Wednesday, 07 June 2017 13:16

ግብፅ በአባይ እናበድንበር ጉዳይ ሱዳንን ለማግባባት እየሞከረች ነው።  በሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች ልዩነታቸው እየሰፋ የሄደው ግብፅና ሱዳን ግንኙነታቸው ከመሻከር አልፎ የንግድ ልውውጣቸው ሳይቀር እየተቀዛቀዘ ሲሆን ከሰሞኑ የሁለቱ ሀገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ባደረጉት ውይይት ግብፅ ሱዳንን የማግባባት ስራን የሰራች መሆኗን የአሶሼትድ ፕሬስ ዘገባ አመልክቷል። የሱዳኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢብራሂም ጋሃንዶር በካይሮ የተደረገላቸውን የውይይት ግብዣ ውድቅ በማድረጋቸው ውይይቱ ተራዝሞ የነበረ ሲሆን ከሰሞኑ በታየው መለሳለስ ሚኒስቴሩ ካይሮ አምርተው ከግብፁ አቻቸው ሳሚህ ሻኩሪ ጋር ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል። ውይይቱን ተከትሎ የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ የተሰጠ ሲሆን፤ ሀገራቱ ያላቸውን ልዩነት በማጥበቡ ረገድ የተሄደበት ርቀት ብዙም ወደፊት ያልገፋ መሆኑን ይሄው የአሶሼትድ ፕሬስ ዘገባ ጨምሮ ያመለክታል።

በሁለቱ ሀገራት የተከሰተው ልዩነት በአንድ መልኩ ሱዳን “በግብፅ ተይዞብኛል” በማለት የይገባኛል ጥያቄ ከምታቀርብበት ደቡባዊ ግብፅ የሀላይብ ግዛት ጉዳይ ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ የአባይ ጉዳይ ነው። ሱዳን በማዕቀብ የተጎዳው ኢኮኖሚዋ እንዲያገግም ለማድረግ ሰፊ መሬቷንና ለሳዑዲና ለሌሎች አረብ ሀገራት በመስጠት የአባይ ውሃን ተጠቅመው የግብርና ስራን እንዲሰሩ የፈቀደች ሲሆን፤ ይህ ሁኔታ “የአባይን የግብፅ የውሃ ፍሰት ይቀንሳል” በማለት ግብፅ ግልፅ ተቃውሞን ስታሰማ ቆይታለች። ይህ የግብፅ ተቃውሞ በሱዳን በኩል ተቀባይነትን ማግኘት አለመቻሉ በሁለቱ ሀገራት መካከል ዲፕሎማሲያዊ መሻከሮች እንዲፈጠር ሌላኛው ምክንያት ተድሮ ይጠቀሳል።

 ሌላው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መሻከር ምክንያት ተደርጎ የሚጠቀሰው ሱዳን የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ የተለሳለሰና አቋምን መያዟ ነው። ግድቡን በተመለከተ ሱዳን ከግብፅ ጋር አንድ አይነት አቋም እንድትይዝ ለማድረግ የግብፅ ባለስልጣናት የነበራቸው ፍላጎትና ውትወታ ሳይሳካ ቀርቷል። ሱዳን እንደውም ከኢትዮጵያ ጋር በሰፊው በኤሌክትሪክ ሀይልና በባቡር መሰረተ ልማት ለመተሳሰር ሰፋፊ ፕሮጀክቶችን እየነደፈች ሲሆን አንዳንዶቹም ፕሮጀክቶች እውን ሆነዋል። 

ግብፅ የበሽርን መንግስት ለማስወገድ የዳርፉር ታጣቂ ሀይሎችን እየረዳች መሆኗን ሱዳን ክስ ከማሰማት ባለፈ የግብፅ ጦር መሳሪያዎችን ሳይቀር ከታጣቂ ሀይሎች በመማረክ የያዘች መሆኗን አስታውቃለች። ግብፅ በአንፃሩ የሱዳንን ሉአላዊነት የምታከብር መሆኗን በመግለፅ መረጃው ተራ ውንጀላ መሆኑን አስታውቃለች። ግብፅ በበኩሏ በግዛቷ ሰርገው እየገቡ የሽብር ጥቃትን ለሚሰነዝሩ ታጣቂ ሀይሎችን ካርቱም መጠለያ እየሰጠች ነው በማለት በአልበሽር መንግስት ላይ ክስ ስታሰማ ቆይታለች።

 የሁለቱ ሀገራት ፖለቲካዊ ውጥረት እየከረረ መሄዱን ተከትሎ የሱዳን መንግስት ወደሀገሩ በሚገቡት የግብፅ የግብርና እና የእንስሳት ተዋፅኦ ምርቶች ላይ እገዳ እስከመጣልም ደርሶ ነበር። እንደ አሶሼትድ ፕሬስ ዘገባ ከሆነ ሱዳን በዚህ ደረጃ ግብፅን ለመገዳደር የበቃችው ኳታርን ከጀርባዋ በማድረጓ ነው በማለት የግብፅ መገናኛ ብዙኋን ተደጋጋሚ ክስ ሲያሰሙ ቆይተዋል።

  ሆኖም ሰኞ ምሽት ሳዑዲ አረቢያ፣የተባበሩት አረብ ኤሜሬት፣ ባህሬንና ሌሎች የአረብ ሀገራት በድንገትና ባልተጠበቀ ሁኔታ ከኳታር ጋር ያላቸውን ማናቸውም ግንኙነቶች ማቋረጣቸውን ተከትሎ የሱዳን መንግስት ገለልተኛ አቋም የሚታይበት መግለጫ በማውጣት ሀገራቱ የተፈጠረውን ውጥረት በሰላምና በውይይት እንዲያበርዱ ጥሪ አቅርቧል።

 ለዓመታት ውስጥ ውስጡን ሲብሰለሰል የነበረው የመካከለኛው ምስራቅ ፖለቲካ አሁን የተለየ የሀይል አሰላለፍና ቅርፅ እየያዘ ሲሆን ከዚህ ቀደም በደሴት ይገባኛል ጥያቄ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ ውስጥ የገቡት ሳዑዲና ግብፅ በወራት ጊዜ ውስጥ ወደተለየ ወዳጅነት ውስጥ በመግባት በኳታር ላይ ያልተጠበቀ አቋምን ይዘዋል። ሆኖም ሳዑዲ በሱዳን የአባይን ውሃ በመጠቀም በሱዳን ሰፋፊ የእርሻ መሬትን ለማስፋፋት እያንቀሳቀሰች ያለውን ቢሊዮኖች ዶላር ግብፅ በአይነ ቁራኛ ስታየው ቆይታለች። በዚህ ጉዳይና በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ሱዳንን ለማግባባት ያደረገችው ሙከራ ሊሳካ አልቻለም። 

ስንደቅ