ሐራ ዘተዋሕዶ

May 15, 2017

. እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ያለውን የፍትሕ ሥራ በማቀናጀት ተግባሩን ይወጣል
. የፍትሕ ዕጦት የተንሰራፋው፣ መንፈሳዊ ፍርድ ቤቱ የይስሙላ መዋቅር በመኾኑ ነው
. ከፓትርያርኩና ከጠቅ/ቤተ ክህነቱ ክፍሎች ጣልቃ ገብነት እንዲጠበቅ ይደረጋል ተብሏል
. ለፓርማው የተላከው የመንፈሳዊ ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ ዐዋጅ፣ ውሳኔ አላገኘም
መንበረ ፓትርያርክ ከኾነው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጀምሮ በቤተ ክርስቲያናችን የተንሰራፋውን፥ የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ የሥነ ምግባርና የውሳኔዎች አስፈጻሚ ማጣትን ችግሮች ለመቅረፍ፣ የቤተ ክህነቱን መዋቅር መልሶ በማደራጀት ማሻሻል እንደሚገባ በመሠረታዊ ችግሮች ላይ የተካሔደው ጥናታዊ ሪፖርት ያመለክታል፡፡
መዋቅሩን መልሶ ከማደራጀት ጋራ በተያያዘ፣ ወጥ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት፣ ቤተ ክርስቲያን ዋነኛ ተልእኮዋን በብቃት እንድትወጣ ለማድረግ የሚያግዙ ሕጎች፣ ደንቦችና የአሠራር ሥርዓቶች እንደሚያስፈልጓትና ያሉትም ተሻሽለውና ተስተካክለው እንደገና መጻፍ እንዳለባቸው ጥናታዊ ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡
በዐዲስ መልኩ እንዲወጡ ከተጠቆሙት ሕጎችና ደንቦች መካከል፥ የቤተ ክርስቲያኒቱን የዳኝነት ሥርዓት የሚደነግገው ሕግ የሚገኝበት ሲኾን፣ ከቅዱስ ሲኖዶሱ፥ የፍርድ፣ የሕግና ሥነ ሥርዓት ተግባርን በሚመለከት ያለውን ሥልጣን፣ ከቋሚ ሲኖዶሱ ጽ/ቤት ውጭ በማድረግ፣ በጠቅላይ መንፈሳዊ ፍርድ ቤት እና በሕግና ሥነ ሥርዓት ኮሚሽን እንዲዋቀር፣ጥናቱ ባቀረበው አማራጭ አደረጃጀት አሳይቷል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶሱ የሕግና ሥነ ሥርዓት ኮሚሽን፣ በኮሚሽነር እንዲመራ በማድረግ፦ የሕግ፣ የሥነ ሥርዓት፣ የኦዲት፣ የቁጥጥር፣ የመሳሰሉት ከተጽዕኖ ነጻ በኾነ መልኩ መሠራት ባለባቸው ጉዳዮች ላይ እንደሚሰማራ፤ የኮሚሽኑም ሓላፊ በቅዱስ ሲኖዶሱ በቀጥታ እንደሚመረጥና ተጠሪነቱም ለቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ እንደሚኾን በአማራጭ መዋቅሩ ተመልክቷል፡፡ በጠቅላይ መንፈሳዊ ፍርድ ቤቱም ኾነ በሕግና ሥነ ሥርዓት ኮሚሽኑ አሠራር፤ ፓትርያርኩ፣ ቋሚ ሲኖዶሱና የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ክፍሎች ከጣልቃ ገብነት ሊጠበቁ እንደሚገባ ጥናቱ ያስገነዝባል፡፡
የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ በዛሬ፣ ግንቦት 7 ቀን 2009 ዓ.ም.፣ የቀትር በፊት ውሎው፣ ጥናታዊ ሪፖርቱንና የከፍተኛ ኮሚቴውን ማብራሪያዎች በማዳመጥ ተወያይቶበታል፡፡ የዳኝነት ሥርዓቱን መልሶ በማደራጀት፣ ጠቅላይ መንፈሳዊ ፍርድ ቤቱን በገለልተኝነት ማዋቀር እንደሚያስፈልግ በጥናቱ የተጠቆመውን በተመለከተ፣ ሰንደቅ ጋዜጣ ባለፈው ሳምንት እትሙ ተከታዩን ዘገባ አውጥቷል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መዋቅራዊ አደረጃጀት፣ የሥራ አስፈጻሚውና የዳኝነቱ ሥራ መቀላቀሉ፥ ለአሠራር ሥርዓት ክፍተት፣ ለመልካም አስተዳደር ዕጦትና ለፍትሕ መዛባት ምክንያት እንደኾነ የሚጠቅስ ጥናት ለቅዱስ ሲኖዶሱ የቀረበ ሲኾን፤ የዳኝነቱን ተግባር በገለልተኝነት የሚሠራ ጠቅላይ መንፈሳዊ ፍርድ ቤት እንዲዋቀር ተጠየቀ፡፡
የቤተ ክርስቲያንን መሠረታዊ ችግሮች አጥንቶ ከመፍትሔ ሐሳቦች ጋራ እንዲያቀርብ ቅዱስ ሲኖዶሱ ባለፈው ዓመት ጥቅምት ምልአተ ጉባኤ የሠየመው ከፍተኛ ኮሚቴ ባረቀበው ጥናታዊ ሪፖርት፥ በጠቅላይ ቤተ ክህነት እና በሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ደረጃ የተቋቋመ መንፈሳዊ ፍርድ ቤት ቢኖርም፣ የአሠራር ደንብ ያልተዘረጋለትና ብቁ ባለሞያዎች ያልተካተቱበት የይስሙላ መዋቅር መኾኑን ተችቷል፡፡
ለቅዱስ ሲኖዶሱ ተጠሪ ኾኖ የተቀመጠው መንፈሳዊ ፍርድ ቤቱ፣ የዳኝነትና የፍትሕ ተግባር ከመሥራት ይልቅ፣ በሥራ አስፈጻሚው ጥላ ሥር ኹኖ የአስፈጻሚነት የሚመስል ሥራ መሥራቱ፤ የአስተዳደር በደል ደርሶብኛል የሚለው ካህንና ምእመን፣ ተገቢውን ፍትሕ እና የዳኝነት አገልግሎት እንዳያገኝ ምክንያት መኾኑን ጥናታዊ ሪፖርቱ ገልጿል፡፡
ካህናትና ምእመናን፣ በብዛት እየተሰበሰቡ ውሳኔ ወደሰጣቸው አስፈጻሚና ወደ ዋናው የሕግ አውጭ አካል(ቅዱስ ሲኖዶስ) እንዲኹም ወደ መንግሥት መደበኛ ፍርድ ቤት ለመሔድ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ፣ እንግልትና መንከራተት በሰፊው ተንሰራፍቶ የሚታየው፥ መንፈሳዊ ፍ/ቤቱ፣ ቀድሞ በነበረው ልማድ ያለበቂ ሥራ በመቀመጡ እንደኾነ ጥናቱ አስረድቷል፡፡
በየመዋቅሩ የሚገኙት ሥራ አስፈጻሚዎች በሚሰጡት ውሳኔ ቅር የተሰኘ አካል የሚያቀርበውን አቤቱታና የፍትሕ ጥያቄ የሚተረጉምና የሚዳኝ ሥርዓት ባለመኖሩ፣ የአስተዳደር ሓላፊዎች ሥልጣናቸውን ያለገደብ እንዳስፈለገ የሚተገብሩበት አጋጣሚ በስፋት እንደሚታይ በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡
የመዋቅራዊ አደረጃጀት ችግር በተለይም፣ የሥልጣን በአንድ ቦታ መከማቸት እና የሕግ አውጭው፣ የሕግ አስፈጻሚውና የሕግ ተርጓሚው አካላት ተለይተው አለመደራጀታቸው፣ የተጠያቂነት ማለትም የእርስ በርስ ቁጥጥርና ሚዛን ሥርዓት እንዳይዳብር ያደረገ፦ የቤተ ክርስቲያን ችግሮች ኹሉ ዋነኛ መንሥኤ መኾኑን ጥናታዊ ሪፖርቱ አስገንዝቧል፡፡
መዋቅራዊ አደረጃጀቱ፥ የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ የሚያሳካ፣ ዓላማዎቿንና ግቦቿን ለማስፈጸም በሚያስችል አኳኋን፣ ስትራተጅያዊና መሠረታዊ በኾነ መልኩ መልሶ ሊደራጅና ሊስተካከል እንደሚገባ የጠቆመው ጥናቱ፤ በዐዲሱ መዋቅራዊ አደረጃጀት ለመሥራትም፣ ቅድሚያ ሊሰጣቸውና በአስቸኳይ ሊወጡ ይገባቸዋል ካላቸው ቃለ ዓዋዲዎች መካከል፥ የዳኝነት አካሉን ከነዝርዝር ተግባሮቹ እንዲኹም የመዋቅሩን ተዋረድና የአሠራር ሥርዓቱን የሚገልጽና የሚደነግግ ሕግ ይገኝበታል፡፡
በአጥኚ ኮሚቴው በቀረበው የዐዲስ መዋቅር አማራጭ መሠረት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ መንፈሳዊ ፍርድ ቤት፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ ሥልጣን ባለው በቅዱስ ሲኖዶስ፣ በገለልተኝነት መዋቀር እንዳለበት ነው የተጠቆመው፡፡
ፍርድ ቤቱ፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያን በተሰጠው ሓላፊነትና ሥልጣን፦ የፓትርያርክ፣ የቋሚ ሲኖዶስ እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ክፍሎች ጣልቃ እንዳይገቡና ሥራውን በገለልተኝነት እንዲሠራ፤ የመጨረሻ የይግባኝ የፍትሕ ዳኝነት ግን የቅዱስ ሲኖዶስ እንደኾነ በጥናቱ ተገልጿል፡፡ የፍርድ ቤቱ ችሎትና ዳኝነትም፣ በሚወጣው ደንብና መመሪያ መሠረት እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ያለውን የፍትሕ ሥራ በማቀናጀት ተግባሩን እንደሚወጣ ተጠቁሟል፡፡
ስድስተኛ ቀኑን ያስቆጠረው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ÷ በዛሬ፣ የቀትር በፊት ውሎው፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን አወቃቀር ጨምሮ የቤተ ክርስቲያንን መሠረታዊ ችግሮችና የመፍትሔ ሐሳቦች የሚጠቁመውን ጥናታዊ ሪፖርትና የከፍተኛ ኮሚቴውን ማብራሪያ አዳምጧል፤ ምልአተ ጉባኤውም በዚኹ ላይ በመመሥረት፣ የለውጥ ሥራውን በተግባር ለመጀመር የሚያበቃ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል፡፡
በሕገ ቤተ ክርስቲያን መሠረት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በምታስተዳድራቸው ካህናትና ምእመናን ላይ፣ የመንፈሳዊ ዳኝነት ሥልጣን ያላት ሲኾን፤ ወንጀል ነክ ከኾኑ ጉዳዮች ውጭ፦ ካህናት፣ ኤጲስ ቆጶሳትና ሊቃነ ጳጳሳት መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን በሚመለከት ቢከሠሡ ወይም ቢከሡ፣ ጉዳያቸው፣ በቤተ ክርስቲያን ሕግና ሥርዓት ይታያል እንጅ በመደበኛ ፍርድ ቤቶች እንደማይዳኙ ተደንግጓል፡፡ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ዳኝነት፣ እንደ ክሡ አቀራረብ እየተመዘነ ከሚታይባቸው አካላት መካከልም፣ መንፈሳዊ ፍርድ ቤት አንዱ እንደኾነ በሕጉ ተመልክቷል፡፡
ቤተ ክርስቲያን በ2003 ዓ.ም.፣ “የፌዴራል መንፈሳዊ ፍርድ ቤቶችን እንደገና ለማቋቋም፣ ለማደራጀትና ለማጠናከር የወጣ ዐዋጅ/ቁጥር 2003” በሚል የዳኝነት ሥርዓቷን ለማደራጀትና በኦፊሴል እንዲሠራበት ለማድረግ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ አጽድቃ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብትልክም፣ ውሳኔው በመዘግየቱ፣ ለአስተዳደር ሥራዋ ልታገኝ የሚገባትን የሕግ ድጋፍ እንዳላገኘች በአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ የጋራ መግለጫ አማካይነት ቅሬታዋን ማሰማቷ አይዘነጋም፡፡ ቅዱስ ሲኖዶሱም፣ ጉዳዩን ተከታትሎ የሚያስፈጽም አካል እንዲሠይም በመግለጫው መጠየቁ ተወስቷል፡፡