ከሸንጎ የተሰጠ መግለጫ

May 29, 2017

ግንቦት 202009 (ሜይ 282017)

የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሽንጎ (ሽንጎ) የስራ አስኪሃጅ ኮሚቴ የሀገራችንን ሁኔታ በየጊዜው እየገመገመ የፖለቲካ አቅጣጫ ማሳየት አንዱ ተግባሩ ነው። የስራ አስኪሃጅ ኮሚቴዉ በቅርቡ ትኩረት የሰጠው አበይት ጉዳይ ዛሬ በሃገሪቱ ሰፍኖ ያለዉ፤ በህወሓትና አጋሮቹ ተቀነባብሮ ሕገመንግሥት የሆነው ብሔርተኮር ፌደራሊዝም (Ethnic Federalism) ያስከተለዉን ሃገር አቀፍ ምስቅልቅል በሰከነ አስተያየት መርምሮ ሊያስከትለው የሚችለውን አደጋ በግልጽና በማያሻማ ደረጃ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማቅረብና መፍትሄዎችን መጠቆም ነው።

በህወሓቶች የበላይነት የሚመራው የኢትዮጵያ ብሄር ተኮር አገዛዝ በተከታታይ የተከተለው ፖሊሲና ስራዎች፤ የስርዓቱን እድሜ ለማራዘም በሚያስችል ደረጃ ብቻ፤ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር የማጋጨት ተንኮሎች መፍጠርና ስኬታማ ማድረግ፤ ብዙ ሚሊየን ሕዝብ ከቀየው እንዲወገድ አስገድዶ ኢትዮጵያዊያንን ከጋምቤላ እስከ አፋር፤ ከኦሞ ሸለቆ እስከ መተማ፤ ከኦጋዴን እስከ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፤ ከአዲስ አበባ እስከ ጎንደር ከተማና በመላው ትግራይ በያሉበት ማፈንና ማሰቃየት፤ በእድገት ስም የገጠርንና የከተማ መሬቶችን ነጥቆ ለጥቂት የህወሓት/ኢህአዴግ አባላት፤ ደጋፊዎችና ኢንቬስተሮች ማዘዋወር፤ ነዋሪዎች አቤቱታ ሲያቀርቡ በተገላቢጦሽ እነሱን ሕገ መንግሥቱን አላከበራችሁም፤ “ሽብርተኞች ናችሁ” በሚሉ ሰበቦች ወንጅሎ ማሰርና ማሰቃየት የተለመዱ ስልቶች ሆነዋል።

ህወሓት እና በበለይነት የሚመራው ኢህአዴግ ከሃገርና ከሕዝብ ፍቅር ይልቅ ለቁሳቁስ ያላቸው ፍቅር ጎልቶ ይታያል። ከጅምሩ ለኢትዮጵያ ረዢም ታሪክና ዘላቂነት ካለው ፍቅር ይልቅ ለራሱ ቡድን፤ አባላትና ደጋፊዎች ያለው አድልዎ ያመዝናል። የኢህአዴግ ዋናው ሀይልና መሪ የሆነው ህወሓት “እወክለዋለሁ” የሚለውን የትግራይን ሕዝብ አስተዋጾ፤ ከሌላው ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ያለውን ጠንካራና ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፈ ግንኙነትና ኢትዮጵያዊነት እንዲቦረቦሩ አድርጎ የኢትዮጵያን ረዢም ታሪክ፤ ደህንነትና የሕዝቧን አንድነት የሚያፈራርሱና የሚበክሉ ሁኔታዎችን በማመቻቸትና በማጠናከር አሁን በአገራችን ላይ ያንዣበበውን የውጭና የውስጥ አደጋዎች ፈጥሯል።
ይህ ራሱን “የትግራይ ነጻ አውጭ ግንባር” ብሎ የሰየመው ቡድን ከአጋሮቹ ጋር ተባብሮ አዲስ አባባ ላይ ስልጣን ከያዘ በኋላም በተከተለው ፖሊሲ የኢትዮጵያ ዘላቂነት ወደ አስከፊ አጠራጣሪና ሊተነበይ ወደ ማይችልበት ደረጃ እንዲሸጋገር የመገንጠል መብትን ሕገመንግሥታዊ አድርጓል።

በሸንጎ እምነት የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት በመሬትና በሌላ የተፈጥሮ ኃብት ባለቤትነትና ነጠቃዎች ዙሪያ የተከሰተው የእርስ በርስ ግጭቶችና የሃገራችን አለመረጋጋት ነው። ይህ ስርዓት ወለድ ሁኔታ እንዳለ ከቀጠለ የእርስ በርስ እልቂትና የአገር የመፈራረስ አደጋዎች ከማይቆሙበት ደረጃ ላይ ይደርሳሉ የሚል ስጋት አለን።

ሸንጎ በአሁኑ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የተለየ ትኩረት ሰጥቶ ሰፊ ጥናትና ምርምር ያካሄደው በአጠቃላይ ስርአቱ ሕገ መንግሥታዊ እውቅና ሰጥቶ ተግባራዊ ባደረገው ብሄርን መሰረት ያደረገ የክልሎች አሽናሽንና በተለይም ደግሞ በቅርቡ ጎልቶ በሚታየው፤ በመሬት ላይ የሕዝብን እምቢተኛነት በፈጠረው በወልቃይት ጠገዴ የማንነት፤ የሰብአዊ መብቶች አፈና፤ በነዋሪዎች ላይ በተከታታይና በተቀነባበረ መልክ በህወሓት መሪነትና ቀስቃሽነት በገዢው ፓርቲ በተካሄደው ግፍ፤ እልቂትና የመሬት ነጠቃ ዙሪያ ነው።

ሸንጎ ጥናትና ምርምር እንዲያካሂድግ የተገደደበት መሰረታዊ ምክንያት ሁኔታው ለነዋሪውና ለአካባቢው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፤ ለኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነት፤ ነጻነት፤ ሉዐላዊነት፤ ሰላም፤ እርጋታ፤ ዘላቂና ፍትሃዊ እድገት አስጊ በመሆኑ ነው። በዚህም መሠረት ባደረገው ጥናታዊ ትንተናና ግምገማ መሰረት ድርጅቱ ጥናቱን ተወያይቶበትና መሰረታዊ ሃሳቦቹን እንደ ተጨማሪ ግብአቶች ተቀብሎ ስርአቱ ተግባራዊ ባደረገው ብሄር ተከር የክልሎች አሽናሽንና በወልቃይትጠገዴ ጉዳይ ላይ ከታች የተዘረዘቱን የአቋም መግለጫዎች ለኢትዮጱያ ሕዝብ አቅርቧል።

ሸንጎ እንደመንደርደሪያ አድርጎ የተጠቀመውና የተቀበለው፤ ከደርግ መወገድ በኋላ ስልጣን የያዘው ድርጅት ኢህአደግ መሪና መሰረት ህወሓት መሆኑን ነው። ይህ ድርጅት በትግል ላይ በነበረበት ወቅት ይከተለው የነበረው በብሄር (በብሔረሰብ) ጥያቄ ዙሪያ የመደራጀት ርእዮተአለማዊና ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ሲሆን፤ ሀገራዊ ሰልጣን ከያዘ በኋላም፤ በዚሁ አገርን አፍራሽ በሆነ አስተሳስብ ቀጥሏል።

ህወሓት/ኢህአዴግ ኢትዮጵያውያንን አርስ በርስ የሚያጋጭና የሀገርን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል የመሬት ነጠቃና ስፊ ክፋፋየ ፖሊሲ እቅድ አውጥቶ ስኬታማ ለማድረግ ችሏል። በነጠቃቸውና እንደፈለገ በሽነሸናቸው መሬቶች የሚኖረውን ሕዝብ አፍኗል፤ አስሯል፤ በአንዳንድ ቦታዎች፤ ለምሳሌ በወልቃይትጠገዴ ዜጎችን ጨፍጭፏል፤ እንዲሰወሩና እንዲሰደዱ አድርጓል።

ከጉራ ፈርዳ፤ ከጋምቤላ፤ ከቤኒ ሻንጉል ጉምዝና ከሌሎች ቦታወችም አጅግ ብዙ ህዝብ አፈናቅሏል። ህወሓት ስልጣን ከመያዙና ከያዘም በሗላም አጠናክሮ የቀጠለው የብሄር ተኮር አይዲኦሎጅ ስር እንዲይዝና የብሄር ተኮር ፌደራሊዝም እንዲመሰረት ነው። በመሆኑም፤ በአሁኑ ወቅት ህወሓት የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነቱን ይዞ፤ ኢትዮጵያንና ህዝቧን የሚመራበትና የሚያሰተዳድርበት የፖለቲካ አመለካከትና የአገዛዝ ስልት የሚመነጨው ከዚሁ የፖለቲካና የአመራር አመለካከቱ፤ ባህርይው፤ ከፈጠራቸው ደጋፊ ተቋማትና ከበላይነቱ አንጻር ነው። ለምሳሌ የምርጫ ቦርድ፤ የፌደራል ጉዳዮች ተቋም፤ መገናኛ፤ የመከላከያና የደህንነት ተቋማት ሙሉ በሙሉ የህወሓት የበላይነት መሳሪያ ናቸው።

ህወሓት በበላይነት የሚመራው የኢህአደግ ብሄር ተኮር አመለካከትን (Ethnicism) እንደ አይዲኦሎጂና እንደ ወሳኝ የፖለቲካ ባህል በማስተጋባትና የብሄር ተኮር ፌደራሊዝምን (ethnic federalism ) እንደ አስተዳደር ቅርጸመንግሥትነት ተቀብሎ ተግባራዊ በማድረጉ፤ በፖለቲካው ዘርፍ ሲታይ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ የዜግነት ድርሻውን መሰረት አድርጎ ፤ በመንግሥት ፖሊሲ አቀራረጽ፤ በባጀት አመዳደብ፤ ስልጣንና በኢኮኖሚ ሙሉ ተሳትፎ እንዳይኖረው አግዶታል። ህወሓት በበላይነት የሚያስተዳድረውን የኢህአደግን የብሄር ተኮር ፌደራሊዝምን የቡድኑ የፖለቲካ መሳሪያ አድርጎታል። በማንነትና በመሬት ስሪት ዙሪያ ጥያቄዎችና ችግሮች የማይፈቱት ለዚህ ነው። ህወሓት በበላይነት የሚያሽከረክረው ኢህአደግ ሆነ ብሎ በፈጠረው ስልት፤ ተራው ኢትዮጵያዊ የማህበራዊ ህይወቱና የሕዝቡ ልምዳዊ፤ ተፈጥሯዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ሰንሰለቶች ሁሉ እንዲፈራርሱና እንዲበታተኑ አድርጓል። ህወሓትትና ተባባሪ ያደረጋቸው የኢህአዴግ ስብስቦችና ደጋፊዎች እነዚህን የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚ፤ የተፈጥሮና የማህበረሰባዊ ኃብቶች በመማረክና የበላይነቱን ሃላፊነት በቁጥጥሩ ስር በማድረጉ የአገሪቱን ባለቤትነት የሚመለከቱ መሰረታዊ ጉዳዮች ሁሉ በዚሁ በብሄር/ ብሄርሰብ ማንነትንና ልዩነትን ተቀዳሚነት መስፈርት እንዲወሰኑ አጉልቷቸዋል። ይህ የጠባብ ብሄርተኝነት አይዲሎጅና ብሄርን መሰረት ያደረገ ፌደራሊዝም ጎልቶ ተቋማዊ መሆኑ በዜግነት መብት ሊመሰረት የሚገባውን የኢትዮጵያዊነት ማእቀፍ፤ መለያና መብት ሙሉ በሙሉ እንዲጠፋ አድርጎታል ባይባልም አድክሞታል።

በዚህ አኳያ፤ በግልጽ የሚታየው ክስተት እንደሚከተለው ነው። የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት፤ ነጻነት፤ ሉዐላዊነትና ስብጥር የሕዝቧ ማህበረሰባዊ ግንኙነትና ትሥስር ስር ነቀል በሆነ ደረጃ የተቦረቦረውና የሚቦረቦረው ገዥው ቡድን የሀገሪቱን የፖለቲካ ስርአት በአምባገነንነት በመምራት በብሄር ማንነት ዙሪያ መደራጀት ብቻ በማበረታታትና በማገዝ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ህብረብሄር ተቋማትና ፖለቲካ ድርጅቶች እጅግ በተጠናከረ አፈና እንዲዳከሙና እንዲፈራርሱ ስለተደረገ ነው።

በሸንጎ እምነት ኢትዮጵያ ዘላቂነት የሚኖራትና መላው ሕዝቧ ከድህነት፤ ከረሃብ፤ ከስራ እድል ማጣት፤ ከኑሮ ውድነት፤ ከሙስና፤ ከጥገኝነትና ከስደት ሰቆቃዎች ራሱን ነጻ ለማውጣት የሚችለው አሁን ያለው ከፋፋይና፤ ጠባብ ብሄርተኛ፤ ጸረፍትህ፤ ጸረሕዝብ፤ ጸረሰላምና ጸረዲሞከራሲ ስርዓት ሲለወጥና በምትኩም ሁሉን አቀፍ የሆነ ሕገመንግስታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ሲመሰረት ብቻ ነው።

በሸንጎ እምነት የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ተስፋና ምኞት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የግልም ይሁን የወል ሰብአዊና ዲሞክራሳዊ መብት ተከብሮ፤ የኢትዮጵያ ዘላቂነትና ሉዐላዊነት ለድርድር የማይቀርብ ሆኖ፤ መላው ሕዝቧ የተሻለ ኑሮ እንዲኖር የተመቻቸ ሁኔታ ሲፈጠር ነው። ህወሓት በፍጹም የበላይነት የሚያስተዳድረውና የሚያዘው ኢህአደግ ለዚህ ብሄራዊ ራእይ መሰናክል ምክንያት ሆኗል።

ይህን የሕዝብ ፍላጎትና ምኞት ስኬታማ ለማድረግ የሚቻለው አሁን ለህወሓት የበላይነት ታማኝ የሆኑ የትግራይ ተወላጆች (የሕወሀት አባላትና ደጋፊወች) እንዲሁም በፖለቲካ ስልጣንና በኢኮኖሚ የግልና የቡድን ጥቅም ዙሪያ ህወሓት የሚንከባከባቸው የኢህአደግ ምርጥና ለስርዓቱ ታማኝ የሆኑ የሌሎች ብሄሮች አባላት በበላይነት የሚመሩትን የመከላከያና የደህንነት ተቋሞቹን ምሰሶዎች (Pillar of critical support) አድርጎ በበላይነት የሚያሽከረክረው አገዛዝ ሲለወጥ ብቻ ነው።

ሸንጎ ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን የሚወክልና የሚያሳትፍ ዲሞክራሳዊ ስርዓት እንዲመሰረት የሚታገል ድርጅት ነው። ለኢትዮጵያ ዘላቂነትና ሉዐላዊነት፤ ዋናው መስፈርት መሆን ያለበት በኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት፤ ሉዐላዊነት፤ በሕዝቧ ትሥስርነትና ዲሞክራሳዊ ስልጣን አምነው የሚታገሉትን ልዩ ልዩና የተበታተኑ ድርጅቶች ሁሉ ሰብስቦና አሳምኖ የዓላማ አንድነት እንዲኖራቸው ያልተቆጠበ ጥረት በማድረግ ነው። ይህ ስኬታማ ካልሆነ፤ ኢትዮጵያን የመሰለች ታሪክ ያላትና ለሁሉም ዜጎቿ የኑሮ መሻሻል እምቅ ኃብት ያላት አገር በብሄር ልዩነቶች ተበክላ ህልውናዋንና ዘላቂና ፍትሃዊ እድገቷን አስተማማኝ ለማድረግ አትችልም።

ሸንጎ የሚቃወመው አንዱ ጉዳይ የአሁኑ ህወሓት በበላይነት የሚመራው የኢህአዴግ ብሄር ተኮር እና አምባገነናዊ ስርዓት ለኢትዮጵያ ዘላቂነትና ለሕዝቧ ብሄራዊ አንድነትና እድገት ዋና ማነቆ መሆኑን ነው። በአብዛኛው፤ ዛሬ በየቦታው በማበብ፤ በመደራጀትና ራሳቸውን በትጥቅም ሆነ በዲፕሎማሲ በማዘጋጀት ላይ የሚገኙትን ለአንድነት ያልቆሙና የራሳቸውን “ነጻ” መንግስት ለመመስረት የሚጥሩ “ነጻ አውጭ ግምባሮች” ከህወሓት አይዲዖሎጅና አደረጃጀት አይለዩም። ህወሓት ከ26 አመታት ሀገራዊ ስልጣን በኋላ አሁንም ራሱን የሚጠራው “የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጭ ግንባር” ብሎ ነው። ይህ ስም ከኢትዮጵያ ዘላቂነት፤ ነጻነት፤ ሉዐላዊነት፤ ከሕዝቧ አብሮ፤ ተደጋግፎና ተጎራብቶ ከመኖርና ከሕዝቧ አንድነት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም።

ህወሓት ከጅምሩ ራሱ በብሄር ተደራጅቶ ሌሎችም በእርሱ ተለጣፊነትና አጫፋሪነት በብሄርም፤ በህብረብሄርም እንዲደራጁ ሁኔታዎችን አመቻችቷል። ይህ ደግሞ ህወሓት የበላይ እንደሆነ እንዲቀጥል ረድቶታል። ሁኔታው ለኢትዮጵያ መፈራረስ፤ ባትፈራርስም በቀጣይነት ለእርጋታ አለመኖርና ለተከታታይ ግጭቶች ግብአት ሆኗል የምንለው ለዚህ ነው።

ከላይ እንደገለጽነው ሸንጎ ብሄርን መሰረት ያደረገ የክልሎች አሸናሸንን እና የወልቃይትን ጉዳይ በሚመለክት ሰፊ ጥናት አካሂዷል፤ ውይይት አድርጓል። ልክ እንደማንኛውም ብሄራዊ ጉዳይ፤ እነዚህ ጉዳዮች እጅግ የሚያሳስቡን ናቸው ። የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ ጉዳያችን ነው። በዚህ መሰረት ሸንጎ የደረሰባቸው ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች የሚከተሉት ናቸው።

ሀገራችን ኢትዮጵያን በብሄር ተኮር ክልል ለመሽንሸን የተወሰነውና ተግባራዊ የተደረገው ህዝብን ባሳተፈ፣ የተለያዩ አመለካከት ያላቸው ባለድርሻዎች ድምጽ በተካተተበትና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የህዝብን ይሁንታ አግኝቶ በተመረጠ የህዝብ ተወካዮች ሳይሆን ኢህአዴግና አጋሮቹ ለብቻቸው በፈጠሩትና በሚቆጣጠሩት ምክር ቤት የወሰኑት ስለሆነ ሸንጎ ይቃወማል።

በሸንጎ ግምገማና እምነት ዛሬ ያለብን ታሪካዊ ግዴታና ሃላፊነት በመጀመሪያ ደረጃ ኢትዮጵያን ከመፈራረስና ሕዝቧን ከእር በርስ እልቂት ማዳን ነው። የዚህ ሃላፊነት ያለበት በኢትዮጵያ ዘላቂነት፤ ደህንነት፤ ጥቅም፤ ሉዐላዊነትነትና በመላው ሕዝቧ አንድነት የሚያምነው ክፍል ነው። ዛሬ እኛ የምንተባበርበት ጊዜ እንጅ የምንጠላለፍበት ጊዜ አይደለም እንላለን። ተባብረን ማስወገድ ያለብን የሚዘገንነውንና አገር አፍራሹን ህወሓት በበላይነት የሚያሽከረክረውን የኢህአዴግን አምባገነን ስርዓት ነው።

የተሽንሸኑት ክልሎች የህዝብን ታሪክ፣ ለአስተዳደር የሚኖርን አመችነት ፣ በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች ነዋሪ በሆነው ህዝብ መሀል ተመጣጣኝ እድገትን ለማስገኘት በሚረዳ ሁኔታ ክልሎች ተመጣጣኝ እድልን እንዲያገኙ የሚያሰችል መመዘኛ ወዘተ ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ሳይሆን በወቅቱ የፖለቲካ ስልጣኑን የጨበጡትን ክፍሎች (የህወሀት/ኢህአዴግንና የአጋሮቻቸውን ) የፖለቲካ፣ ወታደራዊና ወዘተ አላማ ለማሟላት የተደረገ ውሳኔ ስለሆነ ሽንጎው ይቃወማል፡፡
ህወሓት በበላይነት የሚያስተዳድረው ኢህአዴግና አጋሮቹ ብሄር ተኮር በሆነ መልክ የፈጠሯቸው ክልሎች “እኛና እነሱ” የሚል አመለካከትን የሚያበረታታ የሀገሪቱንና የህዝቡን አንድነት የሚያዳክምና ግጭቶችንም የፈጠረና እየተባባሱ እንዲሄዱ የሚያደርግ ስለሆነ ሽንጎ ይቃወማል።

የተሽነሽኑት ክልሎች በየክልሉ ውስጥ የሚገኙትን ማህበረሰቦች እኩልነት የሚያረጋግጡ ሳይሆን በተለያየ ቦታ ማህበራዊ ፍትህን ባዛባ ሁኔታ እኩልነትን ሳይሆን የበላይና የበታችነትን የሚፈጥርና ተግባራዊ የሚያደርግ ስለሆነ ባንዳንድ ቦታወችም የተለያዩ ማህበረሰቦችን ማንነት በሚያዳክም ሁኔታ የሚካሄድ በመሆኑ ሽንጎ ይቃወመዋል።

ብሄርን መሰረት አድርገው የተዋቀሩት ክልሎች በፌደራሊዝምና ራስን በራስ ማስተዳደር ስም የሚንቀሳቀሱ ቢሆንም በተግባር የሚታየው ግን ክልሎች የፖለቲካ ነጻነት የሌላቸው መሆኑ ነው። ክልሎች የሚተዳደሩት በማእከላዊነት በተሰየመው የህወሓትን የበላይነት በሚያንጸባርቀው በህወሓት አጋር ድርጅቶች ተባባሪነት መሆኑን ሽንጎ ይገነዘባል።

ሕዝብ በስርአቱ የተነሳ በማንነቱ የሚደርስበትን በደል፣በመቃወም የማህበራዊ ፍትህ መጥፋትን የመሬት ነጠቃን ፤መፈናቀልና አድልኦን ወዘተ በመቃወም የሚያካሂደውን ሕዝባዊ ትግል (ለምሳሌም በኦሮምያ ፣ በወልቃይትና ጠገዴ፣ በኮንሶ፤ በኦሞ ሸለቆ፤ በኦጋዴን፤ በጋምቤላ ወዘተ ) ሽንጎ ይደግፋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ሸንጎ የወልቃይቴው ህዝብ ጥያቄ አግባብነት እንዳለው ይቀበላል ። ሸንጎ የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ መሆኑን ያምናል። ጥያቄው የጎንደሪዎች ብቻ አለመሆኑን ተቀብሎ ፍትህ እንዲሰፍን ያለውን ፍላጎትና ምኞት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይገልጻል።

ሸንጎ ህወሓት በበላይነት የሚያስተዳድረውና የሚያዘው የኢህአዴግ ስርዓት ኢትዮጵያውያንን በብሄር ተኮር ክልል ሽንሽኖ ከተወሰነ አካባቢ ጋር ብቻ የተሳሰሩ ለማድረግ “በብሄር ወጥ” የሆነ ክልሎችን ለመፍጠር የሚያደርገው እንቅስቃሴ የሀገራችንን ህዝብ ብዙሀዊነት እጅግ ያላገናዘበና ግጭትን የሚጋብዝ ሰለሆነ ይቃወመዋል; አይቀበለውም ። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ያለምንም ወከባ ጥቃትና ተጽእኖ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የመኖር መብት እንዳለው ማወቅና ይህንንም ያለምንም ማመንታት ተግባራዊ ማድረግ ያሰፈልጋል ብሎ ያምናል።

በአንዳንድ ቦታወች ህወሓት ለራሱ ፖለቲካዊ ስትራተጂ ሲል በሽነሸነው ክልሎች የጎሳ ስብጥርን ሙሉ በሙሉ በሚቀይር ሁኔታ የሚያካሂደው ሰፈራ እጅግ አደገኛ የሆነ አካሄድ ብቻ ሳይሆን በወገኖቻችንም መሀል አላሰፈላጊ ቅራኔንና ግጭትን የሚጋብዝ ስለሆነ ሽንጎው የዚህ አይነቱ ተግባር ባስቸኳይ እንዲቆም ያሳስባል። በዚህም መሰረት የአስተዳደር ክልሎች በብሄር ተኮር እንዲሸነስኑ መሆናቸው እጅግ ሰፊ ማህበረሰባዊ ችግርንና በህዝባችንና በሀገራችን አንድነት ላይ ታላቅ አደጋን አስከትሏል። በዚህ ፖሊሲ ምክንያት እጅግ ብዙ ኢትዮጵያውያን ተፈናቅለዋል፣ ንብረታቸው ተነጥቋል፣ ሕይወታቸው ጠፍቷል። ይህ ከቀጠለ እጅግ ሰፊ የእርስበርስ ግጭት የሚጋብዝ እንደሆነ ሽንጎ ያምናል።
መሬት የብሄር ብሄረሰቦች ነው በሚለው ፍልስፍናው ባንድ አካባቢ የሚኖር ዜጋ ካካባቢው ውጭ የሚኖረውን መብት የተሸራረፈ ባይተዋርና ዝቅ ያለ አድርጎታል። ይህ መሬት የክልል የሚያደርገው አመለካከት የክልልን ድንበር ለማስፋፋት አንዱ መሰረታዊ የሆነ የግጭት መንስኤ ሆኗል። በኦሮሚያና በሶማሌ፣ ባአፋርና ሶማሊያ በጉጂና ቦረና፣ በአማራና በትግራይ፣ በኮንሶ፣ በትግራይና በአፋር ወዘተ የሚታዩትን በምሳሌነት መመልከት ይቻላል። ህወሓት በበላይነት የሚያስተዳድረው የኢህአዴግ ስርዓት በመላ ሀገሪቱ የደነገገውና የተከተለው ብሄርን መሰረት ያደረገ የክልል አሽናሽን ነዋሪዎችን ከቀያቸው አባርሮ ሌሎችን ማስፈርና በልማት ስም የመሬት ነጠቃንና ተስፋፊነትትን ፖሊሲና ተቋማዊ ማድረግ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ይጻረራል፤ ያፈርሳል።

ህወሓት የጎንደር/ቤጊምድርን መሬት ሆነ ሌላ መሬት ነጥቆ ያለህዝብ ፍላጎት ወደ ትግራይ ክልል ማጠቃለልና በሌሎች ክልሎችም ያካሂዳቸው ከልልን አንደፈለገ የመንጠቅና፤ የመሽንሽን ተመሳሳይ ፖሊሲወች ነዋሪዎችን ማሰር፤ መግደል፤ እንዲሰወሩ ማድረግ፤ ማሰቃየት፤ ከቀየአቸው ማባረር አገርን ያፈርሳል፤ ተከታታይ ጥላቻንና ግጭቶችን ይፈጥራል፤ እርጋታንና እድገትን ይበክላል። በእኛ እምነት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ድርጅትና ግለሰብ፤ ይኼን አፍራሽና አደገኛ የመሬት ነጠቃና ሽንሸና የህወሓትንና የተባባሪዎቻቸውን አፍራሽ ስራዎችን መቃወም ይኖርበታል።

ሸንጎ በዘላቂነት ሲመለከተው የወልቃይት ጠገዴና የሌላው ሕዝብ ጥያቄ መልስና ፍትህ የሚያገኘውና ከኑሮው የተፈናቀለው ሰፊ ሕዝብ መብት የሚከበረው ህወሓቶት/ኢህአዴግና ደጋፊዎቻቸው በሚከተሉት በጠባብ ብሄርተኛነት ፍልስፍናና በቀረጹት ብሄር ተኮር ፌደራሊዝም ስርዓት እንዳልሆነ ያምናል።

የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ለመስረታዊ መብቱ መከበር ፣ የሚካሄድበትን የመሬት ነጠቃ መፈናቀልና ሌሎችንም የግፍ ተግባሮች ሽንጎ አጥብቆ ያወግዛል። ለዚህም የመብት ትግል ያለውን ድጋፍና ከህዝብ ጎን መቆሙንም ያረጋግጣል።
ወልቃይት ጠገዴ አማርኛም፣ ትግርኛም ሆነ ሌላ ቋንቋ ተናጋሪ ኢትጵያውያን የሚኖሩበት በታ ሲሆን ከህወሀት/ ኢህአዴግ ስርዓት በፊት በነበሩት ያስተዳደር ጊዜያት ውስጥ ማለትም በደርግ፣ በቀዳማዊ ሀይለስላሴ፣ በአጼ ምኒልክ፣ በአጼ ዩሐንስ መንግሥታት የሚተዳደረው በትግራይ ፣ በኤርትራ ወይም በሌላ ሳይሆን በበጌምድር/ በጎንደር ቀደም ሲልም ባካባቢው አስተዳደሮች ስር እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ። ሸንጎ ይኼን የታሪክ ሂደት ይቀበላል።

ሸንጎ የአሁኑ የቋንቋ/ብሄር “ከፋፍለህ ግዛው” ስርዓት አገር አፍራሽ፤ ጸረሰላም፤ ጸረፍትህርትህ፤ ጸረሕዝብና ጸረዲሞክራሲ ስለሆነ፤ ስርዓቱ ተወግዶ እውነተኛ ሕዝብን የሚወክል፤ ለሕዝብ ተገዢና ታዛዢ የሆነ ስርዓትና መንግሥት እንዲመሰረት ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ድርጅቶችና ግለሰቦች ጋር ተባብሮ የሚያደርገውን ትግል ከመቸውም በበለጠ ደረጃ አጠናክሮ ለመቀጠል የወሰነ መሆኑን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ቃል ኪዳን ይገባል።

ለዚህና ለሌሎችም እጅግ ዘግናኝ ግፍ መሰረቱ የህወሀት/ኢህአዴግ አግላይና አንባገን ስርአት በመሆኑ መሰረታዊ የስርአት ለውጥ በማምጣትም በዚህ ጽሁፍ ውስጥ የተጠቀሱትንም ሆነ ሌሎች ችግሮች በብሄራዊ መግባባት፣ በሰጥቶ መቀበልና ፍትሀዊ በሆነ መንገድ የህዝብንና የሀገርን እንድነት በሚያጠናክር ሁኔታ ለመፍታት ሽንጎው ባስቀመጣቸው መለስተኛ መግባቢያ ነጥቦች ዙሪያ ለስርአት ለውጥ የሚታገል ሰፊ የተቃዋሚ ህብረትና የህዝብን ትግል ማፋፋም እንደሚገባ በድጋሚ አጽንኦት ሰጥቶ መታገል አስፈላጊ ነው።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!

            http://www.ethiopanorama.com