መንግሥት ደመወዝ ጨመረ፤ ከዚያስ?

Thursday, 03 July 2014 12:03

    


     መንግስት የዋጋ ንረትን በማይቀሰቅስ ሁኔታ የተጠና የመንግሥት ሠራተኞች የደሞዝ ማስተካከያ ከሐምሌ ወር 2006 ዓ.ም ተግባራዊ እንደሚያደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መግለጻቸውን ሰሞኑን ሰማን።

     ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለ8ኛ ጊዜ በተከበረው የሲቪል ሰርቪስ ቀን ላይ ተገኝተው የተናገሩት ይህ ቁምነገር በተለይ በሚሊየን ለሚቆጠረው የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞችና ቤተሰቦቻቸው የምስራች ነው። ይህንን ተከትሎ ግን የሲቪል ሰርቪሱ የአገልጋይነት መንፈስ ብዙም ባላንሰራራበትና ሁኔታ ደመወዝ መጨመር ብቻውን ፋይዳው ምንድነው የሚል ጥያቄን ያነሱ ወገኖች ቁጥር የትየለሌ ነው።

     በ2003 ዓ.ም መንግሥት በተመሳሳይ ሁኔታ ለመንግሥት ሠራተኛው የደመወዝ ጭማሪ አድርጎ እንደነበር ይታወሳል። ከዚያም በመቀጠል የመንግሥት ሠራተኞችና ኃላፊዎች የመዘዋወሪያ አበል እንዲሁ ተጠንቶ በሚኒስትሮች ምክርቤት ከጸደቀ በኋላ ከሐምሌ ወር 2004 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ መሆኑም የምናስታውሰው ነው። በዚህ መሠረት የዝቅተኛው የሠራተኞች ውሎ አበል ከ82 አስከ 150 ብር፣ የመካከለኛው አበል ከ92 አስከ 173 ብር እንዲሁም ከፍተኛው ከ99 አስከ 225 ብር ድረስ እንዲሆን በተወሰነው መሠረት እየተተገበረ ይገኛል። ከፍተኛ የተባለው 225 ብር የቀን ውሎ አበል ግን ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው አዳማ ከተማ እንኳን ደህና (ንጹህ) የሚባል መኝታ ለመከራየት የሚበቃ ብር አለመሆኑን መናገር ግን ለቀባሪ ማርዳት ይሆናል።

     አለማየሁ ገበየሁ ደራሲና ብሎገር ሲሆን በ2003 የተደረገውን የደመወዝ ጭማሪ አስመልክቶ በወቅቱ በድረገጹ የሚከተለውን አስፍሮ ነበር። “በአንድ ወቅት 320 ብር የነበረውን ደመወዝ 420፤ 3ሺህ 152 የነበረውን የመምሪያ ኃላፊ ደመወዝ 4ሺህ 343 ያስገባ ጭማሪ ተከናውኗል” ይልና በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ የነገሱ ችግሮችን ይዘረዝራል። “መንግስት ለሁሉም ወገኖች በቂ ምላሽ መስጠት የሚቻለው ሳይንሳዊ አሰራርን በመዘርጋት ነው በሚል የጥናት ቁፈሮ ጀመረ። ማዕድንን ፈልጎ ለማውጣት አታካች አመታትን አሳልፏል። በመጨረሻም ቢፒአር /Business Process Reengineering/ የተባለ የከበረ ድንጋይ መገኘቱ ይፋ ሆነ። ከወጪ፣ ግዜ፣ ጥራትና ደረጃ መመዘኛዎች አንጻር አሰራሩ ቀልጣፋ፣ ፍትሃዊና አንጀት አርስ መሆኑ ተነገረለት። ሰራተኞች የፍልስፍናውን ሀሁ በየተቋማቸው በሶስት ቀን ጥልቅ ጥናት ከአኩዋ አዲስ ጋር አጣጣሙት። እንደ እውነቱ ከሆነ ብዙዎቹ ቀድመው መማር የፈለጉት ስለ ደመወዝ የሚያትተውን ምዕራፍ ነበር። ይህ ምዕራፍ ግን እዚህ ጥራዝ ውስጥ አልነበረም። እንደውም ትንሽ ቆይቶ ሀሴትን ሳይሆን መርዶን ማዘሉንም አበሰረ። ጥቂት የማይባሉትን ከእኔ አሰራር ጋር መጓዝ አትችሉም፣ የትምህርት ዝግጅታችሁ በቂ አይደለም፣ አመለካከት ሲቀነስ የተንጠለጠለ ብቃት እኩል ነው C ማይነስ በሚል ከስራ ዉጪ አድርጓቸዋልና። በአንዳንድ መ/ቤትማ ብቀላና ፖለቲካ ሥራቸውን ሰርተዋል።

ከአውሎ ንፋሱ የተረፉት ጥናቱን ተግባራዊ ለማድረግ ማበረታቻና የደመወዝ ጭማሪ የግድ ያስፈልጋል የሚል ዳግማዊ ጥያቄ ከማንሳት አልተቆጠቡም። መንግስትም የሰራን ለመሸለምና ለማሳደግ የሚቻለው የዚህን ተከታይ ሳይንስ እውን በማድረግ ነው በሚል ሌላ ቁፋሮ ውስጥ ገባ። ከአመታት በኃላም ሚዛናዊ የውጤት ተኮር /Balanced Score Card/ ስርዓትን አስተዋወቀ። በዘጠኝ ደረጃዎች የተዋቀረው ውጤት ተኮር ከስትራቴጂ ግንባታ ጀምሮ እስከ ክትትልና ግምገማ ድረስ የሚዘረዘር ነው። ጥናቱ እንደ አሹ ቤት ስጋ የሚያስጎመዥ ነው። በደረጃ ሰባት ላይ የሚገኘው “አውቶሜሽን” የእያንዳንዱን ፈጻሚ ስራ መመዝገብና መተንተን የሚችል በመሆኑ ሰራተኛውን ከለጋሚው ለመለየት የሚያስችል ነው ተብሏል። በሌላ አነጋገር አጭበርባሪው ፊርማ ፈርሞ ሹልክ ማለት ወይም መድረክ ላይ በሚያቀርበው አስመሳይ ተውኔት ብቻ ተላላ ኃላፊዎችን መሸወድ አይችልም። ፋብሪካና ኢንዱስትሪ ውስጥ ባይሆንም ከቢሮ የሚታደለውን ስራ ቆጥሮ ይረከባል በኃላ ደግሞ ቆጥሮ ያስረክባል – ይህ ማለት ግን የሚሰራው ንብረት ክፍል ውስጥ ነው ወይም ከጥበቃ ስራ ጋር በስተደቡብ ይዋሰናል ማለት አይደለም። በፍጹም። ርግጥ ነው ሳይንሱ አንድ ኃላፊ እንደ ጥበቃም እንደ ንብረት ክፍል ኤክስፐርትም ሁለገብ እንዲሆን ያበረታታል። እንግዲህ በዚህ ምክንያት ነው ሳይንሱ ሥራና ሠራተኛን ያገናኛል የተባለለት።

በመሆኑም ምርጥ ፈጻሚዎች ተገቢውን ሽልማትና የደመወዝ እድገት ለማግኘት እንዲችሉ በመነገሩ ስራው ተጧጧፈ። በአንዳንድ ተቋማት የምርጥ ፈጻሚዎችና ምርጥ አመራሮች ፎቶግራፍ ሳይቀር መለጠፍ ጀመረ። ዓመቱ መጨረሻ ላይ ሽልማትና ዕድገት የሚጠበቅ ቢሆንም መንግስት እፍርታም ሆነ። ለምርጦች እውቅና ከመስጠት ይልቅ በርካታ ምክንያቶችን መደርደርን “ደረጃ አስር” አደረገው። ግምገማው ትክክል አይደለም፣ በተቋሙ መሰረታዊ ለውጥ ካልመጣ ሰራተኞችም የተለየ አፈጻጸም ሊኖራቸው አይችልም … የሚሉትን እንደ ዋና ዋና ማሳያነት ማነሳሳት እንችላለን።

በቅርቡ አገር ጥለው የሄዱት የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር አቶ ጁነዲን ሳዶ በአንድ ወቅት የመንግስት መ/ቤቶች ቢፒአርን እንዴት እንደሚጠቀሙበት በቂ ትኩረትና ዝግጅት ሳያደርጉበት ወደ እንቅስቃሴ በመግባታቸው መፍትሄ ሊያመጣ አልቻለም በማለት መግለጫ ሰጡ። ለነገሩ ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነው እንዲሉ ሆኖ እንጂ ቢፒአርና ቢኤስሲ ስልጠና ሲሰጥ ብዙ ችግሮች መኖራቸውን መስማት ነበረባቸው። አንደኛው ችግር በስልጠናው ወቅት ከሠራተኛው የተነሱ መሰረታዊ ጥያቄዎችን አሰልጣኞች በበቂ ሁኔታ መመለስ አለመቻላቸው ነው። እናም አሰልጣኞች ወዴት እየሄዳችሁ ነው? ሲባሉ “ያልገባኝን ነገር ላልገባቸው ሰዎች ልነግርን ነው” አሉ ተብሎ እስካሁንም ይቀለዳል።

የመንግስት ሠራተኛው ሁለቱን የለውጥ መሳሪያዎች ለማስፈጸም ዛሬም እየተንገታገተ ቢሆንም ቃል በተገባለት የደመወዝ ጭማሪና በሳይንሳዊ አሠራሮቹ መካከል ያለው ተጨባጭ ቁርኝት ሊገለጽለት አልቻለም። ብዙ ተቋማት ውስጥም የለውጡ ሥራ መሬት የወረደ፣ የሚታይና የሚቆጠር ከመሆን ይልቅ አንዳንዶች ‘ኮስሞቲክ’ እያሉ እንደሚጠሩት ሳምንታዊ ቅጽ መሙላት፣ ደረት ላይ ባጅ ማድረግ፣ ጠረጼዛ ላይ ስምና የስራ ድርሻን ማስተዋወቅ እየሆነ መጥቷል። የአዲሱ አሰራር ግብ ይህ አይደለም፤ ሠራተኛው አዲሱ አሰራር /ሳይንስ/ ህይወቴን ለመቀየር የሚያስችል መሰረት የለውም የሚል ድምዳሜና የጥርጣሬ ዳርቻ ላይ አዳርሶታል።”

የሲቪል ሠርቪስ ሪፎርሙ ከቢፒአር እና ከባልንስ ስኮር ካርድ ወይንም ቢ.ኤስ.ሲ ትግበራ በተጨማሪ ለራሱ ለመንግሥት ሠራተኛውም ግራ የሚያጋቡና በየጊዜው የሚለዋወጡ አሠራሮችና የማይገቡ ስያሜዎች ከ2003 ዓ.ም ወዲህ አንጠልጥሏል። “የለውጥ ሠራዊት፣ የህዝብ ክንፍ፣ የመንግሥት ክንፍ፣ ግንባር ቀደም ሠራተኛ፣ የዜጎች ቻርተር…” የሚሉና የመሳሰሉት በተጨባጭ በሲቪል ሰርቪሱ ሥራና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያመጡት ለውጥ የሚለካ ሊሆን እንዳልቻለ ያነጋገርናቸው ሠራተኞች የሚስማሙበት ነው። “ስያሜው ምንም ይሁን ምን ዋናው ነገር ሲቪል ሰርቪሱ የአገልጋይነት መንፈሱን ከፍ እንዲል፣ ሠራተኛውና አመራሩ ተደጋግፎ ጥራት ያለው ሥራ እንዲያከናውን ማድረግ መቻሉ ነው። ከሙስናና ኪራይሰብሳቢነት፣ ከብልሹ አሠራርና ከመልካም አስተዳደር ችግሮች የጸዳ ሲቪል ሰርቪስ ለማቆም ግን አሁንም ያልተቻለበት ሁኔታ መኖሩ እውነት ነው” ሲሉ አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የመንግስት ሠራተኛ ያስረዳሉ።

ከሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ እንደሚያትተው በተለይ የውጤት ተኮር ምዘናው ከቢኤስሲ ጥናትና ዲዛይን ይበልጥ እጅግ ከባድ ጉዳይ ነው። “ጥናቱ የዲዛይን ማንዋሉን በመከተል የሚዘጋጅ ቀላል ስራ ሲሆን ምዘናው ግን ከቴክኒክ እስከ አመለካከት የሚዘልቁ በርካታ ችግሮች ያሉበት ነው። በመጀመሪያ ደረጃ እስከአሁን አፈጻጸምን በኢትዮጽያ ደረጃ ከዕቅድ ተነስቶ ለክቶ የሚያውቅ ግለሰብም ሆነ ድርጅት የለም። በተጨማሪም ሥራው ትክክለኛ ሆነ ሣምንታዊና ወርሃዊ ዕቅድን ማቅረብን ይጠይቃል። ይህም የእቅድ ክህሎትን ማወቅን የግድ ይላል። ሌላው ደግሞ አፈጻጸም ዴታ መሰብሰብ፣ መመዝገብ ያስፈልጋል። ይህንን የሚከታተልና ሠራተኛው የሠራውን ሥራ የሚያረጋግጥ ኃላፊም በቅርብ መኖር ይኖርበታል። ይህ ኡደት አድካሚና ሠራተኛው ከዚህ ጥብቅ አሠራር ለማፈንገጥና ወደተለመደው አሠራር የመመለስ አዝማሚያ በስፋት ይታያል።….. ሌላው የውጤት ተኮር ሥራ አፈጻጸም ምዘና ከማበረታቻ ሥርዓት ጋር ካልተዘረጋ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል ተገንዝበናል» ይላል። በተግባርም የሆነው ይኸው ነው። ሠራተኛውን የጥቅምና የሃሳብ ተካፋይ ባልሆነበት ሁኔታ የትኛውም ወርቅ የሆነ ሥርዓት ቢዘረጋ ውጤታማ እንደማይሆን በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ የተሞከሩ በርካታ የለውጥ ሒደቶችና ሥርዓቶች በቂ ምስክሮች ናቸው። እነዚህ የለውጥ መሣሪያዎች የቱን ያህል ወደተግባር መለወጥ እንዳልተቻለ ለመታዘብም ከመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አንዱ ወደሆነው ወደትራንስፖርት ባለሥልጣን ጎራ ብሎ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ፣እድሳትና ሌሎች ተያያዥ አገልግሎቶችን መታዘብ ይቻላል። በቀጥታ ከሕዝቡ ጋር የእለት ተዕለት እንቅሰቃሴ ከሚያገናናቸው ወረዳዎች፣ ክፍለከተማዎች እና የከተማ አስተዳደሮች (ማዘጋጃ ቤቶች) ጎራ ብሎ መቃኘት ስንትና ስንት ገንዘብና ጊዜን የበሉ የለውጥ ጥናቶች በምን ደረጃ እየተተገበሩ እንደሆነ ፍንትው አድርገው የሚያሳዩ መስታወቶች ናቸው።

መንግሥት ኑሮ ውድነትን ተከትሎ በየጊዜው ቢቻል፤ በሚታወቅ ጊዜና ወቅት ለሠራተኛው የደመወዝ ማስተካከያ ማድረጉ የሚጠበቅና መሆንም ያለበት ተግባር ሲሆን በአንጻሩ ግብር ከፋዩ ሰፊ ህብረተሰብ ከሲቪል ሰርቪሱ ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኝ ከላይ ወደታች በሚወረወር የለውጥ ሰበካ ሳይሆን ራሱ ሠራተኛውን ባመነበትና በሚሳተፍበት የለውጥ ሒደት መሻሻሎችን ለማምጣት መትጋት ካልተቻለ በየጊዜው ለሚደረጉ ትናንሽ ጭማሪዎች እንኳን ሀገሪቱ መሸፈን የሚያስችል አቅም ሊኖራት አይችልም። መንግሥትም ያቀደውን ለመፈፀም የሚችልበት ሁኔታ አይኖርም። የሲቪል ስርቪሱ መዳከም ሕዝብና መንግሥትንም በማራራቅ ረገድ ሚናው ይጎላል። እናም በእንዲህ ዓይነቱ ድርብ ድርብርብ ኪሣራ ፈጥኖ የመውጣት ጉዳይ ለምርጫ የሚቀርብ አይሆንም።