June 7, 2017
ማክሰኛ ግንቦት ፳፱ቀን ፪ሺህ ፱ ዓ.ም.                         ቅፅ፭፣ ቁጥር  ፲፯
ዐማራው በባህሉ፣ በሥነ-ልቦናውና በፖለቲካ ታሪኩ እንዲሁም በሚጋራቸው የወል ዕሴቶቹ፣ በእሱነቱና በኢትዮጵያዊነቱ መካከል የተሰመረ ልዩነት ባለመኖሩ፣በዘር ጠላትነት ተፈርጆ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀል ሲፈጸምበት ፣ወንጀሉ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ላይ የሚፈጸም ነው በማለት፣ለምን? እንዴት? ብሎ ለመጠየቅ ከሁለት ዓሥርተ ዓመታት በላይ እንደፈጀበት በግልጽ ይታወቃል። ይህም ዘረኛው የትግሬ ወያኔ ቡድንና አጋሮቹ ከአምስት ሚሊዮን በላይ ዐማሮች ከምድረ ኢትዮጵያ እንዲጠፉ ሠፊ ዕድልና አጋጣሚ እንዲያገኙ ረድቷቸዋል። ይህን ያህል ቁጥር ያለው ከትግሬ፣ ከሶማሌ፣ ከጉራጌ፣ ከሲዳማ፣ ከወላይታ ቢጠፋ ሁሉም የነገዱ አባሎች ጠፉ ማለት ነበር። ዐማራው ይኸን ያህል ቁጥር የሰው ኃይል ጠፍቶበት፣ ምንም ያልመሰለው ከጣና ሐይቅ በጭልፋ ውኃ የመቀነስ ያህል ሆኖ በመታየቱ፣ የሁሉንም የዐማራውን ነገድ ጆሮ ሊስብ እንዳላስቻለ ይታመናል። ይህ ባይሆን፣ የወያኔው ፓርላማ በራሱ አደባባይ  ሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን ዐማራ ስልታዊ በሆነ መንገድ ጠፍቷል ብሎ ሲነገረን፣ ዐማራው ቀፎው እንደተነካበት ንብ ሆ! ብሎ በአንድነት ይነሳ ነበር። ያለመነሳቱ ምክንያቶች የመጀመሪያው እንደ ኢትዮጵያዊ እንጂ፣ እንደዐማራነት አለማሰቡ ነው። ሌላው የቁጥሩ ብዛት፣ «ፀጉራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል» አይነት ሆኖበት እንደሆነ ይታመናል።
ይኸም ሁሉ ሁኖ፣ የትግሬ ወያኔ ቡድን ሥልጣን ከጨበጠ በኋላ፣እንደ መንግሥት ማሰብ አልቻም። የሁሉም ኢትዮጵያ ነገዶች ገዥዎች መሆናቸውን አለማመኑም። ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ የመግዛት ዓላማ  ዓላማችን ብለው አልያዙትም። ዓላማቸው ኢትዮጵያን መበታተን በመሆኑ፣በኢትዮጵያዊነታቸው የሚያምኑ ነገዶችን፣ ቡድኖችንና ግለሰቦች እያሳደዱ ከምድረ ገጽ ማጥፋት ሥራዬ ብለው ይዘውታል። በአስተሳሰባቸው እሳ እና ይሉታ የሚባሉ ዕሴቶች የሏቸውም። ዐማራን ከቻሉ ከምድረ-ገጽ የማጥፋት፣ ካልሆነ በሁሉም መልኩ አናሳና የበታች አድርጎ የመግዛት ፍልጎታቸው የደነደነ ነው።  በመሆኑም ዐማራውን ከኢኮኖሚ እስከ ሕይዎት ነጠቃ፣ የሥራ ዕድል ከመንፈግ እስከ አገር ማሳጣት፣ ከመሬት መንጠቅ እስከ መዋለድ መክልከል ወዘተ ተደራራቢና ተከታታይ ወንጀል ዓይን ባወጣ መልኩ  ፈጽመውበታል። እየፈጸሙበትም ነው። ይህ ተደራራቢ ወንጀም መበራከት ፣ ለካ እንድንጠፋ የተፈረደብን ዐማራነትና ኢትዮጵያዊነትን  አዋህደን በመያዛችን ነው? ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት በቅድሚ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ የሚያምነውን ነገድ ማጥፋት የመጨረሻው መጀምሪያ ይሆናል ብለው አስበው ነው? የሚል ጥያቄ የዐማራው ልጆች እንዲያነሱ ግፊት እያሳደረ ነው።
በተፈጠረው ግፊትም ፣ዐማራው ኅልውናውን አስጠብቆ ማንነቱን ለማስቀጠል ያለው ብቸኛ አማራጭ ፣በማንነቱ ዙሪያ መደራጀት የሚለው ሆነ። በዚህ እሳቤ መሠረትም የተለያየ ዕድገት፣ መጠንና የአደረጃጀት ቅርጽ የያዙ ድርጅቶች በየአቅጣጫው ድምፃቸውን ማሰማት ጀምረዋል። ይህ መልካም መነቃቃትና ጅምር ነው። የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ገዥ ሀሳብ በነገድ ዙሪያ የሚሽከረከር በመሆኑ  ዐማራው ከዚህ ነባራዊ ሁኔታ ውስጭ ሊያደርገው የሚችል ግልጽ አመክንዮ ካለመኖሩም ሌላ፣ ሌሎች በነገዳቸው ዙሪያ ስሰባሰቡ በአውራ ጠላትነት ፈርጀው  እያጠፉት ያለው እርሱን በመሆኑ፣ በማንነቱ ዙሪያ  መሳባሰብ ምርጫው ሳይሆን ግዴታው  ሆኗል።   ይህም ዐማራውም፣ ከቁጥሩና ከደረሰበት ግፍና በደል አኳያ፣ ካንድ በላይ ድርጅቶች ቢኖሩት የሚደንቅ አይሆንም። ከአንድ በላይ ድርጅቶች ኖረው፣ ለዐማራው ድምፅ ቢሆኑ፣ በዙ፣ ለምን እንዴት ሆኖ ሊያሰኝ የሚችል አይሆንም። ግፉ በደሉ ብዙ ነውና!
በአንፃሩ የተለያዩ ድርጅቶች በዐማራው ስም መደራጀት፣ በዕውነት፣ ለዕውነት ለዐማራው ብሦት የቆሙ ከሆነ፣ የዐማራውን ችግር በዝምታና በይሁንታ የዓለም ማኅበረሰብ እንዲጠፋ ጆሮውን የነሳውን ክፍል ደጋግሞ በመጮኽ አድማጭ እንዲያገኝ አዎንታዊ ሚና ይጫወታል። ስለሆነም በዐማራው ስም ከአንድ በላይ ድርጅቶች መደራጀት ከዚህ አንፃር የሚደገፍ እንጂ፣ የሚነቀፍ አይሆንም።
ክፋት የሚኖረው እና የሚነቀፈው፣ እነዚህ ድርጅቶች የሚያራምዱት ዓላማ ምንድ ነው? የተደራጁበት መሠረታዊ ምክንያቶች ምንድናቸው?፣ የተደራጁት በራሳቸው አነሳሽነት ለዐማራው ተቆርቁረው ነው? ወይስ ከኋላ የሚገፋቸው ፀረ-ዐማራ ቡድን አለ? የተደራጁት ጠንካሮቹን የዐማራ ተቆርቋሪ ድርጅቶች እንቅስቃሴ ለማኮስመንና ለማክሰም ነው? ወይስ ሌላ ለሚሉት ጥያቄዎች የሚያስገኙት መልስ አሉታዊ ሲሆን ብቻ ነው።  በዐማራ ስም የተደራጁት ድርጅቶች አንድ ሁኑ ከመባሉ በፊት ለእነዚህ ጥያቄዎች ተገቢና የማያሻማ መልስ መገኘት አለበት። ለጥያቄዎቹ የሚገኙት መልሶች ሁሉም ወይም ጥቂቶቹ በሐቀኞቹ የዐማራ ልጆች የተደራጁ ናቸው፤ ዕውነተኛ የዐማራው ሕዝብ ተቆርቋሪዎች ናቸው፤ የሚለውን መልስ ከጥርጣሬ ውጭ በሆነ መንገድ ማረጋገጥ ከተቻለ፣ ሁለመናዊ ኃይላችሁ ጎልብቶ፣ ወያኔን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከኢትዮጵያ አሽቀንጥሮ ለመጣል መተባበር ሳይሆን፣ አንድ መሆን አለባችሁ የሚለው ከጥርጣሬ ባሻገር፣ በተግባር የሚገለጽ መሆን ይኖርበታል። ማን ምን እንደሆነና ለምን ዓላማ እንደተደራጀ በቅጡ ሳይለዩ፣ በዐማራ ስም ተደራጅተናል ስላሉ ብቻ አንድ ሁኑ የሚለው ግፊት የጤና አይሆንምና ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል።
ከፍ ሲል ለመጥቀስ እንደተሞከረው፣ ለተነሱት ጥያቄዎች አዎንታዊ የሆነና ሁሉም ድርጅቶች ዕውነተኛ የዐማራው ኅልውና ተቆርቋሪዎች ከሆኑ፣ የዓላማ ልዩነት ከሌላቸው፣ ካለማንም ተጽዕኖና ጎትጓች አንድ ጠናካራ ድርጅት ለመፍጠር የሚከለክላቸው አንዳች ምክንያት አይኖርም። ይህ ግን የሚረጋገጠው በሂደት በጊዜ ፍሰት፣ በሚሠሩት ተጨባጭ ሥራዎች ነው። ድርጅቶቹ በአማርኛ ቋንቋ ፕሮግራማቸውን በማዘጋጀታቸው፣ ዓማርኛ ቋንቋ በመናገራቸው፣ በዐማራው ስም ነው የተደራጀነው በማለታቸው፣ ዕውነተኛ የዐማራው ኅልውናና ማንነት ጠበቃዎች ናቸው ማለት አይቻልም። ከኢሕአፓ፣ከመኢሶን፣ ከኢጭአት፣ወዘተ አመሠራረትና የትግል ጉዞ ብዙ የምናማራቸው ነገሮች አሉ። ሁሉም ስማቸው ተግባራቸውን የሚገልጽ አልነበሩም።
እነዚህ በዐማራ ስም ተደራጀን የሚሉ ድርጅቶች የራሳቸውን ዓላማ ዕውን ለማድረግ የተጨበጠ ሥራ ሠርተው ለዐማራው ያላቸውን ወገንተኛነት ሳያሳዩ፣ ተመሠረትን ባሉ ማግሥት ለአንድነትና ለውኅደት ተደጋጋሚ ጥሪ ከማቅረባቸው ባሻገር፣ ማስፈራሪያና ዛቻ የቀላቀለ ማስጠንቀቂያ ሲሰጡ ይደመጣሉ። ምንነታቸውን በተግባር ሳያሳዩ  የአንድነት ጥያቄ የሚያነሱ ቡድኖች ጥያቄአቸው ላይ ላዩን ሲመለከቱት ተገቢ ይመስላል። አንድነት ለሁሉም ነገር የሚበጅ፣ የጥንካሬና የማድረግ ብቃትን የሚያረጋግጥ በመሆኑ የሚጠላ አይደለም። ይህም በመሆኑ ለአንድነት ጥያቄ ማቅረቡ መልካም ነው። ግን አንድነት ከማን ጋር? አንድነት ለምን፣ አንድነት መቼ? ለሚሉት ጥያቄዎች ሁነኛና ትክክለኛ መልስ ሳይዙ አንድ መሆን ለውጤት ያበቃል ተብሎ አይታመንም።
እንደዛሬው በነገዶች መካከል ያለው ልዩነት ጦዞ ጣራ ሳይነካ፣ በኢትዮጵያ ተመሥርተው የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ያደረጓቸው የመዋሐድና የአንድነት ሙከራዎች በተደጋጋሚ ተሞክረው ረጅም ርቀት ሳይጓዙ መበታተናቸውን እናውቃለን። ተባበረን፣አንድ ሆን ካሉ በኋላ ረጅም ርቀት ሊጓዙ ቀርቶ፣ የተፈራረሙበት ቀለም ሳይደርቅ በሚያስችል ፍጥነት ተለያይተው በጠላትነት  ግራና ቀኝ ቆመው፣አዳኝና ታዳኝ ሆነው የምናያቸው አያሌ ስብስቦች፣ መሠረትነው ላሉት አንድነት፣ ኅብረት፣ ቅንጅት፣ ውኅደት፣ ጥምረት፣ ትብብር ወዘተ— መፈራረስ መሠረቱ ከላይ ለተነሱት ጥያቄዎች ተገቢ መልሶች ሳይዙ፣ በይሁን ይሁን እና በአንዳንዶች ቀና አመለካከት በሌሎች መሠሪ ተንኮል የተነሳ፣ ውኅደቱ፣ ቅንጅቱ፣ ኅብረቱ፣ ጥምረቱ፣ አንድነቱ ወዘተ—  ውኃና ዘይት በመሆኑ የተነሳ እንደሆን ከሂደቱ መገንዘብ ይቻላል።
በአገራችን ፖለቲካል ታሪክ ውስጥ በዚህ መልክ አንድነት ከማን ጋር? አንድነት መቼ? አንድነት ለምን? የሚሉትን ጥያቄዎች ሳያብላሉ ፣ውኅደት፣ ቅንጅት፣ ኅብረት፣ ጥምረት፣ትብብር ወዘተ— መሠረትን ብለው ዓመታት ቀርቶ ወራት ሳይጓዙ የተበተኑት ብዙዎች ናቸው። ለአብነት ያህል፦
1 ኢማሌድኅ (የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች ኅብረት) ይህ ማኅበር የመኢሶን፣ የወዛደርሊግ፣ የማሌሪድ፣ የኢጭአት፣እና የአብዮታዊ ሠደድ ድምር የነበረ መሆኑ ይታወቃል።  ተፈጠረ የተባለው ኅብረት ብዙም ሳይጓዝ እርስ በራሳቸው መፋጀታቸውን የምናስታውሰው በሐዘን ነው። አቶ ተስፋዬ መኮንን የተባሉት «ይድረስ ለባለታሪኩ» በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፍ፣ በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው ለመወያየት ያልቻሉ አብዮታውያን በመንግሥቱ ኃይለማርያም እስር ቤት ባንድነት ታስረው ባንድ ጉድጓድ መቀበራቸውን በቁጭት የገለጹት የሚታወስ ነው።
2 ኢሕአፓ ፦ ኢሕአፓ ፣ የአብዮት ቡድን (የነጌታቸው ማሩ ቡድን)፣ የዴሞክራሲያ ቡድን (ይህ የነፀጋየ ገብረመድኅን፣ዘሩ ክሸን፣ ፀሎተ ሕዝቀየል፣ ተስፋዬ ደበሳይ እና ዮሐንስ ብርሃኔ ቡድን መጠሪያ ነው) ፣ የነሙሄ አብዶ ቡድን እና የነአሰፋ እንደሻው ቡድን } በመዋሐድ  የተመሠረተ መሆኑ በግልጽ ይታወቃል። ይህ ቡድን ግን በተከተለው የከተማ ትጥቅ ትግል በደረሰበት የቀይ ሽብር ምት፣ ያስነሳው ክርክር አባላቶቹን ከሁለት መሰንጠቁና የድርጅቱን መሥራቾች ጌታቸው ማሩን፣ ይርጋ ተሰማ(መዝሙር) ወዘተ በራሱ በኢሕአፓ አመራሮች መገደላቸው ይታወሳል። በዚህ ሂደትም ድርጅቱ ከፊሉ ወደ ውጭ ሲሰደድ፣ አብዛኛ «አብዮቴ ማሪኝ» ብሎ ወደ ሰላማዊ ሕዎቱ መግባቱና በፀጋየ ገብረ-መድኅን የሚመራው በቋራ ትግሉን መግፋቱ ይታወቃል። ውጭ የተሰደደውም ኢሕአፓ እና ዴ-ኢሕአፓ ተብሎ ከሁለት መከፈሉ ግልጽ ነው።
3 ኢሠፓአኮ (ኢሠፓ)፦ ይህ ድርጅት ከኢማሌድኅ መበተን በኋላ ሕይዎታቸውን ለማትረፍ በፈለጉ የመኢሶን፣ የወዛደር ሊግ፣ የማሌሪድ እና የፖለቲካ ሥጣኑን የአንበሣውን ድርሻ የያዘው አብዮታዊ ሰደድ ያልተባረከ ጋብቻ የተመሠረተ እንደሆነ ይታወቃል። ኢሠፓ  በዚህ ምክንያት ወጥና ውኅድ ድርጅት  አልነበረም። በመሆኑም በድርጅቱ ውስጥ ታቅፈው የነበሩት ግለሰቦች፣ የየድርጅቶቻቸውን አቋም ይዘው ሲጓዙ የነበሩ እንጂ፣ የኢሠፓ ዓላማ አራማጆች አልነበሩም። ለወያኔ ድል አድራጊነትም፣ ይህ በኢሠፓ አባላትና አመራሮች መካከል የነበረ የመሥመርና መሰል የሥልጣን አጣን ጥያቄዎች አባላቱንና ሕዝቡን በአንድነት አስተባብሮ ለመምራት ያለመቻል ውጤት አንዱና መሠረታዊ ምክንያት ነበር።
4 አማራጭ ኃይሎች ከአሥራ ስድስት በላይ የነገድ ድርጅቶችን አካቶ አዲስ አበባ ጊዮን ሆቴል በ1985 ዓም የተመሠረተና በዶ/ር በየነ ጴጥሮስ ይመራ የነበረው የድርጅቶች ስብሰብ ነበር። ይህም ስብስብ ለረጅ ጊዜ አለመቆየቱ ይታወሳል። በወቅቱ ጠካራ በነበሩት ድርጅቶች ላይ ወደፊት እንዳይገፉ ጥላውን መጣሉ ግን አይዘነጋም።
5 ኅብረት፣ኢሕአፓን፣ መኢሶንን፣ታንድ እና ኦብኮን ጨምሮ በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙትን  ከአሥር በላይ ኅብረብሔራዊና ብሔራዊ ድርጅቶችን አካቶ የያዘ ስብስብ እንደነበር ይታወሳል። ይህም ከ1997 ዓም ምርጫ ዘመቻ በኋላ  ዕድሜ እንዳልነበረው ይታወቃል።
6 በኦነግና በቅንጅ መካከል ተመሠረተ የተባለው ኅብረት፣ ከሣምንታት ጩኸት በኋላ ስለመኖሩ ቀርቶ፣ ስለመመሥረቱ መናገር የተቻለበት ሁኔታ እንዳልነበር የሚታወስ ነው።
7 ኢዴኃቅ የተሰኘው በርካታ ድርጅቶችን አሰባስቦ የነበረው ኅብረት ፣ በተመሳሳይ ሁኔታ የውኃ ሽታ ሆኖ እንደቀረ አይዘነጋም።
8 ግንቦት 7 በከማል ከልቹ ከሚመራው ኦነግ ጋር፣ ከዴምት፣ከዐማራ ኃይል ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ ወዘተ ጋር ተፈጠሩ የተባሉት ጥምረቶችና ኅብረቶች የት እንደደረሱ በተጨባጭ እያየን ነው። ሁሉም ተስማሙ ከመባሉ ተጣሉ፣ ተበታተኑ የሚለው እየቀደማቸው አንዳችም ለውጤት የሚያበቃ ሥራ ተሠርቶ ሕዝባችን የኅብረትን፣ የቅንጅትን፣ የአንድነትን፣ የውኅደትን ፋይዳ ከንድፈ-ሀሳብ ባሻገር በተግባር ሳያይ ዘመናት መቆጠራቸው ዕውነት ነው። እናም  ተደጋግሞ በተሄደበትና ምንም ዓይነት አዎንታዊ የሆነ ገንቢ ውጤት ባልታየበት መንገድ ደጋግመን እንድንጓዝ የሚገፋፉ ቡድኖች፣ለአንድነችን የጓጉ ሳይሆኑ፣ ልክ እንዳለፉት ሁሉ ውድቀታችን የናፈቃቸው መሆን አለባቸው።
ካሁን በኋላ ለትብብር፣ ለኅብረት፣ ለጥምረት፣ ለቅንጅት፣ ለውኅደትና ለአንድነት የሚቀርቡ ጥያቄዎች ከላይ ለተነሱት ጥያቄዎች አዎንታዊ የሆነ መልሶች ከሚያስገኙት ጋር መሆን እንዳለበት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
አንድነት ከማን ጋር? ለሚለው ጥያቄ፣ በወረቀት ላይ የሰፈረ የዓላማ አንድነት ሳይሆን፣ በተግባር የታዬ መሆን ይኖርበታል። አንድነቱን የምንሻው «ትንሽ አሻሮ ይዘን ወደ ቆሎ በመጠጋት» የሌለ ሥልጣን ለመጋራት መሆን የለበትም። ሥልጣን ወይም ኃላፊነት በድርጅት ሳይሆን፣ በግለሰባዊ ችሎታ፣ ዕውቀት፣ ጽናት፣ ቁርጠኝነት ተመዝኖ ሚዛን የሚደፋው እንዲይዝ እንጂ፣ የድርጅት መሪ በመሆን የሚያዝ መሆን አይኖርበትም። ለመዋኃድ፣ለመተባበር ወዘተ በሚሹት ድርጅቶች መካከል ተመጣጣኝ የሆነ ሕዝቡን የማደራጀት፣ ሁለንተናዊ ዐቅም የመገንባት፣ ሥራ የሠሩ መሆናቸው ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት። በጥቅሉ ለአንድነት፣ ለትብብር በሚፈላለጉት ድርጅቶች ወይም ቡድኖች መካከል የሤራ፣ የማዳከምና የጠነከረውን ለማፍረሻ ስልት መጠቀሚያ ለማድረግ ያላሰቡ፣ የሁሉም ድርጅቶች መሪዎች ቆምንለት ለሚሉት ዓላማ የማያወላውል ቁርጠኝነት ያላቸው፣ ይህም ባለፉት ዘመናት በተግባር ያስመሰከሩ እና ከዋናው ሁሉም ጠላታችን ነው ብለው ከፈረጁት ወገን ጋር ምንም ኦይነት ንክኪ የሌላቸው መሆኑ በተጨባጭ ሥራ ያሳዩ መሆን ይጠበቅባቸዋል።
አንድነት መቼ? የሚለው ጥያቄ የጊዜን አስፈላጊነት የሚያመላክት ነው። ለሁሉም ነገር ማንነትና ምንነት ጎልቶ የሚታዬው በጊዜ ነው። ጊዜ የሁሉንም ነገሮች ዕውነተኛ ቅርጽና ይዘት፣ ፍሬ ነገርና ክስተት ማሳያ ነው። ስለሆነም ተደራጀን ያሉ ድርጅቶች ማንነትን ለማወቅ ፕሮግራማቸውና እነሱ እንዲህ ነን ማለታቸው በቂ አይሆንም። ዕውነተኛ ማንነታቸውን በጊዜ ሂደት፣ በፈታኝ ሁኔታዎች በሚወስዱት አቋም ሊረጋገጥ ይገባል። ከአቶ ልደቱ አያሌውና ከአቶ አየለ ጫሚሶ የምንማረው ይኸኑ የጊዜን አስፈላጊነት ነው። ከትግሬ ነፃ አውጭ ግንባር እና ከትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጭ ግንባር ውኅደት እና ከተገኘው ውጤት የምንማረው ሌላ አሳዛኝ ጉዳይ እንዳለ ልብ ልንል ይገባል። እንዋሐድ፣ ኅብረት እንፍጠር፣ እንተባበር ከማለታችን በፊት፣ ማንነታችን ሕዝባችን በግልጽ ሊያውቅበት የሚችለው ጊዜ ሊሰጠው ይገባል። «የነቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ» እንዳይሆን በማስተዋልና በርጋታ ልናየው ይገባል። ኋላ ወጭት ጥዶ ማልቀስ እንዳይሆንብን፣ አስቀድመን ከእርቀት ነገና ከነገ ወዲያ ሊፈጠሩ የሚችሉ ክስተቶችን ካለፉት ጋር በማገናዘብ ወደ ተፈላጊው ግብ ሊያመራን የሚችለውን መንገድ እንድንከተል ለምንሰጣቸው ውሳኔዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል።
አንድነት ለምን? የሚለው መልሱ የሚያሻማ አይሆንም። አንድነት የብቃት፣ የሁለንተናዊ ኃይል መገለጫ፣ የማድረግ ብቃት መለኪያ ወዘተ በመሆኑ አስፈላጊነቱ አጠያያቂ አይሆንም። ከዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ አንድነቱን የፈለጉት ኃይሎች እነማን ናቸው? ከኋላቸው ማን አለ? አንድነቱን የፈለጉት በእርግጠኝነት ከአንድነቱ የሚመነጨው ሁለንተናዊ ጉልበት ለተፋጠነ ድል ያደርሰናል ከሚል ነው? ወይስ በአንድነት ስም ገብቶ የጠነከረውን ለማላላት፣ ሰላሙን ለማናጋት፣ ጥቃቅን ልዩነቶችን በማጉላት ነባር አንድነቱን ለማሳጣት? በአንድነቱ ስም በአቋራጭ የሌለ ሥልጣን ባለቤት ለመሆን?  የሚሉት ሊጤኑ ግድ ይላል።
በግልጽ እንደሚታወቀው፣ አንድ ቡድን ከሌላ ይመሳሰለኛ ብሎ ከሚያስበው ጋር የአንድነት፣ የውኅደት፣ የትብብር፣ የቅንጅት ወዘተ ጥያቄ የሚያቀርበው ከሚከተሉት ምክንያቶች አንዱን ወይም ካንድ በላይ የሆኑትን ለማግኘት ነው።
አንደኛ፦ የሚፈጠረው ወይም የሚመሠረተው ውኅደት፣ አንድነት፣ ኅብረት፣ ቅንጅት፣ወዘተ ሼር የሌለበትና በሐቅ ላይ የተመሠረተ ከሆነ፣ ወይም የሚሆን ከሆነ፣ ወደ ተፈላጊው ግብ በአጭር ጊዜ መድረስ የሚያስችል መታለፍ የሌለበት ጉዳይ መሆኑን በማመን፣ ድርድሩ በዓላማ ላይ እንጂ፣ ሌሎች ጉዳዮች በችሎታ ላይ የሚመሠረቱ መሆኑን ሁሉም ሲገነዘቡና ፣ሁሉም የችሎታችን እናገኛለን ብለው ሲረዱ የሚደረግ ስምምነት አዎንታዊና ዓላማን ከማሳካት ጋር የተቆራኘ በመሆኑ ሁሉም የሚሹትን ሳይሆን የሚችሉትን የሚያገኙበት ነው።
ሁለተኛው፦ ስምምነት፣ አንድነት፣ ወዘተ የሚሹ ቡድኖች፣ በመካከላቸው የኃይል ሚዛን ተፈጥሮ አንደኛው ሌላውን ከጨዋታ ውጭ የማድረግ አቅም የሌላቸው መሆኑን ሁለቱም ሲገነዘቡ፣ ሰጥቶ በመቀበል የጋራ ግባቸው ወደ ሆነው ተግባር በአንድነት ፊታቸውን ማዞር እንዳለባቸው ሲረዱ የሚመሠርቱት ነው። ይህም አቅምን አውቆና ተገንዝቦ ወደ ጋራ ግብ ለመድረስ የሚያስችል በመሆኑ አዎንታዊ ነው። ስምምነቱ ሰጥቶ የመቀበል እና በዓላማ አንድነት ላይ የተመሠረተ ነውና።
ሦስተኛ፦ ለትብብር፣ ለውኅደት፣ ለአንድነት ከሚጠይቁት ቡድኖች አንደኛው በራሱ እንቅስቃሴ ከሚፈልገው ደረጃ መድረስ የማይችል መሆኑን ሲገነዘብ፣ ያለበትን ድክመት በሚመሠርተው ኅብረት ወይም አንድነት ለመወጣት ሲል የሚያቀርበው የአንድነትና የእንተባበር ጥሪ ነው። ይህም  ታይቶ ጠፋ ላለመባል፣ በዚያውም በሚፈጠረው ኅብረት፣ አንድነት ውስጥ የተወሰነ ቦታ አገኝቶ ኅልውናውን ለማስቀጠል በማሰብ፣ የእንተባበርን ጥያቄ አበክሮ ያነሳል። ይህ ከድክመት የሚመጭ በመሆኑ ለሚፈጠረው ኅብረት ወይም አንድነት የችግር ምንጭ ከመሆን አይዘልም። በቅንጅት ውስጥ ከተካተቱት አንዱ የነበረው ቀስተ ዳመና ያደረገው ይኸን ነው። ለጠንካሮቹ መኢአድና ኢዴፓ-መድኅን የውድቀት ምንጭ እንደሆነ ይታወቃል።

አራተኛ፦ አንደኛው ቡድን ወይም ከአንድ በላይ የሆኑት፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ተቀባይነት ያገኘውን ድርጅት ጠልፎ ለመጣል እንዲያመቸው፣ በእንደራደር ስም ወይም ስበብ የዚያን ድርጅት ልዩ ልዩ መረጃዎች፣ የጥንካሬና የድክመት ምንጮች የሆኑትን ለይቶ ለማወቅ ይጠቀሙበታል። በዚህም ድርጅቱ ከየትኛውም አቅጣጫ ሊገጥሙት የሚችሉትን መሰናክሎች  ጥሎ ሊያልፍበት የሚችልበት አማራጭ ስልቶች ከሌሉት በተባለው ድርድር ስም በጠላቶቹ  ተጠልፎ እንዲወድቅ ያደርገዋል። ለመኢአድ  ውድቀት ዓይነተኛ ምክንያት የሆነው ይህ ዓይነቱ ድርድር ነው።
አምስተኛ፦ ተደራዳሪዎች ለሰላም አልቆሙም፣ አንድነትን አይፈልጉም ከሚለው ክስና ሐሜት ራሳቸውን ለመከላከል እንዲችሉ፣ ለሚቀርቡ የአንድነትና የእንተባበር ጥያቄዎች አፋዊ የሆነ መልሶችን በመስጠት ትብብሩ ወደፊት እንዳይገፋ ዲፕሎማሲያዊ ቋንቋዎችን በመጠቀም ጊዜ  ለመግዛትም የሚጠቀሙበት የትብብር ጥያቄ አለ። ሌላው ጠንካራውን ድርጅት የማዳከሚያና በትብብር ስም ይኸን አለ፣ እንዲህ ተባለ የሚሉትን ወሬዎች በአንድነት አፍቃሪነት ስም፣ አንድነት እንዳይኖር፣በአንፃሩ ተቃዋሚው ኃይል ራሱን አጠንክሮ እንዳይወጣ ጊዜ ማባከኛ የድርድርና የኅብረት ጥያቄዎች እንዳሉ ልብ ልንል ይገባል።
በአጠቃላይ በዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ምሕዋር ውስጥ ለአንድነትና ለውኅደት የሚቀርቡ ጥያቄዎችን ለማስተናገድ፣ ከላይ የተነሱትን ጥያቄዎች በማንሳት ተገቢና የማያሻሙ መልሶችን መያዝ ብልኅነት ብቻ ሳይሆን ፣ዐዋቂነት ጭምር መሆኑን ማስተዋል ተገቢ ነው።
,ፈለገ አሥራት የትውልዳችን ቃል ኪዳን ነው!
ዐማራን ከፈጽሞ ጥፋት እንታደጋለን!
አንድ ዐማራ ለሁሉም ዐማራ ፤ ሁሉም ዐማራ ለአንድ ዐማራ!
የዐማራው ኅልውና መጠበቅ፣ ለኢትዮጵያ አንድነት መጠበቅ ዋስትና ነው!