May/30/2020

የአዛውንቱን ምሑር ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያምን ንግግር ከመጀመርያው እስከመጨረሻው ብቻየን ሁኘ ዛሬ በጥሞና ሰማሁት። አንዳንድ ኢትዮጵያውያን የዐምሐራ ድርጅት ደጋፊዎች ነን የሚሉት ወንድሞቸና እኅቶቸ በፕሮፌሰሩ ንግግር ላይ በየማኅበራዊ መገናኛዎቹ አሉታዊ የተመላበት የመልስ አስተያየት ከሠጡት ጋር ሳወዳድረው፣ ከነዚህ ወንድሞቸና እኅቶቸ ጋር የምስማማበት አንድም አሉታዊ ገልፃ ከፕሮፈሰሩ አንደበት የወጣ ቃል ማዳመጥ አልቻልኩም። ፕሮፌሰሩ ከአንድ አረጋዊ ምሑር አባት የሚጠበቀውን ምክርና ተግሣጽ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብና፣ እንወክለዋለን ለሚሉት ልሂቃን የፖለቲካ ስብስብ መሪዎች ለግሠዋል። በዐምሐራ ብሔራዊ ማንነት ስም ተደራጅተናል የሚሉት ወገኖቸ፣ አበሳጨን እያሉ ከሚጠቅሱት የፕሮፌሰሩ ንግግር ውሥጥ ፣ አፄ ቴዎድሮስን ሕዝቡ ጠልቶት ስለነበር ብቻውን ለጠላት ተጋልጦ ሞተ ብለዋል የሚለውና፥ ጀግናው በላይ ዘለቀን ኦሮሞአሉብን የሚሉት አባባሎች ናቸው። እውነት ነው አፄ ቴዎድሮስ በመሳፍንት ተከፋፍላ የነበረችን ኢትዮጵያ መልሰው አንድ ለማድረግ ባደረጉት ጥረት ጊዜ፣ ዘመቻው አልጋ በአልጋ አልነበረም። ብዙ ሕዝብ በተለይ በጎንደር፣ ጎጃምና ወሎ አልቋል። ምክንያቱም በዚያን ጊዜ የአፄ ቴዎድሮስ ዓላማ እና የሕዝቡ ኋላ ቀር አመለካከት ያልተጣጣመ ነበር። ያለ ጊዜው የተወለደ ንጉሥየተባሉትም በዚህ ምክንያት ነበር። በዚህ ምክንያት የትግራዩ በዝብዝ ካሣ ለእንግሊዙ ጀኔራል ናፔር አሳልፈው ሲሠጧቸው፣ ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ይቅርና፥ ከትውልድ ክፍለ ሀገራቸው ጎንደር ሳይቀር አብሯቸው የቆመ አልነበረም። ይህ እውነት ነው። በላይ ዘለቀን ኦሮሞ አሉትየሚለው በተለይ አስቂኝም አስገራሚም ነው። በፋሺስት ጣልያን ወረራ ጊዜ ዕኮ በላይ ዘለቀም ብቻ ሳይሆን ስፍር ቁጠር ያልነበረቸው የኦሮሞ ጀግኖቸ 5 ዓመት ሙሉ ወረራውን በጀግነት ተቋቁመው ለነፃነት አብቅተውናል። እንዲያውም እውነቱን እንነጋገር ከተባለ በዚያን ወረራ ጊዜ የኦሮሞ ባንዳ ጨርሶ አልነበረም ቢባል ማጋነን አይሆንም ብየ አምናለሁ። ሁሉንም ነገር አሁን ወያኔ ካመጣብን የጎሳ ማንነትና መከፋፈል አንፃር እያየን ያለፉትን አባቶቻችን ሁኔታ አሁን ካለንበት ጋር ማያያዝ ትክክል አይደለም። === ነገር ግን የኔ ጥያቄ የሚነሳው እንዴት ነው የወያኔ ዘረኛና ቂም በቀለኛ አገዛዝ ጋር አብረን መክረን እየመጣ ያለውን መጠፋፋት አስወግደን፣ ቂምንና በቀልን ጨርሰን በማጥፋት ሕዝበመንግሥታዊ ሥርዓት መትከል/መመሥረት የምንችለው ? ነው። የዚህ አገዛዝ የመጨረሻ ግብ አጥፍቶ መጥፋት የሚለው የተስፋ ቆራጮችና የደናቁርት መርሕ አይደለም ወይ? ቁልፉ በዚህ ፀረ ኢትዮጵያ አገዛዝ እጅ ስለሆነ እንዴት ነው ፕሮፌሰሩ ካሉት ግብ ላይ ተጉዘን የምንደርሰውና የሕዝብን እልቂትና የሀገር መፈራረስ አደጋን ማስወገድ የምንችለው ? እኔ በስብሰባው የመገኘት ዕድል ገጥሞኝ ቢሆን ኑሮ ጥያቄዎቸ እነዚህን የመሳሰሉ ይሆኑ ነበር።….ለማንኛውም አረጋዊውን ፕሮፌሰር መልካም ምኞታቸው ተሳክቶ ለማየት ያብቃቸው ብየ መልካም ምኞቴን ለእርሳቸውና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመመኘት ሌላ በዚህ ንግግራቸው ላይ ምንም እንከን አላየሁበትም እላለሁ። ከበደ አ. ቦጋለ። እናንተስ ???

Prof Mesfin Woldemariam’s Speech at National Unity Conference Seattle, Washington 2017

Kebede Bogale

ከፌስቡክ የተገኝ