By ሳተናው

May 13, 2017 21:06በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

 

እነዚህን በሰባራ ድልድይ የዘፍጥረትን ሁለተኛ ወንዝ እንደ አእዋፋት በሰማይ የሚሻገሩ ሰዎች አይቶ በሚችለው አተነፋፈስ እማይተነፍስ እንደ ግዑዝ እስተንፋስ አልባ ሊባል ይችላል፡፡ ይህን ምስል እንኳን አእምሮን ተሸክሞ እሚዞርን ሰው ደመ-ነፍስን አንጠልጥሎ እሚንቀሳቀስ ከብትንም “እህህ…” አሰኝቶ እሚያስተነፍስ ይመስለኛል፡፡ ይህንን የሕዝብ ኑሮ አይቶ “እህህ…” ያላለ ወይም በሚችለው መንገድ ያልተነፈሰ ከእእምሮው በተጨማሪ ከከብቶች የሚጋራውን ደመ-ነፍሱንም መፈተሽ  እንዳለበት ይሰማኛል፡፡ ይህንን የሰቆቃ ኑሮ በቃላት ለመግለጽ አስራ ሁለት ሕዋሳት የሚያስፈልጉ ይመስለኛል፡፡
ለማኝ ገዥዎች እንደዚህ ዓይነቱን ሰባራ ድልድይ እያሳዩ ማሰሪያ ገንዘብ ለግፍ ወንበር ካበቋቸው ጌቶቻቸው ገንዘብ እንደሚረጠቡ ይታወቃል፡፡ የተረጠቡትን ገንዘብና ይህ ሕዝብ የሚከፍለውን ግብር ግን እነዚሁ ለማኝ ገዥዎች ፎቅ ይሰሩበታል፣ ለሚስቶቻቸው ንግድ ይከፍቱበታል፣ ልጆቻቸውን ያንቀባርሩበታል፤ የተረፈውንም ሲፈረጥጡ ሊውጡት ከምዕራብ ጌቶቻቸው ባንክ ያስቀምጡታል፡፡
በተመሳሳይ መንገድ ይህ ሕዝብ ለታቦት እሚያስገባውን ሥለትና አስራት ተገዳላይ ‘ፓትርያሪኮች’ና ሐሳዊ “ጳጳሳት” እየሞጨለፉ ፎቅ ይሰሩበታል፤ በሉመዚን ይንቀባረሩበታል፤ ጮማ ይቆርጡበታል፤ ዘመድ አዝማዳቸውን ያንደላቅቁበታል፡፡ ይህ ሕዝብ “ከዚህኛው የግዮን ዳር እዚያኛው ጫፍ ካደረስከኝ ጠቦቴን ሸጬ እከፍልሃለሁ”ን እየተሳለ የሚያስገባውን ስለት የ”አባ” ገረ መድህንና የ”አባ” ማትያስ ጋሻ ጋግሬዎች  እንደ ጩሉሌ ሲልፉት ኖረዋል፡፡ ገዳም አፍርሰው ኒዮርክ የተደበቁት “አባ” ዘካርያስ መጀመርያ “በአባ” ገረ-መድህን ጋሻጋግሬዎች ያዘረፉት በሚሊዮን እሚቆጠር የእናቶች ስለትና አሁን ደግሞ እኒሁ ዘኬኛው ዘካርያስ ከየዋህ ዲያስፖሮች ሰብስበው ለ”አባ” ማትያስ የሰጡት በሚሊዮን እሚቆጠር ገንዘብ ለእነደዚህ ዓይነቱ ዝርፊያ ምሳሌ ይሆናል፡፡
ይህ ነፍሱ በገመድ ያለች ሕዝብ በቀን አስራ ስድት ሰዓት እየሰራ ሰሜኑንም ደቡብንም ምስራቁንም ምእራቡንም ማኛ፣ ማርና ቅቤ ሲመግብ ሺህ ዘመናት አስቆጥሯል፡፡ እንዳለመታደል ግን ይህ ሕዝብ መርፌ እንደ ወጋው ፊኛ ትእቢታቸውን አስተንፍሶ በመለሳቸው ነጫጭባዎች የተመረዙ ያምሮ በሽተኞች በመሶሎኒ ድምፅ ማጉያ “አማራ ጨቋኝ” እያሉ መጮሁን አላባራ ብለዋል፡፡ እነዚህ ያምሮ በሽተኞች ያገር ሰው መስለው ወንበር ተቆናጠው ይህንን ከክርስቶስ በቀር ማንንም የማይፈራ ሕዝብ ከቅረርቶው፣ ከፉከራውና ከነፍጡ አርቀው ለግርፋት፣ ለምክነት፣ ለባሰ ድህነት፣ ለስደት፣ ለባርነትና ለእጅ አዙር ቅኝ-ተገዥነት ዳርገውት ይገኛል፡፡
እጁ አመድ አፋሽ የሆነው ይኸ ሕዝብ ግን ዛሬም በመሶሎኒ የማደጎ ልጆች የመጣበትን የጥፋት ውሀንና እሳተ ገሞራ ተቋቋሞ ብሉይን ከሀዲስ አዋህዶ ይኖራል፡፡ በሞሰሎኒ የማደጎ ልጆች ከምድር እየተሰመረውን የሞሶሎኒ ክልል አሻፈረኝ ብሎ በሙሴ የተሳለውን የዘፍጥረት ካርታ ሙጥኝ ብሏል፡፡ የሞሶሎኒን ደቀ መዛሙርት ኮከብ እምቢኝ ብሎ ለኖህ የታየውን ቀስተ ደመና ከመርከቡ ደቅኖ መቅዘፉን ቀጥሏል፡፡ የዲያብሎስን ክልልና አጥር አፍርሶ ቅዱስ መጽሐፍ እንዳዘዘው በሁለተኛው ወንዝ ተሳስሮ በኤደን ለመኖር ገመዱን ዘርግቷል፡፡ ምንም ምድራዊ ኃይል ሊበጥስ ያልቻለውን  ወንድማማችነትና እህትማማችነት በዓባይ ወንዝ በተዘረጋው ገመድ አጥብቋል፡፡
እንዲያው ለመሆኑ ተለያይቶ ከመኖር ወድቆ መፈጥፈጥን እሚመርጥ እንደዚህ ዓይነት ሕዝብ  በየትኛው ዓለም ታይቷል? እንደ መንታ ጽንስ በአንድ የእትብት ገመድ ተሳስሮ በአንድ ማህጸን እሚዋኝ እንደዚህ ዓይነት ሕዝብ በየትኛው አሀጉር ተፈጥሯል?
ይህ ከመለያየት ሞትን የመረጠ ሕዝብ ለውጪም ሆነ ለውስጥ ጠላቶች ምን ያስጠነቅቃል? ለእኛ ገመድን ለመገናኘትና ለመያያዝ ሳይሆን ለመጓተትና ለመጠላለፍ ሃምሳ ዓመት ለተጠቀምነውስ ምን ያስተምራል? “አማራ ጨቋኙ”ን በኦፔራ ዜማና በሞሶሎኒ ቫዮሊን ለሚዘፍኑት በሽተኞችስ ምን ፈውስ ያቀርባል? በአማራ ጨቋኙ ዘፈን ምክንያት በወልቃይት፣ በደኖ፣ በአርባ ጉጉ፣ በአርሲ ነገሌ፣ በወለጋ፣ በሁመራ፣ በራያ፣ በመተከል፤ በጉራ ፈርዳና ሌሎችም ሥፍራዎች ለረገፉት፣ ገደል ለተጣሉት፣ ለታረዱት፣ ለተቃጠሉት፣ ለታወሩት፣ ለተቆመጡት፣ ለመከኑት፣ ለተፈናቀሉት፣ ለተራቡት፣ ለተጠሙት፣ ለተራቆቱት፣ ለተሰደዱትና ባርያ ለሆኑት ፍትህ የመፈለግ ሂደትስ ምን አስተዋፅኦ ያደርጋል?
መንግስት ባልነበረበት ወቅት ራሱን አደራጅቶ ጣልያንን እንኳን ምሽግና ካምቦ ድንኳን ተክሎ ለማደር ፋታ ያልሰጠ ይህ ሕዝብ ስንት ክፍለ-ዘመን እጁ አመድ እያፈሰ ይኖራል? አማራ ጨቋኝን ኦፔራ ዜማ በሚያንቆረቁሩት አረመኔዎች ደሙን ካፈሰሰበትና አንጥንቱን ከከሰከሰበት ምድር ስንቴ ይባረራል? ምን ያህል ጊዜስ “ጨቋኙ አማራ!” እየተባለ ጠላትን ሊፋለም ከመሸገበት ገደል ይወረወራል? የሌላውን ሀዲድና ድልድይ እየሰራ እርሱ ስንት ዘመን በገመድ መጓዝ ይቀጥላል?
እንደ ፍካሬ እየሱስ መደገም ያለባት የክቡር አቶ ሀዲስ አለማየሁ ትዝታ እንደምታስረዳው በሁለተኛው የጣልያን ወረራ ወቅት ከዚህ ሁለተኛውን ወንዝ በገመድ ከሚሻገሩት ወላጆችና አያቶች የተውጣጡ ሃምሳ ሺ ያህል የጎጃምና የጎንደር አርበኞች እንደልማዳቸው ትግሬን ነፃ ሊያወጡ ዘምተው ነበር፡፡
እንደሚታወቀው እነዚህን ትግሬን ነፃ ሊያወጡ የሄዱትን አርበኞች ኃይለስላሴ ጉግሳና ሰራዊቱ አምባሻ ትተው ፒዛ እየቀረደዱና አማራ ጨቋኝን በከበሮ እየደለቁ ከግራዚያኒ አብረው ወጓቸው፡፡ በትግሬም የግራዚያኒና የባንዶች ኃይል ሲያይል ነፃ ሊያወጡት ከሄዱት ትግሬ ሥልታዊ ማፈግፈግ አድርገው ደቡብ ምዕራብ መሽገው ነበር፡፡
ድካም፣ ርሃብ፣ በሽታና እልቂት ሳይበግራቸው ከፋና ወለጋን ነፃ ሊያወጡ ሞክረው ነበር፡፡ ዳሩ ግን የወለጋው ገዥና ሰራዊትም ጪኮ ትተው መኮሮኒያቸውን እየዛቁና አማራ ጨቋን እየደለቁ ነፃ ሊያወጧቸው የሄዱትን አርበኞች ከሞሶሎኒ ሰራዊት ጋር ሆነው ወጓቸው፡፡
የጨቋኙ አማራ ጣጣ ከዚህ አልቆመም፡፡ እነ አባ ጆቢር የአማራን ራስ ቆርጦ ላመጣ 30 ብር እሰጣለሁ እያሉ በዚያ አካባቢ ያለውን አማራ በኛ ዘመን በጉራ ፈርዳ እንዳየነው ንብረቱን እየቀሙ አባረሩት፡፡ (ትዝታ ገፅ 166-167). አማራ ይኸው ነው! ነፃ አውጥቶም ሽልማቱ ሞት የሆነ ሕዝብ ነው! ከሞት የተረፈው አንዳንዱም የገጠመው ረጅሙን ወንዝ በገመድ መሻገር ነው!
እኔም ከልጅነቴ እስካሁን ያስተዋልኩት ይኸንኑ የአማራ እጅ አመድ አፋሽነት ነው፡፡ በሶማልያ ወረራ ወቅት ይኸው በገመድ እትብት የተሳሰር ሕዝብ ሆ! ብሎ በራሱ ፈቃድ ሃረርጌ ተምሞ ገባ፡፡ ከአንደኛ ትምህርት ቤቴ አጠገብ ገበያ ውስጥ የድምፅ ማጉያው “አገርህ ተደፍራለች! አገርህን ጠላት ወሯታል” ሲል ሊሸጡ ያመጡትን እህልና ከበት በትነው ቤተሰቦቻቸውን ሳይሰናበቱ እያቅራሩና እየፎከሩ ከቀረበላቸው ክፍት መኪና የገቡት አርበኛ ወገኖች ዛሬም ከዓይኔ ናቸው! መኪናው ሞልቶ በመቅረታቸው ጸጉራቸውን የነጩት ጎበዛዝትና “ግንባር-ግንባሩንን ብላችሁት በድል ተመለሱ” እያሉ የተንጎራደዱት ወይዛዝርት ዛሬም በህሊናዬ ይመላለሳሉ፡፡
እነዚህ ወይዛዝርት እንደተመኙትም አርበኞች ከመደበኛው ጦር ጋር ቀደምት አባቶቻቸው የፈጸሙትን ጀብዱ ደገሙ! የሞሶሎኒን ድንፋታ እንደ ፊኛ እንዳስተነፈሱት አባቶቻቸው የሲያድ ባሬን በእንግሊዞች የተደፈደፈ ታላቋ ሶማልያ ቅዠትና ረጅም እጅ አሳጠሩ፡፡
እነዚህ አርበኞች ከድል መልስ ኢትዮጵያን ወግተው ባህር አልባ እንዳደረጓት ከንቱዎች ሁመራና ዳንሻ ለም መሬት አልተሰጣቸውም፡፡ ብዙዎቹ በችጋርና ሊደን በሚችል በሽታ አለቁ፡፡ እድሜውን የሰጣቸው አንዳንዶቹም ዓባይን በዋናና በገመድ እየተሻገሩ ኑሮን ይገፋሉ፡፡ ደማቸውን ያፈሰሱበት ሃረርጌም የእነዚህን አርበኞች ቋንቋ ለሚናገሩት ዜጎች ፊት ነስቷቸው የሰቀቀን ኑሮ ይኖራሉ፡፡ በሃረርጌ አማራ ዛሬ ድምፅ ብቻ ሳይሆን የመኖር ዋስትናም አጥቷል፡፡ አማራ በሃረርጌ የመኖር ዋስትና እንደሌለው የበደኖን ታሪክ ያስታውሷል፡፡

ጨቋኙ አማራ ይኸው ነው! ነፃ ባወጣው አገር መኖር እሚነፈገው ሕዝብ ነው! ጨቋኙ አማራ ይኸው ነው! “ነፃ አውጥቼሃለሁ!” እሚል ጉራ እየነዛ እንደ መሶሎኒ ደቀመዛሙርቶች የሊጥ እቃ ሳይቀር እየዘረፈ ከትውልድ ቦታው እማያግበሰብስ ፈርሀ-እግዚአብሔር ያለው ሕዝብ ነው፡፡

 

ጨቋኙ አማራ ይኸው ነው! እንኳን ሰላማዊ ሕዝብ ጠላቱንም ከቤት እሚያሳድር እንጅ ገደል እማይወረውር ብሩክ ሕዝብ ነው! ጨቋኙ አማራ ይኸው ነው! “ራሴን ሳለማ ሌላው ሕዝብ ይድማ”ን የማያልም በህሊና የተካነ ሕዝብ ነው፡፡ ጨቋኙ አማራ ይኸው ነው! ለሌሎች ሀዲድና ድልድይ እየሰራ ራሱ በገመድ ትልቁን ወንዝ እሚሻገር ነው፡፡ ጨቋኙ አማራ ይኸው ነው! ለሌላው ሆስፒታል እየሰራ እርሱ በአባሎና በወጌሻ እሚታከም ነው፡፡ ጨቋኙ አማራ ይኸው ነው! እርሱ በሁለት እንጨት እየተጋዘ ሌላውን በአንቡላስ ሆስፒታል እሚያደርስ ነው፡፡ ጨቋኙ አማራ ይኸው ነው! እርሱ በበሽታ እየረገፈ ገዳዮቹን በፈረንጅ ሆስፒታሎች እሚያሳክም ነው! ጨቋኙ አማራ ይኸው ነው! እርሱ ቅጥቅጥ እያበራ ፈጣሪ የባረከለትን ቅዱስና ግርማ ሞገስ ያለው ወንዝ ለሌሎች መብራት ማፍለቂያ እሚፈቅድ ነው፡፡ ጨቋኙ አማራ ይኸው ነው! በኩሊና ደመና አርሶ እያመረተ እንደ ጠላት እሚቆጥሩትን ሳይቀር በአውሮጳና አሜሪካ ጤፍ አስነግዶ ቱጃር እሚያደርግ ነው!  ጨቋኙ አማራ ይኸው ነው! እስከ መቼ እንደሚጨቁን ባላውቅም ጨቋኙ አማራ ይኸው ነው! ይኸው ነው! ጨቋኙ አማራ ይኸው ነው! በመለኮት ኃይል ሁለተኛውን ወንዝ እንደ አእዋፍ በሰማይ እየተሻገረ ኑሮውን እሚገፋ፤ ሲሞትም በወሰካ ተሰቅሎ እሚቀበር፤ ሞቷል ሲሉት ግን እንደ ክርስቶስ እሚነሳ ሕዝብ ነው! ጨቋኙ አማራ ይኸው ነው! ይኸው ነው!

ግንቦት ሁለት ሺ ዘጠኝ ዓ.ም.