ዝክረ አበው፤

ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ዘብሔረ ሙላዱ ጎንደር አበ ኩሉ አድያመ ኢትዮጵያ፤ በኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገና ከአሥራ ሁለት ዓመት እድሜያቸው ጀምሮ በመንፈሳዊ ትምህርት ተጠምደው የቃል ትምህርትን  ጸዋዕትዖ ዜማ፣ መዝገበ ቅዳሴ፣ መጽሐፍተ ብሉያት ወሐዲሳትን፣ የሊቃውንት መጽሐፍትና ቅኔን በሚገባ እንዳጠናቀቁ «ዜና ሕይዎቱ ለብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ሊቀ ጳጳስ» በሚል ርዕስ ክቡር ሊቀ ማዕምራን  አበባው ይግዛው በ1994 ዓ.ም አዘጋጅተው ባሳተሙት ባለሦስት መቶ ገጽ መጽሐፍ በስፋት አስተምረውናል።  ክቡር ሊቀ ማዕምራን አበባው ይግዛው በሚኒስተር ማዕረግ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክሕነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ለሰባት ዓመት ያስተዳደሩና የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደር በዘመናዊ መልኩ ያቀኑ ማዕከላዊ ሕግጋቱን ቃለ አዋዲን በተግባር የተረጎሙና በሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ አስተዳደር ላይ ይበልጥ መሠረት የጣሉና የታወቁት ሊቅ የመምህ ጌጡ የኋላእሸት ደቀ መዝሙር ዕውቅ የቅኔ ባለሙያና የቤተ ክርስቲያንኗ ልጅ ነበሩ።

ብፁዕነታቸው በኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የአበው መነኮሳት ታሪክ መንፈሳዊዩን አምልኮታዊ ታምህርት ከዘማናዊ የነገረ መለኮዊ  ቅኝት ጋር በማዋሐድ በግሪክ ሀገር የመጀመሪያውን የነገረ መኮት ትምህርት የድግሪ ተመራቂ ኢትዮጵያዊ መነኩሴ ናቸው።ሁሉንም ደርጃ በደረጃ ከግብረ ዲቅና፣ ምንኩስና፣ቁምስና እስከ ሊቀ ጵጵስና ድረስ በሁሉም የአገልግሎት መስክ ከደብር አስተዳዳሪ ሊቀ ሥልጣናት እስከ መምሪያ ኃላፊነት፤ በመንፈሳዊ ኮሌጆች ከመምህርነት እስከ ዲንነት አገልግለዋል።

በቀድሞው የቅድሥት ሥላሴ ከፍተኛ ትምህርት ቤት የአሁኑ ቅድሥት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በመምህርነት በነገረ መለኮት ዘመናዊ ትምህርት አቡነ  ጳውሎስን፣ እነ ሊቀ ማዕምራን አበባው ይግዛውን፣ እነ አቡነ ጤሞቴዎስን፣ እነ አቡነ ማትያስን ፣ እነ አቡነ ዜናማርቆስን  የመሳሰሉት አባቶች ሁሉ አስተምረዋል። አቢያተ ክርስቲያናት ከመንፈሳዊ ትምህርት በተጨማሪ በግብረ-ገብነት የተገነባ ዘመናዊ ትምህርት ቤት በተጓዳኝ እንዲከፈቱ በማድረግ የመጀመሪያውን የቅድስ ሥላሴ ትምህርት ቤት ከፍተው ያስተማሩ ሲሆን ትምህርት ቤቱ እስከ ዛሬ ድረስ በጥሩ ውጤት ጥሩ ደረጃ የደረሱ ዜጎችን በማፍራት የታወቀ ቅዳሚነት ያለው የቤተ ክርስቲያናቸን የትምህርት ተቋም ነው።ከዚህ ልምድ በመነሳት ዛሬ በተለይም በአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማቱ ትምህርት ቤት በማቋቋም ወጣቱ ትውልድ ዘመናዊውን ከመንፈሳዊ ትምህርት ጋር አዋሕዶ በግብረ ገብነት እንዲያድግ እምነቱን እዲያጸና ቤተ ክርቲያኑን እንዲጠብቅ ለሚደረገው ታላቅ እንቅስቃሴ ሁሉ የመጀመሪያው ፈር ቀዳጅ ብፁዕ አቡነ መልከጸዴቅ በግንባር ቀደም ተጠቃሽ አርአያ ናቸው።

በሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ከፍተኛ ኮሌጅ የኮሌጁ ዲን ከመሆን በተጨማሪ እንደ አንድ መምህር ክፍለ ጊዜ ወስደው ነገረ መለኮት በማስተማር እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ ብቃት ያላቸው ደቀ መዛሙርትን አሰልጥነው እስከ ሊቀ ጵጵስና የደረሱ በሕይዎት ያሉና የሌሎም በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚኖሩ ይገኙበታል።

ብዙ አርቶዶክሳዊ ተዋህዶ ሃይማኖት የማስተምሪያ መጽሐፍትን ጽፈው አሳትመዋል። ጥንታዊ የግዕዝ መጽሐፍትን ለምዕመናን በሚገባ መልኩ ወደ አማረኛ አስተርጉመው በማሳተም ደረጃ የመጀመሪያው ድርሻ የሚይዙ ትጉህ አባት ናቸው። በቁም ጽሑፉ ረቂቅነት በምልክቱ ጥራት በብራናው በድጉሰቱ ብቃት ብልጫ ያላቸውን የቅዳሴ፣ ምዕራፍ፣ዚቅ፣ ዛማሬ መዋስዕት፣ ፆመ ድጓና ድጓዎችን እየፈለጉ በዘመናዊ መልኩ እንዲታተም በማድረግ መጽሐፍቱን በዐት አጽንተው፣ ወንበር ዘርግተው ጉባዔ አስፍተው ለሚያስተምሩ የአብነት መምህራንና ደቀመዛሙርት እንዲዳረስ ያደረጉ የመጀመሪያው ፋናወጊ አባት ናቸው። የመጀሪያውን የሰንበት ትምህርት ቤት «የወጣቶች ማኅበር» በሚል በመንበረ ጽባዖት ቅድሥት ስላሴ ካቴድራል መሥርተዋል። የሰንበት ትምህርት ቤት መሥራች እሳቸው ሲሆኑ በኋላም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ፓትርያርክ ፈቃድ በጠቅላይ ቤተ ክህነት በማዕከል የሰንበት ትምህርት ቤት ማደራጃ መምሪያ ተብሎ እንዲዋቀር ተደረገ።

«ድምፀ ተዋህዶ» በሚል የመጀመሪያውን የሬዴዎ ስብከተ ወንጌል ስርጭት አቋቁመው የተመረጡ ሊቃውንት እንዲያስተምሩ በማድረግ የሬድዎ መርሐ ግብሩን በመምራትና በማስተማር አገልግለዋል። ዛሬ እስከ ቴሊብዥን ስርጭት የደረሰው ብፁዕነታቸው አስቀድመው በሬዲዎ ደረጃ የተለሙት የስብከተ ወንጌል ስርጭት ዘዴ ነው። በመላው የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በተክሊል ጋብቻ ሥርዓት የሚደርሰው ጽሎት መጽሐፈ ተክሊል ከልዮ ልዮ ኦርቶዶክሳዊ የሃይማንኖት ነባር መጽሐፍት  አውጣተው በመቀመር አስጠርዘው ያሳተሙ ናቸው። ዛሬ በሁሉም አቢያተ ክርስቲያናት ሥርዓት ይህ የጸሎት መጽሐፍ ሳይደገምለት ጋብቻ የሚፈጽም ካህን ወይም ምዕመን የለም።

ከታላልቁ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አስተዳዳሪነት በተጨማሪ በንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘውዳዊ ፓርላመንታዊ መንግሥት ውስጥ በሃይማኖቶች ዴክተርነት እስከ ዘውድ አማካሪነት ድረስ መጠነሰፊ አገልግሎት ሰጥተዋል። የቀዳማዊ ንጉሰነገሥት በጣም ቀራቢ ሰው ነበሩ። የዘውድ አማካሪ ናቸው በሚል  በደርግ ዘመን ለሰባት ዓመታት ታስረዋል። በእስር ቤት ዘመናቸው ለእስረኞች የጸሎትና የመንፈሳዊ ትምህርት መርሐ ግብር በማውጣት እስረኞች በሚያገኙ መጠነኛ የመገናኛ ጊዜ ውስጥ በጸሎት ተግተው ፈጣሪያቸውን እንዲያስቡ ከማድረጋቸውም በላይ በእስር ላይ እንዳሉ ብዙ መንፈሳዊ መጽሐፍትን ጽፈው አሳትመዋል።

ዛሬ በአዲስ አበባ  በአራት ኪሎና በፒያሳ አካባቢ ንብረትነታቸው የቤተ ክህነት የሆኑ እድሜ ጠገብ ሕንጻዎች በደርግ ዘመን ተወርሰዉ የቆዩ ሲሆን በንጉሠ ነገሥታዊ መንግሥት ወቅት በግንባታ ሥራ ላይ የብፁዕ አቡነ መልከጼዲቅ  ቀጥተኛና ከፍተኛ ተሳትፎ  ውጤቶች ናቸው። በተሾሙባቸው የአብያተ ክርስቲያናት እና ኮሌጆች ማስተዳደር መምራትና ማስተማር ብቻ ሳይሆን በግቢው ውስጥ ያሉትን  ክፍት ቦታዎች ሁሉ ቆፍሮ በማስቆፈር የደን ልማት ሥራዎችን በትጋት አከናውነዋል። በተለይም በመንበረ ጸባዖት ቅድሥት ሥልሴ ካቴድራል በግቢው ውስጥ የሚታዩት ልዩ ልዩ አጸዶች /ዛፎች በሙሉ የተተከሉት በርሳቸው ሲሆን፤ ጥፋት ያጠፋ አገልጋይ ካህን ወይም ሠራተኛ ሲገኝ ከጥፋቱ እንዲታረም አትክልት በመትከል በመኮትኮትና ውሃ በማጠጣት ሥራ ይቀጡት እንደነበር በወቅቱ በቦታው ላይ የነበሩ አበው ሊቃውንት ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።

መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በንጉሡ ነገሥቱ ጊዜ ልክ እንዳሁኑ የንግሊዝ ዘውዳዊ ፓርላመንታዊ መንግሥት ሁሉ ስብሰባው  በጽሎት የሚከፈትበት፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ዓመታዊ ሁለቱን የጥቅምትና የግንቦት ወራት ጉባዔያትን በጸሎት ከፍቶ በጸሎት የሚዘጋበት ሊቃነ ጳጳሳት ወፓትርያርክ የሚሾሙበት፣ የተከበሩ የወጪ መሪዎችና አንባሳደሮች በእንግድነት የሚታደሙበት የንጉሠ ነገሥቱ ልዩ ቦታ እንደመሆኑ መጠን፤ ማንኛውም መርሐ ግብር ይመራ የነበረው በብፁዕ አቡነ መልከጼዲቅ ዋና ኃላፊነት ሲሆን፤ በግንባር በአገልግሎት የሚሰጡት መነኮሳት በቁማናቸውና በዕውቀታቸው  ዓይነ ግቡዕ የሆኑት የእተመረጡ እንደ መሆኑ መጠን የዛሬው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የቀድሞ ስማቸው አባ ዘሊባኖስ ፋንታ/ቆምስ/ እንዲሁም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የቀድሞ ስማቸው አባ ኃይለማርያም/ቆሞስ/፣ብፁዕ አቡነ ዜናማርቆስ … ሌሎቹም በካቴድራሉ ውስጥ ቀዳሽ ሆነው በሊቀ ሥልጣናት አባ ሀብተማርያም ወርቅነህ ታላቁ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ አስተዳደርና አመራር ሥር  በታዛዥነት አገልግለዋል።

በሰበታ ጌተሰማኒ መካ ደናግል ገዳም በግርማዊት እቴጌ መነን አቅራቢነት የገዳሙ ሙሉ ኃላፊ ሆነው ተሹመው የግዳሙን ሥራዓትና ሕግ በማስከበር ቦታውንም ገዳማዊ መንፈሳዊ ሕይወት እንዲታይበት በማድረግ የልማት ሥራዎች ንዲስፋፉ በግቢው ውስጥ ዕጽዋትን በማስተከል ጭምር ሰፊ አገልግሎት አበርክተዋል። በመንበረ ጸባዕት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የዝጋጃ ምንጣፎች፣ የልብሰ ተክህኖ ስፌት፣ የሙካሽና የጥልፍ ሥራ ዕደጥበባት እንዲቋቋም በማደርግ ቤተ ክርስቲያን፣ ካህናትና ምዕመናን የሙያው ባለቤቶች የምርቱ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ አድርገዋል።

በወቅቱ ከንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በማስፈቀድ ለማኅበረ ስላሴ እና ለዋልድባ የአንድነት ገዳማት መናንያን አቡጀዲድ ጣቃ ልብስ በማከፋፈል በጊዜው በነበረው ደረጃ መናንያንን  የነበረባቸውን የአልባሳት ችግር ለማቃለል ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ ይህን ታሪክ የሚዘክሩት መምህር ገብረማርያም ተስፋሥላሴ /ቆሞስ/ የአድዋ ተወላጅ ሲሆኑ የታላቁ ማኅበረ ሥላሴ ገዳም አበእምኔት የነበሩ የታሪክ ምስክርነታቸውን ደጋግመው ሲጠቅሱትና ሲያስታውሱ የሰሙ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች ያረጋግጣሉ። መምህር ገብረማርያም ተስፋሥላሴ እጅግ ሲበዛ ገዳማዊና ብልህ አስተዳደር አዋቂ ሰው ሲሆኑ ማኅበረ ሥልሴ ገዳምን በመምህርነት የመሩ፣ የታልቁ አቡነ ዩሴፍ እንደራሴና የጅማ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ነበሩ፣ ሞጆ ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያንን ያሠሩ፣አዲስ አበባ ጎፋ ቤዛ ብዙኃን ኪዳነ ምህረትን እንዲሁም አራት ኪሎ የመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ትምህርት ቤትን  ሕንጻ ያሳነጹ ታላቅ አባት ሲሆኑ እድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ በአዲስ አበባ ከተማ የነበራቸውን ማረፉያ ቤትና ንብረት በሙሉ ለዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም በማውረስ በገዳሙ ውስጥ ቀብራቸው የተፈጸመ ታላቅ አባት ነበሩ።

ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ከጀርመን ክርስቲይናዊ ተራድዖ  ድርጅት ጋር በመነጋገር በጎጃም፣ ጎንደር፣ በደብረታቦር፣ በባሌ፣ በአርሲ እናት-አባት የሞቱባቸው፣ በድህነት ምክንያት ትምህርት ቤት መሄድ ያልቻሉ ተማርዎች በአዳሪነት የሚማሩበትን ትምህርት ቤት በመክፈት በዕውቀት የተራቀቁ ለከፍተኛ ማዕረግ የበቁ ዜጎች እንዲወጡበት ያደረጉ ሲሆን፤ ዛሬ በደብረታቦር መሎ የሚገኘው ይኽው አዳሪ ትምህርት ቤት በወያኔ ፈርሶ የጦር ካንፕ ሆኖ ይገኛል።በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ዘመነ ፕትርክና ለኤጴስ ቆጶስነት ታጭተው፤ «እኔ ገና ብዙ መሥራት የሚጠበቅብኝ ስሆን በዚህ እድሜየ ይህን ከፍተኛ ማዕረግ ከተረከብኩ እንደልብ ተዘዋውሬ ቤተ ክርስቲያንን እንዳላገለግል ይከለክለኛል» በማለት ለንጉሰ ነገሥቱ አመልክተው እጩነታችውን ሳይቀበሉት ቆይተዋል።

ብፁዕነታቸው አማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ ግዕዝ፣ እብራይስጥ፣ ግሪክ፣ አረብኛ፣ የእንግሊዘኛ ቋንቋዎችን አጣምረው በማወቃቸው ቤተ ክርስቲያኗን ውክለው በልዮ ልዩ የዓለም አቀፍ ጉባዔዎች በኃላፊነት ተሳተፊ በመሆን ከፍተኛ አገልግሎት አበርክተዋል።  በመንብረ ጽባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የሀገራችን የክብር እንግዶችን ተቀብለው በማስተናገድና ታታላቅ መርሐ ግብሮችንም በኃላፊነት በመምራት የኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ለዓለም ኅብረተሰብ በማስተዋወቅ ደረጃ ከፍተኛውን አገልግሎት ያበረከቱ በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ሲሆን ከክብር እንግዶቻቸው መካከል የእንግሊዝ  ንግሥትና ንጉሳዊያን ቤተሰብ በዋናነት ተጠቃሾች ናቸው።

በአዲስ አበባ አራዳ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዎርጊስ ቤተ ክርስቲያን ግቢ ውስጥ የኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ትምህርተ አበነፍስ በሚል ርዕስ ለሦስት ወራት የሚቆይ ስልጠና በመስጠት አብዛኛው የአዲስ አበባ ካህናትና ዲያቆናት ዛሬ እድሚያቸው ከ45 እስከ 70 የሚደርሱት ሁሉ የዚህ ኮርስ ተጠቃሚ በመሆን ሃማኖታቸውን በብቃት ባለው መልኩ ተረድተው ስልጡን በሆነ መልኩ ለማስተማር ለማገልገል ንስሐ ልጆቻቸውን በአግባቡ ለመጠበቅ የሚያስችል ዕውቀት እንዲያገኙ በማድረግ የምስክር ወረቀት ማስረጃ እየሰጡ በማስመረቅ ለቤተ ክርስቲያን የሚበጅ የማዕዘን ድጋይ አኑረዋል ።

አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በቤተ ክርስቲያንዋ አስተዳደር ውስጥ ጣልቃ ገብቶ ቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስን ከመንበረ ክብራቸው በጠበንጃ ኃይል ገፍቶ አስፈራርቶ  ሲያሳድዳቸው፤ «ሕገ ቤተ ክርስቲያን ተጣሰ ሥራዓት አልበኝነት ነገሠ» በሚል ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ በቅርብ ሆኖ በመርዳት ኃላፊነት ውስደው በስደት የሚገኘውን ቅዱስ ሲኖዶስ አቋቁመው ለአሜካን ኮንግረስ በማሳወቅ፤ በሕገ ቤተ ክርስቲያን የሚደርሰውን ሃይማኖታዊ የቀኖና ሕግጋት መጣስና በሀገሪቱ ላይ በሁለንተናዊ መልኩ የደረሰውን ጥፋትና በደል በትጋት ሲያጋልጡ ቆይተዋል፤ በተጓዳኝም በአሜሪካን ሀገር በሁሉም ግዛቶች የኢ/ኦ/ተ አቢያተ ክርስቲያናት እየተከፈቱ መንፈሳዊ አገልግልቱ እንዲከናወን ስብከተ ወንጌል ስርጭት እንዲጠናከር መጠነ ሰፊ አገልግሎት በማበርከት ላይ ናቸው።

ብፁዕነታቸው  አስቀድመው በ1984 ዓ.ም በመለስ ዜናዊ የሚመራው የይስሙላ «የሽግግር  መንግሥት»  ሀገሪቱን ለመምራት ሙሉ ኃላፊነት ሳይኖረው ያለኢትዮጵያ ሕዝበ-ውሳኔ ኤርትራን ጠቅላይ ግዛት ሲያስገነጥል እንደማይችል ተቃውሟቸውን ለዓለም ህብረተሰብ አሰምተዋል። የወያኔ መንግሥት ታሪካዊ ማንነትን፣ በህላዊ ውበትን፣ ማኅብራዊ የኑሮ ትስስሮችን፣ የአንድነት ዕሴቶችን በማናጋት ብሎም በማጥፋት በሀገራችን ኢትዮጵያና በኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሚደርሰውን በደል ሁሉ ያለመቋረጥ አጋልጠዋል። በሀገራችን የሚደርሰውን የጎሳ መከፋፈል ስልጡን ያልሆነ ፓለቲካ ሥሪት አስመልክቶ ያላቸውን ተቃውሞ የተሰማቸውን ሀዘን ለመጀመሪያ ጊዜ ለአሚሪካን ኮንግረስ በተደጋጋሚ አሳውቀዋል።በልዩ ልዩ ሕዛባዊ ሰልፎችና የወይይት መደረኮች እየተገኙ አባታዊ ገንቢ ሐሳቦችን ሲለግሱና ምክር ሲሰጡ የቆዩ መንፈሳዊ አባት አርበኛ ናቸው ።

ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ምንም እንኳን የአረጋዊነት እድሜያቸው እየተጫናቸው ቢመጣም አሁንም በ94 ዓመት እድሜያቸው በአቋማቸው እንደጸኑ በመንፈሳዊ አገልጎታቸው እንደበሬ እንደተጠመዱ በትጋት አሜሪካን ሀገር በካሊፎርንያ ግዛት ይገኛሉ። እንደሚታወቀው ሁሉ በኢትዮጵያ  ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መንግሥት በተለወጠ ቁጥር ቀኖና ቤተ ክርስቲያን እየተጣሰ ርዕሰ መንበረ ፓትርያርኩ በግፍ እየተገደለ አለዚያም በሰቀቀን ተጎሳቅሎ እንዲሞትና እንዲሰድ ሲደረግ ግማሽ ምዕት ዓመት እየተቆጠረ ነው። ይህ ድርጊት ለቤተ ክርስቲያንኗ ሉአላዊነት እንደ ነበዩ ሙሴ «እንቢ» የሚል ተተኪ እንደ አቡነ መልከጼዲቅ ያለ ሀቀኛና ቆራጥ መንፈሳዊ አባት እስካልተገኘ ድረስ ቤተ ክርስቲያን  መከፋፈልና በቀጥታም ሆነ የእጅ አዙር ተገዥነቷ ያአቋረጥም።

ዛሬ የብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የወያኔን በቤተ ክርስቲያን ጣልቃ ገብነት በመቃውም እንቢ ማለታቸው ግንዛቤ በጎደላቸው በጥቂት የስም ቀበኛ አግድም አደጎች ንዑሳን ዘንድ ተራ ዘለፋ ቢደርስባቸውም፤ ነገ ከነገ ወድያ እንደ ወያኔ ያለ የዘመናችን ፈሮናዊ አገዛዝ ሲነሳ የባቶች እንቢ ባይነት የቤተ ክርስቲያንኗን ልዕልና የሚያስጠብቅ የብረት አጥር ሆኖ የሚኖር ምሰሶና ማገር ነው። ቤተ ክርስቲያን  የታሪክ፣ የሀገር፣ የቀርስ፣ የአንድነትና የተዋህዶ ጠንካራ ኃይል ያላት መሆንዋን  በታሪክ ለመጀመሪ ጊዜ የተመዘገበበት ታላቅ አሻራ ነው።

አሁን የምናየው በወጭ ሀገር የተበተነው ዜጋ /ዲያስፓራ/ የሀገር ተቆርቛሪነት ስሜት የተጸነሰው እና መቅድሙ የታወጀው በብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ የመጀመሪያ ፈር ቀዳጅነት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ምን አልባትም ከዚህ በኃላ መንግሥት በተቀየረ ቁጥር ፓትርያርክን ማሳደድ መገደልና  የሀገራችን ኢትዮጵያ ጎልላት አንጸባራቂ ፈርጥና ጌጥ በሆነቸው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ በቤተ ክርስቲያን ላይ እንደፈለጉ መፈንጨት የማይቻል መሆኑ የታላቁ መለከጼዲቅ እና የሌሎችም ብፁዓን አባቶች  እንቢ ባይነት ትልቅ ትምህርት ሰጥቶ እያለፈ ይገኛል። ዛሬ ለቤተ ክርስቲያን ተቆርቋሪ መስለው እንደ አይጥ ከገቡበት ጉድጓድ ብቅብቅ የሚሉት ግብረበላ ማኅበራት እና «ገለልተኞች» የሚባሉት ሁሉ የብፁዕ ሊቀ ጳጳስ አቡነ መልከጼዴቅን መሠረት ያለው አቋም ተከትለው ቢጓዙ ኖሮ የቤተ ክርስቲያንኗ  የመከራ ዕዳ ደብዳቤ ሳይቀደድ ሃያ ስድስት ዓመት ባልተቆጠረ ነበር።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ለዝክረ ነገር ይሆነን ዘንድ ወደኃላ መለስ ብለን ስናስታውስ፤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ «እርምጃ እንዲወሰድባቸ» በወቅቱ የነበሩ አንዳንድ ሥልጣን ናፋቂ ሊቃነ ጳጳሳት ለደርግ የድጋፍ ፊርማ ባይሰጡ እንደ ቀድሞው እንደ ነቢዩ ሙሴ ሁሉም በአንድነት እንደ አሁኑ እንደ አቡነ መልከጼዲቅና ሌሎቹ ብፁዓን አባቶች እንቢ! ቢሉ ኖሮ ይህ የደርግ ጥፋት እንደገና በወያኔ ተደግሞ ፓትርያርኩም በግፍ ባልተሰደዱ ቤተ ክርስቲያንና በተከታዮቿ ላይ የዕዳ ደብዳቤ ቀንበር ተጭኖባት የፈሪሳዊያን «ቅዱሳን ንዑዳን» ዋሻ ሁና እንዲህ ባልተደፈረች ነበር።

ታላቁ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ለአለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በሃይማኖታቸው፣ በሀገራቸውና በህዝባቸው ላይ የሚደርሰውን ሰቆቃ በትጋትና በጥንካሬ የሞገቱ መንፈስዊ አርበኛ ሲሆኑ፤ በስደት በሚኖሩበት አሜሪካን ሀገር ካሊፎርንያ ግዛት፤ በመንፈሳዊ የረጅም ጊዜ አገልግሎታቸው ትጋታቸው በሰባዊ መብት ተማጋችነታቸው በአሜሪካን መንግሥት ዕውቅና/ የሪኮግኒሽን የምስክር ወረቅት አግኝተዋል። በስማቸውም የመልከጼዴቅ ቀን በሚል በካሎፎርኒያ ከተማ ታስቦ እንዲውል ተፈቅዷል። መልከጼዴቅ ጎዳና የሚባል መንገድም ተሰይሟል። አዎን!! ነብይ በሀገሩ አይከብርም በተሰደደበት ሀገር ግን እጅግ ይከብራልና በሀገራቸው ውስጥ ትላንት በተወለዱ አፈ-ጠቦች፣ ጨቅላዎችና ቁንጽል አስተሳሰብ ባላቸው ብዙ ወሃ የማናሳ ዝርው በሆነ ቃላት በድፍረት የተዘለፉ ሲሆን፤ ዘላን ዘላፊዎችን ማንነታቸውንም ሆነ ተግባራቸውን በስፋት ማጋለጥ ቢቻልም ይህን ለከትና ለዛ ያጣ ኢትዮጵያዊ ትህርምት የጎደለው አግድም አደግ የዘመናቸን «ቅዱሳን ንዑዳን» ዘለፋ በዚህ ወርቃማ ሕያው መዋዕለ ዘመን ታሪክ በስርዋጽነት ማስታወስ በእንቁ ማዕድን ላይ አመድ የመነስነስ፤ በተራራ ላይ ያለችውን መብራት በእንቅብ  ለመሸፈን የሚደረግ መፍጨርጨር የመሆን ያክል ዝቅ ያደርገናል በማለት በፈገግታ ንቀን አልፈነዋል። እግዚአብሔር ያከበረውን ከቶ ማን ዝቅ ያደርገዋል።

ብፁዕነታቸው በጥቅሉ በሰማንያ ስምንት የኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ያልተቋረጠ የአገልግሎት ዘመናቸው በሀገርም ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ለቤተ ክርስቲያንኗ የተጠናከረ መንፈሳዊ አገልግሎትና ስብከተወንጌል ስርጭት፣ ለዘመናዊ ማዕከላዊ አስተዳደር፣ ለልማትና ዕድገት የቤተ ክርስቲያንኗ ህልውና መጠበቅ የብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ዕቅድና ፕላን የተገባር እንቅስቃሴ ቁርጠኝነትና ጎልህ ተጨባጭ አስተዋጽዖ ያልታየበት የሥራ ድርሻ የለም ብሎ መናገር ወርቃማ መዋዕለ ዘመናቸውን፣እንቁ የሕይወት ታሪካቸውንና ቅን አገልግሎታቸውን ሊያጠቃልለው ከሚችል በስተቀር በወረቀት ዘርዝሮ ለመጨረስ አንድ ከፍተኛ ትምህርት  ተቛም ገብቶ ተምሮ የማጠናቀቅ ያክል እጅግ ሰፊና አድካሚ ነው።

የአካላቸው መጠን ክትት ያለ ሲሆን፣ እንደ ዛሬው አረጋዊነት ሳይጫናቸው ደልደል ያለ ተከሻ ያላቸው፣ ልቅም ያለ ጉልህና ጥርት ያለ ብሩህ ገጽ፣ የዝባድ አለሎ የመሠለ ዓይን ያላቸው፤ ግርማ ምገስን የተላበሱ ከረጃጅሞች መካከል ጎልተውና ደምቀው ከሩቅ የሚታዮ መንፈሳዊነትና ስብዕናን የተሞሉ፤ ዋዛ ፈዛዛ ሳቅ ስላቅ የማያበዙ፣ በየትኛውም አጋጣሚ ሁሉ በክፍለ ጊዜ የመጠቀም ስልጡን ባህል ያዳበሩ፣ በቁም ነገር ብቻ የተጠመዱ ብልህ እና አስተዋይ፣ ቁጥብ፣ ጥንቁቅና ነገ-ሊፈጠር በሚችል ጉዳይ ላይ አስቀድመው የሚዘጋጁ እና ለጠላት የማይመቹ፤ አሉባልታን ተራ ወሬን እጅግ የሚንቁና የሚጸየፉ፣ ንቁና ጠንካራ መንፈሳዊነት ከልበ ሙሉነት ጋር በፀጋ የተሰጣቸው፤ አርአያ ተውህቦ ክህነት የተላበሱ የኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ምትክ የማይገኝላቸው እንቁ አባት  ሲሆኑ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ሊቀ ጳጳስን በዕድሜ በበረከት ጠብቆ ያቆየልን የባቶቻችን የአብርሃም የይሕሣቅ አምላክ ቅድመ ዓለም የነበረ ዓለምንም አሳልፎ የሚኖር አብ የቅድስት ድንግል ማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ወልድ  ወመንፈስ ቅዱስ ክብር መስጋና ለእሱ  ይሁን ለዘለዓለሙ አሜን።

 

ሊቃውንቱ ሁሉ በግልጽ እንደሚያውቀው፤

በቅዳሴ ጸሎት የሚባርከው፤

በምዕራፍ  በድጓው በቅኔ ዝማሜ የሚሰበከው፤

በቅዱሳት መጻሕፍት  እንደተዘገበው፤

ካህን  መልከጼዴቅ  ኢትዮጵያዊ ነው።

በዘመነ አብርሃም መሰዋዕት የሰዋው፤

ብሉያት ሐዲሳት ወንጌል የሰበከው፤

ትላንት የነበረ ዛሬም የአየነው፤

አባ  መልከጼዴቅ  ካህኑ ለዓለም ነው።

ሀብተማርያም  ተብሎ ገና በልጅነት ሁሉንም ያወቀ፤

በቃ ተከተተ እምነት ቁምነገሩ አለቀ ደቀቀ፤

ሕግና ሥርዓቱ እንዳለ ጸደቀ፤

በመልከጼዲቅ ስም እንደተረቀቀ።

ከቀደሙት ሰዎች ከአሮን ከዳዊት፤

ፀጋ መንፈስ ቅዱስ ውሉደ ክህነት፤

መዓዛ  ቅዳሴሁ ጥዑመ ልሳናት፤

መስዋዕተ እግዚአብሔር ጽዋ በረከት፤

ለመልከጼዴቅ ነው የሠመረለት።

 

እንዲህ እንደዋዛ እንደቀላል ነገር፤

ቀለሙ ሲደፋ ብዕሩም ሲሰበር፤

መልከጼዴቅ ባይደክም ነገረ-መለኮት ይጽፍበት ነበር።

እጥር ምጥን ያለ ክትት ያለ አሞቱ፤

ትጉህ ሐዋርያ፤ ቀድሶ የሚያቆርብ በቤተ ክህነቱ፤

የፓርላማው ዳኛ በቤተ መንግሥቱ፤

አባ መልከጼዴቅ ምልዑዕ በኩልየ ሊቀ ሥልጣናቱ።

 

ለዋዛ ፈዛዛ ግዜ የሌለው ሰው፤

የነገን ለዛሬ ቀድሞ የሚያስበው፤

ፍትሐ ነገሥት ጠቅሶ የሚከራከረው፤

«ፓትርያርክ እያለ ፓትርያርክ ምንደን ነው?

አባ መልከጼዲቅ  መሠረት የያዘ  በአቋሙ የጸናው።

ሰዋሰው ብርሃን ነገረ መለኮት የቀጸላችሁ፤

በቅድስት ሥላሴ ለአስተዳደር ሥራ የሰለጠናችሁ፤

በገነተ ጽጌ በምስጢረ ክህነትን የተራቀቃችሁ፤

በንጉሡ ዙፋን ለዳኝነት ተግባር የተቀመጣችሁ፤

በቃ ተከተተ  አባ መልከጼዴቅ  ታላቅ መምህራችሁ።

በሕጻንነቱ  ለምናኔ ወጥቶ ገዳም የገባው፤

ታናሽ ታላቅ አያውቅ ከዘመድ የራቀው፤

ታሪኩ በሙሉ እንደ አጥቢያ ከዋክብት  የሚያንጽባርቀው፤

ትናንት ሀብተማርያም፤ ዛሬ መልከጼዴቅ  ካህኑ ለዓለም ነው።

ሁሉም ሐዋርያት መቸ ተቀበሩ በተወለዱበት፤

ስምና ተግባሩ ህያው ነው የማይሞት፤

በአቋሙ እንደጸና ጉዞውን ቀጠለ በተሰማራበት፤

ሊቁ  መለከጼዴቅ  የተዋህዶ  መብራት።

የቅዱስ መርቆሬዎስ  ፈረሱ ቦራው፤

የዜናማርቆስ  ባህታዊ  ቡራኬው፤

የኤልያስ መሰጦ ደመና ሰረገላው፤

የጎርጎሬዎስ ጥዑመ ልሳናት መዐዛ ቅዳሴው፤

ሊቀ ሥልጣናት መለከጼዴቅ  ካህን  መሰዋዕተ አበው።

ጎንደር አባ ጃሌ  የአባታጠቅ ሰፍር፤

ማማው ደብረታቦር ያለቃ ተክሌ አገር፤

ሀገሬ ራስ ጋይንት አፍ አውጣ ተናገር፤

መሪ አስተዳዳሪ ብሉይን ከሀዲስ የሚያመሳጥር፤

መልከጼዲቅ አባታች የተዋሕዶ መምህር