Wednesday, 10 May 2017 12:51

 የትራምፕ አስተዳደር የአሜሪካን የ2018 የፌደራል በጀት ረቂቅ ዝግጅቱን በሚያከናውንበት ወቅት ከውጭ ግንኙነት ጋር በተያያዘ ሀገሪቱ በብዙ አቅጣጫ ታወጣ የነበረውን የቀደሙ መንግስታት ወጪ በከፍተኛ ደረጃ የሚቀንስበትን ሃሳብ አስቀምጧል። ቅድሚያ አሜሪካ ወይም አሜሪካ ትቅደም የሚለው የፕሬዝዳንት ትራምፕ መርህ በሰብአዊና ወታደራዊ እንደዚሁም በልዩ ልዩ የልማት ትብብርና አጋርነት እስከዛሬ ድረስ አሜሪካ ከሌሎች ሀገራት ጋር ትሰራባቸው የነበሩትን ሂደቶች በከፍተኛ ሁኔታ በማጠፍ ከዚሁ የሚገኘውን ትርፍ ገንዘብ በዋነኝነት የመከላከያ በጀቱን ለማጠናከር አስቧል። ይህ የበጀት እቅድ ከዩክሬን እስከ ዮርዳኖስ ብሎም ከምስራቅ አፍሪካ ሰፊው እስያ የሚዘልቅ ነው።

በዚሁ የውጭ እርዳታና የልማት አጋርነት በአለም አቀፍ ደረጃ ለመቀነስ የታሰበው አጠቃላይ የበጀት መጠን ቀደም ሲል ከነበረው አጠቃላይ የገንዘብ መጠን 30 ነጥብ በመቶ የሚደርስ መሆኑን ዘገባዎች ያመለክታሉ። ከአፍሪካ ለመቀነስ የታሰበው አጠቃላይ የበጀት መጠን ደግሞ 777 ነጥብ 1 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ነው። አሜሪካ በተለይ ከሰብአዊ እርዳታና ከልማት አጋርነት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ከምታደርግላቸው የአፍሪካ ቀጠናዎች መካከል አንዱ የሆነው ምስራቅ አፍሪካም የዚሁ የዶናልድ ትራምፕ የበጀት ቅነሳ ሰለባ የሆነበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

በአፍሪካ ደረጃ ለመቀነስ ከታሰበው 777 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ ኢትዮጵያ ስታገኘው ከነበረው አጠቃላይ እገዛ ውስጥ 132 ነጥብ ሚሊዮን ዶላር የበጀት ቅነሳ የተደረገባት መሆኑን ምሰራቅ አፍሪካን በተመለከተ የተዘጋጀው ረቂቅ የበጀት እቅድ ያመለክታል። ከኢትዮጵያ በመቀጠል ኡጋንዳም የ67 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር ቅነሳ ተደርጎባታል። ታንዛኒያ 50 ነጥብ 7 እንደዚሁም ኬኒያ11 ነጥብ 78 ሚሊዮን ዶላር የሚቀነስባቸው መሆኑን የፕሬዝዳንቱ ረቂቅ የበጀት እቅድ ያመለክታል። ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ በአንፃሩ መጠነኛ የሆነ የበጀት ጭማሪ ተደርጎላቸዋል። ፕሬዝዳንቱ በአጠቃላይ አፍሪካ ላይ ጠንከር ያለ አቋምን በመያዝ ለአፍሪካ ህብረት ከሚሰጠው የገንዘብ እገዛ ጀምሮ በአፍሪካ ልማት ፋውንዴሽን አማካኝነት ለበርካታ ከሰሃራ በታች ላሉና  በአነስተኛ ቢዝነስ ለተሰማሩ ሀገራት ዜጎች የሚቀርበው ፈንድም እንዲቀር ሀሳብን አቅርበዋል። ፕሬዝዳንቱ በአጠቃላይ ይሄንን ሁሉ የበጀት ቅናሽ ያደረጉበት ዋነኛው ምክንያት የሀገሪቱን የመከላከያ ወጪ መጠንን በ54 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ለማድረግ በማሰብ መሆኑ ታውቋል።

የፕሬዝዳንቱ ረቂቅ ኢትዮጵያን በብዙ መልኩ የሚጎዳ ይሆናል። በአንድ መልኩ በቀጥታ የሚደረገው የልማትና የእርዳታው በጀት ቅነሳ ሲሆን በሌላ አቅጣጫ ደግሞ አሜሪካ ለሌሎች አለም አቀፍ የልማትና የእርዳታ ድርጅቶች የምታደርጋቸው የበጀት ቅነሳዎች ድርጅቶቹ ኢትዮጵያን በመሰሉ ሀገራት በሚያካሂዷቸው ልማቶች ላይ የበጀት እጥረትን የሚፈጥር መሆኑ ነው። አሜሪካ የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅቶችን ጨምሮ ለበርካታ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ የምታደርግ ሀገር ናት። አሜሪካ ለተባበሩት መንግስታት የምታደርገው የገንዘብ ድጋፍ የአለም ጤና ድርጅትን ጨምሮ በርካቶቹ የድርጅቱ ንዑስ ክፍሎች ሰፉ ስራዎችን እንዲሰሩ ሲያደርጉ ቆይቷል። ሀገሪቱ ለተባበሩት መንግስታት በምታደርገው ከፍተኛ ድጋፍ ዙሪያ ወጪው እንዲቀንስ በማድረጉ ረገድ ቀደም ሲልም ከትራምፕ በፊት ሲነሱ የነበሩ ጉዳዮች ቢኖሩም በቀጣይ የትራምፕ ዘመን ግን እውን የሚሆን ይመስላል። ይህም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገራት ሰፊ ስራን በሚሰሩት የዓለም ጤና ድርጅትና የዓለም ምግብ ፕሮግራምን በመሰሉ ድርጅቶች ላይ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖን ስለሚያሳድር በሀገራቱ የልማት እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን ማምጣጡ አይቀሬ ነው።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ቀጣዩን ሂደት ፈታኝ የሚያደርገው ደግሞ የድርቁ አድማስ እየሰፋ የመሄዱ ጉዳይ ነው። የተባበሩት መንግስታት በአለም አቀፍ ድረጃ በተለይም በአፍሪካ በከፋ ደረጃ የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ ለረሀብ አደጋ የተጋለጡ ሰዎችን ለመርዳት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ያቀረበው የእርዳታ ጥሪ በቂ ምላሽ ካለማግኘቱ ጋር በተያያዘ እልቂት ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋትን አሳድሯል።

እንደ ኤቢሲ ኒውስ ዘገባ ከሆነ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያን ሳይጨምር 20 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በየመን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ ናይጄሪያ በረሃብ አደጋ ውስጥ ናቸው። ዘገባው አሁን በምስራቅ አፍሪካና በየመን የተከሰተው ረሀብ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በታሪክ የከፋ ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ነው። በኢትዮጵያ በተከሰተው የመኽር ዝናብ እጥረት ጋር በተያያዘ ቀደም ሲል የምግብ እህል እርዳታ ያስፈልጋቸዋል የተባሉት 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጎች ቁጥር ቀስ በቀስ ጭማሪን እያሳየ በማሳየት ላይ ነው። መንግስት ላለፈው ዓመትም ሆነ ለዘንድሮው ድርቅ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ያቀረበው ጥያቄ በቂ ምላሽን አላገኘም። ዓለም ለኢትዮጵያ ይቅርና በጦርነት ውስጥ ላሉት ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳንና የመን በማቅረብ ላይ ያለው የእርዳታ መጠንም ቢሆን ውስንነት የሚታይበት ነው። ከሰሞኑ ወደ ሶማሊያ የተጓዘው አለም አቀፍ የጋዜጠኞች ቡድን በተለይ በሶማሊያ የርሃቡ አድማስ ምን ያህል እየከፋ እንደሄደ አሳይቷል።

በምስራቅ አፍሪካም ሆነ በተለያዩ ሀገራት የተከሰተው ድርቅና ረሃብ የከፋ ደረጃ ላይ በደረሰበት ሁኔታ ትራምፕ የበጀት ቅነሳ እንዲደረግ መፈለጋቸው በበርካታ ሰብአዊ መብት ጥበቃ ተከራካሪ ድርጅቶችና መንግስታዊ ያልሆኑ የረድኤት ድርጅቶች አስተችቷቸዋል።

ኢትዮጵያ የገጠማትን ድርቅ እንድትቋቋም በማድረጉ ረገድ የአሜሪካ መንግስት እ.ኤ.አ በ2016/2017 ሰፊ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል። የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት የሆነው ዩኤስአይድ የአደጋ መከላከል ቡድንን በማቋቋም በኢትዮጵያ የድርቁን ሁኔታ ሲገመግም ከቆየ በኋላ ከፍተኛ የሆነ እገዛ ሲያደርግ የቆየ መሆኑን በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢምባሲ ድረገፅ መረጃ ያመለክታል። እንደ መረጃው ከሆነ ችግሩን በመቋቋሙ ረገድ አሜሪካ እ.ኤ.አ በ2015 ለኢትዮጵያ ድርቅ ተጎጂዎች  680 ሺህ ሜትሪክ ቶን ምግብን በማቅረብ ለአራት ሚሊዮን ተረጂዎች እገዛ ስታደርግ ቆይታለች። ይህ ብቻ ሳይሆን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የሴፍቲኔት ፕሮግራም ውስጥም በአሜሪካ መንግስት ተራድኦ ድርጅት ዩኤስኤይድ በኩል በየዓመቱ አንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር ልገሳ ሲደረግ የነበረ መሆኑን ይሄው በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢምባሲ መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያ መንግስት ድርቁን በመቋቋሙ ረገድ የተፈለገውን የእርዳታ መጠን ማግኘት ካለመቻሉ ጋር በተያያዘ ከሀገር ውስጥ መጠባበቂያ ክምችት እንደዚሁም ከውጭ የምግብ እህልን ገዝቶ ለድርቅ ተጎጂዎች በማቅረብ ላይ ነው። ሆኖም ድርቁ ተከታታይነት ያለው መሆኑና አድማሱንም ማስፋቱ የመንግስትን አቅም በከፍተኛ ደረጃ እየተፈታተነ መሆኑን ያለፈው ሳምንት የዋሽንግተን ፖስት ዘገባ ያመለክታል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ቅድሚያ አሜሪካ በሚለው አቋማቸው ለአፍሪካ ሀገራት ሀገሪቱ በምተሰጠው ድጋፍ ላይ ቅነሳን ለማድረግ አቋም መያዛቸው እርዳታን እንደ አንድ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ታሳቢ ለሚያደርጉ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት በቀጣይ ከባድ ፈተናን የሚደቅን ይሆናል። የኢትዮጵያ መንግስት የውጭ ምንዛሪ ገቢ በከፍተኛ ደረጃ እያሽቆለቆለ መሄድ ከጀመረ ዋል አደር ብሏል። ከዚህም ባለፈ ለእርዳታ እህል ግዢ የሚወጣው የውጭ ምንዛሪም ሌላኛው ፈተና ነው። ከፌደራሉ መንግስት ርብርብ ባሻገር  ክልሎች በርካታ የልማት ፕሮግራሞቻቸውን በማጠፍ ቀላል የማይባል በጀታቸውን የድርቅ ተጎጂ ወገኖችን ለማገዝ አውለዋል።  እነዚህ ሁኔታዎች ሀገሪቱ ቀደም ሲል ከገጠማት የፖለቲካ አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ የተፈጠረው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ጋር ተዳምሮ ፈተናውን የከበደ ያደርገዋል። እነዚህ ፈተናዎች ባሉበት ሁኔታ የኢትዮጵያ ዋነኛ የእርዳታና የልማት አጋር ተደርጋ የምትጠሰዋ ሀገር አሜሪካ የበጀት ቅነሳ ሂሳብ ውስጥ መግባቷ ችግሩን የበለጠ ውስብስብ የሚያደርገው ይሆናል።