• በልዩ ሀ/ስብከታቸውና በልዩ ጽ/ቤታቸው ላይ ስለሚጎርፉ አቤቱታዎች በማቃለል ተናግረዋል
  • የሙስናና የአስተዳደር ችግሩ አሳሳቢ እንደኾነ በይፋ ያመኑበትን የመካድ ያህል ተቆጥሯል
  • “መንበሩ ሰው የለበትም” ያሉ አባት፣ “በፊርማዎ ስንቱ ተሰደደ፤ ተፈናቀለ!” ሲሉ አሳበሏቸው
  • 18 ያህል የመነጋገርያ አጀንዳዎችን ያጸደቀው ምልአተ ጉባኤው፣ ጉዳዩን በይደር ይዞታል
  • “ቃለ ዐዋዲ” በሚል ራሱን ሰይሞ የሚንቀሳቀሰው የመናፍቁ አሰግድ ሣህሉ ጉዳይ አንዱ ነው

*                     *                   *

በፓትርያርኩ የመክፈቻ ቃለ ምዕዳን፣ ትላንት ረቡዕ የተጀመረው፣ የ፳፻፱ ዓ.ም. የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ፥ ኹለንተናዊ የቤተ ክርስቲያንን ችግር አስመልክቶ የቀረበውን ጥናታዊ ሪፖርት እና የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫን ጨምሮ 18 የመነጋገርያ አጀንዳዎችን በማጽደቅ ውይይቱን ቀጥሎ ውሏል፡፡

“አይሠሩ፤ አያሠሩ! መንበሩ ላይ ሰው አለ ግን ሰው የለውም!”

 

 

 

 

 

 

 

 

በቅዱስ ሲኖዶሱ የተሠየመው የአጀንዳ አርቃቂ ኮሚቴ፣ ካቀረባቸው 19 የመነጋገርያ ነጥቦች አንዱበይግባኝ ለፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ስለሚቀርቡና በተለይም በልዩ ሀገረ ስብከታቸው የአዲስ አበባ ሥራ አስኪያጅ፣ ጎይተኦም ያይኑ አስተዳደር ላይ የሚጎርፉ አቤቱታዎችን የተመለከተ ቢኾንም፤ በፓትርያርኩ ተቃውሞ ሳይካተት መቅረቱ ተገልጿል፡፡

የአጀንዳው ረቂቅ፣ “በቤተ ክርስቲያኒቱ የአስተዳደር ችግር ምክንያት መልስ የሚሰጠን ዐጣን በሚል አቤቱታ ስለሚያቀርቡና ፈቃድ ስለሚጠይቁ ምእመናን” በሚል በ15ኛ ተራ ቁጥር፣ በኮሚቴው ቀርቦ እንደነበረና ፓትርያርኩ፥ “አልቀበለውም፤ ይውጣልኝ፤” በማለታቸው ውድቅ መደረጉ ተጠቅሷል፡፡

“በአስተዳደር ተበደልኩ ብሎ እኔጋ መጥቶ መልስ ያልተሰጠውና ፍትሕ ያጣ መኖሩን አላውቅም፤” ያሉት ፓትርያርኩ፣ “ኹሉንም አናግራለሁ፤ የመለስኩት የለም፤” ሲሉ የአጀንዳ ረቂቁን ከመቃወማቸውም በላይ፣ “ምንድን ነው ማስረጃችሁ? ማስረጃ አቅርቡ?” በማለት መሟገታቸው፣ የምልአተ ጉባኤውን አባላት በእጅጉ ማስገረሙና ማሳዘኑ ተመልክቷል፡፡

ይኹንና 18ቱ አጀንዳ ጸድቆ፣ በአጀንዳ ተ.ቁ(2) በተቀመጠው መሠረት፣ የቅዱስ ሲኖዶሱ ጽ/ቤትና የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አጠቃላይ ሪፖርት መደመጡን ተከትሎ በነበረው የውይይት ጊዜ፣ ጉዳዩ ዳግመኛ የተነሣበት አጋጣሚ በመፈጠሩ፣ የምልአተ ጉባኤው አባላት የፓትርያርኩን አቋም ሊያሳብሉ የሚችሉና ተግሣጽ የተሞላባቸው ጠንካራ አስተያየቶች በመሰንዘራቸው፣ ስብሰባው ውጥረት ሰፍኖበት መዋሉ ተነግሯል፡፡

ተጠቃሹ አስተያየት፣ ከሊቃውንት ጉባኤው ሰብሳቢ፣ ብፁዕ አቡነ እንድርያስ የተሰነዘረው ነው፡፡ “በእርስዎ ፊርማ ስንት ሰው ተሰደደ? በእርስዎ ፊርማ ስንት ሰው ሞተ? በእርስዎ ፊርማ ስንት ሰው ሥራውን ዐጣ?” ያሉት ብፁዕነታቸው፥ በመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ በምዝበራና በፍትሕ መዛባት ቤተ ክርስቲያን በጣም የሚያሳዝን ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ነው፣ አምርረውና አክርረው የተናገሯቸው፡፡

“የተደራጁ ሌቦች ገብተው ቤቱን ይዘውታል፤” ያሉት ብፁዕነታቸው፣ ከአህጉረ ስብከት – አዲስ አበባ ድረስ ለአቤቱታ ቢመጡም፣ የሚያናግራቸው ጠፍቶ፣ ስንቅ ጨርሰው፣ መኝታ አጥተው፣ አዝነውና አልቅሰው የተመለሱ በርካታ ባለጉዳዮችን እንደሚያውቁ ጠቅሰውባቸዋል፡፡

ማንንም አልበደልኩም፤ ላሉት፣ እኔ ራሴ አለሁ፤ የተደራጁ ሌቦች ገብተው ቤቱን ይዘውት፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ በጣም የሚያሳዝን ደረጃ ላይ ነው ያለችው፤ ከጎንደር መጥተው፣ የሚያናግራቸው ጠፍቶ፣ መኝታ አጥተውና ስንቃቸውን ጨርሰው፣ አዝነውና አልቅሰው የተመለሱ ስንት ሰዎች ናቸው?


ተግሣጻዊ የነበረውና በምልአተ ጉባኤው አባላት የተያዘላቸው የብፁዕነታቸው የመደምደሚያ ንግግር፥ “አይሠሩ፤ አያሠሩ! መንበሩ ላይ ሰው አለ ግን ሰው የለውም!” የሚል ነበር፡፡

የአውሮጳ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሙሴ፣ ፓትርያርኩንና ልዩ ጽ/ቤታቸውን በጣልቃ ገብነት በመክሠሥ፣ በአህጉረ ስብከታቸው አባብሰውታል፤ ያሉትን ችግር ጠቅሰው ማስረዳታቸው ተጠቁሟል፡፡ ይህን ተከትሎም ውጥረት የሰፈነበት ሁኔታ በመታየቱ፣ አጠቃላይ ሪፖርቱ ሳይጸድቅና ውይይቱ ሳይቋጭ በይደር ተይዞ ምልአተ ጉባኤው ተነሥቷል፡፡

ከኹለት ሳምንታት በፊት፣ በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ራድዮ በተደመጠው ቃለ ምልልሳቸው፣ ሙስና መንሰራፋቱንና መልካም አስተዳደር የሚባል ነገር እንደሌለ፣ ቀቢጸ ተስፋ በተመላበት ስሜት በይፋ አምነው የተናገሩት ፓትርያርኩ፣ አኹን ደግሞ፣ በአስተዳደራቸው ችግር እንደሌለባቸውና ይብሱኑም፣ “ፍትሕ ያጣ ካለ አላውቅም” ማለታቸው የክሕደት ያህል ነው የተቆጠረባቸው፡፡

በመክፈቻ ቃለ ምዕዳናቸው እንኳ፣ “የቅን አገልግሎትና የመልካም አስተዳደር ክፍተት” እየተፈታተነን እንደኾነና ቤተ ክርስቲያንን፣ ከዋናው የግብረ ኖሎት ተልእኮዋ እያናጠባት እንዳለ የተናገሩትን በአፍታ የሚፃረር አቋም ማሳየታቸው፣ ለመናገር ያኽል ብቻ የሚናገሩ እንደኾነ አሳብቆባቸዋል፡፡

የመክፈቻ ቃለ ምዕዳናቸውን የተከታተሉት Kaleb Gashaw የተባሉ አስተያየት ሰጭ፣ በፌስቡክ እንዳሰፈሩት፦ የፓትርያሪኩአማላይ ዲስኩሮች ሰለቹን፤ በአፋቸው ይገነባሉ፤ በተግባር ያፈርሳሉ፡፡ እሳቸዉ የተሐድሶ መናፍቃንና የወንበዴአማሳኞች የበላይ ጠባቂና ጠበቃ ሆነው ሳለ ይኸን ዓይነት ንግግር ማድረግ ቤተ ክርስቲያንን መናቅ ነው፤” ያሉት፣ በፓትርያርኩ ቃልና ሥራ መካከል የሚሰተዋለውን ከፍተኛ ተፃርሮ ያሳያል፡፡

ልዩ ጽ/ቤታቸው ከተዋቀረበት የድጋፍ ሰጭ ተግባሩ ውጭ፣ ራሱን የቻለ ከፍተኛ የመዋቅርና የሥልጣን አካል አድርጎ እየሠራ እንዳለ፤ ይህም፥ ለሕግና ለሥርዓት መዛባት፣ ለመልካም አስተዳደር ዕጦትና ለመሳሰሉት ችግሮች ምክንያት እንደኾነ፤ ራሳቸው ፓትርያርኩም፥ ርእሰ አበው እንደመኾናቸው፣ ለአጠቃላይና ለዐበይት የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ትኩረት ሰጥተው ከቅዱስ ሲኖዶስ አካላት ጋራ እየመከሩ መሥራት ሲኖርባቸው፣ ለሓላፊነትና ደረጃቸው በማይመጥኑ ዝርዝር ጉዳዮች ውስጥ እየገቡ፦ ለሓላፊነትና ለተጠያቂነት ክፍተት፣ ላልታሰበበትና ላልተመከረበት ቅጽበታዊ ውሳኔ፣ ለባለጉዳዮች ወቅታዊ ውሳኔ አለማግኘት፣ መንገላታትና መጉላላት ለመሳሰሉት የመልካም አስተዳደር ችግሮች መንሥኤ እንደኾኑ፣ መሠረታዊ ችግሮችን አጥንቶ ባቀረበው ከፍተኛ ኮሚቴ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡

ፓትርያርኩ፣ በምልአተ ጉባኤው ላይ ባሳዩት እውነታውን የማበል አቋም፣ ለመከላከል የሞከሩት፣ ያለብቃቱና ሳይገባው የልዩ ሀገረ ስብከታቸው አዲስ አበባ ሥራ አስኪያጅ አድርገው የመደቡትን ጎይተኦም ያይኑና የምዝበራ አጋሮቹን ጭምር ነው፡፡

አጀንዳው ቢጸድቅ ሊታይ ይችል የነበረው አሳሳቢ ጉዳይ፦ በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት፥ ከሙስና መስፋፋት፣ ከመልካም አስተዳደር ዕጦትና ከኑፋቄ ጋራ ተያይዞ በሥራ አስኪያጁ የሚፈጸመውና ፓትርያርኩም በወገንተኛነት፣ ይግባኝ ሰሚ መኾን ያልቻሉባቸው ሕገ ወጥ ተግባራት፣ በገለልተኛ አካል ተጣርተው ቤተ ክርስቲያንን ከውድቀት የሚታደግ ርምጃ እንዲወሰድ፣ ለቅዱስ ሲኖዶሱ የቀረበ፣ የካህናትና ልዩ ልዩ ሠራተኞች አቤቱታ ነበርና፡፡


በተያያዘ ዜና፣ ምልአተ ጉባኤው፣ ራሱን “ቃለ ዓዋዲ” እያለ የሚጠራውና በመናፍቁ አሰግድ ሣህሉ የሚመራው የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ቡድን፣ በቤተ ክርስቲያናችን ስም በመንቀሳቀስ እየፈጸመ ስለሚገኘው የኑፋቄና የወንጀል ተግባራትየሚወያይበት አጀንዳ፣ በተ.ቁ(3) የያዘ ሲኾን፣ ከፍተኛ ውሳኔ እንደሚያሳልፍበት ይጠበቃል፡፡

በተጨማሪም ምልአተ ጉባኤው፡- የስብከተ ወንጌል መስፋፋትና መጠናከር፤ የቤተ ክርስቲያን ሚዲያ አገልግሎት፤ በኦሮሚያ ክልል ያሉ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ስላቀረቡት አቤቱታ፤ የሥርዓተ ምንኵስና እና የሥልጣነ ክህነት አሰጣጥ፤ የገዳማት መተዳደርያ ደንብ፤ የአብያተ ክርስቲያናትና የገዳማት አስጎብኚዎች፤ በኢየሩሳሌም የዴር ሡልጣን ገዳም ችግር፤ ፈቃድ የሌላቸው አጥማቂዎችና ሰባክያን ጉዳይ፤ የአእምሯዊ ሀብትና ቅርስ ባለቤትነትን፤ በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ስለተከሠተው ድርቅ የተመለከቱ አጀንዳዎችን ማካተቱ ታውቋል፡

Source: Hara Tewahido