ትዝብት (ከአዉስትራሊያ)

ለጓድ ሠርቶ አደር አዘጋጅ ለነበሩት የዛሬዉ የሞረሽ ሊቀ መንበር አቶ ተክሌ የሻዉ! መቼም ስልጣኑን የሚወድ ሰዉ በስልጣኑ ካልተጠራ ችግር ይፈጠራልና ያጎደልኩት ነገር ካለ ከወዲሁ ይቅርታ እጠይቃለሁኝ። ባሉበት የሰዉ ፊት ገርፍዎ ከከፈቱት ካፌ ድረስ ሰላምታዬ ይድረስዎ! ባለፈዉ ለኤፍሬም ማዴቦ የፃፉትን ደብዳቤ አነበብኩት። በጣም የገረመኝ እርስዎ ሞረሽን ወደ ፖለቲካ ድርጅት አዙረዉ ወያኔን የመታገል ፍላጎቱ እንዳለዎት እርስዎም ገንዘብ ለመቃረም በኦዚ ደሞ በአዞ አላልኩም ባደረጉት ጉዞ አዉቀናል። በዚህ ጉብኝትዎ ከኦዚ ይልቅ ትንሽም ከዉርደት ያዳነዎት የኪዊ ማሕበረሰብ እንደነበር ሁላችንም የምናዉቀዉ እዉነታ ነዉ። ይኽን ስልዎት ግን በእዉነት ነዉ የምልዎ የገንዘብ ነገር አንስቼ ዉድድር ዉስጥ ለመግባት በማሰብ አይደለም። እንደዉም የእርስዎ እብደት በጣሙን ስላሳሰበኝም ጭምር እንጂ። መቼም እርስዎ አቶ ኤፍሬምን ባዶ እጁን ወደ አስመራ እንደተመለሰ በጣም አስፈንድቋታል። የጤና ነዉ ግን?

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

ከምሬ ነዉ እኮ ትግሉ ወደ ጎን ይቅር አልተባባልንም እንዴ በየአደባባዩ። ምን አዲስ ነገር ተገኝቶ ነዉ እንኳን ያልሆነዉን ይቅርና ቢሆንስ እዉነት አርበኞች ግንቦት 7 ባዶ እጅን ቢመለሱ ወያኔን እታገላለሁ ለሚል አንድ የድርጅት መሪ የሚያስፈነድቅ ነዉ? ሌላዉ ቢቀር በእርስዎ እድሜ እንዲህ አይነት የምቀኝነት ስሜት በአደባባይ ላይ ማዉጣት እዉነት ኡትዮጵያዊ ባሕሪ ነዉ? በእውነት መድኃኒአለምን በጣም አጥጋቢ እንደተለመደዉ ሰብስበናል። እርስዎ ግን እንደ አንደ የወያኔ ደጋፊ የአርበኞች ግንቦት 7 መዉደቅ እንዲህ ያስደሰትዎት ለፖለቲካ ፍጆታዎ መሆኑን ሳስበዉ ደሞ አፈርኩልዎት። ለመሆኑ ይኼ የፖለቲካ ትርፍ አገኝበታለሁ ብለዉ ያሉት መጣጥፍ ምን ያህል ቁልቁል እንዳዳፋዎ ገብቱዎታል። እኔማ እንደ እርስዎ አሹ ልበል ብዬ አልኩና …… መጣጥፉ የግል ሃሳቤ መሆኑን አንባብያን እንዲረዱልኝ እፈልጋለሁ። ይህንን የምልበት ምክንያት ማንኛዉንም ድርጅት ወይም ተቋም የሚመለከት አለመሆኑን ለማስረዳት እና የግል አስተያየቴ መሆኑን በመሻትና ለሚመጣዉም ማንኛዉም መጠይቅ ኃላፊነት የመዉሰድ ፍላጎቴንም ለመግለጽ ያህል ነዉ።

ምን አልባት ይህን ስል አቶ ተክሌ የሻዉ ላያስደስታቸዉ ይችላል አሊያም ከዚህ በፊት እንዳሉት በድርጅት እና በግለሰቦች መካከል ያለን ልዩነት ካለመረዳት ይሁን ወይም ካለን ዉስጣዊ ፍላጎት እንዲሆን የምንሻዉን በዉስጣችን በማሰባችን ብቻ በገሐዱ ዓለም ያልታየን ነገር እንዳለ አድርጎ በማሰብ ጮቤ ለመርገጥ እና የግል እኩይ አስተሳሰባችንን ተግባራዊ ሆኖ ለማየት ከመጓጓት የተነሳ የምንሻዉ አካሔድ እንዳላቸዉ ከፅሑፋቸው ተረድቼያለሁ። በሁላችንም ዉስጥ በገሐዱ ዓለም የሌለ ነገር ግን በምናባችን ፈጥረን እንዲኖር የምንፈልገዉ ነገር እንዳለ እዉነት ነዉ ጥሩም መጥፎም እንደየስብዕናችን እና ጊዜዉን እና ኩነቶችን እሳቤ ያደረገ የሆነ። ደሞ ሁላችንም አንዳንዴ የምንፈልገዉ መሆኑ የማንደብቀዉ ነዉ። ለምሳሌ በወያኔዎች መኻከል የሚፈጠረዉ ቅራኔ ወይም የርስ በርስ አለመግባባቶች ሲፈጠሩ በጣም ጮቤ እንረግጣለን እንዲሆንም ደሞ አጥብቀን እንለምናለን ከዛም ሲያልፍ እርስበራሳቸዉ ቢጠፋፉ ሁሉ ለሁላችንም የምንፈልገዉ ምናባዊ ፍላጎታችን ነዉ ጠንከር ያለ ስብዕና ያለዉ ግን ይኽ እንዲሆን አጥብቆ ይሠራል።

ይኽን የምናደርገዉ ደሞ ወያኔ አገር ላይ እያደረሰ ካለዉ እኩይ ምግባር የተነሳ በወያኔ ላይ የሚደርስበት ማንኛዉም መጥፎ ነገር በሙሉ ሁላችንንም ስለሚያስደስተንም ነዉ። ግን እንዲህ ስለፈለግነዉ ወይም እንዲሆን ስለፈቀድን ብቻ የሚሆን ሳይሆን ይህንንም ለማድረግ ጥበብ ያስፈልገዋል ጥበቡንም ወደ ተግባር ተለዉጦ ቅራኔዉን የማስፋት ሥራ የግድ ይላል በዚህም የሚገኝ እርካታም ጥግ ድረስ ሊሆንም ይችላል።

ወደ ገደለዉ ስገባ ግን አቶ ተክሌ የሻዉ አቶ ኤፍሬም በፃፉት መጣጥፍ ላይ ተንተርሰዉ በሬ ወለደ አይነት ምንም ከሃሳቡ ጋር ያልተገናኘ የአቶ ተክሌ ያላቸዉን ስብዕና በጣም ያጋለጠበት ጽሑፍ እንደሆነ ማንም ፅሁፋቸዉን ያነበበ ታዳሚ ሊረዳ ይችላል። ሲጀምሩ ኦዚ የሚለዉን የአዉስትራሊያ የማቆላመጥ ጥሪ አዞ ብለዉ ነዉ ሚጀምሩት። ለነገር በጣም መቸኮላቸዉ እንጂ እሳቸዉም ኦዚ መጥተዉ ስለነበር ይኽንን አጠራር ሳይሰሙት የቀሩ አልመሰለኝም። ነገር ግን የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል አይነት ሆኖባቸዉ ኦዚን አዞ ብለዉ ጠሩት። ይኽን አጠራር ግን አቦርጂንዮች እንዳይሰሟቸዉ ምክንያቱም ያቺ ተወርዉራ ተመልሳ ወደ ወርዋሪዉ የምትመጣዉን ዘንግ ሊወረዉሩባቸዉ ሊችሉ ስለሚችሉ ነዉ።

ለነገራቸዉ መግቢያም ያረጉት በድርጅት ሥም ፅፎ የግል ነዉ ይላል እሱና ድርጅቱ አለመግባባት እንዳላቸዉ ያሳብቅበታል ይላሉ ጨምረዉም የድርጅቱ ሃሳብ እንደሆነም አድርገዉ ይመኙታል። ምን አልባትም እርስዎ ኃላፊ ነኝ ብለዉ የሚመሩት ሞረሽ ዉስጥ ግላዊ ሃሳብን ማንፀባረቅ የማይችሉበት ሁኔታ እንዳለ በመጣጥፍዎ በገደምዳሜ በልካችን ነግረዉናል፤ ለዚህም እናመሰግናለን። ይኼም የፃፉት መጣጥፍ በግለሰብነት እንደ ተክሌ የሻዉ ካልሆነ የሞረሽ እንደ ድርጅት የተጻፈ ነዉ ማለት ነዉ። ምክንያቱም እርስዎ ለመግለፅ እንደፈለጉት ድርጅቱና በግለሰቡ መኻከል ልዩነት እንደሌለዉ አርገዉ የገለፁበት መንገድ በመኖሩ የፃፉት የሞረሽን አቋም እና ግብ ከዚህም ሲያልፍ ራዕያችሁ ነዉ ማለት ነዉ እርስዎም ያቀረቡልን? ይኼ ደሞ ፍንትዉ አድርጎ ያስቀመጡት ሞረሽ ክምንም በላይ ከአርበኞች ግንቦት 7 የበለጠ ጠላት እንደሌለዉ ነዉ ሊያስረዱን የሞከሩት። ይኼን ታድያ ምን ይባላል። እዉነት የጤና ነዉ?

አቶ ኤፍሬም ኦዚ እና ኪዊ ብለዉ ለንባብ ባበቁት መጣጥፍ ላይ ለተደረገላቸዉ መስተንግዶ እና በዛ አጋጣሚ ከኢትዮጵያዉያኑ ጋር ስለነበራቸዉ ግኑኝነት የተሰማቸዉን ስሜት እና እነዛም በኦሽኒያ አካባቢ ያሉት ኢትዮጵያዉያኖች ያላቸዉን የሰዉ ፍቅር ኢትዮጵያዊነት ባሕሉን የጠበቀዉ መስተንግዶ ለመግለፅ የከተቡት እንደሆነ መጣጥፉ በደንብ ያሳያል። ነገር ግን በእርስዎ በድርጅትዎ እንዳልል እንደ እርስዎ ቁልቁል በሸርተቴ የምወርድ ስለመሰለኝ ትቼዋለሁ ባለቤቱ እርስዎ እያሉ። አቶ ኤፍሬም በግለ ስብዕናቸዉ የተሰማቸዉን አቀባበል እና መስተንግዶ ስሜት ለመግለፅ የከተቡት ነዉ እንጂ እንደ ድርጅት ወይም ባላቸዉ በድርጅቱ ኃላፊነት ቦታ ተቀምጠዉ የፃፉት አለመሆኑን ለማሳየት የሔዱበት መንገድ እንጂ እርስዎ የሠርቶ አደር ጋዜጣ አዛጋጅ እንዳሉት ይዘዉት የሚመለሱት ኬሻ የሞላ ገንዘብ በማጣታቸዉ አይደለም። ምናልባትም የራስዎን ጉዞ በተመለከተ ከሆነ ሊያስማማን ይችል ይሆናል። በተረፈ ግን አርበኞች ግንቦት 7 እርስዎ እንዳሉት በኦሽኒያ ለአርበኞች ግንቦት 7 የሚሆን ገንዘብ የጠፋ መስሎዎት ከሆነ ኦሽኒያ ያለ አገር ወዳድ በድባብ ይሒድና ለአገሩ ያልሆነ ገንዘብ ኪሱ እንደማያድር ያሳዩበት ትልቅ ተጋድሎ ማድረጉን በሰዉ ኃይል ትንሽ በተባለችዉ ኒዉዚላንድ ዉስጥ ብቻ እንኳን እርስዎ በአጠቃላይ በኦሽኒያ ከሰበሰቡት ገንዘብ በእጥፍ የበለጠ ለመሰብሰቡ እነዛ ወሬ አቀባዮችዎ ሹክ እንዳልዎት ምስክር ነኝ። መቼም እርስዎ ይኽን የሚሉት በቤትዎ ያለዉን የገንዘብ ሽኩቻ ወደ አደባባይ ለማዉጣት እንደማይፈልጉ እዉቅ ነዉ። ለመሆኑ የድርጅትዎ የሒሳብ ክፍለ ለሆነዉ አንዱአለም ተፈራ በገንዘብ ጉዳይ ሰዉ እንዳይሰማዉ ብሎ በኢሜይል ላነሳዉ ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዉት ይሆን??

እኔ ይኽንን ለመፃፍ ያነሳሳኝ ነገር ቢኖር የርስዎ የገንዘብ እንቶ ፈንቶ ሳይሆን እዚሁ ኦዚ በመኖሬ የእርስዎን የኦዚ ጉብኝት በቦታዉ በአካልም ተገኝቼ ያየሁት በመሆኑ እና የርስዎንም ግላዊ ስብዕናዎን በመድረክ ላይ ስላየኹ ትዝብቴን በልቤ አድርጌ መቼም ኢትዮጵያችን ሁልጊዜም አንዱ ከልቡ ሲሠራላት ሌላዉ ደሞ ሊበላባት እንደሚሯሯጥባት ባሳለፍነዉ ተሞክሮ ያየነዉ ነዉ በማለት በትግስት ሁሉን ነገር ለማለፍ ሞክሬ ነበር። በጣም የሚገርመዉ ነገር ግን እንደ እርስዎ ያለ በኢትዮጵያ አንድነት ሥር ሆነዉ በሠርቶ አደር ጋዜጣ ስለ አንድነት ብዙ ሲሰብኩ የነበሩ ሰዉ ዛሬ ላይ በዘር የመደራጀት ስብዕናዎ ገዝፎ የመዉጣቱ ሚስጥር እንቆቅልሽ በሆነብን ሁኔታ የአንድ ተቋም መሪ ነኝ ብለዉ ሲያበቁ አገራችን ምጥ ይዟት በምትሰቃይበት ጊዜ እርስዎ ስለ አርበኞች ግንቦት 7 ጠላትነት ሲያወሩ ማየት እና መስማት በእዉነቱ ስለጤንነትዎ ሁሉ ጥርጣሬ ላይ የሚጥል ነዉ። ምክንያቱም ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላቱ አንድ ወያኔ ብቻ ሆኖ እያለ እርስዎ ይኽንን አገራዊ ጠላት ሰንጎ ይዞ መግቢያ መዉጫ ያሳጣን እና በርካታ ድርጅቶችን አሰባስቦ በአገራችን ላይ ያንዣበበዉን አደጋ ለመቀነስ ብሎም የተደላደለ የዲሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት የአቅሙን እያደረገ ያለን ድርጅት እንዲህ እንደ ኮሶ ያንገሸገሽዎት ነገር ምን እንደሆነ አልገባምም ስላለኝ ጭምርም ነዉ።

ለመሆኑ አርበኞች ግንቦት 7 ምን እየሠራ እንደሆነ ከጥላቻ ወጥተዉ ለማየት ሞክረዉ ያቃሉ?? አገራዊ ራዕይ ሰንቆ ሕበረ ብሔራዊ ሆኖ በዉስጡ የተለያዩ ብሔረሰቦችን ያካተተ ድርጅት ለመሆኑ በተለያየ ጊዜ በእንደዚህ አይነት ድኩማን አስተሳሰብ ተለክፈዉ ለጠየቁት ጥያቄ በደንብ አድርጎ በተለያየ የሚዲያ ተቋማት ለሕዝብ አቋሙን ግልጽ አድርጎ አሰምቷል። ለአቶ ተክሌ የሻዉ ተግባር ምን እንደሆነ ባላቅም አርበኞች ግንቦት 7 ግን በተግባራዊ እንቅስቃሴ ራሱን በመግመዱ ለዚህ አይነት አሉባልታ ጊዜ ሰጥቶ ምላሽ ለመስጠት ያዉም አገር በዚህ ጭንቀት ላይ ሆና አያስበዉም። እርስዎም ሙከራዎ ምን አልባትም ይህንኑ ለማዘናጋት ሊሆን ይችላል ማን ያቃል?? ሆዱን የሚወድ እኮ ሃሳቡ እርቃኑን እንደሚቀር ደሞ አባባልም አለ እና።

ስለ አርበኞች ግንቦት 7 አማራን ይጠላል አማራ አባላቶችም አመራር ላይ የሉም ብለዉ ከሚያናፉ ዉስጥ የርስዎም አባሎች እንደሆኑ በግልፅ የምናዉቀዉ ነዉ። ይኽንን ስልዎት ከሜዳ ተነስቼ ሳይሆን በማስረጃ አስደግፌ ማቀርበዉ ስላለኝም ጭምር ነዉ። ሚረዱ ከሆነ ግን በቅርቡ አርበኞች ግንቦት 7 ሆነዉ ከወያኔ ጋር ሲታገሉ ያለፉት ጓዶቻቸዉን ለሕዝብ ይፋ ማደረጋቸዉ በራሱ በቂ መረጃ ይመስለኛል። ነገር ግን እዉነት መራራ በመሆኑ እርስዎና በእርስዎ ሳንባ ሚተነፍሱት ግን ይቺን መራራ ለመዋጥ አቅም ስለሌላችሁ ይኸዉ ከቀን ወደ ቀን ይዛችሁት ምትመጡት አሉባልታ ማንነታችሁን እያጋለጠ ነዉ።

የጋይንቱን ጀግና እንደ አፄዉ የሽጉጡን ጥይት ጠጥቶ የወደቀዉ የወታደራዊ አዛዡን መሳፍንትን የያዘ እና በምርምር እና ጥናት ላይ ይሰሩ የነበሩትን አቶ ፈቃደ ሸዋቀናን የመሳሰሉትን ወንድሞች (ለእርስዎ ስል አማራዎች ልበላቸዉ) የያዘ ድርጅት መሆኑን ድርጅቱ ባወጣዉ መግለጫ እያሳወቀ እርስዎ ግን የአማራ ጠላት እንደሆነ ሲናገሩ ሕሊናዎ ጋር ያሎትን ዝምድና እንደጠራጠረዉ ሚያረገኝም ይኸዉ ሁሉ ተደማምሮ ነዉ። መቼም እርስዎ ለራስዎ ደሞዝ እየከፈሉ እሰራለሁ ለሚሉት ድርጅት ኃላፊ ሆነዉ ይህንን እዉነታ ማገናዘብ ካልቻሉ አንድ አማራን እወክላለሁ ብለዉ ስሙን ሞረሽ ብሎ ያለ ድርጅት መሪ መሆን ብቃት ያለዎት መሆኑን ጥያቄ ያስጭራል። ምናልባትም የሞረሽ ሳይሆን የፉርሽ ብለዉ የያዙትን ድርጅቱን ስም ይቀይሩ። አይመጥንዎትምና! ያለ አቅምም መሸከምም ስብራት ያመጣልና።

አንድ ነገር ግን ደመቅ አድርገዉ እንዲገነዘቡልኝ እፈልጋለሁ። ያም ምን መሰልዎ? አማራ እንደ ሌሎች የኢትዮያዉያን ብሔረሰቦች በአማራነት ልደራጅ ቢል የሚያግደዉ አንድም ምድራዊ ኃይል ሊያቆመዉ የሚችል እንደሌለ ማንም ሊረዳዉ ይገባል ነገር ግን በአማራዉ ስነ ልቦና ዉስጥ አንድነት እና ኢትዮጵያዊነት ከምንም በላይ እንደ እሳት ስለሚንቦገቦግ ባልኖረበት በባሕሉም መለያየትን ስለማይቀበልና መከፋፈልን እንደ ኃጢያት ስለሚያስበዉ እንጂ ልደራጅ ቢል ሞረሽ ግጣሙ እንዳልሆነ ሊያዉቁት ይገባል።

በተለይ ለመስማት ጆሮ የሌለዉ፤ አርቆ ማሰብ የማይችል፤ ሲናገር አራት ነጥብ የሌለዉ፤ ከሌላዉ ጋር አብሮ መኖርን የማያስብ፤ ፍቅር እና ግብረ ገብነት የጎደለዉ፤ ፈሪሃ እግዚአብሔር የሌለዉን፤ እግዚአብሔርን የካደ ወላዋይ ለአማራዉ አይመጥነዉም ይሰማል!
በፅሁፍዎ መቼም ያልደረሱበት የለም ስለ የቀይ ባሕር ጉዳይ አንስተዉ ልክ ወያኔዎቹ እንዳሰለጠኗቸዉ የኪቦርድ ተዋጊዎች ግንቦቴዎች የቀይ ባሕር የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊ ባሕላዊና ታሪካዊ በር መሆኑን አይቀበሉም። በነገራችን ላይ ግንቦት 7 ከአርበኞች ጋር ተዋሕዶ ግንቦት 7 የሚለዉን ስም ከያዘ ስንት ጊዜ ያለፈ መሰልዎ። እሱ ቀርቶ ስንት ጨዋታ መቶ! አርበኞች ግንቦት 7 እንደ አንድ ነፃ አዉጪ ድርጅት ሆኖ ነዉ ሚንቀሳቀሰዉ። ያም በመሆኑ በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም የተወከለ ድርጅት ባለመሆኑና ከአላማዉም ዋንኛዉ በኢትዮጵያ ወደፊት ለሚቋቋመዉ የዲሞክራሲ ሥርዓት መሰረት ለመጣል በመሆኑ የርስዎን የቀይ ባሕር ጥያቄ ወደፊት በኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመረጠዉ መንግስት የቤት ሥራ እንጂ የአርበኞች እንዳልሆነ ሊረዱት በተገባ ነበር በዛ ላይ ካለብዎ የሥራ ኃላፊነት ተጨምሮ። ወይስ ሞረሽ ይህን ሊያስመልስ ዝግጅቱን አጠናቆ ይሆን?? ለእርስዎ ዋናዉ እና ትልቁ አጀንዳ እርስዎ የሚጨነቁለት (ከባላምብራስ) ይሻዉን ልጅ ስም የሚያስጠራ ስም ከመገንባት ባሻገር ያለዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ችግር ከቁብ ሚቆጠር አይደለም። ይኼ ስብዕና ደሞ ለመሪነት አይደለም ለአፈ ቀላጤነት እንኳን አይመጥንም።

ከምር ይፋቱልን ሞረሽን!
ተጨማሪ ነገር የምነግርዎት በርስዎ አጠራር ግንቦቴ እያሉ ሊያጣጥሉት የሚጥሩትን ሳስበዉ ጠላት ሕዉሐት ሆኖ እያለና በወያኔ ላይ ያለዎትን ጠጠር ሁሉ መወርወር ሲገባዎት አርበኞች ግንቦት 7ን አደክማለሁ በማለት ነጭ ላብ እስኪያልብዎ ድረስ የሚዳክትሩት ነገር የርስዎን ማንነት ካማሳየት ባሻገር ማን እንደላከዎ ሁሉ ጥያቄ አስጭረዉብናል። የአርበኞች ግንቦት 7 ኤርትራ መግባትም ለእርስዎ ልክ እንደ ወያኔ ሁሉ ሰላም አልሰጠዎትም ግን ለምን? እስቲ በአመክንዮ ያስረዱን አሊያ እርስዎ በኦዚ ጉብኝትዎ ላይ ከሲቪል ተቋማትነት ወደ ፖለቲካዉ ለመለወጥ ዝግጁ እንደሆኑ ሲናገሩ በጆሯችን ሰምተንዎታል። ታዲያ ምን አለ አንድ ቦታ መሽገዉ አማራጩን ቢያሳዩን ከምሬ ነዉ ምነግርዎት ይኽንን ቢያረጉ ተከታዮችዎትም ይበራከቱ ነበር። ማን ያቃል እኛም እኮ ሰርቶ ሚያሠራ ድርጅት ስለምንፈልግ አሹ በዙልን ብለን ሙሉ ድጋፋችንን እንቸርዎት ነበር።

የድርጅት እድሜም አንስተዉ ሲናገሩ ሳቄ መጣ ከምር እንዴ እርስዎም እኮ ድርጅትዎ ቢያንስ በርስዎ ሒሳብ ቢ.52 አይሮፕላን የመግዛት አቅም ላይ ባይድርሱም ቢያንስ ታንኮችና አጫጭር ተወንጫፊ የሚሆኑ ሚሳይሎችን መታጠቅ የሚችሉበት ደረጃ ላይ ይደርሳሉ ማለት ነዉ። እናሳ ሞረሽ የት ነዉ ያለዉ? ጠበቃ ገዝቶ የአማራን ጠላት እየሞገተልን ወይስ ጠብመንጃ ይዞ እየተፋለመልን??

ስለፍርሃት የሞነጫጨሯት ነገር ደሞ ግራሞትን ፈጥሮብኛል ግን ምነዉ አቶ ተክሌ መቼም የመን ዉስጥ፤ ሶሪያ ዉስጥ ከሚኖረዉ ዜጋ እርስዎ በተሻለ ስለ ሞት ሳያስቡ እንደሚኖሩ ግልፅ ነዉ። በርግጥ ሞት የትም ሁን የትም ጊዜዉ ሲደርስ ማንም ከዛ እንደማይቀር የሕይወት ዉህድ ለመሆኑ ግልጽ ነዉ። ነገር ግን እርስዎ ሠርቶ አደር ጋዜጣ ሰራተኛ በነበሩበት ዘመን እድሜያቸዉ ከ17 እስከ 25 የሚደርሱ በርካታ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት አባሎች በፈንጅ ላይ ተንከባለዉ ሕይወታቸዉን ለአገራቸዉ ሲሰጡ ባያዩም ሰምተዋል ታዲያ ወደ ቦታዉ በመሔድ ፈንጂዉ ላይ ተንከባለዉ ለአገር የሰጡትን ዉለታ እንዴት እንደሚመለከቱት አይገባኝም። ምክንያቱም ሰላም ከሚኖሩበት አካባቢ ተነስተዉ ወደዛ የጦርነት ቀጠና ሔደዉ መሞታቸዉን ለማሳየት በማሰብ ነዉ።

ዛሬ ኤፍሬምን ግን ፈሪ ብለዉ ለመናገር ወይም ከእርስዎ በተሻለ ሁኔታ ላይ እንደሌለ ለመናገር የሔዱበት እና የደረሱበትን የዝቅጠት ደረጃ ሳስበዉ ምን ያህል የሞራል ዉድቀት እንደ ደረሰብዎ በጉልህ አየሁት። አንድ እዉነታ ግን አለ ያም ኤፍሬም የሞቀ የአሜሪካ ሕይወቱን ለኢትዮጵያዉያን እና ለራሱ የነፃነት ትግል ሲል ሞት ወደ አለበት እርምጃዉን አስተካክሎ ጉዞዉን ከጀመረ ቆየ። ይኼ ደሞ ዲሲ ላይ ተቀምጦ የጥላቻ ነጋሪት ከመምታት በእጅጉ ይለያል። ስለዚህ ኤፍሬም ልክ በርስዎ የሠርቶ አደር የስልጣን ዘመን ሲሰሙት እንደነበረዉ ወጣቱ ራሱን በፈንጂ ላይ ለአገር ብሎ እንደተንከባለለዉ ወቶ አደር/ወታደር ተምሳሌት ለመሆኑ ለደቂቃ አይጠራጠሩ።

ግን የመግደያ የተለየ ቦታ የለዉም ሲሉ ሰማኹዎት ልበል? ከሆነ ዛዲያ ምነዉሳ ስንቱ የወያኔ ባለሥላጣናት በአፍንጫዎ ላይ ሲፈነጭ አንዱን ድዉ አርገዉ ግዳይ ማይጥሉልን? ስለ ሸገር እና ፊንፊኔ ያነሱት ሃሳብ ኤፍሬምንም ሆነ በተግባር እየተነቀሳቀሰ ያለዉን አርበኞች ግንቦት 7ን ለመሳደብ የሔዱበት መንገድ መሆኑ በእዉነት ነዉ ምልዎ ፅሑፍዎ በጣም ነዉ ያሳበቀብዎት ከነ ጥላቻዎት፤ አይ ሰገጤ መሆን አልተሳካልዎም። ምክንያቱም ምን ያለበት ዝላይ አይችልም እንደሚባለዉ ሆነብዎ እንጂ እርስዎ እንደሚሉት የመከፋፈል አባዜን የተፀናወታቸዉቢሆኑ ኖሮ ለረጅም ጊዜ የመገንጠል አላማ የያዙትን በኢትዮጵያ አንድነት ስር ማሰባሰብ ባላስፈለጋቸዉ ነበር። የዚህ አንድነት መምጣት ደሞ የሚያስደነብረዉ ቢኖር ወያኔን እና ደጋፊዎቹን ብቻ ነዉ።

ኤፍሬምን እና የአስመራ ጓደኛዉን ለመግለፅ የሔዱበት መንገድ ስለ እርስዎ አፈርኩ ከምር። ሞረሽ እንዲህ ነዉ ሚያስበዉ? አንድ ለወገኑ የሚቆረቆር በደል ግፍ የተፈፀመበትን ማሕበረሰብ ነፃ አወጣለሁ የሚለዉ ሞረሽ በዚህ መልክ ፖለቲካዉን ሲያወርደዉ ማየት ተክሌ ይሻዉ ከሞረሽ በራሱ ፈቃድ ኃላፊነቱን መልቀቅ አሊያም ቀደም ብዬ እንዳልኩት ሞረሽን ወደ ፉርሽ ይቀይርልን እንጂ በምንም ምክንያት የዚያ ኩሩ ሐይማኖቱን ለሚያጠብቅ እና ስድብን ፀያፍ ባህሉ ያደረገን ማሕበረሰብ ተወካይ ሆኖ ሊያስቀጥለዉ የብቃትም ሆነ የሞራል አቅም የለዉምና። አስመራ ማን ሒድ አለህ ብለዉ የጠየቁት ጥያቄ በጣም ሚገርም ነዉ። መልሱ ምን መሰልዎት ሕሊናዉ፤ የሕዝብ ብሶት፤ የወያኔ የማያቋርጥ ግፍ፤ የፍትህ ጥማት፤ የዲሞክራሲ ጥማት፤ ይኼን ጥማቱን እና ራዕዩን እዉን ለማድረግ በራሱ ፈቃደኝነት ነዋ! ታዲያ መዋጮ ጠብቆ እንደማይኖር እርስዎም በጣም ያቁታል። ጥሩ የአሜሪካ መንግስት መስሪያ ቤት ቋሚ ሠራተኛ እንደነበረና ረበጥ ያለ ደሞዝ ያገኝ እንደነበር ለማንም ግልፅ ነዉ።

እርስዎ እንደሚሉት እየፈራም ቢሆን አገሩ ካለችበት ችግር ለማላቀቅ ብጨምርበትስ ምን ችግር አለዉ? እርስዎ እኮ ከወያኔ ጋር የሚደረገዉን ፍልሚያ ለደቂቃ በሃሳብዎ አምጥተዉት አያቁም። እንደዉም የዚህ አይነት ሃሳብ የሚያነሳ ጠላትዎ ነዉ። ዋሸሁ እንዴ??
ለመሆኑ እነዚህ የሞረሽ አባልዎችዎ ሥራቸዉ እርስዎን በኢንፎርሜሽን ማደናገር ነዉ እንዴ?? ከምር እንደ ፖለቲካ ሰዉ ሆኜ ስመለከተዉ ሳቦታጅ እየተሰራብዎ እንደሆነ ጠረጠርኩ። ምክንያቱም ኤፍሬምን የተቀበሉት የራሱ ዘር ሰዎች ናቸዉ ብለዉ ሲሉ ትልቅ ትዝብት ላይ በራስዎ ደጋፊዎች ጭምር መዉደቅዎን ማን ይንገርዎ? እነዛን ተርብ ሆነዉ የኢትዮጵያ ጠላትን እየተዋጉ ያሉት ጎንደሬ ወልቃይቶችን መቀበል አልፈለጉም ማለት ነዉ ወይስ የነሱን ተሳትፎ ለማሳነስ የሔዱበት እርምጃ ነዉ? እረ ስንቱ የኢትዮጵያን ባንዲራ ይዘዉ ተቀበሏቸዉን ኢትዮጵያዉያኖች ቢያዩ እኮ በኔ ተራ ምነዉ ብለዉ እርገጠኛ ነኝ ሌላ ጭንቄዎትን ሚያሳይ ደሞ ይጣጥፉ ነበር።፡ወደዱም ጠሉ እንኳን በአርበኞች ግንቦት 7 ዝግጅት ላይ ይቅርና በእርስዎም ጥሪ ላይ ቀድመዉ የተገኙት እነዚሁ ኢትዮጵያዉያኖች ነበሩ ግና ሃሳብዎ ስንኩል በመሆኑ ሊከፋፍሉን በመፈለግ የተቀበሉት የራሱ ሰዎች ናቸዉ አሉ። አዎ ለአርበኞች ግንቦት 7 ሁሉም አገሬን የሚል ኢትዮጵያዉያን ሰዎቹ ናቸዉ አይጠራጠሩ!

እቀጥላለሁ!