፃነት በተግባር እየተፈፀመ ነው ለማለት እንደማያስደፍር ጠቁመው፤ በዚህ እና በሌሎች ምክንያቶች ባለፉት 25 ዓመታት በመቶዎች የሚቆጠሩ ጋዜጦች ተወልደው ብዙም ሳይቆዩ መሞታቸውን አውስተዋል፡፡
“ብዙዎቹ ጋዜጦች እንደተወለዱ ነው የሚሞቱት” ያሉት አቶ ተሻገር፤ ከሁለትና ሦስት ህትመት በላይ መቀጠል ያልቻሉ እንዳሉ ሁሉ፤ ሁለትና ሦስት ዓመት ብቻ ቆይተው የሚሞቱ መኖራቸውንና ይህም ለኢትዮጵያ ፕሬስ አንዱ ተግዳሮት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
እስካሁንም ራሱን አጠናክሮ ተቋም የሆነ የግል ፕሬስ እንደሌለ፣ የሀገሪቱ ፕሬሶች በጥቃቅንና አነስተኛ ደረጃ የሚገኙ መሆናቸውን መምህሩ ገልጸዋል፡፡ በጥቃቅንና አነስተኛ ደረጃ ላይ ለመገኘታቸውም፤ የመንግስት ቀናኢ ድጋፍ አለማግኘታቸው፣ የእውቀትና ክህሎት ክፍተት ያለባቸው መሆኑና የተለያዩ ሀሳቦችን በማስተናገድ ራሳቸውን ለማሳደግ አለመትጋታቸው  በምክንያትነት ተጠቅሰዋል፡፡
የህትመት መገናኛ ብዙኃን ዋነኛ ችግሮች ተብለው በዩኒቨርሲቲ መምህሩ ከተጠቀሱት መካከልም የፖለቲካ ወገንተኝነትና የአወዳሽ ጋዜጠኝነት ችግር፣ የተደራሽነት ችግር እንዲሁም ጋዜጦችንና መፅሄቶችን የማንበብ ባህል አለመዳበር የሚሉት ይገኙበታል፡፡ “ባለፉት 25 ዓመታት የግልም ሆነ የመንግስት መገናኛ ብዙኃን ራሳቸውን ከፖለቲካ ወገንተኝነትና ከአወዳሽነት ነጻ አላወጡም” ብለዋል መምህሩ፡፡ አሁንም ድረስ ለሚወግኑት የፖለቲካ ኃይል አወዳሽ ሆነው መዝለቃቸው፣ ለሀገሪቱ ፕሬስ አሳሳቢ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
ሀሳብ በነፃነት የሚገለፅባቸው የውይይት አጀንዳዎች በመፍጠርም ለነፃ የሀሳብ መንሸራሸር የግልም ሆነ የመንግስት ሚዲያዎች አስተዋጽኦ ኢምንት መሆኑን የገለጹት አቶ ተሻገር፤ የሀሳብ ብዝሃነት የማይታይባቸው መሆኑንና በዲሞክራሲ ግንባታ ጉልህ ድርሻ እንደሌላቸው በጽሁፋቸው አመልክተዋል፡፡ በመንግስት መገናኛ ብዙኃን በኩል በመሰረታዊ ጉዳይ ላይ ሂስ እንደማይሰነዘርና ጥቃቅን ጉዳዮች ላይ ብቻ እንደሚያተኩሩ፣ በዚህም አወዳሽና አሞጋሽ ብቻ ሆነው መቅረታቸውን ጠቁመዋል፡፡
በመንግስት የሚደገፉ መገናኛ ብዙሃን በአመዛኙ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ መወሰናቸውና ብዙኃነትን አለማስተናገዳቸው ካላቸው አቅም አንፃር ይቅር ሊባል የማይችል መሆኑን የጠቆሙት አቶ ተሻገር፤ ከ4 አመት በፊት የተሠራ ጥናት፤ 70 በመቶዎቹ የኢቢሲ ዘገባዎች አዲስ አበባ ላይ ብቻ እንደሚየተኩሩና ሌሎች አካባቢዎችን እንደሚይቃኙ ማመልከቱን  ጠቅሠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ነፃ ጋዜጠኞች ማህበር ሊቀመንበር አቶ ወንድወሰን መኮንን፤ የግሉ ፕሬስ ምንም ድጋፍ ባላገኘበትና እንዲማር እድል ባልተፈጠረለት ሁኔታ አስተዋፅኦ አልነበረውም ተብሎ ሊወገዝ እንደማይገባው ጠቁመው፤ ‹‹ለመሆኑ አሁን ነፃ ፕሬስ አለ እንዴ?›› የሚል ጥያቄ ሰንዝረዋል፡፡ ያሉትን ጥቂት የግል ፕሬሶችም በስም ጠቅሰዋል። የሃገሪቱን ገፅታ በአለማቀፍ መድረኮች እያበላሸ ያለው የጋዜጠኞች እስር ጉዳይም እንዲታሠብበት አቶ ወንደሠን ጠይቀዋል፤ መንግስት ከግለሠብ ጋዜጠኞች ጋር እልህ መጋባት እንደማያስፈልገው በመጠቆም፡፡
ከመንግስት ኮሚኒኬሽን እንደመጡ የገለፁት አቶ ታምራት በበኩላቸው፤ የግል ፕሬሶች በአብዛኛው የወደቁት ገበያው ስለጣላቸው ነው ብለዋል፡፡ የቁም ነገር መፅሄት ባለቤት አቶ ታምራት ሃይሉ በሰጡት አስተያየት፤ የኢትዮጵያ ፕሬስ ወደ መጥፋት መቃረቡን፣ የግል ፕሬሶች ለመኖር እየቃተቱ መሆኑንና የፕሬስ ስራ አሁን ላይ ወደ ፌስ ቡክ መዛወሩን ጠቅሰዋል፡፡
የፕሬስ ህጉ ችግሮችን እንዳሉበትና ሊፈተሽ እንደሚገባው የተናገሩ ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡ አሁን ላይ የግል ጋዜጦችን በእጅጉ እያሽመደመደ ያለው የቫትና የታክስ ጉዳይ መሆኑን የጠቆሙ አስተያየት ሰጪዎች፤ ለበርካታ አመታት ችግሩ እንዳለ ቢታወቅም እስከ ዛሬ መንግስት ችግሩን ለመፍታት ቁርጠኝነት አለማሣያቱ ገልፀዋል፡፡
የመንግስት ኮሚኒኬሽን ፅ/ቤት ሚ/ር ዲኤታ አቶ ዛዲግ አብርሃ በበኩላቸው፤ የፕሬስ ህጉ ከህገ መንግስቱ ጋር እንደማይጋጭ ጠቁመው፤ የውጭ ተቋማት የሚያወጧቸው ሪፖርቶችም ከራሳቸው የፖለቲካ አመለካከት የመነጩ በመሆኑ እምብዛም ተቀባይነት የላቸውም ብለዋል፡፡
የዘንድሮ የፕሬስ ነፃነት ቀን ‹‹Critical minds for critical times: media’s role in advancing peaceful, just and inclusive societies›› በሚል መሪ ቃል ባለፈው ረቡዕ በመላው ዓለም የተከበረ ሲሆን በአዲስ አበባም ጥቂት የግል ፕሬስ አባላት፣ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጨምሮ በርካታ የመንግሥት ተቋማት ተወካዮች በተገኙበት ተከብሯል፡፡

አዲስ አድማስ