May 29, 2017

የዛሬው ፅሁፌ የሚያጠነጥነው ሰሞኑን አሜሪካ ሲያትል ተደርጎ የነበረውን የተለያዩ “ድርጅቶችና “ግለሰቦች የተሳተፉበትን ስብሰባ ተከትሎ በሁለት ጉዳዮች ላይ ይሆናል ።

አንድ በፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማሪያም ዙሪያ ሲሆን ሁለተኛው ደሞ አርበኞች ግንቦት 7 በተባለው ድርጅት ላይ ይሆናል።

ከላይ እንደጠቀስኩት የዚህ ፅሁፍ ቆስቋሽ በሲያትል በውስጠ ታዋቂነት በግንቦት7 ዋና አስተባባሪነት የተጣመሩ ድርጅቶች ያዘጋጁት ስብሰባ ነው።

ለሳምንታት ይሄ ስብሰባ ከመደረጉ በፊት በማህበራዊ ድረገፅ የተለጠፈው ማስታወቂያ ላይ የተሳታፊ ተጋባዥ እንግዶችን ስብጥር ስመለከት ቀድሞውንም ጥርጣሬ ነበረኝ። ይሄው እንደጠረጠርኩት አማራ ባልተጋበዘበትና ባልተሳተፈበት ስብሰባ ሲብጠለጠል ዋለ።

ጨቋኟ አማራ ጠላታችን ነው!” ብሎ ደደቢት የገባው አረጋዊ በርሄ፣ “አማራ የሚባል ህዝብ የለም” ያለው ፕሮፌሰር መስፍን፣ የአርባጉጉና የበደኖ አርበኞች የተሳተፉበትና አማራ ያልተወከለበት ስብሰባ ከመሆኑ አንፃር የጉባኤውን ውጤት ቀድሞ መተንበይ የሚያስቸግር አልነበረም።

ፕሮፌሰር መስፍን ረጅም የህይወት ዘመናቸውን አወዛጋቢ ሆነው እንደኖሩ ብዙዎች ይስማማሉ። ቀኑ እየገፋ እየተዋገደ እና እየመሸ ሲመጣ “ኑዛዜ” ያደርጋሉ ብለን ስንጠብቅ አሁንም አወዛጋቢነታቸው ቀጥሏል።

እዚህ ላይ አንባቢ እንድገነዘብልኝ የምፈልገው ለአንድ ክፍለ ዘመን ትንሽ የቀረው አመታት የኖሩትን አረጋዊ “ለመዘርጠጥ” አስቤ የፃፍኩት እንዳይመስልብኝ ነው። ፕሮፌሰሩ አማኝ እንደሆኑ አውቃለሁኝ። ዶሮ ሳይጮህ ሶስት ጊዜ “የለም” ብለው የካዱትን ህዝብ ተፀፅተው ጥፋታቸውን በንስሃ ያጥባሉ ብዬ ስጠብቅ ጭራሽ ሌላ አጀንዳ ይዘው ብቅ አሉ።

በሌላ በኩል ኑዛዜ ማለቴ ምሁሩን ለመክሰስ ሳይሆን በአንድ ወቅት “ጠመንጃው ያለው በእጃችሁ ሆኖ ጊዜውም ሁኔታውም እየፈቀደላችሁ የኛን የብእር ብትር እንደት ትጠብቃላችሁ? መርማሪ ኮሚሽን ምናምን እያላችሁ ስታመነቱ በስፔን አቢዮት እንደደረሰው ጎርፉ እኛንም እናንተንም ጠራርጎ እንዳይወስድ አፈራለሁ።”

የሚል ወኔ ቀስቃሽ ንግግር ለደርግ አድርገዋል የሚል ክስ ከብዙ ሰዎች ስለተነሳባቸው እንደው ይሄን ጉዳይ በደንብ ቢያብራሩት ለማለት ነው።

ይሄ ነገር መንግስቱ ሃይለማሪያምም ተናገረው። ጠቅላይ ሚንስቲር የነበረው ፍቅረስላሴም ወግደረስም ደገመው፣ ምክትል ፕሬዚደንት የነበረው ፍስሃ ደስታም ሰለሰው። ፕሮፌሰሩም የትርጉም ልዩነት እንዳለው ነገሩን እንጅ የተባለውን ማለታቸውን አልካዱም።

አውቄ በስህተት ሳላውቅ በድንቁርና የሰራሁት ሃጢያት ካለ ይደምሰስልኝ?” ማለት ባህላችን ነው። ቢያንስ እርምጃ ከተወሰደባቸው 90 በመቶ የሚሆኑት አማራ ናቸው በማለት ነው።

አሁን ይዘው የመጡት አጀንዳ ደሞ ” ማንነትን መስረቅ መመንተፍ” ነው። አርበኛው በላይ ዘለቀ “ኦሮሞ” ነው የሚል ነው። https://www.youtube.com/watch?v=_uK66IcXfHs ይሄ ነገር ቆየት ያለ ነው። መጀመሪያ ተስፋዬ ገ/አብ ያለው መሰለኝ። ኦነጎቹ ዘፈን ዘፍነውበት ኢሳት ላይ ሰምቸዋለሁኝ። አሁን ፕሮፌሰሩ የተስፋዬ ገ/አብ ቃለአቀባይ ሆነው ቁጭ አሉ። ይሄ የበላይ ዘለቀ ማንነት ጉዳይ የግለሰብ ብቻ ሳይሆን ውስጡም ፖለቲካዊ ተንኮል አለበት። ለጊዜው ያን መግለፅ አልፈልግም።

 

ፕሮፌሰር የሞተ ሰው ስለራሱ አይናገርም ፣ ስሙ ሲጠፋ ፣ ማንነቱ ሲመነተፍ ቀና ብሎ “ውሸታም!” ብሎ አያሳፍርም በማለት መዘላበድ ነውር ነው። በደራ ገበያ በሃሰተኛ ሚዛን የፖለቲካ ትርፍ መሸመት ያስነውራል። ለነገሩ ፕሮፌሰሩ “አማራ የሚባል ብሄር የለም” ስላሉ በላይ ዘለቀ፣ ሌላም አማራ By default ወይ ኦሮሞ፣ ወይ ወላይታ፣ ከፋ፣ ትግሬ ወዘተ ተረፈ መሆኑ አይቀርም ነበር ማለት ነው።

እዚህ ላይ አንድ ነገር ማስታወሱ አይከፋም። በአንድ ወቅት የፕሮፌሰር መስፍን ማንነት በየመፅሄቱና ጋዜጣው አወዛጋቢ ሆኖ እንደቀረበ አስታውሳለሁ። ተስፋዬ ገ/አብ በሚያዘጋጀው “እፎይታ” በተባለ መፅሄት ፕሮፌሰር መስፍንን የወላይታ ተወላጅ ናቸው ብሎ ፅፎ ነበር። በኋላ ተስፋዬ የጋዜጠኛው ማስታወሻ በተባለ መፅሃፉ “ውሸታችንን ስም ለማጥቆር ታዝዤ የፃፍኩት ነው” በማለት አስተባብሏል።

ከአመት በፊት ይመስለኛል ፕሮፌሰሩ በኢሳት ቀርበው የአባታቸው አገር ሸዋ የእናታቸው ደሞ ወሎ እንደሆነ ተናገሩ። ብዙም ሳይቆይ ከ6 ወር በፊት ደሞ በአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ (VOA) ቀርበው ከአድዋ የሚወለዱ ትግሬ እንደሆኑ ሲናገሩ ተሰማhttps://www.youtube.com/watch?v=BtnGi-wTf78  ) በወቅቱ ይሄ ምስቅልቀል ያለ ንግግራቸው አልገባኝም ነበር።

ለካ ፕሮፌሰሩ የተምታታባቸው የ40 ሚሉዮን ህዝብ ማንነት ብቻ ሳይሆን የራሳቸውም ነው።

ወደ ግንቦት 7 ጉዳይ ልመለስ። ግንቦት 7 የሚሰራውን ፖለቲካ በየሚዲያውም እሰማለሁኝ፣ ስለድርጅቱ የሚነግረኝም ካለ አዳምጣለሁኝ። የዚህ ድርጅት የፖለቲካ አካሄድ በሁለተኛው የአለም ጦርነት ተሞክሮ የከሸፈውን እና ያረጀ ያፈጀውን “አፒዝመንት” የሚባለውን ፖሊሲ ያስታውሰኛል ።

አፒዝመንት” የሚባለው ፖሊሲ ባለቤት በወቅቱ የእንግሊዝ ጠ/ሚ የነበረው ቻምበርሌየን ነበር። በዚህ ፖሊሲ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና ሩሲያ የሒትለርን አላማ እያወቁ አዉሮጳን ለመሰልቀጥ በርሊንን ለሚያስደልቀዉ ለናዚዎች የጦርነት ዛር ሐገራትን ጭዳ በማድረግ (ናዚዎች እንዲወስዱ) በመፍቀድ ትልልቆቹን ሐገራት በተለየም ብሪታንያን ከትልቆች ትልቅናት ሊሽቀነጥራት ከሚችለዉ ትልቅ ጦርነት ማዳን ይቻላል የሚል መርሕ ነበራቸዉ። ይሄን ፖሊሲ “አፒዝመንት” ይሉታልመርሁን።

አፒዝመንት” ማለት ማርካት፣ ማስደሰት፣ አለማስቆጣት፣ ቦታ መልቀቅ፣ ፈቀቅ ማለት፣ ሌላውን ለማስደሰት ዝም ማለት፣ ራስ እስካልተነኩ ለሌላው ደንታቢስ መሆን ማለት ነው።

የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔቪል ቻምበርሌይን ይህንን ለአገሩ ሰዎች በመስከረም መጨረሻ 1938 በሬድዮ ሲናገር፥ “አዶልፍ ሂትለር ከእኛ ጋር እንድስማማ ድንበሩን ተሻግሮ የያዛቸውን አገሮች ይወስድ ዘንድ መፍቀድ አለብን። እሩቅ አገር ያሉ ሁለት የማናውቃቸው ሕዝቦች እርስ በርሳቸው ስለተዋጉ እኛ ምሽግ እየቆፈርንና የመርዝ ጋዝ መከላከያ ጭምብል እየለካን የምናደርገው ይህ አሳፋሪ ነገር ምንድርነው?” ብሎ ነበር።

ያኔ የፓርላማ ተመራጭና ኋላ የጦርነቱ ዘመናት ጠቅላይ ሚኒስትር የሆነው ዊንስተን ቸርቺል ይህን ሲሰማ እንዲህ አለ፣ An appeaser is someone who feeds a crocodile hoping it will eat him last. የመሪዎቹን ስምምነት በመንቀፍም፥ The choice they made was between war and dishonor. They chose dishonor; they will have war!” አለ። እውነትም፥ አስደሳችና የማያስቆጣ ሰው ዐዞው ራሱን እስኪበላው ድረስ ጊዜ ለመግዛት ዐዞውን የሚቀልብ ሰው ማለት ነው። መበላት ካልቀረ ማብላት ጠቀሜታው ምንድር ነው? እውነትም እነ እንግሊዝ ፈረንሳይና ሩሲያ ሂትለርን ለማስደሰትና ላለማስቆጣት ብለው ከጦርነት ይልቅ ዝምታን መምረጣቸው ውርደትን መምረጣቸው ነበር ጦርነቱ አልቀረላቸውምና ሁለቱንም አገኙት። ቀድሞ ዝም ባይባል ለውጥ ሊፈጠርና 2ኛው የዓለም ጦርነት ላይከሰትና ከ60 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ላያልቁ ይችል ነበር።

አርበኞች ግንቦት 7 የተባለውን ድርጅት ብዙ ጊዜ በብዙ ሰዎች በፀረ አማራነት ሲከሰስ እሰማለሁም አዳምጣለሁም። እነዚህ ሰዎች ይሄን የሚሉት ከሜዳ ተነስተው አይመስለኝም። የሰሙት ያነበቡት እጅ ከፍንጅ የያዙት ጉዳይ ይኖራል። በእኔ በኩል ይሄን ድርጅት “ፀረ አማራ ነው!” የሚል መደምደሚያ ባልደርስም ድርጅቱ አማራን አግላይ የሆነ ፖለቲካ እንደሚሰራ አምኛለሁ።

ግንቦት 7 የአማራ ብሔርተኝነት የማየሉ እና የመስፋፋቱ ሁኔታ ጥሩ ስሜት የሰጠው አይመስልም።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሃይሎች የኦሮሞ ልሂቃንን ለማስደሰት የሚሄዱበት መንገድ አስቂኝም አሳፋሪም ነው። ፖለቲካቸው የከሰረ፣ ተሞክሮ የከሸፈ እና ኢሳይንሳዊ የሆነ ነው። የዚህ ዋነኛ አቀንቃኝ ግንቦት 7 የሚባለው ድርጅት ነው። የግንቦት 7ን ፖለቲካ አስቀያሚ የሚያደርገው ኮኦነግ እና ሌሎች ተገንጣይ ድርጅቶች ጋር ለሚያደርገው መሞዳሞድ እንደ ጥሎሽ መጠቀም የሚፈልገው አማራውን መሆኑ ነው።

ግንቦት 7 በየቀኑ በአንድ እግሩ ሌላኛውን እግሩን ጠልፎ የመጣል ያህል ድርጊት እየፈፀመ መሆኑን ሳይ አሳዘነኝ። ሰው አይኑን ገለጥ አድርጎ ማየት እንዴት ይሳነዋል? ዛሬ ላይ ተቀምጠው በዛሬ 100 ዓመት ካርድ ቁማር ከሚጫወቱት ጋር ትዳር እየመሰረቱ፤ የዛሬውን ጭቁን ለመጨፍለቅ መሞከር ራስን በራስ ጠልፎ ከመጣል ይቆጠራል።

ግንቦት 7 የኦነግና የኦብነግን ያበጠ እዥ እያከኩ፤ የአማራ መደራጀት የኢትዮጵያ አንድነት ከፍተኛው ስጋት ነው ሲሉ ያሳፍራል።

በብሔር መደራጀት ኢትዮጵያዊነትን ከጎዳ ለኦነግም፣ ለኦብነግም ለአማራ ድርጅቶችም እኩል ቀይ ካርድ ማሳየት ጀግንነትንና የአላማ ፅናትን ያመለክት ነበር። ግንቦት 7 ግን ውስጡ የተቦረቦረ ግንድ ማለት ነው ወይም ፀጉራም ውሻ።

ለአመታት ፕሮፌሰር መስፍን ማንነታችንን ቢክዱ እንኳን በአማራዊነት ጨዋነት “ጋሼ አለን! ” ከማለት ውጭ ክፉ ተናግረናቸው አናውቅም። እሳቸው ግን ይባስ ብለው በየሚዲያው የሚያወሩት ሁሉ እንደ አዛውንት አልሆን አለ። ነቢዩ ዳንኤል የተናገረው ትንቢት ለፕሮፌሰር እና ለግንቦት 7 የሚሆን መሰለኝ።

ነቢዩ ዳንኤል “ማኔ ቴቄል ፋሬስ (በሚዛን ተመዘንህ፥ ቀልለህም ተገኘህ !) አለ ትን. ዳንኤል ፭፡፳፭።