ከስዩም ተሾመ

ምሁራን መንግስትን በመደገፍ ወይም በመፍራት ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ስራና አሰራሩን ከመተቸት ይልቅ የመንግስት ቃለ-አቀባይ ከሆኑ፣ የመንግስት ባለስልጣናት ደግሞ የአመራርና አስተዳደር ሥራቸውን ከመስራት ይልቅ የምሁራኑን ሃሳብና ዕውቀት ስለ ምን እንደሆነ መወሰን ከጀምሩ ነገሩ ሁሉ የተገላቢጦሽ ሆኗል። ይህ ሲሆን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ይጨናገፋል፣ ጨቋኝና አምባገነናዊ ስርዓት ይወለዳል። 

ስዩም ተሾመ

ጨቋኝ ስርዓት ወደ ስልጣን የሚመጣው የሀገሪቱ ምሁራን በፍርሃት አንደበታቸው ተለጉሞ የመንግስትን ስራና አሰራር መተቸት ሲቆሙ ወይም በጥቅም ሕሊናቸው ተለጉሞ የመንግስት ቃል-አቀባይ ሲሆኑ ነው። በተለይ ምሁራን ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው ባሳዩት የወገንተኝነት ስሜት ልክ ለሌሎች ሀገራትና ሕዝቦች የጠላትነት ስሜት ያዳብራሉ። 

ከዚህ በተጨማሪ፣ ምሁራን የመንግስት ደጋፊ ሲሆኑ የፖለቲከኞቻቸውን ስራና ተግባር እየተከታተሉ ከመተቸት ይቆጠባሉ። ስለዚህ፣ ማህበራዊ ግዴታቸውን ከመወጣት ይልቅ የመንግስት ቃል-አቀባይ ሆነው ያገለግላሉ። አምባገነናዊ መንግስት ደግሞ እነዚህን የጭቆና ፈረሶች እየጋለበ ሕዝብና ሀገርን ወደ ጦርነትና እልቂት ይወስዳል። ለዚህ ደግሞ በ20ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያ ሩብ ዓመታት በጀርመን እና የጃፓን የተፈጠረውን እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል። 

በአንደኛው የዓለም ጦርነት መገባደጃ ላይ አብዛኞቹ የምዕራብ አውሮፓ ምሁራን በብሔራዊ ስሜት እየተናጡ ነበር። የፈረንሳይ፥ እንግሊዝ፥ ቤልጂዬምና ዴኒማርክ የመሳሰሉ ሀገራት ምሁራን ለሀገራቸው ሕዝብ ከፍተኛ ወገንተኝነት፣ በዚያው ልክ ለጀርመን ሕዝብና መንግስት ደግሞ የጠላትነት ስሜት በስፋት ሲያንፀባርቁ ነበር። ነገር ግን፣ ምሁራኑ በብሔርተኝነት ስሜት ውስጥ ተዘፍቀው ስለነበረ የፖለቲከኞችን ስራና ተግባር መከታተልና መተቸት አቁመው ነበር። ይህ ደግሞ በጀርመን ለአዶልፍ ሂትለር ወደ ስልጣን መምጣትና ለሁለተኛው የዓለም ጦርነት መነሻ ምክንያት ሆኗል። ለምሳሌ፣ “Albert Einstein” በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ እንደሚከተለው ገልፆታል፡-  

“The passions of nationalism have destroyed this community of the intellect, … The men of learning have become the chief mouthpieces of national tradition and lost their sense of an intellectual commonwealth. Nowadays we are faced with the curious fact that the politicians, the practical men of affairs, have become the exponents of international ideas. It is they who have created the League of Nations.” THE WORLD AS I SEE IT፡ Paradise Lost, Page 19

የአንደኛው ዓለም ጦርነት አሸናፊ ሀገራት ምሁራን በብሔራዊ ስሜት ውስጥ ተዘፍቀው በነበረበት ወቅት የፖለቲካ መሪዎች በ“Treat of Versailles”አማካኝነት “League of Nations” የተባለውን ሕብረት መመስረታቸው ይታወቃል። ነገር ግን፣ ስምምነቱ ሲረቀቅ ጀርመን አንደ ባለድርሻ አካል አልተሳተፈችም። ነገር ግን፣ በስምምነቱ መሰረት፤ የተለያዩ የጀርመን ግዛቶችን ለፈረንሳይ፥ ቤልጅዬም፥ ዴኒማርክ፥ እና የመሳሰሉት ሀገራት እንዲሰጡ፣ ቅኝ-ግዛቶቿን ሙሉ-በሙሉ እንድትቀማ፣ በአንደኛው የዓለም ጦርነት በራሷና በሌሎች ሀገራት ላይ ለደረሰው ኪሳራ ካሳ እንድትከፍል ይደነግጋል። በመጨረሻም ጀርመን ስምምነቱን በግድ እንድትቀበል ተደረገ። 

የጀርመንን ግዛቶችን የተቀራመቱት እንደ ፈረንሳይና ቤልጂዬም ያሉ የአውሮፓ ሀገራት ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ሞክረዋል። የአሜሪካ ኮንግረስ ግን የ“Treat of Versailles” የተባለውን የስምምነት ሰነድ ተቀብሎ አላፀደቀውም ነበር። ምክንያቱም፣ ስምምነቱ ከምሁራን እይታና አስተያየት ውጪ እንደመሆኑ በቀጣይ የሚስከትለውን ችግር ከግንዛቤ አላስገባም። ምሁራን በስምምነቱ መነሻ ምክንያትና የመጨረሻ ውጤት ዙሪያ ሃሳብና አስተያየት ሳይሰጡበት በግልብ ስሜታዊነት የተዘጋጀ ነበር። በመጨረሻም የአውሮፓን ሰላም ለማረጋገጥ የተፈረመ ስምምነት የሁለተኛውን የዓለም ጦርነት አስከተለ። 

ምሁራን በብሔራዊ ስሜት እና በመንግስት ቃል-አቀባይነት ተጠምደው በነበረበት ወቅት የተፈረመው ኢ-ፍትሃዊ ስምምነት በአዶልፍ ሂትለር መሪነት የናዚ ፋሽስት ወደ ስልጣን እንዲመጣ ምክንያት ሆነ። ፅንፈኛ አክራሪነትና ዘረኝነት እያቀነቀነ የመጣው ሂትለር በአውሮፓዊያን ላይ ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት፣ በአይሁዶች ላይ ደግሞ የዘር-ማጥፋትን አስከተለ። በአጠቃላይ፣ ምሁራን ለራሳቸው ሕዝብ ከመጠን ያለፈ ወገንተኝነት፣ ለሌሎች ደግሞ የጠላትነት ስሜት በሚያንፀባርቁበት ወቅት ለራሱ ሕዝብ ጨቋኝ፣ ለሌሎች ሕዝቦች ደግሞ ጨፍጫፊ የሆነ ፋሽስታዊ ስርዓት ይፈጠራል። 

በመሰረቱ፣ የጭቆና ስርዓት በሁለት መርሆች ላይ የተመሰረተ ነው። የመጀመሪያው መርህ “ሕዝብና መንግስት አንድ ናቸው። የቡድን መብት ከግለሰብ ነፃነት ይቀድማል። ስለዚህ፣ የግለሰብ ነፃነት ለቡድን/ሕዝብ/መንግስት ፍላጎት ተገዢ መሆን አለበት” የሚል ነው። ሁለተኛው የጨቋኞች መርህ ደግሞ “የእኛ ቡድን/ሕዝብ/መንግስት በሌሎች ተበድሏል እና/ወይም ከሌሎች የተሻለ መብትና ነፃነት ይገባናል” የሚል ነው። 

በመጀመሪያው በሕዝብ ስም የግለሰብን ነፃነትን የሚገድብ – “ፀረ-ነፃነት” ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በማንነት ወይም በታሪክ የሌሎችን እኩልነት የሚፃረር – “ፀረ-እኩልነት” ነው። ስለዚህ፣ ምሁራን የጨቋኞችን “ፀረ-ነፃነት” እና “ፀረ-እኩልነት” አመለካከቶች ገና በእንጭጩ ለመቅጨት መረባረብ አለባቸው። ምክንያቱም፣ አንደኛ፡- እንደ ጀርመናዊው ፈላስፋ “Nietzsche” አገላለፅ፣ “የኃላፊነት ስሜት ያለው ግለሰብ ብቻ ነው” (Only individuals have a sense of responsibility)። ስለዚህ፣ ቡድን፣ ብሔር፣ ወይም ሕዝብ በራሱ የኃላፊነት ስሜት አይሰማውም። የኃላፊነት ስሜት የሌለው አካል ደግሞ የራሱ የሆነ መብትና ነፃነት ሊኖረው አይችልም። ስለዚህ፣ ከቡድን መብት የግለሰብ ነፃነት መቅደም አለበት። 

ሁለተኛ፣ ምሁራን የእነሱ ብሔር ወይም ሕዝብ በሌሎች ብሔሮች/ሕዝቦች/መንግስት ተበድሏል” እያሉ ከመዘርዘር ባለፈ በቀድሞ ስርዓት የተፈፀመውን በደልና ጭቆና ሁሉን-አቀፍ ማድረግ፣ በሌሎች ብሔሮችና ሕዝቦች ላይ ከደረሰው ጋር አያይዘው ማቅረብ አለባቸው። ነገር ግን፣ “ከዚህ ቀደም የእኛ ብሔር ወይም ሕዝብ በሌሎች ብሔሮች/ሕዝቦች/መንግስት ተበድሏል” ብቻ እያሉ ከሆነ፤ “በእኛ ላይ የተፈፀመው በደልና ጭቆና በሌሎች ላይ መደገም አለበት” እንደ ማለት ይቆጠራል።

ምሁራን የመንግስት ቃል-አቀባይ ከመሆን አልፈው የገዢውን ቡድን የፖለቲካ ዘይቤን (Idelology) በሕዝቡ ውስጥ ለማስረፅ መንቀሳቀስ ከጀመሩ እንደ ወታደራዊ-ፋሽስት ስርዓት ይፈጠራል። የጃፓን ምሁራን አክራሪ ብሄርተኝነትና ዘረኝነት እያቀነቀኑ እ.አ.አ. በ1915 ዓ.ም የፈጠሩት ወታደራዊ ፋሽስት በስተመጨረሻ ሀገሪቱን ለከፍተኛ የሞራል ኪሳራና አሰቃቂ እልቂት ዳርጓታል። 

በጃፓን አክራሪ ብሄርተኝነትና ዘረኝነት መነሻ ምክንያቱ እ.አ.አ. በ1868 ዓ.ም ወደ መሪነት ከመጣው የ“Meiji dynasty” ጋር የተያያዘ ነው። ይህ ዘውዳዊ አገዛዝ ከረጅም ግዜ በኋላ ጃፓንን ማስተዳደር እንደጀመረ የራሱን የፖለቲካ አይድዮሎጂ በሕዝቡ ውስጥ ማስረፅ ጀምረ። በዚህ ረገድ የጃፓን ምሁራን የነበራቸውን ሚና እና በስተመጨረሻ ያስከተለው የሞራል ቀውስ በተመለከተ “Edward Said” እንዲህ ገልፆታል፡- 

 “The tennosei ideorogii (the emperor ideology) was the creation of intellectuals during the Meiji period, and while it was originally nurtured by a sense of national defensiveness, even inferiority, in 1915 it had become a fully fledged nationalism capable simultaneously of extreme militarism and a sort of nativism that subordinated the individual to the state. It also denigrated other races to such an extent as to permit the wilful slaughter of Chinese in the 1930s, for example, in the name of shido minzeku, the idea that the Japanese were the leading race. …After the war, most Japanese intellectuals were convinced that the essence of their new mission was not just the dismantling of tennosei (or corporate) ideology, but the construction of a liberal individualist subjectivity.” REITH LECTURES 1993: Representations of an Intellectual፡ Lecture 2: Holding Nations and Traditions at Bay, 30 June 1993.   

ከላይ በዝርዝር ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ እንደ ምዕራብ አውሮፓ ምሁራን በብሔራዊ ስሜት በመዋጥ የመንግስት ቃል-አቀባይ ሆነው ሲያገልግሉ እና በሌሎች ሕዝቦችና ሀገራት ላይ የደረሰውን በደልና ጭቆና ከግንዛቤ ሳያስገቡ በራሳቸው ሀገርና ህዝብ ላይ የተፈፀመን በደልና ጭቆና ብቻ መተረክና መዘከር፣ እንዲሁም እንደ ጃፓን ምሁራን የሰዎችን እኩልነትና ነፃነት የሚገደብ የፖለቲካ አይዲዮሎጂ መፍጠርና ማስረፅ በመጨረሻ ሀገርና ሕዝብ ለጦርነትና ለእልቂት ይዳርጋል።