24 May, 2017
By ዮሐንስ አንበርብር
በአፋር ክልላዊ መንግሥት የሚኖሩ የትግራይ ብሔር ተወላጆች ያነሱትን የልዩ ወረዳ ጥያቄ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውድቅ አደረገ፡፡
በአፋር ክልል አብዓላ ወረዳ ሥር የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ያነሱትን ልዩ ወረዳ የመሆን ጥያቄ ለክልሉ ምክር ቤት አቅርበው ተባይነት በማጣታቸው፣ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቤቱታ አቅርበው ነበር፡፡ በዚሁ አቤቱታ መሠረት የምክር ቤቱ የሕግ መንግሥት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ማጣራቶችን አከናውኖ፣ ሰኞ ግንቦት 14 ቀን 2009 ዓ.ም. ጉባዔውን ላካሄደው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የውሳኔ ሐሳቡን አቅርቧል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው በአብዓላ ወረዳ የሚኖሩ የትግራይ ብሔር ተወላጆች ላነሱት መሠረታዊ ጥያቄ መነሻ በክልሉ ራሳቸውን የማስተዳደር መብታቸው መሸራረፉ መሆኑን አመልክቷል፡፡ ራስን የማስተዳደር ጥያቄያቸው በክልሉ መንግሥት ተመልሶ በወረዳነት ራሳቸውን በማስተዳደር ላይ መሆናቸውን የጠቀሰው ቋሚ ኮሚቴው፣ አሁን ለተነሳው ጥያቄ የጀርባ ምክንያቱ በሌሎችም አካባቢዎች የተስተዋለው የመልካም አስተዳደር ችግር መሆኑን በማስረዳት፣ ያቀረቡት የልዩ ወረዳነት ጥያቄ ውድቅ እንዲሆን የውሳኔ ሐሳቡን አቅርቧል፡፡
ምክር ቤቱም በቋሚ ኮሚቴው የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ተቀብሎ የልዩ ወረዳነት ጥያቄውን ውድቅ አድርጓል፡፡
ምን ጭ      –