June 2, 2017 –

ሕወሃት (ወያኔ) ኢትዮጲያን ከተቆጣጠርበት ከ 1983 (እንደ አውርፓውያን አቆጣጠር 1991) ጀምሮ ልዩ በሆነው ያገዛዝ ዘዴው ተጠቅሞ እየፈለጠና እየቆረጠ ለ26 አመታት ዘልቋል። ይህ የጥቂቶች ጅምር የሆነው መሰሪ ድርጅት ከ 1967 ጀምሮ፤ በዘረኝንት መንፈስ ተጠምቆ፣ በጸረአማራ ጥላቻና ቅናት ስሜት ተወልዶ፣ በኤርትራ ገንጣይ ወንድሞቹ ታግዞ  ጎርመሰና በብልጣብልጥ መሪዎቹ እየተመራ ላልገመተው ነገር ግን ለሚያልመው ድል በቃ።

የደርግ መንግስት ወታደራዊ አገዛዝ ያስመረረው ህዝብና  ተፈጥሮ ና ሰውሰራሽ የረሃብ አደጋ ያጎሳቀለው አገር  ተጨምሮ ለወያኔ ድል ማደርግ መንገዱን አመቻቸለት። በ1977 አመተ ምህረት በትግራይና ሰሜን ኢትዮጵያ በረሃብ ለሚረግፉ ወገኖች ህይወት ማዳኛ  ከነ ቦብ ጌልዶፍ በልመና የተገኘውና ለወያኔ የተሰጠውን 100 ሚሊዮን ፓወንድ ( በዛሬ ዘመን እጅግ ትልቅ ገንዝብ) ለጦር መሳሪያና የወያኔን ደርጅት ማስፋፍያነት ተጠቀሞበት ከተራ ሽፍታ ጦር መሆን ተለወጦ፤ በአካባቢው ባሉ አገራት ሱዳን፣ሶማሌና የአረብ አገራት እርዳታ ቦኋላም በአሜሪካ ከፍተኛ እርዳታ ተጨምሮ ብዙ አስርት አምታት ታግሎ ሻቢያ እንኳን ያላገኘውን ድል ወያኔ ያለ ብዙ ድካምና እንቅፋት አዲስ አበባን ለመቆጣጠር ቻለ።

የወያኔ መሪዎች መሰሪ፣ ነገር ግን ብልህነት የሞላቸው ስለነበሩ ያልጠበቁትን ትልቅ ድል በቀላሉ ላልመነጠቅ ትልቅ ስራ ሰርተዋል። ምናልባትም ከደርግ ወይም ሻቢያ በተለየ  የአገዛዝ ዘዴያቸውን በደንብ ያጠኑ ሁነው ተገኘተዋል። በዚህም መሰረት ጥቂት ሁነው 6% (የትግራይ ህዝብን ሁሉ አይወክሉም ነግር ግን ደጀኔ ነው ብለው ያምናሉ) አብዛኛውን  94% ኢትዮጲያውያንን ለመግዛት የሚያስችል ስልት መንደፍ ነበርባቸው። ተንኮልኞቹ መሪዎቻቸው ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጲያን ስትወር የተጠቀመችበትን ‘በጎሳና በሃይማኖት ለያይተህ ግዛ’ የሚለውን መመርያ ከልብ በማመን ከስታሊንና ማኦ  ( ኮሚኒስቶች ነን ባዮችመጽሃፍት ስለ ብሄር ብሄረሰቦች የተተነተነውን በወል እንኳን ሳይሆን ቀድተው፤ ላገዛዛቸው እንዲያመቻቸው በ’ከፋፍልህ ግዛው’ ዘዴ ጥቂቶቹ ብዙሃኑን እንደልባቸው ለ26 አመታት በቀላሉ እንዲገዙ አስችሏቸውል።

ወያኔ እንደ እስስት ቆዳ በሚለዋወጥ ባህሪው ፈራንጆቹንም አደናግሮ፤ የነሱንም ጥቅም አስከባሪ ሆኖ፣  የነሱን እሺታ ከሚፈልጉ ድርጅቶች ጨምሮ  በብዙ  ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ና እርዳታ የፈጠርው መንግስታዊ እንዲሁም ወታደሪዊ አቅም ገንብቶአል። መሪዎቹ በሚያስደነቅ ሁኔታ ፈረንጆቹን ሲያታልሉ፤ በፈረንጅ አፍ (እንግሊዘኛ) ስለዲሞክራሲ ግንባታና የእድገት ሲለፍፉና ሲያሳምኗቸው፤ በዚያኑ ያህል  ደሞ  ለኛ ባገራቸን በሚገባን ቋንቋ (አማርኛ) ሲያስፈራሩና ሲቆጡን ኖረዋል። ይሄ ጸሃፊ የሚያስታወሰውን እዚህ ለምስክረነት መስጠት ይፈልጋል።

ታዋቂውን የእንግሊዝ ጋዜጠኛ ጆናታን ዲንቢልቢ ከቀዶምው የወያኔ መሪ መልስ ዜናው ጋ ተገናኛቶ  አቶ መልስ እንዴት አድርጎ “እንደ ሸወደው” ማወቅ ያስደንቃል። አቶ መለስ “የኔ ልፋትና ትግል ውጤት የሚለካውና የምርካብት እኔን እራሴን በዘርጋሁት ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ስሸነፍና ስልጣን ስለቅ ነው” ብሎት ጆናታን ዲቢልቢልን ሲያሰድንቀውና  “እንደዚ ያለ ታላቅ አፍሪካዊ መሪ አይቼ ሰምቼም አለወቅም” ብሎ ለአቶ መለስና ደርጅቱ ትልቅ ከበሬታ ሰጥቶ ነበር። ሁላችንም እንድምናወቀው ግን  1997 ምርጫ ና የአቶ መለስ እርምጃ እንዴት እንደነበር የምናወቀው ነው። ፈረንጆቹን የማታለል ዘዴ ወያኔ ተክኖበታል።  ምርጫ በየግዜው ማድርግ፣ ተከሳሽን ወደ “ነጻ ፍርድ ቤት” መወስድ፣ አስምሳይ ተቃዋሚ ጋዜጦችን ወይም ሬድዮኖችን መፈቀድ  የመሳስሉት ፈርንጆችን ያስታል። የውሽት ምርጫ መሆኑን፤ ፈራጁም ዳኛ የወያኔን ፍርድ አስፍጻሚ መሆኑን፣  ሚዲያውም በወያኔ መዳፍ ስር መውደቁን ግን አያወቁም።

ወደ ወያኔ አገዛዝ ዘዴ ስንመለስ በጎሳና በክልል ኢትዮጲያውያንን አጥሮ፣ አንዱን ባንዱ ላይ በጠላትነት አስተሳስሮ፣ ታላላቆቹን ነገዶችና ሃይማኖቶች  አተራምሶ፡  ራሱ ወያኔ ዳኛ፣ ፈራጅ፣ ጠብቃ፣ ፖሊስ ሆኖ ብዙዎችን አታሎ አሳምኖ አሁን ድርስ በሀይለኛነት ይገዛናል።

ወያኔ ትንሽ የለውጥ ምጥ በመጣበት ቁጥሩ ራሱን ቀለም እየቀባና እያሰምሰለ ከርሞል። ከማርክሲስት ሌኒንስት ርዮት አለም  ወደ አብዮታዊ ዲሞክራሳዊ መዝሙር፤ ከዚያም በቦናፓርቲዝም ዘፈን ወደ ልማታዊ መንግስትነት እያሰመሰለ ፈረንጆቹንም፣ የኛዎቹን የውኋችን እያታለለ ቆይቷል። መሰረታዊ ባህሪይው (ለአማራ ብሄር ያለው ጥላቻና ‘አከርካሪውን’ መስበር ድርጊት፣ የትግራይ በኢኮኖሚ፣ ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ የበላይነትን ማስቀጠል፤ ወያኔ፡ ሃገር እስከገዛ ድርስ በኢትዮጲያ ስር ለሞቆየት፤ ነገር ግን ወያኔ የማይግዛ ከሆነ የትግራይ ሪፐፕሊክን ከኢትዮጲያ ሀብት በተዘረፈ ንብረትና መሬት መምስርት) ግን የማይለውጥ የወያኔ ቃል ኪዳን ነው።

ወያኔ በፕላን ባቀደው መሰረት የሀገሪቷን ኢኮኖሚ በትልቅ እጅ በመንግስትነትና በኤፈርት በሚባለው ዘራፊ ‘የልማት” ደርጅቱ ሲቆጣጠርው (እባኮውን የቀድሞው ሚንስቴርዴታ የነበረውን የአቶ ኤርሚያስ ለገሰን “የመለስ ልቃቂት” በእወንተኛ ማስርጃ የተሞላ መጽሃፍ ያንብቡ)፤ በወታደራዊና በደህንነት  መድሩኩ በኩል ደግሞ ፡ ሃላፊነቱን ሙሉ በሙሉ (ከትንሽ ሌላ ጎሳ ተወላጅ፤ ታማኝ ሰዎች በቀር) ተቆጣጥሮታል።             በፖለቲካውም መድረክ የያንዳንዱን ሚኒስቴር መስሪያ ቤት አድርጋና ፈጣሪ ወያኔዎች ሲሆኑ ለስሙ ፊት ለፊት የሚቀመጡ የሌሎች ጎሳ ተወላጅ ታማኝ አገልጋዮችን አሰቀምጠዋል። ክልል ብለው በከለሉት የሚግኙት ትናንሽ መንግስታት ከወያኔ ፈቃድ ወጪ አንዲት ወሳኔ የማይወስኑ፤ ከ ዘፈን ውጪ ሌላ የማይፈቀድልቸው፣ የወያኔን ውስኔ የሚያስፈጽሙ ሁነው ተገኘተውል።

በሀገር ቤት የወያኔን ተንኮልና አጥፊ አገዛዝ የተረዱ ደፋር ኢትዮጲያወያን ወገኖች በግል ና በመደራጀት የሚያደርጉትን ትግል፡ ወያኔ በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ሲያጠፋ ይታያል። ለይስሙላ ያስቀመጠወን ህገመንግስት፡ መጀመርያ አፍርሽ የሆነው ራሱ ወያኔው ነው።  ደረቁ ደርግ አታድርግ፤ ካደርክ ግን እቀጣሃለው” የሚለወን ፊት ለፊት የሚታይ አሰፈሪ ህግ፤ ዘዴኛው ወያኔ ፈርንጆች ወዳጆቹን የሚያታልልበት ዘዴው        እንድ ልብህ አድርግ፡ ተፈቅዶልሃል፤ ግን ከኔ ቅጣት አታመልጥም” በሚለው ቀይሮ ተግብሮታል።

ጋዚጠኞችን፤ የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪዎችን፣ ሃገር ወዳድ ባለሞያዎችን፣ ሙሁራኖችንና የኪነ ጥበብ አዋቂዎችን እያሳደደ፤እያስፈራራ፤ ስም እያጠፋ፣እያሰረ፤ሲያስፈለግም እየገደለ አገዛዙን ቀጥሎአል። የውሽት ተቃዋሚ ድርጅት እየመሰርተ፤ ዲሞክራቲክ መድርክ ያለ እያስመሰለ፣ ሰላዮቹን እየገጠገጠ፡ ምርጫ ቦርዱን መደነሻ ቤት አድርጎታል።

ግፍና መከራ የበዛበትን ህዝብ ለለውጥ እንዳይነሳ ባስፈሪ የስለላ መዋቅሩ ጠላለፎ፡ ህዝቡ እንዲፈራራና እንዳይተማመን፣እንዳይነጋግር አድርጎት፤ በተለይ ገንዘብና ዳቦ ጥቅማ ጥቅም በሚወዱ ደካሞች  በወገኖቻቸው ላይ ሰላይና ጠቋሚ አደርጎ ቆልፎ ይዞታል። ለሰላሚው ትግል የተነሱ ወጣቶችን አስቀድሞ በማፈን፣ ከትምህርት፣ ከስራ በማባረር ካአገር እንዲሰደዱና ተስፋ እንዲቆርጡ የሚያስደርገ፤ ሰባዊነት የጎደለው ግርፋትና ስቃዩ ፤ ጨካኝነትና አውሬ ባህሪው ሌላው የአገዛዝ ስልቱ ነው።

ወያኔ የእግር ቁስል ሆነው  ስራውንና ክፋቱን  ለአለምና ለአገሬው ሰው የሚያጋልጡትን፤  የለውጥ ተስፋን  ሃገር ውስጥ ላለው ህዝብ የሚሰጡትን እንዚህን በውጭ ሀገር ያሉ ኢትዮጲያውያንን ለተወሰኑ አመታት እንዴት አድርጎ መቆጣጠር ተስኖት ሲበሽቅና ሲናደድ የኖረ ቢሆንም አሁን ግን በተለመደው የሽፈጥ ዘዴው፡ እሩቅ የሚደርስ የክፋት ተንኮሉን በውጭ ሀገራት ዘርገቶአለ። ከውስጡ አምልጠው የሚወጡ መርጃዎችና ስርአቱን ትተው ከሚመጡ የወያኔ መንግስት ሃላፊዎችና የመረጃ ሰራተኞች ብዙ ነገር ይሰማል። ይህን በውጭ ሃገር የሚደርገውን ወያኔዊ ትግል የሚያስፈጽሙ ሰራዊት ወያኔ  በብዙ አገራት አሰማርቷል። እነዚህም እንድሚከትሉት ናቸው።

  1. በኤምባሲ ና  ቆንስላዎች የሚመደቡ ወያኔውችና ከሌሎች ጎሳ የሚወለዱ ሆድ አደር ዜጎች። ተልኮአቸው የተቃዋሚ ግለስቦችን እና ድርጅቶችን ፣ በተለይም የብዙሀን መገናኛ (እንድ ኢሳት ያሉትን) መከታተልና መርጃና ማስረጃ መሰብሰብ። አብዝኛውን በተቀዋሚ አስተሳሰብ  ያለ ህዝብን  የመሬት ቦታ፣ የቤት፤ የቢዝንስ እንዲሁም ሌሎች ጥቅማጥቅምን የሚስገኝ አማላይ ፕሮፓጋንዳን መንዛት።

  2. በደህንነት ከፍሉ የተሰማሩ (ከሃገር እንዲወጡ ለስድተኝነት ጥያቄ የሚበጅ ማስርጃ በደህንነት ከፍሉ የተዘጋጀላቸው ) ባሉበት አገር በሃስት የስደተኛ ጥግኝነት ጥያቄ ያቀርቡና እስክ ዜግነት ድርስ የተቀበሉ የወያኔ ደጋፊዎችና የመረጃ ሰራተኞች። የነዚ ተልኮአቸው፡ በየተቀዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ተቃዋሚ ደጋፊ መስለው የፓርቲው አመርር ወስጥ በመግባት፤ ድርጅቱን እንዳይራመድ፤እርስ በርሱ እንዲጠላለፍ፣ አባላቱ እንዳይተማምኑ ማድረግ፣ ከሌሎች ድርጅቶች ጋ ህብረት እንዳይደርግ ማድርግ፤ የታወቁ የድርጅት መሪዎችን ስም ማጥፋት፤ እንዲሁም ከድርጅቱ የቃርሙትን ሁሉ ለ ወያኔ ደህንነት ማሳወቅ።

  3. ድምጽ አጥፈተው ሀገር ወዳድ  አትዮጲያዊ መስለው በሚዲያ ስራ በተለይ  በራድዮ፣ በቲቪ፣ በመሃበራዊ ሚዲዎች እንዲታወቁ የተደርጉና እምነት እንዲጣልባቸው ታዋቂ የተቃዋሚ አክቲቪስቶችንና መሪዎችን በሚዲያቸው የሚያቀርቡ፤ በህዝብ ዘንድ አመኔታ እንዲያግኙ የተደረጉ (እንዲይንቀላፉ የተደረጉ) ፤ የመረጃ ክፍሉ በሚሰጣቸው የሚስጥር ትዛዝ (ከተኙበት የሚነቁ) አሉ። የነዚህ ተልእኮ፡ ወያኔ የሚፈራቸውና በህዝብ ዘንድ ትልቅ ተጽኖ ፈጣሪ፣ ሀገር ወዳድ ሙሁሮችን፣ የኪነጥበብ ሰዎችን ስማቸውን ና ስራቸውን ማራከሰና ማጥፋት ፤ ውጭ ሀገር የሚኖረውን ህዝብ ማደናገርና መከፋፈል።

  4. ቀድሞ በተቀዋሚ ድርጅት ታዋቂ ደጋፊነታቸውና አመራር አባልነታቸው የሚታወቁ ፡በኩርፊያ ከዚያም  በጥቅም የተደለሉ፣ ወደ ወያኔ ካንፕ  “አገሬ ስተልማ አይቻልሁ፤ አባይን የደፈረ መሪና ደርጅት አይቻልሁ” የሚል ዋሾ ዜማ እየዘፈኑ እውነቱን እያወቁ ለወያኔ ፕሮፓጋንዳ መሳርያነት ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ ሆድ አደሮች። ለነዚ  የተሰጣቸው ተለኮ፡ በሶሻል ሚዲያ (ፓል ቶክ፣ ፌስ ቡክ፤ ዩ ቱዩብ  እንዲሁም የኢንተርኔት ሬድዮና ቲቪ) የተቃዋሚ መሪዎችን የሚሳድቡ፣ ስም የሚጠፉ፤ አዲስ ወያኔዊ ደጋፊ የሚመለምሉ፤ ወያኔን ደግፎ ሰልፍ እንዲወጣ  የሚያስተባብሩ) እንዲሁም በሚያስተናግዱት ሚዲያ የወያኔን ቱባ ባለ ስልጣኖችን እይጠሩ ፕሮፕጋንዳ የሚሰሩ፤ እነዚህን አረመኔ ወንጅልኞች ባለ ስልጣናትን  ጀግና አድርጎ  ቀባብቶ መፍጠርን፤ ሰማይ ማደርስን  የመሳሰሉትን  እንከፍ ሚና የሚወጡ፣  በወያኔ እርጥባን የሚጣልላቸውና ደግሞም ወያኔ የሚንቃቸው ናቸው።

  5. ወያኔ ለትምህርትና ለ ስልጠና የላካቸው ወያኔዎችና ደጋፊዎቻቸው። የነዚ ተልኮ አብዛኛእውን ግዜ በውጭ ሀገር ለሚያግኙት ጋዜጠኛ፣ ታዋቂ ሰው፣ ፕሮፌሰር፣ የሌላ አገር ተማሪዎች፣ ባልስልጣኖች፤ የተማሪና ሙያ ማህበርት ወስጥ ሰርጎ በመግባት የወያኔን ዲሞክራሳዊነት፤ የእድግት ጉዞ ፣ፕሮፕጋንዳ መንዛት ነው። ተቀዋሚ ድርጅቶችን በሚያድርጉት ስብስባ በመገኝት ሙሁር መሰል አደናጋሪ ጥያቄ መጠየቅና አድማጩን ማደናበር። በውጭ ለሚታተሙ ወያኔን የሚኮንኑ  ጽሁፎችን የፈርንጅ ጋዜጣዎችን የአምስቲ ኢንተርናሽናል (Amnesty International) ሁይማን ራይትስ (Human Rights Watch) ና የመሳሰሉትን ዘገባዎች  የሚቀወም ጽሁፍ የሚያቀርቡ  ናቸው።

  6. ቀደም ብሎ ወያኔ ጫካ እያለ ሲደግፉ የነበሩ፣ ኑሮአቸውን በውጭ አገር ያደርጉ፣ የሚኖሩበትን ሃገር ዜግነት የወሰዱ፤ ነግር ግን የትግራይ ተውላጅ ብቻ በመሆናቸው በዘርኝነት የበላይንት መንፈስ የተጠናወታቸው ጭፍን  ደጋፊዎችና ሙሁር ነን  ባይ ዘርኛ ትግሬዎች። እንዚ በገንዝብ፤ በማባባል፣ በሌላም በሁሉም መስክ በተሰጣቸው ሚና የሚሳትፉ ሌላወን ኢትዮጵያዊ የሚንቁ ና የማይቀበሉ ናቸው።

  7. ብዙ በሺዎትና  ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወያኔው የሚከፍላቸው ሎቢ የሚሰኙ የፈርንጆች ድርጅቶች፤ ለሚከፍላቸው ገንዝብ የሚሰጣቸውን ስራ የሚሰሩ። እንዚህም አብዛኛውን ባአሜሪካ አገር እና ባአወሮፓ የሚገኙ፤  የአሚሪካንና አውሮፓውያን ፖለቲከኞችን፡ ወያኔን የሚጠቅም ፖለቲካዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ ወሳኔ ምክር ቤታቸው ወይም ካቢኔያቸው  እንዲደግፍ የሚያባብሉ፤ወያኔ ላይ የተቃጣ ነቃፊ ህግ እንዳይጸድቅ እንዲተጉ የሚያደርጉ ናቸው።  ታዋቂ  የፈርንጅ ጋዜጠኞችን በማባባባልና በመደለል በ ጋዜጣ ወይም መጽሄታቸው ስለ ወያኔ መልካም ነገር የሚሰብኩ፤ በውሸት በዚህ አሃዝ የኢትዮጲያ ኢኮኖሚ አደገች ብለው የሚያሳትሙትን የሚለማመጡ ናቸው። በተጨማሪም በገንዘብ የተገዙ የኮምፒትርና ስልክ መርጃ ጠላፊ የወጭ ሀገር ባለሞያዎችን (hacker) ይጨምራል። የተቃዋሚ መሪዎችን፣ ተጽኖ ፈጣሪ ሙሁሮችን ግልሰቦችን እንዲሁም የፖለቲካ ድርጅቶችን  ኮምፒተር ፋይሎችን፣ መረጃዎችን፣መልክቶችን፣ የስልክ ንግግሮችን በህገ ወጥ መንገድ ወያኔ እንዲሰርቅ የሚያስችሉ ናቸው።

ወያኔ እንዚህን ሁሉ ሰራዊቱን  በወጭ ሃገር ባለው ኢትዮጲያዊ ላይ አሰምርቶአል።

ይህ እንግዲህ  በተለይ ታላላቆቹ አገሮች አሜሪካና አወሮፓ በተለይ ዮናይትድ ኪንግድምን ጨምሮ  በይፋ ከሚሰጧቸው ገንዘብ፣ ብድርና ወታደራዊ እርዳታና ስልጠና ጨምሮ ( በነዚሁ አገራት የሚሰጡትን ግዳጅ ወያኔ በተለይ በሱማሌና በሱዳን ያለውን አከራሪ እስልምናን በወታደር በመዋጋት  ትዛዝ ስልሚፈጽም ርዳታውና ድጋፉ ይስጠዋል) የሰባዊ መብት ተከበረ አልተከበረ  አንዳች ደንታ ከሌላት፣ ባአፍሪካ አዲሲትዋ ቀኝ አዙር ኮሎኒያሊስት ከሆነችው ቻይናን ጨምሮ የአልም ባንክና፣ አይ አሜ አፌ (IMF) የሚሰጡት  ገንዘብ  የፋፋው ወያኔ  በህዝባችን ላይ የሚፈጽመው የግፍ አገዛዝ ቀጥሎአል። ከኢትዮጲያውያን የሚዘርፈውና ከመኖሪያቸው እያፍናቀለ መሬት የሚሸጠው ወያኔ፡ አሁንም ከእኔ በላይ ላሳር ብሎ በተሃደሶ አዲስ ሽንገላ የተቆጣወን ህዝብ በአስቸኳይ መንግስት  (State of Emergency decree) እያስፈራራ  እድሜውን አስረዝሞአል።

ይህን ሁሉ እርዳታና የገንዝብ፣ የመሳርያ ሀይል ከታጠቀው ወያኔ ሰላማዊ፣ ፍታሃዊ  አስተዳደርና  አገር የኢትዮጲያ ህዝብ አያግኝም።  ተስፋ ሳይቆርጥ በአላማው ጸንቶ፣ ወገቡን ታጥቆ ፣ የወያኔን መከፋፋያ ዘዴ አፍርሶ፤ በመተባበርና ባንድነት በመታገል ይህን አስከፊ አገዛዝ መጣል ያስፈለገዋል። እርስ በራስ በወያኔው ወጥምድ ገብተን ከምንጣጣል፤  በህብረት ወያኔን በሚያስፈልገው የትግል ዘዴ ሁሉ ጥለን የጋራ ፍትህ የሰፍነባትን፣ ሁሉም ዜጋ በእኩልነት የሚታይበት፣ የሚዳኝበት ሰላማዊ ሃገር መገንባት ይገባናል።

ለሁሉም አምላክ ይርዳን።  አሜን!