Sunday, 11 June 2017 00:00

  መታሰቢያ ካሣ

ለወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ዳጎስ ያለ በጀት ተይዟል

ለድርቅ አደጋው 8.3 ቢሊዮን ብር በጀት ተመድቧል

የኮሜርሻል ብድሮች ለተወሰነ ጊዜ ይገደባሉ ተባለ

ከወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ 1.95 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው

– 98.1 ቢሊዮን ብር ከታክስ ተሰብስቧል

የመኸር እህል ምርት 290.3 ሚሊዮን ኩንታል ነው

ለመንግስት ብቻ በተተዉ የኢንቨስትመንት ዘርፎች፣ የግሉ ዘርፍም ይሰማራል

በመጪው ዓመት ዘጠኝ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ሥራ ይጀምራሉ

የቀጣዩን ዓመት የፌደራል መንግስት በጀት አስመልክቶ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር አብርሃም ተከሰተ፤ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መግለጫና ማብራሪያ ሰጡ። በጀቱ በቋሚ ኮሚቴዎች ታይቶ እንዲፀድቅ ለቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከትናንት በስቲያ ባካሄደው 38ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ባቀረበው የበጀት ዝርዝር መግለጫ ላይ እንደተገለፀው፤ በቀጣዩ በጀት ዓመት ለወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ዳጎስ ያለ በጀት ተይዟል፡፡ ከአጠቃላይ የ2010 በጀት ውስጥ 61.8 በመቶ የሚሆነው ለመንገድ፣ ለትምህርት፣ ለግብርና፣ ለውሃ፣ ለጤና እና ለገጠር ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራሞች የተመደበ ሲሆን ለወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድና ለከተማ ልማት ስራዎች እንዲሁም ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ከፍ ያለ በጀት ተበጅቷል፡፡ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲን መረጃ ጠቅሶ መግለጫው ይፋ እንዳደረገው፤ በዘንድሮው ዓመት ከዋናው የመኸር ምርቶች 290.3 ሚሊዮን ኩንታል እህል ተሰብስቧል። ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 8.8 በመቶ ብልጫን አሳይቷል፡፡ በበጀት ዓመቱ ለተከሰተው የድርቅ አደጋም 8.8 ቢሊዮን ብር በጀት ተመድቧል፡፡ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሃም ተከስተ በዚሁ ዝርዝር መግለጫቸው ላይ እንደገለፁት፤ በኤክስፖርት ገቢው ላይ የሚታየው ማሽቆልቆል አሳሳቢ ነው። በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ወራት ከኤክስፖርት የተገኘው 1.95 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ሲሆን ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ከተገኘው የ2.9 ቢሊዮን ዶላር ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ድክመት አሳይቷል ብለዋል፡፡