Wednesday, 07 June 2017 13:59

የአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ጉዳይ ዛሬም አሳሳቢ ሆኖ እንደቀጠለ ነው። የከተማዋ አስተዳደር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የነዋሪዎች የቤት ፍላጎት በከፊል እንኳን መመለስ የማይችልበት ሁኔታ ላይ ደርሷል። መሰራት ከሚገባው ስራ ይልቅ በተሰራው ጥቂት ስራ ላይ ሲነገር የነበረው የስኬት ታሪክ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያፈጠጠና እያገጠጠ በመጣው የመሬት ላይ እውነታ መፈተን ግድ ሆኖበታል። በመሬት እየታየ ያለው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ጉዳይ በሚገባ መፈተሸ ያለበት መሆኑን የሚያሳዩ እውነታዎች ፍንትው ብለው ቢታዩም፤ ዛሬም ቢሆን በሚመለከታቸው የመንግስት ኃላፊዎች የሚሰጠው መግለጫ ከስህተት መማር አለመፈለግን የሚያሳይ ነው።

  ተቋማዊ ችግርን እንደዚሁም የግለሰቦችን የአመራር ብቃትን ማነስን ከጠቅላላ ሀገራዊ አቅም ጋር ጭምር በማስተሳሰር የሚሰጡ ምላሾች እየጎሉ መጥተዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከዓመታት በፊት የነበሩ አሁንም እየተሄደባቸው ያሉትን የተደበላለቁ የቤቶች ልማት አካሄዶችን በተወሰነ መልኩ ለመመልከት ሞክረናል።

                                                                                                             የቤቶች የግንባታ ጉዳይ

የቤቶቹን የግንባታ ቦታ በተመለከተ በፕላን ደረጃ በዝርዝር ተቀምጦ የተመላከተ አሰራር አይታይም። የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ከተጀመረበት ዓመት ጀምሮ ቤቶቹ በምን አይነት ቦታ መገንባት አለባቸው የሚለው ጉዳይ ቁርጥ ያለ መልስ አግኝቶ አያውቅም። ግንባታው በተጀመረባቸው ዓመታት አካባቢ በርካታ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ይገነቡ የነበረው በመሀል ከተማ ያሉ ክፍት ቦታዎች እየተፈለጉ ነበር። በዚህም ለተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎት ይውሉ የነበሩ የመሀል ከተማ ቦታዎች በጋራ መኖሪያ ቤት ከመያዛቸው ጋር በተያያዘ በርካታ ቅሬታዎች ሲሰሙ ቆይተዋል። ከዚያ በኋላም በነበሩት ጊዜያት የአንዳንድ የመንግስት ተቋማት ይዞታዎችን በመረከብ በተወሰነ ደረጃም የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ሲካሄድ ቆይቷል። እንደ ምሳሌ ያህልም የቀድሞ የስንቅና ትጥቅ ማዕከል የነበረው ቦታ ጎተራ ኮንደሚኒየም ግንባታ እንዲከናወንበት ተደርጓል። የጎፋ ካምፕ ኮንደሚኒየምም በዚህ ተጠቃሽ ሊሆን የሚችል ነው። በእርግጥ የአዲስ አበባ ቦታን በአግባቡ ለመጠቀም በርካታ ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎችን ፈትሾ ጥቅም ላይ ማዋሉ ግድ የሚል ነው። የከተማው አስተዳድር ለልማት በሚል ሰፋፊ ቦታዎችን አጥሮ አስቀምጧል። ባለሀብቶችም ቢሆኑ ለዓመታት በመሃል ከተማ በርካታ ቦታዎችን አጥረው ያየዙበት ሁኔታ ይታያል። ይህ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ባሉ በርካታ ከተሞች ቀላል የማይባሉ የመንግስት መስሪያቤቶች ጥቅም ላይ ያልዋሉ ሰፋፊ ቦታዎችንም ይዘው ይታያል። ኢትዮቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና ሌሎች መሰል ተቋማት በተለያዩ አካባቢዎች ከሚጠቀሙበት በላይ ሰፋፊ የመሬት ይዞታዎችን በመያዝ ሊጠቀሱ የሚችሉ ተቋማት ናቸው። በኢትዮጵያ ከተሞች ዙሪያ ሰፊ ጥናት በማድረግ Ethiopia Urbanization Review በሚል ርዕስ ባለፈው ዓመት አንድ ሰነድ ይፋ ያደረገው ዓለም ባንክ  ይሄንን እውነታ ያስረገጠ ሲሆን፤ በዚህ ዙሪያም ባደረገው ጥናት በብዙ የኢትዮጵያ ከተሞች በርካታ ሰፋፊ ቦታዎች በመንግስታዊ ተቋማት የተያዙ መሆኑን አመልክቷል። ከተሞቹ አጠቃላይ ልማት ላይ ከዋለው ቦታ አንፃርም በእነዚህ ተቋማት ያለምንም ጥቅም በስፋት የተያዙት ቦታዎች ስፋት በቀላሉ የማይታይ መሆኑን ይሄው ጥናት ጨምሮ ያመለክታል። እነዚህ ቅሬታዎች መነሳታቸውና በመሀል ከተማም በቂ የግንባታ ቦታ ካለመኖሩ ጋር በተያያዘ  ያረጁና የጎሰቆሉ አካባቢዎች በአዲስ ገፅታ ለመቀየር በሚል በሚፈርሱ የመሀል ከተማ አካባቢዎች የጋራ መኖሪያ ቤቶች የመገንባት ስራም ሲካሄድ ቆይቷል። የጋራ መኖሪያ ቤቶቹን በመሀል ከተማ ለመገንባት ሲታሰብ የተጎሳቆሉ አካባቢዎችን በአዲስ ገፅታ ለመቀየር ከተያዘው እቅድ ጋር የቤቶችን ልማት ለማቀናጀት በማሰብ ሲሆን የከተማዋ ነዋሪዎችን ከመሀል ከተማ ማህበራዊ ኑሯቸው በማራቅ የሚፈናቀሉበትን ሁኔታ ለመቀነስ የተያዘውን እቅድ ታሳቢ በማድረግ ጭምር ነበር። ከዚሁ ጋር በተያያዘም  የልደታ መልሶ ማልማት እና ሌሎች መሰል የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ የዚህ እቅድ ውጤት ናቸው። ሆኖም ይህ እቅድ ከተወሰኑ የመሀል ከተማ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ሊያልፍ አልቻለም። ከዚህ ይልቅ በከተማዋ ዳርቻዎች የሚገነቡት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በስፋት መካሄድ ጀመረ። ይህም አዳዲስ የግንባታ ቦታዎችን ጠርጎ በማፅዳት  ሙሉ የመሰረተ ልማት ስራዎችን በአዲስ መልኩ ዘርግቶ እየተከናወነ ያለ ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓት የሚበዛው የጋራ መኖሪያ ቤት የሚገኘው በእነዚሁ የከተማዋ ዳርቻዎች ነው። ሆኖም በዚህ በኩል የሚታዩ በርካታ ችግሮችም አሉ። አንደኛው ችግር መኖሪያ ቤቶቹ ከከተማ እንዲወጡ ከመደረጉ ውጪ አብዛኛው የስራና ማህበራዊ ግንኙነት እንቅስቃሴ በመሀል ከተማ ላይ ተወስኖ መቅረቱ ነው። ወርሃዊ የመብራትና የውሃ ክፍያ ማዕከላት ሳይቀር ከመሀል ከተማው አልፈው ዳርቻውን አካባቢ ሊያዳርሱ አልቻሉም። በእነዚህ አካባቢዎች በቂ የትራንስፖርት አቅርቦትም  አይገኝም። የታክሲ አገልግሎትን በተመለከተ አዳዲስ መስመሮች ሲፈጠሩ የከተማዋ የትረንስፖርት ቢሮ ክትትል በማድረግ በአፋጣኝ ታሪፍ የማውጣት እንደዚሁም ክትትል የማድረግን ስራን ስለማይሰራ የከተማዋ ዳርቻ ነዋሪዎች ሁለት ኪሎ ሜትር ለማይሞላ መንገድ እስከ አምስት ብር ታሪፍ መክፈል ይጠበቅባቸዋል። አሁን በስራ ላይ ያለው የአዲስ አበባ አስረኛው ማስተር ፕላን ከተማዋ ቅይጥ መሪ ፕላንን(Mixed Master plan) የምትከተል መሆኗን ይገልፃል። ይህም ማለት ከተማዋ የምትለማው መኖሪያ ቤቶችና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች ባጣመረ መልኩ ነው ማለት ነው። ሆኖም ይህ ማስተር ፕላን በጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ላይ ሲተገበር አይታይም።

የግንባታ ጥራት ጉዳይ

የጋራ መኖሪያ ቤቶች የግንባታ ጥራት ጉዳይ ትላንትም ሆነ ዛሬም እየደጋገመ የሚነሳ ጉዳይ ነው። አንድ ሰው እጣ ከወጣለት በኋላ ቤቶቹ ወደ መኖሪያ ቤትነት ደረጃ ለማድረስ ለቅድመ ክፍያ ወጪ ካደረገው ገንዘብ በላይ ከፍተኛ ገንዘብ ማውጣት ይጠበቅበታል። ፍሳሽ ማስወገጃ እንደዚሁም የኤሌክትሪክ ስራዎችና የመሳሰሉት ግንባታዎች ከደረጃ በታች የሆኑና በተገቢው ባለሙያ መሰራታቸውም አጠራጣሪነት የሚታይበት ነው። በርካታ ግብዓቶችም ከደረጃ በታች (Substandard) ናቸው። ከዚሁ ጋር በተያያዘም በአንድ መልኩ ህብረተሰቡ እነዚህ ቁሳቁሶች ታሳቢ ተደርገው የቤቶቹ ባለእዳ ይሆናል፤ በሌላ መልኩ ደግሞ እነዚህን ግብዓቶች በሌላ ቁሱች ለመቀየር ተጨማሪ ገንዘብን ለማወጣት ይገደዳል። ከዚህም በተጨማሪ በህብረተሰቡ በኩል እስከዛሬም ድረስ ተቀባይነትን ሊያገኝ ያልቻለው አግሮስቶን የተባለው የግርግዳ ማካፈያ ግብዓት ነው። አብዛኞቹ ቤት ተረካቢዎች የቤት ማጠናቀቂያ ግንባታ ስራን (Finishing) ሲሰሩ የግርግዳ አካፋይ አግሮስቶኖችን ያስወግዳሉ። አግሮስቶን አካፋይ በህብረተሰቡ በኩል ተቀባይነትን አለማግኘቱ የታወቀ ቢሆንም አሁንም ድረስ ግንባታው ቀጥሏል። በዚህም ሀገሪቱም ሆነ ህብረተሰቡ ለከፍተኛ የሀብት ብክነት እየተዳረገ ይገኛል። በበርካታ አዳዲስ የጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ የሚታየው የተወገደ አግሮስቶን ክምር ሲታይ ይህች ሀገር በምን አይነት የሀብት ብክነት ውስጥ እንዳለች መረዳት ይቻላል። ህብረተሰቡ አግሮስቶንን ካልተቀበለው ምንም ማድረግ አይቻልም። ህዝቡን ለተጨማሪ ወጪ፤ የሀገሪቱም ሀብት ለብክነት ከመዳረግ ተቀባይነት ያላገኘን ግብዓት አለመጠቀሙ የተሻለ በሆነ ነበር። ግን አልሆነም።

የእፎይታ ጊዜውና የወለዱ ጣጣ

የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከሰማኒያ እስከ ዘጠና በመቶ የባንክ ንብረት ናቸው። የቤት እድለኛው እጣ ከወጣለት በኋላ ከባንክ ጋር የብድር ውል መዋዋል ይጠበቅበታል። ከሚከፍለው ቅድመ ክፍያ ውጪ ቀሪውን እዳ ለባንክ መክፈል ይኖርበታል። አንድ እድለኛ የኰንደሚኒየም እዳ ክፍያን ለመጀመር የአንድ ዓመት የእፎይታ ጊዜ ይሰጠዋል። ሆኖም ይህ የእፎይታ ጊዜ ከወለድ ነፃ የሚሆንበት ጊዜ አይደለም። ወለዱ መቁጠር የሚጀምረው የቤት ባለእጣው ከባንክ ጋር የብድር ውል ከተዋዋለበት ዕለት ጀምሮ ነው። በመሆኑም የእፎይታ ጊዜው ከወለድ ነፃ መሆኑን የማያጠቃልል በመሆኑ የቤት ባለቤቶች ቤታቸውን አድሰው መጠቀም ሳይጀምሩ የእዳ መጠናቸው እያደገ ይሄዳል። እዚህ ጋር ያለው ፈተና ደግሞ አንድ ሰው ከባንክ ጋር ውል የሚዋዋልበት ጊዜ እና በእጣ ያገኘውን ቤት ቁልፍ የሚረከብበት ጊዜ የተራራቀ መሆኑ ነው። አንድ ባለዕጣ ነዋሪ ቁልፍ የሚረከበው ምን አልባትም የቤቱ እጣ ከወጣበት ከስድስትና ከሰባት ወራት በኋላ ነው። አንዳንድ ጊዜም የእፎይታ ጊዜው ተጠናቆ ቁልፍ የሚረከብባቸውም አጋጣሚዎች አሉ። ይህ የሚሆነው ቤቶቹ በተገቢው መልኩ ሳይጠናቀቁ እጣ የሚወጣባቸው መሆኑ ነው። የቤቶች ልማት ኤጀንሲ ቤቶቹ ሳይጠናቀቁና በቂ የመሰረተ ልማት ሥራ ሳይከናወንባቸው እጣ በማወጣት ከባንክ ጋር ያለውን ግንኙነት በአስቸኳይ ወደ ግለሰብ ቤት ባለዕጣዎች ያዛውራል። ግለሰቦቹን ከባንክ እዳ ጋር ካቆራኘ በኋላ በእነሱ የእፎይታ ጊዜ በመጠቀም ቀሪውን የግንባታ ስራ ይሰራል። በዚህ መልኩ ገንቢው አካል በሁሉም አቅጣጫ የራሱን ጥቅም አስጠብቆ ቤቶቹን ለተጠቃሚው ያስረክባል።

የቁጠባው ፈተና

ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የዜጎች ከሚታይባቸው ሀገራት መካከል በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀስ ሀገር ናት። በአንድ ሀገር ኢንቨስትመንት የሚስፋፋው  ቁጠባ ሲዳብር ነው። ዜጎች የባንክ ቁጠባቸው እያደገ ሲሄድ የፋይናስ ተቋማት ለልማት የሚያበድሩት የገንዘብ መጠን እየጨመረ ይሄዳል። በኢትዮጵያ ካለው አጠቃላይ ዓመታዊ ሀገራዊ ምርት አንፃር የቁጠባው ምጣኔ ሲታይ ከሰሃራ በታች ካሉት ሀገራት አንፃር እንኳን ሲታይ በዝቅተኛ ደረጃ የተመዘገበ ነው። መንግስት የመጀመሪያውን አምስት ዓመት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ሲነድፍ የሀገር ውስጥ የዜጎች ቁጠባን ለማሳደግ እቅድ ነድፎ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። የዜጎችን ቁጠባ ለማሳደግ እገዛ ያደርጋሉ ተብለው ታሳቢ ከተደረጉት ስራዎች መካከል የህዳሴው ግድብ ቦንድ ግዢ እና የቤቶች ልማት ፕሮጀክት በዋነኝነት የሚጠቀሱ ናቸው። 2005 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ድጋሚ ምዝገባ በአዲስ መልኩ ሲካሄድ ከዘጠኝ መቶ ሺህ በላይ የአዲስ አበባ ነዋሪ በቤት ፈላጊነት ተመዝግበው የባንክ የቁጠባ ደብተር አውጥተዋል። በርካታ ከኢትዮጵያ ውጪ ያሉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ሳይቀሩ በየኢምባሲውና ቆንስላ ፅህፈትቤቱ በተካሄደው ምዝገባ በአርባ ስልሳ የቤቶች ፕሮግራም ተጠቃሚ ለመሆን በቁጠባ ስርዓቱ ውሰጥ የገቡበት ሁኔታም ታይቷል። ይህም ሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ የምታገኝበት አንዱ የገቢ ምንጭ ተደርጎም እንዲታይ አድርጎታል። እነዚህ መልካም ጅምሮች የሀገሪቱን ብሄራዊ የቁጠባ አቅም በአጭር ጊዜ ውስጥ እያሳደጉ ባለበት ሁኔታ ቤት ገንቢው አካል የገባውን ቃል የተስፋ ዳቦ ማድረጉ የበርካቶችን የቁጠባ ተነሳሽነት ቀዝቃዛ ውሃ እንዲፈስበት አድርጓል። በምዝገባው ወቅት በከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች ሲገቡ የነበሩት ቤቶቹን ገንብቶ የማስረከቢያ የጊዜ ሰሌዳዎች በተግባር ሊታዩ አልቻሉም። ከሁለት ሺህ አምስቱ የቤት ፈላጊዎች ምዝገባ በኋላ ከሁለት ጊዜ በላይ የቤቶችን እጣ ማውጣት አልተቻለም። ይህም ቢሆን የሃያ ሰማኒያ እና የአሰር ዘጠና የቤት እድለኞችን የሚመለከት እንጂ፤ የአርባ ስልሳ ተመዝጋቢዎችን የሚመለከት አልነበረም። በአሁኑ ሰዓት በ1997 ተመዝግበው ከአስር ዓመት በላይ ቤት በመጠበቅ ላይ ያሉ ከመቶ ሺህ በላይ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች አሉ። እነዚህን ዜጎች የቤት ባለቤት ማድረግ ካልተቻለ በስተቀር፤ ስለ ሁለት ሺህ አምስት አዳዲስ ቤት ፈላጊ ተመዝጋቢዎች የቤት ባለቤትነት የማድረጉ ጉዳይ የማይታሰብ ነው። እነዚህ ሁኔታዎች የበርካቶችን የቁጠባ ተነሳሽነት አውርዷል። የቤቶቹ ግንባታ የኤሊ ጉዞ መሆኑ ብቻ ሳይሆን መንግስትን አምነው የቤት ባለቤት ለመሆን ከአሰር ዓመት በላይ የጠበቁ ዜጎች ባለበት ሁኔታ በየጊዜው በሚቀያየር አሰራር ከመደበኛው አሰራር ውጪ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የሚሰጡበት ሁኔታ እየተስፋፋ መሄዱም አንዱ ቁጣባን እያወረደ ያለ ፈተና ነው። ለመምህራን፣ለጡረተኞች፣ የአገልግሎት ጊዜያቸውን ላጠናቀቁ የፓርላማ ተመራጮች፣ ለልማት ተነሺዎችና ለመሳሰሉት የህብረተሰብ ክፍሎች የጋራ መኖሪያ ቤቶች በተለያየ መልኩ ሲሰጥ ይታያል። ይህ ቀደም ሲል የቤቶች ፕሮግራም ሲነደፍ ታሳቢ ያልተደረገና የየጊዜውን ተለዋዋጭ ሁኔታ እየተከተሉ በመሄድ የሚተገበር አሰራር ነው። የከተማዋ መስተዳደር ቀደም ሲል የገባውን ቃል በተገቢው ባልፈፀመበት ሁኔታ ከተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት በሚያደርጋቸው አዳዲስ ውሎች በየጊዜው የሚፈጠሩ አዳዲስ ፍላጎቶችን ማስተናገድ መጀመሩ የተመዝጋቢ ቆጣቢዎችን ፍላጎት የሚያወርድ ሆኖ ይታያል። በመጋቢት 2007 ለህትመት ከበቃው መንግስታዊው ዘመን መፅሄት ጋር ቆይታ አድርገው የነበሩት የቀድሞው የከተማ ልማትና  ኮንስትራክሽን ሚኒስትር አቶ መኩሪያ ኃይሌ ቤት ለማግኘት ተመዝግቦ መቆጠብ ከጀመረው የህብረተሰብ ክፍል ውስጥ ቁጠባውን ያቋረጠ መሆኑን ያመለከቱበት ሁኔታ ነበር። በዚሁ ዙሪያ ለመፅሄቱ የሚከተለውን ሀሳብ ሰጥተው ነበር። ተመዝጋቢው ከ940 ሺህ በላይ ነው እንበል እንጂ ቀላል ያልሆነው ሰው ደግሞ ቁጠባ ያቋረጠ ነው። ቁጠባ እንዲያቋርጥ ሰውን አንመክርም። በተሟላ ሁኔታ እየቆጠበ ያለው ግን ከአራት መቶ እስከ አምስት መቶ ሺህ የሚሆነው ሰው ነው። ስለዚህ አስቀድሜ በጠቀስኩት መንገድ ስራችንን እስካከናወንን ድረስ በአጭር ጊዜ እነዚህ ዜጎች የቤት ባለቤት እንዲሆኑ ለማድረግ እየሰራን ነው።”  በአቶ መኩሪያ መረጃ መሰረት እሳቸው ይሄንን ቃል በሰጡበት 2007 መጋቢት ወር ላይ  ከ940 በላይ ከሆነው የቤት ፈላጊ ተመዝጋቢ ውስጥ በአግባቡ መቆጠብ የቻለው ከአምስት መቶ ሺ የበለጠ መሆን አልቻለም። ቀሪው ተመዝጋቢ ቁጠባውን አቋርጧል። ይህም ማለት በጊዜው ከአራት መቶ ሺህ በላይ ዜጋ የቤት ቁጠባውን አቋርጧል ማለት ነው። ይህ የሆነው የዛሬ ሁለት ዓመት በ2007 መሆኑ ሲታሰብ ከዚያ በኋላ ምን ያህል ሰው ተስፋ ቆርጦ ቁጠባውን እንዳቋረጠ ማንም ሰው እንዲሁ ሊገምተው የሚችለው ነው። በዜጎች ቁጠባ እያቋረጡ መውጣት አሳሳቢ ቢሆንም በ2005 የቤቶች ምዝገባ ሲካሄድ የአዲስ አበባ ነዋሪነት ጊዜያቸው ሁለት ዓመት ያልሞላቸው በመሆኑ ምዝገባው ያመለጣቸው የመንግስት ሰራተኞች በየመስሪያቤታቸው ምዝገባ እንዲያካሂዱ እድሉ ቢሰጥም የተመዘገበው ነዋሪ ሰራተኛ ቁጥር ያን ያህል አመርቂ አልነበረም። በቤቶች ፕሮግራም ዙሪያ የታየው የአሰራር ዝርክርክነት፣ሙስና፣ የሀብት ብክነት፣ብሎም የተስፋና ተግባር አለመገናኘት ዜጎችን ብሎም በመውተርተር ላይ የነበረውን የሀገሪቱን ብሄራዊ የቁጠባ ሂደት በብዙ መልኩ ጎድቶታል። ይህ ችግር ባልተፈታበት ሁኔታ ዛሬም አዳዲስ የቤት ፍላጎቶች በመጨመር ላይ ናቸው። የፍላጎቱና አቅርቦቱ ክፍተት  እየሰፋ መሄድ ደግሞ ነዋሪዎች ለቤት ኪራይ የሚያወጡትን ወጪ ከጠቅላላ የነፍስ ወከፍ ወጪያቸው ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ እንዲይዝ እያደረገው ይገኛል። ይህን ችግር በቀላሉ የሚፈታበት አቅጣጫ ተቀምጦ ወደ ተግባር መግባት ካልተቻለ በስተቀር ከማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ባለፈ ፖለቲካዊ ፈተናም ሆኖ መምጣቱ አይቀሬ ነው። አሁን ያለው የቤቶች ልማት አካሄድ የትም እንደማያስኬድ ካለፉት 12 ዓመታት በላይ ሌላ አስርና ሃያ ዓመት መጠበቅ የሚያስፈልግ አይሆንም። የቤቶች ልማት ፕሮግራምን ከማኔጅመንት ኮንትራት ጀምሮ የሀገር ውስጥ ተቋራጮች ከውጭ ባለሀብቶች ጋር በንዑስ ተቋራጭነት በመሳተፍ ልምድ የሚቀስሙበት አሰራር መፈተሸ መቻል አለበት። አሁን የሚታየው የጋራ መኖሪያ ግንባታ ጊዜ የሚፈጅ፣ ከፍተኛ የሀብት ብክነትን እያስከተለ ያለና ይህ ነው ተብሎ ሊነገር የማይችል ዘርፈ ብዙ የጥራት ችግር የሚታይበት ነው።

ስንደቅ