ከስዩም ተሾመ

እጅግ ከማደንቃቸው የአፍሪካ ምሁራን አንዱ የሆነው ናጄሪያዊው ዋሌ ሶይንካ (Wale Soyinka) ስለ ሽብርተኝነት በሰጠው ትንታኔ “ፍርሃት ፍርሃትን ይወልዳል” ይላል። በእርግጥ የአሸባሪዎች የተወሰነ የሕብረተሰብ ክፍልን በፍርሃት ቆፈን ውስጥ እንዲወድቅ በማድረግ የራሳቸውን ፖለቲካዊ፣ መንፈሳዊ፣ ኢኮኖሚያዊ…ወዘተ አጀንዳ በሌሎች ላይ መጫን ነው። ለዚህ ደግሞ በተወሰነ ግዜና ቦታ አሰቃቂ የሆነ የሽብር ጥቃት በመፈፀም ሕብረተሰቡን በፍርሃት ያርዱታል። ሕብረተሰቡ አንዴ በፍርሃት ቆፈን ከተያዘ መብትና ነፃነቱን አይጠይቅም። ጠያቂ ያልሆነ ሕብረተሰብ ደግሞ ለጨቋኞች ተገዢ ይሆናል።

እንደ ዋሌ ሶይንካ አገላለፅ፣ በተለያዩ የዓለም ሀገራት የተንሰራፋውን ሽብርተኝነት ዋና መፈልፈያ ማዕከሉ ፍልስጤም (Palestine) ነው። ነገር ግን፣ “ፍርሃት ፍርሃትን ይወልዳል” እንዳለው፣ ሽብርተኝነት በራሱ ከሌላ ፍርሃት የተወለደ ነው። በዚህ መሰረት፣ ፍልስጤም የሽብርተኝነት መነሻ ማዕከል የሆነችበት ምክንያት እስራኤል በፍልስጤሞች ላይ የምትፈፅመው ግፍና በደል ነው። በእርግጥ ግፍና በደል የደረሰበት ሁሉ በድንገት ተነስቶ አሸባሪ ልሁን አይልም። በአንድ ጉልበተኛ ቡድን ወይም መንግስት የሚፈፀመው በደልና ጭቆና ገደቡን አልፎ ሰዎችን ከተገዢነት ወደ አሸባሪነት እንዲቀየሩ የሚያደርገው ዜጎች ሰብዓዊ መብታቸውና ክብራቸው ሙሉ በሙሉ ሲገፈፍ፣ በዚህም ከመጠን ያለፈ የሽንፈትና ውርደት (Humiliation) ሲሰማቸው ነው።

“ውርደት ማለት…” ይላል ዋሌ ሶይንካ፣ “ውርደት ማለት ከአያት – ቅድመ አያቶችህ የወረስከውና የቤተሰብህ ሕልውና የተመሰረተበት የወይራ ዛፍ በእስራኤል ለሚገነባው የግንብ አጥር ቦታ ለማስለቀቅ የእስራኤል ወታደሮች በኤሌክትሪክ መጋዝ እየቆረጡ ሲጥሉት፣ ከቤተሰቦችህ ጋር ቆመህ እያየህ ምንም ማድረግ አለመቻል ነው”። አያት ቅድመ-አያቶችህ ከኖሩበት መሬት ላይ በነፃነት እንዳትንቀሳቀስ ለሚገነባ የግንብ አጥር በቅርስነት የወረስከው የወይራ ዛፍ ተቆርጦ ሲጣል፤ አባትና እናት፣ ዘመድ-አዝማድ፣ የሀገር ሽማግሌ ሆነ መንግስት፣… ብቻ ማንም ምንም ሊደርግልህ እንደማይችል፣ አንተም በራስህ ምንም ማድረግ እንደማትችል ስታውቅ፣ በእጅህ ላይ ያለውን ብቸኛ አማራጭ ትጠቀማለህ፡- “አጥፍቶ-መጥፋት”። ፍልስጤሞች በአጥፍቶ-መጥፋት በእስራኤሎች ላይ ጥቃት መፈፀም የጀመሩት በዚህ መልኩ ነው።

በመሰረቱ፣ የእስራኤል መንግስት በፍልስጤሞች ላይ ግፍና በደል የሚፈፅመው እሱ ራሱ የሰቆቃ ልጅ ስለሆነ ነው። የአሁኗ እስራኤል እንደ ሀገርና መንግስት የተፈጠረችው አዶልፍ ሂትለር በአይሁድ ሕዝቦች ላይ በፈፀመው ግፍና ጭፍጨፋ ነው። ሂትለር አይሁዶችን ከምድረ-ገፅ ለማጥፋት ያንን ሁሉ ህዝብ ሲያስጨፈጭፍ በወቅቱ የነበሩ የአይሁድ ልሂቃን አሜሪካና እንግሊዝን ከመለመን ባለፈ ምንም ማድረግ አልቻሉም ነበር። እንደ ማንኛውም ሕዝብ የራሳቸው ሀገርና መንግስት ስላልነበራቸው ስድስት ሚሊዮን አይሁዶች ተጨፍጭፈዋል። በዚህም አይሁዶች ለከፍተኛ ሽንፈትና ውርደት ተዳርገዋል።

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንደተጠናቀቀ አይሁዶች የራሳቸውን ሀገርና መንግስት ለመመስረት ጥረት አደረጉ። ይህን ደግሞ ከሶሪያ፣ ግብፅና ሊባኖስ ከመሳሰሉ የአረብ ሀገራት መሬት በመቀማት፣ እንዲሁም ፍልስጤምን ከመሬቷም በተጨማሪ እንደ ሀገር ሉዓላዊነቷን በማሳጣት፣ “እስራኤል” የተባለች ሀገር “ዳግም” ተመሰረተች። በዚህ መልኩ፣ በአዶልፍ ሂትለር በአይሁዶች ላይ የፈፀመው ጭፍጨፋ “የአይሁድ አፓርታይድን” ፈጠረ።

በመሰረቱ፣ አፓርታይድ (apartheid) ማለት መለየት፥ ተለይቶ ወይም ተለያይቶ መኖር ነው። የአሁኑ የእስራኤል መንግስት ራሱን “የአይሁዶች መንግስት” (Jews’ State) ብሎ ነው የሚጠራው። ይህ በእስራኤል መንግስታዊ ስርዓቱ በዘር-ልዩነት ላይ የተመሰረተ ስለመሆኑ በግልፅ ይጠቁማል። ስለዚህ፣ ሂትለር አይሁዶችን ከምድረ-ገፅ ለማጥፋት የፈፀመው ጭፍጨፋ በእስራኤል የአይሁዶች አፓርታይድ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።

የአይሁዶች አፓርታይድ ስርዓት በፍልስጤሞች ላይ የሚፈፅመው ግፍና በደል ደግሞ እንደ ሃማስ፣ ሂዝቦላህና አል-ቃይዳ የመሳሰሉ የሽብር ቡድኖች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል። በተለይ አል-ቃይዳ በአሜሪካ ላይ የፈፀመውን የመስከረም አንድ (9/11) የሽብር ጥቃት ተከትሎ አሜሪካ ዓለም-አቀፉን የፀረ-ሽብር ጦርነት (Global War on Terror) በማወጅ እንደ አፍጋኒስታን፣ ፓኪስታን፣ ኢራቅና የመን በመሳሰሉ ሀገራት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን ለሞት፣ የአካል-ጉዳትና ስደት ዳርጋለች።

የዓለም-አቀፉ የፀረ-ሽብር ጦርነት ከአረብ ሀገራት በተጨማሪ በተለያዩ የዓለም ሀገራት በሚገኙ ሙስሊሞች ላይ የሽንፈትና ውርደት ስሜት ፈጥሯል። ይህ ደግሞ በተራው እንደ ቦካ-ሃራም እና “ÏSIS” ዓይነት የሽብር ቡድኖች እንደ አሸን እንዲፈሉ ምክንያት ሆኗል። ስለዚህ፣ ዛሬ ላይ ከናይጄሪያ – አፍጋኒስታን፣ ከእንግሊዝ እስከ ሶማሊያ ባሉ ሀገራት እያስጨነቀ ያለው የአሸባሪዎች እንቅስቃሴ በእስራኤል ካለው የአይሁዶች አፓርታይድ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። የአይሁዶች አፓርታይድ ደግሞ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከነበረው የናዚ ፋሽስታዊ ስርዓት ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው።

የአዶልፍ ሂትለሩ ናዚ በጀርመን ወደ ስልጣን የመጣበት መሰረታዊ ምክንያት በአንደኛው የዓለም ጦርነት ሀገሪቱ ያጋጠማት ሽንፈትና ውርደት ነው። ለዚህ ደግሞ “Treat of Versailles” በመባል የሚታወቀው ስምምነት የሚጠቀስ ነው። ይህ ስምምነት ሲረቀቅ ጀርመን የመሳተፍ እድል እንኳን ተነፍጓት ነበር። ይህ የተለያዩ የጀርመን ግዛቶች ልክ እንደ ኬክ እየተቆረሱ ለፈረንሳይ፥ ዴኒማርክ እና ቤልጂዬም እንዲሰጥ፣ የቅኝ-ግዛቶቿን ሙሉ በሙሉ እንድትቀማ፣ በጦርነቱ ወቅት በራሷ ላይ ለደረሰውና በአሸነፊዎቹ ሀገራት ላይ ለደረሰው ጉዳት ካሳ እንድትከፍል የሚያስገድድ ስምምነት ነበር። የጀርመን መሪዎች ይህን ስምምነት በግድ እንዲፈርሙ ተደረገ። በተለይ የቀኝ-አክራሪዎች የነበሩ ቡድኖች ለዚህ ተጠያቂ ናቸው ያሏቸውን ባለስልጣናት እስከ መግደለ ደረሱ።  ስለዚህ፣ የአዶልፍ ሂትለር ወደ ስልጣን የመጣው በአንደኛው የዓለም ጦርነት በጀርመኖች ላይ በደረሰው አሰቃቂ ሽንፈትና ውርደት ምክንያት ነው ማለት ይቻላል።

በአጠቃላይ፣ ዛሬ ላይ በስፋት ለሚስተዋለው የሽብርተኝነት ችግር መነሻ ምክንያቱን በግልፅ ለመረዳት የምክንያት-ውጤት ሰንሰለቱን ተከትለን መቶ አመት ወደኋላ መጓዝ ይቻላል። ከዚህ የምንረዳው ነገር ቢኖር እያንዳንዱ ታሪካዊ ክስተት የራሱ የሆነ አሳማኝ ምክንያት እንዳለው ነው። በጀርመን የነበረው የአዶልፍ ሂትለር ናዚ፣ በእስራኤል ያለው የአይሁዶች አፓርታይድ እና በዓለም ለተስፋፋው ሽብርተኝነት፣ ሁሉም የሽንፈትና ውርደት ውጤት ናቸው።

በሰዎች ሕይወት ውስጥ መከራና ስቃይ የሚያበዙ ፖለቲካዊ ስርዓቶች የኋላ ታሪካቸው ሲጠና ሁሉም የሰቆቃ ልጆች ሆነው እናገኛቸዋለን። ስለዚህ፣ “የሰቆቃ ልጆች” ማለት በአንድ የታሪክ አጋጣሚ በሕዝባቸው ላይ የተፈፀመን አሰቃቂ በደልና ጭቆና ተከትሎ ወደ ስልጣን የመጡ የፖለቲካ ኃይሎች በሌሎች ሕዝቦች ላይ ተመሳሳይ ዓይነት በደልና ጭቆና የሚፈፅሙ ናቸው።