June 10, 2017 11:13

ባለፉት ሃያ ስድስት አመታት በውጭ ስለሚኖሩ ዜጎቻችን የምንሰማው ዜና በአሰሪዎቻቸው ተደበደቡ፣ ከፎቅ ላይ ተወረወሩ፣ ተደፈሩ፣ ተገደሉ እና የመሳሰሉ አሳዛኝ ዜናዎች ሲሆኑ በዚህም ሂደት ገዥው ቡድን በዜጎቻችን ላይ የሚፈፀሙ በደሎችን ለመከላከል ፍላጎት የለውም የሚል ወቀሳ ነው፡፡

ከዚህ የስደትና የመከራ ሕይወት ጋር በተያያዘ በአሁኑ ወቅት የሳውዲ አረቢያ መንግስት በሐገሩ የሚገኙ ሰነድ የሌላቸው የውጭ ዜጎች ሐገሩን ለቀው እንዲወጡ የቀነ ገደብ የወሰነ ሲሆን በተሰጠው ጊዜ በማይወጡ የውጭ ዜጎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ እያስጠነቀቀ ይገኛል፡፡ በሳውዲ አረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በተሰጠው የጊዜ ገደብ ያችን ሐገር ለቀው ካልወጡ የሚጠብቃቸው ሞትና እንግልት መሆኑን እያወቁ ለመውጣት ያደረጉት ዝግጅት አነስተኛ መሆኑ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በሐገራቸው በሚደርስባቸው የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ መገልል ምክንያት በኢትዮጵያ ከመሞት በባዕድ ሐገር መሞትን የመረጡ ይመስላል፡፡ ይህ አሳዛኝ የዜጎች ምርጫ ዛሬ ሐገራችን ያለችበት አገዛዝ የዜጎችን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማሕበራዊ ኑሮ ችግሮች ለማቃለል የማይችል መሆኑንና ዜጎች የሕይወት ዋጋ ለመክፈል በመጋፈጥ ጭምር እያረጋገጡት ይገኛል፡፡

የሳውዲ አረቢያ መንግስት ከዛሬ ሦስት ዓመት በፊት በወሰደው የውጭ ዜጎችን ከሐገሩ የማስወጣት እርምጃ በርካታ ወገኖቻችን ከፍተኛ የሆነ ኢሰብአዊ ድርጊት ተፈፅሞባቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን በጭካኔ ተገድለዋል፣ ተደፍረዋል የአካልና የኢኮኖሚ ጉዳትም ደርሶባቸዋል፡፡ በወቅቱ ሰማያዊ ፓርቲ በሳውዲ መንግስት የተወሰደውን አረመኔያዊ ድርጊት አውግዞ የሳውዲ መንግስት ይህንን የጭካኔ ተግባር ባስቸኳይ እንዲያቆም ለመጠየቅ በኢትዮጵያ የሳውዲ አረቢያ ኢምባሲ ጽ/ቤት ያደረገውን ሰላማዊ ሰልፍ የእኛው ገዥ ቡድን ታጣቂዎች በሰልፈኞች ላይ በፈፀሙብን አረመኔያዊ ድብደባ ሰልፉን በትነዋል፡፡ ገዥው ቡድን ከሳውዲ አረቢያ ለተመለሱ ዜጎች ተገቢውን ማቋቋሚያና ድጋፍ ባለማድረጉ ባለፈው ከተመለሱት መካከል አብዛኛዎቹ እንደገና ተመልሰው ወደ ሳውዲ አረቢያ መጓዛቸው ይነገራል፡፡ ዜጎች በሐገራቸው ሰርተው የመኖር ተስፋቸው እየመነመነ በመሔዱ ለሕወታቸው አደገኛ የሆኑ ጉዞዎችን በመጋፈጥ አሁንም መሰደዳቸውን አላቆሙም፡፡

አገዛዙ ለሌሎች ሐገር ስደተኞች ሳይቀር ድጋፍና እንካካቤ አድርጋለሁ በማለት ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ብዙ ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ያገኘ ሲሆን የራሱ ዜጎች ሰርተው የሚኖሩበት መንገድ ሊፈጥር ባለመቻሉ በተለይ ባለፉት ሦስት ዓመታት ችግሩን ለመፍታት ምንም የሰራው ነገር ባለመኖሩ ችግሩ እስካአሁኑ ሰዓት ድረስ ተከትሎን ይገኛል፡፡ አገዛዙ አሁንም በሳውዲ አረቢያ የሚገኙ ዜጎች እንዲመለሱ ተራ የማታለያ ፕሮፓጋንዳ ከመንዛት ውጭ ዜጎች ወደ ሐገራቸው ቢመለሱ ሰርተው መኖር የሚችሉበት ዋስትና ሊያቀርብላቸው ባለመቻሉ የገዥውን ቡድንና የአስመሳይ አርቲስቶችን ጥሪ ሰምተው ከመምጣት ይልቅ ባሉበት ሐገር ሆነው ሞትን መጠበቅ ምርጫቸው አድርገዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በዜጎቻችን ለሚደርስባቸው ሞትና መከራ ገዥው ቡድን ኃላፊነቱን ይወስዳል፡፡

የሳዉዲ መንግስት ስደተኞችን ከሐገሩ ለማስወጣት የሚወስዳቸው እርምጃዎች አረመኔያዊ መሆኑን ባለፈው ጊዜ በዜጎቻችን ላይ የደረሰው መከራና ሞት በቂ ማሳያ መሆኑን እያስታወስን አሁንም የሳውዲ መንግስት የሚወስዳቸው እርምጃዎች ለዓለም ዓቀፍ የሰው ልጅ መብትና ለሰው ልጅ ፍጡር ያለን ክብር የጠበቀ እንዲሆን እናሳስባለን፡፡ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ ዓለም ዓቀፍ የስደተኞች ድርጅት፣ ዓለም ዓቀፍና አገር አቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች በስደተኞች ላይ የሚፈፀም ኢሰብአዊ ድርጊት እንዲቆም እና በስደት ላይ ላሉ ሁሉ አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጎ በሕይወት የመኖር መብታቸው እንዲከበር የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪያችንን እናስተላልፈለን፡፡

በመጨረሻም በሳውዲ የሚገኙ ዜጎቻችንም ከሳውዲ አረቢያ መውጣትን አስመልክተው የሚወስኗቸው ውሳኔዎች ሕይወታቸውን አደጋ ውስጥ የማያስገባ መሆኑን ማጤን እንዳለባቸው እንመክራለን፡፡ በሐገርና ከሐገር ውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ይሕን በዜጎቻችን ላይ ያንዣበበ አደጋ በቅርበት በመከታተል የሚደርስባቸወን የሰብአዊ መብት ጥሰት ለሚመለከታቸው ሁሉ በማጋለጥ የበኩላችሁን እንድትወጡና የሚደርሰውንም ሞትና መከራ መቀነስ እንድንችል ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

ሰኔ 3 ቀን 2009 ዓ.ም
አዲስ አበባ