May 14, 2017

በሥርዓተ ጥምቀት፣ ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋራ ያደረገችው ስምምነት ሲኖዶሱን አወያየ
“ኢትዮጵያውያን ከሊቃውንቶቻቸው ጳጳስ አይሹሙ” የሚለው ቀኖና፣ ከፍትሐ ነገሥቱ ይወጣል
በግል አታሚዎች ስሕተት የተጨመረባቸው፥ የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት እንዲስተካከሉ ታዘዘ
ስለ አቡነ ጳውሎስ እና ኮ/ል መንግሥቱ ኃ/ማርያም የሚያወራው ‘ተኣምረ ማርያም’ ይገኝበታል
ቤተ ክርስቲያን፥ መተርጎም ያለባቸውን፣ ሊቃውንት መድባ ተጠቃሽ ኅትመት ማዘጋጀት አለባት
* * *
(አዲስ አድማስ፤ ቅጽ ፲፮ ቁጥር ፱፻፬፤ ቅዳሜ፣ ግንቦት ፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም.)

 

 

 

 

 

 

 

 

በክርስትናው የነገረ መለኰት እና የምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ፣ ከግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋራ፣ የቆየ የታሪክ ግንኙነትና የዶግማ አንድነት ያላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሁለቱ እኅትማማች አብያተ ክርስቲያናት መካከል መታየት ጀምሯል የሚባለው የትምህርተ ሃይማኖት ልዩነት እንዲመረመር፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አዘዘ፡፡
የስብሰባው ምንጮች እንደተናገሩት፣ ምልአተ ጉባኤው ትእዛዙን የሰጠው፣ ምሥጢረ ጥምቀትን በተመለከተ፣ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፣ ሚያዝያ 20 ቀን 2009 ዓ.ም.፣ በካይሮ የተፈራሙትን የጋራ ስምምነት የቅርብ መነሻ በማድረግ በተካሔደ ውይይት ነው፡፡
የካቶሊኩ ፖፕ ፍራንሲስ በቅርቡ ግብጽን በጎበኙበት ወቅት፣ ከኮፕት ቤተ ክርስቲያን ፖፕና የእስክንድርያ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዎድሮስ ጋራ የተወያዩ ሲሆን፤ ከተፈራረሙት ባለ12 አንቀጾች የጋራ ስምምነት ውስጥ፣ አንዱ የሌላውን ምእመን ጥምቀት ላለመድገም የተስማሙበት አቋም(shared baptism) እንደሚገኝበት ገልጿል፡፡
በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት፣ የሥርዓተ ጥምቀቱ አፈጻጸምና የሃይማኖት ምስክርነቱ፣ መሠረታዊ ልዩነት እንዳለው የገለጹ ምንጮች፤ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን አካሔድ፣ የነገረ መለኰትና የምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አንድነት ባላቸውና ኦሪየንታል ተብለው በሚታወቁት፥ የኢትዮጵያ፣ የሶርያ፣ የአርመንና የሕንድ እኅትማማች አብያተ ክርስቲያናት ቅዱስ ሲኖዶሶች ያልተመከረበት እንደኾነ አስረድተዋል፡፡
በሥርዓተ ጥምቀት ላይ የሚፈጠረው ልዩነት፣ በሌሎቹ የምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ በሚኖረው አንድነት ላይ ተጽዕኖ እንዳለው ምንጮቹ ጠቅሰው፥ በሥርዓተ ቊርባን፣ ከጥንተ አብሶ አንጻር የድንግል ማርያም ቅድስና፣ የካህናቱ ሥነ ምግባር (ሲጋራ ማጤስ)፣ የመሳሰሉት ኻያ ያህል ልዩነቶች በውይይቱ ወቅት እንደተነሡና ከቀደሙት ታላላቅ አባቶች አስተምህሮ ጋራ ያላቸው መጣጣም ጥያቄ ማሥነሳቱን አመልክተዋል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶሱ በየጊዜው በሚያካሒደው ስብሰባ፣ ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋራ በትብብር መሥራቱ እንዲጠናከር፣ በተለይም ከግብጽ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋራ ለቆየው ግንኙነት ትኩረት እንዲሰጠው ቢያሳስብም፣ በትምህርተ ሃይማኖት ረገድ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከሚታዩት ተናጠላዊ አካሔዶች አንጻር ዶግማዊና ቀኖናዊ አንድነቱ እንዲመረመር ስምምነት ተደርሶበታል፤ የሊቃውንት ጉባኤውም፣ ልዩነቶቹን አጥንቶ ለቀጣዩ ዓመት የጥቅምት ምልአተ ጉባኤ እንዲያቀርብ መወሰኑን አስታውቀዋል፡፡
ኮፕቶች፣ የጥንቶቹን ደጋግ አባቶች አስተምህሮ ጠብቆ በመሔድ በኩል ችግር እየታየባቸው ነው፡፡ እመቤታችን ጥንተ አብሶ አለባት፤ ይላሉ፤ ከካቶሊኮች ጋራ “ጥምቀትን አንደግምም” ብለው አንዱ ያጠመቀውን ሌላው ላለማጥመቅ ተስማምተዋል፤ የእነቅዱስ አትናቴዎስንና የእነቅዱስ ዲዮስቆሮስን ውግዘት ወዴት አድርገውት ነው?… ቅዱስ ቊርባኑም ከዚኹ ጋራ ተያይዞ የሚታይ ነው፤ ተረፈ መሥዋዕቱን አውጥተው ለሕዝብ ያድሉታል፤ በመንገድ ይሸጡታል፤ በዐውደ ምሕረት ሲጋራ የሚያጤሱ ጳጳሳትን አይተናል፤ ይኼን ፈቅደዋል፤ የመዝሙር ሥርዓታቸው እንደ ፕሮቴስታንቶች በባንድ ነው፤ የኮፕት ቤተ ክርስቲያን ወዴት ነው እያመራች ያለችው? የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በእኒኽና መሰል ዶግማዊና ቀኖናዊ ልዩነቶች ላይ የተጠና አቋም መያዝ አለባት፡፡ የልዩነት ነጥቦቹ፣ በታመነባቸው የሊቃውንት ኮሚቴና በቋሚ ሲኖዶሱ የቅርብ ክትትል ተጠንተው ለቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ ሊቀርብ ይገባል፡፡

በተያያዘ ዜና፣ ምልአተ ጉባኤው፣ ግብጻውያን በፍትሐ ነገሥት ፍትሕ መንፈሳዊ በጣልቃ(ሥርዋጽ) የጨመሩት ነው የተባለው አንቀጽ፣ በቀጣይ የመጽሐፉ ኅትመቶች እንዲቀር መወሰኑ ተገልጿል፡፡ “ኢትዮጵያውያን ከሊቃውንቶቻቸው ጳጳስ አይሹሙ”የሚለው ሥርዋጹ፣ በግብጾች እንደሚነገረው፣ በኒቂያ ጉባኤ 42ኛ አንቀጽ ያልተወሰነ፣ የነጻነትን ክብር የሚቀንስ ዘረኛና ሐሰተኛ ቀኖና (pseudo canon) ነው፤ ተብሏል፡፡
በአራተኛው ክፍለ ዘመን፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ጥያቄና ፈቃድ በግብጽ ከተሾመው ቅዱስ ፍሬምናጦስ በኋላ እስከ 1951 ዓ.ም. ይሾሙ የነበሩት ጳጳሳት ግብጻውያን እንደነበሩ ያስታወሱት ምንጮቹ፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ከሥራቸው ለማድረግና ጳጳሳትን በሾሙ ቁጥር የኢትዮጵያ ነገሥታት የሚልኩላቸው የወርቅ የብር የዕንቁና የአልማዝ ገጸ በረከት እንዳይቀርባቸው፣ ከአገራቸው ከሊፋዎችና ሡልጣኖች ጋራ መክረው ያስገቡት መኾኑን አስገንዝበዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከራሷ ልጆች የራሷን ፓትርያርክና ጳጳሳት መሾም ከጀመረች ግማሽ ምእት ዓመት በመቆጠሩና አንቀጹም ሐሰተኛ ቀኖና በመኾኑ፣ በቀጣይ ኅትመቶች እንዲቀር ቅዱስ ሲኖዶሱ ወስኗል፡፡
ከዚኹ ሥርዋጽ ጋራ በተመሳሳይ፣ የስንክሳር ሚያዝያ 10 ቀን ንባብ አብሮ ታይቷል፡፡ ጉዳዩ፥ በመንበረ ፕትርክና ራስን የመቻል ጥያቄ ባፈለቀው በቅዱስ ንጉሥ ሐርቤና በጊዜው ግብጻዊ ጳጳስ አባ ሚካኤል የተፈጠረውን ጠብ መነሻ ያደረገ ነው፡፡ ቅዱስ ንጉሥ ሐርቤ፥ የኢትዮጵያን ስፋት የሕዝቡን ብዛት በማየት፣ ሰባት ኢትዮጵያውያን ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ፣ የጊዜውን ግብጻዊ ጳጳስ አቡነ ሚካኤልንና ሊቀ ጳጳሱን አባ ገብርኤልን ደጋግሞ ጠይቋል፡፡
“ኢትዮጵያውያን ኤጲስ ቆጶሳት ይሹሙልኝ” ማለቱን እንደ ኃጢአት፤ የግብጹን ሊቀ ጳጳስ አባ ገብርኤልን እንደ ገባሬ ተኣምር በመቁጠር ስሙን እንኳ ሳይጠራ፦ “ንጉሡ፥ ኢትዮጵያውያን ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ በመጠየቁ እግዚአብሔር ተቆጥቶ በአገሩ በኢትዮጵያ ላይ መቅሠፍት አወረደበት፤” ይላል፣ በዘመኑ የወረደውን ድርቅና በሽታ በመጥቀስ፡፡ እግዚአብሔር እንዲኽ ዓይነቱን የተቀደሰ ሐሳብ ይባርካል እንጅ በዚኽ የማይቆጣ በመኾኑ፣ ምልአተ ጉባኤው፣ ይህም ንባብ ከስንክሳሩ ቀጣይ ኅትመቶች እንዲወጣ ወስኗል፡፡

በሌላ በኩል፣ በግል አታሚዎች እየታተሙ በሚወጡ የአዋልድ መጻሕፍት ውስጥ፣ ወቅት እየጠበቁ ኾነ ተብለው በግለሰቦች ተጨምረዋል፤ የተባሉ ተኣምራትና የሕዝቦች ስያሜዎች የመሳሰሉት፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን የማይወክሉና ከዕውቅናዋ ውጭ የወጡ ኅትመቶች(unauthorized versions) እንደኾኑ በምልአተ ጉባኤው ተመክሮበታል፡፡ የቀድሞዎቹን ትክክለኛ ቅጅዎች(authoritative texts) የሚያፋልስና አስተምህሮዋን የሚፃረር ይዘት በግል አታሚዎቹ ተጨማምሮባቸዋል ከተባሉት ውስጥ፥ የራእየ ማርያም እና የተኣምረ ማርያም መጻሕፍት በምሳሌነት የተጠቀሱ ሲኾን፤ የቀድሞውን ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስንና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን በማካተት የታተመ ‘ተኣምረ ማርያም’ በአስረጅነት ቀርቧል፡፡
በበላይ ሕጓ እንደተደነገገው፣ ቤተ ክርስቲያን፣ ከጥንት ጀምሮ በሊቃውንት ልጆችዋ አማካይነት እየጻፈች፣ እየተረጎመችና እያዘጋጀች ስትገለገልባቸው፣ ስትጠብቃቸውና ስታስተምራቸው የኖሩትን መጻሕፍት ኹሉ፣ ዛሬም በያሉበት በባለቤትነት የመጠበቅና የማስጠበቅ መብት ያላት በመኾኑ፣ በዚኽም በኩል፥ ስግብግብ አታሚዎችን በማስቆምና የትክክለኛ ቅዱሳት መጻሕፍቷን ኅትመትና ሥርጭት በመቆጣጠር አስፈላጊው ኹሉ እንዲፈጸም፣ ምልአተ ጉባኤው ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና ምሁራን፥ መሰል ችግሮችን በመንቀስ፣ በቤተ ክርስቲያን በኩል ተገቢ ርምጃ የማስተካከያ ርምጃ እንዲወሰድ በጽሑፎቻቸውና ጥናቶቻቸው ሲጠቁሙ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡
************************
ታዋቂው ዓለም አቀፍ ምሁር ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌም፣ “Vision of Mary(ራእየ ፡ ማርያም) Under Attack”በሚል ርእስ ባሰፈሩት ጽሑፍ የሚከተለውን ብለዋል፦
But to the church’s credit, a comparative of its literature of different times shows that a silent change is in progress. The edited version of ራእየ ማርያም is an example. My only hope is that a distinction should be made between books and versions sanctioned by the church and those published by greedy money makers who care less of the implication for the church of their unauthorized version of religious books.
ከቤተ ክርስቲያናችን የአዋልድ መጻሕፍት የሚመደበውና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በልጇ በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር በጎልጎታ ስትጸልይ ያየችውን የሚገልጸው ራእየ ማርያም፥ ለዮሐንስ ወንጌላዊ እየነገረችው የጻፈው ነው፡፡ መጀመሪያ የተጻፈው በግሪክ ቋንቋ ሲኾን፣ ወደ ሀገራችን ከመምጣቱ በፊት ወደ ዐረብኛ(የግብጽ) ተተርጉሟል፡፡
በሀገር ቤትና በአውሮጳ ቤተ መጻሕፍት፣ ከ39 በላይ ልዩ ልዩ የራእየ ማርያም ቅጅዎችን ማየታቸውን የሚናገሩት፣ የጥንት ሥነ ድርሳናት ምሁሩ ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ፥ ራእየ ማርያም፣ መቼ ወደ ግእዝ እንደተተረጎመ ዘመኑን በውል መናገር ባይቻልም፣ እስከ አኹን ከታዩት የራእየ ማርያም ቅጅዎች ውስጥ ቀዳሚው፣ የ፲፭ኛው መ/ክ/ዘ ብራና ጽሑፍ እንደኾነና እርሱን መነሻ ማድረግ እንደሚቻል፥ «የራእየ ማርያም ትርጉም ችግር» በሚል ርእስ ለዐደባባይ ብሎግ በጻፉት ጥናት ገልጸዋል፡፡
የብራና መጻሕፍት ሲቀዱ/ሲገለበጡ፣ በቅጅዎቹ ጥራት ላይ የጸሐፊዎቹ/ቀጅዎቹ ጥንቃቄ ወሳኝነት እንዳለው የሚጠቅሱት ዶ/ር አምሳሉ፣ የአንድ መጽሐፍ ከአንድ በላይ ቅጅዎች(different versions) መኖር፣ ተርጓሚው የትኛውን ቅጅ በምን መስፈርት እንደመረጠ ካላስቀመጠ፣ የመጽሐፉን ታሪክ(literary history of the text) በትክክል ለመረዳት አስቸጋሪ እንደሚያደርገው አስገንዝበዋል፡፡
እነዚኽን ኹሉ ኹኔታዎች ከግምት በማስገባት፣ የራእየ ማርያምን የአማርኛ፣ በተለይ የ1961 ዓ.ም. ትርጉም ሲታይ፣ ግእዙን ሙሉ በሙሉ ካለመተርጎሙም በላይ ግእዙ የሌሉና የመጽሐፉም ዓላማ ያልኾኑ ቃላትን መያዙን ምሁሩ አስረድተዋል፡፡
የ1961 ዓ.ም. የራእየ ማርያም የአማርኛ ትርጉም፣ ከመሠረቱ የሌሉ ቃላትን አካቷል፡፡ በግእዙ ላይ “ኦሮሞ፣ ከሻንቅላ ከፈላሻ” የሚል የለም፡፡ ይህ ተርጓሚዎቹ ያስገቡት እና የጨመሩት ሐረግ ነው፡፡ ይህን የተረጎሙት ሰዎች፣ የዘነጉት መሠረታዊ ነገር፣ ራእየ ማርያም መጽሐፍ ኢትዮጵያ ውስጥ የተደረሰ አለመኾኑን ነው፡፡ ከላይ እንደተብራራው መጽሐፉ፣ ከግሪክና ዐረብኛ ወደ ግእዝ የተተረጎመ ነው፡፡ ስለዚኽ መጽሐፉ በምንም ዓይነት መንገድ፣ “ኦሮሞ ከሻንቅላ ከፈላሻ” ሊል እንደማይችል መረዳት ይገባል፡፡ የአንድን መጽሐፍ የትመጣ ታሪክ ማወቅ የሚጠቅመው፣ እንዴት ተብሎ መተርጎም እንዳለ ስለሚረዳንና ማብራሪያም ቢያስፈልግ ለአንባቢ መግለጽ ጠቃሚ ስለኾነ ነው፡፡ በ1961 ዓ.ም. የአማርኛ ትርጉም ላይ ከምናየው አንዱ ችግር ይህ ነው፡፡ በኋላ በታተሙ የራእየ ማርያም የአማርኛ ትርጉሞች “ኦሮሞ ከሻንቅላ ከፈላሻ” የሚሉ ቃላት የሉም፡፡ ይህ መሠረታዊ ስሕተት መታረሙ ያስመሰግናል፡፡
… በግእዝ የተጻፉ ኹሉ በቤተ ክርስቲያን ተቀባይነት ያገኙ መጻሕፍት ናቸው፣ ማለት አይደለም፡፡ በግእዝ የተጻፉ የክርስትና ሃይማኖትን የሚፃረሩ ጽሑፎች፣ በመናፍቃን የተዘጋጁ መጻሕፍት፣ የአስማትና የጥንቆላ መጻሕፍት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተቀባይነት የላቸውም፡፡ እነዚኽንና የመሳሰሉትን መጻሕፍት አንዳንድ ሰዎች እየገለበጡ ሰዎች ቢያባዟቸው፣ ወደ አማርኛ ቢተረጉሟቸውና ቢያሠራጯቸው፣ በተደጋጋሚም ቢያሳትሟቸው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መወቀስ የለባትም፡፡ መጠየቅ ያለባቸው፣ ለግል ጥቅም ሲሉ ይህን የመሰለ ጥፋት በመተርጎም፣ በማሳተምና በማከፋፈል በየዋህ ሕዝብ ላይ የሚፈጽሙ ሰዎች ናቸው፡፡ የትርጉም ሥራውም የሞያው ሥነ ምግባር ባላቸው ሰዎች በጥንቃቄ መሠራት ይኖርበታል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅዱሳት መጻሕፍትን ቀኖና፣ ፹፩ ብላ ሠፍራ ቆጥራ እንዳስቀመጠቸው ሌሎቹንም ሕዝቡ የማያውቃቸውንና በቀላሉ ሊያገኛቸው የማይችላቸውን የግእዝ መጻሕፍት መዘርዘር፤ ከቤተ ክርስቲያን ምሁራን ውጭ በስሟ የተጻፉትን ዘርዝራ ለምእመናን ማሳወቅ ይጠበቅባታል፡፡ ካሏት በርካታ መጻሕፍት፣ ውስጥ መተርጎም ያለባቸውን፣ ሊቃውንትን መድባ ተጠቃሽ የኾነ መጽሐፍ ማዘጋጀት አለባት፡፡ ይህን የሚሠራው የሊቃውንት ጉባኤ የሠራቸው፥ እንደ ስንክሳር – 1994፤ ግብረ ሕማማት – 1996 ያሉ፥ የቤተ ክርስቲያን ተጠቃሽ ኅትመቶች(authoritative texts) አሉ፡፡ በዚኽ መልኩ የሌሎቹም መጻሕፍት ትርጉም ተዘጋጅቶ ቢቀርብ ብዙዎችን ከስሕተት መጠበቅ ይቻላል፡፡
ብፁዕ ዶ/ር አቡነ ገሪማ፣ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፩ኛ ዓመት በዓለ ሢመት ላይ፥ “ንጹሐን ከሚኾኑ ከሕግ ምንጮች የተገኘ ጥሩ ምንጭ፣ ይኸውም የሐዋርያት የሥራቸው ነገር ነው፤” በሚል መነሻ ባቀረቡት ጽሑፍ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ማድረግ ያለበትን በሚከተለው መልኩ ጠቁመው ነበር፤
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገልገያዎች ቅዱሳት መጻሕፍት ከዓረብኛ ወደ ግእዝ የተተረጐሙት፣ በ፲፭ኛው መቶ ዓመት፣ ዳግማዊ ቆስጠንጢኖስ የሚል ስያሜ በተሰጠው በዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት በመኾኑ፣ ከዓረብኛ ወደ ግእዝ ከተተረጐሙት ቅዱሳት መጻሕፍት መካከል ፍትሐ ነገሥት እና ተኣምረ ማርያም ይገኙበታል፡፡
“ወሰብአ ኢትዮጵያሰ ኢይሢሙ ሊቀ እማዕምራኒሆሙ” የሚለው፣ በ፯ኛው መቶ ዓመት የገባው ሥርዋጽ ከዓረብኛ ወደ ግእዙ ተተርጉሞ በመቅረቡ፣ ፫፻፲፰ቱ ቅዱሳን አበው የደነገጉት አንቀጽ ነው፤ በሚል ደግነት ይኹን የዋህነት፣ ኢትዮጵያውያን ለ፲፮፻ ዘመናት ያህል ተቀብለው ኖረናል፡፡
ከታሪካችን እንደምንረዳው ብሔራዊና ሃይማኖታዊ ስሜት የነበረው በ፲፩ኛው መቶ ዓመት የነገሠው ቅዱስ ሐርቤ ወስመ ጥምቀቱ ገብረ ማርያም፦ የኢትዮጵያን ስፋት፣ የሕዝበ ክርስቲያኑን ብዛት በማየትና በመመልከት መላ ኢትዮጵያን ዞረው፤ ተዘዋውረው በሕዝቡ ቋንቋ የሚያስተምሩ፣ የሚባርኩ፣ የሚቀድሱ፣ የሚክኑ ዐሥር ኢትዮጵያውያን ቆሞሳት፣ የኤጲስ ቆጶስነት ሥልጣነ ክህነት በመስጠት እንዲሾምለት በምስር ካይሮ የመካነ መአልቃውያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጠይቆ ነበር፡፡
ይኹንና ከላይ የተጠቀሰውን በ፯ኛው መቶ ዓመት የገባውን ሥርዋጽ ተገን በማድረግ፣ የካይሮው ቅዱስ ሲኖዶስ ለንጉሥ ሐርቤ ተገቢውን መልስ ካለመስጠቱም በላይ፣ ሚያዝያ ፲ ቀን በሚነበበው የስንክሳር መጽሐፋችን፣ “ወበዛቲ ዕለት” በሚለው፥ “ኢትዮጵያውያን የማይገባቸውን ኤጲስ ቆጶስነት ስለተመኙና ስለፈለጉ እግዚአብሔር ተቆጥቶ በሀገራቸው ላይ ሦስት ዓመታት ሙሉ ጠል ለመከር፣ ዝናም ለዘር ከልክሏቸው በድርቅ ቀጣቸው” በማለት፣ ግብጻዊው ፓትርያርክ ገብርኤል ዳግማዊ በታሪክ መዝግቦት ይገኛል፡፡ እኛም ይህን ስንክሳር እንደ መልካም ነገር አድርገን፣ ሚያዝያ ፲ ቀን ወበዛቲ ብለን እናነበዋለን፡፡
ይህ ወበዛቲ ዕለት የሚለውንና “ወሰብአ ኢትዮጵያሰ ኢይሢሙ ሊቀ እማዕምራኒሆሙ” የሚለውን፣ ቅዱስ ሲኖዶስ አስቦበት፣ ከዚኽ ጊዜ፣ ከዛሬ ዕለት ጀምሮ፣ ከስንክሳሩ እና ከፍትሐ ነገሥቱ ቢያወጣው ያማረ፣ የሰመረ ታሪክ በኾነ ነበር፡፡
የቀድሞው የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስም፣ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን” መጽሐፋቸው፣ የሥርዋጹን ዳራ በተመሳሳይ መልኩ ከገለጹ በኋላ የሚከተለውን አስፍረዋል፦
… ነገር ግን እግዚአብሔር እንዲኽ ያለውን የተቀደሰ ሐሳብ ይባርካል እንጅ በዚኽ አይቆጣም፡፡ እንደ አጋጣሚ ኹኖ በዚያ ዘመን ድርቅ ወይም በሽታ በሀገሪቱ ላይ ቢወርድም፦ “ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት እንዳይሾሙ፣ እግዚአብሔር ተቆጥቶ ያመጣው ነው፤” ማለት እውነት አይደለም፡፡ ከአባ ገብርኤል በኋላ የተነሡ አባ ዮሐንስም፣ የአባ ገብርኤልን እልክ ተከትለው፣ ለኢትዮጵያውያን ኤጲስ ቆጶስነትን አልሰጥም አሉ፡፡
ያም ኾነ ይህ፣ በቅዱስ ሐርቤ አነሣሽነት የተጀመረው ጥያቄ ዛሬ ተሟልቶ፣ ኢትዮጵያ የራሷን ልጆች በራሷ መሬት ላይ እስከ ፓትርያርክነት ለመሾም ስለበቃች፣ የቅዱስ ሐርቤ ሐሳብ ተፈጸመ ለማለት ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም ኹልጊዜ በታሪክ ስታውሰው ትኖራለች፡፡ በዚያ በጨለማው ዘመን፣ ይህን ራስን የመቻል ሐሳብ ያፈለቀ ቅዱስ ንጉሥ ነውና፡፡ /ገጽ 36 እና 37/