June 9, 2017

የቅንጅት አመራር የነበሩ ጊዜ በጣም ከማደንቃቸው ፖለቲከኞች መካከል በቀዳሚነት ዶር ብርሃኑ ነጋና አቶ ልደቱ አያሌው ነበሩ። ዶክተር ብርሃኑ በዚያን ወቅት ቅንጅትን ወክለው በስቶክሆልም ሲዊድን ስብሰባ አድርገው ነበር። ሰላማዊ ትግል ዋጋ እንደሚያስከፍል በግልጽ ያስረዱ ነበሩ። “እነርሱ(ወያኔዎች) ጠመንጃ አላቸው። እኛም የራሳችን መሳሪያ አለን፤ የራሳችን ኮልት አለን። ፍቅር የሚባል። እየሞትን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለዉጥ እናመጣለን” ነበር ያሉን። አንድ ተሰብሳቢ እጁን አንስቶ “ወያኔ በሚገባው ቋንቋ ካላናገርነው አይሰማም” የሚል አስተያየት ሰጠ። ዶር ብርሃኑ በንዴት መለሱ። “የማን ልጅ ነው ጦርነት ተብሎ የሚማገደው። አንተ ልጅህን ለጦርነት ትልካለህ ?” ነበር ያሉት።አሁን ታሪክ ተቀይሮ ዶክተሩ ያሉበትን ሁኔታ ሳስበው ያስገርመኛል።

ግፍ ሲበዛባቸው ነፍጥ የሚያነሱትን መቃወሜ አይደለም። እነርሱን የመቃወም የሞራል ብቃት የለኝም። ማነኝና ነው ሲመረው በረሃና ጫካ የወጣውን ዜጋ ለምን ይሄን አደረክ የምለው ?

ነገር ግን ራሳቸው መስዋትነት ሳይከፍሉ፣ የተመቻቸ ቦታ እየኖሩ፣ በሌላው ዜጋ ሕይወት ቁማር የሚጫወቱ ፖለቲከኞች ግን አይመቹኝም። ዶር ብርሃኑ ነጋ ፣ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ የመሳሰሉ ወገኖች ራሳቸውን እንደ “አርበኛ”አድርገው ነው የሚቆጥሩት። አንዳንድ ተከታዮቻቸውም አስመራ ከተማ መሄድን በረሃ እንደ መውረድ፣ ግንባር እንደ መሄድ የሚቆጥሩም አሉ። በዚህ አልስማማም። ቲራቮሎ(የአስመራ ቦሌ) በቪላ ቤት እየተኖረ፣ ሜሎቲ እየተጠጣ ፣ ከኤርትራ ባለስልጣናት ጋር እየተዋለና እየተመሸ በረሃ ተገባ ማለት አይስኬድም። ይልቅ ተረቱ እንደሚለው ስንተዋወቅ አንተላለቅ።

ብዙዎቻችን ግንቦት ሰባት ነን ብለው ከወጡ ጊዜ ጀምሮ አስጠንቅቀንና መክረን ነበር። በግልም በአደባባይም። ለምሳሌ ከአራት አመታት በፊት

“በኤርትራ በኩል እንታገላለን የሚሉ አንዳቸውም፣ ይኸው ሕወሃት/ኢሕአዴግ ስልጣን ከያዘ 21 አመታት አለፉ፣ አንድ ቀበሌ ነጻ አላወጡም። ወኔዉና ጀግንነቱ ሳይኖራቸው ቀርቶ አይደለም። ነገር ግን የኤርትራ መንግስት መዳፍ ዉስጥ ስላሉ እንጂ። እናንተንም ለጊዜዉ መጠቀሚያ ያደርጓቹሃል። ትንሽ አደግ ስትሉ ግን መመታታችሁ አይቀርም። ከኦነግ፣ ከአርበኞች ግንባር ከመሳሰሉት መማር አለባችሁ። ግድ የለም ከሻእቢያ ጥገኝነት ዉጡ”

ብዬ ጽፌ ነበር።ይኸው የተናገርነው፣ ያስጠነቀቅነው አንድ በአንድ ተግባራዊ እየሆነ ነው። ተሳስታቹህ ነበር ብሎ የሞሞግት ካለ ለመስማት ዝግጁ ነኝ።

አንድ ሌላ መታወቅ ያለበት ነገር ቢኖር፣ ሻእቢያን በማመን፣ እነ ዶር ብርሃኑ ብዙ ወጣቶች እንዳሰበሉ ነው። ኢሳትን በመጠቀም የተቀላቀሉን ጥሪ በማቅረባቸው ብዙ ወጣቶች ኤርትራ ገብተዋል። እነዚያ ሁሉ ወጣቶች የት እንደደረሱ እግዜር ነው የሚያወቀው። በስድሳ ስድስቱ እነ ብርሃነ መስቀል ወጣቱን እንዳስበሉት ማለት ነው።

ግንቦት ሰባት እንኳን ቃል እንደገባው ወያኔን አፍንጫውን ሊል፣ ከፍተኛ አመራሮችና አባላቶቹ አንድ በአንድ እየከዱት እንደ ድርጅት ሕልውና ራሱ አደጋ ዉስጥ የገባ ድርጅት ነው። ትላንትና ፊሽካው ተነፍቷል ብሎ ሲሸመጥጠን የነበረው ከፍተኛ ባለስልጣናቸው፣ ዘመነ ካሴ፣ ይኸው ግንቦት ሰባትን ለቆ ወጥቷል። ግንቦት ሰባት ሲቋቋም ከፍተኛ አመራር የነበሩ ብዙዎቹ አሁን የሉም። እነ መስፍን አማን፣ እነ አንተነህ ሙሉጌታ፣ እነ ዳንኤል አሰፋ የመሳሰሉት። ግንቦት ሰባት ጥርስ እንደሌለው ዉሻ በባዶ የሚጮህ የወያኔዎች መሳቂያ ድርጅት እንደሆነ ነው በገሃድ ያስመሰከረው። አንድ ጊዜ ዶር ደብረ ጽዩን ግንቦት ሰባት እየመጣ ነው ይባላል ሲባል፣ “አዎን እየመጡ ነው። በሕልማቸው” ብሎ ነበር የቀለደባቸው።

ሌላው ግንቦት ሰባቶች በተደጋጋሚ ብዙ ጊዜ ከመዋሸታቸው የተነሳ ፣ እዉነትን የመናገር፣ ስህተታቸውን የማመን አቅም ተሰኗቸዋል። ትልቅ ፖቴንሻል ነበራቸው። አሁን ግን ራሳቸውን በራሳቸው እያጠፉ ነው። እዉነቱ ሲነገራቸው ቁስላቸው የተነካ ይመስል ያኮራፍል። ይኸው ከጥቂት አመታት አራት ኪሎ ሲጠበቁ የነበሩ፣ ከወያኔ ጋር ይፋለማሉ ሲባሉ የነበሩት፣ የዉጊያን ሜዳዉን ቶሮንቶ፣ ሎስ አንጀለስ፣ ሲያትል አድርገዉት በዉጭ ካሉ የአማራ ድርጅቶች ጋር እየተቷከሱ ነው።ያን ያህል ሰዎቹ ወርደዋል።

ግንቦት ሰባትን ተስፋ አድርገን ፣ መዳን በኤርትራ በኩል ይመጣል ብለን አንጋጠን ስንጠብቅ የነበርን እንግዲህ እርማችንን እናውጣ። በተለይም አገር ቤት ያላቹህ ወገኖች፣ እናንተ ጋር ያለውን ሃይልና አቅም ዘንግታችሁ፣ ወይም አሳንሳችሁ፣ ጆሯችሁን የግንቦት ሰባት ፕሮፖጋንዳ ሜዲያ ኢሳት ላይ አድርጋችሁ በፕሮፖጋንዳ እየተሞላችሁ፣ ብዙ ተታላቹሃል። ያ መቆም አለበት። በፌስ ቡክ፣ በራዲዮና ቲቪ ከዳያስፖራ በባዶው ከሚጮኹና ከሚፎክሩ እንደ ግንቦት ሰባት ካሉ ድርጅቶች ጋር ሳይሆን መፍትሄው ያለው እናንተው ጋር እዚያው አገር ቤት ነው። ወደ ራሳችሁ ተመልከቱ። ከግንቦት ሰባት ሆነ ዉጭ ካሉ ድርጅት ይልቅ፣ ገና ከአንድ ሳምንት በፊት በአገር ቤት የተቋቋመ ድርጅት ካለ፣ እርሱ የበለጣ ለዉጥ የማምጥት እድል አለው።

(ከአራት አመት በፊት ግንቦት ሰባቶች ለማግባባት የተጻፋ EMF)