Skip to content
Wednesday, 07 June 2017 13:26

በዕለተ ሰኞ በመካከለኛው ምስራቅ አዲስ የሃይል አሰላለፍ ሊያስከትል የሚችል የዲፕሎማሲ ስንጥቅ ተከስቷል። የገልፍ ካውንስል ወይም “GCC” በሚል ማዕቀፍ ውስጥ የተሰበሰቡት የሱኒ እስልምና እምነት ተከታይ የዓረብ ሀገራት ባልተጠበቀ ሁኔታ፤ ኳታር አሸባሪዎችን ትደግፋለች ሲሉ ከሰዋል።
ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ግብፅ፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬት እና ባሕሪን በይፋ ከኳታር ጋር የነበራቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋርጠዋል። ይህንን ውሳኔያቸውን ተከትሎ የአየር ክልላቸውን፣ የየብስ ክልላቸውን እና የባሕር ክልላቸውን፤ ኳታር እንዳትጠቀም ማዕቀብ ጥለዋል። ይህንን የሀገሮቹን ውሳኔ ዘግይተው በምስራቅ ሊቢያ ተቀማጭ የሆነው የሊቢያ መንግስት እና ማልዲስ ተቀላቅለዋል።
በገልፉ ሀገራት መካከል የተፈጠረው የዲፕሎማሲ ግንኙነት መሰንጠቅ በዘርፉ ላይ ያሉ ባለሙያዎች የተለያዩ ትንታኔዎችን አቅርበዋል። አሜሪካ፣ ቱርክ፣ ሩሲያ እና ኢራን በበኩላቸው የገልፉ ሀገራት በጠረጴዛ ዙሪያ ችግሮቻቸውን እንዲፈቱ እየጎተጎቱ ይገኛሉ። ኩዌት በበኩሏ የአደራዳሪነት ሚናዋን ከወዲሁ በመጀመር ኳታር ከማንኛወም መግለጫ እንድትቆጠብ እና የኩዌት ባለስልጣናት ማክሰኞ ወደ ሪያድ በመጓዝ የሳዑዲ አረቢያ ንጉስን ለማነጋገር ቀጠሮ መያዛቸውን ይፋ አድርገዋል።
በገልፉ ሀገራት ውስጥ ውስጡን ሲብላላ የነበረው ልዩነት ፈጦ የወጣው በሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች መሆኑ ይነገራል። አንደኛው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሳዑዲ አረቢያን ጎብኝተው ከተመለሱ በኋላ የኔቶ–ዓረብ የፀረ–ሽብር ወዳጅነት መመስረት እንደሚፈልጉ ማስታወቃቸውን ተከትሎ ነው። ዶናልድ ትራምፕ በጉብኝታቸው የዓረብ ሀገራት አሸባሪነትን ለመዋጋት ቅድሚያውን መውሰድ አለባቸው የሚል ማሳሰቢያም አቅርበዋል። በተጨማሪም በኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ መንግስት ላይ ጠንከር ያለ ውንጀላ ሰንዝረዋል። ፕሬዝደንቱ፣ ኢራን አሸባሪዎችን ትደግፋለች ሲሉ ከሰዋል። በአንፃሩ ሳዑዲ አረቢያን የፀረ–ሽብር ዋና አጋራቸው ማድረጋቸውን በተግባር፣ ለወዳጅም ለጠላትም አሳይተዋል። ይኸውም፣ የ350 ቢሊዮን ዶላር የጦር መሣሪያ ሽያጭ ስምምነት ከሳዑዲ ነገስታት ጋር ፈርመዋል። የስምምነቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ በ110 ቢሊዮን ዶላር የጦር መሣሪያ ሽያጭ ተጀምሯል።
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጉብኝታቸውን ጨርሰው ወደ ሀገራቸው ቢመለሱም፣ በፀረ–ሽብር ዘመቻው ያስቀመጧቸው ማሳሰቢያዎች በገልፉ ሀገራት መካከል አዲስ የሃይል አሰላለፍ ሊያመጣ ችሏል። በምክንያትነት የሚቀመጠው የገልፉ ሀገራት አሸባሪ ብለው የሚፈርጇቸው ሃይሎች ወጥነት የሌላቸው በመሆናቸው ነው። እነዚህ ሀገሮቹ ከራሳቸው ሥርዓት ወይም ከብሔራዊ ጥቅም አንፃር አሸባሪ የሚሏቸው ሃይሎች ከባሕሪም ከእምነትም አንፃር ልዩነት አላቸው። ከዚህ ባልተናነሰ የአልጀዚራ መገናኛ ብዙሃን ለልዩነታቸው ከፍተኛ ሚና እንዳለው እየተነገረ ይገኛል።
ሁለተኛው ምክንያት፤ በኳታር ሚዲያ ኤጀንሲ ድረ ገፅ ላይ ሰፍሮ ተገኘ የተባለው ጽሁፍ መሆኑ በስፋት ይታመናል። ይኸውም የኳታሩ ኢሚር፤ የኢራንን ኅብረት በመደገፉ እና ሳዑዲ ዓረቢያ ኢራንን ለማግለል የምትከተለውን ፖሊሲ እቃወማለሁ ብለዋል መባላቸውን ተከትሎ ነው። (“he expressed support for alliance with Iran and criticized the Saudi-led effort to isolate Tehran”) ሆኖም ግን የኳታር ኃላፊዎች በኳታሩ ኤሚር እንዳልተፃፈ አስተባብለዋል። የሚዲያ ኤጀንሲው ድረ–ገጽ ተሰብሮ የተፃፈ መሆኑንን አስታውቀዋል። እንዲሁም ኳታር ከድረ ገጽ የመረጃ ቋት ሰበራ በስተጀርባ ሳዑዲ አረቢያ አለችበት ስትል ከሳለች። በዶሃ ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ በመክፈት ውንጀላዋን በመረጃ ለማስደገፍ እየሰራች ነው ብላለች።
በማሕበራዊ ሚዲያ የኤሚሩ አቋም ነው ተብሎ ለተገለጸው ጽሁፍ ከእስልምና አክራሪ ሃይሎች ከፍተኛ ድጋፍ ተችሮታል ተብሏል። የቀድሞ የአልቃይዳ ጃብሃት አል ኑስራ ከፍተኛ መሪ የነበረው በቲውተር ገጽ ሃሽታግ በማድረግ ድጋፉን መግለፁን ተከትሎ ነው።
ሌሎች ባለሙያዎች በበኩላቸው አሁን ላይ ገንፍሎ የወጣው የገልፍ ካውንስል ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ስንጥቅ የውጭ ግንኙነት ፖሊስ ማስፈጸሚያ መንገዶች ጋር ተያያዥነት አለው ይላሉ። ይህም ሲባል፣ ገሚሶቹ የውጭ ግንኙነት ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም አክራሪ የእስልምና ኃይሎችን ይጠቀማሉ፤ ገሚሶቹ ደግሞ የውጭ ግንኙነት ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም አክራሪ የእስልምና ኃይሎችን መዋጋት አስፈላጊ ነው ብለው ያምናሉ። በሁለቱም ቡድን ውስጥ የሚገኙ ሀገራት ግዴታ ማኅበር አይጠበቅባቸውም። ሆኖም ግን ይበጀኛል ብለው አሰላለፋቸውን ማስተካከላቸው ግን፣ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ችግር በሱኒ እና በሺዓ እስልምና እምነት ተከታዮች መካከል በሚፈጠር የበላይነት ግብግብ ተደርጎ የሚወሰደውን አመለካከት ከሥሩ ጥያቄ ውስጥ የሚጥል ነው።
ለምሳሌ ኳታር እና ኢራን በሙስሊም ወንድማማቾች ሕብረት መሰረቶች ላይ ችግር የለባቸውም። በአንፃሩ ግብፅ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ባሕሪን፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በበኩላቸው የሙስሊም ወንድማማቾች ሕብረትን በአሸባሪነት ይፈርጃሉ። በግብፅ ታሪክ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡት ፕሬዝደነት መሐመድ ሙርሲ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ሲደረግባቸው፣ ኳታር በይፋ ድርጊቱን አውግዛ ፕሬዝደነት ሙርሲ ወደ መንበረ ሰልጣናቸው እንዲመለሱ መጠየቋ የሚታወስ ነው። በሌላ በኩል ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ በፕሬዝደነት ሙርሲ ላይ የተደረገው መፈንቅለ መንግስት ደግፈዋል። ዋና ምክንያታቸው ፕሬዝደነት ሙርሲ የሙስሊም ወድማማቾች ፓርቲ ተመራጭ በመሆናቸው ነበር።

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የኔቶ–አረብ የፀረ–ሽብር ሕብረት ለመስረት ፍላጎታውን በገለፁበት ሳምንታት ውስጥ የነበራቸው ልዩነት ጎልቶ የወጣበት ምክንያት አንዱ፣ የሙስሊም ወንድማማቾች ሕብረት በአሸባሪነት በመፈረጅ እና ባለመፈረጅ ከተፈጠሩት ልዩነቶች አንዱ ነው። ሌላው ኳታር የኔቶ–አረብ ሕብረት አባል ለመሆን፤ በአሜሪካ እና በሳዑዲ አረቢያ አሸባሪዎችን ትደግፋለች የሚል ከፍተኛ ውንጀላ ከሚቀርብባት ኢራን ራሷን ማራቅ ይጠበቅባታል። ከላይ የሰፈሩት ፍላጎቶች አንድ ከሚመስለው ገልፍ ሀገራት ዶሴ ውስጥ የተቀመጡ ልዩነቶች ናቸው።
አሁን ከተፈጠረው የዲፕሎማሲያው ስንጥቅ ከፍ ባለ ደረጃ በኳታር እና በሳዑዲ አረቢያ እንደዚሁም በተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ መካከል በጣም የቆየ የገዘፉ ልዩነቶች መኖራቸውን ከዚህ በታች በሰፈረው ከቅርብ ጊዜ ልዩነቶች እስከ 90ዎቹ ድረስ የነበራውን መቆራቆዝ በግልፅ ያሳያል። ይህም ሲባል፣ የተሰበረ የኢሜል ቋት የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከእስራኤል ገር ያላቸውን ትብብር ያሳያል፣ የኳታር ኒውስ ኤጀንሲ ቋት መሰበር፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የውጭ ግንኙነት ተልዕኮ፣ የአረቦች ፀደይ፣ በኳታር የተደረገ መፈንቅለ መንግስት፣ የጋዝ ማስተላለፊያ ፍቃድ ማጣት እና የድንበር ግጭቶችን በወፍ በረር የሚያስቃኝ ነው።
ጁን 4 ቀን 2017
መገናኛ ብዙሃን በአሜሪካ የተባበሩት አረብ ኤሜሬት አምባሳደር የኢሜል ቋታቸው መሰበሩን ይፋ አደረጉ። ከተሰበረው የኢሜል መረጃ ሳጥን የተገኘው ፅሁፍ፣ በአምባሳደር ዩስፍ ል–ኦታይባ እና በእስራኤል ቲንክ–ታንክ መካከል የኳታርን ገፅታ የሚያበላሽ ሥራዎች እንቅስቃሴዎች መኖራቸው ያሳያል። ከዚህም በላይ በኳታር የሚገኘው የአሜሪካ የጦር ማዘዣ ጣቢያ ወደ ተባበሩት አረብ ኤሚሬት እንዲዘዋወር ማሴራቸውን ይፋ አድርጓል።
ሜይ 23 ቀን 2017
የኳታር የዜና ኤጀንሲ ድረገፅ ተሰበረ። በዚህ በሃከሮች የተሰበረው ድረ–ገፅ፣ የኳታር ኢሚር ሼክ ታሚሚ ቢን ሃማድ አል ታኒ አሳትመውታል የተባለ ጽሁፍ ለንባብ በቃ። የድረ ገጽ ቋት መሰበሩን ይፋ ያደረጉት የኳታር ከፍተኛ ሃላፊ በኢምሩ ስም ተፅፏል የተባለው መረጃ ሃሰት መሆን አስታወቁ። ዘግየት ብሎም የተሰበረውን የኳታር ሚዲያ ኤጀንሲን ቋት ለማስተካከል ኤፍ.ቢ.አይ መስታፉ ታውቋል። ሆኖም ግን ለሳዑዲ ዓረቢያና ለተባበሩት ዓረብ ኤሚሬትስ ቅርብ የሆኑ የቀጠናው ሀገራት የሚዲያ ተቋማት፣ ተሰብሮ የተፃፈውን ጽሁፍ በጥቀስ ለገልፉ ሀገራት በስፋት አሰራጭተውታል።
ዲሴምበር 2016
የሳዑዲ ንጉስ ሳልማን ቢን አብዱላዚዝ ዶሃ ተገኝተው ጉብኝት አደረጉ። የጉብኝቱ ዓላማ በመካከላቸው ያለውን ልዩነት ለማጥበብ ነበር።
በ2015
ዴይሊ ሜል፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ የውጭ ግንኙነት ዓላማቸውን ለማስተዋወቅ ተቀማጭነቱ በእንግሊዝ ሀገር የሆነ የኮንሰልታንት ድርጅት መቅጠራቸውን አስነበበ። ሁሉም እንቅስቃሴዎች በጥብቅ ሚስጥርነት እንዲከናወኑ ከሥምምነት መድረሳቸውንም ይፋ አድርጓል። ከተቀመጡት የውጭ ግንኙነቶች ዓላማዎች አንዱ፣ ኳታር ለአሸባሪዎች ድጋፍ እንደምታደርግ፣ ለባለድርሻ አካላት ግንዛቤ ማስጨበጥ ነበር።
በኖቬምበር 2014
ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ እና ባሕሪን ከስምንት ወራት በኋላ አምባሳደራቸውን ወደ ዶሃ ለመመለስ ከስምምነት ላይ ደረሱ።
ማርች 5 ቀን 2014
ሳዑዱ አረቢያ፣ ባሕሪን እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬት፤ ኳታር የሙስሊም ወድማማቾች ሕብረትን ትደግፋለች በሚል ምክንያት ያላቸውን ግንኙነት አቋራጡ። ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ የሙስሊም ወድማማቾች ሕብረትን በአሸባሪነት ፈርጀውታል።
በኳታር ላይ የቀረበው ሌላው ክስ፣ ከገልፍ ካውስሉ ስምምነትን ውጪ ተግባር ላይ ተሰማርታለች የሚል ነው። ይኸውም በገልፉ ካውንስል የታቀፉ አባል ሀገራት፣ አንዱ በሌላው የውስጥ ጉዳይ እጁን አያስገባም የሚለውን አንቀጽ በመተላለፈ ጥላቻ የሚሰብክ ሚዲያ ትጠቀማለች ሲሉ ከሰዋታል፤ የአልጀዚራ የሚዲያ ጣቢያን መሆኑ ነው።
ማርች 3 ቀን 2014
የኳታር ዜግነት ያለው ግለሰብ በተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ፍርድ ቤት የስምንት ዓመት እስር ተፈርዶበታል። የክሱ ጭብጥ አል–ኢስላህ የተባለ የኢስላሚስት ፖለቲካል ሶሳይቲ ደጋፊ ነው የሚል ነው። ድርጅቱ ደግሞ የሙስሊም ወድማማቾች ሕብርት አባል ነው በሚል የተፈረጀ ነው።
በ2011 የአረቦች ፀደይ የፖለቲካ ቀውስ
የአረቦች ፀደይ በገልፍ ካውንስል ሀገራት ላይ ያስከተለው ቀውስ ከፍተኛ የሚባል አይደለም። ባሕሪንን ቀውሱ እስካሁን ንጧታል። ከገልፉ ካውንስል ሀገራት ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ከተነሳው የማሕበራዊ ፍትህና የፖለቲካ ቀውስ አንፃር ድጋፋቸውን በተለየ መልኩ ለይተው ነበር። የመረጡት መስመር በሀገራት መካከል ውጥረትን ፈጠረ። በተለይ የሙስሊም ወንድማማቾች ኅብረት ፓርቲን ወደ ስልጣን መምጣት ተቃውመዋል።
በ2010
ሼክ ሃማድ ቢን ካሊፋ ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ በመፈንቅለ መንግስት ተጠርጥረው ለታሰሩ የሳዑዱ አረቢያ ዜጎች ምህርት ሰጡ። ምህረቱ የተሰጠው የሳዑዲ ንጉስ በጠየቁት ጥያቄ መሰረት ነው። ለግንኙነታቸው መሻሻል ከፍተኛ ድርሻ ነበረው።
ጁላይ 2008
ኳታር እና ሳዑዲ አረቢያ ድምበራቸውን ለመከለል ተስማሙ። አልጋ ወራሽ ሱልጣን ቢን አብዱል አዚዝ በምላሹ ዶሃን ጎበኙ።
በ2006
ሳዑዲ አረቢያ ኳታር በሳዑዲ ግዛት አቋርጣ የነዳጅ ዘይት ማስተላለፊያ ወደ ኩዌት ለመዘርጋት ያቀረበችውን እቅድ ፈቅዳ የነበረ ቢሆንም፣ መልሳ ስባዋለች። በኳታር እና በኩዌት በኩል የመግባቢያ ሰነድ የፈረሙት እ.ኤ.አ. በ2000 ነበር። በስምምነቱ መሰረት ኩዌት ከኳታር ጋዝ ኢምፖርት ታደርጋለች። ሳዑዲ በግዛቷ በሚገኘው የውሃ ድንበር አቋርጦ የጋዝ ማስተላለፊያ ቱቦ እንዲዘረጋ ፈቃዷን የሰጠችው በ2003 ነበር።
ሳዑዲ በ2006 ኳታር ወደ ተባበሩት አረብ ኤሜሬት እና ኦማን ጋዝ ለማስተላለፍ ያቀረበችውን እቅድም ተቃውማለች። በአሁን ሰዓት ዶልፊን ፓይፕላይን ተብሎ ይታወቃል። በ2005 ሳዑዲ ከኳታር ወደ ተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ሊዘረጋ የነበረውን ድልድይ ግንባታ ተቃውማለች። በኳታር እና በባሕሪን በኩል የተዘረጋውም ድልድይ በገንዘብ እጥረት ቆሟል።
በ2002
ሳዑዲ አረቢያ ከዶሃ አምባሳደሯን አስወጥታለች። ይህ የሆነውም በአልጀዚራ በተዘገበ መረጃ መነሻ ነው።
በ2000
የሳዑዲ አረቢያ አልጋ ወራሽ አብዱላህ ቢን አብዱል አዚዝ በኳታር ዶሃ በተደረገው ኢስላሚክ ኮንፈረንስ ሳይካፈሉ ቀርተዋል። ይህንን ያደረጉት ኳታር ከእስራኤል ጋር የንግድ ልውውጥ በመጀመሯ ነው።
በ1996
ኳታር እና ሳዑዲ አረቢያ ድምበራቸውን ለማካለል ከስምምነት ደርሰው ተፈራርመዋል። በስምምነቱ መሰረት በሶስት አመት ክለላው የሚጠናቀቅ መሆኑ የተገለጸ ቢሆንም ሳይካለል ከአስር አመታት በላይ ሆኖታል።
በ1992
በድንበር በተነሳ ግጭት ሶስት ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።
ስንደቅ
Like this:
Like Loading...