ደም እና  ዕንባ

 

 

( ግንቦት 1997 ዓ . ም . የግፍ ዕልቂት 12 ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ )

ኢትዮጵያችን ልዩ ዕትም  ቅ ጽ 1 ቁጥር 4……… ………………… ……………………………………………………………….…………………………………………………………………………. ………………… ግንቦት ፯ ቀን ፪ ሺህ ፱ ዓ .ም.

ኢትዮጵያችን በተለያየ ምክንያትና ወቅት በርካታ ልጆቿን አጥታለች። ራቅ ብለን የታሪክ ማህደርን ብናገላብጥ ዛሬ ላለችው ኢትዮጵያችን ህልውና በርካቶች ደማቸውን በፍቅር አፍስሰውላታል። ቀሪዎች አንብተውላታል። በደርቡሽ፣ በመቅደላ፣ በዐድዋ፣ በዶጋሌ፣ በሽምብራ ኩሬ፣ በማይጨው፣ በሶማሌ፣ በባድሜ ወዘተ ጦርነቶች በርካታ ጀግኖቿንና ልጆቿን ኢትዮጵያችን አጥታለች። ለሀገሩ ክብርና ለዳር ድንበሩ መከበር ከመሪ ነገሥታቶቿ ጀምሮ ክቡር ሕይወትን የለገሱ፣ አኩሪ ታሪክ አስመዝግበው ያለፉ በዘረኝነት ወጥመድ ሳይሆን ኢትዮጵያዊነትን አንግበው ነው። ኢትዮጵያ ሲባል አብሮ ማለት ብቻ ሳይሆን ሞተውላታል። ዕንባቸውን ለማፍሰስ “. . . ሀገር ከሌለ በማን ይለቀሳል” በሚል ጀግንነት በሕይወታቸው ኢትዮጵያን አስረክበውናል። ዛሬ ይህች ኢትዮጵያችን በመንግሥትና በዘረኞች እኩይ ፍላጎት ወደ መበታተንና መገነጣጠል እንዳታመራ የጋራ ጥረትን ይጠይቃል።
እኛ ኢትዮጵያ ስንል የተለያዩ ጎሳዎቿን፣ የተለያዩ ቋንቋዎቿን፣ የተለያዩ ሃይማኖቶቿን፣ የተለያዩ ባህሎቿን ብርቅዬነት ያካተተችዋን አንድ ኢትዮጵያ፣ አንድ ሕዝብ ነው። እኛ ኢትዮጵያ ስንል ለልጆቿ የዜግነትና ዴሞክራሲያዊ መብት ያለ ገደብ ምታጎናጽፈዋን ነው። እኛ ኢትዮጵያ ስንል ከገነጣጠሏትና ሊገነጣጥሏት ካሰፈሰፉት ጉያ ሥር ተወሽቀን አይደለም። እኛ ኢትዮጵያ ስንል አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማዋን ከፍ አድርገን እያውለበለብን ነው። እኛ ኢትዮጵያ ስንል ዘረኝነትን አስቀድመን አይደለም። እኛ ኢትዮጵያ ስንል የጥቂት አምባገነኖችና ዘራፊዎች ሳይሆን ለመላው ሕዝቧ የሆነችውን ኢትዮጵያ ነው። ይህቺን ኢትዮጵያ ራዕያችን አድርገን ከዘረኛው የወያኔ/ህወሀት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ልናላቅቃት፣ አለንልሽ ላልናት ሀገራችን የተከፈለውንና እየተከፈለ ያለውን መስዋዕትነት ክብር በመስጠት፤ ወቅቱን ጠብቀን በማስታወስ ነው። ያፈሰሳችሁት ደም፣ የከሰከሳችሁት አጥንት የኢትዮጵያዊነት የድል ሐውልት እንደሚሆን ጥርጣሬ አይገባንም እያልን ነው።
“አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ” የዛሬ ልዩ ዕትማችንን የዛሬ 12 ዓመት በወያኔ የግፍ ጥይት ለተጨፈጨፉት የግንቦት 1997 ዓ.ም. ሰማዕታት ይኸው ትውስታችን በማለት ነው። የ1997 ዓ.ም. የምርጫ ፖለቲካ ህወሀት/ኢሕአዴግ ሽንፈትን በደም ያጠበበት ወቅት፣ ሥልጣኑን በሽብርና በሕፃናት፣ ወጣቶች፣ አዛውንት እናትና አባቶች ደም ያራዘመበት ወርሃ ግንቦት 1997 ዓ.ም. ሊረሳ አይገባውም። ይህንን ቀን ስናስታውስ ለሰው ልጅ ደም፣ ለንፁሃን ደም ኢትዮጵያ ምንጊዜም እየጮኸችና እንደምትጮህ ጆሯቸው አልሰማ ላለ እንደ ገደል ማሚቶ ዳግም እያስተጋባን ነው። ታሪክ እራሱን ይደግማል ነውና በግንቦት 1997 ዓ.ም. በዘረኛው ወያኔ በሕዝብ ላይ የደረሰው አሰቃቂ ሽብርና ግድያ፣ እየዬና ዋይታ ኢትዮጵያን ዳግም አስታወሳት። የ10 ዓመት ሕፃን ሳይቀር የተገደለበት፣ “ልጄን” ብላ ለሮጠች እናት ጥይት የተቸራት፣ ልጅህን አምጣ ተብሎ የተገደለ አባት፣ ከደርግ ቀይ ሽብር በኋላ ዳግም ብልጭ ያለበት የግንቦት ወር 1997 ዕንባ ዛሬም ውስጣችን አለ። የሕፃን ሽብሬ ደሳለኝንና መሰሎችን ደም ለጠጣ ወያኔ/ህወሀት/ኢሕአዴግ ጥምር አገዛዝ የፍርድ ቀን ካልመጣ “ሕግ ምኑን ሕግ ሆነ?”
ግንቦት 97 በኢትዮጵያ ሕዝብ የትግል ታሪክ ከየካቲቱ 66 ሕዝባዊ አብዮት ቀጥሎ የተከሰተ ሕዝባዊ ማዕበል ነበር። መሪ ያጣው የካቲት አብዮት ፋሽስት መንግስቱ ኃይለማርያምን ሲያነግስ፤ የግንቦት 97 እንቅስቃሴ ወያኔን እንደተሸከመ አሥራ ሁለት ዓመት አስቆጠረ። በሁለቱም የከሸፉ አብዮቶች አምባገነኖችና ዘረኞች በጠጡት ደም ኢትዮጵያ አንብታለች። የሰው ልጅ መብት ተከርችሟል። እጅና እግሮች ለካቴናና እግር ብረት ተዳርገዋል።
ኢትዮጵያችን ልዩ ዕትም  ቅ ጽ 1 ቁጥር 4……… ………………… ……………………………………………………………….…………………………………………………………………………. ………………… ግንቦት ፯ ቀን ፪ ሺህ ፱ ዓ .ም.

ከነኚህ የከሸፉ ሁለት ሕዝባዊ ንቅናቄዎች መማር የሚገባን ቢኖር ትግል መደራጀትን መጠየቁን ነው። በሕዝብ ሀብት እጅግ ዘመናዊ መሣሪያ የታጠቀን፣ የስለላ መረቡን በቤተሰብ ደረጃ የዘረጋ፣ ሕዝባችንን በዘርና በጎሳ የከፋፈለ፣ ተከባብሮ ያለ ሃይማኖታችንን ሊያበጣብጥ መርዙን የረጨ፣ መናቅ የሌለበት አጥፊ ኃይል ለመታገል ከመደራጀት በተጨማሪ ብልህ አመራርን ይጠይቃል።
ዘር፣ ሃይማኖት፣ ዕድሜ፣ ክልል ሳይገድበው በመላዋ ኢትዮጵያ የሕዝብን ጥያቄ አንግቦ የተነሳው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) አነሳስና አወዳደቅ የትግል ትምህርት ቤት ሊሆን ይገባል። የየካቲት 66 ሕዝባዊ አብዮት ዓመት ባልሞላው ጊዜ በደርግ አቅጣጫውን በመሳቱ ለመደራጀትና ሕዝብን ለማሰባሰብ የተጠቀመበት ኢሕአፓ በአጭር ጊዜ መሠረቱን ሊጥል ቢችልም ለሕዝባዊ ድል ሊበቃ ግና አልቻለም። ለምን? ጊዜና ወቅትን እያገናዘቡ፣ የጠላትን የኃይል ሚዛን እየመረመሩ፣ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን እየገመገሙ ትግሉን ከግብ ማድረስ ከመደራጀት የበለጠ ብልህነትን ይጠይቃል፣ የአመራር ብቃትን ያሳያል። ኢትዮጵያን ለኢትዮጵያውያን ለማድረግ ትግሉ እየገደሏት ካሉት ብቻ ሳይሆን ከገደሏትም ጋር ነውና ከአለፉት በርካታ ስህተቶች ትምህርት ልንቀስም ካልቻልን ሀገርን ከአምባገነኖች ማላቀቅ በቀላል የሚታይ አይሆንም።
ከ14 ዓመት የወያኔ/ኢሕአዴግ አገዛዝ በኋላ “እምቢኝ ለሀገሬ” ብሎ የወያኔ ዘረኛ ፖሊሲ ሳይበግረው እጅ ለእጅ ተያይዞ በአንድ ኢትዮጵያዊነት መንፈስ የተነሳው የግንቦት 97 እንቅስቃሴ ሲከሽፍ “ለምን?” ብለን ጠይቀን ቢሆን የመስከረም 2009 ዓ.ም. የተለያዩ አካባቢ እንቅስቃሴዎች መሪ ድርጅት ማጣት ባልተከሰተ ነበር። በግንቦት 1997 ዓ.ም. የተከሰተውን ኢትዮጵያዊነት ሀገራዊ ስሜት ተጠቅመንበት ቢሆን ዛሬ ከዘርም አልፎ በአካባቢ ተሸንሽኖ መደራጀት አየሩን ባልሞላው ነበር።
ኢትዮጵያን ለማዳን “ኢትዮጵያ አይልም ወይ…” እንዳለው ድምጻዊ ለወያኔ የተመቸውን ዘረኝነት በማጋጋል ሳይሆን ኢትዮጵያችን ብለን ስንነሳ ስኬታማ እንሆናለን። በምንም መልኩ የዘር ፖለቲካ ከኢትዮጵያዊነት ሊልቅ አይገባውም፣ አይችልምም። ወደድንም ጠላን ኢትዮጵያን ከትግራይ፣ ኢትዮጵያን ከኦሮሞ፣ ኢትዮጵያን ከአማራ፣ ኢትዮጵያን ከጉራጌ፣ ኢትዮጵያን ከጋምቤላ፣ ኢትዮጵያን ከአፋር፣ ኢትዮጵያን ከሀደሬ፣ ኢትዮጵያን ከወላይታ፣ ኢትዮጵያን ወዘተ. ወዘተ. ነጥለን ኢትዮጵያችን ብለን መጮህ ስህተት ነው። ቴዎድሮስ የኢትዮጵያ፣ አሉላ የኢትዮጵያ፣ ዮሐንስ የኢትዮጵያ፣ ምኒልክ የኢትዮጵያ፣ ካልን ምስክርነታችን ለተዋደቁላት እናት ኢትዮጵያ ይሆናል።
ሊቁ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ፡
የሹም-አጥርን ካማራ፡ ጎበናን ከኦሮሞ፡  አሉላን ከትግሬ። ከጉራጌ ነስሩን፡ ጦናን ከወላሞ አልያን ከአደሬ። በፍቅር አንድነት፡ ለውቀት ስልጣኔ። . . .

ያሉት ዘመን ያለወጠው፣ ግዜ ያልሸረሸረው እምቅ ግጥማቸው ዛሬ ያለንበትን ዘመን ጠያቂ መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል።            . . . ያለበለዚያ ግን፡ ሁኔታችን ሁሉ፡                የንቧይ ካብ፡ የንቧይ ካብ።. . .
ኢትዮጵያችን ልዩ ዕትም  ቅ ጽ 1 ቁጥር 4……… ………………… ……………………………………………………………….…………………………………………………………………………. ………………… ግንቦት ፯ ቀን ፪ ሺህ ፱ ዓ .ም.
ያሉት እኛ ላይ ሲደርስ እውን እንዳይሆን ነቅተን መጠበቅ ይኖርብናል። ነገራችን ሁሉ ከንቱ አይሆን ዘንዳ ምኞታችን ከሆነ ሁሉን ጎሳ ይዘን ኢትዮጵያ እንበል።

ስለምን?  ጎሳው ወይም ነገዱ የእኔ በሚላቸው ፍላጎት ላይ የተንተራሰ የትግል ዘይቤ ወይም የእኔ ጎሳ፣ የእኔ ነገድ ከሌሎች ጎሳዎች በበለጠ ተጠቅቶአል በሚል ምክንያቶች ዘርን ተገን ባደረገ አተሳሰብ ላይ ከተደራጀን ቀስ በቀስ ሀገር አቀፉ ትግል እየጫጫ፤ የጎሳዊ፣ የነገዳዊ ትግል እየጎላ መሄዱ አይቀሬ ነው። ይህም ደሞ ያለንበትን የወያኔ/ህወሀት ዘረኝነት ሳንወጣ ሌላ ትግል አጫሪና በተለያየ አቅጣጫና መስመር የተሰለፈውን የጎሳና የነገድ ቀጠና ወደ አንድ የኢትዮጵያ ወረዳ ለመመለስ አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን አደገኛም ነው።
በመሆኑም ከ“ድጡ ወደ ማጡ” መሄድ አይኖርብንም። ሁኔታችንም “የምቧይ ካብ” መሆን የለበትም።
ስለሆነም! የእኛ “ኢትዮጵያችን ንቅናቄ” በነገድ እና በጎሳ ዓይን ሳይሆን፤ በሀገር አቀፍ፣ በኢትዮጵያ ዓይን ተመልካች በመሆኑ ለዚህም ዓላማ ዘብ ቆመናል።

ዛሬ የግንቦት 97 አስራሁለተኛ ዓመትን ስናስታውስ የትግሉን መሪ መፈክር ኢትዮጵያዊነታችን መሆኑን ከፍ በማድረግ አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ ብለን ለመሰባሰብ በመዘጋጀት ነው። ሀገራችን ኢትዮጵያና መላው ሕዝባችን ላይ በወያኔና አጫፋሪዎቹ የተደቀነውን አስከፊ አደጋ እንዴት እንከላከለው? ልዩነታችንን አቻችለን፣ የጋራ ትግላችንን በጋራ እንድ ሆነን፣ ተሰባስበን አብረን ለመነሳት ምን ማድረግ አለብን? ይህን በቋፍ ያለ ዘረኛ አገዛዝ እናኮማትረው ዘንድ ኃይልና አለኝታችን ሕዝባችን ነውና ከሕዝብ ጋር ሆነን ብሶቱ ብሶታችን፣ ስቃዩ ስቃያችን ሁኖ እየተካሄደ ያለውን ፀረ-ወያኔ ትግል በበላይነት ለመምራት ወያኔን መለመን ሳይሆን ለምኖን እንዲንበረከክ ያለንበትን ጉዞና አቅጣጫ ቆም ብሎ መመርመር ከሁሉም ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የብዙሃን ድርጅቶች፣ የሃይማኖት ተቋሞች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ምሁራን፣ ወጣቶች፣ ሴቶች እህቶቻችን፣ በውጭው ዓለም ተበትኖ ካለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ብዙ ይጠበቃልና ቀና ብለን ሀገራችንንና ሕዝባችንን እንመልከት።
ግንቦት 97 ሲባል የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሀገሩ፣ ለዳር ድንበሩ፣ ለነፃነቱ ከፍተኛውን ተጋድሎ ያደረገበትና መስዋትነት የከፈለበት በመሆኑ ነው የሚታወሰው። የሕዝብ የ14 ዓመት የነጻነትና የመብት ተጋድሎ ውጤት የፈጠረውን የግንቦት 97 እንቅስቃሴ ስናስታውስ በፍልሚያው ሜዳ የተሰዉትን እየዘከርንና ለፈሰሰውም ደም ወያኔ/ኢሕአዴግን ተጠያቂ እያደረግን፣ ወያኔ በአገዛዝ ዘመኑ ደብዛቸውን ያጠፋቸውን ሁሉ የት እንደደረሱ እየጠየቅን፣ አካለ ስንኩል ያደረጋቸውን እያበረታታን፣ የስደት ኑሮ ቀማሽ ያደረጋቸውን አንድነታችሁ ይጠንክር እያልን፣ በየማጎሪያው የሚያሰቃያቸውን የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ መፈታት እየታገልን በአጠቃላይም ለሀገራችንና ለሕዝባችን ዘለቄታዊ ሰላምና አንድነት የትግል አርማችንን እያደስን መሆን ይኖርበታል።
በወያኔ/ኢሕአዴግ በ26 ዓመት አገዛዝ ዘመኑ ለፈሰሰው የግፍ ደም፣ የጅምላ ጭፍጨፋ፣ የሀገር ሀብትና ንብረት ዘረፋ ተጠያቂዎችን ለፍርድ ለማቅረብ የፍትህ ያለ! የሀገር ያለህ! የሕዝብ ያለህ! በሚል መርህ መመራትን ይጠይቃል። የፍትህ መጓደልና አምባገነንነት ዳግም እንዳያንሰራራ ካስፈለገ አጥፊዎችን ሀገርና ሕዝብ ለሕግ መስጠት ይኖርባቸዋል። በወንጀልና በደም የተጨማለቁ ተጠያቂነትን ስለሚፈሩ እራሳቸውን እንጂ ሀገርና ሕዝብን አይጠብቁም፣ አይከላከሉምና ለሀገር አንድነት ስንል ውስጣችን ሰግስገናቸው መጓዙ ጥቅሙ ሳይሆን ጉዳቱ ሚዝን እንደሚደፋ ግንዛቤ መውሰድ ይጠበቅብናል። ኢትዮጵያችንና ሕዝባችን የፍትህ ያለህ ያሉት ላለፉት 26 ዓመታት ሳይሆን
ኢትዮጵያችን ልዩ ዕትም  ቅ ጽ 1 ቁጥር 4……… ………………… ……………………………………………………………….…………………………………………………………………………. ………………… ግንቦት ፯ ቀን ፪ ሺህ ፱ ዓ .ም.

በትንሹ 53 ዓመታት መሆኑን የጉዳቱ ሰለባዎች ብቻ ሳይሆኑ ስለ ሰው ልጅ ሚሞግቱ ሁሉ ይገነዘቡታል። የመንግስት ስልጣንን መከታ አድርጎ እንደ እንሰሳ የፈሰሰ የንጹሐን ደም ሁሌም ይጮሃልና የግፍ ዕንባ ያበቃ ዘንድ ክንዳችንን በጋራ እንድናነሳ “አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ” ጥሪአችን ሁሌም ይቀርባል።
የዜግነት ክብር ለሰፈነባት ኢትዮጵያችን ዘብ እንቆማለን!!!

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር! እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ! “አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ”

ግንቦት 7 ቀን 2009 ዓ.ም. (May 15, 2017)

ዋቢ ማጣቀሻ፦
 “ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ አጭር የሕይወቱና የጽሁፉ ታሪክ”፤ ዮሐንስ አድማሱ እንደጻፈው 1929 – 1967፤ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ፕሬስ 

 

“ኢትዮጵያ” ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ሚያዝያ 2009 ዓ.ም. አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ  “ግንቦት ሰባት ሁለት ዓመት ሆነው”፤ ግንቦት 02 ቀን 1999 ዓ.ም. አቶ ተማቹ
ማሳሰቢያ ፡

 ውድ ወገኖቻችን ይህንን «አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ» « ኢትዮጵያችን » ልሳን በተለይ በሀገር ቤት ኮምፒዩተር የማግኘት ዕድል ለሌላቸው በማባዛት ታሰራጩት ዘንድ ቀና ትብብራችሁን በትህትና እንጠይቃለን። 

 

«አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ» መስከረም 8 ቀን 2009 ዓ.ም. እራሱን ይፋ ያደረገ ሕዝባዊ ድርጅት ሲሆን የንቅናቄውን ማንፌስቶና ፕሮግራም  www.ethiopiachen.org ከሚለው ድረ ገጻችን ማግኘት ትችላላችሁ።

ኢሜል ፡ ethiopiachen2009@gmail.com           info@ethiopiachen.org

ድረ ገጽ ፡ www.ethiopiachen.org            www.ethiopiachen.com ምስለ ገጽ : 1H1H Ethiopiachen