በመስከረም አበራ (e-mail meskiduye99@gmail.com) 

መስከረም አበራ

ሃገራችን ኢትዮጵያ መማር ብቻውን “ንወር ክበር!” የሚያስብልባት ምድር ነች፡፡ተምሮ ለወገኑ ምን ሰራ? ለሃገሩ ምን አበረከተ? የሚሉት ወሳኝ ነገሮች ከክብሩ በፊት ጥያቄ ውስጥ የሚገቡ ነገሮች አይደሉም፡፡ብዙሃኑ ምሁራን በበኩላቸው ትምህርታቸው ደሃ አደግነታቸውን የሚበቀሉበት ብርቱ በትር፣ የቅንጦት ህይወት የይለፍ የሚወስዱበት ሰልፍ ብቻ ይመስላቸዋልና ዲግሪ በደራረቡ ቁጥር ከትናንት በተሻለ ራሳቸውን ለማገልገል፣ከሰው በልጦ ለመታየት ይታጠቃሉ፡፡ትምህርታቸው ያልሰራውን ቁስ ከየፈረንጁ ሃገር ይሰበስባሉ፡፡ ቁሱን ይበልጥ ለማጋበስ ከግፈኛ መንግስት ጋር ማህበር ይጠጣሉ፡፡ ከደም አፍሳሽ ጋር ግንባር ይገጥማሉ፤ከእናት ሃገር ሆድ ወጥተው የሷኑ ደካማ ጎን ይመታሉ፡፡

 

ከትናንት በስቲያ እግረኛ ወታደር የነበረ ኩሽሹን በከረባት ቀይሮ  ባላዋቂ እጁ ሲያቦካው የኖረው ፖለቲካ እንደ ቂጣ ምጣዱላይ እንክትክት ሲልበት ‘ኑና ስራየ ልክ እንደ ነበረ ዱክትርናችሁን እየጠቀሳችሁ ከሙያ አንፃር አስረዱ ሲላቸው’ ሊያስረዱ ይሽቀዳደማሉ፡፡ በኢቢሲ አንድ ሁለት ቀን ካናዘዛቸው በኋላ አያያዛቸውን አይቶ፣ፍልስፍናቸው እንደ ቅማል “እራስ ደህና” ማለት እንደሆነ አጥንቶ ለሙሉ ጊዜ አገልጋይነት ያጫቸዋል፡፡ “የዶክተሮች ካቢኔ አቋቋምኩ” ብሎ ከመጠላቱ በላይ እንዲጠሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህም ለነሱ ክብር መስሎ ይታያቸዋልና ሹመቱ ሃሴታቸው፣የሹመቱ ቱርፋት እርካታቸው ይሆናል፡፡

 

የመማር ዋና አላማው በስብ መጥገብ ከሆነ ዳርቻው ይህ ቢሆን አይስገርምም፡፡ በስብ ለመጥገብ ግን መማር ግድ አልነበረም፡፡ እንደውም ለቁስ ሰቀቀን ፍቱን መድሃኒቱ፣ የቀጥታ መንገዱ ተደራራቢ ዲግሪ የግድ የማይለው የመነገድ ማትረፉ ጎዳና ነው፡፡መማር ግን ቁስ ከማንጋጋት፣ ሆድ ከመቀብተት ያለፈ ተልዕኮ ያለው ነገር ነው፡፡ መማር መንጋው ያላየውን ቀድሞ አይቶ ማሳየትን፣ባልደላው ማህበረሰብ ውስጥ እውነተኛ ድሎት እንደማይኖር የመገንዘብ ራስ ወዳድነትን የመሰናበት ልዕልና፤ለእውነት እና ለሃቅ ብቻ የመወገን እና ይሄው የሚያመጣውን ቱርፋትም ሆነ ችግር የመቀበል ልቅና ነው፡፡ይህ ልቅና በተለይ በድሃ ሃገር እንደልብ የሚገኝ አዘቦታዊ ገጠመኝ ሳይሆን እንደ ማዕድን በመከራ ተፈልጎ የሚገኝ ብርቅ ነገር ነው፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

ፕ/ሮ መስፍን ወ/ልደማርያም በግብር መማራቸውን ከሚመስሉ፣ሁሉን ከሚመረምሩ፣ሳይደክሙ ከሚጠይቁ፤የቁስ ምኞት የራስ ድሎት እምብዛም ከማያስጨንቃቸው ብርቆች ወገን ናቸው፡፡ ሰውየው ከጉብዝና እስከ ሽምግልናቸው ወራት ሲፅፉ ሲሞግቱ የኖሩ የሃገር አድባር ናቸው፡፡ እውቀት ልምዳቸውን በወረቀት አስፍረው፣ በቃል ተናግረው አይጠግቡም፡፡ የተናገሩ የፃፉት ለብዙ የፖለቲካችን ህማማት መልስ አለው፡፡ ሆኖም የሚታያቸውን ለማየት፣ የሚሰማቸውን ለመረዳት አቅሙም ልምዱም የሚያጥረን ሰዎች ልንወርፋቸው እንጣደፋለን፤ የምናስበውን እንዲናገሩልን እንሻለንና ብዙ ጊዜ ባልሆኑት እንከሳቸዋለን፡፡ በበኩሌ ሰው ፍፁም ነው ብየ አላምንም፤ይህን መጠበቅም ደግ አይመስለኝም፡፡ ሰው ናቸውና ፕ/ሮ መስፍንም ሊስቱ፣ ሊያጠፉ ይችላሉ፡፡ወይም በእኛ ግንዛቤ ያጠፉ ሊመስለን ይችላል-       ሁላችንም የግንዛቤያችን ነፀብራቅ ነንና! ይሄ ጤናማ ነው፡፡

 

ዋናው ጉዳይ ግን ጥፋትን እና ልማትን የመመዘን እርጋታ፣ ቅሬታችንን የምንገልፅበት ሁኔታ፣በተለይ የተቃውሟችን ሁለመና ሌት ተቀን ከምናወራለትን ኢትዮጵያዊ ማንነት አንዱ የሆነውን ታላቅን የማክበር ጨዋነት ጋር አብሮ ይሄዳል ወይ የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ይሄን ያስባለኝ በተደጋጋሚ ከፕ/ሮ መስፍን ጋር በማይጥም ሁኔታ የሚሟገተው የርዕዮት ሚዲያ ባልደረባ አቶ ታምራት ነገራ ከሰሞኑ ፕ/ር መስፍን የተናገሩትን አንስቶ ከሰውየው ጋር ያለውን ልዩነት የገለፀበት ድንፋታ ነው፡፡ ራሴም በአንድ ወቅት ከፕ/ሮ መስፍን ሃሳብ ጋር ባለመስማማት ተሟግቼ ነበርና ታምራት ነገራ ለምን የፕ/ሮ መስፍንን ሃሳብ ሞገተ የሚል አቋም የለኝም፡፡ ጥያቄየ እሳቸውን ሲሞግት እንደዚህ ጣራ አድርሶ በሚያፈርጥ ንዴት የሚበግነው ለምንድን ነው የሚል ነው፡፡በእውነት እና በእውቀት፣በደንብ በገባው ነገር ላይ ለሚሞግት ሰው ጥርስ በሚያፋጭ ብግነት ውስጥ መሆን ምን ይረዳዋል? በንዴት ፈረስ ላይ ሆኖ አያት የሚሆንን ትልቅ ሰው መዘርጠጥስ አስተዳደግን ከማስገመት፤ የራስን ኪሎ ከማቅለል ያለፈ ምን ረብ አለው? ንዴት እውቀት፣ስድብ ሙግት ሆኖ አያውቅም! ማወቅ ያረጋጋል እንጅ አያንተገትግም፤ስድብ እና ዝርጠጣ ያዋቂነት ምልክት አይደለም፡፡ ስድብ የመከነ አእምሮ ውላጅ እንጅ እንደ ታምራት ነገራ ሃሳብ አለኝ ብሎ ሚዲያ ላይ ከተሰየመ ሰው የሚጠበቅ “አበጀህ” የሚያስብል ነገር አይደለም፡፡ በተለይ ፕ/ሮ መስፍንን ከመሰለ ባለ ከባድ ሚዛን ምሁር ጋር ሲሟገቱ ሰውየው የተናገሩትን በደንብ መረዳት፣መረጋጋት፣ የሚናገሩትን ማወቅ፣ራስን መግዛት ተሻይ ነው፡፡ ካልሆነ ንግግር የሚያስገምተው ራስን ነው! ስለተደጋጋመ ዝም ብየ ማለፍ ስለከበደኝ የታምራትን ጉዳይ አነሳሁ እንጅ የፅሁፌ አላማ ስላልሆነ በዚህ ትቼ ፕ/ሮ መስፍን ሰሞኑን በሲያትል ተገኝተው በተናገሩት ጠቃሚ ንግግር ዙሪያ ወዳለኝ ሃሳብ ልለፍ፡፡

 

ስለ ጎሳ አጥራችን ገበና፤የልዩነት አንድነት እንዴትነት

 

ፕ/ሮ መስፍን ያደረጉት ንግግር የሚጀምረው  በሃገራችን ወቅታዊ ፖለቲካ ዋነኛ መዘውር የሆነው አግላይ የጎሳ ፖለቲካ የሃገራችንን የማህበረ-ፖለቲካዊ ታሪክ የማይወክል ልብ ወለድ ነው በማለት ነው፡፡ይህው ስሁት እሳቤ ስህተቱን የሚያባብሰው በጎሳ መሃል አንድነት እንጅ ልዩነት የለም ብሎ ሲደመድም፤የዚህ ተቃራኒ የአንድነት አቀንቃኖች ደግሞ በሚዘምሩለት አንድነት ውስጥ ልዩነትነትን የሚያስተናግዱበት ቦታ የሌለ ወይ የጠበበ መሆኑ ነው በሚል ግራ ቀኙን የሚገስፅ እና ልብ ላለው በዚህ መሃል ያለውን አዋጭ መንገድ የሚያሳይ ነው -የፕ/ሮ መስፍን ተግሳፅ አዘል ንግግር፡፡ የጎሳ ፖለቲካ ማቆሚያ የሌለው የሽንሸና እና የማነስ ጉዞ እንደሆነም ጠቆም አድርገዋል፡፡መስማት የምንችል ብልሆች ከሆንን ይህ የፕ/ሮ መስፍን ንግግር ለፖለቲካችን ፍቱን ፈውስ የሚሆን መድሃኒት ያለው ነገር ነው፡፡

 

ነገሩን ከነባራዊው የሃገራችን ፖለቲካዊ ሁኔታ ጋር ለማመሳከር ያህል ቆየት ካለው የኦሮሞ ጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኞች እሳቤ አንፃር ብናየው ሰፊው የኦሮሚያ ክልል ያቀፋቸውን ኦሮምኛ ተናጋሪ ሰፊ ህዝቦችን እንደመንታ ልጆች ተመሳሳይ መልክ፣እሳቤ፣ፍላጎት ያቸው አድርጎ “ኦሮሙማ” የሚል የጅምላ ማንነት ሊያላብስ ይለፋል፤ከኦሮሞ በቀር ለኦሮሞ የሚያስብ እንደሌለ  እርግጠኛ ሆኖ ‘ኦሮሞዎች ብቻ ተሰብሰቡና ምከሩ’ ሲል በር አዘግቶ ሲያስዶልት አይተናል፡፡ በዚህ እሳቤ መሰረት ኦሮሞዎች እንደነዶ ለብቻቸው ታስረው የተቀመጡ ህዝቦች ስለሆኑ እነሱ ለብቻቸው የሚወስኑት ውሳኔ በሌላው ኢትዮጵያዊ ላይ ተፅዕኖ የለውም፤ወይም ሌላው ኢትዮጵያዊ የነሱን የብቻ ውሳኔ አሜን የማለት እዳ አለበት፡፡ኦሮሞ በተባለው ሰው ውስጥ በሚናገረው ቋንቋ ምክንያት ካገኘው አንዱ ማንነቱ (ኦሮሞነት) በቀር ሌላ ማንነት ስለሌለው ፍላጎቶቹ፣ጥያቄዎቹ፣ምኞቶቹ ሁሉ የሚመነጩት ከሚናገረው ቋንቋ ብቻ ስለሆነ መነጋገር ያለበት ከቋንቋ መሰሎቹ ጋር ብቻ ነው-እንደ እሳቤው፡፡ እውነታው ግን ሌላ ነው፡፡የሚናገሩት ቋንቋ (ጎሳቸው) በፍፁም የማይገናኝ ሁለት በገጠር የሚኖሩ አማራ እና ኦሮሞ አርሶ አደሮችን በአንድ በኩል ሁለት ከተሜ አማራ እና ኦሮሞዎችን በሌላ በኩል አስቀምጠን ምኞት ፍላጎታቸውን ችግር ጥያቄቸውን ብንጠይቅ ከሚናገሩት ቋንቋ ይልቅ በተሰማሩበት የኑሮ ፈርጅ የተነሳ ተመሳሳይ እምነት፣ፍላጎት፣ጥያቄ፣ዝንባሌ እንደሚኖራቸው አያጠራጥርም፡፡ይሄን በጾታ፣በእድሜ፣በትምህርት ደረጃ ወዘተ እየተካን ብናሰላው ውጤቱ ተመሳሳይ ነው፡፡ በተጨማሪም አካባቢ እየሰፋ በሄደ ቁጥር ሰዎች ተመሳሳይ ቋንቋ እየተናገሩም ቢሆን እምነት፣ ዝንባሌ፣ ጥያቄ፣ ፍላጎታቸው በአጠቃላይ ባህላቸው ከመመሳሰል ይልቅ እየተለያየ መሄዱ ሳይንሳዊ ነው፡፡ ፕ/ሮ መስፍን ‘በጎሳ ውስጥ ልዩነት የሌለ አይምሰላችሁ’ የሚሉት እንዲህ ያለውን ጉራማይሌነት ነው፡፡ ሌላ ማሳያ ለማከል ያህል አንድ አይነት ቋንቋ መናገር አንድ ወጥ ማንነት የሚያመጣ ቢሆን ኖሮ ኦሮሞው አቶ አባዱላ የተሰለፉበት የፖለቲካ እምነት ኦሮሞውን አቶ በቀለ ገርባን እስርቤት የሚያመላልስ አይሆንም ነበር፡፡

 

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ከምክንያታዊነት እና ነባራዊነት ጋር ጥብቅ ጠብ የተጣላው የጎሳ ፖለቲካችን ለምክንያት የዝሆን ጆሮ ሰጥቶ ይነጉዳል፡፡ በየጎሳ ፖለቲካ “ቄሰ-ገበዙ” አቶ ጃዋር መሃመድ በአንድ ወቅት አቶ አባዱላ ገመዳ ዛሬ ኦ.ኤም.ኤን ካባረረው ጋዜጠኛ አብዲ ፊጤ እና ሌሎች ጋር የነበራቸውን እራት ግብዣ አስመልክቶ ‘እንዴት የኦሮሞ ወጣቶችን ከሚያስረው ሰው ጋር ማዕድ ትቀርባላችሁ?’ በሚል ትችት ሲቀርብበት ‘ኦሮሞ ሁሉ ወገናችን ነው አበሾች በልዩነታችን ማትረፍ ስለምትወዱ እኛ ስንሰባሰብ አትወዱም’ ሲል መልስ በሰጠ አንድ አመት ሳይሞላው ነው ኦህዴድ በሚመራው የኦሮሚያ ክልል የዚያ ሁሉ የኦሮሞ ደም የፈሰሰው፡፡ ጃዋር ባለው መሰረት ኦሮሞ ሁሉ የኦሮሞ ወገን፤ ኦሮሞ ያልሆነ ሁሉ ለኦሮሞ የማይተኛ ከሆነ ለምን ኦህዴድ በሚመራው ክልል፤ወገኔ ብሎ እራት ያቋደሳቸው አቶ አባዱላ ዋና በሆኑበት ስርዓት ያሁሉ ኦሮሞ ሞተ፣ ጃዋርስ እንዴት የሞት ነጋሪት ጎሳሚ ተደርጎ በስሙ ፋይል ተከፈተ? ‘ይህን መዛባት አጢኑና ወደ መስመር ግቡ’ ነው የፕ/ሮ መስፍን ምክርና ተግሳፅ፡፡

 

የአማራ ብሄርተኝነት ለማስፈን የሚለፉ የአማራ የጎሳ ፖለቲከኞች እንደ ኦሮሞ ጓዶቻቸው አንድ አማራዊ ማንነት አለን እንጅ ጎጃሜ፣ጎንደሬ፣ወሎየ፣መንዜ አትበሉ ይላሉ፡፡እኔን ጨምሮ አብዛኛው ኢትጵያዊ ደግሞ ይበልጥ የሚያውቀው ጎጃሜ፣ጎንደሬ፣ተጉለቴ የሚለውን እንጅ አማራ የሚለውን ማንነት አይደለምና ይህም ትልቅ ፖለቲካዊ አጀንዳ ሆኖ ያነታርካል፡፡እንዲህ ብሎ ለያይቶ መጥራት የአማራን ህዝብ ማንነት የማጥፋት ሂትለራዊ ተንኮል ተደርጎ ይወገዛል፡፡ የአማራ ህዝብ ራሱ ግን ይህ ውድቅ የሚያደርግ በልጅነቴ እየሰማሁት ያደግኩት አንድ አባባል አለው -“የጎንደሬን አማርኛ እንኳን መንዜ ጎጃሜም አይሰማው” ይላል፡፡አባባሉ የሚያስረዳው በአሁኑ የሃገራችን የጎሳ ፖለቲካ ፈሊጥ  የፍፁም መመሳሰል ዳርቻ እየተደረገ ባለው በአንድ አይነት ቋንቋ በመግባባት ውስጥ እንኳን ልዩነት መኖሩን ነው፡፡ እንደሚባለው አማራነት፣ከአማራ ምድር መወለድ እንደ ፋብሪካ ምርት አንድ የሚያደርግ፣ ሁሉን ፍጡር አንድ አይነት ነገር የሚያሳስብ ከሆነ በትቂቱ ቤተ-አማራ ከሞረሽ ወገኔ ተለይቶ አናየውም ነበር፡፡ እውነታው እና የሚያስኬደው መንገድ ፕ/ሮ እንዳሉት ሰው ባለበት ሁሉ ልዩነትም አንድነትም መኖሩን ተቀብሎ የማያልቀውን የጎሳ አጥር እያጠበቡ ሲያጥሩ ከመኖር እልፍ ማለቱ ነው፡፡

 

የጎሳ ፖለቲካ አጥር ማለቂያ የለውም የሚለው አባባል አሁንም ሰከን ብሎ ለሰማ፣ሰምቶም ለመማር ለተዘጋጀ ጥሩ ጥቁምታ ነው፡፡ ይህን ነገር ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና በአንድ ወቅት “በዘር ፖለቲካ ሄደህ ሄደህ የምትገባው ቤትህ ነው” ካለው ግሩም እይታ ጋር መሳ ነው፡፡ ነገሩን ወደ ነባራዊው የሃገራችን የጎሳ ፖለቲካ ሃቅ ስንመልሰው እኔ የምኖርበት የደቡብ ክልል በርካታ ብሄረሰቦችን ያቀፈ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ለስራ ጉዳይ ከክልሉ ብሄር የአንዱ ተወላጅ ከሆነ ሰው ጋር እሱ ተወልዶ ባደገበት የገጠር ቀበሌ የኔ መስሪያቤት የሚሰራው ስራ ኖሮ ከእኛ ጋር ይጓዝ ነበር፡፡እናም የሄድንበትን ስራ ጨርሰን የእርሱን የትውልድ መንደር ለቀን ግን በዛው ዞን ውስጥ ከትውልድ መንደሩ አንድ አስር ኪሎሜትር ርቀን እንደተጓዝን  አንዲት ትንሽ ከተማ እንደደረስን ሰውየው “እኔኮ እዚች ከተማ ልጄን ማስቀጠር አልችልም” ብሎ ዝምታችንን የሚሰብር ንግግር አመጣ፡፡ “ለምን አንድ ዞን አይደል እንዴ?” አልኩኝ በጣም ስለገረመኝ ተሸቀዳድሜ፡፡ “አንድ ዞን ቢሆን፣ቋንቋው አንድ ቢሆን ጎሳችን ግን የተለያየ ነው፤ እነሱ ጎሳቸው ያልሆነን ሰው አበጥረው ያውቃሉና የኔ ልጅ ይወዳደር ይሆናል እንጅ መቀጠር የማይታሰብ ነው” ሲል የደረስንበትን አዘቅት ቁልጭ አድርጎ አሳየኝ፡፡ ቀጥየ ጥያቄ አላነሳሁም፤ዝም ዝም ሆነ! የሚያፅናናው ነገር ግን ፕ/ሮ እንዳሉት የጎሳ ፖለቲካ ቀሳውስት ለስልጣን እና ለጥቅም ዘር እያቋጠሩ ሃረግ ሊያማዝዙት ቢሞክሩም የኢትዮጵያ ሰፊ ህዝብ ግን እየተጋባ እየተዋለደ ኢትዮጵያዊነቱን በሰውነቱላይ፤ዜግነቱን በኢትዮጵያዊነቱ ላይ እያፀና “ሃዘንህ ሃዘኔ፤ደምህ ደሜ”  እየተባባለ በሩቅ እየተነጋገረ ይኖራል፡፡ ይህ ሁሉ ዘመን አመጣሽ እትብት የመማዘዝ ፖለቲካ የመጣውም በትቂቶች ነውና ፅናት አይኖረውም፤እነዚህ ትቂቶች የመሰረቱት ክፉ አግላይ  ስርዓት በስብሶ ሲወድቅ ሁሉም ይስተካከላል፡፡

 

ቂም፣ልግም፣የክፋት አዙሪት – ቆሞ መቅረት! 

ፕ/ሮ መስፍን እንደህዝብ ያለብንን ችግር በደንብ ተረድተው፣የተረዱትን እውነት  በሚገባን፣መሬት በወረደ ቋንቋ ተርጉመው ጉድፋችንን በማስረጃ አበልፅገው በማንክደው ሁኔታ በማሳየት ተወዳዳሪ የሌላቸው ምሁር ይመስሉኛል፡፡ “የኔታ” የሚለው የኢ-መደባዊ ማዕረጋቸው ትርጉምም ይሄው ይመስለኛል፡፡ የኔታ የሚለው ማዕረግ ፊደል ማስቆጠር ብቻ ሳይሆን የመገሰፅ የመኮርኮም ሞራላዊ ስልጣንንም ይይዛል፡፡ ፕ/ሮ መስፍን በማህበረ-ፖለቲካዊ ችግሮቻችን እና በመፍትሄዎቻቸው ዙሪያ በአማርኛም በእንግሊዝኛም በደንብ ፅፈዋል፡፡ፅፌያለሁ ብለው መናገራቸውንም አይተውም፡፡የፃፉ የተናገሩትን ወጣቱ ትውልድ እንዲያነብ፤በትኩረት እንዲያደምጥ ይፈልጋሉ፡፡ አብዛኛው የዘመናችን ጋዜጠኛ፣ፖለቲከኛና ተንታኝ ደግሞ ማንበብ ላይ ወገቤን ባይ ስለሆነ የተናገሩ የፃፉት የሚመልሰውን ጥያቄ ይዞ ወደ እሳቸው ሲመጣ ይቆጣሉ፤ይገስፃሉ፡፡ “ቁጣው የፃፍኩትን ሁሉ አሜን ብላችኑ እመኑ” ከማለት አይመስለኝም፡፡ አንብቦ “እርስዎ በመፅሃፍዎ እንዲህ ብለዋል ግን እኔ እንዲህ ይመስለኛል” ለሚላቸው ቦታ የሌላቸው ሰው አይደሉም፡፡ ሳያነቡ፣በውል ሳያዳምጡ ከበሬ ፊት ሊበሉ ለሚመጡ ጥጆች ግን ትዕግስት የላቸውም፡፡ ቁጣቸው ይነዳል፡፡ በበኩሌ ቁጣው አያስቀይመኝም፤ይልቅስ ከመናገር ከመፃፋችሁ በፊት አንብቡ የማለት የታላቅ ምክር አድርጌ እወስደዋለሁ፡፡

ፕ/ሮ ረዥም የህወት ልምዳቸው እና ምጡቅ ታዛቢነታቸው እንዳቀበላቸው የኢትዮጵያ ህዝብ ግፈኛን የሚያሸንፍባቸውን ዘዴዎች አሳይተውናል፡፡የኢትዮጵያ ህዝብ ግፍ ሲበዛበት ያቄማል፣አቂሞ ይለግማል፣ ለግሞም አይቀርም ጊዜ ጠብቆ ቂሙን  ክፉን በክፉ በመመለስ ተንፈስ ያደርጋል፡፡ ክፉን በክፉ ሲመልስ   የሚጠላውን፣የተቃወመውን ክፋት ራሱ መልሶ ያደርገዋል፡፡ ይህ አካሄድ ውጊያው ከክፋተኛው ግለሰብ እንጅ ከክፉ አስተሳሰቡ ስላልሆነ ክፋተኛ ነቅሎ ሌላ ክፋተኛ ይነተክላል፡፡ ስለዚህ የሃገራችን ፖለቲካ ከክፋት አዙሪት ሊወጣ አልቻለም ይላሉ፡፡ መፍትሄውን ሲያስቀምጡ መዋጋት ያለብን ክፋትን ራሱን አስተሳሰቡን መሆን አለበት፡፡ ይህ መንገድ በደንብ ገብቶን ከጀመርነው ክፋትን ለማጥፋት ሌላ ክፋትን እንደመሳሪያ አድርገን መጠቀም እናቆማለን ይላሉ፡፡ ክፉ አስተሳሰብን ለመዋጋት ደግሞ ከራስ ጋር ብቻ የማውራት አድፋጭነትን አስወግደን መነጋገርና መግባባት መጀመር አለብን፡፡ እስከዛሬ ሳንነጋገር ስንግባባ የኖርነው ክፋትን በክፋት በመመለሱ ማድፈጥ ውስጥ ባለ ክፉ ቋንቋ ነው፡፡ አሁን ግን እርስበርስ ተነጋግረን ከሃሳባችን ፍጭት ክፉን በክፉ ከመቃወም የተለየ፣የተሻለ፣የዘመነ መንገድ ማውጣት አለብን ባይ ናቸው-የኔታ መስፍን!

 

ሌላ ሳንካ…..!

 

ጨቋኝ መንግስታትን ለመንቀል ስንታገል የግፍ አስተዳደርን እሳቤ፣ክፋትን ራሱን በፅንሰሃሳብ ደረጃ ተቃውመን፤ክፉን ካስወገድን በኋላ በጎ የመትከሉ ነገር ለእኛ ለኢትዮጵያዊያን እስከ ዛሬ አልተቻለንም፡፡ ለምን ቢባል ክፉን ለመንቀል የሚያስችለን የቂም፣የልግመኝነት እና ክፉን በክፉ የመመለስ ሃይል በሙላት ስላለን ክፉን መንቀል ችለናል፡፡ እነዚህ ክፉን ለማስወገድ ሃይል የሆኑን ነገርግን ቂም፣ልግመኝነት፣ማድፈጥና፣ክፉን በክፉ መመለስ በጎ ስርዓትን ለመትከል የሚያስችል ልዕልና የሌላቸው፤ለዘመነ ፖለቲካ ስፍነት፣የተሻለ አኗኗር እውንነት  የማይመጥኑ ኋላ ቀር እና ተራ ልምዶች ስለሆኑ ፖለቲካችንን ቆሞ-ቀር አድርገውታል፡፡ እስከዚህ ድረስ ከፕ/ሮ መስፍን ጋር እስማማለሁ፡፡ ነገር ግን ለፖለቲካችን ቆሞ መቅረት ሃላፊነቱን መውሰድ ያለበት አካል በየፈርጁ መታየት ያለበት ይመስለኛል፡፡

 

እንደሚታወቀው አብዛኞቹ በኢትዮጵያ የተካሄዱ ጨቋኝ አስተዳደርን የማስወገድ እንቅስቃሴዎች ወጣኔያቸውን እና ፍፃሜያቸውን የሚያገኙት ከፖለቲካ ልሂቃን ሆኖ ህዝቡ የሚፈለገው መሃል ላይ ለለውጡ ጉልበት ለመስጠት ሲባል ነው፡፡ ኢህአዴግ ወደ ስልጣን የመጣበትን ሁኔታ ብናይ ፕ/ሮ መስፍን እንዳሉት በማራቶን ሩጫ ሃገሪቱን ከመቆጣጠሩ በፈት የህዝቡን እርዳታ ማግኘት ምትክ የሌለው ወሳኝ ጉዳይ ነበር፡፡ወደ አፈሙዝ ላንቃ የሚማገድ እግረኛ ወታደር ወልዶ መስጠቱ፣ ለወታደሩ እህል ውሃ ማቅረቡ፣ቁስለኛ ማስታመሙ፣ የጠላትን ሁኔታ ሰልሎ መረጃ ማቀበሉ፣ ጠላት ገፍቶ ሲመጣ መደበቅ መሸሸጉ ሁሉ ኢህአዴግ በመጨረሻዎቹ አመታት ወደ አዲስ አበባ ለመገስገስ ያስቻሉት ቀደም ብሎ ያገኛቸው የህዝብ ድጋፎች ነበሩ፡፡ ‘ህዝቡ ይህን ድጋፍ ለምን ሊያደርግ ቻለ?’ ለሚለው ጥያቄ አንዱ መልስ ፕሮፌሰር መስፍን ያነሱት በግፈኛ ላይ የማቄም፣የመለገም፣ክፉን የመበቀል ዝንሌ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ሆኖም ህዝቡ ይህን ሲያደርግ ‘በወታደር ጫማ እየረገተህ ያለውን ክፉ ጥለን ዲሞክራሲን እናመጣልሃለን’ ያሉትን ሸማቂዎች አምኖ የተሻለ ያደርጉልኛል ብሎ ተማምኖ ይመስለኛልና ክፉን ነቅሎ ደግ ባለመትከል እጅግም መወቀስ ያለበት አይመስለኝም፡፡ ክፉ ነቅሎ በጎ ባለመትከል መወቀስ ያለበት ዲሞክራሲ ላመጣልህ እታገልኩ ነው ብሎ የህዝብን አጥንት እየጋጠ፣በህዝብ ጫንቃ ላይ እየተረማመደ ለስልጣን የበቃው የትናንት ነፃ አውጭ ነኝ ባይ ሸማቂ የዛሬ ተረኛ ግፈኛ አስተዳደር ይመስለኛል፡፡

 

ይህ አካል በቃል አባይነት፣በመሰሪነት እና በአታላይነት መወቀስ፤ለፖለቲካችን ቆሞመቅረት የአንበሳውን ድርሻ መውሰድ አለበት፡፡ህዝባችን በየዋህ ልቦናው አምኗቸው የመሶብ የቡኾእቃውን ገልብጦ እንዲያበላቸው፣ ልጆቹን ለሞት መርቆ እንዲሰጥ ያደረገው የሸማቂዎቹ አስመሳይነት ነበር፡፡ ሸማቂዎቹ የልባቸውን እሲኪያደርሱ፤እንጦጦ አፋፍ እስኪደርሱ ዲሞክራትነታቸውን ለየዋሁ ህዝብ የሚያስረዱት “ቅጫማም” እየተባሉ ሲሰደቡ ዝም በማለት፣ “የተሰማችሁን ተናገሩ መብታችሁ ነው” በሚል ሽንገላ፣ሌባ የተባለን ሁሉ ያለፍርድ በየመንገዱ በጥይት በመቁላት ወዘተ እንደ ነበር ያየ የሰማ የሚናገረው ነው፡፡ያለፍርድ ሌባ የተባለን ሁሉ አስፋልት ላይ ሲያጋድሙ የነበሩት የፍትህ አለቃ ነን ባዮች በወንበራቸው ሲደላደሉ መንግስታቸው የሌባ መርመስመሻ እንደሆነ ራሳቸው ‘የመንግስት ሌባ ከቦናል’ ሲሉ በፓርላማ መስክረዋል፡፡ተራ ስድብ ሲሰደቡ ዝም ሲሉ እንደ ባህታዊ ይቃጣቸው የነበሩ ሸማቂዎች ዛሬ ጋዜጠኞች ስራቸውን ስለሰሩ ብቻ የሚያስሩ ፈርኦኖች ወጥቷቸዋል፡፡ ‘ደርግ የሰማኒያ አመት ሽማግሌ አሰረ ብለን ደደቢት ነጎድን’ ያሉ የነፃነት ነብያት ነን ባዮች ዛሬ የሰማኒያ አመት ሽማግሌ አስረው ቦክስ የሚያቀምሱ “ጎበዞች” ፤እናትን በልጇ አስከሬን ላይ አስቀምጠው የሚደበድቡ ጉዶች ሆነዋል፡፡

 

ከላይ በተንደረደርንበት ነባራዊ ሃቅ ላይ ቆመን ለፖለቲካችን ቆሞ-መቅረት፣አልለቅ ላለን የክፉ አስተዳደር አዙሪት ስፋኔ ዋነኞቹ ተጠያቂዎች የትናንቶቹ የነፃነት ታጋይ፣የእኩልነት አደላዳይ፣የዲሞክራሲ ነብይ ነን ባዮቹ ሃገራችን የፖለቲካ ልሂቃን መሆን አለባቸው ብየአስባለሁ፡፡ የእነዚህ አካላት አታላይነት፣አስመሳይነት፣ግብዝነት እና መሰሪነት ፕ/ሮ መስፍን ለፖለቲካችን ክፉ አዙሪት በምክንያትነት ካነሷቸው ቂመኝነት፣ልግም፣ማድፈጥ፣እና ክፋት እኩል ፖለቲካችንን የክፋት አዙሪት ውስጥ የከተቱ መሆናቸው ታውቆ ለፈውሳችን መላ መባል አለበት፡፡

ያልተስማማኝ….

ከላይ እንደተቀስኩት ፕ/ሮ መስፍን እግራቸው ስር ቁጭ ብለን የፃፉ የተናገሩትን ልናስተውል የሚገባን ድንቅ መካር ናቸው፡፡ ብዙ የሚያመርት ፈጣን ጭንቅላት ያላቸው፣ፍርሃት የማያውቃቸው፣ብዙ ምሁራንን የሚያንገላታው የቁስሰቀቀን ሲያልፍም የማይነካካቸው፣ ሃገር ወዳድ አድባር እንደሆኑ አያነጋግርም፡፡ሆኖም ከሃሳባቸው ጋር አለመስማማትም ሆነ በከፊል መስማማት ተፈጥሯዊም ጤናማም ነው፡፡ግን አለመስማማታችንን ስንገልፅ ሽምግልናቸውን ብቻ ሳይሆን አዋቂነታቸውን የሚመጥን ክብር ልንነፍጋቸው አይገባም፡፡ ለትልቅነታቸው ያለኝ ክብር እንዳለ ሆኖ፤በንግግራቸው ብዙ በመማሬ እያመሰገንኩ ከንግግራቸው ያልተስማሙንን አንድ ሁለት ነጥቦች ላንሳ፡፡ አንደኛው ከላይ የጠቀስኩት ህዝቡን እና አታላዩን ልሂቅ በአንድ ላይ አይተው ለፖለቲካችን ክፉ አዙሪት በእኩል ተጠያቂ ያደረጉበት መንገድ ቢነጣጠል እና ልሂቁ እንደጥፋቱ መጠን ትልቁን ሃላፊነት ቢወስድ የሚል ነገር አለኝ፡፡ ፕ/ሮ መስፍን የሚሉት በጎ ስርዓትን ለመትከል ሚገፋውን በጎ ሃይል ያጣው አስመሳይ መልቲነትን ተከናንቦ ስልጣን ላይ ቂጢጥ ያለው ልሂቅ ነው፡፡ ‘ህዝቡስ በዚህ አዙሪት ውስጥ ድርሻ የለውም ወይ?’ የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም ህዝቡ ከተወቀሰ የሚወቀሰው በደርሶ አማኝነቱ ምክንያት ለልሂቁን ብልጣብልጥነት መረዳት ባለመቻሉ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ የግንዛቤ ነገርም ስላለበት በብዛት ላልተማረው ህዝባችን ይቅርታ ለማድረግ በቂ ምክንያት ነው  ብየ አስባለሁ፡፡ ህዝቡ ሸማቂዎች ስልጣን ላይ ከወጡ በኋላ ቃልአባይነታቸውን ተረድቶ ለምን በጊዜ አይሸኛቸውም የሚል ሌላ ጥያቄ ከመጣ ህዝቡ ይህን የሚያደርግበት የህግ የበላይነት፣ለይስሙላ ህግ በወረቀት ከመቸከቸክ ባለፈ ህግን የሚያስፈፅም ተቋማዊነት እንዳይኖር የልሂቃኑ አታላይ የፖለቲካ ማንነት ስላልፈቀደ፤ህዝቡ ገፍቶ ሲመጣም ልሂቁ በጥይት ቋንቋ ስለሚያናግረው አሁንም ወደ ማድጥፈጡ ከመመለስ ያለፈ አማራጭ የለውም፡፡ ስለዚህ ትልቁ ስራ የቀረው ስልጣን ላይ ካለው የፖለቲካ ልሂቅ ይመስለኛል፡፡

 

ሁለተኛው ጥቅሙን ያጣሁት የፕ/ሮ መስፍን ንግግር ስለ በላይ ዘለቀ እና አፄ ኃ/ስላሴ፤ ኦሮሞነት ስለ ኃ/ማርያም የወላይታ የመጀመሪያው ባለስልጣን ያለመሆን ጉዳይ ያነሱት ነገር ነው፡፡ ይሄ በተለይ  እንደ እርሳቸው ለሰብአዊ ፍጡር ሁሉ መብት ለሚሟገት፤ይህንንም በሃገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ተቋም መስርቶ በማስኬድ ለሚወደስ የሰብዐዊነት ምልክት ሰው አይመጥንም፡፡ ለፖለቲካችን ፈውስም አስፈላጊነቱ አይታየኝም፡፡

የምንጣፉ ውበት!!!! 

 

ፕ/ሮ መስፍን በንግግራቸው መጨረሻ ላይ በሃገራችን የፖለቲካ ወለል ላይ መነጠፍ ስላለበት በነፃነት፣በእኩልነት፣በህግ ስርዓት የተማገረ ውብ ምንጣፍ የተናገሩት ውብ ንግግር በጣም ድንቅ ነው፡፡ምንጣፉ ዜጋን ሁሉ በእኩልነት የሚያንከባልል መሆን እንዳለበት፤ ሆኖም የሚንከባለሉ ሰዎች ወደ ምንጣፉ ሲመጡ ምንጣፉን እንዳያቆሽሹና ወደ ተለመደው አዙሪታችን እንዳይጨምሩን አእምሯቸውን፣ከቂም በቀል ማፅዳት፣ ከክፋት መፈወስ አለባቸው ይላሉ፡፡ ነገሩ ድንቅ ነው፡፡ ሆኖም ጉዳዩን ከምኞት ባለፈ ገቢራዊ ለማድረግ ደግሞ የፖለቲካ ንቃትን በህዝቡ አእምሮ ውስጥ ማስረፅ አስፈላጊ እንደሆነ በደንብ ሊጤን ይገባል፡፡ አእምሮን የሚያቆሽሽ፣ክፋት የሚሞላ፣ጨለምተኝነት፣ጠጠራጣሪነት፣ቂምበቀልንየሚያሸክም፣በምኞትፈረስየሚያስጋልብ፣በልቼ ልሙት የሚያስብል ራስ ወደድነት፣ የህግ ማህበረሰብ ያለመሆን፣አምባገነንን ለመሸከም የማጎንበስ አድርባይነት ሁሉ ምንጩ አለማወቅ ነው፡፡ ስለዚህ በሃገራችን የሲቪክ ማህበራት እንደልብ ተንቀሳቅሰው ህዝቡን ስለመብቱ፣ግዴታው፣ከመንግስት ጋር ሊኖረው ስለሚገባ ተገቢ ግንኙነት እንዲያስተምሩ መሆን አለበት፡፡ ይሄኔ የነቃው ህዝብ ዲሞክራሲ መብቱን ለማስከበር ተቋማትን ገንብቶ ለመብቱ ተቋማዊ ጠበቃ ያቆማልና አምባገነን እየተፈራረቀ ሊያስጨንቀው አይችልም፡፡