By ሳተናው
June 4, 2017 08:42

 

በስያትል ግንቦት 19 – 20 2009 ዓ. ም ተካሄድ በነበረው “ኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ጉባሄ” ላይ በዋናነት ተሳትፎ ያደረገው “የኢትዮጵያ ሃገር አድን ንቅናቄ” ያሰባሰቡት ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዎርጊስ እና ፕ/ር ጌታቸው በጋሻው  ንቅናቄው የአማራን ድርጅት ያላካተተበትን ምክንያት ሊያስረዱ የሞከሩት በሁለት መልኩ ነው።የመጀመሪያው ካሉት የአማራ ድርጅቶች አንዱ የሆነው ሞረሽ ወገኔ የአማራ ድርጅት በፅሑፎቹ “ኦሮሞ የለም” ብሎ ፅፏል የሚል ነው። ሁለተኛው ደግሞ ከተቀሩት ድርጅቶች ውስጥ “ሁሉንም የአማራን ሕዝብ  የሚወክል ድርጅት አላገኘንም” የሚል መንፈስ ያለው ነው።

በኔ ግምት ሁለቱም ምክንያቶች አሳማኝ አይደሉም። በመጀመሪያ ሻለቃ ዳዊት “ሞረሽ ወገኔ በኢትዮጵያ ውስጥ  የኦሮሞ ሕዝብ የሚባል የለም ብለው ፅፈዋል”  ብለው ያቀረቡት ክስ ውሸት ብቻ ሳይሆን አላፊነት የጎደለው አገላለፅ ነው።  ሻለቃ ዳዊት ይሄንን  እንዲሉ ምክንያት የሆነው በሞረሽ  ሰዎች ከሶስት አመት በፊት “በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ወራሪው ማን ነው? ተወራሪዎቹስ?”  በሚል አርስት የተከተበች አንዲት መጣጥፍን ምክንያት በማድረግ ነው።  መጣጥፏ  በወቅቱ ጎልጉል ገፅም ላይ ተለጥፋ ስለነበር  ሙሉውን ለማንበብ ይሄንን ሊንክ መጠቀም ይቻላልል።http://www.goolgule.com/modern-ethiopia-and-its-invaders/
ፅሑፉ በዋናነት በወቅቱ በኦሮሞ ኢሊቶች ይስተጋባ የነበረውን “አማራ ወራሪ ነው” የሚል አዲስ የፈጠራ ድርሰት ለመመከት የተሰነዘረ የመልስ ምት ነበር። ሁሉም እንደሚረዳው እስከ ዛሬ ያለው  የአማራ ፖለቲካ በዋናነት የመከላከል (defensive) እንጂ የማጥቃት (offensive) ስሜት አልነበረም።ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተንቀሳቀሱት ቡድኖች ኢላማቸውን ያደረጉት የአማራን ሕዝብ እና የኦርቶዶክስ ሐይማኖትን እንደመሆኑ ላለፉት አርባ አመታት በተለይ ደግሞ ላለፉት ሃያ ስድስት አመታት የአማራን ሕዝብ ከሌሎች ለመነጠልና ለመምታት ያልተፈነቀለ ድንጋይ አልነበረም። ቡድኑንን በዋናነት ይመሩት የነበሩት ደግሞ የህውሃትና የኦነግ መሪዎችና ደጋፊዎቻቸው ናቸው።እነዚህ ቡድኖች የአማራን ሕዝብ ለመነጠል የተጠቀሙበት የፖለቲካ ስልት አማራን ወራሪ አድርጎ  መሳልን ነበር። በዚህም ህውሃትና ኦነግ “የአማራ ክልል” ብለው ካጠሩት አጥር ውጪ ያለውን የአማራ ወገን  ሀብት ንብረቱን እየተቀማ እዲፈናቀል አድርገዋል።እንግዲህ ከላይ የተፃፈው መጣጥፍ  ይሄንን መሰሉን የፖለቲካ ግድፈት ታሪካዊ ጭብጦችን በማቅረብና በመሞገት  ለማስቆም ነው የተሞከረው። በዛ ፅሑፍ ውስጥ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ኦሮሞ የሚባል ሕዝብ የለም የሚል ሀሳብ የለበትም። ይልቅስ ዛሬ ኢትዮጵያ የምንላት አገር በተለያዩ የታሪክ ክስተቶች የተቀላቀለ ሕዝብ ያለባት አገር መሆኖን ነው የሚተነትነው። መጣጥፉ የሚጀምረው “በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ታላቅ የሕዝብ ቅልቅል ተካሂዷል” በማለት ነው።ስለዚህ አንደኛው አባራሪ ሌላው ተባራሪ የሚሆንበት ምክንያት የለም ለማለት የቀረበ ሙግት ነበር።
ሌላው ጉዳይ ደግሞ የሞረሽ ሰዎች ከላይ የተገለፀውን ሀሳብ  በአንድ ወቅት አንስተውት ነበር ተብሎ እንኮን ቢታሰብ ድርጅቱ ዛሬ ባለበት አቋሙ እንጅ ትላንት ባነሳት አንዲት መጣጥፍ “አይንህን ላፈር”  መባል ያለበት አይመስለኝም። ይሄንን የምለው አነ ሻለቃ ዳዊት “በኢትዮጵያ ሃገር አድን ንቅናቄ” ውስጥ ያካተቷቸውን ሰዎች  የትላንትም ሆነ የዛሬ ማንነት የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይ ደግሞ የአማራ ሕዝብ በሚገባ ያውቃል። ስብስቡን በበላይነት ከሚመሩት አንደኛው የሆኑት አቶ ሌንጮ ለታ ትላንት  “Down with Ethiopian Colonialism, Oromia shall be free!”  የሚል መሪ ቃል አስቀድመው  አገር ለመገንጠል የታገሉ ናቸው።እርግጥ ነው ዛሬ እሳቸውም ሆኑ የሚመሩት ድርጅት ያንን አመለካከታቸውን እንደቀየሩ በተደጋጋሚ ሲገልፁ ተሰምተዋል። ሌላው እውነታውን ግዜ የሚፈታው ቢሆንም  ኦነግ ከህውሃት ጋር በማበር በርካታ አማራ ወገኖቻችን  በበደኖ፣ በአርባ ጉጉ፣ በወተር፣ በአረካ፣ በአሰቦት ገዳም ወዘተ በጨፈጨፈበት ወቅት የድርጅቱ መሪ እሳቸው ነበር።ዛሬ በመሰረቱት “የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፍሮንት” ውስጥ ያሉት በርካታ ግለሰቦችም ተመሳሳይ አላማና ታሪክ ያላቸው ናቸው።ይሄ በሆነበት ሁናቴ “ሞረሽ  የስብስቡ አካል ያላደረግነው ከሶስት አመት በፊት አንዲት መጣጥፍ ለጥፎ ስለነበር ነው” የሚል  ውሃ የማያነሳ መከራከሪያ ማንሳት አሳማኝ አይደለም።
ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ “ሁሉንም አማራ የሚወክል የአማራ ድርጅት የለም” የሚል ነው። ዛሬ ከሞረሽ ሌላ ወደ ሶስት የሚጠጉ የአማራ ድርጅቶች አሉ።ቤተ አማራ፣ ቤተ አማራ መድሕን እና ዳግማው መአሕድ።  ከነዚህ ውስጥ ቤተ አማራ አደረጃጀቱም፣ አላማውም ከ“የኢትዮጵያ ሃገር አድን ንቅናቄን” ጋር የማይገጥም በመሆኑ እሱን ታሳቢ አለማድረጉ የሚያስኬድ ነው። ነገር ግን የተቀሩትን ሁለት ድርጅቶች “የአማራን ሕዝብ አይወክሉም” አይነት ድምዳሜ መስጠት  አግባብነት የጎደለው ብቻ ሳይሆን  እጅግ አደገኛ የሆነ ደባ  እንዳለ የሚጠቁም ነው።በአጠቃላይ የቀረበው  ምክንያት በሚከተሉት ነጥቦች አሳማኝ አይደለም። በመጀመሪያ ከአገር ውጪ የሚቋቋሙ ድርጅቶችን የሕዝብ ውክልና አላቸው የላቸውም ብሎ ማወዳደር አይቻልም።ይሄንን መመዘኛ የሚያሞሉበት የምርጫ ሂደት ስለማይኖር  የሕዝብ ውክልና  እንደ መመዘኛ መስፈርት ሊቀመጥ አይችልም። ሁለተኛው አንድ ድርጅት ይሄንን መሰል ስብስብ ውስጥ ለመካተት ቆሜለታለሁ የሚለውን ሕዝብ ሙሉ  ውክልና ማግኘቱ የግድ ሊሆን  አይገባምም አይችልምም። ሶስተኛ በስብስቡ ውስጥ የተካተቱት ሶስቱ የብሔር ድርጅቶች እንወክለዋለን የሚሉት ሕዝብ  ሙሉ ውክልና እንደሌላቸው የሚታወቅና የየድርጅቶች መሪዎች ያመነት ጉዳይ ነው። ለምሳሌ “የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፍሮንት” በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ያለው ቅቡልነት ይሄን ያህል መሆኑ የሚታወቅ ነው።በተለይ ወጣቱ የኦሮሞ ትውልድ በሌላ መስመር የተሰለፈ እንደሆነ አቶ ሌንጮ ባቲም የጠቆሙት ጉዳይ ነው።በዝግጅቱ  እንደ OMN ያሉና ሚሊዮን የኦሮሞ ወጣቶች የሚከታተሉት ሚዲያ አለመታየቱ  አንደኛው ምክንያትም ይሄው ነው።አራተኛው ከላይ የጠቀስኮቸው የአማራ ድርጅቶች እንደ ድርጅት  የማያሟሉትና በስብስቡ ውስጥ የተካተቱት ሶስቱ የብሔር ድርጅቶች የሚያሟሉት ይሄ ነው የሚባል ነገር የለም። ስለዚህ “የአማራ ድርጅቶችን የስብስቡ አካል ያላደረግነው ሁሉንም የአማራ ሕዝብ የሚወክል ድርጅት እስክናገኝ  ድረስ ነው “ የሚለም አካሄድ ውሃ አያነሳም በፍፁም አሳማኝ አይደለም።
እንግዲህ ከላይ የጠቀስኮቸውና በአዘጋጆቹ እየቀረቡ ያሉት  ሁለቱም ምክንያቶች የአማራን ተወካዮች  የጉባሄው አካል ለማድረግ አሳማኝ  ምክንያቶች አይደሉም። ይሄንን መሰል የአማራ ተወካይ ያልተካፈለበት ጉባይ ሲደረግ ደግሞ የመጀመሪያው አይደለም። ቪዢን ኢትዮጵያ (Vision Ethiopia) በሚል ተካሄዶ በነበረው ተመሳሳይ ስብሰባ ላይም ያስተዋልነውና በወቅቱ የተቸነው ጉዳይ ነው። ስለዚህ የአማራን ድርጅቶች እንዲህ ከመሳሰሉ እና በተመሳሳይ ሰዎች ከተደረጉ ጉባዬዎች   ውስጥ ማካተቱን አስቸጋሪ ያደረገው ምንድን ነው?? የሚለውን የግሌን አስተያየት ላስፍርና ሀሳቤን ልቋጭ።
በ“ኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ጉባሄ” ላይ በዋናነት የተንፀባረቀውና “የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ ሕብረት ህውሃትን ለመጣል ወሳኝ ነው” የሚለው ሀሳብ ትክክለኛና መሰረታዊ የሆነ ሀሳብ ነው።ዋናው ጉዳይ እነዚህን ሁለት ታላላቅ ሕዝቦች በመካከላቸው መተማመን እንዲኖር በማስቻል በአንድነት ማሰለፍ የሚቻለው እንዴት ነው? የሚለው ነው። በኔ እይታ ለሂደቱ ወሳኙና የመጀመሪያው እርምጃ  “የኢትዮጵያ ሃገር አድን ንቅናቄ” የተባለውን ስብስብ እያሰባሰቡ ያሉ ግለሰቦች ድርጅቶች አብረው እንዲሰሩ ለማድረግ የተስማሙባቸውን መሰረታዊ ነጥቦች ለሕዝብ ይፋ በማድረግ እንዲተቹ ማድረግ ይኖርባቸዋል።በስያትሉ ጉባዮ ላይ የጋራ አገራዊ አጀንዳ ተብሎ የቀረበው “ህውሃትን በማውረድ ዲሞክራያዊ ኢትዮጵያን መመስረት” የሚለው  ነው ። ይሄ  የቃል አገላለፅ የጉባዮው ታዳሚዎችን የሚያስማማ  ቢሆንም ንቅናቄውን የመሰረቱት አራቱ ቡድኖች የተፈራረሙበት ሰነድ ላይ ግን ሌሎች አሳሪ አንቀፆች እንዳሉት ሰነዱ በእጃቸው ባለው እንደ ሞረሽ በመሳሰሉ ድርጅቶች  ተደጋግሞ ተገልፆል። ለምሳሌ የሚከተሉት ሶስት ነጥቦች በሰነዱ የተካተቱ ናቸው።
1. አዲስ ወደ ንቅናቄው የሚገቡ ድርጅቶች በአራቱ ድርጅቶች የጸደቀውን ይህንን ሰንድን እንዳለ ተቀብለው መግባት እንጅ ሰነዱ እንዲሻሻልና እንዲስተካከል የመጠየቅም ሆን የማሻሻል መብት የሚያግድ አንቀፅ እንዳለው።
2. የንቅናቄው ሰነድ በወያኔ መንግስት የወጣውን እና አሁን ወያኔ እየተገበረው ያለውን ህገ መንግስት ሙሉ በሙሉ የተቀበለ መሆኑን።
3. ንቅራቄው በወያኔ መንግስት የተዘረጋውን የአስተዳደር መዋቅር እንዳለ የተቀበለ መሆኑን።
“የአማራ ድርጅቶችን ያላካተትነው በዚህና በዚያ ምክንያት ነው” እያሉ ክስ ከማሰማት በፊት ከላይ የተጠቀሱት ሶስት አሳሪ አንቀፆችን ለሕዝብ አውርዶ ማስፈተሽ የሚገባ ይመስለኛል።ዛሬ “ህውሃትን በማውረድ ዲሞክራያዊ ኢትዮጵያን መመስረት”የምትለዋን  ሀረግ እንደ ማታለያ ተጠቅሞ የአማራን ሕዝብ ከጎን ማሰለፉ ከባድ ነው። “ደርግ ይውቅ እንጂ የመጣው ይምጣ “ የሚለው የጅል አካሄድ  ህውሃት ወልዷል።ነገ ሌላ የባሰ እንዳይመጣ ተመሳሳይ ስጋት ያለበት ማሕበረሰብ እንዳለ መታወቅ አለበት።
ከላይ የተጠቀሱት ሶስት አንቀፆች የአማራን ሕዝብ ንቅናቄው ውስጥ ሊያካትቱ የማይችሉ  እጅግ አደገኛ  የሆኑ አንቀፆች ናቸው። የመጀመሪያ አንቀፅ ፀረ ዲሞክራሲ ብቻ ሳይሆን ንቀት የተሞላበት አንቀፅ ነው።እኛ የተስማማንበትን ተቀበሉን ብሎ ዲሞክራሲያዊ አገር መገንባት አይቻልም። ቀጣዮቹም ሁለቱ አንቀፆች ከኢትዮጵያም ቀጣይ እጣፋንታም ሆነ ከአማራ ሕዝብ ህልውና ጋር የተያያዙ አንቀፆች ናቸው።ሁሉም እንደሚያውቀው ደርግን ለመጣል የታገሉት ሶስቱም ሀይሎች ማለትም ህውሃት፣ ሻብያና ኦነግ የመገንጠል አጀንዳን ይዘው የታገሉ ናቸው።በተጨማሪም ሶስቱም ቡድኖች የታገሉት ሕብረ ብሔራዊ የሆነውን ደርግን ቢሆንም  በግልፅም በስውርም “ዋና ጠላታችን የአማራን ሕዝብ ነው” እያሉ ነው። ስለዚህ ደርግ በወደቀበትና የሽግግር መንግስት በተቋቋመበት ወቅት የአማራ ሕዝብ ላይ መገለል ብቻ አይደለም የደረሰበት።
እንደ ጠላት የተፈረጀ ሕዝብ እንደመሆኑ በወቅቱ የተወሰኑ ውሳኔዎች በሙሉ ሆን ተብሎ  የአማራን ሕዝብ ለመጉዳት   የተደረጉ ነበሩ። ይሄ ሀቅ እየታወቀ እነዚህ ሶስት  ፀረ አማራና ፀረ ኢትዮጵያ ተገንጣዮች  የተከሉትን አስተዳደር እንዳለ እንቀበላለን የሚል አሳሪ አንቀፅ ይዞ የአማራን ትብብር መጠየቅ የሚያስኬድ  አይደለም።ንቀትም ነው።
ለማጠቃለል ኢትዮጵያ ዛሬ ተተብትባ  የሰታሰረችበትን ገመድ አጥብቀው የቋጠሩ ሰዎች የቋጦሯቸው ውል ያለው ቋንቋን መሰረት ተደርጎ በተገመደው ክልላዊ መስተዳደር ላይ መሆኑን መገንዘብ ይገባል። ችግሩንም ለመፍታት የሚታትር ሰው ግዜና ጉልበቱን ማጥፋት ያለበት ይሄንን ቋጠሮ መፍታት ላይ ነው። ዋናው ቋጠሮ ተፈርቶና ወደ ጎን ተገፍቶ ችግሩ ይፈታል ፣ ሰላምና መረጋጋት ይመጣል  ብሎ መመኘት የችግሩን ግዝፈት አለመረዳት ነው።በሂደቱ ላይ የአማራን  አስተዋፅኦ በተመለከተ  ከብአዴን ውጪ “በወያኔ መንግስት የተዘረጋውን የአስተዳደር መዋቅር እንዳለ እንቀበላለን” የሚልን አንቀፅ የሚቀበልና የንቅናቄው አካል ይሆናል ተብሎ የሚታሰብ የአማራ ድርጅት ሊኖር አይችልም። የእርስት ጉዳይ ለአማራ ሕዝብ የሕልውና ጉዳይ ነው።የአማራ ሕዝብ ጠላቶቹ ሆን ብለው ዙሪያውን ሸራረፈው የፈጠሩለትን  የአማራ ክልል የሚባል አጥር ተቀብሎ ይቀጥላልል የሚለው አመለካከት ያለው ሰው ካለ እርሙን ቢያወጣ ነው የሚሻለው።
 ስለዚህ አንደኛውን ወገን ለማስደሰት ሲባል ብቻ የሌላኛውን ህልውና አደጋ ላይ የጣለን ሰነድ  መልሼ እጭንበታለሁ ብሎ ማሰብና ያንን ደግሞ አሜን ብሎ የሚቀበል ቡድን አገኛለሁ ብሎ ማሰብ አያስኬድም። መፍትሄው ሃሳቦችን በግልፅ ወደ ሕዝብ አውርዶና አስተችቶ እንዲስተካከሉ ማድረግ ብቻ ነው። ከዚህ በተረፈ የአማራን ሕዝብ የሚወክል ድርጅት አጣን በሚል ውሸት ምክንያቶች እየደረደሩ  ሌላ ብአዴንን በውጪ ለመመስረትና ሕዝብን ለማታለል መሞከር “ህመምን ቢደብቁት አስከሬን ብቅ ይላል” እንደሚባለው የተጀመረው ጥሩ ጅምር ፈርሶ ከተወሰነ አመት በፊት ሌላ ስብስብ ጅማሮ ይሆናልና ከአሁኑ አስቡበት።
ቸር  እንሰንብት።