ክፍል አንድ

 

ዮርዳኖስ ቶላ ከቶሮንቶ ካናዳ

yordanosbtola@gmail.com

የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ስለ ኦሮሞ ህዝብ ታሪካዊ አመጣጥ፣ አሁን ያሉ ተጨባጭ ሁኔታዎችን ለማሳየትና አሉ የሚባሉት ችግሮችም በቀጣይ በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ የሚፈቱበትን ግላዊ አስተያየት ለመስጠት እንጂ ከማንኛውም ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ጋር በተያያዘ ወገናዊነትን ለማሳየት አሊያም አንደኛውን ወገን ሂስ ለመስጠት የተዘጋጀ ጽሁፍ አይደለም። የዚህ ጽሁፍ አቅራቢም የማንኛውም ፖለቲካ ድርጅት አባልም ደጋፊም አይደለችም

የኦሮሞ ህዝብ ታሪክ እንደየፀሃፊው የፖለቲካ አመለካከትና ከዘገባው በስተጀርባ ካለው ጥቅምና ጉዳት እየተመዘነ በመልካምነቱም ሆነ መልካም ባልሆነው መልኩ ተፅፎ ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገረ በመምጣቱ እንኳንስ ኦሮሞ ባልሆኑት ላይ ኦሮሞ ነን ብለን  ራሳችን በምንጠራው ሰዎች ላይ ሳይቀር ለዘመናት የሚዘልቅ ብዥታ ፈጥሯል። ታሪክ ብዙውን ጊዜ ስልጣንና ሃይል ባላቸው ሰዎች ስለሚጻፍ ወገናዊነት እንደማያጣ የታወቀ ነው። በአንድ ወቅት የተጻፈው ታሪክ ባብዛኛው የገዢውን መደብ ፍላጎትና አስተሳሰብ የሚያስተናግድ ሆኖ ይጻፋል። በንጉሳዊ አገዛዝ ዘመን የተጻፉት ታሪኮች የንጉሱን ስልጣንና ቤተሰባዊ ውርስ በሚያስተናግድ መልኩ የተቀረጹና ንጉሱና ቤተሰቡ ከሌላ ዜጋ የተለየ ማህበራዊና መንፈሳዊ ዋጋ ያላቸው የሚያስመስሉ ጽሁፎች ነበሩ። በኋላ ኮሚኒዝም እከተላለሁ ብሎ የብሄር ብሄረሰቦችን መብት አስከብራለሁ በማለት ስልጣን ላይ የቆየው ወታደራዊ መንግስትም እንደዚሁ ታሪኮች ኮሚኒዝምንና አስፈጻሚዎቹን እንዲያወድስ አድርጎ አስጽፏል

በዘመነ መሳፍንት ጊዜ የግዛት መስፋፋትና አንዱ ባንዱ ላይ መነሳት፣ ያንደኛውን የግዛት ክልል ወደራስህ በማስገባት ግዛትህን የማስፋፋት ተግባርና ባጠቃላይ ችግሮች በሰለጠነ መንገድ ሳይሆን በጦርነት ብቻ የሚፈታ አሰራር እንደ ፋሽን ነግሶ ነበር። በዚያ ዘመን አመጣሽ ታሪካዊ ጣጣ ሳቢያም በርካታ ብሄሮችና ብሄረሰቦች በደረሰባቸው በደልና ግፍ ለክፍለ ዘመን የዘለቀ ጠባሳ ትቶባቸው አልፏል። የዚያ ታሪካዊ ጠባሳ አደገኛ የጎን ጉዳትም እስካለንበት ዘመን ድረስ ዘልቆ አልፎ አልፎ እራሳቸው በዳይና ተበዳይ አድርገው ባሰለፉ ብሄሮች መካከል የቂም ቁርሾ ሲያስነሳ ተስተውሏል። በተለይ በሃገራችን ባለፈው ክፍለ ዘመን የተፈጸመውን በደል ማለትም በአያቶች የተሰራውን ስህተት የተበዳይ ወገንም የልጅ ልጁን አጥፊ አድርጎ የማየት በዳይ ተብሎ የታወቀው ወገንም ላለፈ ስህተት ይቅርታ ጠይቆ እንደማስተኛት እራሱ ሃላፊና ተጠያቂ የሚያስመስሉት ስህተቶችን ሲፈጽም ማየት የተለመደ ነው

እንዲህ ሲባል ግን ይህ የብሄር ብሄረሰብ፣ የዘር፣ የጂኦ-ፖለቲካዊ ማንነት ላይ ተመስርቶ የሚከሰት ያለመግባባት ጣጣ በሃገራችን ብቻ የተከሰተና በሰው ልጅ ታሪክ ያልነበረ ችግር መስሎ የሚታየው ሰው ብዙ ነው። እውነታው ግን የተለየ ነው። በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ካለማወቅና ከክፋት የተነሳ በድሃና በሃብታም፣ በሚያምንና በማያምን፣ በጥቁርና በነጭ፣  በሃይማኖቶች መካከል፡ በዘር በቋንቋና፣ በባላባትና በዝቅተኛው የማህበረሰብ ክፍል ወዘተ ለመቁጠር የሚታክቱ ግጭቶች ተከስተዋል። እነዚህ በያንዳንዱ ማህበረሰብ የተፈጠሩ ጥላቻዎችና አነስተኛ ግጭቶች መንስኤ ተብለው የሚወሰዱ ምክንያቶች በአደገኛ ሰዎች እጅ ሲገቡ ደግሞ ወደ ከባድ ግጭትና የዘር ማጥፋት ወንጀል ያድጋሉ

በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ የአይሁድ ሃይማኖት ተከታዮች ላይ በአዶልፍ ሂትለር አስተባባሪነት የተፈፀመ ጭፍጨፋ፡ በክፍለ ዘመኑ ማብቂያ በኢንተር ሃምዌ ሚሊሺያዎች አማካኝነት በሁቱና በቱትሲ ብሄረሰቦች መካከል ሩዋንዳ ላይ የደረሰው እልቂት እንዲሁም ሌሎች ብዙ ዘግናኝ ምሳሌዎችን ማቅረብ በቂ ማስረጃ ነው።

ሃሳቦች በመጀመሪያ ደረጃቸው ላይ ከእውነትና ከማስረጃ ጋር ሳይጣጣሙና የግለሰቦች ስሜት ላይ ተመስርተው ሲወጡ ቀላል ቢመስሉም በፕሮፖጋንዳ ደረጃ ከተሰራጩ በኋላ እውነትነታቸውን ወደኋላ ሄዶ የሚመረምር ብዙ ሰው አይደለም። ያ አፍራሽ ፕሮፖጋንዳ ስር ሰዶ በቆየበት ሰዓት ተነስቶ ብዙ ስራ ቢሰራም ሃሳቦች በፊት ወደነበሩበት ደረጃ ለማስመለስ የሚኖረው አቅም ከፍተኛ ላይሆን ይችላል። በርካታ ሰዎች እውነትን ለማስተማር በሚነሱበት ሰዓት እውነትን ቀብረው የያዟት ባህሪያቶች (factors) የበላይነት የያዙ  (dominant) ሆነው ሲያገኟቸውና ሰላማዊ አማራጮም ዝግ ሲሆኑባቸው ወደ አመጽ ተግባር (revolution) ይገባሉ። በዚህም ጊዜ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ መፈታትን ትተው በግጭት ይፈታሉ። ይሁን እንጂ አሁን ባለንበት የሰለጠነ የሰው ልጅ የአስተሳሰብ ደረጃ ሬቮሉሽን በጣም የሚናፍቅና የሚያጓጓ የመፍትሄ መንገድ አይደለም። “ቦ ጊዜ ለኩሉ” እንደሚባለው ሁሉ ለእንደዚያ ዓይነቱ
አስተሳሰብ መንገስ ራሱ የቻለ ጊዜ ነበረው፡ እሱም አልፏል። አሁን ችግሮች በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ እንጂ በአመጽና አጸፋ በመመላለስ ሊፈቱ አይችሉም።

ወደ ዋናው ርዕስ ስንመለስም የአውሮፓ ተስፋፊዎች ወደ ሰሜን አሜሪካ በዘመቱበት ወቅት በሰሜን አሜርካ ይኖሩ የነበሩ አቦሪጅናሎች ላይ የፈጸሙትን ስህተት ማስታወስ ያስፈልጋል። እነዚህ የአውሮፓ ተስፋፊዎች ዋናው ዓላማቸው የግዛት አድማሳቸውን በማስፋት እራሳቸውንና ዘራቸውን የተደላደለ ህይወት እንዲኖራቸው ማድረግ ነበር። ለቤተሰብና ለራስ የተደላደለ ህይወት እንዲኖር መስራት የሌሎችን መብትና ክብር ሳይነካ ከሆነ እንደ ጀግንነት የሚታይና የሚያስከብር ሲሆን የራስን ማንነት በሌሎች ውድቀትና መከራ ላይ ሲመሰረት ግን መጥፎ ይሆናል። በዘመነ European expedition ወደ ሰሜን አሜሪካና አውስትራሊያ የገቡ አውሮፓውያን በቦታው ሲኖሩ የነበሩ ነባር ህዝቦች (indeginous people) በገዛ ሃገራችው ሌሎች መጤዎች እንዲገቡና እንዲኖሩ በመፍቀዳቸው ምስጋና እንደማቅረብ እራሳቸውን እንዳይመስሉ ብቻ ሳይሆን ቅኝ ገዢዎቻቸውን  እንዲመስሉ የተገደዱበት ታሪክ ተፈጽሞባቸዋል። በኦሮሞ ህዝብ ላይም በዳግማዊ አጼ ምኒልክ የሚመራው ተስፋፊ የአቢሲንያ ጦር ተመሳሳይ በደል አድርሶና ለዘመናት የቀጠለ የህዝቡ ማንነትና ክብር የሚያዋርድ ተግባር ተፈፅሟል። ዳግማዊ አፄ ምኒልክ እንደማንኛውም የዘመኑ መስፍን በግዛት የማስፋፋት ተግባር ላይ በተጠመዱበት ወቅት በኦሮሞ ህዝብና በሌሎች ህዝቦች ላይ ሰራዊታቸውን በማዝመት በሂደቱ የብዙ ኦሮሞ ቤተሰብ በትነዋል፡ የስነልቦናና የማንነት ቀውስ እንዲፈጠር አድርገዋል። ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በወቅቱ በነበራቸው ስብዕና እሳቸው ግዛቴ በሚሉት ምድር ላይ ሊኖር የሚገባው “ልከኛ” ቋንቋ አማርኛ “ብቸኛ” ሃይማኖት ደግሞ ኦርቶዶክስ ብለው ከማሰብ በላይ የማይሄድ ነበር። ይህ አስተሳሰብ የጠቅላላ ዕውቀታቸና የብስለት ደረጃቸው አመልካች እንጂ ከሌሎች በርካታ አማራጮች ይህኛው ይሻላል ብለው ያራመዱት እንዳልሆነ ለመገንዘብ ቀላል ነው።

ይህ የኔ ትክክል ነው አባዜ የሌሎችን ውድቅ (dismiss) በማድረግ ለማረጋገጥ መሞከር በዚያ ዘመን ዕውነት ይመስል ስለነበር እንድሁሉም የዓለም ወራሪዎችና ተስፋፊዎች ዳግማዊ አጼ ምኒልክም ተግባር ላይ ለማዋል ሞክረው ነበር። አጼ ምኒልክ መልካም ተግባራቸው ሁሉ እንደተጠበቀ ሆኖ የግዛት ክልላቸውን ለማስፋፋት በነበራቸው ጉጉት ሳቢያ በኦሮሞ ህዝብ ዘንዳ የማይጠገን ሰባራ ፈጥረው አልፈዋል። ይህ የመበደል ስሜት ሲንጸባረቅ እንደ ሃላፊ ጊዜ እንጂ እንደ ወቅታዊ ቁርሾ (active dispute) ማየት ተኣማኒነትም (plausibility) ተቀባይነትም (acceptability) የለውም። በዚህ ባህሪው ምክንያትም በተወላገደ (distorted) መንገድ ለወቅቱ ፖለቲካዊ ድራማ ሊጠቀምበት የሚነሳ መኖሩ የግድ ቢሆንም ተቀባይነትና ተኣማኒነት በቦታቸው ሳይኖሩ የሚሞከር የማነሳሳት ተግባር ተፈጻሚነት (practicability) ሊኖረው አይችልም። ቢሆንም ታዲያ በነበረው ያልጠገነ ስብራት ላይ በተመሳሳይ መንገድ ሌላ ግርሻ ለማምጣት ግን አመቺ ሁኔታዎችን ሊፈጥር ይችላል።

በዳግማዊ አጼ ምኒልክ የተጻፈው አዲስ የአስተዳደር ድርሳን እንደ ተገቢ ባህል ስለተወራረደ በዚህ ውርሻ (legacy) ከኚህ ንጉስ በኋላ የመጡት ገዢዎችም አፄ ምኒልክ የጀመሩትን የወረራና የዘር ማጥፋት ተግባር መጥፎና ታሪካዊ ስህተት እንደነበር ከማስተባበልና ነገሮች ለማለዘብ ከመሞከር ይልቅ ባጠቃላይ የኦሮሞ ህዝብ የማንነቱ መገለጫ የሆኑት ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶች ንጉሱ ራሳቸውን በሚገለፁበት ባህልና ቋንቋ እንዲተኩ እምነቱን የሚገልጽባቸው መንገዶች የንጉሳውያኑን እንዲመስሉ ብዙ ስራ ተሰርቷል። ቀለም የቆጠረና የመንግስት ስራ ለመቀጠር የሚሻ ኦሮሞ ስሙ ሳይቀር ወደ አማርኛ እንዲቀይር ጫና በመፍጠር የኦሮሞ ህዝብ በማንነቱ እንዳይኮራ ብሎም እንዲሸማቀቅ ብዙ በደል አድርሰውበታል። የኦሮሞ ህዝብ የባህሉና የማንነቱ መገለጫ የሆኑት ስሞቹ ሳይቀር በአማርኛ እንዲቀየሩ አድርገዋል። ስምህ ታይፕ ይሰብራል በሚል በጣም አሳዛኝ አገላለፅ ክብሩ ዝቅ እንዲልና በኦሮሞነቱ እንዲሸማቀቅ እራሱን ኦሮሞ ከማለት ይልቅ ሌላ ብሄረሰብ ነኝ ብሎ እንዲያቀርብ ወደ ተገደደበት ከባድ መከራ አስገብተውት ነበር።

በኋላ ኮሚኒስት ስርዓት ላይ የተመሰተ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ እመሰርታለሁ ብሎ የተነሳውን  ማርክሲዝም ሌኒኒዝምን ያራምድ የነበረው መንግስትም የብሄር ብሄረሰቦች እኩልነት መከበር አለበት ብሎ በብሄረሰቦች ላይ ይፈጸም የነበረው ስም ማስቀየርና አስነዋሪ አጠራርም ሆነ ስድብ ቢያግድም በተግባር የኦሮም ህዝብ ባህላዊ እሴቶቹ እንዲመለሱና መብቱን እንዲለማመድ መንገድ አልፈጠረም ነበር። ወታደራዊ አገዛዙም በኦሮሞ ህዝብ ላይ የተበዳይነት ስሜት ከመፍጠር ባሻገር ለህዝቡ መብት እንታገላለን የሚሉትን ሁሉ ለማጥፋት ከፍተኛ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ዘመቻ አካሂዷል። ኦሮሞዎች በተርጣሪነት በየእስር ቤቱ ማቅቀዋል፡ ተገድለዋልም።

እንዲያውም ወታደራዊ መንግስቱ የብሄር ብሄረሰብ ጥያቄ አንግቦ የተነሳውን ሁሉ ተገንጣይ፣ ጠባብ ብሄርተኛ ወዘተ በሚሉ ስያሜዎች ስር መድቦ ትግላቸውን ባለበት ለማቀጨጭ ሰፊ በጀት መድቦ ተንቀሳቅሷል። ህዝቡን ከአኗኗሩና ከማንነቱ ጋር ባያሌ በሚጣረስ የሰከረ (unrealistic) ብሄራዊ ስሜት (patriotism) ሃገሪቱን በግድ አንድና የሰመረች አስመስሎ ለማቅረብ ብዙ ድራማ ተጫውቷል። ይሁን እንጂ ያ ዘዴም ሊያስኬድ ስላልቻለ ያ ስርዓትም በወቅቱ ተገረሰሰ።

የኦሮሞ ህዝብ አንድ ተግባራዊ እርምጃ (practical step) የተራመደው ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ነው ቢባል ወያኔን ከመደገፍ አልያም ከመጥላት ጋር ምንም ትስስር ሊኖረው አይችልም። ባሁኑ ጊዜ ኦሮምኛ የኦሮሚያ ክልል የመንግስትም የስራ ቋንቋ ነው። ኦሮሞ መሆን አያሳፍርም። ሌሎች ከህዝቡ ጥቅም ጋር የተያያዙ ያሁኑ መንግስት በግድ መመለስ ያለበት በርካታ ጥያቄዎች ቢኖሩም እንኳ ይህ መንግስት ባመጣው ለውጥ የኦሮሞ ህዝብ በቋንቋው መማሩ፣ መዳኘቱ፣ መናገሩና አለመሸማቀቁ በራሱ በቂ ዕውቅና (credit) የሚያሰጥ ታሪካዊ ድል ነው።

ይህ የኦሮሞ ነጻነት በቋንቋና በባህል ላይ የተመሰረት ነው ወይ? በቃ ኦሮሞ በቋንቋው ስለተናገረና ስለተዳኘ ብቻ የክፍለ ዘመን ጥያቄዎቹ መልስ አግኝተዋል ወይ? አይደለም። የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ምንድነው ብሎ ማጤን በራሱ የመልስ መስጠቱ አቡጊዳ (ABCD) ነው።

እነዚህ ጥያቄዎች ህጋዊ (legitimate) ናቸው ወይ ብለን ከመጠየቃችን በፊት ግን የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄዎች ማን ያነሳቸው ናቸው። መሰረታዊ የህዝቡ ጥያቄዎችን ለትክክለኛ ዓላምማ የሚያነሱት እንዳሉ ሆነው ጥያቄውን በመጥለፍ በራሳቸው ስሜትና መነጽር ስር እንዲያልፍ የሚፈልጉት የሚሉትስ ምንድነው? ብለን መነሳት አስፈላጊ ነው። የኦሮሞ ህዝብ በደልን በመቁጠርና ስላለፈው ብቻ በመቆዘም አሁን ያለው አዲስ ትውልድ የዚህ እንካ ስላንትያህ ሰለባ እንዲሆን አይፈልግም። ይህ ነው በሰሜን አሜሪካ ያሉት ተበዳይ ጥቁሮች ላይ ያለው የአንድ ትውልድ ውድቀት። ጥቁሮች በባርነት ከአፍሪካ መጥተው በከባድ ታሪካዊ ምዕራፍ ውስጥ ተጉዘው መብታቸው ወደሚያስከብሩበት ደረጃ ላይ ቢደርሱም በተፈጠረው ቀዳዳ ልጆቻቸውን በማስተማርና በመአዱ ዙሪያ ተቀምጠው ተቋዳሽ እንዲሆኑ ከማድረግ ይልቅ አብዛኛዎቹ ያለፈውን በደል በመቁጠርና በመበሳጨት ብቻ ጊዜያቸውን ስለሚያሳልፉት ልጆቻቸውን የኢኮኖሚ ባርነት ላይ የሚጥል አዲስ ራስ ፈጠር (self-imposed) ባርነት ውስጥ እየኖሩ ይገኛሉ።

የኦሮሞ ህዝብ ከዚህ ዓይነት አደገኛ አመለካከት የመታደግ ስራ ምሁራን ከሚባሉት ተወላጆች የሚጠበቅ ተግባር ነው። ያለፈው መከራና ስቃይ እንዳይመለስ ሆኖ ወደ ጥልቁ ቢጣልም ህዝባችን ባለፈው ዘመን እየተቆጣ እንዲኖርና ባሁኑ ጊዜ በሃገሪቱ ያለውን ጸጋ እኩል የሚካፈልበት ሁኔታ እንዳይፈጠር የሚያደርጉ ለጊዜያዊ ጥቅማቸው ብቻ የሚያስቡና የሚታገሉ ሰዎች መኖራቸው ያሳዝናል። እነዛ ሰዎች የኦሮሞን ህዝብ በተለይ ወጣቱን በስሜት በማነሳሳት ክልሉ የልማትና የሰላም ሆኖ ምድሪቱ የምትሰጠውን ጸጋ በጋራ እንዳይጠቀም የተሳሳተ የትግል መንገድ እያሳዩት ናቸው።

የኦሮሞ ህዝብ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን መቃወሙና ማስተር ፕላኑ የኦሮሞ ገበሬን በማይጎዳ ብቻ ሳይሆን ተጠቃሚና ለጥቅሙም ቅድሚያ የማግኘት መብት እንዳለው ለመንግስት ማሳየት መልካምና ሊደገፍ የሚገባ ሃሳብ ነው። ከዚሁ ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን በላይ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ እንደ ሁሉም የሃገራችን ክልሎች ሙስና፣ ፍትሃዊ ያልሆነ የሃብት ክፍፍል፣ የፍትህና የዲሞክራሲ እጦት እንዳለ ጸሃይ የሞቀው ሃቅ ነው። ይህንን ጥያቄ በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ይዞ እምቢኝ ማለትም ተገቢ ነው። ሌሎች በህዝቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ በሚታዩ አሉታዊ ለውጦች (negative changes) ላይም እንደዚሁ በቁጣ መናገርና ባለስልጣናት እንዲሰሙት ብለውም እንዲያርሙት ማድረግም የግድ ነው።

ይህ ፍጹም ህጋዊ የሆነ የህዝቡ የመብት ጥያቄ ማንም የሚሰጠውና የሚከለክለው አይደለም። ይሁን እንጂ በግልጽ የተቀመጠውን የመብትና የዕኩልነት ጥያቄ ወዳላስፈላጊ መንገድ በመጥለፍ በየውጭ ሃገሩ መዋጮ ለመሰብሰብና የግል ሃብት ለማካበት ሲሉ አንደበተኝነት (sophism) ላይ በተመሰረት አቀራረብ ወጣቱን ህግ እንዲተላለፍና ሰላማዊ ጥያቄው አንዴ በዘር ጥላቻ ላይ አንዴ ደግሞ ባልታወቀ ነገር ላይ የተመሰረተ ግጭት እንዲሆን በየማህበራዊ ሚዲያው ሲቀሰቅሱና ቀላል ያልሆነ ጉዳት ሲያመጡ አይተናል። ግጭት በተፈጠረ ቁጥር ለእስር፣ ለስደት፣ ለሞት የሚጋለጠው በየማህበራዊ ሚዲያ ቁጭ ብሎ የሚያላዝነው ብልጥ ሳይሆን የነሱን ፕሮፖጋንዳ በማመን በደመ ነፍስ
የሚጋጨው የኦሮሞ ህዝብ ልጅ የሆነ ወጣት ነው። እነዚህ ግጭቶች መንግስት ራሱን ከማየት ይልቅ ለበለጠ አፈናና ጭካኔ የሚያዘጋጅ የራሱ ፖለቲካዊ ትንተና እንዲፈጥር ምክንያት ይሆኑታል።

ለዚህም ሲባል መጀመሪያ የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ነጥሮ መውጣት አለበት። ጂኦ-ፖለቲካዊ ዕውነታዎችን ሳያገናዝቡ ምናልባት ኦሮሚያ ኤርትራውያን እንደተሳካላቸው እንደመንግስት ራሷን የቻለች ሃገር ብትሆን ስልጣንና ጥቅም እናገኛለን በማለት የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ጥቂት ሰዎች እንዳሉ ሆነው ባብዛኛው የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ እንደጸሃፊዋ ግንዛቤ የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር በሰላምና በመፈቃቀድ አብሮ እንዲኖርና በሃገሪቱ ያለው ሃብትም በጋራ እኩል ተጠቃሚ የሚሆንበት ስርዓት ማየት ነው። የመብትና የህልውና ጥያቄው ቋንቋውና ባህሉን በነጻነት በመጠቀም የጀመረው ቢሆንም በርካታ ያልተመለሱ ጥያቄዎች ግን አሉት።

ዋናው መነሻ የኦሮሞ ህዝብ በእውነተኛ ዲሞክራሲና ፍትህ ላይ በተመሰረተች ኢትዮጵያ ውስጥ እኩል መብትና ክብር ኖሮት እንዲኖር ከሆነ ጥያቄዎቹ አሁንም በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ ደግሞ ደጋግሞ አቤት በማለትና አመጽ በሌላቸው ዝምታና መንግስትን ባለመታዘዝ ሊመለሱ ይችላሉ። አንድ የፖለቲካ ፓርቲ እንዳለውም  ኦሮምኛ ከአማርኛ ጋር የፌደራል መንግስት የስራ ቋንቋ እንዲሆን መጠየቁ ፍጹም ህጋዊ ነው። የኦሮሞ ህዝብ ካለው ብዛትና ባህላዊ እሴቶች አንጻር ቋንቋው እንደተጨማሪ የፌደራል መንግስት ቋንቋ እንዲሆን መደረጉ ከጉዳቱ ጥቅሙ እጅግ በጣም የበለጠ ነው። ይህ ስሌት ከኦሮሞ ህዝብ መብት አንጻር ብቻ የሚሰላ ሳይሆን የሁሉም ህዝቦች ዘላቂ ሰላምና ማህበራዊ ትስስር ማደግ ጋር ሊታይ የሚገባው ቅዱስ ሃሳብም ነው።

በካናዳ በእንግሊዘኛ ተናጋሪዎችና በፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች ተመሳሳይ ጥያቄ ተነስቶ ህጋዊና ትክክለኛ መልስ ተሰጥቶታል። አሁን ካናዳ 10 ክፍለ ሃገራትና 3 ልዩ የአስተዳደር ክልሎች ሲኖሩዋት በአንዷ ክፍለሃገር ጥያቄ ምክንያት ፈረንሳይኛ ከእንግሊዘኛ ቋንቋ ጋር የሃገሪቱ የስራ ቋንቋዎች ሆነው እንዲሰሩ በመደረጋቸው ያገሪቱን ሰላም አበዛ እንጂ የጎዳት ነገር የለም። ይህ አርቆ ማሰብና ለመጪው ትውልድም የሚጠቅም ተግባር መፈጸም ነው። ኦሮምኛ የፌደራል መንግስት የስራ ቋንቋ ሆኖ ከአማርኛ ጋር ቢነገር፣ ቢጻፍበት፣ ቢሰራበት ወዘተ ከኦሮሞው ይልቅ የሌላ ብሄር ተጨማሪ ቋንቋ በማወቅ ተጠቃሚ የሚሆንበት አስደሳች መንፈስ ይፈጥራል እንጂ በጥላቻ ታውረን በጥላቻ ላደግን የዚህ አሳዛኝ ትውልድ አባላት ለሆንነው ሰዎች የሚሰማን ዓይነት ስጋት አይፈጥርም። በመጀምሪያም እኮ ቋንቋ ከለያየን ቋንቋውን በመማርና ከቋንቋው በስተጀርባ ያሉትን እሴቶች በሙሉ በማወቅ ስለህዝቡ ያለን ስሜት ማሳመር እንችላለን።

ሰላም እንሰንብት ቀሪው በክፍል ሁለት ይቀርባል ዮርዳኖስ ቶላ ከቶሮንቶ ካናዳ     yordanosbtola@gmail.com