አዳዲስ የባቡር መስመር ፕሮጀክቶች ህልውናቸው በአበዳሪ ተቋማት ላይ የተመሠረተ መሆኑ ተጠቆመ
10 May, 2017
በዘመኑ ተናኘ

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሠረት ወደ ግንባታ ይገባሉ ተብለው የታቀዱ አዳዲስ የባቡር መስመር ፕሮጀክቶች፣ ህልውናቸው በአበዳሪ ተቋማት ላይ የተመሠረተ መሆኑ ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ተፈራ ሰኞ ሚያዝያ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በአገሪቱ በስምንት ኮሪደሮች በአጠቃላይ ከ4,744 ኪሎ ሜትር በላይ የባቡር መስመር ለመዘርጋት ታቅዷል፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለመገንባት የታቀዱ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው የሚጀምረው አበዳሪ የፋይናንስ ተቋማት ብድር ሲፈቅዱ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የባቡር ፕሮጀክት ብዙ ገንዘብ የሚጠይቅ በመሆኑ፣ አገሪቱ የባቡር መስመር ገንብቶና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን አሟልቶ ለመንቀሳቀስ የሚያስችል ቁመና ላይ እንዳልደረሰች አቶ ደረጀ ተናግረዋል፡፡
በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ይገነባሉ ተብለው ከተያዙ ፕሮጀክቶች መካከል ከሞጆ – ሐዋሳ – ሻሸመኔ እስከ ሞያሌ፣ ከአዲስ አበባ – ጅማ እስከ በደሌ፣ ከነቀምት – አሰላ እስከ ኩምሩክ፣ ከፍኖተ ሰላም – ባህር ዳር – ወረታ እስከ መተማ፣ ከአዳማ እስከ አሰላ፣ ከመቐለ እስከ ሽረ ድረስ ያሉትን አካባቢዎች እንደሚያካትት አቶ ደረጀ ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት 653 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ከሰበታ – መኢሶ እስከ ደወሌ፣ 392 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ከአዋሽ እስከ ወልድያ ድረስ፣ እንዲሁም ከመቐለ እስከ ወልድያ ያሉ የባቡር መስመር ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
የእነዚህ ፕሮጀክቶች ግንባታ በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ መሆኑን አቶ ደረጀ ጠቁመው፣ የእነዚህ ፕሮጀክቶች ግንባታ ተቋርጧል ተብሎ በማኅበራዊ ሚዲያዎች እየተወራ ያለው ሐሰት ነው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በቅርቡ ከመቐለ እስከ ሽረ ሊዘረጋ ታቅዶ ስለነበረው የባቡር መስመር ከዓደዋ ነዋሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ተጠይቀው፣ ‹‹መምጣቱ አይቀርም፡፡ ግን ደግሞ ያልሆነ ቃል ልገባላችሁ አልችልም፤›› በማለት የባቡር መስመር ዝርጋታ መቼ ሊጀመር እንደሚችል ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ኅብረተሰቡ እንደዚህ ዓይነት ፕሮጀክቶች እንዲገነቡለት የሚፈልግ በመሆኑ፣ ካሁን በኋላ የባቡር ሥራ በኢትዮጵያ እንደማይቆም አቶ ደረጀ ጠቁመዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከአዲስ አበባ – ጂቡቲ የባቡር መስመር ላይ የሚሠሩ 1,171 ጎታችና ተጎታች ባቡሮች እንዳሉና በአንድ ጊዜም 3,500 ቶን የማንሳት አቅም እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከልም 1,100 ጭነቶችን የሚጎትቱ፣ 30 ደግሞ የመንገደኞች ማጓጓዣ ተጎታች ባቡሮች፣ እንዲሁም 11 ሎኮሞቲቮች እንደሆኑ አቶ ደረጀ ተናግረዋል፡፡
ከአዋሽ – ወልድያ እስከ ኮምቦልቻ ያለው የባቡር ፕሮጀክት ሥራም በዘንድሮ የክረምት ወራት ተጠናቆ ሥራ እንደሚጀምር አረጋግጠዋል፡፡ በቅርብ ጊዜም የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ከቻይና መንግሥት የአንድ መቶ ሚሊዮን ዩዋን (3,331,303 ብር) የገንዘብ ድጋፍ እንዳገኘ ጠቁመው፣ ይህንን ገንዘብም የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የባቡር አካዳሚውን የማስፋትና ኢትዮጵያዊ ኢንጂነሮችን አስተምሮ በማስመረቅ ወደፊት በአገር ልጆች ባቡርን ዲዛይ አድርጎ እስከ መሥራት የሚያስችል እንቅስቃሴ ውስጥ አስረድተዋል፡፡

ምንጭ       –        Home