ድመጻዊ ቴዲ አፍሮ በአዲሱ አልበሙ ማር እስከ ጧፍ ብሎ ፍቅር እስከ መቃብር የተሰኘውን ስራቸውን ያደመቀላቸው ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ፤ አሁን ደግሞ በትውልድ ቦታቸው ደብረማርቆስ ከተማ ሀውልት እንደቆመላቸው ተሰማ።

ስለ እርሳቸውም አጭር የህይወት ታሪክ በዚህ መልኩ በአጭሩ እናካፍላችሁ ።

ደራሲ ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ በምስራቅ ጎጃም ጎዛመን ወረዳ በእንጾር ኪዳነ ምህረት ቀበሌ 1902 ተወለዱ። ገና በጨቅላ እድሜያቸው በቤተ ክርስቲያን የሚሰጠውን ትምህርት በቤተሰባቸው አጠገብና በአባታቸው አገር ደብረኤልያስ ሄደው የግእዝ ትምሕርት ቤት ቅኔ ተቀኝተዋል።

የቤተክርስቲያን ስርዐታትንና መንፈሳዊ ትምህርትን በጎጃም ገዳማት በደብረ ኤልያስ፣ በደብረ ወርቅና በዲማ ከቀሰሙ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመሄድ በስዊድን ሚሽነሪ ትምህርት ቤት በኋላም በራስ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ተከታተሉ። ለትንሽ ጊዜ በአስተማሪነት ሥራ ተሰማርተው እንዳገለገሉ የፋሽስት ጣሊያን ወረራ ተከሰተ።

የኢጣልያ ወረራ ወቅት ከልዑል ራስ ዕምሩ ኃይለ ሥላሴ ጦር ጋር በምዕራብ ኢትዮጵያ በአርበኝነት ሲዋጉ ቆይተው በመያዛቸው ጣሊያን ከልዑል ራስ ዕምሩ ጋር በግዞት ለሰባት ዓመታት በ ፖንዞ ደሴትና በሊፓሪ ደሴት ታስረው ቆይተዋል።

ከዚያም የተባባሪ ኃያላት ወታደሮች በ 1935 ዓ.ም. ሲያስመልጧቸው በተመለሱበት ጊዜ በትምህርታቸው እንደገና በኦክስፎርድ ከገፉ በኋላ በተለያዩ የመንግስት ተቋማት በተለይም በ ትምህርት ሚኒስቴር ለረጅም ጊዜ አገልግለዋል።

ዲፕሎማትና ደራሲ አቶ አዲስ አለማየሁ በተለታዩ ዘርፎች በመሰማራት ሃገራቸውንና ህዝባቸውን ያገለገሉ ሲሆን በተለይም፦

~1936 – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሠራተኛ

~1937- 1938 – የኢትዮጵያ ቆንሱል በኢየሩሳሌም

~1938- በ International Telecommunications Conference አትላንቲክ ከተማ ፣ ኒው ጄርዚ ወኪል

~1938 -1942- በተባበሩት መንግሥታት ቢሮ ኒው ዮርክ ሠራተኛ

~1942 -1948- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዳይረክተርና ምክትል

~1948- 1952- የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ አምባሰደር

~1952 – የትምህርት ሚኒስትር

~1952- 1957- የኢትዮጵያ አምባሰደር ወደ እንግሊዝ ናሆላንድ

~1957- 1958 – የልማት ሚኒስትር

~1960- 1966- ሴናቶር ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

ሀዲስ ዓለማየሁ በርካታ የስነ-ጽሑፍ ሥራዋችን አበርክተዋል። ከነዚህም ውስጥ ታላቅ አድናቆትንና እውቅናን ያተረፈው ሥራቸው ፍቅር እስከ መቃብር (1958 ) በሁለት የተለያዩ መደቦች ውስጥ የሚገኙ የሁለት ሰዎች የፍቅር ታሪክ ላይ ሲያተኩር፤ በጊዜው የነበረውን ወግና ልማድ ቁልጭ አድርጎ ይገልጻል።

እንዲሁም በ1970 ወንጀለኛው ዳኛ በ 1980 ደግሞ ስለ ማህበራዊ ጉዳዮችና ስለ ጣሊያን ወረራ የሚዳስሰውን የልም እዣት የተሰኙትን ልብ ወለድ ታሪኮች ለንባብ አቅርባዋል።

ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ በኢትዮጵያ የስነ ጽሑፍ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ በማበርከታቸው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክተርነት ማዕረግ ተሰጥቷቸዋል።

በህዳር 26/ 1996 ዓ.ም በ94 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።