ታዋቂው አዛውንት አገር ወዳድ ታጋይ እና ደራሲ ኮሎኔ አሥናቀ እንግዳ ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸው የጎንደር ሕብረት ለኢትዮጵያ አንድነት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ይገለፃል። እኒህ ታዋቂ ጀግና በቀደሙት ዘመናት ለፍትህ እና ርትእ በመታገል፤ ለእሥራት እስከመዳረግ ደርሰው የነበሩት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብሎም ለጎንደር ሕዝብ እጅግ የሚቆረቆሩ በመሆናቸው ነበር።
እኒህ ታላቅ ሰው ለፍትህ ታጋይ ብቻ ሳይሆኑ፤ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር ታሪካዊ እና እርዮታዊ ብዛት ያላቸው መፃህፍትን ጽፈዋል። ለምሳሌ ከፃፏቸው መጻህፍቶች ጥቂቶቹን ብንጠቅስ፤ “ሸክም የማይከብደው ትውልድ፤ አረባዊ አጼነት እና የአፍሪቃ ቀንድ ፍዳ፤ ዘመን ያልሻረው የሴቶች አበሳ ወዘተ…” ለትውልድ የሚተላለፍ የተሞክሮ ቅርስ ጥለው አልፈዋል።
እኒህ ጀጋና አርበኛ እና ታጋይ፤ ስሜታቸውን በወረቀት ብቻ ያስቀምጡ የነበሩ ሳይሆኑ ጨቋኙ መንግሥት በህዝብና በአገር ላይ የሚያደርሰውን ግፍ እና በደል፤ ማንንም ሳይፈሩ፤በማንኛውም አጋጣሚ ሁሉ በድፍረት በየአደባባዮች ተቅውሟቸውን በማሰማት ማንም ሰባዊ ፍጡር በፍርሃት ግፍና በደልን መሸከ እንደሌለበት እና በመታገልም መብቱን ማስከበር እና ነጻ እንደሚመጣ ያስተማሩ ለአብነት ለዘለዓለም ከምዝከራቸው ጀግኖቻችን አንዱ ተተኪ የሌላቸው ቆራጥ ዜጋ ነበሩ። ይህንም በማድረጋቸው፤ በግፍ የኢትዮጵያን ሕዝብ እስከወዲያኛው ለመግዛት ይመኙ በነበረው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ለረዥ ዓመታት በእሥር እና በግዞት እንዲቆዩ ተደርገው ነበር።
በመቀጠልም የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን መንግሥት የተካውን የደርግ ሥራዓት በሕዝብ ላይ የሚያደርሰውን ግፍ እና በደል በመቃወም እስከ በርሃ ድርሰ በመዝለቅ ለበርካታ አመታት ከወጣቱ ጎን ተሰልፈው ታግለው አታግለዋል።
በመጨረሻም እድሜ የጉልበት ማነሥ ሳይገድባቸው የወያኔንም ግፈኛ ሥራዓት በመቃወም አቅማቸው የቻለውን የትግል ሥልት በመጠቀም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን እስከ እለተ ሞታቸው መቆማቸውን አሥመዝግበው አልፈዋል።

በመሆኑም፤ኮሎኔል አሥናቀ እንግዳ ዘመናት የማይሽረው ሀገራዊና ሕዝባዊ ፍቅራዊ ታሪካቸውን በሁላችን ልብ ውስጥ የተከሉ ታልቅ ዜጋ በሥጋ ሲለዩን የተሰማን ኃዘን የአጠቃላይ አገሩን እና ወገኑን የሚወድ ዜጋ ሁሉ ሃዘን ነው ብለን እናምናለን።

የጎንደር ሕብረት ለኢትዮኢያ አንድነት የእኒህን ታላቅ የአገር እና የሕዝብ ባለወለታ ከዚህ ዓለም መለየት ምክንያት በኃዘን ልባቸው የተጎዱ ቤተሰቦች፤ ዘመዶች እና ወዳጅ ጓደኞቻቸው እግዚአብሔር መፅናናትን ይሰጣቸው ዘንድ እንመኛለን።

የጎንደር ሕብረት ለኢትዮጵያ አንድነት።