By ሳተናው
May 13, 2017 21:4
ኢትዮጵያ በዚች ምድር ከዘፍጥረት ጀምሮ  በብዙዎች እጅ የሚገኘው መጽሀፍቅዱስ ሲገልጸው የዛሬዋ ኢትየጵያ አስኳል (ኒውክለስ) እንደሆነች በማያሻማ መልኩ የግዮንን (አባይን) ወንዝ ምልክት አድርጎ ነው፡፡ በዛን ዘመን ስማቸው ተገልጾ ዛሬም ድረስ የሚታወቁ አገራት ወይም አነስተኛ ሥፍራ ለመኖሩ እጠራጠራለሁ፡፡ ፕ/ር ኃይሌ ላሬቦ ኢትዮጵያ የሚለውን ቃል ረቂቅ ሀሳብ ነው ማለታቸውን በሌሎች ረቂቅ መባሉን ሲፌዝበት ነበር፡፡ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በእርግጥም ረቂቅ ነው፡፡ ብዙዎች ያልተረዱትም ይሄን ነው፡፡ ማፈሪያ የሆንው እኛ የዛሬዎቹ የኢትዮጵያ ምድር ነዋሪዎች እንጂ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት አደለም፡፡ ይህ ምድር ከጥንት ጀምሮ ልዩ የሆኑ ሕዝቦች መኖሪያ እንደነበር ብዙ መዛግብትና ምሁራን ይገልጹታል፡፡ ጥንታውያን የግርክ ጸሀፊዎች የኢትዮጵያን ጥንታዊ ሕዝቦች በሰማይ አምላክ የሚያመልኩ የመጀመሪያዎቹ ሕዝቦች ይሏቸዋል፡፡ ቀጥሎም ስለጠፈር ከፍተኛ ምርምር የሚያደርጉ ፈላስፎች ብለው ይጠቅሷቸዋል፡፡
ምድሩም እንደዛሬ ጠቦ ወደ የአባይን ምንጮች ወደሆኑት ተራራዎች የተሰበሰበ ሳይሆን በደቡብ ምስራቅ አፍሪካ እስከ ደቡብ ምዕራብ አፍሪካ ይደርስ ነበር፡፡ ሰሞኑን የዛሬው አትላነቲክ ውቂያኖስ ከምድር ወገብ ደቡብ በኩል የኢትዮጵያ ውቂያኖስ ይባል እንደነበር በየፌስቡኩ ተለጥፎ አየሁ፡፡ ብዙዎቻችን ይህን አናውቅም ነበር ማለት ነው፡፡ ግን እኮ ይሄ የታወቀ ነበር፡፡ https://en.wikipedia.org/wiki/Aethiopian_Sea . በሊንኩ ላይ ያለውን ታሪክ አንቡቡት.  እውነታው ብዙዎች እንደሚሉት በጥንት ጊዜ ኢትዮጵያ የሚባለው ከግብጽ ደቡብ ያለው ምድር በሙሉ ነው ብቻም ሳይሆን በእርግጥም ኢትዮጵያውያን እዛ ድረስ እንደተስፋፉ (ቢያንስ ደቡብ ምስራቅ አፍሪካ ጫፍ) አሁን እየወጡ ያሉት የሰዎች መለዘር(ዲኤንኤ) መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በቅርቡ አጋርቻችሁ የነበረው የኢትዮጵያውያን መለዘር ጥናት ውጤት አንዱ ነው፡፡ አሁንም አንሆ http://www.cell.com/ajhg/pdf/S0002-9297(12)00271-6.pdf ሁሉም ኢትዮጵያዊ ራሱን ሊያይበት የሚችልበት ሳይንሳዊ የጥናት ውጤት ነው፡፡ በጭፍኑ እኔ የእከሌ የሚባል ጎሳ ነኝ እኔ እንደዚህ ነኝ ማለት አይቻልም፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን ከእኛ ርቀው ወደደቡብም የሄዱ ኢትዮጵያዊ ወገኖችን የምናይበት ገሀዳዊ ምስክር ነው፡፡ ይህ ማንነት ነበር ታዲያ ለእኛ እንደ ገጸ በረከት ሆኖ የተሰጠን፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው ክብራችንን ናቅን፡፡ ወደተነሳሁበት ዋና ጭብጥ ልመልሳችሁ ለአንባቢ ይመች ዘንድ በንዑስ ርዕስ ባደርገው ወደድሁ፡፡
ቴዲ አፍሮና ኢትዮጵያዊነት
ለቴዲ ኢትዮጵያ በወደዳት መጠን አንዳከበረችው ሰሞኑን የምናየው እውነታ ምስክር ነው፡፡ ቴዲ በቢልቦርድ ሰንጠረዥ በአንደኝነት መስፈሩ ከልቡ የሆነው የኢትዮጵያዊነት ኃይል እንደሆነ ነው የተሰማኝ፡፡ እንዲህ ነው ኢትዮጵያዊነት፡፡ ቴዲ ነብሱ ከቀደሙ ኢትዮጵያን ብለው መስዋዕት ከሆኑ አባቶች የተጣበቀች ይመስል ኢትዮጵያንና ለኢትዮጵያ ክብር መስዋዕት የሆኑትን በመዘከሩ ብዙ ዋጋን እንደከፈለ እናውቃለን፡፡ ግን ኢትዮጵያ ዝም ብሎ ዝሩዕ ቃል አደለም፡፡ ከልብ ሲመጣ ታላቅ ኃይል አለው፡፡ ፕ/ር ኃይሌ እንደገለጹትም ረቂቅ ነው፡፡ በኢትዮጵያዊነት ከልቡ መጥቶ ያፈረ በታሪክ የለም፡፡ ግን በኢትዮጵያዊነት ከልባቸው የመጡ ጥቂት የታደሉ ብቻ ሳይሆኑ አልቀሩም፡፡
ቴዲ ምልክቶቻችን ናቸው የሚላቸውን የቀደሙ ነገስታትና ታላላቅ ጀግኖች አባቶቻችን የስኬት ሚስጢራቸውም በኢትዮጵያዊነት ረቂቅ ሀሳብ ውስጥ ያለ ልዑል አምላክ የሰጣቸው ኃይል ነበር፡፡ እግዚአብሔር ከልብ በሆነ ኢትዮጵያዊነት የሚነሳን ሀሳብ ይደግፈዋል፡፡ እግዚአብሔርን ለማምለክ ከጥንት ጀምሮ ለተመረጡ ሕዝቦች የተሰጠ ረቂቅ ሀሳብ ነው፡፡ ግሪካዊው ጥንታዊ የታሪክ ጸሀፊ ዲዎዲሮስ የሚመሰክረው እውነትም ይህን ነበር፡፡ የመጀመሪያዎቹ እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ሕዝቦች የሚኖሩባት ይላል፡፡ ዲዎዶረስን እንተወውና በየቤታችን ያለው መጽሀፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ከእስራኤላውያን በፊት እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ሕዝቦች እንደነበሩ እንረዳለን፡፡ በሰፊው የሚነገረው የሙሴ አማት ካህን አንደነበር በግልጽ እናነባለን፡፡ ያም ብቻም አደለም ሙሴ 40ዓመት በእሱ ዘንድ ሲቀመጥ የእግዚአብሔርን አምልኮት በመከተሉ ኋላ ለዛ ሁሉ ታላቅ ክብር መመረጡን ማስተዋልም እንችላለን፡፡ ከዚያም በኋላ ሙሴ ህዝቡን ሲመራ አማቹ ዮቶር ሥርዓትን ይነግረው እንደነበር እናነባለን፡፡ ከዚያም ሲወርድ ሲዋረድ መጥቶ ታላላቅ ነገስታት የተነሱባት አገር ኢትዮጵያ አንዷ ኆና ተመዘገበች፡፡ በብዙ አረብ መጻሕፍት የዛሬ ሁለት ሺ ዓመታት ገደማ ኢትዮጵያ ፋርስ(ኢራን)፣ ሕንድና ሮም ታላላቅ ተብለው ከተጠሩ አገራት ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያውያን የባሕር ኃይል ሁሉ እንደነበራቸው ይነገራል፡፡ ዛሬ የሱዳን፣ ሶማሌ፣ ጂቡቲ ከፊል ግብጽን ጨምሮ በአጠቃላይ የሀበሾች ምድር  ኢትዮጵያውያን እጅ ነበር፡፡  ይህ መዛግብት የሚያሳዩት ነው፡፡ ዛሬ ላይ ግን ሳይንስ እውነቱን በነዋሪዎቹ እያመሳከረው ነው፡፡ ኢትዮጵያ የብዙ ሕዝቦች መኖሪያ ነች፡፡ አንዴ ትገዝፋለች አንዴ ታንሳለች፡፡ ምልክቷ ጊዮን አሁንም አለ፡፡ ይመሰክራል፡፡ ኋላ ግን ኢትዮጵያ በመሳፍንቶች ምክነያት ተበታተነች፡፡ ካሳ(አጼ ቴዎድሮስ) የተበተነችውን ኢትዮጵያ አንድ ለማድረግ ከልብ ተመኙ፡፡ በዛን ሁኔታና ዘመን ሆኖ ይሄን ማሰብ ከባድ ነበር፡፡ ግን ከልብ የመጣ ኢትዮጵያዊነት በመሆኑ ሀሳባቸውን ሊያግድ የቻለ ኃይል አልነበረም፡፡ ሚኒሊክን በሕፃንነት ይዘው በምርኮ አሳደጉ፡፡ ምኒሊክ የቴዎድሮስን ሀሳብ ከልባቸው አሰቡት በእርግጥም ሊታመን በማይቻል ሁኔታ ዛሬ ያለችውን ኢትዮጵያ አንድ አድርገው አስረከቡን፡፡ ብቻም ሳይሆን አለም ላይ አለ የተባለ የፈጠራ ሥራንም ወደአገር በማምጣትና በማስፋፈት አገሪቱን ወደ ልዩ ምዕራፍ አሸጋገሩ፡፡ የአገዋን ድል ታሪክ ሌላው የኢትዮጵያዊነት ኃይል የታየበት ክስተት ነው፡፡ ቴዲ አፍሮ ምልክቶቻችን ናቸው ምልክት የሌለው ሕዝብ ይጠፋል ሲል ይህን ማለቱ ነው፡፡ ይህን የማንዘክር ከሆነ በእርግጥም እንጠፋለን፡፡ እነዚህን ምልከቶች ሊያስጥሉን የተነሱብን ብዙ ጠላቶች አሉ በዙሪያችን፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያዊነት ረቂቅ ሀሳብ ነውና የኢትዮጵያ ጠላቶች 26 ዓመት እንቅልፍ አጥተው መዋቅር ዘርግተው ኢትዮጵያዊነትን አጠፋን አዳክመናል በአሉበት ወቅት ዛሬ ነው ቴዲ ኢትዮጵያ ማለት ረቂቅ ሀሳብነቱ እውን እንደሆነ ያሳየን፡፡ በእርግጥ ቴዲ የእኔ ብቻ አደለም ብዙዎች ዘንድ ኢትዮጵያዊነት ስላለ ነው አንደመስመር ላይ ያገናኘን ይለዋል እወነታውን፡፡ ቴዲ እንደ ተራ ዘፋኝ ብቻም ሳይሆን እንደ ቀደሙ አባቶች ፈላሰፋነቱን የሚያሳብቅበትን ቃለምልልስ ነበር ለቪኦኤዋ ጽዮን ግርማ ጥያቄዎች ሲመልስ፡፡
በእርግጥም የቴዲ አፍሮ መልሶች ይገርማሉ፡፡ ብዙዎች ብዙ ስለኢትዮጵያ ያወራሉ ምን አልባትም ከልብ የጎደለ ስለሆነ ይሆናል እንደቴዲ በሙሉ ልብና፣ ፍልስፍናዊ አገላለጽ ስለ ኢትዮጵያዊነት የተናገረ ለመኖሩ እንጃ፡፡ ቴዲ ዘፈኖቹ አሱም እንዳለው እንደውም ከፍልስፍናው ትንሽ ዝቅ አድርጎ ነው ያቀረባቸው፡፡ እውነትና እውነት በመሆናቸው፣ የስሜትም ብቻ እንዳይሆን፡፡
ኢትዮጵያዊነት ቢሆን ጥሩ ነው ይምንለው ሳይሆን እንኑር ካልን መሆን ያለበት መሆኑን አቅጩን ሳያቅማማ መናገሩን ብዙ የኢትዮጵያ ጠላቶችን ሳያስበረግግ አልቀረም፡፡ ለነገሩ ቢልቦርድላይ በአንደኝነት ሲታይ ሁላቸውም ክው ነው ያሉት፡፡ እውነታው የቱንም ያህል አዳከምንው ቢሉም ኢትዮጵያዊነት ጭራሽ እንደ እሳተ ገሞራ ከታመቀበት የወጣበት አስመስሏልና፡፡ ይህን ጉዳይ ቀጥሎ በማነሳው ሀሳብ አነሳዋለሁ ይቆይ፡፡ ግን ዛሬ ሰዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን የሰጠው አስተያየት እንዳልተመቸኝ ሳልገልጽ አላልፍም፡፡ አምሳሉ ለቴዲ መልዕክት ያስተላለፈው በመቆጨት ይመስላል፡፡ ሆኖም ሀሳቡ ልክ አደለም፡፡ ቴዲን ለዚህ ሁሉ ድል ያበቃው ታጋሽነቱና በኢትዮጵያዊነቱ ምክነያት እግዚአብሔር ከእሱ ጋር ስለሆነ እንጂ በተራ በቀለኝነት አደለም፡፡ በቴዲ ቃለ መጠይቅ የወያኔ ፕሮፓጋንዳ ማሰራጫ የሆነው ኢቲቪ አድማጭ አገኛለሁ ብሎ ከሆነ  ጥሩ ነው፡፡ ቴዲን ለማድመጥ ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዛ ውጭ የሕዝብ እስካልሆነ ድረስ ማንም አይሰማው፡፡ ይልቁንም ቴዲ አሁንም አጋጣሚውን ተጠቅሞ የእሱን የቪኦኤና ሌሎች ቃለ መጠይቆች ላልደረሰው ኢትዮጵያዊነትን ለሕዝብ ጆሮ ለማድረስ ከ26 ዓመት በኋላ እድሉን ቢጠቀምበት እላለሁ፡፡ ይህም ሆኖ ግን ቴዲ ኢቲቪ ላይ ለመቅረቡ እርግጠኞች አደለንም፡፡ የቴዲን ፍልስፍና የሚፈሩት ጭራሽ በቴሌቪዥን ለሕዝብ ፍልስፍናውን እንዳያሰራጭ ይፈራሉና፡፡
ከመጀመሪያዊም ቢቢሲና ዘ ጋርዲያን ሳይቀሩ ቴዲን ማናገራቸው ኢቲቪን ራሱ አሳፍሮት እንጂ ምን አልባትም የወያኔ ወሮበሎች ነገር ሊያሴሩበት በኢቲቪ ቴዲ ኢትየጵያዊነት ከመቼውም ጊዜ አደጋ ላይ ወድቋል እንዴት ይላል፣ የመይሳውን ከመቃብር ተነስ አንተ የሞትክላት አገር ክብሯ ሳይረሳ ማለቱን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚጻረረ ነው በሚል በአቀነባበረ ነበር፡፡ ኢቲቪን የምናውቀው እንዲህ ነው፡፡ ብዙዎች ዛሬ በወህኒ ያሉ ፍርድ ቤት ሳይሆን የሚዳኙት በኢቲቪ በተቀጠሩ የወሮበሎቹ ጋዜጠኞች ነው፡፡  ሌላው ሰዎችን የሚያጠምድበት ቃለመጠይቅ ማድረግ ነው፡፡ ይልቅ ቴዲን አሁንም እነሱ እንደሚፈልጉት ነገር የሚሰሩበትን ቃለመጠይቅ አዘጋጅተውለት እንዳይሆን እሰጋለሁ፡፡ ሙሉ ቃለምልልሱን እንዳለ ሳይሆን ቃላት እየቆረጡና ለነገር እያስተካከሉ ማቅረብ በ26 የወሮበሎቹ ወያኔ ጋዜጠኞች ተክነናል የሚሉት ያላቸው ብቸኛ ችሎታቸው ነውና፡፡
የዶ/ር ብርሀነመስቀል አበበ ሰኚ ኦኤም ኤን ቃለ መጠይቅ
ኦኤም ኤን የተባለውን ሚዲያ የምናውቀው የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ጥላቻ ሲሰራጭበት ነው፡፡ አሁን አሁን እማ ለይቶላቸው ምሁርነታቸውንና አልፎም ስብዕናቸውን አዋርደው ከእውነት በራቆ የሐሰት ታሪኮች መናገር ትንሽ እንኳን  የማይማቸው ምሁራን በዚህ ሚዲያ የዕለት ከዕለት ትዕይንቱ ናቸው፡፡ ሰሞኑን ግን በስህተት ይሁን ወይም ታስቦበት እስከዛሬ ከምናውቃቸው የኦሮሞ ምሁራን ነን ከሚሉት ለየት ባለ ሁኔታ እውነትን በድፍረት የሚናገረውን ዶ/ር ብርሀነመስቀል አበበ ሰኚን ጋብዞ ሳይ እኔም እስኪ ብዬ ማደመጤን ቀተልኩ፡፡ ያልኩትም አልቀረ ብርሀነመስቀል መሠረታዊ የሆኑትን ለ26ዓመት የኦሮሞ ወጣት እንዳያውቃቸው የተከለከሉትን እውነታዎች ዘረገፋቸው ብል ይሻላል፡፡ ብርሀነመስቀል ከሌሎች የኦሮሞ ምሁራን የሚለይበት የአስተዳደግ መሠረቱ ይመሰላል፡፡ ብርሀነመስቀል ራሱ እንደተናገረው ተወልዶ ያደገው ሸዋ ነው፡፡ ሊያውም ደግሞ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግም ሆነ ከወጭ ወራሪዎች ለመጠበቅ መሥዋዕት ከሆኑት ከፈረሰኞቹ ጀግኖች አባቶች ወገን ከአቢቹ፡፡ ብርሀነመስቀል ይህን ታሪክ ክዶ ቢናገር የአባቶቹ አጥንት ይወቅሰዋል፡፡ በእርግጥም ከልጅነት ጀምሮ የሚያውቀውን እውነት መካድ አይቻለውም ነበርና፡፡ ለእሱ እነዚያ አባቶች የማንነቱ ትልልቅ ምልክቶች ናቸው፡፡ ለእሱ ምልከቶች አሉት፣ አንድ ሳይሆን ሺዎች፡፡ አገላለጹም ለማውራት ሳይሆን እውነታውን ነው፡፡ እውነትን መናገር ደግሞ ሊያውም የሚያኮራና ወኔ ሊሆን የሚችልን ታሪክ መናገር ክብር ነው፡፡
ሆኖም እየተናገረ የነበረበት ሚዲያ አጋጣሚውን ለመጠቀም ሲል መጠንቀቅ እንደነበረበት አያለሁ፡፡ በእርግጥም በብልሀት ተጠቅሞበታል፡፡ እውነት ነው ዛሬ ባዶውን እንዲሆንና ምልክት የሌለው ሕዝብ የሆነው የኦሮሞ ሕዝብ የወደቀው ምልክቶችህን ጣል የተባለ ዕለት እሽ ብሎ ለጠላት ቃለ መታዘዙ ነበር፡፡ አውቃለሁ ብዙ የኦሮሞ ምሁራን ብርሀነመስቀል እንደሚያስበው እንደሚያስቡ፡፡ ግን በድፍረት ሊናገሩት አልደፈሩም፡፡ ምክነያቱ ደግሞ አደማጭ የለም፡፡ የኦሮሞ ቁቤ ትውልድ ምልከቶቹን ከአእምሮ አጥፍቶ ዛሬ የባዘነ ሆኗል፡፡ ኦሮሞ ገዥ እንጂ ተገዥ አልነበረም ሲባል ደሙ ይፈላል፡፡ ሁኔታው ያሳዝናል ገዥ መሆን ክብር ነው እኮ፡፡
በወራዶች የወራዳ አስተሳሰብ እየወረደ መጥቶ ዛሬ አልቃሻና እንደ ተፈለገ የሚዘወር መሆኑ ሊገባው አልቻለም፡፡ ስለዚህ እውነታውን የሚያውቁት ምሁራንም ድፍረቱ ኖሯቸው ይህን መናገር አልቻሉም፡፡ ዶ/ር መረራ ጉዲና እንዲህ ያሉ እውነታዎችን በመናገሩ ነበር ለዘመናት ይሄ የነፍጠኛ ቅጥር እየተባለ የኖረው፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ዛሬ ላይ ለኦሮሞ ሕዝብ ነጻነት ራስን መስዋዕት አድርጎ እየታገለ ያለ ብቸኛው ቡድን የመረራ መሆኑን ዘግይቶም ቢሆን ሊያውም መረራና አጋሮቹ ራሳቸውን ስለሕዝብ አጋልጠው ተቀባይነት እያገኙ መጥተዋል፡፡ በተለይም ደግሞ የእውነተኛው የቀደሙ ጀግኖች አባቶች ታሪክ ዛሬም ጨርሶ ባልጠፋው የሸዋ ኦሮሞዎች፡፡ የሸዋ ኦሮሞ የምለው እኔ ኦሮሞን የመከፋፈል ሕልም ኖሮኝ አደለም፡፡ እውነቱ እንዲህ ግልጥ ብሎ ካልተነገረ በጅምላ ኦሮሞነት የሚነገደው ንግድ ብዙ ጥፋቶችን እያጠፋ እንደሆነ ስለማውቅ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ እመጣበታለሁ፡፡
ብርሀነመስቀል ብልሀተኛውንና ጥበበኛውን ታላቁን ራስ መኮንን ወልደመስቀል ጉዲሳን ጨምሮ ሌሎች ታላላቅ አባቶችንና የኢትዮጵያ ብርሀን የምትባለውን ጣይቱን ከታሪክ ይጠቅሳል፡፡  አዎ ብርሀነመስቀል እንደተናገረው ነው እውነታው፡፡ ሌላ ያልጠቀሰው ነገር ግን ኃይለሥላሴ (ተፈሪ መኮንን) የራስ መኮንን ወልደመስቀል ጉዲሳ ልጅ መሆናቸውን ነው፡፡ እንጊዲህ ኦሮሞ ገዥ አልነበረም የሚባለው በደም ከሆነ ይህን ታሪክ ከመጸፍም፣ ከሰዎች አእምሮም እስኪጠፋ  የሚሳካ አይደለም፡፡ ኦሮሞን ተገዥ ነበርክና ነጻ እናወጣሀለን የሚሉት ዋና ኢላማ ያደረጉት ትውልድን ከእዚህ እውነት አላቆ ምልክት የሌለው የመከነ ማድረግ ነበርና ስለዚህ እውነት እንደወራ ፈጽሞ እድል አይሰጡም፡፡ የሚኒሊክ ቀኝ እጆች፡ ራስ መኮንንን ጨምሮ ጣይቱ ብጡል፣ ገበየሁ ጎራ፣ ራስ ሚካኤል (ራስ አሊ)፣ ባልቻ ሳፎ (ባልቻ አባ ነብሶ) በጉልሕ የአደዋው ድል የሚዘክራቸው ከኦሮሞ ሕዝብ የሆኑ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውጭ ከሌሎች ሕዝቦች ቢባል ከአንድ ወይም ሁለት በላይ መጥቀስ አይቻልም፡፡ አሉላና ራስ መንገሻ ትግራይ፣ ንጉስ ተክለሀይማኖት ከጎጃም ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡  በነገራችን ላይ ባልቻ አባ ነብሶ የአደዋውንም የሁለተኛውንም የኢጣሊያ ጦርነት የተዋጉ ናቸው፡፡ በአደዋው ጦርነት ወጣት ነበሩ፡፡ በሁለተኛው ጦርነት የተሰው ታሪክ እንደልዩ ሊዘክራቸው ከሚገባ ሰው ናቸው፡፡ እነዚህ ልጆቿን ኢትዮጵያ አትክዳቸውም፡፡ የቱንም ያህል ከሀዲ ትውልድ ቢነሳ እነዚህ ጀግኖች ለዘህች ምድር ያፈሰሱት ደም የቆጠሩት አጥንት ምድሪቱ አትረሳም፡፡ ለዛም ነው ከዘመናት በፊት አልፈዋል የተባሉት የእነዚህ ጀግኖች አባቶች መንፈስ ዛሬ ኢትዮጵያን በጠላትነት የተነሱባት ከሀዲ ወሮበላ ትውልድ አሁንም የሚያስበረገጋቸው፡፡  በተለይ እንዲህ ሰፊ የታሪክ ድርሻ የነበራቸው የኦሮሞ ሕዝብ ጀግኖች ዛሬ ለመከነውና እነሱን ለካደው የቁቤ ትውልድ ፍርሀት የሆኑበት፡፡ ያለነበረ ታሪክ የሰፈር ወሮበሎች እየጻፉለት ለገዳዮቹ እጁን ያጣመረ ትውልድ፡፡ ለዛሬው የኦሮሞ ትውልድ ይሄ አይገበውም፡፡ የወያኔ ቅትረኛሰው ተስፋዬ ገ/አብ የአባቶቹን ታሪክ እንዲጥል የጻፈለትን የቡርቃው ዝምታ፣ የጀሚላ እናትበ ምናምን የሚሉ የአዚም ድርሰቶች እያነበበ መክኗል፡፡ በሕይወት ኖረው ምስክር የሆኑትን አባቶች ሳይቀር አዋረዷል፡፡ በቅረቡ በሞት የተለዩን ጀግናው ጃጋማ ኬሎ አንድ ማሳያ ናቸው፡፡ ጃጋማ ኬሎ ታመው ለሕክምና እርዳታ ለማሰባሰብ በድረገጾች በተበተነው መልዕክት ላይ በአነበብናቸው ኦሮሞ ነን በሚሉ ግለሰቦች በተጻፉ ምላሾች ብዙ ታዝበናል፡፡ ይህ ባረጋገጥናቸው ማለቴ እንጂ በየፌስቡኩ የሚሰጠው ምላሽ የማን እንደሆነ የማይታወቀውን ማለቴ አደለም፡፡ ጃጋማ  በእርግጥም ጀግና መሆናቸው ብቻም ሳይሆን በሕየወት የተገኙ ምልክት በመሆናቸው በትልቅ መተማመን መንፈስ ነበር የደረገ ገጽ የእርዳታ ዘመቻው በተለይ ከኦሮሞ ተወላጆች በጎ ምላሽ ተጠብቆ የነበረው፡፡ ከብዙ ኦሮሞ ነን ከሚሉት ግን የተሰጠው ምላሽ አሳዛኝ ነበር፡፡ ጃጋማ ለአገር ያበረከቱትን አስተዋጽዖ እንኳን ማንቆጥር በስብዕና ከቻልን መርዳት ቢያንስ ግን መልካም መምኘት ከከፋ ደግሞ ዝም ማለት ጥሩ በሆነ፡፡ ግን እንደሰው ማሰብ የሚከብዱ ምላሽ ስንሰማ እጅግ አዝነናል፡፡ ለእንደነዚህ አይነቶች አእምሮአቸው ለመከነና በሌሎች አስተሳሰብ ባርነት ወድቀው ሌሎችን ወደ ውድቀት የሚስቡ የጃጋማን መጥላት ምክነያታቸው የጃጋማ ኢትዮጵያዊነት ነበር፡፡ አዎ እንኳን በሕይወት ያሉት የሞቱትም የባነኗቸዋል፡፡ በጅምላ ግን እነሱም ኦሮሞ በሚል ዋናውን ቦታ ይዘው የሚፈልጉትን ያነግሳሉ ሌላውን ይጥላሉ፡፡ ይህ ክስተት በእርግጥም ባለማወቅ የወረዱትን አመለካከት ሲከተሉ የነበሩ እንዲባንኑ እድል ፈጥሯል፡፡
ዛሬ የኦሮሞን ትግል በመሪነት የተቆጣጠሩት የአርሲ እስልምና አክራሪ ናፋቂዎች ናቸው፡፡ ለእነሱ ከሶማሌ ጋር አባሪ የነበሩት እነ ዋቆ ጉቱ እንጂ የኢትዮጵያ ኩራት ሆነው ሶማሌን የተዋጉት እነ ጃጋማ ኬሎ ጠላቶች ናቸው፡፡ ጀጋማ ኬሎ እንደ ባልቻ አባነብሶ ሁሉ በጣሊያን በልጅነታቸው ተዋግተው በሶማሊ ወረራም የተሳተፉ ጀግና መሆናቸውን እያስታወስን ማለት ነው፡፡ ብርሀነ መስቀል ኢትዮጵያ የጅግኖች ልጆቿን ታሪክ አልረሳችም፡፡ ዛሬ ስለነዛ ጀግኖች ታሪክ እያነሳን መዘከር የእኛ ፋንታ ነው፡፡ ሀውልት ማቆም፣ በሥማቸው፣ ተቋማትን መመስረት የመሳሰሉት፡፡ እነሱ ታሪክ ሰሩ እንጂ የራሳቸውን ታሪክ ሲጽፉም ሆነ ለራሳቸው ማስታወሻ አላኖሩም፡፡ ችግሩ አሁን አሁን አንዳንዶች ወደራሳቸው ቢመለሱም አሁንም ብዙ የኦሮሞ ሕዝብ ልጆች የአባቶቻቸውን ታሪክ እየረገሙ ጠላቶቻቸው በሰጧቸው ታሪክ ታውረዋል፡፡ ከኦሮሞ ሕዝብ ልጆች ይልቅ የቀደሙ የጀግኖች አሮሞ አባቶቻችንን ክብር እየዘከረ ያለው ሌላው ነው፡፡ ሸዋ የብዙዎቹ ጀግኖች መፍለቂያ ስለነበር ዛሬ በኦሮሞዎች ዘንድ የዳጬ ዘር እየተባለ እንዲሸማቀቅ ነው የተደረገው፡፡ አማራው ሸዋም እንዲሁ የሚኒሊክ ዘር ነው፡፡ ጎበና ዳጬ ግን የኦሮሞ ከብርን በሚኒሊክ ዘመን እንዲያበብ ከዛም በኃይለስላሴ እንዲቀጥል ታላቁ ምልክት ነበር፡፡ ዛሬ መሰደቢያ ነው፡፡
ሌላው ስለአዲስ አበባ የአርሲው እስላማዊ ቡድን አደለም የሚያገባውና የሚመለከተው፡፡ የሸዋው የጎበና ዳጬ ልጆች እንጂ፡፡ ልብ በሉ እኔ እስላማዊ የምለው የእስልምናን እምነት ተከታዮችን ከመጥላት አደለም፡፡ ወሎም፣ ጉራጌም፣ ሲጤም ጂማም እስልምና ተከታዮች የሚበዙበት ህዝብ አለ፡፡ በታሪክና በኢትዮጵያዊነቱ ግን አይደራደርም፡፡ አርሲም ስል የእስላማዊ አክራሪነትን የሚመኘውን የአረብ አገር ፍልስፍናን በኢትዮጵያ ምድር የሚናፍቀውን ነው፡፡ በሜጫ እንገታችንን በየቀኑ በየሚዲያው የሚቀነጥሱትን ማለቴ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በዝህ አገላለጼ ሊያንሻፍፉት የሚሞክሩትን ስላየሁ ነው፡፡ ወደ ጉዳዬ ልመለስሳችሁ፡፡ ስለሆነም የአዲስ አበባን ጉዳይ በቅርብ በሀሳብ እንደተነሳው ለሸዋ መስጠትን የመሰለ መፍትሄ ሊኖረው አይችልም፡፡
ከብርሀነመስቀል ጋር የማንግባባው አዲስ አበባ በኦሮሚያ ሥር ትሁን የሚለውን ሀሳብ ነው፡፡ ሲጀምር ኦሮሚያ የሚባው ክልል ለኦሮሞ ሕዝብ ነጻነት ሲባል ፈርሶ ሁሉም እንደድሮው መሆን አለበት የሚል ጽኑ እምነት ያለኝ ሰው ነኝ፡፡ ዛሬ የኦሮሞ ሕዝብ መከራ እያየ ያለው በጅምላ ኦሮሞነ ነህ በሚል ሌሎች መጠቀሚያ እያደረጉት ነው፡፡ እንደልኩት ሸዋ በሸዋነቱ ክልል መሆኑ የአዲስ አበባን ንትርክ ከተማዋን ለሕዝቦቿ (ለሸዋ) በመስጠት መፍትሄ ከማምጣቱም በላይ ሸዋ የሕዝቦች መስተጋብር ተምሳሌት ሆኖ ለወደፊት ኢትዮጵያ የፍትህ አገር እንድትሆን እድል ይሰጣል ከሚል ነው፡፡ ወያኔ በሰራችልን ኦሮሞ፣ አማራ፣ ምናምን እየተባለ በተከለልንው መዋቅር ግን መቀጠል ከኢትዮጵያዊነት አንጻር  አንችልም፡፡ እየተመቸ ያለው ለጠላቶቻችን ነው፡፡ አሁን ላይ አማራ በሚል የተነሱ ሌላ ቡድን እንደኦሞው እነሱም አማራ በሚል የጅምላ መጠሪያ ሕዝቡን ከማንነቱ አምክነው ለራሳቸው መነገጃ ሊያደረጉት የሥራ ዕድል በወያኔ የተሰጣቸው መሆኑን ሰው ሊረዳ አልቻልም፡፡ ዛሬ ኦሮሞ በወለጋነቱ ማሰብ አይችልም፣ በሸዋነቱማ ቆየ፣ ጂማም ድምጽ የለውም፡፡ ሁሉም በኦሮሞነት በአርሲ ተወክሏል፡፡ ልብ በሎ ዛሬ አማራ ነን ብለው የተነሱትን አማራ በተባለው ክልል ሁሉ የሚኖረው ሕዝብ ወኪል እኛ ነን እያሉን ናቸው፡፡ ልክ የአርሲውና አጋሮቹ ቡድን ኦሮሞን ሁሉ እኔ ብቸኛ ወኪል ነኝና ከእኔ ውጭ መናገርም፣ መንቀሳቀስም እንደሚለው ማለት ነው፡፡ አማራ ውስጥ እኮ ሌሎች ዛሬም ድረስ በትላልቅ ሕዝብነት ያሉ ሕዝቦች አሉ፡፡ ቢያንስ በኢትዮጵያ ውስጥ በጥንታዊነቱ የሚታወቀውና ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የሉት የሰው ሰራሽ አሻራዎች( አክሱምንም፣ ላሊበላንም) ባለቤት የሆነው የአገው ሕዝብ፡፡ አማራ ነኝ የሚለው ቡድን በወያኔ እንደሚደገፍ እንዴት ሰው ሊረዳ እንዳልቻል አልገባንም፡፡ አላማው በአማራ በሚባለው ክልል ውስጥ መለያየትን ለመፍጠር ነው፡፡ ይሄ ቡድን ተቀባይነቱ እየጎላ ሲሄድ አገው እኔ አደለሁም አገው ነኝ ይላል፡፡ ቀጥሎ ለዘመናት የወሮበላው የወያኔ ቡዲን ሲያሴረው የነበረውን ሴራ በይፋ ያንቀሳቅሳል፡፡ ያም የአገውን ሕዝብ ከሌሎች ጋር በማጋጨት ሲቀጥል በዚህ አጋጣሚ አገውን ወደ ትግራይ ማካለል ነው፡፡ አደለም ሰቆጣን በመኀል ጎንደር ቅማንትና አማራ በማለት እንዴት እንደከፋፈለ እናስታውሳለን፡፡ ወያኔዎች የረጅም ጊዜ ሕለም ብለው ከተነሱበት ላሊበላን ወደ ትግራይ መገንጠል ነበር፡፡ ለነገሩ የቱሪስት ማስታወቂያው አሁንም እየጠቀሰ የነበረው ላሊበላን ትግራይ ውስጥ ነው፡፡ ሆኖም አሁን በአለው ሁኔታ አደለም አገውን ወልቃይትም ከእጁ እያመለጠ ስለሆነ ለጊዜው ሕዝብን መለያየት የሚችልበትን አማራ የሚል ቡድን ማቋቋምና እንደ ኦሮሞ ሁሉ ሕዝቡን በጅምላ አማራነት ከአመከነ በኋላ የፈለገውን ሊያደርግ የተሴረ ነው፡፡ በቀላሉ ቤተ አማራ ነን የሚሉትንና ደጋፊዎቻቸውን ቢናይ በወያኔ አዲስ አበባ ውስጥ ስልጠና ሲሰጣቸው ያደጉ ዛሬ በሌሎች አገራት እየኖሩ የተሰጣቸውን የቤት ሥራ የሚያከናውኑ ናቸው፡፡ ይህ ቡድንና የአርሲው ቡድን እንዴት ያለ ሕብረት እንዳላቸው አዚም ተደርጎብን ካልሆነ መቼም ማስተዋል የሚያቅት ሆኖ አደለም፡፡
አሁን ላይ ኢትዮጵያንነና ሕዝቦቿን ለመታደግ ጎንደሬውም በጎነደሬነቱ (እስላም ክርስቲያን፣ አማራ፣ ቅማንነት ምናምን የለም ጎንደሬ ጎንደሬ ነው)፣ ጎጃሜውም በጎጃሜነቱ፣ ሸዋም በሸዋነቱ፣ ወለጋም፣ ኢሉ አባቦራም እንደ ድሮው ተመልሰን የሚበጀነን እኛው በወሰንው መኖር ነው የሚያዋጣው፡፡ እንደ አመችነቱ ሊጣመሩ የሚችሉ ይኖራሉ፡፡  ክልሎቹን የሰሯቸ ወያኔና ኦነግ እንጂ አንድም የኢትዮጵያ ሕዝብ ፈቅዶና ወዶ አደለም፡፡ ሸዋ ከአሁን ጀምሮ ኦሮምኛና አማርኛን የሥራ ቋንቋ አድርጋ መጠቀም የሚያስችላት አቅሙ አላት እንደ አስፈላጊነቱ ጉራጊኛንም፡፡ ሌሎችም እንደተመቻቸው በየራሳቸው ይወስናሉ፡፡ ይህን ሀሳብ መቼም ብዙዎች የአጼዎቹ ሥርዓት እንደሚሉት አልጠራጠርም፡፡ እውነታው የአጼዎቹም ሆነ የደርግ የክፍለሀገር መዋቅር ችግር አልነበረበትም፡፡ ችግሩ የነበረው ፍትሀዊነት ላይ ነበር፡፡ ፍትሀዊነት ደግሞ ሕዝቦን እንዲራራቁ የሚያደርግ የዘር ክልል በመከልል አደለም፡፡ ዛሬ በጅምላ እንደልባቸው እየፈነጩ ላሉ ወሮበሎች ባልተጋለጥ ነበር፡፡ ጅማም በኢጂሌ ጂማነቱ ባሌም በኢጆሌ ባሌነቱ፣ ሌላውም በየአካባቢው ጎሳ ሀይማኖት ሳይለየው በሕብረት የሚኖርበት እድል መፍጠር በጃልን ነበር፡፡ ያኔ በጅምላ በኦሮሞነት አሁን ደግሞ በአማራነት ለሚነግዱብን ጠላቶቻችን እድል አይኖርም፡፡ በይፋ የኢትዮጵያን ከምድረ ገጽ መጥፋት የሚያውጁብንን ጠላቶቻችንን ያኔ አናያቸውም፡፡ የኢራኑ መሀመድ ነጂብ እስራኤልን ከካርታ ማጥፋት ብሎ የተናገረው ንግግር ዛሬም ድረስ ትልቅ ጉዳይ ሆኖ ኢራን ላይ ችግር ነው፡፡ ኢትዮጵያን እናጠፋለን፡፡ በኢትዮጵያ መቃብር ላይ ኦሮሚያን፣ አማራን እንመሰረትታለን እያሉ ከአሉት በላይ ጠላት የለንም፡፡ ኢትዮጵያዊነት የሕልውና ጉዳይ እንጂ ቢሆን ጥሩ ነው ተብሎ የሚታለፍ አደለም፡፡ ብዙዎች ያለ ኢትዮጵያ መኖር አይችሉም፡፡ በደቡቡ አገራችን የሚገኙ በርካታ የተለያዩ ሕዝቦች ከኢትዮጵያዊነት ውጪ አደጋ ላይ እንደሆኑ ያውቁታል፡፡ ከኢትዮጵያዊነት ውጭ እንኳን ትንንሾቹ ትልልቅ የተባሉትም አደጋ ላይ ናቸው፡፡ ዛሬ ኦሮሚያ የተባው ብቻውን አገር ቢሆን በወማግስቱ እርስ በእርሱ ተባልቶ ሰባት ትንንሽ ሊሆን ከሚችልበት አደጋም በላይ በዙሪያው ከአሉ ሕዝቦች ሁሉ በሚየገጠመው ውጊያ የአሮሞ ሕዝብ ራሱ ሕልውናው አደጋ ላይ ሊሆን እንደሚችል ብዙዎች አያስተውሉም፡፡
ብርሐነ መስቀል የኦሮምያ ከተሞችን አስመልክቶ ያነሳህው አመክንዮዋዊ ቢሆንም ተፈጻሚነቱን ትክክል ነው ብለህ የምታምነው ከተሞቹን ለኦሮሚያ ለሚባለው ክልል ነው ብለህ ከአመንህ ስህተት እንደሆነ በድጋሜ እነግርሀለሁ፡፡ 26 ዓመት የሄድንበት ሂደት ሕዝቦችን አደጋ ላይ ጥሏል፡፡ አሁን ወደነበርንበት ተመልሰን ነው ማሰብ የምንችለው፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ በገዛ ክልሉ በአሉ ከተሞች ተገፍቷል ለሚለው፡፡ ጥያቄ የለውም፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ግን በኮታ በሚሰጠው እድል ሳይሆን እንደማንኛውም ዜጋ እኩል እድል አግኝቶ የሚሳተፍበትን እድል ነው ትግላችን፡፡ ይህ ደግሞ ለሁሉም ነው፡፡ ትክክል ነው የኦሮሞ ኤክስፖርተር የለም፡፡ ለምን ብለህ ግን አልጠየቅክም፡፡ አነሰም በዛም ኦሮሞ እስከደርግ ጊዜ ድረስ በገር ጉዳይ ውሳኔዎችም ሆነ በኢኮኖሚ ተሳታፊ ነበር፡፡ ዛሬ ተበዳይ ብቻ አድርገው እንደሳሉት አልነበረም፡፡  አሁን ግን እንደተባለው ነው የኦሮምኛ ቋንቋ በአዲስ አበባ ከተማ የነዋሪ ሳይን በከተማዋ የሚገኙ የእስር ቤቶች ቋንቋ ነው፡፡ ለምን፡፡ ምልክት የሌለው ትውልድ ይልሀል ይሄ ነው፡፡ ምልክቶቹን ባይተው እንዲህ እንደፈለጉ ሊዘውሩበት የሚችሉትን እድል በአላገኙ፡፡ ኦነግ ነህ በሚል ስንቱ እንዲሁ ጠፍቶ ቀርቷል፡፡ ዛሬ ለኦሮሞ ትውልድ ጠላቱ አባቶቹ የበላይነት የነበራቸው የሚኒሊክ ታሪክ እንጂ ዛሬ የሚገድሉትና የሚያሰቃዩት አደሉም፡፡ አየህ ምልከቶቹን ያጣ ትውልድ እንዲህ ነው!! ደቡብ አፍሪካን ተመልከቱ የደቡብ አፍሪካ ጥቁር ሕዝብ አደገኝነቱ ለጥቁር ሕዝብ ነው፡፡ ነጮቹ ዛሬም ጌቶቹ ናቸው፡፡ እንዲህ ነው ትውልድ ሲመከን!!!!
አመሰግናለሁ!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይጠብቅ
አሜን
ሰርጸ ደስታ