June 12, 2017

አገራችን ኢትዮጲያ ወደ አስጊ መንገድ እየሄድች ነው። አብዛኞቻችን ይህ ሁኔታ ይሆናል ብለን አናስበው ይሆናል። አንዳንዶቻችን የተጋነነ አባባል አደርግን እንውስደዋላን። የተወሰነው ደግሞ በተለየ ሁኔታ አገራችን በቅርቡ አስርት አመታት ከተከሰተው ታሪካችን በመንሳት ኢትዮጲያ በተሻለ መንገድ ላይ ናት ብለን እናስባለን። እውነታው ግን በኢትዮጲያ ታሪክ ታይቶ በማይታውቅ ደርጃ የመበታተንና አስከፊ የእርስ በርስ ጦርነት አሳት ወስጥ ልንገባ የሚያስችል እጣ ፈንታ የተዘረጋልን መሆኑ ነው። ይህ ክፉ እጣን ማስቀረት ይቻላል! ይሄ የአሁኑ ትውልድ ማስጠንቀቂያወን ቸላ ያለው እንደሆነ የተፈራው በማይመልስ መልክ ሊፈጸም ይችላል።

አሁን አንገብጋቢ ሆኖ የሚፈታተነን ችግር የዲሞክራሲ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን፤ ሁላችንንም አቅፎ በኢትዮጲያ አገራችን የያዘን ምሰሶና ማገር እንዲበሰብስና እንዲዝግ በላያችን ላይ ጊዜ ወስዶ እንዲደረመስ ስለ መደርጉ ነው። ሕወሓት (ወያኔ) የሚመራው አገዛዝ በሃሰትና የተጋነነ የውሸት ታሪክ፣ ቋንቋችንን፣ የባህል እንዲሁም የሃይማኖታችንን ልዩነት እያጎላ የዘራው የተንኮል ዘር ፤ በመካከላችን የጠላትነት ፣ የጥርጣሬ፣ የጥላቻና የመከፋፈል እኩይ ተግባር ፈጥሯል።

የጥቂቶች የሆነው የወያኔው ቡድን ያምነበትና ተግባር ላይ ያወለው አጥፊ የአገዛዝ ስልት ዘርግቷል። የ አነስተኞች ወገን ሁኖ ብዙሃኑን ኢትዮጲያውያን ለመገዛት፤ ብዙሃኑን በመከፋፈልና በማዳከም፣ እንዳይደራጅ አድርጎ በ “ከፋፍለህ ግዛው” ዘዴው ሰውሮ ይዞታል። ይህንንም ለማስፈጸም የማጭበርበሪያ የፌድራል ክልል አበጅቷል። ‘ብሄር ብሄረሰቦችን’ የሚከፋፍል፣ የሚያራርቅ፣ የሚያጋጭ ፖሊሲ ነድፎ፤ እያጋጨ፣ ራሱ ፖሊስና ዳኛ ሆኖ ወያኔው ስልጣን ላይ ለዘመናት ፊጥ ብሏል። የቀደሙት አገዛዞች በመደብ ለይተው ህዝቡን ይግዙ እንጂ እንደ አሁኑ አገዛዝ እርስ በርስ ሊያጨራርስ በሚያስችል የተንኮል አገዛዝ አልተጠቀሙም። በዋናው የመደብ ልዩንት አገዛዝ ላይ አንዳንዴ የጎሳና ሃይማኖት ቅባቶች ተጠቀሙ እንጂ አንዱን ባንዱ የሚያስነሳ ፖሊሲ አልተጠቀሙም።

ወያኔ በ1983 በመሳርያ ሃይል ስልጣን ላይ ከተቀመጠ ጀምሮ በዚህ ከፋፍለህ ግዛው ዘዴው አውቆም ይሆን ሳየውቀው በአገራችን ኢትዮጲያ ሁላችንንም ተሽክሞ የያዘነን ምሰሶ እየናደው መሆኑን ነው። የተለያዩ የጎሳ “መሪዎች” በወያኔው የፈጠራ ታሪክና ፕሮፓጋንዳ ራሳቸውን ልዩ ጎሳ እንደሆኑ እንዲያስቡ አድርጎቸዋል። ጎሳ ለጎሳ እንዳይተማመን አድርጎ፤ በተለይ ወያኔው የአንድነት ጠበቃ ናቸው ብሎ የሚያስባቸውን “አማራ” እና “ኦርቶዶክስ” ሃይማኖትን እንዲጠሉ ተድርገዋል። የወያኔው ሽንገላ ባንዳንዶች የጎሳ “መሪዎች” ላይ “የራስህን አገር መምስረት ትችላልህ” የሚል ቀቢጸተስፋ በህገመንግስቱ አንቀጽ 39 አስፍሮ ፡ የግብዞቹን አይን አውሮ የቅጠፈት አገዛዙን አንሰራፍቷል።

ወያኔው አስቀድሞ በያዘው እቅዱና ትልሙ ኢትዮጲያን በበላይነት እየገዛና እይዘረፈ፤ ክፉ ቀን ሲመጣ “የትግራይን ሪፐፕሊክ” ከኢትዮፒያ በዘርፈው ንብረት መስርቶ፡ ሌሎችንም ጎሳዎች እንዲገንጠሉና መንግስት እንዲመስርቱ፤ ኢትዮጲያን እንዲያፈርሱ አልሟል።

መራራው እውነት ግን ወያኔው በፈጠረላቸው ማንነትና የግዛት ወሰን የሚደርገ ግንጠላና አዲስ አገር የሞህን ጉዳይ ከዩጎስላቪያና ሶማሌ በበለጠ ወደ ማያባራ የእርስ በርስ ጦርነትና ደም መፋሰሰ ያመራል። “የትግራይ ሪፐፕልክም” የእሳቱ ቃጠሎ ይደርሳታል። የ ምስራቅ አፍሪካንም ያወካል።

ኢትዮጲያውያን ልንረዳው የሚገባን አንገብጋቢው ጥያቄ የዲሞክራሲ እጦት ብቻ ሳይሆን፤ ዋናው አገር የማዳን ጉዳይና ትልቅ የእርስ በርስ ደም መፋሰስ እልቂትን ማዳን ነው። እስኪ ላአንዳፍታ አገር ተገነጣጥሎ ያለውን እውነታ እንየው። ኦሮሚያ የምትባል አገር ወያኔ በሰፈርላት የድንበር ወሰን ብትገንጠልና አዲስ አገር ብትሆን በሰሜን በኩል ከአማራው ጋ፣ በምስራቅና ደቡብ ምስራቅ ከኢትዮጲውያን ሶማሌ ጋ፣ በምራብ ና ደቡብ ምራብ ከደቡብ ህዝቦች ጎሳ ጋ የማያባራ የድንበር ና የጎሳ ጦረነት ላይ ስትወድቅ አስቡት። አማራ የሚባል አገር ተመስርቶ በሰሜን ከ”ትግራይ ሪፐፕሊክ” ጋ፣ በደቡብ ከኦሮሚያ ጋ፤ በምስራቅ ከአፋር ጋ የማያባራ የግዛት ና ወሰን ጦረነት ሲከሰት። ደቡብ ኢትዮጲያ ውስጥ ያሉ ብዙሃን ጎሳዎች አገር እንሁን ብለው በድንበር ወሰን ምክንያት እርስ በርሳቸው ሲጨራረሱ ። ይህ ሁሉ ቢሆን ማንንም ሳይጠቅም መንግስት ከሌላት ሱማሌ የባሰ ጥፋት ይደርሳል።

ውድ እህትና ወንድሞች፤ እንድምናየው ኢትዮጲያችን ወደ አስፈሪ መንግድ እየትጓዘች ነው። አገዛዙን የምትደግፉ ወገኖች ሁሉ ይሄ ነገር ሊያሳስብቸሁ ይገባል። ለዚህ መፍቴው ይህንን አስከፊ እጣ ፈንታ የዘረጋብንን አስከፊ አገዛዝ መቃወም ነው። ኢትዮጲያውያን በጎሳ፣ በሃይማኖት፣ በዘር፣ በፖለቲካ አምለካክት፣ በትምህርት. በችሎታ፣ በጾታ ሳንለያይ በጋራ በመሆን የጋራ አገራችንን በማደን የወያኔን አገዛዝ ሞት ማፋጠን ይኖርብናል።

ወያኔው ለ 26 አመታት ካደነዘዘን የህልም እዣት ውስጥ መንቃት አለበን። ተደራጅተን በትብብር ካልሰራን፤ በወያኔው ገዳይ ወጥመድ ወስጥ ወድቀን ወደ ሚያስፈራው መራራ ቀን መቀርባችን ነው። አገራችንና የወደፊት እጣ ደርሻችንን የመወሰኑ ጉዳይ የራሳችን እንጂ ሌላ የውጭ ሃይል ይህን ለኛ ይሰራልናል ብለን መጠበቀም ተስፋ ማድርገም የለብነም። ሱማሌ ከ 1983 ጀምሮ ያለችበትን የእርስ በርስ እልቂትና የጦረነት አገር መሆኑዋን መርሳት የለበንም። አገራችንና ህዝባችንን ከዚህ መሰል እልቂት ማዳን አለበን።

አገራችንን ካዳንና የተደገሰልንን የእርስ በርስ እልቂት ማቆም ስንችል፤ ተመካክርን ሰላም የነገስባትን፣ ሁሉም ዜጋ በእኩለነት የሚታይበትን፤ ለትምህርት፣ ለስራ፣ ንግድና ሌላም ሌላ የፖለቲካ ተሳትፎንም ጨምሮ ሁላችንም እኩል እድል ያለን ዲሞክራሲያዊና ፍታሃዊ አገር እንገነባለን። የፌድራል መንግስት ማድርግ ቢያሻንም የክልል ወስኖች ለኢኮኖሚ እድገትና ህዝብን በሚያቀራርብ መልክ ይዘረጋል እንጂ እንደወያኔው አገዛዝ ልዩነታችንን የሚያጎላ የአኮኖሚ ችገር ፈጣሪ መሆን አይገባውም።

ዋናው ሁሌም ማስታወስ የሚገባን ቁም ነገር ግን ተባብርን በመስራት ብቻ ነው አገራችንን ማዳን የምንችለው። ስለዚህም ወያኔውን በመቃወም ላይ ያላችሁ የፖልቲካ ሀይሎች ሁሉ እንዲሁም በወያኔው ጎራ ያላችሁ ወገን፤ አንድ ላይ በመሆን አገር የማዳን ግዴታችንን እንድንወጣና የተደቀነብንን ክፉ እጣ አስቀርተን በነጻነት ራስችንም ልጆቻችንም እንድንኖር ጥሪ አቀርባለሁ።